Skip to main content
x
የጎንደሩ ሳይንስ ማዕከል

የጎንደሩ ሳይንስ ማዕከል

ጎንደር ሳይንስ ማዕከል ከአራት ዓመት በፊት የተቋቋመ ማዕከል ሲሆን፣ በጎንደር ከተማ ከ7ኛ እስከ 12ኛ ክፍል የሚማሩ ተማሪዎችን ያስተናግዳል፡፡ ተማሪዎች በሳይንስ በንድፈ ሐሳብ የተማሩትን በተግባር የሚያጤኑባቸው ቤተ ሙከራዎችና የፈጠራ ዝንባሌ ያላቸው ታዳጊዎች ችሎታቸውን የሚያዳብሩባቸው ወርክሾፖች ይገኙበታል፡፡ ባለፉት ዓመታት በሳይንስ ዘርፍ ተስፋ ሰጪ የሆኑ የፈጠራ ሥራዎች በማዕከሉ ሠልጣኞች ተሠርተዋል፡፡ ማዕከሉ በጎንደር ከተማ እያደረገ ስላለው እንቅስቃሴ የጎንደር ሳይንስ ማዕከል አስተባባሪ አቶ ግርማ ወርቄን ምሕረተሥላሴ መኰንን አነጋግራቸዋለች፡፡

ሪፖርተር፡- ጎንደር ሳይንስ ማዕከል መቼና ምን ዓላማ አንግቦ ተመሠረተ?

አቶ ግርማ፡- ማዕከሉ የተመሠረተው እ.ኤ.አ. በ2013 ማርክ ገልፈንድ በተባለ አሜሪካዊ እስራኤላዊ ዕርዳታ ሰጪ አማካይነት ነው፡፡ ተማሪዎች በንድፈ ሐሳብ ያገኙትን ትምህርት በተግባር የሚያዩበት ማዕከል ነው፡፡ በተግባር ካሳየናቸው በኋላ የፈጠራ ሥራዎች እንዲሠሩ ድጋፍ እናደርጋለን፡፡ የመንግሥትና የግል ትምህርት ቤቶች ተማሪዎችም ወደ ማዕከሉ ሲመጡ ደስተኛ ናቸው፡፡ ከማዕከሉ በራቁ አካባቢዎች የሚኖሩ ተማሪዎች ዕድሉን ለማግኘት ስለሚቸገሩ በየትምህርት ቤታቸው የመስክ (አውትሪች) ፕሮግራም እናካሂዳለን፡፡ ዋና ዓላማችን ተማሪዎች በንድፈ ሐሳብ የተማሩትን በተለያዩ ሳይንሳዊ ቁሳቁሶች በመታገዝ እንዲረዱ ማድረግ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ማዕከሉ ለተማሪዎች ምን ዓይነት አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል?

አቶ ግርማ፡- ማዕከሉ ውስጥ አገልግሎት እየሰጡ ያሉት የኦፕቲክስ፣ የኤሌክትሮኒክስ፣ የመካኒክና የአይቲ (ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ) ቤተ ሙከራዎች ናቸው፡፡ የፈጠራ ችሎታ ያላቸው ተማሪዎች ክህሎታቸውን የሚያዳብሩበት ወርክሾፕ አለ፡፡ የባዮሎጂና ኬሚስትሪ፣ ፕላንት ሳይንስ ለወደፊት የሚሟሉ ቤተ ሙከራዎች ናቸው፡፡ ተማሪዎች አሁን ባሉት ቤተ ሙከራዎችና ወርክሾፖች እየተጠቀሙ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ማዕከሉ የሚያስተናግደው በየትኛው የትምህርት ደረጃ ያሉ ተማሪዎችን ነው? የሥልጠናው አካሄድስ ምን ይመስላል?

አቶ ግርማ፡- ከመጀመሪያ ደረጃ ተማሪዎች ማለትም ከአምስተኛና ስድስተኛ ክፍል ተማሪዎች ጀምሮ ያሉትን እናካትታለን፡፡ ለወደፊት ከኬጂ (አፀደ ሕፃናት) ጀምሮ ተማሪዎች በሕፃንነታቸው የሳይንስ ፍላጎት እንዲያድርባቸው ለመሥራት ሥርዓተ ትምህርት ነድፈናል፡፡ አሁን ከአምስተኛ ክፍል በታች ያሉ ተማሪዎች ለጉብኝት ብቻ ወደ ማዕከሉ ይመጣሉ፡፡ ተማሪዎችን የምንመርጠው ለሚመለከተው አካል ደብዳቤ በመላክ ነው፡፡ በሒሳብና በሳይንስ ትምህርቶች ከፍተኛ ውጤት ያላቸውና የፈጠራ ዝንባሌ ያላቸው  ተማሪዎች እንዲላኩልን እንጠይቃለን፡፡ መጀመርያ ሲመጡ ደኅንነታቸውን እንዲጠብቁ (ሴፍቲ ሩል) እናሳያቸዋለን፡፡ ወደ ቤተ ሙከራ ሲገቡ ቅደም ተከተሉን ጠብቀው ነው፡፡ የምናሳያቸው ነገር ከሚማሩት ጋር አብሮ የሚሄድ መሆን አለበት፡፡ እያንዳንዱ ቤተ ሙከራ ማንዋል ያለው ሲሆን፣ የተወሰነ መመሪያ ከሰጠናቸው በኋላ ራሳቸው እንዲሠሩ እናደርጋለን፡፡ ተማሪዎቹ በግላቸው እንዲመራመሩ ይጠበቃል፡፡ የሠሩትንም ሪፖርት ያደርጉልናል፡፡ ተማሪዎቹ በየሴሚስተሩ ሲመጡ በስም ዝርዝራቸው መሠረት እንከታተላለን፡፡ የማይከታተል ተማሪ ካለ ሌላ ተማሪ እንዲተካ እናደርጋለን፡፡

ሪፖርተር፡- በማዕከላችሁ ሠልጣኞች ከተሠሩ የፈጠራ ሥራዎች መካከል ለዘርፉ ዕድገት አስተዋጽኦ ያበረክታሉ የሚሏቸውን ቢጠቅሱልን?

አቶ ግርማ፡- አንዱ ፈጠራ አውቶማቲክ ስትሪት ላይት (የመንገድ መብራት) ነው፡፡ መብራቱ በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሠራ ሲሆን ሰው ሳይቆጣጠረው ጨለማ ሲሆን በርቶ ቀን ላይ ይጠፋል፡፡ አውቶማቲክ ስለሆነ ኃይል ይቆጥባል፡፡ በተግባር ውሎ አገልግሎት የሚሰጥበት መንገድ እንዲፈጠር ለሚመለከታቸው አሳውቀናል፡፡ ሌላው ፓርኪንግ ሎት ነው፡፡ በተለምዶ በሆቴሎች፣ በቢሮዎችና በግለሰብ ቤቶች መኪና ፓርክ ለማድረግ ጥበቃዎችን ጠይቀን በር አስከፍተን ነው፡፡ ፈጠራው በፓርኪንግ አካባቢ ያለውን ክፍት ቦታ በመቁጠር ያለሰው እገዛ ክፍት ቦታ ካለ ለመግባት ያመቻል፡፡  በአገር አቀፍ ደረጃ በተካሄደ ውድድር ከ78 ፕሮጀክቶች መካከል አንደኛ የወጣ ሲምፕል ሮቦቲክ ካር አለን፡፡ ፈጠራው ዕቃዎችን በቀላሉ ከቦታ ቦታ ማንቀሳቀስ የሚያስችል መኪና ሲሆን፣ አማኑኤል ደምሴ የተባለው ፈጣሪው ላፕቶፕ ተሸልሟል፡፡ መኪናውን በምን መልኩ በተግባር እናውለው? የሚል ጥያቄ በዞን ደረጃ ተነስቶም ነበር፡፡ የትራፊክ መብራት፣ ስሞክ ኤክስራክተር፣ ሞባይል ዲተክተርም ከፈጠራዎቹ መካከል ይጠቀሳሉ፡፡ ሞባይል ዲተክሩ ስብሰባ በሚኖር ወቅት ወይም በትምህርት ቤት አካባቢ የሞባይል ድምፅ እንዳይረብሽ በተወሰነ አካባቢ ብቻ ሞባይል እንዳይሠራ የሚያደርግ ነው፡፡ ስሞክ ኤክስራክተሩ ቤታችን ውስጥ ጭስ በሚበዛበት ወቅት በቀላሉ የሚያስወግድ ነው፡፡ ተማሪዎች የፈጠራ ፕሮቶታይፕ (ሞዴል) ማዘጋጀት እንጂ ትልቅ ሥራ አይጠበቅባቸውም፡፡ ወደሚቀጥለው ደረጃ ለመሸጋገር በጀትም ያስፈልጋል፡፡

ሪፖርተር፡- ከፈጠራ ሥራዎቹ መካከል ከሞዴል በተግባር ላይ የዋሉና ኅብረተሰቡ የሚገለገልባቸው አሉ?

አቶ ግርማ፡- በፕሮቶታይፕ የሚገኙ እንጂ በተግባር የዋሉ አይደሉም፡፡ እኛ የምንጠቀምበት ሶላር ኦቨን (በፀሐይ ብርሃን የሚሠራ ምድጃ) አለ፡፡ አንድ ወቅት በባዮጋዝ ወተር ፓምፕ ለማሠራት ሞክረን ወደ መኪና ማንቀሳቀሻነት ቀየርነው፡፡ የፈጠረውን ልጅ ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ ጋር አገናኝተነው ባዮጋዙን በሞተር ቦታ ዳማስ በምትባል መኪና እንዲገጥም ተደረገ፡፡ መኪናዋ ስሊንደር ተገጥሞላት በባዮጋዝ ከተማ ውስጥ እየተንቀሳቀሰችም ነበር፡፡ ዩኒቨርሲቲው ለልጁ ነፃ የትምህርት ዕድል በመስጠትና መኪናዋ በተግባር እንድትውል በማድረግ ተባብሮናል፡፡ ልጁ መኪናዋን የሠራው የ12ኛ ክፍል ተማሪ ሳለ ሲሆን፣ ከተማ ውስጥ ይነዳት ነበር፡፡ አሁን ወደ ውጪ አገር ለትምህርት ሄዷል፡፡ የመድኃኒት መርጫ አውሮፕላን ዲዛይን አድርጎ ጨርሶ ወደ ውጪ የሄደም ልጅ አለ፡፡ ለአውሮፕላኑ (ማረጋገጫ) አፕሩቫል የሚሰጠን ግን አላገኘንም፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድን ጠይቀን ነበር፡፡ ከጊዜ እጥረት ነው መሰለኝ አልመጡልንም፡፡ አውሮፕላኑ በአልሙኒየም የተሠራ ሲሆን፣ አንድ ሰው ጭኖ መድኃኒት የሚረጭ ነው፡፡ አሁን ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ይገኛል፡፡ 

ሪፖርተር፡- ድጋፍ የሚያደርግላችሁ አካል አስተዋጽኦ ምን ድረስ ነው?

አቶ ግርማ፡- ዕርዳታ የሚያደርግልን ማርክ ገልፈንድ ከልጅነቱ ጀምሮ የሳይንስ ሰው ነው፡፡ ብዙ የራሱ ፈጠራዎች ያሉት ሲሆን፣ ሳይንስን በአገሪቱ ለማስፋፋት ተነሳስቷል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ከጎንደር በተጨማሪ ደብረ ዘይት፣ ባህር ዳር፣ መቐለ፣ አዳማና ሐዋሳ የሳይንስ ማዕከሎች አቋቁሟል፡፡ በማዕከሉ ከሚሠሩ ፕሮጀክቶች መካከል ያመነባቸውን ይደግፋል፡፡ የሳይንስ ፌር (መድረክ) ስናዘጋጅና በሌሎች አጋጣሚዎችም እየመጣ ይጎበኛል፡፡

ሪፖርተር፡- አገሪቱ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ በጅማሮ ደረጃ ከሚገኙ አገሮች መካከል እንደመሆኗ፣ ማዕከሉ በዚህ አካባቢ ያሉ ታዳጊዎችን በሳይንስ ዘርፍ በማብቃት ረገድ ስላለው አገራዊ አበርክቶ ቢገልጹልን?

አቶ ግርማ፡- ትልቅ ለውጥ እያመጣን ነው፡፡ ተማሪዎች ንድፈ ሐሳብ ብቻ ሲማሩ ሳይንስ ምናባዊ ብቻ ይሆናል፡፡ ለምሳሌ ተማሪዎች ዲፍራክሽን ምንድነው? ሲባሉ ንድፈ ሐሳቡን ብቻ ያውቃሉ፡፡ ነገር ግን በቤታቸው የሚተገብሩት ነገር ነው፡፡ አትክልት ውኃ ሲጠጣ የትቦ ጫፍ በእጅ ሲያዝ ዲፍራክሽን እየተሠራ ነው፡፡ በዚህ መንገድ ሲቀርብላቸው ደስ ስለሚላቸው ለሳይንስ ያላቸው ፍላጎት ይጨምራል፡፡ ማዕከሉ እየታወቀ ሲመጣ ብዙ ቤተሰቦች ልጆቻቸው እንዲገቡ እየጠየቁን ነው፡፡ ኅብረተሰቡ ለሳይንስ ባለው አመለካከትና በተማሪዎች ላይም ለውጥ እየታየ ነው፡፡ ልዩ የፈጠራ ችሎታ ያላቸው ተማሪዎች በትርፍ ጊዜያቸው እየመጡ ይጠቀማሉ፡፡ ኅብረተሰቡ የሳይንስ ማዕከል መኖሩን ሲያውቅና ፈጠራዎቹ አገር ውስጥ መሠራታቸውን ሲያይ የአነሳሽነት ባህሪ አለው፡፡ ተማሪዎች የተወዳዳሪነት ባህሪ እንዲኖራቸው ያደርጋቸዋል፡፡ ሰዎች የፈጠራ ሥራዎቹን ሲያዩ አገር ውስጥ መሠራታቸውን ማመን እስኪያቅታቸው ይገረማሉ፡፡

ሪፖርተር፡- ብዙ ፈጠራዎች የማኅበረሰቡን ችግር ከግምት በማስገባት መፍትሔ ለመስጠት ቢሠሩም፣ ፈጠራዎች ከሞዴልነት ባለፈ እምብዛም በተግባር ሲውሉና በተመጣጣኝ ዋጋ ለኅብረተሰቡ ሲቀርቡ አይስተዋልም፡፡ ይህን ውስንነት ለመቅረፍ ምን መደረግ አለበት?

አቶ ግርማ፡- የተባለው ውስንነት አለ፡፡ ችግሩን ለመቅረፍ ግለሰቦች፣ ድርጅቶችና መንግሥትም መሳተፍ አለበት፡፡ ብዙ ሰው የሆነ ነገር ፈጥሮ በአቅም ማነስ የተነሳ ወደ ተግባር አይቀይረውም፡፡ ፈጣሪው አቅም ካለው ሰው ጋር ላይተዋወቅ ወይም ማሳመን አይችል ይሆናል፡፡ የፈጠራ ሰዎች በብዛት ዕድሉን አያገኙም፡፡ ፈጠራዎቻቸው ወደ ተግባር የማይመጡትም ለዚህ ነው፡፡ እኛ ፈጠራዎችን ወደ ተግባር ለማስገባት ከብዙ አካሎች ጋር እየተነጋገርን ነው፡፡ መንግሥት ለሳይንስ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ነው፡፡ ያሉት ችግሮች ተቀርፈው አገሪቱ በሳይንስ ከፍተኛ ደረጃ የምትደርስበት ጊዜም ቅርብ ይመስለኛል፡፡

ሪፖርተር፡- ከከተማ ቀመስ አካባቢዎች በዘለለ አብዛኛው ማኅበረሰብ ወደሚኖርበት ገጠራማው አካባቢ ሳይንስን ለማስፋፋት ጥረት ታደርጋላችሁ?

አቶ ግርማ፡- ትክክለኛ ጥያቄ ነው፡፡ እኛም እንዴት ማዳረስ እንደምንችል ዕቅዶች ይዘናል፡፡ በ2010 ዓ.ም. በጀቱን ካገኘን በወረዳዎች ለመሥራት ዕቅድ አለን፡፡ ገጠር ውስጥ በጣም ጎበዝ ልጆች አሉ፡፡ እነሱን ለመደገፍ ፕሮግራሞች ይዘናል፡፡ በአገር አቀፍ ደረጃ በየገጠሩ የትራንስፖርት፣ የኤሌክትሪክና ሌሎችም የመሠረተ ልማት ዝርጋታዎች ባለመኖራቸው ለሳይንስ ብቻ ሳይሆን ለአጠቃላይ ትምህርት የሚሰጠው ዋጋ አነስተኛ ነው፡፡ ለምሳሌ ብዙ ፕላዝማዎች ከዓመታት በፊት ከውጪ መጥተው እስካሁን አገልግሎት መስጠት እንዳልጀመሩ በሚዲያ ሰምቻለሁ፡፡ ይህ ማለት የኤሌክትሪክ ኃይል እጥረት አለ ማለት ነው፡፡ ኃይል በሌለበት ሳይንስን ማስፋፋት አስቸጋሪ ነው፡፡ መንግሥት በየገጠሩ የመብራት አገልግሎት እየዘረጋ ስለሆነ ሳይንስንም አብሮ ማስፋፋት ይቻላል፡፡ ተማሪዎች ወደ ሳይንስ የሚያዘነብሉት በመጽሐፍ ከሚያነቡት ንድፈ ሐሳብ ባለፈ በቴሌቪዥን፣ በኢንተርኔትና በሌሎችም የቴክኖሎጂ ውጤቶች ሲታገዙ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- አሁን ምን ያህል ሠልጣኞች አሏችሁ?

አቶ ግርማ፡- በዚህ ዓመት 830 ተማሪዎችና በአውትሪች ፕሮግራም ከ2,000 በላይ ተማሪዎች ተካተዋል፡፡