Skip to main content
x
የኬንያ ምርጫ ውጤት መሰረዝ አንድምታዎች

የኬንያ ምርጫ ውጤት መሰረዝ አንድምታዎች

የአፍሪካ አገሮች ከኢትዮጵያና ከላይቤሪያ በስተቀር ለረጅም ዓመታት  በአውሮፓውያን ቅኝ ግዛት ሥር ነበሩ፡፡ ከደቡብ አፍሪካ እስከ ሊቢያ፣ ከኮትዲቯር እስከ ሶማሊያ በአራቱም አቅጣጫ ያሉ አገሮች በቅኝ ገዥዎች እጅ ወድቀው ነበር፡፡ እነዚህ ቅኝ ገዥዎች የአፍሪካን የተፈጥሮ ሀብት ወደ አገራቸው ሲያግዙ ነበር፡፡

ከዛሬ 50 እና 60 ዓመታት በፊት አፍሪካ የጨለማው አኅጉር እየተባለም ይጠራ ነበር፡፡ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ቦታ ያልነበራቸውና በቅኝ ገዥዎች በጎ ፈቃድ የሚመራ አኅጉር እንደነበር ታሪክ ይናገራል፡፡ አፍሪካዊያን ባደረጉት የፀረ ቅኝ አገዛዝ ትግል ሳቢያ እ.ኤ.አ. ከ1960ዎቹ ጀምሮ አኅጉሩ ሙሉ በሙሉ ከቅኝ ገዥዎች እጅ ወጥቷል፡፡ በ11ኛው ሰዓት ከቅኝ ገዥዎች እጅ ነፃ ከወጡ የአፍሪካ አገሮች መካከል ኬንያ አንዷ ነበረች፡፡

ኬንያ ነፃ አገር ከሆነች 62 ዓመት ሞልተዋል፡፡ ከእንግሊዞች እጅ ነፃ የወጣችው እ.ኤ.አ. በ1955 እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ኬንያዊያን እስከ ዛሬ ድረስ እንደ ስጦታ የሚቆጥሯቸው የቀድሞው ታጋይና መሪ ጆሞ ኬንያታ አገሪቱ ከቅኝ ገዥዎች እጅ እንድትወጣ ዋነኛውን ሚና እንደተጫወቱ ይወሳል፡፡ በዚህም የተነሳ በአሁኑ ወቅት የአገሪቱ ዋና ዋና መንገዶችና ሌሎች ተቋማት በእርሳቸው ስም የተሰየሙ ናቸው፡፡ ከእነዚህ መካከልም አንዱ የኬንያ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ነው፡፡ የአገሪቱ ዋነኛውና ግዙፍ ዩኒቨርሲቲም በእሳቸው ስም ይጠራል፡፡

ኬንያ ነፃነቷን አግኝታ ራሷን ችላ እንደ አገር ከተመሠረተች ረጅም ዕድሜ  ባይኖራትም፣ በአሁኑ ወቅት በመሠረተ ልማትና በዴሞክራሲ ግንባታው ዘርፍ ከአፍሪካ ቀዳሚ አገሮች ተርታ የምትሠለፍ መሆኗን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት እ.ኤ.አ. በ2010 የመጀመሪያው ሩብ ዓመት ብቻ የአገሪቱ ጠቅላላ ዕድገት 12.4 በመቶ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ በአሁኑ ወቅት ያለው ዕድገትም 5.47 በመቶ ሆኖ የተመዘገበ ሲሆን፣ በዓመት ብቻ ከግማሽ ሚሊዮን የሚበልጥ የአገሪቱ ወጣት ኃይል የሥራ ዕድል እንደሚፈጠርለት መረጃዎች ያመለክተሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት በኢኮኖሚ በተለይም በትራንስፖርት፣ በሪል ስቴት፣ በኮንስትራክሽን፣ በትምህርት፣ በእርሻና ተፈጥሮ ሀብት እንክብካቤ ከአፍሪካ ቁንጮ አገሮች ተርታ እንደምትሠለፍ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

አገሪቱ በአሁኑ ወቅት በኢኮኖሚና ማኅበራዊ ዘርፎች እያደገች ከመምጣቷ በላይ፣ በፖለቲካው ዘርፍም በአኅጉሪቱ ካሉ አገሮች መካከል የተሻለ ሪኮርድ እንዳላት ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡

ኬንያዊያን በየአምስት ዓመቱ የሚያደርጉት ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ዘንድሮም እ.ኤ.አ. ነሐሴ 8 ቀን 2017 ተካሂዷል፡፡ የምርጫ ቦርድ ይፋ ባደረገው ውጤት መሠረት ኡሁሩ ኬንያታ 54 በመቶ አብላጫ ድምፅ በማግኘት ዳግመኛ ማሸነፋቸውን ይፋ አድርጓል፡፡ ኡሁሩ ዋነኛ ተፎካካሪ የነበሩት ራይላ ኦዲንጋ የምርጫ ቦርድ ይፋ ያደረገውን ውጤት አልቀበልም በማለት፣ በወቅቱ በኬንያ የተወሰኑ ከተሞች መጠነኛ ግጭቶች ተከስተው ነበር፡፡

በዚህም ሳቢያ በሰው ሕይወት ላይ ጉዳት ከመድረሱ በተጨመሪ ንብረት ላም ውድመት ደርሷል፡፡ ይህን ምርጫ ለመታዘብ ኬንያ ታድመው የነበሩ ዓለም አቀፍ ተቋማትና የምሥራቅ አፍሪካ በይነ መንግሥታት (ኢጋድ) የተሳተፉ መሆናቸው አይዘነጋም፡፡ የወቅቱ የኢጋድ ፕሬዚዳንት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝን ጨምሮ ሌሎች የዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች ምርጫው ፍትሐዊና ትክክለኛ እንደነበር፣ ኬንያውያን ደግሞ ውጤቱን በፀጋ እንዲቀበሉ መግለጫ መስጠታቸው ይታወሳል፡፡ 44ኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት የነበሩት ባራክ ሁሴን ኦባማም እንዲሁ ብለው ነበር፡፡

የተቃዋሚው ዋነኛ መሪ አዲንጋ ይህን ዓለም አቀፍ ግፊት ተቋቁመው  ምርጫው ፍትሐዊ እንዳልሆነ በመግለጽ፣ ጉዳዩን ወደ አገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ወሰዱት፡፡ ኡሁሩ ኬንያታ ማሸነፋቸው ከተበሰረ ወር ሳይሞላው በአፍሪካ ምድር ታቶና ተሰምቶ የማይታወቅ ጉዳይ ተፈጸመ፡:፡ ይህም የኬንያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምርጫው ፍትሐዊነት የጎደለው ነው በማለት እንደገና በ60 ቀናት ውስጥ እንዲካሄድ ውሳኔ አሳለፈ፡፡ ይህ በኬንያ ምድርም ሆነ በአፍሪካ ተደርጎም ሆነ ተሰምቶ የማይታወቅ ውሳኔ በመሆኑ፣ የኦዲንጋን ደጋፊዎች የደስታ ዕንባ ሲያራጭ ሰንብቷል፡፡ በአፍሪካ ምድር ለመጀመሪያ ጊዜ በሚባል ደረጃ በሥልጣን ላይ ያለውንና በድጋሚ አሸንፌያለሁ ብሎ ያወጀው የኬንያታ መንግሥት በፍርድ ቤት ውሳኔ ውጤቱ ሲሰረዝና ለድጋሚ ምርጫ ሲዘጋጅ የታየው ኬንያ ውስጥ ነው፡፡

ወደዚህ ጉዳይ እንዴት ሊመጣ እንደቻለ ባለሙያዎች የተለያዩ አስተያየቶችን ሲናገሩም እየተሰማ ነው፡፡ ምንም እንኳ ፍርድ ቤቱ ምርጫው ተሰርዞ እንደገና እንዲካሄድ የወሰነው፣ በምርጫ ሒደቱ ውስጥ መጭበርበሮችና የምርጫ ቦርድን ገለልተኛነት ጥያቄ የሚያስገቡ ጉዳዮች በመገኘታቸው እንደሆነ ጠቅለል አድርጎ ገልጿል፡፡

የፖለቲካ ተንታኞች የዚህ ዓመት የኬንያ ምርጫ በችግሮች የተሞላ እንደነበር ይናገራሉ፡፡ ከምርጫ በፊት በኬንያታና በኦዲንጋ ደጋፊዎች መካከል በማኅበራዊ ሚዲያዎች የነበረው ጦርነት፣ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሩ ድንገተኛ ሞት እ.ኤ.አ. በ2007 በምርጫ ሰሞን በድንገት ከሞቱት የደኅንነት ኃላፊ ጋር መገጣጠሙ፣ በዚያ ምርጫ ሳቢያ ተካሂዶ የነበረው ብጥብጥና ሁከት ሊደገም እንደሚችል አመላካች መሆኑ፣ መንግሥት በከፍተኛ ወጪ የአድማ መበተኛ መሣሪያዎችን ከውጭ ማስመጣቱና የፀጥታ ኃይሎች ከምርጫው አንድ ወር አስቀድሞ ወደ ሥልጠና መግባታቸው፣ የምርጫውን ውጤት በኤሌክትረኒክስ መሣሪያዎች በመታገት በቀጥታ ለሚዲያዎችና ለሕዝብ ለማስተላለፍ የተቋቋመው የምርጫ ቦርድ የኦንላየን ሰርቨር ዋና ኃላፊ ተገድሎላ መገኘታቸውና የመሳሰሉት ጉዳዮች፣ ምርጫው በሰላም እንዳይጠናቀቅ አመላካች እንደነበሩ ተንታኞች ሲናገሩ ተደምጧል፡፡

ተቃዋሚው ራይላ ኦዲንጋ ምርጫው መጭበርበሩንና ውጤቱን እንደማይቀበሉ ምርጫ ቦርዱ ውጤቱን እያስተላለፈ በነበረበት ወቅት ተናገሩ፡፡ ጉዳዩንም ወደ ፍርድ ቤት ወስደው ህልማቸው ተሳክቷል፡፡ ወደ ፍርድ ቤት እንዲወስዱት መነሻ የሆናቸው ግን ምርጫውን ይታዘቡ ከነበሩ የአገር ውስጥ ተቋማት መካከል አንዱ የሆነው የኬንያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (KNHRC) እንደሆነ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ ይህ ተቋም ምርጫውን በታዛቢነት ከተሳተፉ ሌሎች ዓለም አቀፍና አኅጉር አቀፍ ተቋማት መካከል በብቸኝነት ምርጫው መጭበርበሩን ደፍሮ ለመናገር መቻሉ ተነግሯል፡፡

ምርጫውን ኢትዮጵያ የተወከለችበት የአፍሪካ ኅብረት፣ ኢጋድ፣ የካርተር ማዕከል፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና ሌሎች በታዛቢነት ተሳትፈውበታል፡፡ የካርተር ማዕከልና የአፍሪካ ኅብረት ምርጫው ትክክለኛና ፍትሐዊ እንደነበረም ገልጸዋል፡፡

ኡሁሩ ኬንያታም በፍርድ ቤቱ ውሳኔ ማዘናቸውን፣ ነገር ግን ሁሉም ሰው ለሕግ ተገዥ መሆን ስላለበት ውሳኔውን በመቀበል በድጋሚ በሚካሄደው ምርጫ ለመሳተፍ እንደሚፈልጉ ገልጸዋል፡፡ ‹‹ስምንት ሚሊዮን ሕዝብ የሰጠኝን ድምፅ ስድስት ሰዎች አይገባህም ብለውኛል፡፡ እኔ ደጋፊዎቼ ወደ ሁከትና ብጥብጥ እንዲገቡ አልፈልግም፡፡ ደጋፊዎቼ በድጋሚ በሚካሄደው የምርጫ ቀን እንደገና ወጥታችሁ ሰላማዊ በሆነ መንገድ ድምፃችሁን ስጡኝ፤›› ብለዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ በሰጠው ውሳኔም ተጠያቂ ያደረገው የምርጫ ቦርዱን ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱን በመጣስ ኡሁሩ ኬንያን አሸናፊ አድርጓል በማለት ጥፋተኛ አድርጎታል፡፡ በምርጫው ውጤት ማሳወቅ ጊዜ ይጠቀሙባቸው የነበሩ ወረቀቶች የምርጫ ቦርድ ትክክለኛ ማኅተም ያላረፈባቸው፣ የተቃዋሚዎችና የታዛቢ ተወካዮች ፊርማ ያላረፈበት የድምፅ መስጫ ካርዶች መኖራቸውን በምርመራ ማረጋገጡን አስታውቋል፡፡

የተቃዋሚዎች መሪ ራይላ ኢዲንጋ ይህ ውሳኔ በተላለፈበት ዕለት ከደጋፊዎቻቸው ጋር በመሆን የደስታ ዕንባ ሲያነቡ ታይተዋል፡፡ ደጋፊዎቻቸውም እያቀፉ ሲስሟቸውና አምላካቸውን ሲያመሰግኑ ነበር፡፡ ኦዲንጋ ባደረጉት ንግግር፣ ‹‹ይህ ውሳኔ ለኬንያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካዊያንም ኩራትና ትምህርት ነው፡፡ የምርጫ ቦርድ ኃላፊዎች የሠሩት ስህተት በአገሪቱ ሕግ ወንጀል በመሆኑ ይጠየቁበታል፡፡ ለፍርድ ለማቅረብም ጠንክሬ እሠራለሁ፤›› ብለዋል፡፡

ኡሁሩ ኬንያታና ምክትላቸው ዊልያም ሩቶ በድጋሚ ለሚካሄደው ምርጫ ቅስቀሳ ለማድረግ ወደ ተለያዩ ቦታዎች እያመሩ መሆኑም እየገለጹ ሲሆን፣ ደጋፊዎች ግን እንደ ቀድሞው እየተቀበሏቸው እንዳልሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

በአውሮፓ ወይም በአሜሪካ ሳይሆን በኬንያ ምድር የተካሄደው የምርጫ ቦርድን ውሳኔ የሻረው ፍርድ ቤት ውሳኔ በዓለም ዙሪያ እያነጋገረ ነው፡፡ ይህም ውሳኔ ምሥጋና የሚገባውና ለአፍሪካ አገሮች ተምሳሌት ሊሆን እንደሚችል የቢቢሲ ፎከስ ኦን አፍሪካ ተንታኞች ሲናገሩ ነበር፡፡

ፍርድ ቤቱ ገለልተኛ ሆኖ የምርጫ ሒደቱን እንደገና የመፈተሽና ውጤቱ እንዲሻር የማድረግ ተሞክሮውን ኢትዮጵያ ልትማርበት እንደሚገባ የሚናገሩ አለ፡፡ የቀድሞው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህር ዳኛቸው አሰፋ (ዶ/ር)፣ ኬንያ ኢትዮጵያን በሩጫ ብቻ ሳይሆን በፖለቲካውም እንደምትበልጥ ይናገራሉ፡፡ ኬንያ ውስጥ ነፃ የሆነ ዳኝነት እንዳለ ገልጸዋል፡፡ ‹‹ዳኝነት ነፃነት የሚጠይቅ ሥራ ነው፡፡ እነሱ ደግሞ ለሁላችንም ብርሃን ነው ጥለው የሄዱት፤›› ብለዋል፡፡

ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አንድ ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊ በዶ/ር ዳኛቸው ሐሳብ አይስማሙም፡፡ ኢትዮጵያ በበኩሏ በተለይ ካለፉት 20 ዓመታት ወዲህ ፍትሐዊና ትክክለኛ ምርጫ ስታካሂድ መቆየቷን ገልጸዋል፡፡ የነበሩ ምርጫዎች ፍትሐዊና ትክክለኛ ከመሆናቸው አኳያም ወደ ፍርድ ቤት እንዳልሄዱና የሄዱትም ቢሆን ተመርምረው ስህተት በመሆናቸው ውድቅ መደረጋቸውን ይናገራሉ፡፡

ፖለቲከኛውና ምሁር ንጋት አስፋው (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ የኬንያ ፍርድ ቤት ውሳኔ የሕግ የበላይነትን የሚያሳይ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ዶ/ር ንጋት እንደሚሉት፣ ጆሞ ኬንያታና ጁልየስ ኔሬሬ አገራቸው ከቅኝ ገዥዎች ነፃ ሳይወጡ በ1955 ዓ.ም. አዲስ አበባ መጥተው ነበር፡፡ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴና በጠቅላይ ሚኒስትር አክሊሉ ሀብተ ወልድ፣ እንዲሁም በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ከተማ ይፍሩ ደማቅ አቀባበል አድርገውላቸዋል፡፡ በወቅቱ ዶ/ር ንጋት ልጅ ስለነበሩ ለእነዚህ ሰዎች የአበባ ጉንጉን መስጠታቸውን አስታውሰዋል፡፡ እነዚህ አገሮች ነፃነታቸውን የተቀዳጁት በቅርብ ጊዜ መሆኑንና ኢትዮጵያ ደግሞ በወቅቱ የተሻለች አገር እንደነበረች ተናግረዋል፡፡

ኡሁሩ ማለት በስዋህሊ ነፃነት ማለት እንደሆነ የሚገልጹት ዶ/ር ንጋት፣ ኬነያ ውስጥ ከነፃነት ወዲህ ሦስት ወይም አራት መሪዎች ቢፈራረቁም አንዳቸውም ግን መፈንቅለ መንግሥት ወይም በኃይል ለመገልበጥ እንዳልሞከሩ ያስረዳሉ፡፡ የመቻቻል ዴሞክራሲ የሚባለውም በኬንያ እየታየ እንደሆነም ይገልጻሉ፡፡ ከራስ ፍላጎት ይልቅ የሕዝብ ፍላጎት ይቅደም የሚለው መርህ ተግባራዊ እየተደረገ ያለውም በኬንያ  እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

ኬንያ በቅርቡ ባካሄደችው ምርጫ ምን ይፈጠራል የሚለው የዓለም አቀፉ  ማኅበረሰብ ትኩረት እንደነበር ዶ/ር ንጋት ጠቅሰው፣ ኡሁሩ ኬንያታ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ መቀበላቸው ለአፍሪካውያንን ፖለቲከኞችና ምሁራን ትምህርት የሰጠ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡ ይህ የተስፋ ጭላንጭል በአፍሪካ መታየት መጀመሩ ለሌሎች የአፍሪካ አገሮች ትልቅ ተሞክሮ እንደሆነም ይናገራሉ፡፡

ከዚህ ምርጫ ኢትዮጵያ የምትማረው ትልቅ ነገር እንዳለም ዶ/ር ንጋት ያብራራሉ፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ የተካሄደው የ1997 ዓ.ም. ምርጫ ብዙ ውስብስብ ጉዳዮች እንደነበራት አስታውሰዋል፡፡ በዚህም ሦስቱ የመንግሥት አካላት ከኬንያ ምርጫ ብዙ የሚማሩት ነገር እንዳለ ተናግረዋል፡፡

ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የመንግሥት ኃላፊ በበኩላቸው ከዶ/ር ንጋት ሐሳብ ጋር አይስማሙም፡፡ በ1997 ዓ.ም. ኢሕአዴግ በተወሰኑ ቦታዎች ላይ መሸነፉ እንደሚታወቅ ጠቅሰው፣ ተቃዋሚዎች በመላ አገሪቱ እንዳሸነፉ አድርገው ያነሱት የነበረው ጉዳይ ሚዛን የሚደፋ አልነበረም ይላሉ፡፡ መንግሥት ሕገ መንግሥቱ እንዲከበር ግዴታ ስላለበትና አገሪቱ ወደለየለት ሁከት እንዳትገባ በወሰደው ዕርምጃ የሰዎች ሕይወት እንዳለፈ አስታውቀዋል፡፡ የኬንያ በተመለከተ ዓለም አቀፍ ታዛቢዎች ፍትሐዊነቱንና ትክክለኛነቱን የመሰከሩለት ምርጫ በፍርድ ቤት መሻሩ ግን የታዛቢዎችን ክፍተት የሚያሳይ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ዶ/ር ንጋት ኢትዮጵያ ውስጥ ከዚህ የከፋ ችግር እንዳይከሰት ፖለቲካውን ፕራይቬታይዝ ማድረግ ተገቢ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ‹‹ኬኒያ ከ1963 ተነስታ የሦስት ሺሕ ዘመን ታሪክ ያላትን ኢትዮጵያ በልጣ በመገኘቷ በጣም አዝናለሁ፤›› ብለዋል፡፡

የኬንያ ምርጫ ከታዘቡት ተቋማት መካከል አንዱ የአፍሪካ ኅብረት ነው፡፡ የአፍሪካ ኅብረት ምርጫው ትክክለኛና ፍትሐዊ እንደነበር በመገለጽ፣ ዶ/ር ንጋት፣ ‹‹የአፍሪካ ኅብረት ሲጀመር የአምባገነኖች ኅብረት ነው፤›› በማለት የኅብረቱን የታዛቢነት ውጤት ኮንነዋል፡፡ የአፍሪካ መሪዎች እከከኝ ልከክህ እንጂ በአፍሪካ ፖለቲካ ውስጥ ለውጥ እንዲመጣ የሚታገሉ አይደለም ብለዋል፡፡ ለአብነትም የኡጋንዳ፣ የጂቡቲ፣ የኤርትራና የዚምባብዌ መሪዎች ሥልጣንን የዕድሜ ዘመን መጠቀሚያ እያደረጉ እንደሆኑና ከእነዚህ አገሮች ለውጥ እንደማይታሰብ ሞግተዋል፡፡

የቀድሞው የኢዴፓ ፕሬዚዳንት አቶ ሙሼ ሰሙ በበኩላቸው፣ የምርጫ ቦርድ በተወሰነ መልኩ ገለልተኝነት ይንፀባረቅባቸዋል በሚባሉት አገሮች ውስጥ ሳይቀር ለገዥው ፓርቲ በቀላሉ ሰለባ እንደሚሆንና የምርጫ ውጤቱን እንዴት ሊያዛባ እንደሚችል የኬንያ ምርጫ ያሳያል ይላሉ፡፡

ሁለተኛ መከራከሪያ ነጥባቸው ደግሞ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በምርጫ ወቅት ሁሌም ምስክር ሆኖ ሲቀርብ ምርጫው ትክክለኛና ፍትሐዊ ነው ማለቱ ነው፡፡ ከፖለቲካ ጥቅምና ሽብርን በመዋጋት ኬንያ ባላት ሚና ብቻ ተመዝኖ የምርጫውን ውጤት አንቆላጳጵሰውት እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ የካርተር ማዕከልና ሌሎች እንደዚህ ዓይነት ምርጫ ታይቶ እንደማይታወቅ ከከረሙ በኋላ፣ መጨረሻ ላይ ማንነታቸው ፍንትው እንደወጣ ተናግረዋል፡፡ የተናገሩት ቃል ሳይደርቅ ውሳኔው መሻሩ በጣም የሚያሳፍር እንደሆነ አክለዋል፡፡ የካርተር ማዕከልና ሚዲያዎች ጭምር እጅ ከፍንጅ መያዛቸውን አውስተዋል፡፡ ስለዚህ አፍሪካውያን ነጮችን ተማምነው የምርጫ ውጤቱን መቀበልና አለመቀበል ላይ መድረስ እንደሌለባቸው አንዱ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡

አቶ ሙሼ ሦስተኛ መከራከሪያ አድርገው የሚያቀርቡት የፍትሕ አካላት ገለልተኝነት ላይ ነው፡፡ በኬንያ የታየው የፍርድ ቤት ነፃነት እስከ ታች ድረስ ወርዶ ሕዝቡ በሥርዓቱ ላይ እምነት እንዲኖረው እንደሚያደርግ ገለጸዋል፡፡ ከዚህም ኢትዮጵያ ብዙ የምትማራቸው ነገሮች አሉ ሲሉ አቶ ሙሼ ያስረዳሉ፡፡ በምርጫ መሸነፍም ሆነ ማሸነፍ የዓለም መጨረሻው እንዳልሆነ የሚጠቅሱት አቶ ሙሼ፣ ‹‹ከስህተትህ ተምረህ፣ ነገ ከዚህ የተሻለ ተጠናክረህ መጥተህ አገርህን የምታገለግልበት አዲስ አማራጭ ቀርፀህና አሸንፈህ ውጤታማ መሆን ላይ ነው ትኩረትህ መሆን ያለበት እንጂ፣ ዕድሜ ልክህን መሳሳት መብት ነው እያልክና እየተሳሳትክም እንደ መንግሥት መቀጠል ውጤቱ ከባድ ነው የሚሆነው፤›› ይላሉ፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ችግር እየሆነ የመጣው መራጩ ሕዝብ መረጠም አልመረጠም፣ ተቀበለም አልተቀበለም፣ ውጤቱ የአንድ አካል እንደሆነ እርግጠኛ መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡ ‹‹ስለዚህ ለምርጫ ያለው እምነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሸረሸረ ደምፅ ለመስጠት መውጣትን እየተወ፣ መረጥኩም አልመረጥኩም ውጤቱ አንድ እንደሚሆን የታወቀ ስለሆነ ምን ትርጉም አለው? ኪሳራ ነው እንጂ ምን ትርፍ አለው? እያለ ነው፤›› ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከዚህ ለመማር የሚያዳግታት አገር እንዳልሆነች የሚየስረዱት አቶ ሙሼ፣ ኬንያውያን የተለዩ ሰዎች ስለሆኑ ወይም ደግሞ ተዓምረኛ ስለሆኑ እንዳልሆነ ጠቁመዋል፡፡ በእርግጥ ኬንያዊያን በዚህ ጉዳይ ላይ ከኢትዮጵያ አንድ ዕርምጃ ወደፊት እንደሄዱና ኢትዮጵያ ከዚህ ለመማር ባህሉ፣ አስተሳሰቡና የአገር ፍቅሩ እንደሚፈቅድ ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ ያለው የዳኝነት ሥርዓት ፓርላማውን ሙሉ በሙሉ በያዘው ገዥው ፓርቲ የሚሾም መሆኑን ጠቅሰው፣ ተሿሚዎቹ ሁልጊዜ ሹመቱን ለሚያፀድቅላቸው ፓርቲ ተጠሪ ነናቸው ብለዋል፡፡ ይሁን እንጂ በዚያው ልክ አገሪቱ ውስጥ ፍትሕ እንዲሰፍን የሚታገሉ፣ በምንም ነገር የማይታለሉና እጃቸው የማይጠመዘዝ እንዳሉ አስታውቀዋል፡፡

‹‹ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፍትሕን በተመለከተ በአብዛኛው ሰው የሚማረርበትና ተስፋ የቆረጥበት ጉዳይ ነው፤›› ብለዋል፡፡ ‹ከመክሰስ መከሰስ› ይሻላል እየተባለ የሚተረትበት ዘመን ላይ መደረሱንም አስረድተዋል፡፡

አንድ ፓርቲ ብቻውን ሥልጣን ላይ ተቀምጦ የሚፈልገውን ሰው የሚሾምበትና የሚያነሳበት አካሄድ እስካለ ድረስ አዲስ ነገር መጠበቅ እንደማይቻል ገልጸው፣ የኬንያና የኢትዮጵያ ልዩነትም የእውቀት ማነስ ሳይሆን ቃለ መሃላ ለገቡለት አገርና ሕዝብ የመቆምና ያለመቆም ጉዳይ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ይህ ግን ሁሉንም ሰው ይመለከተዋል ማለት እንዳልሆነ አክለዋል፡፡

ኬንያና ኢትዮጵያ የጋራ ድንበር ያላቸው አገሮች ሲሆኑ፣ ሁለቱ አገሮች አልሽባብን ከመዋጋት ጀምሮ የጋራ የንግድ ቀጣና እስከ መመሥረት የደረሱ አገሮች ናቸው፡፡ በተለይ በምሥራቅ አፍሪካ ኃያል እየተባሉ የሚጠሩት እነዚህ አገሮች፣ ሽብርተኝነትን ለመዋጋት ከአፍረካ ኅብረትና ከተመድ ጋር የተሠለፉ ናቸው፡፡

ኬንያ በእንግሊዞች ሥር ለብዙ ዓመታት ብትቆይም፣ በአሁኑ ወቅት ኢኮኖሚያቸው እያደገ ከመጡ የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች መካከል ቀዳሚ ናት፡፡ አሁን የአገሪቱን የምርጫ ቦርድ ውሳኔ በመሻር ሌላ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ እንዲካሄድ ተወስኗል፡፡ በዚህም በአገሪቱ ጠንካራ የፍትሕ ሥርዓት ለመኖሩ ማሳያ እንደሆነ እየተነገረ ሲሆን፣ ከዚህም የአፍሪካ አገሮች በተለይም ኢትዮጵያ ብዙ መማር ያለባት ነገር እንዳለ ባለሙያዎች ይስማማሉ፡፡

ቀጣዩ የኬንያ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ እ.ኤ.አ. ጥቅምት 17 ቀን 2017 እንዲካሄድ ተወስኗል፡፡ ተፎካካሪዎቹም ካሁኑ የምርጫ ቅስቀሳቸውን ጀምረዋል፡፡