Skip to main content
x

የግብፅ 'ተውሪታዊ' ታክቲኮች በአፍሪካ ቀንድና በባህረ ሰላጤው አካባቢ

በሚካኤል ምናሴ

አርዕስቱን እንዳነበባችሁ በአማርኛ ያልተለመደ አንድ ቃል ታያላችሁ፡፡ በእርግጥ ስላልተለመደም ሳይሆን ከናካቴው አማርኛ ስላልሆነ ነው፡፡ ‘ተውሪት’ የዓረቢኛ ቃል ሲሆን፣ ፖለቲካዊ ትርጉሙም አንድ ሰው/አካል በሌላ ሦስተኛ ሰው/አካል ላይ ጥቃት እንዲያደርስ በመገፋፋት፣ የራስን ጥቅም የሚያስከብር ፖለቲካዊ ክስተትን መፍጠር ማለት ነው፡፡ ግብፅ በዚህ ታክቲክ የተካነች አገር ናት፡፡ በቅርቡ የተከናወኑ ወቅታዊ ሁኔታዎችን ልብ ብለው የሚከታተሉ ሁሉ፣ በባህረ ሰላጤውና በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ የግብፅ ‘ተውሪታዊ’ አሻራን ማየት ይችላሉ፡፡ በፕሬዚዳንት አልሲሲ የሚመራው መንግሥት ኳታርን ለፅንፈኛው የግብፅ ሙስሊም ብራዘርሁድ በአገሯ ከለላ በመስጠት፣ የእስላማዊ መንግሥት (IS) ርዕዮትን በማስፋፋትና በግብፅ የውስጥ ጉዳይ በመግባት ሲከስ ከቆየ በኋላ የሳውዲ ዓረቢያ፣ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶችና የባህሬን እግር ተከትሎ ከኳታር የነበረውን የሻከረ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አቋርጧል፡፡

ሦስቱም አገሮች በአየርና በባህር ከኳታር የነበራቸውን የንግድ ግንኙነትም አስቁመዋል፡፡ ከዚህም አልፎ ግብፅ በኳታር ቁስል ላይ እንጨት ለመስደድ የተለያዩ አገሮች መንግሥታት ይኼንን አቋም እንዲደግፉ ደጅ ስትጠና ነበር፡፡ የኤርትራ መንግሥት ይህንን የግብፅ ተውሪታዊ ታክቲክ አስተናግዳ የረዥም ግዜ ወዳጁና ደጋፊው የሆነችውን ኳታርን አስከፍቶ “ውጣ አትበለው ግን እንደሚወጣ አድርገው” እንደሚባለው፣ ኤርትራንና ጂቡቲን ከሚያጨቃጭቀው የዱሜራ ተራራና የዱሜራ ደሴት ጦሯን እንድታስወጣ ገፋፍቷታል፡፡ የኤርትራ መንግሥት በበኩሉ በተፈጠረው ክፍተት ኃይሉን በማስገባት የኢትዮጵያ የቅርብ ወዳጅና የባህር በር የሆነችውን ጂቡቲን በመንካት በኢትዮጵያም ላይ ያነጣጠረ የራሱን ‘ተውሪት’ ተለማምዷል፡፡ ሲደመር ለግብፅ በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ ይሆናል፡፡ የሚገርመው ነገር ግን በባህረ ሰላጤው ቀውስ ላይ ከኤርትራ ጋር ተመሳሳይ አቋም የያዘችው ጂቡቲ ተውሪቱ ያስከተለው ውጤት ሰለባ መሆኗ ነው፡፡ ይህ ውጤት በውክልናም አይገኝም፡፡    

በናይል ወንዝ ጉዳይ ከኢትዮጵያ ጋር ባላት ቁርሾ ምክንያት ግብፅ በአፍሪካ ቀንድ ያሉትን አንዳንድ አገሮች የኢትዮጵያን ወይም የቀጣናውን የጋራ ጥቅም የሚፃረሩ ዕርምጃዎችን እንዲወስዱ አደፋፍራለች፡፡ ኢትዮጵያ በሱዳንና በደቡብ ሱዳን መካከል የነበረው ግጭት እንዲረግብ የኢጋድን የአደራዳሪነት ሚናን በመምራትና የሰላም አስከባሪ ጦሯን ሁለቱንም አገሮች በሚያጨቃጭቀው የአቢዬ ግዛት በማሥፈር፣ እንዲሁም በደቡብ ሱዳን ተፋላሚ ወገኖች መካከል የሰላም ስምምነት እንዲደረስ ቁልፍ አስተዋጽኦ አድርጋለች፡፡ ነገር ግን ደቡብ ሱዳን በናይል ወንዝ አጠቃቀም ላይ የተነደፈው የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት (CFA) በመፈረም ረገድ እግሯን እንድትጎትት፣ ግብፅ የተለያዩ መደለያዎችን በመጠቀም ጫና እየፈጠረችባት እንደሆነ የሚያሳዩ ምልክቶች አሉ፡፡ የናይል ውኃን አትንኩብኝ የሚለውን የግብፅ አቋም በፅኑ ሲቃወሙና ሲያብጠለጥሉ የነበሩት የኡጋንዳው ዮዌሪ ሙሴቪኒ ደግሞ ግብፅ ውስጥ ለውስጥ በሠራችው ሥራ የመለሳለስ አዝማሚያ ይዘዋል፡፡

የሱዳን መንግሥት ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ እየገነባችው ላለው ታላቁ የህዳሴ ግድብ ድጋፍ በመስጠቱ የተቀየመችው ግብፅ፣ ሁለቱን አገሮች በሚያወዛግበው የሙሰላስ ሐላይብ ላይ ትንኮሳዎችን በመፈጸምና የደቡብ ሱዳን መንግሥትን በማስታጠቅ፣ ከሱዳንና ሱዳን ትደግፋቸዋለች ከሚባሉ የሳልቫ ኪርን መንግሥት  የሚቃወሙ ኃይሎች ላይ ያነጣጠረ ተውሪት ሥራ ላይ እያዋለች ነው፡፡

በሶማሊያ ሁሉን አቀፍ የሰላም ስምምነት እንዲደርስ ለረዥም ዓመታት ያላሰለሰ ጥረት ስታደርግ የቆየችው ኢትዮጵያ ወደዚህ ግብ በተጠጋች ቁጥር፣ ግብፅ በትይዩ/አማራጭ የሰላም ጥረት ስም ሒደቱን ወደኋላ የሚመልሱ መድረኮችን ስታዘጋጅና ለተለያዩ ኃይሎች አሉታዊና አድሏዊ ድጋፎችን ስትሰጥ ቆይታለች፡፡

ኢትዮጵያ በውስጧ ፖለቲካዊ መረጋጋትና ልማት ሠፍኖ በአካባቢው ጂኦፖለቲካ ላይ ተፅዕኖ ፈጣሪ መሆኗ የሚያሳስባት ግብፅ፣ ከሕግ ማዕቀፉ ውጪ ለሚንቀሳቀሱት የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ኃይሎች አለሁላችሁ በማለትና የገንዘብና የማቴሪያል ድጋፍ በመስጠት ከ‘ተውሪት’ የሚገኘውን ከደፈረሰ ኩሬ ዓሳ የማጥመድ አባዜዋን የሙጥኝ ብላዋለች፡፡ የግብፅ ዲፕሎማቶች ተውሪትን ብዙ ጊዜ ሲጠቀሙበት የሚታዩት ዘዴው ሊያስከትለው ከሚችለው መዘዝና ተጠያቂነት በማምለጥ የሚያመጣውን ትሩፋት መቋደስ ስለሚያስችላቸው ነው፡፡ የግብፅ ዲፕሎማቶች የተውሪት ተልዕኮ ማወቅ አንድ ነገር ሆኖ፣ ዋናው ጥያቄ ግን የኢትዮጵያ የውጭ ፖሊሲ መሐንዲሶችና ዲፕሎማቶች በዚህ ረገድ ምን እያደረጉ ነው? ምንስ ሊያደርጉ ይገባል? የሚለው ነው፡፡ ከርቀት የማየውን ትዝብት መሠረት በማድረግ የመሰሉኝን እንደሚከተለው ለማስቀመጥ ሞክሬያለሁ፡፡

ተውሪትን አስቀድሞ ማምከን 

በቅድሚያ የኢትዮጵያ የውጭ ፖሊሲ መሐንዲሶችና ዲፕሎማቶች በቅርብም በሩቅም ያሉ የኢትዮጵያ ወዳጅ አገሮች፣ አካላትና ግለሰቦች ለግብፅ ተውሪት ተጋላጭ እንዳይሆኑ ለማገዝ የራሳቸው የቤት ሥራ መሥራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይህም በወሳኝነት ማድረግ የሚቻለው ከእነዚህ አገሮች ጋር ያሉንን የግንኙነት ገመዶች በማብዛትና በማወፈር ነው፡፡ በዚህ መንገድ አንድም የትስስር ገመዶቹ በተውሪት ፍላፃዎች በቀላሉ እንዳይበጣጠሱ፣ አሊያም ተጨባጭ ዘላቂ ጥቅሞቻቸው ግብፅ ለምትዘረጋው መደለያ ግብር እንዳይሆኑ ማድረግ ይቻላል፡፡ በአሁኑ ወቅት ከጂቡቲና ከኬንያ ጋር በተጨባጭ ዘላቂ ጥቅም ላይ የተመሠረተ አስተማማኝ ግንኙነት ስላለን ነው፣ ግብፅ እነዚህን አገሮች ለተውሪት ዘይቤዋ መመልመል የማትችለው፡፡

ከሱዳን ጋር ያለን ዝምድናም በዚህ በጎ አቅጣጫ እየተጓዘ በመሆኑ ነው ግብፅ ሱዳንን ከመደለል ወደ ማስፈራራቱ ያዘነበለችው፡፡ ከሌሎች አገሮች ጋር እርስ በርስ የሚያስተሳስሩ ክሮችን የማጠናከሩ ተግባር ከደቡብ ሱዳን፣ ከኡጋንዳና ከሌሎች የኢጋድ አገሮችም ሌት ተቀን ሊሠራበት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ የደቡብ ሱዳንን የሰላም ሒደት ለማንሠራራት እየጣርኩኝ ነው የሚለው ኢጋድ፣ ‹በአንድ ራስ ብዙ ምላስ› ሆኖ የአካባቢው ግጭቶችን የመፍታት አቅሙ ስለተመናመነ በቅድሚያ ራሱን አድሶ ለውጭ ተፅዕኖ የማይንበረከክ፣ ለቀጣናው ሰላም፣ ዕድገትና ኢኮኖሚያዊ ትስስር በሙሉ ልብና ጉልበት የሚሠራ አካል እንዲሆን ኢትዮጵያ የመሪነት ሚና መጫወት አለባት፡፡

የራስን ቤት በሥርዓት ማሰናዳት

ከዚህ የመከላከል ሥልት የሚዛመድ ሌላው ነጥብ የራሳችን የውስጥ ችግር ለተውሪታዊ ጥቃት ተጋላጭ እንዳያደርገን መጠንቀቅ ነው፡፡ ለዚህ ቁልፉ ደግሞ ሕዝቡን በምልዓት የሚያሳትፉ አዎንታዊ ምኅዳሮችን (ሰላም፣ ዴሞክራሲ፣ እኩልነት፣ ፍትሕ፣ ነፃነት፣ መልካም አስተዳደር፣ ግልጽነትና ተጠያቂነት) የማስፈን ሒደት ላይ በቀጣይነት መረባረብ የግድ ነው፡፡ በዚህ ሒደት ሊንገዋለሉ የሚችሉ በርካቶች ቢሆኑም፣ ለሕዝብ ዘላቂ ተጠቃሚነት ሲባል በቁርጠኝነት ማራመድ ያስፈልጋል፡፡

ብዙ ትልልቅ ኤሊዎች

የኢትዮጵያ የውጭ ፖሊሲ መሐንዲሶችና ዲፕሎማቶች አገራችን ከሌሎች አገሮች ያላት ግንኙነት ብቻ ሳይሆን፣ ከሌሎች አገሮች ጋር ያላቸውን አዎንታዊና አሉታዊ ግንኙነቶች ከእነ ምክንያታቸውና ተለዋዋጭ ባህሪያቸው ማጥናትና በአሁኑ ወቅት ለኢትዮጵያ የሚኖራቸው አንድምታዎች እየፈተሸ የፖሊሲ አቅጣጫዎችን ለመቀየስ የሚረዱ ግብዓቶችን ካለማቋረጥ ማዘጋጀት ይጠበቅባቸዋል፡፡ በአንድ አገር በሚከሰት ሁኔታ ሊደሰት ወይም ሊከፋ፣ ያንን ሊደግፍ ወይም ሊቃወም የሚችል ሌላ አገር፣ ኃይል ወይም ዓለም አቀፍ አካል አለ? ካለስ በምን ደረጃ? መቼና እንዴት ምላሽ ሊሰጥ ይችላል? ለምን? እኛስ ምን ማድረግ እንችላለን? ብሎ መጠየቅና መልስ ይዞ መንቀሳቀስ ያሻል፡፡ ለዚህ ሥራ የሚረዳ ተቋማዊና የዲፕሎማቲክ የሰው ኃይል ብቃት ማዳበር፣ የዲፕሎማሲ ሹመቶች በሌላ መስክ ለተሠራ ሥራ መሸለሚያ ወይም መጣያ ሳይሆን ለቦታው የሚመጥን ፖለቲካዊና ሙያዊ ብቃት ያላቸው ሰዎች የሚመደቡበት መሆን አለበት፡፡

የጥንት ሰዎች ‹መሬት ጠፍጣፋ ናት› ብለው በሚያምኑበት ዘመን መሬትን በጀርባው የተሸከማት አንድ ትልቅ ኤሊ ነው ይሉ ነበር፡፡ “ያንን ትልቅ ኤሊስ ማን ነው የተሸከመው?” ብሎ ለሚጠይቅ መልሳቸው ሌላ ትልቅ ኤሊ እያሉ ማለቂያ የሌላቸው ትልልቅ ኤሊዎች ከመሬት ሥር መኖራቸው ይናገሩ ነበር፡፡ ‹ለጌታም ጌታ አለውና› የኢትዮጵያ ዲፕሎማቶች ከአንድ አገር ጀርባ ያለው አገር/አገሮች እነማን እንደሆኑ ለይተው የሁሉም ጌቶች ፍላጎት፣ ባህርይ፣ ደልዳላና ስስ ብልት በማወቅ ከጎናችን የማይሆኑት ቢያንስ ከባላንጣችን ጎን እንዳይሠለፉ፣ ከእኛ ጎን የሚሆኑት ደግሞ ጥቅሞቻችን የሚፃረሩ ኃይሎች እኛንና ወዳጆቻችንን እንዳያጠቁ ልንጠቀምባቸው የምንችልባቸው ዘዴዎችን ማሰላሰልና አሠላለፎችን ማስተካከል ይገባል፡፡

በዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ አንድ ነገር ከዚህ በፊት ሆኖ ስለማያውቅ ወደፊትም አይሆንም ብሎ ማሰብ ትክክል አይሆንም፡፡ ለፋሲካ የታረደው በግ ከፋሲካ ቀን በፊት ለብዙ ወራት ባለቤቱ በየቀኑ ሲቀልበውና ሲንከባከበው ነበረ፡፡ ከዚያ በፊት ታርዶ አያውቅምና አይታረድም ማለት ግን አይደለም፡፡ እኛ ለሌሎች መልካም መሆንን ሁሌም የምንሻው ቢሆንም እንኳን እንዲያ ስለሆንን ሌሎች ምንግዜም መልካም ይሆኑልናል ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው፡፡ ኤርትራ በ1990 ዓ.ም. የወረረችን መልካም ስላልሆንንላት አልነበረም፡፡

የኢትዮጵያ የውጭ ፖሊሲ ላይ የመወሰን ኃላፊነት ያላቸው ባለሥልጣናትና ዲፕሎማቶች ግብፅ በለመደቻቸው ተውሪታዊ ሥልቶች የምታደራውን ቋጠሮ ውሉን ማግኘትና መፍታት አለባቸው፡፡ ለዚህም ቋጠሮው እንዴት እየተሠራ እንደሆነ ማጤንና ልልና ጠንካራ ቦታዎቹን መለየት ያስፈልጋል፡፡ ያለበለዚያ ቋጠሮው ተወሳስቦ ከተሠራ በኋላ “ይህ ደግሞ ምን ይሉት ቋጠሮ ነው?” እያሉ በመደመም ከማየትና በትብታቡ ከመጠለፍ ውጪ አማራጭ አይኖርም:: አንዱ የአገራችን አንጋፋ ፖለቲከኛ፣ “ግብፆች ሜዳ ላይ አስከሬን እንዳየ ጥንብ አንሳ በዙሪያችን እያንዣበቡ ነው፤” እያለ ሲናገር ሰማሁት ብሎ ወዳጄ የነገረኝ አባባልም፣ ግብፅ በኢትዮጵያ እንዲኖር የምትቋምጥለትን አቅመ ቢስነት ቁልጭ አድርጎ ያሳያል፡፡             

የጎርዲዬስ ቋጠሮ

ከሁሉም የበለጠው ግን በኤርትራ ላይ የተሠራውና የጎርዲዬስን ያህል የተተበተበው ቋጠሮ ነው፡፡ ከክርስቶስ ልደት በፊት በ333 ዓ.ም. ገናናው የመቄዶኒያ መሪ ታላቁ እስክንድር የአሁኗ ቱርክ በምትገኝበት አከባቢ የነበረውን የፍርጂያ ግዛትን ለመውረር በዘመተ ጊዜ፣ የግዛቷ ርዕሰ ከተማ ወደሆነችው ጎርዲዬም ሲጠጋ ጥልፍልፍ ያለ ቋጠሮ በከተማዋ በር ላይ ያገኛል፡፡ ንጉሥ ጎርዲዬስ እንዳሠራው የሚነገርለት ይኼንን ቋጠሮ የፈታ ማንኛውም ሰው የመላው እስያ ገዢ ይሆናል የሚል ትንቢት ነበር፡፡ ግዛቱን የማስፋፋትና መላዋን እስያን የመቆጣጠር ህልም የነበረው ታላቁ እስክንድርም ይኼንን ቋጠሮ እንደምንም ለመፍታት ይፈልጋል፡፡ ብሎ ብሎ ሳይሳካለት ይቀርና ጎራዴውን ከአፎቱ መዞ፣ “ቁም ነገሩ ያለው እንዴት ተፈታ በሚለው ላይ ሳይሆን መፈታቱ ነው፤” በማለት ቋጠሮውን ለሁለት ከፍሎ ግዛቲቷን ከዚያም አልፎ ትንቢቱ እንዳለው መላዋን እስያን ሊቆጣጠር ችሏል፡፡ ለዚህ ታዋቂ አፈ ታሪክ ምሥጋና ይግባውና “የጎርዲዬስ ቋጠሮ”ን መፍታት የሚለው አባባል በአሁኑ ወቅት በዓለም ሥነ ጽሑፍ ውስጥ ገብቶ የተወሳሰበን ችግር በአቋራጭ የመፍታት ፈጠራ የተመላበት ጥበብ የሚል ትርጉም የሚሰጥ አገላለጽ ሆኗል፡፡ ከኤርትራ ጋር በተያያዘ ያለው ችግር ግን የጎርዲዬስን ቋጠሮ በአሌክሳንደር ሥልት ከመፍታት የላቀ ብልኃትና ጥንቃቄን የሚፈልግ፣ መፈታቱ ብቻ ሳይሆን አፈታቱንም ማጤን የሚሻ ጉዳይ ነው፡፡

ኢትዮጵያዊው የታሪክ ምሁር ፕሮፌሰር ገብሩ ታረቀ ኤርትራ በመንግሥቱ ኃይለ ማርያም አንገት ዙርያ የተንጠለጠለ የድንጋይ ወፍጮ ነበረች በማለት፣ ችግሩ የደርግ መንግሥትን መቀመቅ ያወረደ እንደነበር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ካለው አባባል በመዋስ ጽፈዋል፡፡ ነገር ግን ችግሩ የደርግ መንግሥት ብቻ ሳይሆን ከዚያ በፊት የነበረው የአፄ ኃይለ ሥላሴ አገዛዝን ወደ ሞቱ ከወሰዱት ምክንያቶች አንዱ እንደነበር ይታወቃል፡፡ የኤርትራ ችግር አሁኑ በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ራስ ምታት ከሆነም ቆይቷል፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት መንግሥታቱ በኤርትራ የሚከሰቱ ተለዋዋጭ ሁኔታዎችን አንብበው ወቅቱን የጠበቀ ምላሽ ሳይሰጡ በመቅረታቸውና ሁኔታዎቹ ቀድመው ሌላ መልክ እየያዙ በመሄዳቸው ነው፡፡

ይህ አካሄድ የእንግሊዝ መንግሥታት የአየርላንድ ጥያቄን ለመፍታት ከተከተሉዋቸው አካሄዶች በአንዳንድ መልኩ ይመሳሰላል፡፡ ሴላርና ዪትማን የተባሉ ሁለት ጸሐፊዎች በደረሱት የአገረ እንግሊዝ ታሪክ እንግሊዞች የአየርላንድን ጥያቄ ለመመለስ የተቃረቡ በመሰላቸው ቁጥር፣ ጥያቄው ተቀይሮ ያገኙት እንደነበር በመግለጽ የጉዳዩ ውስብስብነት ከእንግሊዛውያን መሪዎች የማሰብ ችሎታ በላይ እንደነበረ አመላክተዋል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት እስካሁን የተከተለው ኤርትራን የማቀብ ፖሊሲም የተፈለገው ውጤት እያስገኘ እንዳልሆነ ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ ስለሆነም ለዚህ እጅግ ተለዋዋጭና ውስብስብ መፍትሔ የሁለቱ አገሮች የወል ተዘክሮ ባለቤቶች የሆኑ ሕዝቦች በተለይም የአገር ሽማግሌዎች፣ ምሁራን፣ ወጣቶች፣ ሴቶች፣ በአጠቃላይ በየደረጃው ያለው ኅብረተሰብ አዲስ ሐሳብ የሚያፈልቁበት ዕድል እንዲኖር መንግሥት ሁኔታዎችን ማመቻቸት ይጠበቅበታል፡፡

ግብፅ ሁሉም የተውሪት መንገዶች ዝግ መሆናቸው ስትረዳ ወደ ትክክለኛውና ቀጥተኛው መስመር ትገባለች፡፡ ሰላማዊውን አማራጭ በመውሰድም ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ጉዳይ በውይይት ለመፍታት ትገደዳለች፡፡ ያኔ ነው ሁለቱም አገሮች የጋራ ጥቅማቸው የሚያረጋግጥ ትብብር ማራመድና ለአካባቢያቸው መረጋጋትና ዕድገት ገንቢ አስተዋጽኦ ማድረግ የሚችሉት፡፡ 

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው ዲስኮርስ በሚባል መጠርያ የሚታተመው በአፍሪቃ ጉዳዮች ላይ ትንታኔ የሚያቀርብ ጆርናል ማኔጂንግ ኤዲተር ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው  [email protected]. ማግኘት ይቻላል፡፡