Skip to main content
x
የዐውደ ዓመት ድባብ በጋራው መንደር

የዐውደ ዓመት ድባብ በጋራው መንደር

ቤት ተከራይተው የግላቸውን ኑሮ እስከጀመሩበት ጊዜ ድረስ የኖሩት ከወላጆቻቸው ጋር በአጥር ግቢ በሚገኝ ቤት ውስጥ ነበር፡፡ በልጅነትም ሆነ ካደጉ በኋላ ከእህት ወንድም ወይም ከዘመድ አዝማድ ጋር ካላቸው ግንኙነት ባለፈም ከጎረቤቶቻቸው ጋር ያላቸው መስተጋብር እምብዛም አልነበረም፡፡ የወላጆቻቸው ግንኙነትም ከለቀሶ ወይም ከሰርግ የዘለለ አልነበረም፡፡

ምንም እንኳን በየጎረቤቶቻቸው እኩያ ልጆች ቢኖሩም፣ ወጥቶ አብሮ የመጫወቱ፣ በዓል ሲሆን በተለይ ቡሄና እንቁጣጣሽ ሲመጣ ከየቤቱ ተጠራርቶ በየጎረቤቱ እየሄዱ መጨፈሩን ብዙም አላለፉበትም፡፡ በበዓል ወቅት አብዛኛው ግንኙነታቸውም ከቤተሰብ ጋር እዛው ግቢ ውስጥ የተገደበ ነበር፡፡ ‹‹የበፊቱ ሕይወት ንጥል ነበር›› ሲሉም የቀደመ ኑሮዋቸውን ይገልጹታል፡፡

በተሰበጣጠረና ወጥነት በሌለው መንገድ በተገነቡበት የከተማዋ ቤቶች ገሚሱ ችምችም ባሉ ሰፈሮች ሲያድግ አንዳንዱ ደግሞ በፕላን በግል በተሰሩና በአጥር ግቢ በታጠሩ ቤቶች ኖሯል፡፡ በአፓርታማ ላይ ኑሮን የሚገፉም አሉ፡፡ ከየአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር ያለን መስተጋብር እድር በሚባለውና በተለይ ሞት ሲመጣ የሟች ቤተሰቦችን ለመርዳት ታስቦ በተቋቋመው ተቋም በተወሰነ መልኩ መተሳሰር የተፈጠረ ቢሆንም፣ ግቢያቸውን አጥረው በሚኖሩ ማኅበረሰቦች በኩል ያለው ማኅበራዊ ግንኙነት በተለይ ጉርብትና ችምችም ብለውና ተጠጋግተው በሚኖሩ ሠፈሮች እንደሚኖሩ ሰዎች የጎላ አይደለም፡፡ ሆኖም የግል ግቢያቸውን አጥረው ኑሮን ባብዛኛው በግለኝነት በሚመሩ አካባቢዎች በጋራ የሚከበሩ በዓላትን ሲመጡ በየአካባቢያቸው ባሉ ክፍት ቦታዎች ተሰባስበው የሚያሳልፉም አይጠፉም፡፡ በተለይ በማኅበር በተሠሩ ቤቶች አካባቢና ረዥም ዕድሜ ባስቆጠሩ መንደሮች እንዲህ ዓይነቱ መስተጋብር የተለመደ ነው፡፡

ተጠጋግተውና ቤት ለቤት ተያይዘው ባሉ ሠፈሮች ደግሞ በዓል በደረሰ፣ ቡና በሸተተም ሆነ በማንኛውም አጋጣሚ ከጎረቤት ጋር ያለውን መካፈሉ፣ ፀብም ቢመጣ መናቆሩ የጎላ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ችምችም ብለው የተቆረቆሩ መንደሮች በመልሶ ማልማት እየፈረሱና ነዋሪዎችም በኮንዶሚኒየም ቤቶች የሚኖሩበት ሥርዓት መዘርጋቱ ደግሞ በፅዱ አካባቢ ከመኖር አንስቶ አኗኗር ቀይሯል፡፡ ቀድሞ አብረው የነበሩ ሰዎች በተለያዩ ሥፍራዎች በሚገኙ ኮንዶሚኒየሞች ገብተዋል፣ ለመግባት የሚጠባበቁም አሉ፡፡ አዲስ ሕይወትንም በኮንዶሚኒየም መኖር የጀመሩ ጥቂት አይደሉም፡፡

በከተማዋ በተለያዩ አቅጣጫዎች በተሠሩ የጋራ መኖሪያ መንደሮች ዕጣ እየደረሳቸውና እዳቸውን እየከፈሉ የሚኖሩ አሊያም የተከራዩ ሰዎች በተፋፈገና ባረጀ ሰፈር ይኖሩ የነበሩ ብቻ ሳይሆኑ፣ ከቤተሰቦቻቸው ጋር በመሆን በታጠረ ግቢ እንዲሁም በአፓርታማ ይኖሩ የነበሩም ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡

‹‹የበፊቱ ሕይወት ንጥል ነበር›› ያሉን አቶ የምሥራችም፣ በተዘጉ ግቢዎች ውስጥ ካደጉት አንዱ ናቸው፡፡ ዛሬ ላይ ደግሞ ትዳር መስርተውና ልጆች አፍርተው የካ አባዶ የጋራ መኖሪያ መንደር በደረሳቸው ቤት ከ2008 ዓ.ም. መስከረም ጀምሮ መኖር ጀምረዋል፡፡ ኑሮን በዚህኛው መንደር ከመጀመራቸው በፊት ለዓመታት ያህል በኪራይ የቆዩት በአያት ጨፌ ኮንዶሚኒየም ሲሆን፣ በዚህ አካባቢ የበዓል አከባበር የተደራጀና በአካባቢው ያለው ነዋሪ ንቁ ተሳትፎ እንደነበረው ያስታውሳሉ፡፡

የአያቱ ጨፌ ኮንዶሚኒየም ነባር መንደር ስለሆነ ነዋሪዎች በተለይ በጋራ የሚከበሩ በዓላትን አድምቀው የሚያከብሩት ቢሆንም፣ አሁን ባሉበት አዲሱ የየካ አባዶ መንደርም የሚከበሩ በዓላትን በየብሎኩ ያሉ ነዋሪዎች በጋራ እንደሚያከብሩትም ይናገራሉ፡፡

በጋራ ማክበሩ ላይ ከተከራዮች ይልቅ የቤት ባለቤቶች የነቃ ተሳትፎ ያላቸው ሲሆን፣ በዓሉን ለማድመቅም የሚውሉትን ቡና፣ ስጋ፣ ዳቦና ሌሎችንም ለሟሟላት አቅሙ ያላቸው ገንዘብ ያዋጣሉ፡፡ በዓሉን አክብረው ሲጨርሱም ለሚቀጥለው ዓመት በዓል በሰላም ካደረሰን ይኼን እናደርጋለን ተባብለው ቃል የሚገቡ ነዋሪዎች እንዳሉም ያክላሉ፡፡

እሳቸው ባሉበት መንደር በአንድ ብሎክ 25 ቤቶች ሲኖሩ የልጆች ጭፈራ ያለበት በዓል ሲሆን፣ የብሎኩ ሕፃናት እዛው ሕንፃቸው ላይ ያሉ ቤቶች በመሄድ በዓሉን በጭፈራ ያደምቃሉ፡፡ እንደ አቶ የምሥራች፣ ይህ ወላጆች ቀድመው ያላሰቡበትን ማታ ላይ ወጥቶ በዓሉን የማክበር ሁኔታ ይቀይረዋል፡፡ ወላጆች የልጆችን ጨዋታ ሲያዩ ከየቤታቸው በመውጣት በዓሉን በአንዴ ያደምቁታልም ይላሉ፡፡

ኢምፔሪያል አካባቢ አዲስ እየተገነባ ካለው ስታዲየም በላይ ካሉ የኮንዶሚኒየም ቤቶች 24  ኮንዶሚኒየም አንዱ ነው፡፡ በዚህ መንደር ቤት ተከራየተው ላለፉት አምስት ዓመታት ያሳለፉት አቶ ታምራት፣ ትዳር ይዘው ከወላጆቻቸው ቤት ከመውጣታቸው በፊት በቤተሰቦቻቸው ቤት የነበረውን የቡሄና የዘመን መለወጫ እንዲሁም የመስቀል በዓል አከባበር ያደንቁታል፣ ከአእምሮዋቸውም አይጠፋም፡፡

‹‹መገናኛ እግዚአብሔር አብ ቤተ ክርስቲያን አካባቢ የሚገኘው የወላጆቼ ቤት የግልና አጥር ጊቢ ውስጥ ቢሆንም፣ በጋራ የሚከበሩ በዓላት ሲኖሩና ችቦ የሚለኮስ ከሆነ በሰፈሩ ያሉ 22 የግል ቤት ባለቤቶች አንድ ላይ ችቦ ይለኩሱ ነበር፤›› ይላሉ፡፡ ለዚህም ከልጆቹ ይልቅ ወላጆች የጎላ ተሳትፎ ነበራቸው፡፡ ገንዘብ አዋጥተውና ችቦ ተክለው ከልጆቻቸው ጋር በጋራ ችቦ ወደተሠራበት የአካባቢው ክፍት ቦታ በመሄድ በጋራ ያከብሩም ነበር፡፡

‹‹ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ ይኼንን አጥቼዋለሁ›› የሚሉት አቶ ታምራት፣ በሚኖሩበት ኮንዶሚኒየም ግቢ ውስጥ ከወላጆች ይልቅ ሕፃናት በዓል በጋራ ለማክበር ያላቸው ጉጉት የተለየ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡

በየቤቱ እያንኳኩ ለበዓል ማክበሪያ ገንዘብ በመጠየቅ በዓሉን ለማድመቅ ቀዳሚ ፍላጎት የሚያሳዩት ሕፃናት ሲሆኑ፣ ማታ ላይ ለሚከበረው በዓል የሚወጡ ወላጆችም ጥቂት ናቸው፡፡ ‹‹ምናልባት ብዙዎቻችን ተከራዮች ስለሆንን ይሆናል ብዙ ሰው ከፍልሰታ ፆም ጀምሮ አስከመስቀል የሚከበሩ ችቦ የሚለኮስባቸው በዓላትን ለማክበር ሲወጣ አላይም፤›› ይላሉ፡፡

ሆኖም በየዓመቱ ግንቦት አንድ የሚከበረው የልደታ ማርያም በዓል ሲመጣ ከወትሮው በተለየ መልኩ የቤት ባለቤት ሆነ ተከራይ በነቂስ ወጥቶና ገንዘብ አዋጥቶ በዓሉን ያከብራል፡፡ በዚህ በዓል ከመጠጥ ውስኪን ጨምሮ ከምግቡም የበግ ጥብስ፣ ዳቦና ንፍሮው፣ ቡናና ለስላሳው ሁሉ በገፍ የሚቀርብበት፣ ነዋሪውም በጋራ የሚደሰትበት እንደሆነም ይናገራሉ፡፡

መንግሥት የቤት ፈላጊዎችን ችግር ለማቃለል አስቦ ከ10 ዓመታት ወዲህ ተግባራዊ ባደረገው የቁጠባ ኮንዶሚኒየም ቤቶች ግንባታ ከጥራት፣ ከፍሳሽ ማስወገጃ፣ የነዋሪውን የቀደመ ማኅበራዊ ሕይወት ከማፍረስ፣ በለመዱት ቦታ ነግዶ ማደርንና ለትምህርት ቤትም ሆነ ለማንኛውም አገልግሎት ቅርብ መሆንን ያሳጣል በሚል ብዙ ተተችቶበታል፡፡ በተለይ የነዋሪዎች ማኅበራዊ ሕይወት መፍረሱ አጀንዳ ሆኖ ነበር፡፡ ሆኖም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች በሚኖሩባቸው ኮንዶሚኒየሞች ኑሮ መልሶ በማኅበራዊ ትስስር መጠናከር ጀምሯል፡፡ በተለይ በጋራ የሚከበሩ በዓላት ሲመጡ የጋራ መኖሪያ መንደሮች በተለይ ሲደምቁ ይስተዋላሉ፡፡ በጀሞ ኮንዶሚኒየም ያገኘናቸው እናት ያሉትም፣ አብዛኛዎቹ ከተለያየ ስፍራ መጥተው የገቡ ቢሆንም፣ ማኅበራዊ ሕይወታቸው ቀስ በቀስ እየተሳሰረ መምጣቱን ነው፡፡

ጀሞ አካባቢ የሚኖሩት መምህርት አዜብ ጌታቸው በስፍራው ከሁለት ሴት ልጆቻቸው ጋር አብረው መኖር ከጀመሩ ከራርመዋል፡፡ ወ/ሮ አዜብን ያገኘናቸው በአቅራቢያቸው ከሚገኝ አንድ ሱቅ የፍጆታ ዕቃዎችን ገዝተው ወደ ቤታቸው ሲያመሩ ነው፡፡

በጋራ መኖሪያ ቤት አካባቢ የበዓል አከባበር እንዴት ነው? ብለን ጠይቀናቸው፣ ‹‹ጥሩ ነው ድሮ በተለይ መንፈሳዊ በዓላት በመጡ ቁጥር ሁላችንም አጥር ግቢያችንን ዘግተን ለየብቻ እናከብር የነበረው ዛሬ እንደ አንድ ቤተሰብ በጋራ ማክበር ጀምረናል፤›› ብለዋል፡፡

በጋራ ችቦ እንደሚያበሩና ዓመታዊውን የግንቦት ልደታን በዓል በጋራ እንደሚያከብሩ፣ ይህ ዓይነቱም ሁኔታ ይበልጥ እንዳቀራረባቸው፣ በመካከላቸውም የመፈቃቀርና የመረዳዳት ስሜት እንዳዳበረላቸው ወ/ሮ አዜብ ይናገራሉ፡፡

የዘመን መለወጫንና የመስቀል በዓላትን በሕብረት ለማክበር የግልና የጋራ ዝግጅት እንዳደረጉ፣ በቡድን በቡድን ተደራጅተው ሰንጋቸውን ገዝተው ሥጋ እንደሚቀራጩም ነግረውናል፡፡

ይኼም ሆኖ ግን በተለይ በበዓላት ወቅት ሙዚቃ በኃይል የሚለቁ፣ በስካር መንፈስ ፀጥታ የሚያውኩ፣ መወጣጫ ደረጃዎች ላይ ደረቅ ቆሻሻ የሚጥሉ አሉ፡፡  በዚህም የተነሳ የእድርና የተለያዩ ኮሚቴዎችን በማቋቋም የተጠቀሱትን ችግሮች ለማስተካከል ጥረት እንደሚደረግ ወ/ሮ አዜብ ያስረዳሉ፡፡ በጋራ ኮንዶሚኒየም ቤቶች ሊያጋጥሙ ይችላሉ የተባሉ ሥጋቶችን ለመቅረፍም በአብዛኞቹ ኮንዶሚኒየሞች ከነዋሪው የተውጣጣ ኮሚቴ ያላቸው ሲሆን፣ ይኼ ኮሚቴ በበዓላት ወቅት ማኅበረሰቡ በጋራ እንዲያከብርም የበኩሉን ሚና ይጫወታል፡፡ ከዚህ ባለፈ ከግንባታና ከሌሎች ጉዳዮች ጋር የተያያዙ ችግሮችን ለመፍታትም ይንቀሳቀሳል፡፡

(ለዚህ ዘገባ ታደሰ ገብረማሪያም አስተዋጽኦ አድርጓል)