Skip to main content
x
የኳታር ከባህረ ሰላጤው አገሮች መቆራረጥ

የኳታር ከባህረ ሰላጤው አገሮች መቆራረጥ

ዛሬ በነዳጅ ሀብቷ የበለፀገች ብትሆንም እ.ኤ.አ. ከ1939 በፊት የነበራት የሀብት ደረጃ ደሃ ከሚባሉት አገሮች ያሠልፋት ነበር፡፡ በ1700ዎቹ ለንግድ በሚዘዋወሩ ሰዎች በባህረ ሰላጤው ደሴት ላይ ተመሠረተችው ኳታር፣ አሁን ከባህረ ሳላጤው ሀብታም አገሮች በሀብቷ ከቀዳሚዎቹ ትሠለፋለች፡፡ በተለይ እ.ኤ.አ. በ1939 በአገሪቱ የተገኘው የነዳጅ ክምችት የአገሪቱ የብልፅግና መሠረት ሆኗል፡፡ በጌጣጌጥና በዓሳ ምርት ንግድ ላይ ብቻ ተመሥርታ የነበረችው ኳታር፣ አሁን ግን ዋና የገቢ ምንጯ ነዳጅ ነው፡፡

የኳታር ዋና ከተማ ዶሃ በመስፋፋት ላይ ስትሆን፣ በዓለም ግንባር ቀደም ከሆኑ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች በአጭር ጊዜ ዝናን ያተረፈው አልጄዚራ መቀመጫም ናት፡፡ ይህ በአገሪቱ መንግሥት የሚደገፈው የቴሌቪዥን ጣቢያ፣ የአሜሪካውን ሲኤንኤን እንዲሁም የእንግሊዙን ቢቢሲ የሚገዳደር ከሆነም ሰነባብቷል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2022 የሚካሄደውን የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ለማስተናገድ የታጨችም ናት፡፡ በአፍጋኒስታን የሰላም ስምምነት እንዲደረግ ግንባር ቀደም ሚና የተጫወተች ሲሆን፣ በጋዛ የሚገኘውን ሐማስ እንዲሁም በግብፅና በሶሪያ ያሉትን የአይኤስ ቡድን አባላት ትረዳለች ተብላም ትታማለች፡፡

ሰሞኑን ደግሞ ከሽብርተኞች ጋር ግንኙነት አላት ተብላ ሳዑዲ ዓረቢያ፣ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ እንዲሁም ባህሬን ከአገሪቱ ጋር ያላቸውን ዲፕሎማቲክ ግንኙነት አቋርጠዋል፡፡ ግብፅም ያላትን ግንኙነት ማቋረጧን አሳውቃለች፡፡ በጦርነት አሳሯን የምታየው የመን መንግሥትም ግንኙነትን ማቋረጡን አስታውቋል፡፡

የሳዑዲ ዓረቢያ ዜና አገልግሎት እንዳስታወቀው፣ ሳዑዲ ዓረቢያ ከኳታር ጋር ያላትን ግንኙነት ያቋረጠችው የአገሪቱን ብሔራዊ ደኅንነት ከሽብርና ከጽንፈኝነት ለመከላከል ነው፡፡ ለዚህም ሁለቱን አገሮች የሚያገናኙ ድንበሮች በሙሉ እንዲዘጉ አድርጋለች፡፡ ሳዑዲ ዓረቢያ፣ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ፣ ባህሬን፣ ኦማንና ኳታር የባህረ ሳላጤው አገሮች ትብብር ካውንስል አባላት ሲሆኑ፣ ይህ ጥምረታቸውም በመካከለኛው ምሥራቅ ተፅዕኖ ፈጣሪ በመባል ይታወቃል፡፡

ከጥምረቱ ከኦማንና ከኩዌት በቀር ሁሉም አገሮች ከኳታር ጋር ያላቸውን ግንኙነት ያቋረጡ ሲሆን፣ ለዚህም ምክንያቱ ኳታር ለሽብርተኞች ትረዳለች የሚል ነው፡፡

አገሮቹ ኳታር ሽብርን ትደግፋለች በማለት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን ከማቋረጣቸው ሁለት ሳምንት አስቀድሞ ሳዑዲ ዓረቢያ፣ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ፣ ባህሬንና ግብፅ የኳታር የዜና ምንጮችን አግደው ነበር፡፡ አገሮቹ አልጄዚራን ጨምሮ የኳታር መገናኛ ብዙኃንን ያገዱት የኳታር አሚር ሼክ ታሚም አል ሐማድ አል ታኒ፣ ‹‹ኢራን ለእስልምና የጀርባ አጥንት ናት፤›› በማለት አሜሪካ በቴህራን ላይ ያላትን አሉታዊ ፖሊሲ ኮንነዋል በማለት ነው፡፡

የኳታሩ አሚር በኳታር ዜና አገልግሎት በሰጡት መግለጫ ሪፖርቱ በውሸት የተፈጠረና የተሠራጨበት ጣቢያም በኢንተርኔት ጠላፊዎች ተጠልፎ እንደነበር ቢያሳውቁም፣  ሳዑዲ ዓረቢያና ኢራን የቆሙበት ጽንፍ ለኳታሩ አሚር ማስተባበያ ቦታ አልሰጠም፡፡ ሳዑዲ ዓረቢያና ኢራን በተለያዩ አካባቢያዊ ጉዳዮች ይናቆራሉ፡፡ በተለይ የኢራን የኑክሌር ፕሮግራም ለሳዑዲ ዓረቢያ ራስ ምታት ነው፡፡ የኢራን ኑክሌር መታጠቅ፣ በቀጣናው ያላትን ተፅዕኖም በተለይ በሶሪያ፣ በሊባኖስና በየመን ላይ የሚያሳድረው ጉልህ ተፅዕኖ ለሳዑዲ ዓረቢያ ተግዳሮት ነው፡፡

የካውንስሉ የውጭ ግንኙነት ከፍተኛ ባለሙያ ታዝማች ሌሞን፣ በሳዑዲ ዓረቢያና በኳታር መካከል የተፈጠረው አለመግባባት የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሳዑዲን ጎብኝተው ከሄዱ በኋላ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ሳዑዲ ዓረቢያ ከፕሬዚዳንት ትራምፕ ጉብኝት በኋላ ከአሜሪካ ከፍተኛ ድጋፍ አገኛለሁ የሚል እምነት በማሳደሯ፣ አሜሪካ በኢራን ላይ ያላት ጠንካራ አሉታዊ አቋም አገሮች በኳታር ላይ ላጎረፉት ዱላ የልብ ልብ ሰጥቷል፡፡ የኳታር ዜና አገልግሎት በኢንተርኔት ጠላፊዎች ተጠልፎ  እንደነበር በኳታር አሚር መነገሩም ሌላው ጉዳይ ነው፡፡

የትራምፕ ሳዑዲ ዓረቢያን መጎብኘትና በጉብኝታቸው ጊዜም 55 የሙስሊም አገሮች መሪዎችን ሽብርን ለመዋጋት ጥረታቸውን እንዲያጠናክሩ መጠየቅ፣ ለዚህም አሜሪካ ድጋፍ እንደምታደርግ ማሳወቃቸው፣ የኳታር ዜና አገልግሎት በኢንተርኔት ጠላፊዎች መጠለፉና የኳታሩ አሚር ኢራንን ደግፈው አሜሪካን አጣጥለው መናገራቸው የተፈበረከ ወሬ መሆኑ፣ ይህም ቢሆን ግን የባህረ ሰላጤው ሀብታም አገሮች ከኳታር ጋር ያላቸውን ግንኙነት ማቋረጣቸው ጉዳዩን ውስብስብና ግልጽነት የጎደለው አድርጎታል ተብሏል፡፡

ጉዳዩ ውስብስብ ቢሆንም የኳታር ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መሐመድ ቢን አብዱልራህማን አል ታኒ በኳታር ላይ የመገናኛ ብዙኃን ዘመቻ እንደተከፈተ፣ የአገራቸውን የዜና አውታር ግንኙነት በመዝረፍና የተሳሳተና የተፈበረከ ዜና በአሚሩ ስም በመለጠፍ ኳታርን ከሌሎች አገሮች ያጋጩትን ለፍርድ እንደሚያቀርቡ ተናግረዋል፡፡ ቢቢሲ እንደሚለው፣ በመገናኛ ብዙኃን ተሠራጭቷል የተባለው ዜና ብዙ አነጋጋሪ ጉዳዮችን የያዘ ቢሆንም፣ የሳዑዲ ዓረቢያን ተቀናቃኝ ኢራን ማቆላመጡና የሳዑዲን መንግሥት መንቀፉ ሳዑዲ ዓረቢያን አስቆጥቷል፡፡

‹‹ዓረቦች በኢራን ላይ ካላቸው ጥላቻ ጀርባ ምንም ነገር የለም የእኛ ከእስራኤል ጋር ያለው ግንኙነትም መልካም ነው፤›› የሚለው የአሚሩ ንግግር የቀጣናው አገሮችን አስከፍቷል፡፡ በሌላ በኩል ከኢራን ጋር ግንኙነት አላቸው የሚባሉትን የሒዝቦላህ ታጣቂዎችን በተመለከተ አዎንታዊ ነገር መናገራቸው ኳታርን አስኮንኗል፡፡ ዜጎቿም ከተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ በሁለት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ ለቀው እንዲወጡ የጊዜ ገደብ ተሰጥቷቸዋል፡፡ ለዚህ ሁሉ ምስቅልቅል ምክንያቱ ግን የተፈበረከ ወሬ መሆኑን ኳታር ‹‹ልብ በሉልኝ፤›› ብላለች፡፡  

የሳዑዲ ዓረቢያ መንግሥትም ለአጋር አገሮች፣ ለዓለም አቀፍ ተቋማትና፣ ለትራንስፖርት ድርጅቶች በኳታር ላይ ተመሳሳይ ዕርምጃ እንዲወስዱ እንደሚሠራ አስታውቋል፡፡ ‹‹ኳታር ፀረ ግብፅ አካሄድ ታራምዳለች፤›› በማለትም፣ ግብፅ የኳታርን አካሄድ ከሽብር ለይታ እንደማታየው አሳውቃለች፡፡

ኳታር ከአጋሮቿ ጋር ያጣላትንና ከኳታር ቴሌቪዥን ጣቢያ ተወስዷል ተብሎ በፓን ዓረብ ስካይ ኒውስ፣ በዓረቢያ ቴሌቪዥን፣ በቪዲዮ የተላለፈው አወዛጋቢ ዜና ሐሰት መሆኑን የኳታር መንግሥት ቢያሳውቅም፣ በሳዑዲ ተቀባይነት ሳይገኝ ቀርቶ የየዕለቱ መነጋገሪያና አስተያየት መጉረፊያ ሆኗል፡፡

የባህረ ሰላጤውን አገሮች ያወዛገበውንና 36 ዓመታት ያስቆጠረውን የባህረ ሰላጤው አገሮች ኅብረት አደጋ ላይ የጣለውን ክስተት ለማርገብ፣ የቀጣናው አገሮች ልዩነቶቻቸውን ማጥበብ መወያየት እንዳለባቸው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሬክስ ቴለርሰን ተናግረዋል፡፡

በባህረ ሰላጤው አገሮች መካከል የተፈጠረውን ቀውስ ለመፍታት ዲፕሎማሲያዊ ውይይት ወሳኝ መሆኑን፣ የባህረ ሰላጤው አገሮች የትብብር ካውንስል አባል የሆነችውና ሌሎች አገሮች ኳታር ላይ ገደብ ሲጥሉ ዝምታን የመረጠችው ኩዌትም የአስታራቂ ሚናውን ይዛለች፡፡

በኳታር ላይ በረራን ጨምሮ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶቻቸውን ያቋረጡት አገሮች ዕገዳ ከጣሉበት የኳታሩ አልጄዚራ ጋር ቆይታ ያደረጉት የኩዌት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፣ የኩዌት አሚር ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ በማቅናት ሰላም በሚወርድበት መንገድ ላይ እንደሚመክሩ ተናግረዋል፡፡ የኳታሩ አብዱራህማን አል ታኒም ኳታር ግልጽነትና መተማመን ያለበት ውይይት እንደምትፈልግ ገልጸዋል፡፡

ሳዑዲ ዓረቢያ፣ ባህሬን የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ከኳታር ጋር ያላቸውን የአየር፣ የባህርና የየብስ ትራንስፖርት ማቋረጣቸው ለዓለም አቀፍ በረራዎች እምብርት የሆነችውንና የ1.9 ሚሊዮኖች አገርን ኳታር ረብሿታል፡፡ ሳዑዲ ዓረቢያ በአገሯ የሚገኘውን የኳታር ኤርዌይስ ፈቃድ የሰረዘች ሲሆን፣ ኩባንያውም በ48 ሰዓታት ውስጥ ቢሮውን ለቆ እንዲወጣ አሳስባለች፡፡ ከዶሃ ወደ ተለያዩ አገሮች የሚበሩት ኢትሃድ ኤርዌይስ፣ ኳታር ኤርዌይስና ኤምሬትስ በጉዞ ማዕቀቡ ተመትተዋል፡፡

ከባህረ ሰላጤው አገሮች 11,437 ስኩዌር ካሬ በመሸፈን በትንሽነቷ፣ በነዳጅ ሀብቷና በገቢዋ በሀብታምነቷ የምትታወቀው ኳታር ጌጣጌጥና የነዳጅ ምርት ለውጭ ገበያ ብታቀርብም ምግብን ጨምሮ የተለያዩ መሠረታዊ ፍላጎቷን ምታስገባው ከውጭ ነው፡፡ የየብስ፣ የአየርና፣ የባህር ላይ ጉዞ መታገዱና ሳዑዲ ዓረቢያ ሁሉንም ድንበሯን መዝጋቷ ከሁለት ሚሊዮን ላልዘለሉ ዜጎቿ ራስ ምታት ነው፡፡

ሮይተርስ እንዳሰፈረው፣ የኳታር ዜጎች ለመሰንበቻ የሚሆናቸውን የምግብ ክምችት በመያዝ ላይ ናቸው፡፡