Skip to main content
x
የፍትሕ ሥርዓቱ ምን እየሠራ ነው?

የፍትሕ ሥርዓቱ ምን እየሠራ ነው?

በአገሪቱ የፍትሕ ሥርዓት ላይ ከሚነሱ ዋነኛ ችግሮች መካከል በሕዝብ ዘንድ ያለው አመኔታ ማጣት ነው፡፡ በተለያዩ መድረኮች ከተሰሙ ድምፆች ለመገንዘብ እንደተቻለው፣ የፍትሕ ሥርዓቱ በተለያዩ ምክንያቶች ሳቢያ በሕዝብ ዘንድ ያለው አመኔታ የተሸረሸረ ነው፡፡ ለዚህ ሰበቡ ደግሞ በፍትሕ ሥርዓቱ ላይ የሚነሱ የገለልተኝነት ጥያቄዎች ሲሆኑ፣ የግልጽነት መጥፋት ደግሞ ሁኔታዎችን አባብሰዋል፡፡ ብዙዎች በፍትሕ ሥርዓቱ ውስጥ የሚፈጸሙ ሕገወጥ ድርጊቶች እያማረሯቸው ፍትሕ መነፈጋቸውን ሲናገሩ፣ የግድ ሆኖባቸው እንጂ ፍርድ ቤት ደጃፍ ባይደርሱ ይመርጣሉ፡፡ በእርግጥም መንግሥት ሕዝብን አማረዋል ብሎ በአደባባይ ካመናቸው ጉዳዮች መካከል፣ ሕዝብ በፍትሕ ሥርዓቱ ላይ ያሰማው ቅሬታ ነው፡፡ በቅርቡም የፍትሕ ሳምንት ሲከበር የተደመጠው የሕዝብ እሮሮ ይህንን ችግር ያጠናክራል፡፡ ስለዚህ የፍትሕ ሥርዓቱ ምን እየሠራ ነው ብሎ መጠየቅ አያስፈልግም?

እንደሚታወቀው በአንድ መንግሥታዊ ሥርዓት ውስጥ ከሕግ አውጪውና ከሕግ አስፈጻሚው ጋር እየተናበበ በነፃነት ኃላፊነቱን የመወጣት ኃላፊነት ያበለት የፍትሕ ሥርዓቱ ነው፡፡ የፍትሕ ሥርዓቱ ከማናቸውም የአስፈጻሚው ተፅዕኖዎች ራሱን ነፃ አድርጎ ሥራውን ለማከናወን በተማረ የሰው ኃይል፣ በጠንካራ ተቋማዊ ነፃነት፣ ዘመኑ ባፈራቸው ቴክኖሎጂዎችና አቅም በፈቀደ መጠን በምቹ ከባቢ ውስጥ መሥራት መቻል አለበት፡፡ ዳኞች፣ ዓቃቢያነ ሕግ፣ ጠበቆችና ሌሎች ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች የሙያ ሥነ ምግባራቸውን ጠብቀው የሚሠሩበት ድባብ መኖር ይገባዋል፡፡ በዚህ መሠረት ዜጎች በሕግ የበላይነት ተማምነው ሥራቸውን እንዲያከናውኑ ማድረግ፣ ችግር ሲፈጠር ደግሞ ሁሉም በሕግ ፊት እኩል ሆነው የሚስተናገዱበት አሠራር መፍጠር፣ ማንም ሰው ከሕግ በላይ አለመሆኑን ማረጋገጥና የመሳሰሉት የአንድ ጠንካራ የፍትሕ ሥርዓት ማረጋገጫ ናቸው፡፡ ፖሊስ በተሰጠው ሕጋዊ ኃላፊነት መሠረት ምርመራውን ማከናወን፣ ዓቃቤ ሕግ በዚህ መሠረት ክሱን ማደራጀት ወይም ውድቅ ማድረግ፣ ዳኛው ደግሞ ሕጉና ህሊናው በመራው መሠረት ውሳኔ መስጠት፣ ማረሚያ ቤት ደግሞ የታራሚውን ሰብዓዊ መብት ጠብቆ ማቆየት የጤናማ የፍትሕ ሥርዓት ማሳያ ነው፡፡ ይህ በተግባር ባለመታየቱ ግን ብዙ ችግሮች አጋጥመዋል፡፡ አሁንም እያጋጠሙ ነው፡፡

በቅርቡ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ባቀረበው ሪፖርት፣ በበርካታ መንግሥታዊ ተቋማት በቢሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ አለመወራረዱን፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠር የጥሬ ገንዘብ ጉድለት መገኘቱን፣ የብዙዎቹ የፋይናንስ አያያዝ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ከወጣው መመርያ ጋር እንደሚጣረስ፣ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ግዥና ጨረታ ከሕጉ ጋር እንደማይጣጣም፣ ከፍተኛ የሆነ ገቢ ግብር አለመሰብሰብ፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ወጪና ገቢ በአሳፋሪ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ፣ ወዘተ. በስፋት ተተንትኖ ቀርቧል፡፡ ዋና ኦዲተር ለዓመታት እነዚህን ችግሮች እየቀነሰ የተብራራ ሪፖርት ቢያቀርብም፣ ዕርምጃ ባለመወሰዱ ብቻ የአገሪቱ ሀብት ለብክነት መዳረጉ ተገልጿል፡፡ ይህ ሪፖርትም ደረጃውን ጠብቆ ለጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ቀርቧል፡፡ የሕግ ጥሰት በፈጸሙ ላይ በአስቸኳይ ምርመራ ተጀምሮ ሕጋዊ ዕርምጃ ይወሰዳል ተብሎ ቢነገርም፣ የሚታይ ነገር የለም፡፡ በሹክሹክታ አጥፊዎች እየተያዙ እየተመረመሩ ነው ቢባልም፣ የሚመለከተው አካል ለመናገር ፈቃደኛ አልሆነም፡፡ ግልጽነት ባለመኖሩ ብቻ ሕዝብ በአገሩ ጉዳይ ባዕድ ሆኗል፡፡ ግልጽነት እየጠፋ አለመተማመን ከፍቷል፡፡

በሌላ በኩል የፍትሕ ሥርዓቱ ከሚተችባቸው በርካታ ጉዳዮች መካከል አንዱ የገዥው ፓርቲን የልብ ትርታ ብቻ እያዳመጠ ስለመንቀሳቀሱ ነው፡፡ በሕገ መንግሥቱ መሠረት ግን ነፃ የዳኝነት አካል ተቋቁሟል፡፡ በአንቀጽ 79 መሠረት በፌዴራልም ሆነ በክልል የዳኝነት ሥልጣን የፍርድ ቤቶች ብቻ መሆኑን፣ በየትኛውም ደረጃ የሚገኝ የዳኝነት አካል ከማንኛውም የመንግሥት አካል፣ ከማንኛውም ባለሥልጣን ሆነ ከማንኛውም ሌላ ተፅዕኖ ነፃ መሆኑን፣ ዳኞች የዳኝነት ተግባራቸውን በሙሉ ነፃነት እንደሚያከናውኑ፣ ከሕግ በስተቀር በሌላ ሁኔታ እንደማይመሩ፣ ወዘተ. በግልጽ ሠፍሯል፡፡ እውነት እንነጋገር ከተባለ የሕገ መንግሥቱ መንፈስ በተግባር ይታያል? ይህ ቢሆን ኖሮማ በዘመቻ በሚወሰዱ ዕርምጃዎች ለክስ የሚሯሯጠው ኃይል፣ የፌዴራል ኦዲተር ሪፖርትም ሆነ ሌሎች አስከፊ ሕገወጥ ተግባራት እንቅልፍ ሊነሱት ይገባ ነበር፡፡ በቅርቡ በተካሄደው የፍትሕ ሳምንት አገር አቀፍ ውይይት ላይ ከተነሱት ፍሬ ነገሮች መካከል አንዱ የፍትሕ ሥርዓቱ አካላት በሚባሉ (ፖሊስ፣ ዓቃቤ ሕግ፣ ፍርድ ቤትና ማረሚያ ቤት) ውስጥ ያሉ ትንንሽ አምባገነኖችና ብልሹ አሠራሮችን የሚያሰፍኑ ኃይሎች ሕዝቡን ወደ አመፅ እየገፉት መሆኑ ነው፡፡ ይህ ምን ማለት ነው? ከሕግ የበላይነት አስተሳሰብ ጋር መጋጨት አይደለም?

የፍትሕ ሥርዓቱ አካላት ሥራቸውን በነፃነት እንዲያከናውኑ መደረግ ሲገባው፣ አላስፈላጊ ሥምሪት ውስጥ ስለሚገቡ ሕዝቡ ፍትሕ እንዲያጣ እያደረጉ ነው፡፡ ሥራቸውን በነፃነት ማካሄድ ሲያቅታቸው ሙስና ውስጥ ይገባሉ፡፡ በዚህም ከምርመራ ጀምሮ እስከ መጨረሻው የፍርድ ውሳኔ ድረስ ሕዝቡን የሚያማርሩ አስከፊ ድርጊቶች ይፈጸማሉ፡፡ መከሰስ ያለበት አይከሰስም፡፡ መከሰስ የሌለበት ደግሞ ያለ ኃጥያቱ ፍዳውን ይበላል፡፡ የፍትሕ ሥርዓቱ ነፃነቱን ተነጥቆ ራቁቱን የቆመ ይመስላል፡፡ በፍትሕ ሥርዓቱ ውስጥ በኃላፊነት መንፈስ የተጣለባቸውን አደራ የሚወጡ በርካታ ሀቀኛ ባለሙያዎች ያሉትን ያህል፣ የእነሱን ልፋትና ጥረት በዜሮ የሚያባዙ የዚያኑ ያህል እየሆኑ ናቸው፡፡ በመልካም አስተዳደር ዕጦት የሚማረረው ሕዝብ የሕግ የበላይነት የለም ብሎ ደምድሟል፡፡ ችግር ፈጣሪዎች ሕጋዊ ዕርምጃ ቢወሰድባቸው ግን ይህ ስሜት አይፈጠርም ነበር፡፡ ሕጉ እየተጣመመ የሚፈረድበት ዜጋ በንፅህናው እየተንገበገበ ለወንጀል ራሱን እንዲያዘጋጅ የሚገደደው፣ የፍትሕ ሥርዓቱ ሥራውን በአግባቡ ማከናወን ሲሳነው ነው፡፡ ግልጽነት እንዳይሰፍን በማድረግና ከተጠያቂነት በመሸሽ ፍትሕ ማዛባት ማስጠየቅ አለበት፡፡ ሕግን ለሕገወጥ ተግባር በሚጠቀሙ ላይ የማያዳግም ዕርምጃ መውሰድ ካልተቻለ አደጋው የከፋ ነው፡፡

የፍትሕ ሥርዓቱን በማስተካከል ለሕግ የበላይነት መከበር ከሕግ አወጣጥ ጀምሮ ልዩ ትኩረት ያስፈልጋል፡፡ በሕግ የበላይነት ሥር አገር ማስተዳደርና በሕግ መግዛት መካከል ትልቅ ልዩነት አለ፡፡ ሕጎች ጥራታቸውን ጠብቀው ካልወጡ፣ በክፍተቶች የሚጠቀሙ ቀበኞች ብዙኃኑን ይጎዳሉ፡፡ የፍትሕ ሥርዓቱ አካላት ግልጽነትና ተጠያቂነት በሌለበት ሁኔታ ውስጥ የሚሠሩ ከሆነም ጦሱ የሚተርፈው ለአገር ነው፡፡ የፍትሕ ሥርዓቱ ለኃላፊነት የሚመጥኑ፣ ብቃት ያላቸው፣ በልምድ የበለፀጉና ለሕግ የበላይነት የሚማስኑ ዜጎች ያስፈልጉታል፡፡ ይህ ካልሆነ ግን የፍትሕ ሥርዓቱ ብቃት የሌላቸው ሙሰኞች መጫወቻ ይሆናል፡፡ ሕዝብ ፍትሕን በገንዘብ እንድገዛ እየተገደድኩ ነው በማለት በመንግሥት ላይ እሮሮ ሲያሰማ፣ የፍትሕ ሥርዓቱ አካላት ምንም እንዳልተፈጠረ ከሆኑ ያሳዝናል፡፡ ችግርን እየደበቁና እያድበሰበሱ መዝለቅ አይቻልም፡፡ ይልቁንም የፍትሕ ሥርዓቱን ችግሮች አንድ በአንድ ዘርዝሮ በማውጣት መፍትሔ መፈለግ ይጠቅማል፡፡ ‹ፖሊስ በምርመራ ወቅት ያሰቃያል፣ ዓቃቤ ሕግ እዚህ ግባ በማይባል ክስ ዜጎችን ያንገላታል፣ ዳኛው ያለ ጉቦ ንቅንቅ አይልም፣ ማረሚያ ቤት የሰብዓዊ መብት ጥሰት ይፈጽማል፣› ወዘተ. እየተባለ እስከ መቼ ጩኸት ይሰማል? በዚህ ዘመን እንዲህ ዓይነት ነውረኛ ነገሮች መስማት አያስከፋም ወይ? ዜጎች በሕግ የበላይነት ተማምነው ሥራቸውን ማከናወን ሲያቅታቸውና ሕዝቡም በፍትሕ ሥርዓቱ ላይ ያለው አመኔታ ሲጠፋ ማን ነው የሚጠቀመው? በዚህ ሁኔታስ እዚህ አገር ውስጥ መቼ ይሆን ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ መሠረት የሚጣለው? ይህ ችግር የሚያሳስባቸው አገር ወዳድ ዜጎች ድምፃቸውን ማሰማት አለባቸው፡፡ እስከዚያው ግን የፍትሕ ሥርዓቱ ምን እየሠራ እንደሆነ በግልጽ ይናገር!