Skip to main content
x

የገበያ ሥርዓቱ ዝብርቅርቅነትና አወዛጋቢው የቀን ገቢ ግምት

ስለአገራችን የግብይት ሥርዓት ስናወሳ መልካም ነገር ለመናገር የማንችልበት እጅግ በርካታ ተጨባጭ እውነታዎችን መዘርዘር እንችላለን፡፡ የግብይት ሥርዓቱ ጤናማ ስላለመሆኑ የሚያሳዩ በርካታ ነጥቦችንና ድርጊቶችን በዚህ ዓምድ ላይ በመጠኑም ቢሆን ለማሳየት ተሞክሯል፡፡ ለአብነት ያህልም ከልክ በላይ የትርፍ ህዳግ ይዞ መሸጥ፣ ምርትን ሸሽጎ አርቴፊሻል ዋጋ መትከል፣ ጊዜ ያለፈባቸው ምርቶችን ያለ ይሉኝታ መሸጥ፣ ምግብ ነክ ምርቶችን ከባዕድ ነገሮች ጋር ደባልቆ መሸጥ በየጊዜው ስናነሳና ስንጥላቸው የነበሩ ጉዳዮች ናቸው፡፡

አንድን አጋጣሚ ተንተርሶ በአንድ ሌሊት ያልታሰበ ዋጋ ጭማሪ ተደርጎ የሸማቾችን ቆሽት ያቃጠሉ በርካታ አጋጣሚዎችን አሳልፈናል፡፡ አሁንም በዚህ ችግር ውስጥ ሆነን እየኖርን ነው፡፡ በአንድ ሊትር ናፍጣ ላይ 25 ሳንቲም ጭማሪ ስለመደረጉ በተገለጸ በቅጽበት፣ የአንድ እንቁላል ዋጋ 50 ሳንቲም ጨምሮ ሲሸጥ የአገራችን የግብይት ሥርዓት ምን ደረጃ ላይ እንደሆነ ያሳየናል፡፡

በየወሩ የነዳጅ ዋጋ ማስተካከያ እንደሚደረግ ይታወቃልና የነዳጅ ዋጋ ይጨምራል በሚል የነዳጅ ማጠራቀሚያቸውን ከርችመው ነዳጅ የለም በማለት የሚፈጠረው ትርምስምስ ያለ ሁኔታ የግብይት ሥርዓታችን መጓደል ሌላ ማሳያ ነው፡፡ ነገር ግን እንዲህ ያለውን ተግባር ለማረም ይኼ ነው የሚባል ዕርምጃ ባለመወሰዱ ችግሩ አሁንም ሲያጋጥም እናያለን፡፡ ይህም በነዳጅ የለም ሰበብ የተፈጠረውን የትራንስፖርት አገልግሎት መስተጓጎል እናስታውሳለን፡፡ ይህም የግብይት ሥርዓታችን ጭፍግግ ገጽታ ነው፡፡

በምሕንድስና ከተቀመጠላቸው ደረጃ በታች ግንባታዎች ሲካሄዱ መመልከትም ቢሆን የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ የንግድ ኅብረተሰቡ ላይ ይታያል ከሚባለው ችግር ባለፈ በመንግሥት በኩል የሚታዩ ክፍተቶችም አሉ፡፡ የግብይት ሥርዓታችን ሌላው አደገኛው ጉዳይ ፍትሐዊ የሆነ ገበያ እንዳይኖር አንዳንዶች ምርቶቻቸውን እንዲሸጡ የሚደረግበት መንገድ የተዘበራረቀ መሆን ነው፡፡ በተመሳሳይ ሥራ ላይ ያሉ የንግድ ድርጅቶች የተጨማሪ እሴት ታክስ አክለው ሲሸጡ፣ አንዳንዶች ደግሞ ከዚህ ውጭ ሲሠሩ መታየታቸው ፍትሐዊ የሆነ የግብይት ሥርዓት እንዳይኖር ማድረጉንም መዘንጋት የለብንም፡፡

በግብይት ሥርዓቱ ውስጥ ሊነሱ የሚችሉ ሌሎች በርካታ ነገሮች እንደተጠበቁ ሆነው ለምሳሌ ከነዋሪው ይልቅ ተከራይ እንደሚበዛበት በሚገመትበት አዲስ አበባ ውስጥ ስንቱ አከራይ ግብር እንድሚከፍል ባይታወቅም፣ የተጋነነ ዋጋ የሚጠየቅበት የቤት ኪራይ የገበያ ዋጋ ስለመሆኑ አረጋግጦ ፍትሐዊ እንዲሆን አለመደረጉም ቢሆን ሌላው የግብይቱ ሥርዓቱ ዝብርቅርቅነት ማሳያ ነው፡፡ ብዙዎች ታክስ ከፍለው ያገኙትን ገንዘብ ታክስ ለማይከፍሉ አከራዮች መስጠታቸው በራሱ፣ ያልተፈለገ የዋጋ ዕድገት እንዲኖር ያደርጋል፡፡ መንግሥትም ከአራዮች መሰብሰብ ያለበትን ግብር እንዳያገኝ ያደርገዋል፡፡

ሌላው ቀርቶ ዛሬ ለአንድ ወር በመቶ ሺሕ ብር ወርኃዊ ክፍያ እየተከፈለባቸው ነው ከሚባሉ የከተማችን ቪላዎች ውስጥ፣ ከምን ያህሉ ግብር ተሰብስቦ ይሆን? ይህም ሌላው ጉዳይ ነው፡፡

ይህም የግብይት ሥርዓቱ እንዲዛባ ከማድረጉም በላይ፣ በዚህ ክፍተት ሕገወጥ ግብይቶች እንዲፈጸሙና ሕግን የተከተሉ አሠራሮች እንዳይጎለብቱ ምክንያት ሆኗል፡፡ የሕጋዊ ንግድ መስፋፋት ጠቃሚ መሆኑ ባይጠረጠርም፣ ሕገወጥ ንግድ እንዳይስፋፋ ዕርምጃ ባለመወሰዱና መፍትሔ ሳይበጅለትም በመቆየቱ እንዲሁም መፍትሔው ሁሌም እሳት ማጥፋት ላይ ብቻ በማተኮሩ፣ ያለንግድ ፈቃድ የሚደረጉ ግብይቶች ቁጥር እንዲጨምር ምክንያት መሆኑ መዘንጋት የለበትም፡፡ ያለ ንግድ ፈቃድ በየመንገዱ የሚነግድ ላይ ዕርምጃ ባለመወሰዱና ሕጋዊ ነጋዴው ተጎድቻለሁ ሲል አጥጋቢ መልስ በመስጠት ባለመቻሉ፣ በሕግ የሚሠራውም ሕገወጥነትን እንዲከተል መንገድ ሊከፍት መቻሉ ግንዛቤ የተወሰደበት አይመስልም፡፡

እንዲህ ባሉና በሌሎች በተለያዩ ችግሮች የተተበተበው የግብይት ሥርዓት  በግድም ይሁን በውድ ግብር ያስከፍላል፡፡ ከገንዘብ ሽክርክሪቱ አንፃር አሁን በዓመት ለመንግሥት የሚከፈለው ግብር ኢምንት ነው፡፡ ምናልባትም በሚሊዮን የሚቆጠር ግብር መክፈል ያለበት ‹‹ነጋዴ›› በግብር ሥርዓት ውስጥ አለመግባቱም የግብር አሰባሰቡ በመጠን ደረጃ ዝቅተኛ አድርጎታል፡፡ አብዛኛው ግብር መክፈል ያለበትን ዜጋ ወደ ሥርዓቱ ማስገባትም ሳይቻል ቆይቷል፡፡ ግብር በጥቂቶቹ ላይ ያነጣጠረ ነው፡፡ ስለዚህ የግብይት ሥርዓቱ እንዲጎለብትና ከታች ጀምሮ ግብር የመክፈል ባህል እንዲጎለብት ባለመሠራቱ፣ ከገቢ ግምት ጋር ለተነሳው ሰሞናዊ ጡዘት አንድ ምክንያት ነው ማለት ይቻላል፡፡ ዛሬ ሰምተን የማናውቀው ግብር ሊጭንብን ነው ብለው አደባባይ የወጡት የንግዱ ኅብረተሰብ አባላት፣ ከመንግሥት ጋር የተፋጠጡበት ዋነኛ ምክንያት ነጋዴው ግብሩ ስለበዛበት ብቻ ሳይሆን ቀድመው ሊሠሩ የሚገባችው ሥራዎች ባለመሠራታቸው ጭምር ነው፡፡ የተበላሸው የግብይት ሥርዓታችን ውጤት ነውም ማለት ይቻላል፡፡

ግብር የዜግነት ግዴታ የመሆኑን ያህል ይህንን ግዴታውን በአግባቡ ሊወጣ የሚያስችልና የተስተካከለ የግብይት ሥርዓት እንዲኖር አልተደረገም፡፡ ሕጋዊ አሠራሮችን እንዲከተል ከሥር ኮትኩቶ አለማሳደጉና በደቂቃ የመክበር ባህልን የሚኮንን አሠራር ባለመስረፁ፣ በትክክል የተገመተለትም ሆነ ያላግባብ ግብር ሊመጣብኝ ነው ያለው ሆ ብሎ ድምፁን ሊያሰማ ችሏል፡፡

ግብር ለመገመት የተደረገውን ብርቱ ትግል ያህል ዜጎች ግብር መክፈል እንዳለባቸው ግንዛቤ ባለመሰጠቱ፣ ሌላው ቀርቶ የግብር ሥርዓትን በአግባቡ ያለመናገር ችግር እንዳስከተለ መገንዘብ ይቻላል፡፡ ወትሮም ቢሆን ችግር ያለበት የግብይት ሥርዓት ያልታሰበ ግብር ሲመጣ መደንበሩ አይቀርም፡፡ ምንም ግንዛቤ ሳይኖረው ይህን አምጣ ሲባል ትክክለኛውም ወስላታውም ለምን? ብሎ ቢነሳ የማይገርመው ለዚህ ነው፡፡ ደግሞ ከሰሞኑ መገንዘብ እንደተቻለው ጥቂት የማይባሉ የቀን  ገቢ ግምቶች ፈጽሞ አሳማኝ ያልሆኑና የተጋነኑ መሆናቸው ነው፡፡

በአግባቡ እስከሆነ ድረስ ግብር ግድ ነው፡፡ ማንም ነጋዴ እስካተረፈ ግብር መክፈል እንዳለበት የሚታወቅ ነው፡፡ ይህንን ያህል ግብር አምጣ ከማለት በፊት፣ ንግዱን የሚበርዙ አካሄዶችን በማስተካከልና ከፋዩም ለምን ይህንን ያህል እንደመጣበት ማስረዳት ጠቃሚ ነው፡፡

ስለዚህ አሁንም ግብር አስከፋዩ መሥሪያ ቤት በትዕግሥት ሁኔታውን መመልከትና ጥያቄዎቹንም ተቀብሎ በአግባቡ ማስተናገድ አለበት፡፡ ያላግባብ ተጫነብኝ የሚለውን መለየትና አወንታዊ ምላሽ መስጠት ተገቢ ነው፡፡ ከሰሞኑ የግምት አሰጣጥ እንደታዘብነው የአዞ እንባ የሚያፈስ እንዳለ ሁሉ፣ ያላግባብ የተገመተበት መኖሩ ግልጽ ነው፡፡ ለምሳሌ አምስት አልጋ ያለው ድርጅት አንዱን አልጋ 200 ብር እያከራየ ይሠራል፡፡ 1,800 ብር የቀን ገቢ አለው ቢባል፣ የአገማመት ሥልቱ እንዴት ቢሆን ነው? ያስብላል፡፡

እስካሁን የተፈጠረውን ትኩሳት ለማብረድ መንግሥት የራሱ የሆነ የቤት ሥራ አለበት ማለት ነው፡፡ የንግዱ ኅብረተሰብም ቢሆን በትክክል በመሥራት ገቢና ወጪውን በማስላት የነጠረ መረጃ ይዞ ሊቀርብ ይገባል፡፡

ሌላው የግብር ሥርዓት በመንግሥት ተገዶ የሚከፈል ያለመሆኑንና በትርፍ ልክ የሚሰላ ስለመሆኑ በአግባቡ ማስተማርም ያስፈልጋል፡፡ ዜጎች ከሥር ጀምሮ የግብር ባህል እንዲያዳብሩ ማድረግ እስካልተቻለ ድረስ፣ አሁንም መተማኑ ስለማይኖር በሰሞኑ ችግር የባሰ ግብይቱ እንዳይበላሽ ሁሉም በጊዜ እስካልመከሩ ድረስ ጉዳቱ የሁላችንም ይሆናል፡፡  

ባለሥልጣኑ በቡድን የሚቀርብ ቅሬታ አልቀበልም ብሏል፡፡ አብዛኛው ነጋዴ ግምቱ ላይ ቅሬታ አለኝ እያለ ስለሆነ፣ ይህንን ለማስተናገድ አቅምን ማዳበር ይጠበቅበታል፡፡ ያልተገባ ግምት ተገመተብኝ ብሎ ቅሬታ ያቀረበ ሁሉ ትክክል ነው ማለት ባይቻልም፣ ባለሥልጣኑ የዕለት ግምት ለመሰብሰብ ከወሰደበት ጊዜ በላይ ሊወስድበት የሚችል ሥራ ሊጠብቀው ስለሚችል፣ ሁኔታውን በአግባቡ ለማስተናገድ የሚችልበትን አሠራር መዘርጋት አለበት፡፡

ከጥያቄው ብዛት አንፃር እያንዳንዱ ጉዳይ በአግባቡ ለመመለስ ኃላፊነት አለበት፡፡ አሁንም ቢሆን ግን ጥያቄ እናስተናግዳለን ማለት ብቻ ሳይሆን፣ የቀን ገቢ ግምት ሥሌቱን ማስረዳትና ለከርሞም ችግር እንዳይኖር ማድረግም ያሻል፡፡

የቀን ተመኑ አሁን ያለውን የአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ከግንዛቤ ያስገባ መሆን ይኖርበታል፡፡ ለምሳሌ በወር ውስጥ አሥርና 15 ቀናት በመሥራት የሚስተጓጎልበት ድርጅት እንዲህ ባለው ምክንያት የማይሠራበት ጊዜ ታስቦለት ነው ወይ? የሚል ጥያቄ ስለሚነሳ፣ የንግዱን ኅብረተሰብ ጥያቄ ከሁሉም ማዕዘን ማየት ያስፈልጋል፡፡ ጥሩ ግብር ከፋይ ዜጋ ለመፍጠር ከተፈለገ እንደ አሁኑ ዱብ ዕዳ በመጣል ሳይሆን ከሥር ሁኔታውን በማስረዳትና በመተማመን ላይ በተመሠረተ መንገድ ቢሆን ይመረጣል፡፡