Skip to main content
x
 የዋይት ሐውስ ውጥንቅጥ

የዋይት ሐውስ ውጥንቅጥ

ቀድሞውንም ትችት፣ ወቀሳ፣ ነቀፌታና ተቃውሞ የበዛበት የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር፣ ሰሞኑን ደግሞ አዲስ ውጥንቅጥ ውስጥ ገብቷል፡፡

ሕግ ነክ በሆኑና የአሜሪካን ጥቅም ያስጠብቃሉ በሚባሉ ጉዳዮች በዋይት ሐውስ የእርስ በርስ ጦርነት የተነሳ እስኪመስልም፣ ከሪፐብሊካኑ ሳይቀር በትራምፕ ላይ ነቀፌታ እየተሰነዘረባቸው ነው፡፡

በኮንግረሱ የሚገኙ ከፍተኛ የሪፐብሊካን አባላት ከፕሬዚዳንታቸው ተቃርነው በመቆም፣ ትራምፕ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉን ጄፍ ሴሽንስን ከሥራ አባርራለሁ ማለታቸውንም ተሳልቀውበታል፡፡ በሩሲያ ላይ አዲስ ማዕቀብ ለመጣል የቀረበውን ሐሳብ በማፅደቅም፣ ትራምፕ ከሩሲያ ጋር መፍጠር እፈልጋለሁ የሚሉት መልካም ግንኙነት ላይ አደጋ ጋርጠውበታል፡፡

ትራምፕ ሰሞኑን በትዊተር ገጻቸው የተመሳሳይ ፆታ ግንኙነት የሚያደርጉ ሰዎችን ከውትድርና ተሳትፎ የሚያግዱ መሆናቸውን ማሳወቃቸውም፣ በአሜሪካ ለግብረ ሰዶማውያን ይሁንታ የሰጡ ግዛቶችንም ያነጋገረ ነበር፡፡

በአሜሪካ ወግ አጥባቂው ጸሐፊና ብሮድካስተር ቻርሊ ስኪይስ፣ ያለፈውን ሳምንት ከትራምፕ የሥልጣን ጊዜ ‹‹የከፋ›› ሲል ያስቀምጠዋል፡፡ ‹‹እሳት በማንደድ በሚደሰተው ትራምፕ ምክንያት ዋይት ሐውስ እየቀለጠ ነው፤›› ማለቱንም ዘጋርዲያን ዘግቧል፡፡

የአሜሪካ ሔልዝኬር ሥርዓት መቀየር አለበት ብለው በተለያዩ ጊዜያት ያቀረቧቸው ሐሳቦችም ከአከራካሪነታቸው ባለፈ ይሁንታን አላገኙም፡፡ ሴኔቱም እዚህ ግባ የሚባል ድጋፍ አልሰጠውም፡፡ የሪፐብሊካን ሔልዝኬር ሕግ በሪፐብሊካኑ ካሉ 52 ጠንካራ ቡድኖች የ50 ያህሉን ድጋፍ ማግኘትም አልቻለም፡፡

በምረጡኝ ቅስቀሳ ወቅት በተሰጡ ድምፆች በዴሞክራቷ ሒላሪ ክሊንተን ሲመሩ የነበሩትና ባልተጠበቀ ሁኔታ ሒላሪን አስከንድተው የመራጮችን ቀልብ መሳብ የጀመሩት ትራምፕ፣ ከፕሬዚዳንትነታቸው በኋላ ግን በፓርቲያቸውም ሆነ በሚዲያው፣ በአውሮፓ ኅብረትና በሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች እየተወቀሱና ሐሳባቸውም እየተነቀፈ ነው፡፡ ይህ ደግሞ በዋይት ሐውስም ውጥንቅጥ ፈጥሯል፡፡ ሪፐብሊካኖች ሳይቀሩ ትራምፕን ‹‹ተሳስተሃል›› በማለት በምርጫቸው ሐሳባቸውን እያጣጣሉ ነው፡፡ የትራምፕ አስተዳደር የተለያዩ የአገር ውስጥ ፈተናዎች እየገጠሙት ቢሆንም፣ ትራምፕ የግላቸውን ከመናገርም ሆነ ትዊት ከማድረግ አልተቆጠቡም፡፡

የባለሥልጣናት ሹመትና ሽረትም የትራምፕ መለያ ሆኗል፡፡ ለድስት ወራት ብቻ ያገለገሉትን የዋይት ሐውስ ኃላፊ ሹም ሬንስ ፕሪበስ በሲቪል ማኅበረሰብ ብዙም ልምድ በሌላቸው ጡረተኛና ባለአራት ኮከብ ባህር ኃይል ጆን ኬሊ ተክተዋል፡፡ ትራምፕ ይህንን በትዊታቸው ያሳወቁት ከአሥር ቀናት በፊት የሾሙትና በአሥር ቀኑ ከሥራ ያሰናበቱዋቸው አዲሱ የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አንቶኒ ስካራሙቺ፣ ‹‹ፕሪበስ ለጋዜጠኞች መረጃ ያሾልካል›› ብለው በተናገሩ ማግሥት ነበር፡፡

ፕሪበስ ተሰናብተው ቀናትም ሳይቆይ ስካራሙቺ ከሥራ ተሰናብተዋል፡፡ ሲኤንኤን እንዳሰፈረው፣ ስካራሙቺ ከሥራቸው ለመልቀቅ ምንም ፍላጎት አልነበራቸውም፡፡ ሆኖም አዲስ የተሾሙት የዋይት ሐውስ ጆን ኬሊ ሰኞ ዕለት ሥራ ሲጀምሩ፣ ስካራሙቺ ደግሞ በዕለቱ ከሥራ ተሰናብተዋል፡፡

የዋይት ሐውስ ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተሩ ስካራሙቺ ከሥራ መሰናበት በትራምፕ አስተዳደር ውስጥ አለመግባባት ስለመኖሩ ማሳያ ነው ያለው ሲኤንኤን፣ በቅርቡ በዋይት ሐውስ ከነበሩ ክስተቶችም የከፍተኛ ባለሥልጣን ስንብት መሆኑን ገልጿል፡፡

የዋይት ሐውስ ፕሬስ ሴክሬታሪ ሳራ ሃክቢ ሳንደርስ፣ ‹‹አንቶኒ ስካራሙቺ ከዋይት ሐውስ ኮሙዩኒኬሽንስ ዳይሬክተርነቱ ቢሰናበትም፣ አዲሱ ሹም ኬሊ የራሳቸውን አዲስ ቡድን እንዲያቋቁሙ ዕድል ይሰጣል ብሎ ያምናል፤›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ሆኖም ዘገባዎች የሚያሳዩት ሚስተር ኬሊ በስካራሙቺ ላይ እምነት እንደሌላቸውና እንዲሰናበቱ ይፈልጉ እንደነበር ነው፡፡

መሻርና መሾም ሥራ የሆነባቸው ትራምፕ፣ ሥልጣን ከያዙ ካለፉት ስድስት ወራት ወዲህ ብቻ ስካራሙቺን ጨምሮ ሦስት የዋይት ሐውስ ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተሮች ከሥራ ተሰናብተዋል፡፡

ለሦስት ወራት በሥፍራው ሲሠሩ የቆዩት ማይክ ዱብክ ከለቀቁ በኋላ የቀድሞ የዋይት ሐውስ ፕሬስ ሴክሬታሪ ሾን ስፓይሰር ይዘውት የነበረ ቢሆንም፣ እሳቸውም በመልቀቃቸው አንቶኒ ስካራሙቺ ተተክተው ነበር፡፡ ከእነዚህ በተጨማሪ የዋይት ሐውስ ኃላፊ ፕሬበስ፣ የቀድሞ የዋይት ሐውስ ምክትል ኃላፊ ካቲ ዋልሽና ረዳት ፕሬስ ሴክሬታሪ ማይክል ሾርት ከሥራ ተሰናብተዋል፡፡ ይህም በዋይት ሐውስ ውስጥ ለአንድ ዓላማ ከመቆም ይልቅ መከፋፈሉ እንዳየለ ያሳያል የሚሉት ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች፣ ይህንን ሁሉ ያስከተለው ደግሞ የትራምፕ አስተዳደር ጠንካራ አለመሆንና በግላዊነት የተሸበበ መሆኑ ነው ይላሉ፡፡

ትራምፕ ሥልጣን ከያዙ በኋላ ከስደተኞች፣ ከሜክሲኮ ግንብ፣ ከቀረጥ ነፃ ንግድና ከተለያዩ ጉዳዮች ጋር ተያይዞ ውዝግብ ውስጥ ገብተዋል፡፡ በሌላ በኩል የሰሜን ኮሪያ የኑክሌር ሙከራና ኢራን ሥጋት ሆነዋል፡፡

የአገር ውስጥ ጉዳያቸውን በቅጡ መወጣት ያልቻሉት ትራምፕ ዓለም አቀፍ ጉዳዮችን ለመምራት አቅሙ አይኖራቸውም ተብለው እየተተቹ ነው፡፡ በትራምፕና በአስተዳደሩ መካከል መግባባት እንደሌለ፣ ለዚህ ማሳያውም በዋይት ሐውስ ውስጥ የሚታየው ክፍፍል መሆኑም ይነገራል፡፡ ትራምፕ ብዙዎቹን ባለሥልጣናት የማያምኑና  የማይተማመኑ መሆናቸውም ይነገራል፡፡ ከዋይት ሐውስ መረጃ ይሾልካል፣ ቅሬታም ይቀርባል፡፡ በውስጥ የሚታየው መከፋፈልና አለመተማመንም ትራምፕ አብረዋቸው የሚሠሩትን፣ ሠራተኞችም ከትራምፕ ጋር እንዳይመጋገቡ ማድረጉን ዘ ጋርዲያን አስፍሯል፡፡