Skip to main content
x

የጠቅላይ ሚኒስትሩና የንግዱ ማኅበረሰብ ውይይት በሙያዊ ዕይታ

በጌታቸው አስፋው

     ጠቅላይ ሚኒስትሩ ነሐሴ 13 ቀን 2009 ዓ.ም. ከንግዱ ማኅበረሰብ ጋር ባደረጉት ውይይት ከነጋዴዎች ለቀረቡ በርካታ ጥያቄዎች መልስ ሰጥተዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩና የግል ባለሀብቶቹ በሦስት ነገሮች ላይ ተስማምተዋል ብዬ አምናለሁ፡፡ አንደኛው ለአገር ዕድገት መዋዕለ ንዋይ ያስፈልጋል፣ ሁለተኛው ገበያው ጉድለት ስላለበት አገር የምትፈልገውን መዋዕለ ንዋይ ማቅረብ አልቻለም፣ ሦስተኛው ማንኛውም አገር ወደ አንዱ ወይም ወደ ሌላው የሚያጋድል ቅይጥ ኢኮኖሚ ነው እንጂ ሙሉ በሙሉ የገበያ ኢኮኖሚ አገር፣ የለም ሙሉ በሙሉ መንግሥታዊ ኢኮኖሚ አገርም የለም፡፡

በውይይቱ ላይ በቂ ግንዛቤ አላገኘም የምለው አገሮች በኢኮኖሚ ፖሊሲያቸው የሚከፈሉት በሁለት አማራጮች በኒዮ ሊበራልና በልማታዊ መንግሥታት ብቻ ሳይሆን፣ በሦስት አማራጮች መሆኑን አለመረዳት ነው፡፡ ከሦስቱ አማራጮች ሁለቱ በገበያ ኢኮኖሚ ውስጥ ያሉ የተለያዩ የገበያ ኢኮኖሚ ደረጃዎች ሲሆኑ፣ ሦስተኛው የልማት ኢኮኖሚ የሚባለው ነው፡፡ የእነዚህን ሦስት አማራጮች ፍረጃ ምክንያታዊነት፣ የገበያ ኢኮኖሚና ልማትና የአገሮችን ታሪካዊ ጉዞ ጠቅሼ አብራራለሁ፡፡

በቅድሚያ ግን የሁለት አመራርና አስተዳደር የተሰኙ ቃላትን ትርጉሞች ልዩነት እገልጻለሁ፡፡ መንግሥት የግል ገበያ ኢኮኖሚውን በብሔራዊ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ምልክት በመስጠት አቅጣጫ ለማስያዝ የሚወስደው ዕርምጃ የኢኮኖሚ አመራር ይባላል፡፡ መንግሥት የሕዝብ ንብረትን ለምርትና ለልማት በውክልና ለማስተዳደር የሚያደርገው እንቅስቃሴ የመንግሥት ኢኮኖሚ አስተዳደር ይባላል፡፡

የመንግሥት አመራር ሀብት በግለሰቦች እጅ ሆኖ መንግሥት በብሔራዊ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ግለሰቦች ለአገር በሚጠቅም የኢኮኖሚ ዘርፍ እንዲሰማሩ አቅጣጫ የሚያስቀይርበት ሁኔታ ሲሆን፣ የመንግሥት አስተዳደር ግን መንግሥት እንደ ግለሰቦች ኢኮኖሚው ውስጥ ገብቶና በሕዝብ ውክልና የሀብት አስተዳዳሪ ሆኖ የገበያውን ጉድለት በመንግሥት ተሳትፎ በመሙላት ምርት አምርቶ የሚሸጥበት ሁኔታ ነው፡፡

የገበያ ኢኮኖሚ አገሮች ታሪካዊ ጉዞ

የገበያ ኢኮኖሚ በሁለት ሲከፈል አንዱ የነፃ ገበያና የካፒታሊዝም ሥርዓት ኢኮኖሚ በ18ኛው ክፍለ ዘመን በአዳም ስሚዝ ከተተነተነበት ጀምሮ የኖረ በገበያ ላይ ትልቅ ዕምነት የነበረው የግል ገበያ ኢኮኖሚ ፖሊሲ (Liberal /Micro/ Economic Policy) ሲሆን፣ ሌላው ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት እስከ 1980ዎቹ የገነነው የግል ገበያ ኢኮኖሚን በመንግሥት ብሔራዊ ኢኮኖሚ ፖሊሲ መምራት (Macro Economic Policy Guidance) ነው፡፡ ከ1980ዎቹ በኋላ የብሔራዊ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ውጤት ስለከሸፈ የገበያ ኢኮኖሚ አገሮች በፕሬዚዳንት ሬጋንና በማርጋሬት ታቸር አማካይነት ወደ ቀድሞው የግል ገበያ ኢኮኖሚ ተመልሰው ኒዮ ሊበራል ኢኮኖሚ የሚል ስያሜ ተሰጣቸው፡፡ እ.ኤ.አ. ከ2008 የገንዘብ ቀውስ በኋላ ገበያው ስላላስተማመነ እንደገና ወደ የብሔራዊ ኢኮኖሚ ፖሊሲ አመራር ተመለሱ፡፡ 

ምዕራባውያን የገበያ ኢኮኖሚ አገሮች የሚጫወቱት በእነዚህ ከሁለት አንዱ የግል ገበያ ነፃነትና ሌላው በብሔራዊ ኢኮኖሚ ፖሊሲ የግል ገበያውን መምራት የገበያ ኢኮኖሚ ደረጃዎች መካከል ነው፡፡ ለምሳሌም አሜሪካ፣ እንግሊዝና አንዳንድ ምዕራብ አውሮፓውያን በግል ገበያ ኢኮኖሚ መርህ ገበያው ራሱን በራሱ ስለሚያስተካክል በኢኮኖሚው ውስጥ የመንግሥት እጅ አጭር ይሁን ሲሉ፣ ሌሎች ስዊድንና ኖርዌይን የመሳሰሉ አገሮች መንግሥት ኢኮኖሚውን በብሔራዊ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ተቆጣጥሮና መርቶ ለተጎዳው የኅብረተሰብ ክፍል ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ አገልግሎት በመስጠት፣ መሠረተ ልማትንም በማስፋፋት በኢኮኖሚው ውስጥ ረጅም እጁን ማስገባት አለበት ይላሉ፡፡

የልማታዊ መንግሥት አገሮች ታሪካዊ ጉዞ

ልማታዊ መንግሥት የሚባሉት የእስያ አገሮች ወደ የዳበረ የገበያ ኢኮኖሚ ሥርዓት ከመግባታቸው አስቀድሞ፣ ከኋላ ቀር የኢኮኖሚ ሥርዓት በቀጥታ ወደ መንግሥታዊ የኢኮኖሚ አመራርና የኢኮኖሚ አስተዳደር በአንድ ጊዜ የገቡ አገሮች ናቸው፡፡ የግል ገበያውን ጉድለት ለማረም የኢኮኖሚ አመራሩንም የኢኮኖሚ አስተዳደሩንም ቀላቅለው ተጠቅመዋል፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥ በኢኮኖሚ ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ለውጥም አምጥተዋል፡፡

ኢትዮጵያና አንዳንድ ታዳጊ አገሮች የእስያውያንን የልማታዊ መንግሥት የኢኮኖሚ ፍልስፍና ሊከተሉ አስበው የገበያ ኢኮኖሚው ሳይዳብር በፊት ወደ የሕዝብ ንብረትን ማስተዳደር ልማታዊ መንግሥትነት ፈጥነው ስለገቡ፣ የግሉን ኢኮኖሚ በብሔራዊ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ለመምራትና ምልክት በመስጠት አቅጣጫ ለማስያዝ ምን ጥረት አድርገን ምን አልተሳካም? ለምን አልተሳካም? ብለው  ራሳቸውን አልጠየቁም፡፡ እነርሱ የታያቸው የገበያውን ጉድለት እኛው ወደ ምርት በመግባት እንሞላዋለን የሚለው ብቻ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ምስቅልቅል ያለበት ምክንያትም አመራርንና አስተዳደርን ለይቶ አውቆ፣ መቼ የትኛውን ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ አለመለየት ነው፡፡ 

የመንግሥት ጣልቃ ገብነት መቼ ያበቃል ጥያቄ

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከንግዱ ማኅበረሰብ ጋር ባደረጉት ውይይት ከነጋዴዎቹ ለቀረበው የመንግሥት ጣልቃ ገብነት መቼ ያበቃል ጥያቄ ሲመልሱ መንግሥት መቼም ቢሆን እጁን አይሰበስብም በማለት ለ200 ዓመታት የሊበራሊዝምና የኒዮ ሊበራሊዝም ሰባኪዎች ሆነው የኢኮኖሚውን ችግሮች ገበያው ይፈታል፣ መንግሥትና የግል ባለሀብት ግንኙነት የላቸውም ብለው ሲሰብኩን የኖሩ ሰዎች፣ አሁን ሲጨንቃቸው የባለሀብቱና የፕሬዚዳንቱ ምክር ቤት ብለው መከራቸውን እየበሉ ነው፡፡ የመሠረቱት ምክር ቤትም ተበትኖባቸዋል በማለት መንግሥት ጣልቃ ገብነቱን መቼም እንደማይገታ፣ በአሜሪካ መንግሥት ተምሳሌትነት ምላሻቸውን ሰጥተዋል፡፡       

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያላቸው መረጃ ትክክል ሊሆን ይችላል፡፡ ሆኖም የአሜሪካ መንግሥት ከግል ባለሀብቱ ጋር ለማድረግ ያቀደው ምክክር ኢኮኖሚውን ለመምራት ይሁን ወይስ ኢኮኖሚውን ለማስተዳደር ለይተው አልተናገሩም፡፡ የአሜሪካ መንግሥት የገበያውን ጉድለት ለመሙላት የግል ባለሀብቱን ተክቶ ኢኮኖሚውን ለማስተዳደር ይቃጣል ብሎ ማሰብ በጣም የዋህነት ነው፡፡ አስከትለው መንግሥት ክፍተት ባለበት ውስጥ እየገባ ድርሻውን ይወጣል በማለታቸው ግን፣ በኢትዮጵያ የመንግሥት ሚና በብሔራዊ ኢኮኖሚ ፖሊሲ የኢኮኖሚው ሞተር እናንተው ናችሁ ያሉትን የግል ባለሀብት የመምራት ብቻ ሳይሆን፣ ገበያ ውስጥ ገብቶ ምርት በማምረት ኢኮኖሚውን ማስተዳደርም እንደሆነ ወደፊትም እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡

መምራትን ሳይሞክሩ ማስተዳደር ውስጥ መግባት፣ መምራትና ማስተዳደር ተደበላልቀው ዋጋ ያስከፍላል፡፡ ኢትዮጵያ መክፈል የጀመረችውና ወደፊት የምትከፍለው ዋጋም ይህ መምራትንና ማስተዳደርን የመደበላለቅ ዋጋ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የግል ክፍለ ኢኮኖሚዋ በብሔራዊ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ያልተገራ መሆኑ ደካሞች ናቸው በሚለው የመንግሥት ፍረጃ ራሱ የተረጋገጠ ነው፡፡ ደካማው መሪው ነው ወይስ ተመሪው ጥልቅ ፍተሻ የሚፈልግ ሥራ ነው፡፡ በብሔራዊ ኢኮኖሚ ፖሊሲ አመራር ሊስተካከል የሚገባው ነገር ሳይስተካከል በችኮላ ወደ ማስተዳደሩ ተገብቶ፣ የግሉን ባለሀብት ሥራ መንግሥት ተሻምቶ የግሉን ክፍለ ኢኮኖሚ ሊያሽመደምዱት ወይም ራሳቸው የማይወጡት ጣጣ ውስጥ ሊገቡ ችለዋል፡፡

የፋይናንስ አቅርቦት ዕጥረት ጥያቄ

ሌላው የንግዱ ኅብረተሰብ ጥያቄ የፋይናንስ አቅርቦት ነው፡፡ ፋይናንስ መንግሥት በብሔራዊ ኢኮኖሚ ፖሊሲ የግሉን ክፍለ ኢኮኖሚ ከሚመራባቸው መንገዶች አንዱና ዋናው ነው፡፡ እዚህም ላይ የሁለት ቃላትን ትርጉሞች ልዩነት መግለጽ ያስፈልጋል፡፡ ብሔራዊ ባንክ የሚያሰራጨው ምንዛሪና ንግድ ባንኮች የቁጠባ ተቀማጫቸውን አርብተው በማበደር የሚፈጥሩት ብድር የመገበያያ መሣሪያ ጥሬ ገንዘብ (Money) ይባላል፡፡ ጥሬ ገንዘብ ላይ ለገበያ የቀረቡ አክሲዮንንና ቦንድን የመሳሰሉ ሰነዶች ሲጨመሩበት ድምር ውጤቱ ገንዘብ (Finance) ይባላል፡፡

በዓለም ላይ ሁለት ዓይነት የገንዘብ አስተዳደር ሥርዓቶች ሲኖሩ የመጀመርያው በባንክ አሠራር ላይ ብቻ የሚያተኩረው የብድር አስተዳደር የገንዘብ ሥርዓት (Credit-Based Financial System) ሲባል፣ ሁለተኛው በሰነዶች ገበያ ላይ የሚያተኩረው ገበያ ተኮር የገንዘብ አስተዳደር ሥርዓት (Market-Based Financial System) ይባላል፡፡ በአፍሪካ ወደ ሃያ ሦስት የሚጠጉ አገሮች የገበያ ተኮር የገንዘብ አስተዳደር ሥርዓት ሲኖራቸው፣ ኢትዮጵያ ግን ገና በብድር ተኮር የገንዘብ አስተዳደር ሥርዓት ውስጥ ነች፡፡ የብሔራዊ ባንክ ባለሥልጣናት ለዚህ የሚሰጡት መልስ ገበያ ተኮር የገንዘብ አስተዳደር ሥርዓትን ለመምራት የሚችል የሠለጠነ የሰው ኃይል የለንም ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ አቅም አላጣም ዕድሉን ቢያገኝ ተዓምር ይፈጥራል፡፡ ሌላ ምክንያት ቢፈልጉ ይሻላል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለብድር አሰጣጥና ንግድ ባንኮች ለግል ተበዳሪዎች ከሚያበድሩት ሃያ ሰባት በመቶ ለልማት ባንክ በሦስት በመቶ ብቻ ወለድ ማበደር ስለሚኖርባቸው የብድር እጥረት እንደተፈጠረ ነጋዴዎቹ ላነሱት ጥያቁ መልስ ሲሰጡ፣ ‹‹ልማት ባንካችን የፖሊሲ ባንክ ስለሆነ በፖሊሲያችን ላይ አንደራደርም፤›› ብለዋል፡፡ ልማት ባንክ ለተመረጡ በኢኮኖሚው ውስጥ ቁልፍ ሚና አላቸው ለተባሉ ዘርፎች ስለሚያበድር ይኼንን ነው የፖሊሲ ባንካችን ነው ያሉት፡፡

የብሔራዊ ባንክ ገዢው ከሪፖርተር ጋዜጣ ጋር ጥር 14 ቀን 2009 ዓ.ም. ስለ ባንኮች ሥራና የትርፍ መጠን ቃለ ምልልስ አድርገው ነበር፡፡ “ባንኮች ለቆጣቢዎች የሚከፍሉት ወለድ አምስት በመቶ ነው፡፡ ሲያበድሩ ደግሞ እስከ 17 በመቶ ወለድ ይጠይቁበታል፡፡ በዚህ መሀል አስራ አንድ ብር ያህሉ ትርፍ ነው፡፡ ወጪያቸው ሦስት በመቶ አይሞላም፡፡ ለቁጠባ በሚከፍሉትና ለብድር በሚጠይቁት ወለድ መካከል ያለውን ህዳግ ብሔራዊ ባንክ መቆጣጠር አልፈለገም፡፡ 27 በመቶው ተቀንሶ በቀሪው ተቀማጭ ገንዘባቸው የሚያገኙት ትርፍ በጣም ብዙ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ዋነኛው ምክንያት የግል ባንኮች በአብዛኛው ብድር የሚሰጡት ለአገልግሎት መሆኑም ለትርፋቸው ዕድገት አንድ ምክንያት ነው፡፡ አገልግሎት አካባቢ ያለውን ነገር ደግሞ ያው የምናውቀው ነው፡፡ አገልግሎት ሰጪው ነጋዴ ከውጭ በአንድ ሺሕ ብር ጠቅላላ ወጪ ያስገባውን ሸቀጥ መርካቶ ውስጥ ሁለትና ሦስት ሺሕ ብር ስለሚሸጥ፣ ከንግድ ባንክ በአስራ ሰባት በመቶ ወለድ ቢበደር አይጎዳውም፤” ነበር ያሉት፡፡ 

የጠቅላይ ሚኒስትሩንና የብሔራዊ ባንክ ገዢውን መልሶች አንድ ላይ አገናዝበን ስንመለከት፣ ልማት ባንክ የፖሊሲ ባንክ ስለሆነ ከንግድ ባንኮች በሦስት በመቶ ወለድ ብቻ በሚያገኘው ብድር ለተመረጡ ድርጅቶች ብድር ይሰጣል፡፡ ንግድ ባንኮቹ ለልማት ባንክ በሦስት በመቶ ወለድ ብቻ በሚያበድሩት ከስረው እንዳይጎዱ፣ ብሔራዊ ባንክ ከቆጣቢው በአምስት በመቶ ወለድ ተበድረው በአስራ ሰባት በመቶ ወለድ ሲያበድሩ፣ የትርፍ ህዳጋቸው ትልቅ መሆኑን እያወቀ አልተቆጣጠራቸውም፡፡

ልማት ባንክ በንግድ ባንኮች አማካይነት በእጅ አዙር ከቆጣቢው የሚያገኘውን ጥሬ ገንዘብ ለስኳር ፋብሪካዎችና ለጋምቤላ እርሻ ልማት፣ እንዲሁም ለሌሎች ድርጅቶች አበድሮ ሳይመለስለት ሲቀር የመጨረሻው ተጎጂ በኪሳራ ወለድ ለንግድ ባንኮቹ ያበደረው ቆጣቢው ነው፡፡ ይህ ማዕከላዊ የገንዘብ አስተዳደር የሆነው ብድር ተኮር ሥርዓት ነው ደናን የበለጠ የሚያደኸይና ሀብታሙን የበለጠ የሚያከብረው፡፡

የዋጋ ንረት አሥር በመቶ በሆነበት አገር አንድ ቆጣቢ ባንክ ጥሬ ገንዘብ በማስቀመጡ የሚያገኘው አምስት በመቶ ወለድ በድምር ውጤት፣ ቆጣቢውን በዓመቱ መጨረሻ ለተጣራ የአምስት በመቶ ኪሳራ ዳርጎት ተቀማጩ ሸቀጥ በመግዛት አቅሙ ወደ ዘጠና አምስት ብር ይወርዳል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆኑ የብሔራዊ ባንክ ገዢው ተጎጂውና በእንቅስቃሴው ተበዝባዡ ደሃው ቆጣቢ መሆኑን ያውቃሉ፡፡ የኢኮኖሚ ሕግ ቆጣቢው እንዳይከስር የቁጠባ ወለድ መጣኙ ቢያንስ ከዋጋ ንረት መጣኙ በላይ እንዲሆን ያዛል፡፡

ደሃው ለዚህች አገር ኢኮኖሚ ዕድገት መስዋዕትነት እየከፈለ ነው፡፡ በደሃው መክሰር አገሪቱ ሕንፃ ትገነባለች፣ መንገድ ትዘረጋለች፣ ሕንፃው ውስጥ የሚኖሩትም ሆኑ በመንገዱ የሚነዱት ሌሎች ናቸው፡፡ የዛሬ ወር ገደማ በዋጋ ንረት ግብር (Inflationary Taxing) ደሃው ምን ያህል እንደሚበዘበዝ ገልጬያለሁ፡፡ የቁጠባ ወለድ መጣኝ ዝቅተኛነት ሁለተኛው የብዝበዛ መንገድ ነው፡፡ አገሪቱ ለሀብታሙ ባለውለታና ለደሃው ባለዕዳ ሆናለች፡፡ ይኼንን የባለፀጋውን ሀብትና የደሃውን ሞራላዊና አካላዊ ኪሳራ ወይም ዕዳ ያላመዛዘኑ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ዘወትር ስለአሥር በመቶ ዕድገት ብቻ ያወራሉ፡፡

መፍትሔው ምንድነው?

ስለመንግሥት ጣልቃ ገብነት የምሰጠው መፍትሔ የኢኮኖሚ አመራርንና የኢኮኖሚ አስተዳደርን እንደገና ፈትሾ ትክክለኛ ፖሊሲ መንደፍ ነው፡፡ ስለገንዘብ አቅርቦቱ ባለፉት ጽሑፎቼ ከሁለትና ከሦስት ጊዜያት በላይ ስለገበያ ተኮር የገንዘብ ሥርዓት  ወይም የአክሲዮንና የቦንድ የሰነዶች ካፒታል ገበያና የጥሬ ገንዘብ ገበያ በማለት ለሁለት ከፍዬ ጥቅማቸውን ጽፌአለሁ፡፡ እነዚህ የገንዘብ ገበያዎች በጥቅል ስም አጠራር ሥውር የባንክ ሥራ (Shadow Banking) ተብለውም ይታወቃሉ፡፡ 

በአውሮፓና በአሜሪካ እንዲሁም በቻይና ዕድገት ትልቅ አስተዋፅኦ ያደረጉት፣ ሕጋዊ የቁጠባ ተቀማጭ ሒሳብ መያዝና ብድር የመስጠት የንግድ ባንክ ሥራ ፈቃድ ሳይኖራቸው በሥውር የባንክ ሥራ ገንዘብ የሚያገበያዩ የገንዘብ አስተላላፊ ተቋማት ሲሆኑ፣ ሕጋዊ የንግድ ባንኮችም በተባባሪዎቻቸው አማካይነት በዚህ ተግባር በስፋት ይሳተፋሉ፡፡

እነዚህ እንደ ንግድ ባንክ የተቀማጭ ሒሳብ ምንዛሪ ጥሬ ገንዘብ ለመቀበል ሕጋዊ መሠረት የሌላቸው የገንዘብ ተቋማት፣ የአባሎቻቸውን ጥሬ ገንዘብ በማንቀሳቀስ ብቻ በአውሮፓ፣ በአሜሪካና፣ በቻይና ከንግድ ባንኮቹ ያልተናነሰ ሀብት ያንቀሳቅሳሉ፡፡ በቻይና ሃያ ትሪሊዮን ዶላር የሚጠጋ ሀብት አላቸው፡፡ በአሜሪካም እስከ ሃያ አምስት ትሪሊዮን ዶላር ይንቀሳቀሳል፡፡ በአውሮፓ ኅብረት አባል አገሮች ዘንድ እስከ 28 ትሪሊዮን ዩሮ ይደርሳል፡፡ ቡድን ሃያ በሚባሉት አገሮች የሥውር ባንክ ሥራ ከጠቅላላው የገንዘብ እንቅስቃሴ ከ25 እስከ 30 በመቶ ይሆናል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2012 በዓለም አቀፍ ደረጃ በሥውር ባንኮች የተሰጠ የጥሬ ገንዘብ አገልግሎት አንድ መቶ ትሪሊዮን ዶላር እንደደረሰ ተገምቷል፡፡

ሥውር የባንክ ሥራ የሚያከናውኑ የገንዘብ ተቋማት የጋራ መዋዕለ ንዋይ ጥሪቶች (Mutual Investment Funds)፣ የጡረታ ጥሪቶች (Pension Funds)፣ ብድር ሰጪ የመዋዕለ ንዋይ ባንኮች (Investment Banks)፣ የመያዥያ ኩባንያዎች (Hedge Companies)፣ የብድር ዋስትና ሰጪዎች (Credit Guaeantee Insurance)፣ ሌሎች የጥሬ ገንዘብ ገበያዎችን የመሳሰሉ የብድር አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ናቸው፡፡

ሥውር ባንኮች እንደ መደበኛ ንግድ ባንኮች ብድር ይሰጣሉ፡፡ የገንዘብ ክፍለ ኢኮኖሚውን ጥሬነትም ይጨምራሉ፡፡ ሆኖም እንደ መደበኛ ንግድ ባንኮች ተቀማጭ ከሕዝብ ስለማይሰበስቡ በብሔራዊ ባንክ ቁጥጥር ሥር አይደሉም፡፡ እንደ መደበኛ ንግድ ባንኮቹ ከብሔራዊ ባንክ የመበደርና ላበደሩት ገንዘብ የብሔራዊ ባንክን ዋስትና ማግኘትም አይችሉም፡፡ በሚያበድሩት ገንዘብ ላይ መጠባበቂያ ተቀማጭ እንዲይዙም አይገደዱም፡፡ ከብሔራዊ ባንኩ ጋር ያላቸው ግንኙነት የላላ ይሁን እንጂ፣ የሚተዳደሩት ግን በአገሪቱ የፋይናንስ ንግድ ፈቃድ ሕግ መሠረት ነው፡፡

ገበያ ተኮር የገንዘብ ገበያ ሥርዓት ከፍተኛ የገንዘብ ኢኮኖሚክስ፣ የሒሳብ መዝገብ አያያዝና የኮሚሽን ኤጀንትነት ሙያ ባላቸው ሰዎች የሚከናወን ስለሆነ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ የዩኒቨርሲቲ ምሩቃን የሥራ ዕድል መፍጠር የሚችል ዘርፍም ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው  [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡