Skip to main content
x
የእንቦጭ አረምን ለመከላከል የፌዴራል መንግሥት ድጋፍ ውስን እንደሆነ ተገለጸ

የእንቦጭ አረምን ለመከላከል የፌዴራል መንግሥት ድጋፍ ውስን እንደሆነ ተገለጸ

በጣና ሐይቅ ላይ የተንሰራፋውን የእንበጮች አረም ለመከላከል በሚደረገው ጥረት፣ የፌዴራል መንግሥት ድጋፍ ውስን እንደሆነ ተገለጸ፡፡

የአማራ ክልል የአካባቢ፣ ደንና ዱር እንስሳት ጥበቃና ልማት ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር በላይነህ አየለ (ዶ/ር) ማክሰኞ ነሐሴ 30 ቀን 2009 ዓ.ም. ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ የእንቦጭ አረምን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት የፌዴራል መንግሥት የሚጠበቅበትን ሠርቷል ብሎ አፍን ሞልቶ መናገር አይቻልም፡፡ አሁን በተጨባጭ የእንቦጭ አረምን ለማስወገድ እየታገሉ ያሉት የአካባቢው አርሶ አደሮችና በጣና ሐይቅ ዙሪያ ያሉ ወጣቶች እንደሆኑ አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል 500 ሜጋ ዋት የሚሆነውን የአገሪቱን ኤሌክትሪክ ኃይል የሚያመነጨው ከጣና ቢሆንም፣ ድጋፍ እያደረገ እንዳልሆነም ገልጸዋል፡፡ ይኼንን ችግር ለመቅረፍ የዕውቀት፣ የፋይናንስና የልምድ ክፍተት እንዳለ የጠቆሙት ዋና ዳይሬክተሩ፣ የሚመለከተው የፌደራል ተቋም ይኼንን ማሟላትና ማስተካከል ይገባው ነበር ብለዋል፡፡ በአሁኑም ወቅት በአርሶ አደሮችና በወጣቶች አማካይነት የእንቦጭ አረምን ለማስወገድ በሚደረገው ጥረት፣ የፌዴራል ተቋማት ለአርሶ አደሮች የእጅ መሣሪያ፣ እንደ ልብ ተንቀሳቅሰው አረሙን ለመከላከልም ምቹ መንገድና ተሽከርካሪ ማመቻቸት ይገባቸው እንደነበር ጠቁመዋል፡፡

በተደጋጋሚ ጊዜ ይኼንን አረም ለማስወገድ ጥረት የተደረገ ቢሆንም፣ በዘንድሮው ዓመት ለየት ባለ መንገድ አዲስ ኮሚቴ በማቋቋም ወደ ሥራ መግባቱን ዳይሬክተሩ አስረድተዋል፡፡ ይኼን ኮሚቴ በኃላፊነት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው እንደሚመሩት ገልጸው፣ በኮሚቴ ውስጥ የፌዴራል ተቋማትም እንዲካተቱ መደረጉን ተናግረዋል፡፡ በባህር ዳር በዚህ ጉዳይ ላይ ስብሰባ እንደነበር አስታውሰው፣ በስብሰባውም የፌዴራል ተቋማት የሆኑት የአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ሚኒስቴር፣ የብዝኃ ሕይወት፣ የኢትዮጵያ የደን ምርምር ማዕከል፣ የውኃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትር ተወካዮች ተገኝተው እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ በዚህ ወቅትም ተቋማቱ የእንቦጭ አረምን ለመከላከል የሚያስችል ዕቅድ አዘጋጅተው እንዲያመጡ እንደተጠየቀ ገልጸው፣ የተወሰኑት ብቻ እንዳስገቡ አስረድተዋል፡፡

በቀረበው ጥሪ መሠረትም የአካባቢ፣ ደንና አየር ንብረት ሚኒስቴር ብቻ አንድ ተሽከርካሪና ሁለት ሚሊዮን ብር ለመለገስ ፈቃደኝነቱን እንደገለጸ ጠቁመዋል፡፡ ለአሁኑ ተሽከርካሪው እስከሚመጣ ድረስ አሮጌ ተሽከርካሪ ተሰጥቷቸው ለዘመቻው እየተጠቀሙበት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ጣና ሐይቅ የአማራ ክልል ሀብት ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ሕዝቦች ንብረት እንደሆነ የጠቀሱት ዋና ዳይሬክተሩ፣ መንግሥትና ያገባኛል ያለ ማንኛውም አካል ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የእንቦጭ አረም በጣና ሐይቅ ላይ የተከሰተው በአምስት ወረዳዎችና 18 ቀበሌዎች እንደሆነ ከዚህ በፊት መዘገባችን የሚታወስ ነው፡፡ ባለፈው ሳምንት በተደረገው ዘመቻ ከ50 ሺሕ በላይ ወጣቶችን በማንቀሳቀስ አመርቂ ሥራ እንደተከናወነ ተገልጿል፡፡

ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስፋፋ የመጣውን የእንቦጭ አረም ለመከላከል በክልሉ በተለይም የጣና ሐይቅ በሚያዋስናቸው አካባቢዎች ያሉ አርሶ አደሮችና ወጣቶች፣ እንዲሁም በደብረ ታቦር፣ በጎንደርና በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲዎች አማካይነት የጣና ሐይቅን ሰፋ ያለ ክፍል ከአረሙ ነፃ ማውጣት እንደተቻለ ዋና ዳይሬክተሩ አስረድተዋል፡፡