Skip to main content
x
የኢትዮጵያ የለንደን ዓለም ሻምፒዮና ቆይታና የቤት ሥራዎቹ

የኢትዮጵያ የለንደን ዓለም ሻምፒዮና ቆይታና የቤት ሥራዎቹ

ከሐምሌ መገባደጃ ጀምሮ ለ10 ቀናት የዓለምን ትኩረት ስቦ በነበረው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ተካፋይ የነበረው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን ነሐሴ 9 ቀን 2009 ዓ.ም. ንጋት አዲስ አበባ ሲደርስ አቀባበል ተደርጎለታል፡፡

የእንግሊዝ መዲና ለንደን ባዘጋጀችው 16ኛው ሻምፒዮና፣ ኢትዮጵያ አልማዝ አያና በ10 ሺሕ ሜትር፣ ሙክታር እድሪስ በ5 ሺሕ ሜትር ባስገኙት ሁለት ወርቅና ታምራት ቶላ በማራቶን፣ ጥሩነሽ ዲባባ በ10 ሺሕ ሜትር እንዲሁም አልማዝ አያና በ5 ሺሕ ሜትር ባስገኙት ሦስት ብር ሜዳሊያዎች ሰባተኛ ሆና አጠናቃለች፡፡

የዘንድሮው ውድድር ለኢትዮጵያ ለየት ያለ ውጤት፣ በወንዶች ያስገኘው በ2001 ዓ.ም. በበርሊን በተዘጋጀው የዓለም ሻምፒዮና ቀነኒሳ በቀለ በ5 ሺሕ ሜትር ካስገኘው ወርቅ ስምንት ዓመት በኋላ በሙክታር እድሪስ መገኘቱ ነው፡፡ በተከታታይ በተካሄዱት ሻምፒዮናዎች የኢትዮጵያ ውጤት በብርና በነሐስ ሜዳሊያዎች ላይ የተወሰነ ነበር፡፡

በ34 ዓመታት የ5 ሺሕ ሜትር ታሪክ ኢትዮጵያ ሁለት ጊዜ ብቻ በቀነኒሳና በሙክታር ብቻ ነበር ያሸነፈችው፡፡ በነዚያ ዓመታት በተወሰኑት 5 ብርና 4 ነሐስ ብቻ አግኝታለች፡፡ የተሻለ ውጤትና ስኬት የነበረው በ10 ሺሕ ሜትር ለ12 ዓመታት (1991 እስከ 2003 ዓ.ም.) የዘለቀው ነበር፡፡ በኃይሌ ገብረ ሥላሴና በቀነኒሳ በቀለ የቀጠለው እስከ ዴጉ ሻምፒዮና ኢብራሂም ጄይላን ድል ካደረገ በኋላ የ10 ሺሕ ሜትር ውጤት እንደራቀ ነው (በመካከለኛ ርቀት በ800 ሜትር መሐመድ አማን ያስገኘው ወርቅ ሳይዘነጋ)፡፡ በለንደን ሻምፒዮናም ሽንፈቱን ታይቷል፡፡ በአንፃራዊ መልኩ የሴቶች ውጤት ግን የላቀና በሻምፒዮናው ክብረ ወሰኑን እንደያዙ ናቸው፡፡ በደራርቱ ቱሉ፣ ጌጤ ዋሚ ብርሃኔ አደሬ፣ ጥሩነሽ ዲባባና አልማዝ አያና ስሙር ውጤት የታየ ነው፡፡

የለንደኑ 16ኛው ሻምፒዮና

ከ203 አገሮች የተወጣጡ አትሌቶች በተሳተፉበት የዘንድሮው ሻምፒዮና የኢትዮጵያ ቡድን ተገቢውን ዝግጅት ማድረጉን ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ መግለጹ ይታወሳል፡፡ የተገኘው ውጤት ሲታይ ሁለት ወርቅና ሦስት ብር ሆኗል፡፡

በዘንድሮው ሻምፒዮና የተገኘው ውጤት ካለፉት ሁለት ሻምፒዮናዎች ሲነፃፀር ዝቅተኛ ሆኗል፡፡ ኢትዮጵያም እ.ኤ.አ. በ2013 በሞስኮ 3 ወርቅ፣ 3 ብርና 4 ነሐስ በድምሩ 10 ሜዳሊያዎች በማግኘት 6 ደረጃ፤ በ2015 በቤጂንግ 3 ወርቅ፣ 3 ብርና 2 ነሐስ በድምሩ 8 ሜዳሊያዎች በማግኘት 5ኛ ደረጃ ይዛለች፡፡ ዘንድሮ በ2 ወርቅና በ3 ብር ያለነሐስ በድምሩ በ5 ሜዳሊያዎች ሰባተኛ ሆና አጠናቃለች፡፡   

ምንም እንኳን የሜዳሊያው ማነስና በዓለም አቀፍ ደረጃ በቀዳሚነት የመጠራት ጉዳይ ባያሳስብም ኢትዮጵያ የቀድሞ የበላይነቷን ለመመለስ ከወዲሁ መሠራት ስላለበት የቤት ሥራ ሁሉም የስፖርት ቤተሰብ ያሳሰበ ጉዳይ መሆኑ እየተገለጸ ይገኛል፡፡

ኢትዮጵያ እየተሳተፈችባቸው ባለው ዓለም አቀፍ ሻምፒዮናዎች ላይ እያስመዘገባችው ያለው የወንዶች ውጤት ማሽቆልቆል ሌላኛው አነጋጋሪና አሳሳቢ ጉዳይ ሆኗል፡፡

እ.ኤ.አ. ከ2011 ዴጉ ዓለም ሻምፒዮና በኋላ የወንዶች ውጤት እየጠፋ መጥቶ በአንፃሩ ደግሞ ሴቶቹ በተሻለ ውጤት መታየታቸውን ቀጥለዋል፡፡ ምንም እንኳን እ.ኤ.አ. በ2013 ሞስኮ የዓለም ሻምፒዮና ላይ በ800 ሜትር መሐመድ አማን ወርቅ ማምጣቱ በአጭር ርቀቱ እንደ መልካም ጎኑ ቢቆጠርም፣ ከዴጉ ውጤት በኋላ አትሌቲክሱ ትኩረት እንደሚያስፈልገው የአትሌቲክሱ ባለሙያዎች አስተያየት ቢሰጡትም ሰሚ በማጣታቸው አትሌቲክሱ ውጤት እየቀዘቀዘ እንዲመጣ አድርጎታል የሚሉ አልጠፉም፡፡

በዘንድሮው ሻምፒዮና በማራቶን በሁለቱም ፆታ፣ በ1,500 ሜትር ሴቶች፣ በወንዶች 10 ሺሕ፣ በ5,ሺሕ ሜትር ሴቶች ወርቅ ያመጣሉ ተብለው ቅድሚያ ግምት የተሰጣቸው አትሌቶች በጥቃቅን ስህተት ምክንያት ውጤት ማምጣት አለመቻላቸው ብዙውን ተመልካች ያስቆጨ አጋጣሚ ነበር፡፡

የኢትዮጵያን ቡድን መርተው የሄዱት የብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ምክትል ፕሬዚዳንት ገብረ እግዚአብሔር ገብረ ማርያም ሻምፒዮናው ከተጠናቀቀ በኋላ ለዶቼቬሌ ጋዜጠኞች በሰጡት ቃለ ምልልስ፣ የተገኘው ውጤት ከዝግጅቱ አንፃር እንደማይመጥን ነው የተናገሩት፡፡

‹‹አለ የሚባለውን ሁሉ ለማሟላት ጥረት ተደርጓል፡፡ አትሌቶቻችን የሚችሉትን ያህል ተዘጋጅተዋል፤ ያገኘነው ውጤት ለተዘጋጀው ዝግጅት ይመጥናል ብዬ አላስብም፤›› ነበር ያሉት፡፡ ምክትል ፕሬዚዳንቱ በ5 ሺሕ ሜትር ሴቶች ወርቁ ሜዳሊያ ያልተገኘው ከውድድሩ በፊት ከአትሌቶቹ ጋር በተነጋገሩት ታክቲክ መሠረት ባለመከናወኑ ነው ብለዋል፡፡ ‹‹እኛ ያልነው በቡድን ታክቲክ ከአምስትና ስድስት ዙር በኋላ ቢወጣ ነበር፡፡ የአልማዝን ትዕግስት ለመፈተን የቡድኑንም ትዕግስት ለመፈተን በሚመስል መንገድ ውድድሩ ቀዘቀዘ፡፡ ስለዚህ አልማዝን ወደ አልተፈለገ ጉልበት ማውጣት ገፏፏት፤ የወጣችበት ታክቲክ ዋጋ አስከፍሎናል፤፤››

በሻምፒዮናው ላይ የወርቁ መምጣት ዋና ነገር እንዳልሆነ የሚገልጹት ባለሙያዎች የተሳታፊዎችን ወቅታዊ ብቃትና ቀጣይ ሥራዎች ቅድሚያ መስጠት ይኖርበታል የሚል እምነት አላቸው፡፡ ‹‹በሻምፒዮናው ላይ ወርቅ መጠበቅ ብቻ በቂ አይደለም፡፡ በውድድሩ ላይ የታዩትን ችግሮችና ምን የተጨመረ ነገር አለ? ምን የተቀነሰስ አለ ብሎ መመልከቱ ተገቢ ነው ባይ ነኝ፤›› በማለት የአትሌቲክስ ከፍተኛ ባለሙያው ዶ/ር ይልማ በርታ ለሪፖርተር አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

እንደ ባለሙያው አስተያየት ከሆነ ‹‹ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ወርቅ ያመጣሉ ተብለው ትልቅ ግምት የተሰጣቸው አትሌቶች ማሳካት ሲሳናቸው እየተመለከትን እንገኛለን፡፡ በዚህም ክፍተቱ ምኑ ጋር እንደሆነ መጠየቅ ያስፈልጋል፤›› በማለት አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ ብቁ የሆኑና ከየትኛው ዓለም አትሌት እኩል የሆኑ አትሌቶች አሏት፡፡ ስለዚህ እነዚህን አትሌቶች እንዴት ሜዳልያ ማምጣት እንዳለባቸው በደንብ ማሳወቅ ያስፈልጋል፤››› በማለትም ዶ/ር ይልማ  አክለዋል፡፡

በሴቶች በ10 ሺሕ ሜትር ወርቅ ለአገሯ ያበረከተችው አልማዝ አያና ለረዥም ጊዜ በሕመም ምክንያት መቆየቷና በ5 ሺሕ ሜትር ያስመዘገበችው ውጤት እንደ ትልቅ ስህተት መወሰድ እንደሌለበትም ባለሙያው ያስረዳሉ፡፡ አልማዝ የራሷ የአሯሯጥ ዘይቤ እንዳላትና በ10 ሺሕ ሜትር ላይ ዙሩን በማክረር የተካነች ስትሆን፣ በአንፃሩ ደግሞ በፍጥነት የማጠናቀቅ ሒደቷን በልምምድ ማዳበር እንደነበረባትና እንዳለባት ተገልጿል፡፡ አልማዝ በርቀቱ የቻለችውን ማድረጓ ሕመሙ በውስጧ የፈጠረው የሥነ ልቦና ጉዳት ለኬንያዋ አትሌት ምቹ ዕድል ፈጥሮላታል፣ አሸናፊዋ አትሌትም አሠልጣኞችዋ የመከሯትን መተግበሯን ባለሙያው ጠቅሰዋል፡፡

በዓለም የ10 ሺሕ ሜትር ሪከርድ ባለቤቷ አልማዝ አያና ጋር ተሠልፈው ከነበሩት ለተሰንበት ግደይና ሰምበሬ ተፈሪ ጋር የቡድን ሥራው ቢኖር ተጨማሪ ሜዳልያ የማግኘት ዕድል ሰፊ እንደነበር ተጠቁሟል፡፡

የሪዮ ኦሊምፒክን ጨምሮ ለሁለተኛ ጊዜ ታክቲካዊ ስህተት የፈጠረችው አልማዝ አያና ከውድድሩ በኋላ በሰጠችው ቃለ ምልልስ፣ ውድድሩ ከባድ እንዳልነበረ በጥሩ አቋም ላይ እንደነበረች መጨረሻ ላይ ግን አለመቻሏን ተናግሯለች፡፡

‹‹በልምምድ ወቅት ከጉዳት በኋላ ስለተመለስኩ ፍጥነት ላይ መሥራት አልቻልኩም፤ ከ10 ሺሕ በኋላ የተወሰነ ሕመም ሲሰማኝ ነበር፤›› ያለችው አልማዝ ከዚህ በኋላ በ5 ሺሕ ሜትር እንደምትሮጥም ሳትናገር አላለፈችም፡፡

በሌላ በኩል የገንዘቤ ዲባባ በሻምፒዮናው ላይ ስኬታማ አለመሆኗ አነጋጋሪ ሆኖ ነበር፡፡ ገንዘቤ 1,500 ሜትርና በ5 ሺሕ ሜትር አገሯን ለመወከል ከተመረጡት አትሌቶች አንዷ ነበረች፡፡ አትሌቷ በሻምፒዮናው ላይ ለመካፈል በውጭ አገር ልምምዷን ስታደርግ የነበረ ሲሆን፣ 1,500 ሜትር ማጣሪያውን በብቃት ማለፍ ብትችልም በፍጻሜው ውድድር 12ኛ በመውጣቷ ትችት ማስተናገዷ ይታወሳል፡፡ በተለይ የአገርና የግል ውድድርን በማያያዝ ጉዳዩን ከግል ጥቅም ጋር ሲነሳ ቆይቷል፡፡

በ1,500 ሜትር የዓለም ክብረ ወሰን ባለቤት የሆነችው ገንዘቤ በለንደኑ ዓለም ሻምፒየና ላይ ውጤት ያላመጣችበት ምክንያት ባጋጠማት የጀርባ ሕመም ምክንያት እንደሆነ ተናግራለች፡፡ አትሌቷ 1,500 ሜትር ላይ የነበራትን ውጤት ተመልክታ የ5 ሺሕ ሜትር ማጣሪያ ላይ ላለመሳተፍ መወሰኗን አብራርታለች፡፡ ከአገር ይልቅ የግል ውድድር ውጤት ላይ ታተኩራለች ተብላ የማኅበራዊ ሚዲያው መነጋገሪያ የሆነችው ገንዘቤ፣ ‹‹ሰባት ዳይመንድ ሊግ ውድድር አድርጌ 40 ሺሕ ዶላር ነው የማገኘው፡፡ የዓለም ሻምፒየና ላይ ግን አንድ ውድድር ካሸነፍኩ 60 ሺሕ ዶላር ነው የማገኘው፡፡ ስለዚህም ይኼ የገንዘብ ጉዳይ ሳይሆን የአገር ክብር ጉዳይ ነው፤›› በማለት አስተያየቷን ሰጥታለች፡፡ ከገንዘብም ባሻገር አዳዲስ የስፖንሰርሺፕ ስምምነቶችን ለመፈረም የዓለም ሻምፒዮና ትልቅ ዕድል እንደሚፈጥርላት አስረድታለች፡፡

በሌላ በኩል ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በለንደን ባደረጉት ቆይታ ወቅት በሙክታር እድሪስ የተገኘው ወርቅና የጊዜው ረጅም ርቀት ባለድል ሞ ፋራ አልበገሬነት የተገታበት መሆኑን ነው፡፡ ሙክታር በዩሚፍ ቀጄልቻና ሰለሞን ባርጋ በመታገዝ ርቀቱን 13 ደቂቃ ከ32 ሴኮንድ ከ79 በማጠናቀቅ የቡድን ሥራ ጭላንጭል እንዲታይ አድርገዋል፡፡

በሻምፒዮናው አትሌቶቹ ያደረጉት የቡድን ሥራ በጥቂቱም ቢሆንም የቀድሞ አትሌቶችን የቡድን ሥራ አስታውሰዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር አትሌቶች እርስ በርስ ያላቸው ግንኙነት መጠንከር እንዳለበትና በውድድር ወቅት የቡድን ሥራው መላላት  በዓለም  ሻምፒዮኖች ላይ የሌሎች አገሮች የበላይነት እንዲኖር አድርጎታል የሚሉ አሉ፡፡

በዚህም መሠረት ቀድሞ በምሥራቅ አፍሪካ አገሮች ፉክክር ሲታጀብ የኖረው የረዥም ርቀት ሻምፒዮና በአሜሪካ አውሮፓና ሌሎች የአፍሪካ አገሮች እየተጎበኘ ይገኛል፡፡ በዘንድሮም የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ በወንዶች 5 ሺሕ ፑዋላ ቺሊሞ ሦስተኛ ደረጃን በመያዝ፣ በማራቶን ወንዶች ታንዛንያው አልፎንሲ ሲምቦ ሦስተኛ በመውጣት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ውጤታማ የሆኑ ናቸው፡፡

በሴቶቹም በኩል አሜሪካዊቷ ጄንፈር ሲምፕሰን በ1,500 ሜትር ሁለተኛ፣ በ5,000 ሜትር ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ ሲፋን ሀሰን ሦስተኛ ደረጃን በመያዝ እንዲሁም ለመጀመርያ ጊዜ በማራቶን የነሐስ ሜዳልያ ባለቤት የሆነችው አሜሪካዊቷ ኤሚ ክራው መጥቀስ ይቻላል፡፡

ኢትዮጵያ በለንደን ቆይታዋ ከውድድር በስተጀርባ ብሔራዊ ቡድኑ የተለያዩ ችግሮች ሲያስተናግድ መቆየቱ ተነግሯል፡፡ የብሔራዊ ቡድኑ አሠልጣኞችና የማናጀሮች ፍጥጫ ተጠቃሽ ነው፡፡ ወደ አመራር መንበሩ ከመጡ ዓመት ያልሞላቸው የቀድሞ አትሌቶች ችግሩን በሒደት እንደሚፈቱ እየገለጹ ይገኛሉ፡፡

‹‹በማናጀርና በአሠልጣኞች እንዲሁም በአትሌቶች ቤተሰብ መካከል ያለው ነገር ሦስቱም አካል ለአትሌቲክሱ ጠቃሚ ናቸው፡፡ ግን ሁሉንም በማቻቻል እንሠራለን፤›› በማለት የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ሻለቃ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ በቀጣይ የምታደርጋቸውን ዓለም አቀፍ ሻምፒዮናዎች ከወዲሁ የቤት ሥራዋን ማጠናቀቅና የታዩት ችግሮች ድጋሚ እንዳይደገሙ የብሔራዊ ቡድን መንፈስን በአትሌቶች ውስጥ ማስረፅ ትልቁ ሥራ እንደሆነም ፕሬዚዳንቱ አብራርተዋል፡፡

በልምምድ ወቅትም ትልቁ ችግር የነበረው በማናጀሮችና በአትሌቶች እንዲሁም ከአሠልጣኞች ጋር ያለው አለመግባባት እንደነበር አስታውሰው፣ በቀጣይ ማስተካከል እንደሚያስፈልግ ፕሬዚዳንቱ አክለዋል፡፡

አትሌቶቹ ከአሠልጣኞች ይልቅ ከማናጀሮቻቸው ጋር የበለጠ ቁርኝት ስላላቸው ላለመግባባቱ መንስኤ እንደሆነም አስረድተዋል፡፡

ከዚህም ባሻገር የዘንድሮ የዓለም ሻምፒዮና ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ  በቀጣይ መሥራት የሚገባው የቤት ሥራ ያሳየ እንደሆነ ሳይናገሩ አላለፉም፡፡

 ኢትዮጵያ በተሳተፈችበት የ3 ሺሕ መሰናክል በታሪኳ ለመጀመርያ ጊዜ ሦስት አትሌቶችን ለፍጻሜ ማድረስ ችላለች፡፡