Skip to main content
x
የኮሪያን ልሳነ ምድር መልሶ ሥጋት ላይ የጣለው የአሜሪካና የደቡብ ኮሪያ ወታደራዊ ልምምድ

የኮሪያን ልሳነ ምድር መልሶ ሥጋት ላይ የጣለው የአሜሪካና የደቡብ ኮሪያ ወታደራዊ ልምምድ


በኮሪያ ልሳነ ምድር ትልቅ ወታደራዊ የጦር ሠፈር ላላት አሜሪካ ወዳጅ የሆነችው ደቡብ ኮሪያ ከጎረቤት ሰሜን ኮሪያ ጋር የጦርነት ሥጋት ቢኖርባትም፣ አሜሪካ በሰሜን ኮሪያ ላይ ማንኛውንም ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት ከመፈጸሟ በፊት አንድታሳውቃት፣ ብሎም ያለ ደቡብ ኮሪያ በጎ ፈቃደኝት አሜሪካ በሰሜን ኮሪያ ላይ ጥቃት መሰንዘር እንደማትችል ባለፈው ሳምንትም አሳውቃለች፡፡

ደቡብ ኮሪያ ያለኔ ፈቃድ ሰሜን ኮሪያን ማጥቃት አይቻልም እንድትል ያደረጋት፣ የሰሜን ኮሪያ ፕሬዚዳንት ኪም ጆን ኡንና የአሜሪካው አቻቸው ዶናልድ ትራምፕ በሰሜን ኮሪያ ኑክሌር ፕሮግራም ላይ እሰጥ አገባ መግባታቸውና በኮሪያ ልሳነ ምድር የጦርነት ሥጋት በማጥላቱ ነው፡፡

ሰሜን ኮሪያ አሜሪካ በቀጣናው ያላትን ወታደራዊ የጦር ሠፈር የምታየው ሰላም ከማስከበር አንፃር ሳይሆን፣ የአገሪቱን መንግሥት ለመገልበጥና በምትኩ የአሜሪካን ፍላጎት የሚያስጠብቅ መሪ ለመተካት ነው በሚል ነው፡፡

አሜሪካ ይኼ ሐሰት ነው ብትልም፣ ሰሜን ኮሪያ ራስን ለመከላከል በሚል ኑክሌር ታበለፅጋለች፣ እ.ኤ.አ. 2017 ከገባም ብቻ 18 ጊዜ የባለስቲክ ሚሳይል ሙከራ አድርጋለች፡፡ በዚህም ፕሬዚዳንት ትራምፕ ‹‹ሰሜን ኮሪያ ላይ ዓለም አይቶት የማያውቀው እሳት እናወርዳለን፤›› ሲሉ፣ ሰሜን ኮሪያም ሞክሩንና የጦርነት በሮች ይከፈታሉ ብላለች፡፡

በዚህ ውዝግብ መሀል ሰሞኑን ከአሜሪካው የጦር ሰፈር ጉአም የተነሱ የአሜሪካ የጦር ጄቶች በኮሪያ ልሳነ ምድር ላይ ቅኝት ማድረጋቸው ሰሜን ኮሪያን ያስቆጣ፣ ለምላሹም ሰሜን ኮሪያ የጉአምን አካባቢ በአራት ሚሳይል ለመምታት ዝግጅት ማጠናቀቋን ያሳወቀችበትም ሰሞን ነበር፡፡ ደቡብ ኮሪያና ጃፓን ከአሜሪካ ጋር መክረው ቀናትም ሳያስቆጥሩ የሰሜን ኮሪያው ኪም፣ በጉአም ላይ ሊዘነዝሩ ያቀዱትን ምት ለጊዜው መተዋቸውን አሳውቀዋል፡፡ ይኼንንም ተከትሎ አካባቢው ትንሽ መረጋጋ ታይቶበት ነበር፡፡

 ሆኖም በየዓመቱ ደቡብ ኮሪያና አሜሪካ ለአሥር ቀናት የሚያከናውኑት የጋራ ወታደራዊ ልምምድ ኪምን አስቆጥቷል፡፡ ምንም እንኳን ወታደራዊ ልምምዱ የተለመደና በየዓመቱ የሚደረግ ቢሆንም፣ በአሜሪካና በሰሜን ኮሪያ መካከል ከአፈሙዝ ጥይቱ ለመውጣት የሰኮንድ ያህል ጊዜ ነው ያለው በሚባልበት በዚህ በተጨናነቀ ወቅት መሆኑ ለሰሜን ኮሪያ አልተመቸም፡፡ ሰሜን ኮሪያም የአሜሪካ ወታደራዊ ልምምድ ወደ እውነተኛው ጦርነት ሊያመራን ይችላል ስትል አስጠንቅቃለች፡፡

የአሜሪካና የደቡብ ኮሪያ የጋራ ወታደራዊ ልምምድ ለማብሰር ወታደራዊ ሠልፍ ባደረጉበት ነሐሴ ሰኞ 15 ቀን 2009 ዓ.ም. ንግግር ያደረጉት የሰሜን ኮሪያው ኪም፣ ‹‹አሁን የሚደረገው ወታደራዊ ልምምድ ሰሜን ኮሪያን ለመውጋት ቅድመ ዝግጅት ነው፡፡ ለዚህም ምሕረት የለሽ ብቀላ ይኖረናል፤›› ሲሉ አሜሪካ ላይ ዝተዋል፡፡

ሰሜን ኮሪያ በየዓመቱ የሚደረገውን የአሜሪካና የደቡብ ኮሪያ ወታደራዊ ልምምድ ተከትሎ ዛቻ ወይም ለአፀፋ የሚሰየም ሙከራ ማድረጓም የተለመደ ነው፡፡ ሆኖም የአሁኑን ለየት የሚያደርገው፣ የኮሪያ ልሳነ ምድር ሰላሙን ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ሊያጣ በተቃረበበት ወቅት መሆኑ ነው፡፡

በሁለቱ ኮሪያዎች መካከል ያለው ግንኙነት ሁሌም በውጥረት የተሞላ ቢሆንም፣ በተለይ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ትራምፕ ጦርነት ጦርነት የሚሸቱ ንግግሮችን ማድረጋቸውና ከኪም ጋር የቃላት ጦርነት ውስጥ መግባታቸው ችግሩን አግዝፎታል፡፡

ሰሜን ኮሪያ በተለይ በቅርቡ ያስወነጨፈታቸቸው ረዥም ርቀት ተምዘግዛጊ አኅጉር አቋራጭ ባላስቲክ ሚሳይሎች ከማንም በላይ ያስቆጡትም አሜሪካን ነው፡፡ ጃፓን፣ ቻይናና ደቡብ ኮሪያ ጉዳዩን በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ለመፍታት ፍላጎት ሲያሳዩ፣ አሜሪካ ግን ጦርን በጦር ዓይነት ውዝግብ ውስጥ ገብታለች፡፡

 ዴሞክራቶችን ጨምሮ የትራምፕ ጦር ጦር የሚሸት ንግግር ያልጣማቸው አሜሪካውያን፣ አሜሪካ ከሰሜን ኮሪያ ጋር ጦርነት አትገጥምም፣ የሰሜን ኮሪያን መንግሥት የመገልበጥ ዕቅድ የላትም ሲሉም ተሰምተዋል፡፡

ሆኖም ከሰሜን ኮሪያ ሊሰነዘር ይችላል የሚባለውን የሚሳይል ጥቃት ለማክሸፍ የሚያስችል ወታደራዊ ሥርዓት ለመፈተሽ፣ የአሜሪካ የጦር ጄኔራሎች ወደ ደቡብ ኮሪያ መመላለስ ከጀመሩ ሰነባብተዋል፡፡

ሆኖም ሰኞ እንደተጀመረው ‹‹ኡልቺ ፍሪደም ጋርዲያን ድሪልስ›› (Ulchi Freedom Guardian Drills) የተባለው ዓመታዊ የጋራ ወታደራዊ ልምምድ ኪምን ያስቆጣ የለም፡፡

ከሰሜን ኮሪያ የወጣ መግለጫም ልምምዱ ለቁጥር በሚያዳግት ወታደራዊ መሣሪያዎች የታጀበ፣ ሥልጠናውም ‹‹አንገት የመቅላት ዘመቻን›› ያካተተና ዓላማውም ትክክለኛውን የሰሜን ኮሪያ መሪ ኪምን ከሥልጣን የማስወገድ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

‹‹በደቡብ ኮሪያ የተሰባሰበው ከፍተኛ ወታደራዊ ኃይል በኮሪያ ልሳነ ምድር ያለው ውጥረት ጫፍ በነካበት በአሁኑ ወቅት፣ ወደ እውነተኛው ጦርነት ሊገባ አይችልም ብሎ ምስክርነቱን ሊሰጥ የሚችል የለም፡፡ የወራሪዋ አሜሪካ መከላከያ መሪዎችም ደቡብ ኮሪያ የገቡት ለጦርነት ነው፡፡ ይህም በአካቢው ያለውን የጦርነት ሥጋት አጉልቶታል፤›› ሲል መግለጫው ማስፈሩን አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡

በአሜሪካና በደቡብ ኮሪያ መካከል በየዓመቱ የሚደረገው የጋራ ወታደራዊ ልምምድ በሰሜን ኮሪያ በኩል ሁሌም ወቀሳና ዛቻ ቢሰነዘርበትም፣ ከልምምድ ያላለፈ መሆኑን አሜሪካ አስታውቃለች፡፡

አሁን እየተደረገ ባለው ልምምድ 17,500 የአሜሪካ፣ እንዲሁም 50,000 የሰሜን ኮሪያ ወታደሮች እየተሳተፉ መሆኑን፣ በደቡብ ኮሪያና በሴኡል የሚገኘው የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስቴር ወታደራዊ ኮማንድ አስታውቋል፡፡

ሰሜን ኮሪያ ልምምዱ ብዛት ባላቸው ዘመናዊ መሣሪያዎች የታገዘ ነው ብትልም፣ ልምምዱ በኮምፒዩተር ሲሙሌተር ጌም የሚከናወን መሆኑን፣ ምንም ዓይነት የተኩስ ልምምድም ሆን በታንክ ላይ የሚደረግ ወታደራዊ ሥልጠናን እንደማያካትትም አክሏል፡፡ በሥልጠናው የመስክ ላይ ልምምድም የለም ብሏል፡፡

ወታደራዊ ልምምዱ በኮምፒዩተር የታገዘና በባህሪውም ራስን መከላል ላይ ያተኮረ መሆኑም ተነግሯል፡፡ ይኼን ግን ሰሜን ኮሪያ የምትቀበለው አይደለም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ወታደሮች መስክ ላይ በብዛት በመታየታቸው ነው፡፡

የፕሬዚዳንት ትራምፕ ንግግርና ትዊትም በሰሜን ኮሪያ በኩል ያለውን ብሶት የሚያባብስ ነው፡፡ በዚህ ላይ ደግሞ የአሜሪካንና የደቡብ ኮሪያ የጋራ ወታደራዊ ልምምድ ውጤቱን ለመተንበይ ያዳግታል ለሚባለው የሰሜን ኮሪያና የአሜሪካ ጦርነት ውስጥ የመግባት ሥጋት ላይ ጨው የመነስነስ ያህል ነው ሲል፣ የፖለቲካ ተንታኙ የሚያወጣው ዴቪድ ኢንደልማን ተናግሯል፡፡