Skip to main content
x
የኤርትራ ማዕቀብና ውስብስቡ የኢትዮ-ኤርትራ ግንኙነት

የኤርትራ ማዕቀብና ውስብስቡ የኢትዮ-ኤርትራ ግንኙነት

በኢሳያስ አፈወርቂ የምትመራው ኤርትራ ከኢትዮጵያ ከተነገጠለች ከሩብ ክፍለ ዘመን በላይ ተቆጥሯል፡፡ አነስተኛ የሆነ ሕዝብና የቆዳ ስፋት ያላት ኤርትራ በምሥራቅ አፍሪካ ካሉ አገሮች በተለያዩ ምክንያቶች አነጋጋሪና አወዛጋቢ ከሆነች ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡

የአሰብና የምፅዋ ወደቦች ባለቤት የሆነችው ይህች ትንሽ አገር የምትገኝበትን የጂኦ ፖለቲካ ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ ብዙ አገሮች ፊታቸውን ወደ እሷ ሲያዞሩም ይታያሉ፡፡

ኢትዮጵያና ኤርትራ ወደ ሁለት አገሮች ከተከፈሉ በኋላ የተለያየ አሠላለፍ እንደያዙ ይነገራል፡፡ ኢትዮጵያ ወደ አውሮፓና አሜሪካ ፊቷን ስታዞር ኤርትራ ደግሞ ወደ ሳዑዲ ዓረቢያና ግብፅ ማዘንበሏን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ይኼ አሠላለፍ ቆይቶም ሁለቱ አገሮች በተቃራኒ ጎራ እንዲሠለፉ ከማድረግ ባሻገር ወደ ለየለት ጦርነት እንዲገቡም አድርጓቸው ነበር፡፡

በሁለቱ አገሮች አመራሮች አለመግባባት የተነሳም ሕዝቦቹ እንዲለያዩ ተገደዋል በማለት የሚተቹ ተንታኞች አሉ፡፡ የሰማያዊ ፓርቲ የወቅቱ ፕሬዚዳንት አቶ የሸዋስ አሰፋ በዚህ ጉዳይ ላይ ይስማማሉ፡፡ ‹‹እነዚህ አንድ የነበሩ ሕዝቦች አሁን ሁለት ከመሆናቸው ባሻገር በመሪዎች አለመግባባት የተነሳ ወንድማማችና እህትማማች ሕዝብ ወደ ጦርነት ገብቶ ነበር፤›› ብለዋል፡፡

ሳዑዲ ዓረቢያ የአሰብን ወደብ በሊዝ ለመከራየት ከኤርትራ ፈቃድ አግኝታለች፡፡ ይኼ ለሳዑዲ ዓረቢያ መልካም አጋጣሚ እንደሆነ ሲነገር ይሰማል፡፡ ይህም በገልፍ አገሮች ዘንድ ያላትን ተሰሚነት ከፍ ከማድረጉም ባሻገር፣ በቀይ ባህር በኩል ያለውን አካባቢ በቅርብ ርቀት ለመከታተል ዕድል እንደከፈተላት ይነገራል፡፡ ምንም እንኳ የአሰብና የምፅዋ ወደቦች እስከዛሬ ድረስ ከግመል ውኃ መጠጫነት እንዳልዘለሉ እየተነገረ ቢሆንም፣ አገሮች በተለይም የገልፍ አገሮች በዚህ አካባቢ የራሳቸው ቀጣና እንዲኖራቸው ደፋ ቀና ሲሉ ይታያል፡፡ ለአብነት ያህልም ግብፅ በተደጋጋሚ ጊዜ በዚህ ቀጣና ድርሻ እንዲኖራት ጥረት እያደረገች መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

ግብፅ በተለይ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የዓባይ ወንዝ ሙግት በበላይነት ለመወጣት ዙሪያ ጥምጥም ስትሄድ ተስተውሏል፡፡ ከኢትዮጵያ ጋር እያደረገች ካለችው ዲፕሎማሲ ባሻገር በቀይ ባህር በኩል በተለይም በአሰብና በምፅዋ ወደቦች አካባቢ ወታደራዊ ቤዝ ለመገንባት ጥረት እያደረገች ነው፡፡ ከኤርትራ ጋር ያላትን ግንኙነት እንደ መልካም አጋጣሚ ተጠቅማም አጋርነቷን አጠናክራለች፡፡ የኤርትራ ፕሬዚዳንት በተደጋጋሚ ጊዜ ወደ ካይሮ ሲያቀኑ መታየት ሚስጥሩም ይኼ እንደሆነ ይነገራል፡፡

በምሥራቅ አፍሪካ በተለይም በሶማሊያ እየተስፋፋ የመጣው የአሸባሪነት ድርጊት አንዱ መንስዔም ኤርትራ እንደሆነች በርካታ ሪፖርቶች ይጠቁማሉ፡፡ አልሸባብን በመደገፍና በማስታጠቅ በቀጣናው ያለው ሰላምና መረጋጋት እንዲደፈርስ ኤርትራ እየሠራች መሆኑን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ሲገልጽ ቆይቷል፡፡

ኢትዮጵያን በመተንኮስ ሳይቻላት ደግሞ አሸባሪዎችን በማስታጠቅና በመደገፍ አገሪቱ እንድትዳከም ሌት ከቀን እየሠራች እንደሆነ ይነገራል፡፡ ይኼንን ጉዳይም ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ ጊዜ ለተመድ የፀጥታው ምክር ቤት አቤት ስትል መቆየቷን የውጭ ጉዳዩ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም ተናግረዋል፡፡

በዚህም የተነሳ የተመድ የፀጥታው ምክር ቤት በኤርትራ ላይ እ... 2009 ማዕቀብ ጥሎባታል፡፡ በዚህ ማዕቀብ አገሪቱ ከውጭ የጦር ማሣሪያ እንዳታስገባ ከልክሏል፡፡

በፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የሚመራው የኤርትራ መንግሥት ከድርጊቱ ሊቆጠብ ባለመቻሉ የተመድ የፀጥታው ምክር ቤት እ... ታኅሣሥ 16 ቀን 2016 ባደረገው ስብሳባ በአገሪቱ ላይ ዳግመኛ ማዕቀብ ጥሎባታል፡፡ ይኼ ማዕቀብ እ... እስከ ኅዳር 15 ቀን 2017 የሚቆይ እንደሆነ በተመድ ውሳኔ 2317 ምዕራፍ ሰባት ላይ በዝርዝር ሰፍሯል፡፡ ማዕቀቡ ሩሲያን ጨምሮ በአንጎላ፣ በቻይና፣ በግብፅና በቬንዙዌላ ድምፅ ተአቅቦና በአሥር አገሮች ድጋፍ ፀድቋል፡፡

በዚህ ማዕቀብ ኤርትራና ሶማሊያ የጦር መሣሪያ ግዢ እንዳይፈጽሙ ዕግድ ተጥሎባቸዋል፡፡ ይሁን እንጂ አገሮች በተለይም ኤርትራ የተጣለባትን ማዕቀብ እየጣሰች መሆኑ እየተነገረ ነው፡፡

ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ለሦስተኛ ጊዜ የተመድ የፀጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባል አገር ነች፡፡ አባል ከሆነች አንድ ዓመት ባይሞላትም በቆይታዋ ብዙ ሥራዎችን ስታከናውን መቆየቷን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገልጿል፡፡

የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ኢትዮጵያ የፀጥታው ምክር ቤት አባል በመሆኗ በምሥራቅ አፍሪካ ያለውን ጉዳይ ትኩረት እንዲሰጠው ተደርጓል፡፡ ከደቡብ ሱዳን እስከ ሶማሊያ፣ ከቻድ እስከ ኤርትራ ያለውን የፀጥታ ጉዳይ በማንሳትና ለውይይት በማቅረብ ትኩረት እንዲሰጠው መደረጉን ገልጸዋል፡፡

ኤርትራ በአካባቢው ያላትን የጠብ አጫሪነት ድርጊትም ኢትዮጵያ እንዳጋለጠች ጠቁመዋል፡፡ ኢትዮጵያ ይኼን ዕድል ተጠቅማ ኤርትራ የተጣለባትን ማዕቀብ እያከበረች እንዳልሆነ በተደጋጋሚ ጊዜ ስትገልጽ መቆየቷም ተጠቅሷል፡፡ በዚህም የተነሳ የፀጥታው ምክር ቤት ወደ ኤርትራ አጣሪ ቡድን ሊልክ መሆኑን መረጃዎች አመልክተዋል፡፡ የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚሉት፣ ይኼ ውጤት ሊመጣ የቻለው ኢትዮጵያ የፀጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባል በመሆኗ ነው፡፡ ይኼ ደግሞ አገሪቱ ምን ያህል አሸባሪ ቡድን እንደምትደግፍና ለቀጣናው ሰላም መስፈን አደናቃፊ መሆኗን እንደሚያጋልጥ ተስፋ እንዳላቸው እየተናገሩ ነው፡፡ አቶ መለስ በዚህ ጉዳይ ላይ አይስማሙም፡፡

አቶ መለስ እንደሚሉት፣ በኤርትራ ላይ ሲጀመር ማዕቀብ የተጣለበት ዝርዝር ምክንያቶች እንዳሉ ያብራራሉ፡፡ ከእነዚህ መካከልም የኤርትራ መንግሥት በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ባለው የአተራማሽነት ፖሊሲ፣ የጂቡቲን ደኅንነት አደጋ ላይ በመጣሉና ከአልሸባብ ጋር አንድ ላይ ሆኖ በሽብር ተግባር ላይ መሰማራቱ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ እነዚህን ጉዳዮች መሠረት በማድረግ የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት (ኢጋድ) እና የአፍሪካ ኅብረት ውይይት አድርገው ጉዳዩን ወደ ተመድ የፀጥታው ምክር ቤት እንደላኩት አቶ መለስ ተናግረዋል፡፡ በዚህ መሠረት በኤርትራ ላይ የተጣለውን ወይም ደግሞ ወደፊት ሊጣል የሚችለውን ማዕቀብ ከኢትዮጵያ ጋር አያይዞ ማቅረብ፣ የኤርትራ መንግሥት የአሸባሪነት ድርጊትን አሳንሶ ማየት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ተንታኞች በኤርትራ ላይ የተጣለው ማዕቀብ መጣሱን የሚያጣራ ቡድን ወደ አገሪቱ ሊላክ መሆኑን በተመለከተ የተለያዩ አስተያየቶችን እየሰጡ ነው፡፡ የመጀመርያው ጉዳይ ኤርትራ ይኼንን ቡድን አሜን ብላ ትቀበለዋልች ወይ የሚለው ሲሆን፣ ሌሎች ደግሞ አገሪቱ የባሰ የአተራማሽነት ድርጊቷን እንድትገፋበት የሚያደርግ ሊሆን እንደሚችል ይናገራሉ፡፡ ኢትዮጵያ በመስከረም ወር 2010 .. በሚኖራት የአንድ ወር የፀጥታው ምክር ቤት ፕሬዚዳንትነት፣ ኤርትራን በተመለከተ ለንግግር የሚጋብዝ አጀንዳ ማቅረብ እንደሚገባትም አክለው ያስረዳሉ፡፡

በተለያዩ አካላት ተጠንቶና ታይቶ በኤርትራ ላይ ማዕቀብ ቢጣልም፣ አሁንም ማዕቀቡን እየጣሰች ለመሆኑ የሚያጣራ ቡድን ሊላክ መሆኑ እተየሰማ ቢሆንም፣ አሁንም ኤርትራን ለንግግር መጋበዝ ተገቢ እንደሆነ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡

በውጭ ግንኙነት ስትራቴጂካዊ ጥናት ኢንስቲትዩት የጂኦ ፖለቲካ ጉዳዮች ተመራማሪና ተንታኝ አቶ አበበ አይነቴ በዚህ ጉዳይ ላይ ይስማማሉ፡፡ አቶ የሸዋስ በበኩላቸው ይኼንን ሐሳብ ይቃወማሉ፡፡ ድርድር መልካም ቢሆንም እነዚህ ፓርቲዎች እስካሉ ድረስ ለውጥ ሊመጣ እንደማይችል እምነታቸውን ይናገራሉ፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ መለስ ደግሞ የኤርትራ መንግሥት ከኢትዮጵያ ተደጋጋሚ የሆነ የእንነጋገር ጥያቄ ቀርቦለት እንዳልተቀበለው ግልጽ አድርገዋል፡፡ የኤርትራ መንግሥት አሁን ካለው የአተራማሽነት ባህሪው ለውጥ እንዳላመጣ፣ ይኼን ጉዳይ የሚከታተለው የተመድ የፀጥታው ምክር ቤት አጣሪ ቡድን ከወራት በፊት ማረጋገጡንም ጠቁመዋል፡፡

የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚሉት ኤርትራ የተጣለባትን ማዕቀብ ማክበርና አለማክበሯን በተመለከተ የሚያጣራ ቡድን ሊላክ የታቀደውም ከዚህ ቡድን ሪፖርት ተነስቶ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ተንታኞች ይኼን ይበሉ እንጂ አቶ የሺዋስ ኢትዮጵያ የተመድ የፀጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባል በመሆኗ የተነሳ ይኼንን ጉዳይ የቤት ሥራዋ አድርጋ በመሥራትና በመከተል የፈጠረችው ጫና ነው ይላሉ፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት በኤርትራ ላይ ሁለት ፖሊሲዎችን ሲያራምድ እንደነበር ይታወቃል፡፡ አንደኛው ተመጣጣኝ ዕርምጃ የሚለው ሲሆን፣ ሁለተኛው መደራደር ነው፡፡ እነዚህ የኢትዮጵያ ፖሊሲዎች በተደጋጋሚ ጊዜ ውጤት እንዳላመጡም ሲነገር ነበር፡፡

በዚህም የተነሳ መንግሥት ከወራት በፊት በኤርትራ ላይ የሚከተለውን ፖሊሲ ለመቀየር አዲስ ፖሊሲ እያረቀቀ መሆኑን ገልጾ ነበር፡፡ ይኼ አዲሱ ፖሊሲ ምን እንደሆነ ባይታወቅም፣ አብዛኞቹ የዘርፉ ባለሙያዎች ኤርትራን ወደ ድርድር የሚያመጣት ሊሆን እንደሚችል ይናገራሉ፡፡

በሌላ በኩል ኢትዮጵያ የተመድ የፀጥታው ምክር ቤት በኤርትራ ላይ ሌላ ማዕቀብ እንዲጥልባት ግፊት ማሳደሯና አሁን ደግሞ ማዕቀቡን ማክበሯንና አለማክበሯን የሚያጣራ ቡድን እንዲላክ ሐሳብ ማመንጨቷ፣ አገሪቱ ልትከተል ካሰበችውና የብዙ ባለሙያዎች እምነት የሆነውን ተቀራርቦ የመነጋገር ፖሊሲ ሊያሻክረው እንደሚችል ይናገራሉ፡፡ አቶ የሸዋስ ግን በዚህ ሁኔታ ሁለቱ መሪዎች ተቀራርበው መነጋገር እንደማይችሉ እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡ አቶ አበበ በበኩላቸው፣ ይኼ ሐሳብ የማይጣረስ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ‹‹የተለየ ፖሊሲ የተባለው ኤርትራ የያዘችውን ፖሊሲ እንድታስተካከል ለማድረግ ያለመ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በኢጋድ መድረክ ውጤታማ የሆነችውም በዚህ ምክንያት ነው፤›› ብለዋል፡፡

አቶ የሺዋስ ግን በዚህ ሐሳብ አይስማሙም፡፡ ‹‹ፖሊሲዬን አሻሽላለሁ የሚለው በእኔ እምነት አይሠራም፡፡ በሁለቱ መንግሥታት መካከል ያለው ግንኙነት የጌታና የአሽከር ነው፤›› በማለት ይናገራሉ፡፡

‹‹የኤርትራ መንግሥት ሁሌም ጌታ መሆን ነው የሚፈልገው፡፡ ይኼኛው ደግሞ ትልቅ አገርና ሰፊ ሀብት ስለያዝኩ አይሆንም ይላል፡፡ ስለዚህ ይኼ ጉዳይ መቼም አይፈታም፡፡ ሰዎቹም እነዚያው ናቸው፡፡ የትውልድ ለውጥም የለም፤›› በማለትም ይገልጻሉ፡፡

አቶ የሸዋስ ሁለቱ ተስማምተው የሚኖሩበት ጊዜ አይኖርም ብለው፣ ‹‹የሕዝቡን ግንኙነት ግን ለብቻ እንዲታይ እፈልጋለሁ፤›› በማለት አክለዋል፡፡ የሁለቱ አገሮች ሕዝቦች አንድ እንደነበሩና ተመሳሳይ ቋንቋ የሚናገሩ ሕዝቦች ለሁለት መከፈላቸውን አስታውሰዋል፡፡

ምንም እንኳ ኤርትራ ማዕቀብ የተጣለባት አገር ብትሆንም ወደ ዓረብ አገሮች እየተሳበች የጦር መሣሪያ ግዥና ሌሎች ሸቀጣ ሸቀጦችን እንደምታስገባ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ አቶ የሸዋስ እንደሚሉት፣ ማንኛውም አገር አንዱ ፊቱን ካዞረበት ወደ ሌላው ይሄዳል፡፡ ‹‹ኤርትራ በሕዝብ ቁጥር፣ በተፈጥሮ ሀብትና በቆዳ ስፋት ትንሽ አገር ነች፡፡ ኤርትራ ትንሽ አገር ብትሆንም ለዚህ ቁመና የበቃችው ደግሞ በዓረብ አገሮች ድጋፍ ነው፤›› ይላሉ፡፡

በአሁኑ ወቅት እነዚህ የዓረብ አገሮች ወደ ቀይ ባህር እየተሳቡ ወታደራዊ ቤዝ እያቋቋሙ እንደሆነ ይነገራል፡፡ በዚህ አካባቢ ወታደራዊ ቤዝ ማቋቋም በተመለከተ አቶ የሸዋስ ሲገልጹ፣ ‹‹ወታደራዊ ቤዝ በጂቡቲም ሆነ በኤርትራ ማቋቋም ቦታ የሰጡትን የእነዚህን አገሮች ድክመቶች፣ የእነዚያን ደግሞ ድንበር ተሻግሮ መምጣት የሚያሳይ ነው፤›› ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያና ኤርትራ በተለይም ከ1990 .. ወዲህ ዓይንና ናጫ ሆነው እየኖሩ ያሉ አገሮች ናቸው፡፡ በሁለቱ ድንበሮች መካከል ውዝግብ ከተፈጠረ ከሃያ ዓመታት በላይ ተቆጥሯል፡፡ ምንም እንኳ የሁለቱ አገሮች ሕዝቦች አንድ የነበሩ ቢሆንም፣ በተፈጠረው የፖለቲካ ልዩነት ሳቢያ መለያየታቸውን በቅሬታ የሚያቀርቡ ድምፆች ከየአቅጣጫው ይሰማሉ፡፡

በተጠንቀቅ ላይ ያለው የሁለቱ አገሮች ግንኙነት በድንበር አካባቢ ያሉ የሁለቱን አገሮች ሕዝቦች ተረጋግተው እንዳይኖሩ እያደረገ መሆኑም ይነገራል፡፡ በተደጋጋሚ ጊዜ የኤርትራ መንግሥት ወደ ኢትዮጵያ በመግባት ዜጎችን አፍኖ እየወሰደና በጉልበት ሥራ እያሰማራ መሆኑ ደግሞ፣ ጉዳዩን የከበደ እንደሚያደረገው በተደጋጋሚ ተገልጿል፡፡

ኢትዮጵያ ተደጋጋሚ የሆነ የእንነጋገር ጥያቄ እንዳቀረበች ስትናገር ቢሰማምና ኤርትራን በተመለከተ አዲስ ፖሊሲ ለመከተል ብታቅድም፣ በተመድ የፀጥታው ምክር ቤት ግፊት በማድረግ ኤርትራ የተጣለባትን ማዕቀብ ባለማክበሯ ጫና ለመፍጠር ጥረት ማድረጓ ግልጽ እየሆነ ነው፡፡ ኤርትራ በአካባቢው በበጥባጭነት ስሟ በተደጋጋሚ መነሳቱ ደግሞ ወደፊት ከበድ ላሉ ማዕቀቦች ሊዳርጋት እንደሚችል ብዙዎችን ያስማማል፡፡