Skip to main content
x

የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በእነ አቶ በቀለ ገርባ ጉዳይ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽንን አስጠነቀቀ

የሽብርተኝነት ወንጀል ፈጽመዋል ተብለው በእነ ጉርሜሳ አያኖ መዝገብ ክስ በተመሠረተባቸው አቶ በቀለ ገርባ፣ አቶ ደጀኔ ጣፋ፣ አቶ አዲሱ ቡላን ጨምሮ በ22 ግለሰቦች ላይ ከሳሽ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ካቀረበው የድምፅ ማስረጃ ጋር በተያያዘ፣ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አራተኛ ወንጀል ችሎት የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽንን አስጠነቀቀ፡፡

ፍርድ ቤቱ ማስጠንቀቂያ የሰጠው በተለይ የኮርፖሬሽኑ የክልል ቋንቋዎች ኃላፊ እንደነበሩ ለተናገሩትና በቅርቡ ወደ ሌላ ክፍል መዛወራቸውን ለገለጹት አቶ ፀጋ ልዑል ወልደ ኪዳን ነው፡፡ ዓቃቤ ሕግ የሰዎች ምስክሮቹን አሰምቶ እንዳጠናቀቀና ተጨማሪ በኦሮሚኛና በእንግሊዝኛ የተቀረፀ የድምፅ ማስረጃ እንዳለው ካስረዳ በኋላ፣ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ተርጉሞ እንዲልክ እንዲታዘዝለት ጠይቋል፡፡ ፍርድ ቤቱ በተደጋጋሚ ያስተላለፈውን ትዕዛዝ ያልፈጸመው ደግሞ አቶ ፀጋ ልዑል በኃላፊነት የሚመሩት ክፍል ነው፡፡

ፍርድ ቤቱ በተከታታይ ሁለት ጊዜ ትዕዛዝ ሲያስተላልፍ ኮርፖሬሽኑ በጽሑፍ በሰጠው ምላሽ ተደራራቢ የሥራ ጫና እንዳለበት ሲገልጽ ፍርድ ቤቱ በሌላ አካል እንዲያስተረጉም ካዘዘ በኋላ፣ የኮርፖሬሽኑ ኃላፊ ሚያዝያ 5 ቀን 2009 ዓ.ም. ለምን የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ ማክበር እንደልተፈለገ ቀርበው እንዲያስረዱ ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር፡፡

ኮርፖሬሽኑ ሐሙስ ሚያዝያ 5 ቀን 2009 ዓ.ም. ወደ ፍርድ ቤት የላከው ዋና ኃላፊውን ሳይሆን፣ የክልል ቋንቋዎች ኃላፊ አቶ ፀጋ ልዑል ወልደ ኪዳንና ሁለት የተለያየ የሥራ ኃላፊዎች ነው፡፡ ፍርድ ቤቱ ማንነታቸውን ሲያረጋግጥ አቶ ፀጋ ልዑል የክልል ቋንቋዎች ኃላፊ መሆናቸውን ሲናገሩ፣ ለምን ፍርድ ቤቱ የሰጠውን ትዕዛዝ እንዳላከበሩ ተጠይቀዋል፡፡

ቀደም ባሉት ትዕዛዞች መሠረት ኮርፖሬሽኑ በእንግሊዝኛና በኦሮሚኛ የተቀረፁ የድምፅ ማስረጃዎችን አስተርጉመው ያላቀረቡት፣ ያሏቸው ተርጓሚዎች ጋዜጠኞች በመሆናቸውና ፕሮፌሽናል ስላልሆኑ ኃላፊነት መውሰድ ፈርተው መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም ለኃላፊዎች ያንኑ ገልጸው ሪፖርት ማድረጋቸውን አክለዋል፡፡

ኮርፖሬሽኑ ቀደም ላሉት ትዕዛዞች በጽሑፍ የሰጠው ምላሽ ኃላፊዎች የሥራ ጫና እንዳለባቸው፣ በቂ ጊዜ እንደሌላቸውና ፍርድ ቤቱ በሌላ አካል እንዲያስተረጉም ማለታቸው አግባብ ስለመሆኑ ለአቶ ፀጋ ልዑል ጥያቄ ቀርቦላቸዋል፡፡ ነገር ግን ደብዳቤው በተጻፈበት ወቅት እሳቸው ከኃላፊነታቸው ላይ ተነስተው እንደነበር ሲገልጹ፣ ‹‹ታዲያ አሁን ለምን መጡ?›› የሚል ጥያቄ ፍርድ ቤቱ አስከተለ፡፡ ‹‹አሁን የመጣሁት ቀደም ብሎ አንተ ጉዳዩን ስለምታውቀው ሂድና አስረዳ›› የሚል ትዕዛዝ ከአለቆቻቸው ደርሷቸው መሆኑን አስረዱ፡፡

ዓቃቤ ሕግ የመንግሥት አካል መሆኑን ኮርፖሬሽኑ እንደሚያውቅና በብዙ ባለሙያዎች የተሞላ መሆኑን ፍርድ ቤቱ አስታውቆ፣ አቶ ፀጋ ልዑል ‹‹የባለሙያ ችግር አለ›› በማለት የሰጡት ምላሽ አሳማኝ አለመሆኑን ገልጿል፡፡ ‹‹ይህ ተራ ትዕዛዝ አይደለም፡፡ ተራ ነገር ተርጉሙ አልተባላችሁም፡፡ ፍትሕ እንዲቃለልና ተገቢ ትርጉም እንዲሰጥበት ነው፡፡ ነገር ግን ኮርፖሬሽኑ በአንድ ፓራግራፍ ደብዳቤ እንደማይችል ምላሽ መስጠቱ ምን ዓይነት ጉዳት እንደሚያመጣበት ባለማሰቡ ነው፡፡ ፍርድ ቤቱ ዕርምጃ መውሰድ አላቃተውም፡፡ ያነበበ፣ የሠለጠነና ልምድ ያለው የሰው ኃይል ያለው ኮርፖሬሽን ይህንን ድርጊት ይፈጽማል የሚል እምነት ስለሌለው ነው፤›› ብሏል፡፡ የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ደግሞ የመንግሥት ትዕዛዝ መሆኑ መታወቅ እንዳለበትም አክሏል፡፡

ኮርፖሬሽኑ የያዘው አዝማሚያ ጥሩ እንዳልሆነና የፍርድ ቤትን ትዕዛዝ በተደጋጋሚ እንደ ተራ ነገር ማየቱ ጥሩ እንዳልሆነ ፍርድ ቤቱ አስታውቆ፣ ፍርድ ቤት የሚልከውን ትዕዛዝ ለሌላ አካል እንዲሰጥ ምላሽ ከመስጠት በፊት አዎንታዊና አሉታዊ ነገሮችን ማስተዋሉ እንደሚጠቅም ማወቅ አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝቧል፡፡

አቶ ፀጋ ልዑል በድጋሚ ለፍርድ ቤቱ እንደተናገሩት፣ ኮርፖሬሽኑ መተባበር ብቻ ሳይሆን ግዴታም እንዳለበት፣ ወቅታዊና ተደራራቢ ሥራ ስለገጠመው፣ ባለሙያዎቹ አንድ ቀን አንድ ቦታ ሌላ ጊዜ ሌላ ቦታ ለሥራ ስለሚመደቡና የተሰጣቸው ጊዜ አጭር መሆኑን በመጠቆም ቀደም ብለው የተናገሩትን ‹‹ፕሮፌሽናሎች አይደሉም›› ያሉትን ለማረም ሞክረዋል፡፡ ወቅቱም የበዓል ወቅት መሆኑንም እንደ ማካካሻ ጠቁመዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ በመቀጠል የጠየቀው በዕለቱ አስተርጓሚ ይዘው ስለመምጣታቸው ቢሆንም፣ ምላሻቸው ‹‹አላመጣንም›› ሆኗል፡፡ በኮርፖሬሽኑ እንዲተረጎም ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ የሰጠው ጉዳዩ ጠንከር ያለ በመሆኑ እንደሆነ ሲያስታውቅ፣ አቶ ፀጋ ልዑል ቀጠል በማድረግ፣ ‹‹ጉዳዩ አንገብጋቢ ስለሆነ በቂ ጊዜ ያስፈልጋል፡፡ በተጨማሪ ከሕግ ጋር በተያያዘ ወደ ኮርፖሬሽኑ በርካታ ትዕዛዞች እየመጡ ስለሆነ ፍርድ ቤቱ ከአለቆቻችን ጋር ሊነጋገር ይገባል፤›› ብለዋል፡፡

እንዲተረጎም የተፈለገው የኦሮሚኛ ድምፅ ትንሽ ስንኞች ያሉት የኦሮሚኛ ዘፈን ነው በሚል መሆኑን ፍርድ ቤቱ ገልጾ፣ እንግሊዝኛውም ቢሆን ያን ያህል እንዳልሆነ በመቁጠር የኮርፖሬሽኑ የበላይ ኃላፊዎችም ሆኑ የበታች ሠራተኞች ጉዳዩን አቅልለው ባያዩት የተሻለ መሆኑን አስረድቷል፡፡

የተከሳሾች ጠበቆች አስተያየታቸውን ተጠይቀው የአቶ በቀለ፣ ደጀኔ፣ አዲሱና ጉርሜሳ ጠበቃ አቶ አመሐ መኮንን በሰጡት አስተያየት፣ ‹‹ፍርድ ቤቱ ለሦስት ጊዜ የሰጠው ትዕዛዝ አልተፈጸመም፡፡ ፍርድ ቤቱም የዕለቱ ቀጠሮ የመጨረሻና መቋጫ መሆኑን ቃል ገብቷል፡፡ የተቀጠረው የኮርፖሬሽኑ ኃላፊ ቀርበው ለምን የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ እንዳልፈጸሙ እንዲያስረዱና ተርጓሚ ይዘው እንዲቀርቡ ቢሆንም አልቀረቡም፡፡ ኮርፖሬሽኑ የእኛ ተከራካሪ ባለመሆኑ ተወክለው ለመጡት ኃላፊዎች ምላሽ አንሰጥም፡፡ መጀመሪያውኑ ከሳሽ ዓቃቤ ሕግ ክስ ሲያቀርብ ሁሉንም ማስረጃዎች በፍርድ ቤቱ መሥሪያ ቋንቋ አስተርጉሞ ማቅረብ ነበረበት፡፡ ይህንንም የማረጋገጥ ኃላፊነት የፍርድ ቤቱ ነበር፡፡ ያም ሆኖ ማዛናዊ ለማድረግ ፍርድ ቤቱ የቻለውን ሁሉ ሲያደርግ በዝምታ አልፈናል፡፡ ከዚህ በኋላ ግን ተጨማሪ ቀጠሮ ሊሰጥ ስለማይገባ ማስረጃው ታልፎ ዓቃቤ ሕግ ቀደም ብሎ ባሰማው ማስረጃ መሠረት ብይን እንዲሰጥ መታዘዝ አለበት፤›› ብለዋል፡፡ የሌሎቹም ጠበቆች ተመሳሳይ ተቃውሞ በማሰማት ተጨማሪ ቀጠሮ እንዳይሰጥ ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል፡፡

በዚህ መሀል አቶ በቀለ ገርባ አቤቱታ እንዳላቸው ፍርድ ቤቱን ሲጠይቁ ተፈቅዶላቸዋል፡፡ ‹‹ይህ ቀጠሮ ለምን ያህል ጊዜ እንደተቀጠረና እንደተራዘመ ለእናንተ እተዋለሁ፡፡ ኮርፖሬሽኑ ሦስተኛ አካል ሆኖ ገብቷል፡፡ የማይመለከታቸውን ከሚልክ አንድ ባለሙያ ቢልክ ይሻል ነበር፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹ስንት ባለሙያዎች እንዳሉት እናውቃለን፡፡ ፕሮፌሽናል የለም መባሉ የሚያሳየው የሥርዓቱን ሁኔታ ነው፡፡ እኛ የምንታገለው ይህንን ሁሉ ነበር፡፡ ፍርድ ቤት የሚመጡት የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት ለመውሰድ ሳይሆን ፍትሕ ለማግኘት ነው፤›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ከዚህ በኋላ ተጨማሪ ቀጠሮ የሚሰጥ ከሆነ ወደ ፍርድ ቤት የሚመጡት በፈቃደኝነት ሳይሆን ተደብድበው በቃሬዛ ሊሆን እንደሚችል ተናግረው ‹‹በጣም አዝናለሁ›› ብለዋል፡፡ የሕግ ባለሙያዎች ስንት ነገር የሚሠሩበትን ጊዜያቸውን በአንድ ቀጠሮ ያለምንም ውጤት በመመላለስ እንዲያጠፉ መደረጉ፣ ሌላ የሕግ ባለሙያ ጫናውን በመፍራት እንዳይቀርብላቸው ለማድረግ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

ሌላው አቤቱታ ያቀረቡት አቶ ደጀኔ ጣፋ ናቸው፡፡ ለፍርድ ቤቱ እንደገለጹት፣ እንኳን በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ቀርቶ በማንኛውም ሚዲያ ውስጥ የሚቀጠሩ ጋዜጠኞች የመጀመሪያ መለኪያ የቋንቋ ችሎታ ነው፡፡ በኮርፖሬሽኑ ያሉት ባለሙያዎች እየታወቁ፣ ወደ ፍርድ ቤት የማይመለከታቸውን ኃላፊዎች እየላኩ በሰው መጫወት ተገቢ እንዳልሆነ አስረድተዋል፡፡ ክስ ሲቀርብባቸው ሆን ተብሎ የተቀነባበረ መሆኑን በወቅቱ ማስረዳታቸውን አቶ ደጀኔ ገልጸው፣ እየተሰቃዩ ያሉት እነሱ ብቻ ሳይሆኑ የኦሮሞ ሕዝብ መሆኑን አክለዋል፡፡

የከሰሳቸው ዓቃቤ ሕግ ልጃቸው እንደሚሆንና እሳቸው የተማሩና ትልቅ ሰው መሆናቸውን ጠቁመው፣ ቢዋሹና ያልሆነ ነገር እያደረጉ ቢቀጥሉ ኖሮ በአሁኑ ጊዜ ሚኒስትር ወይም አምባሳደር ሊሆኑ ይችሉ እንደነበር ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን ለዴሞክራሲና ለነፃነት መከበር በመታገላቸው ለእስር መዳረጋቸውን ተናግረዋል፡፡ እስካሁን ዝም ብለው ክሳቸውን የሚከታተሉት ፍርድ ቤቱን አክብረው መሆኑን ገልጸው፣ እየሆነው ያለው ነገር ግን እያሳዘናቸው መሆኑን በመጠቆም ‹‹ወይ ይፍረድብን ወይም ይግደለን፤›› ብለዋል፡፡

ፍርድ ቤቱም እነሱም ግራ እየተጋቡ መሆኑን የገለጹት አቶ ደጀኔ፣ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት የሰጠውን ትዕዛዝ ፍርድ ቤቱ ማገዱን አስታውሰው፣ እዚህ ግን የፍትሕ ሥርዓቱን ማንም ካድሬ እየተጫወተበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ሕዝብ እየጮኸ በመሆኑ ፍርድ ቤቱ ግራ ቢገባውም የሕዝብ ስቃይ ሊሰማው ይገባል ብለዋል፡፡

እሳቸው ብቻ ያረጁ መሆኑን ጠቁመው የመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪ ያላቸውን የ23 ዓመት ወጣቶች ማሰር ተገቢ እንዳልሆነም አክለዋል፡፡ ‹‹ከኮርፖሬሽኑ የመጣችሁ ኃላፊዎች የምንነግራችሁ አብረን እንኑር፣ አንጠፋፋ፣ እባካችሁ፣ እባካችሁ፤›› ብለዋል፡፡ ከዓቃቤ ሕግ ጀርባም ያለውን እንደሚያውቁ የገለጹት አቶ ደጀኔ፣ ፍርድ ቤቱ ጠንከር ብሎ ዕርምጃ ቢወሰድ ለሚመጣበት ነገር ሁሉ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከበስተጀርባው የሚቆም መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ የኮርፖሬሽኑን ተወካይ አቶ ፀጋ ልዑልን ‹‹ኃላፊ ነኝ ብለዋል›› በማለት በድጋሚ ካረጋገጠ በኋላ፣ የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ያልተፈጸመበትን ሁኔታ በሚመለከት ያስረዱት በቂ አለመሆኑንና በማስጠንቀቂያ እንዳለፈው ገልጾ ተጨማሪ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል፡፡ የፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ በድጋሚ ባይፈጸም በራሳቸው አቶ ፀጋ ልዑል ላይ ዕርምጃ እንደሚወሰድ በመንገር፣ ኦሮሚኛውንና እንግሊዝኛውን የድምፅ ማስረጃ በይዘት ጭምር በመተርጎም በጽሑፍ እስከ ሚያዝያ 18 ቀን 2009 ዓ.ም. ድረስ ለጽሕፈት ቤት ገቢ እንዲያደርጉ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ ኮርፖሬሽኑ በላከው ትርጉም ላይ ጠበቆች እስከ ግንቦት 6 ቀን 2009 ዓ.ም. ምላሻቸውን እንዲያቀርቡ በማሳሰብ፣ ብይን ለመስጠት ለግንቦት 7 ቀን 2009 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡