Skip to main content
x
የፖለቲካ ሹማምንት ዲፕሎማትነት መበራከትና አንድምታው

የፖለቲካ ሹማምንት ዲፕሎማትነት መበራከትና አንድምታው

ከቀናት በፊት የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር) ኢትዮጵያን በውጭ አገር ለሚወክሉ አምባሳደሮች ሹመት ሰጥተዋል። በዚህም መሠረት በባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደርነት የተሾሙት አቶ ካሳ ተክለ ብርሃን፣ ወ/ሮ አስቴር ማሞ፣ ዶ/ር ሽፈራው ተክለ ማርያም፣ አምባሳደር ብርሃነ ገብረ ክርስቶስ፣ ፕሮፌሰር መርጋ በቃና፣ አቶ ዓሊ ሱሌይማን፣ ፕሮፌሰር አድማሱ ፀጋዬ፣ አምባሳደር ተበጀ በርሄ፣ አቶ መታሰቢያ ታደሰ፣ አቶ ሙሉጌታ ዘውዴና ወ/ሮ ሉሊት ዘውዴ ናቸው፡፡ አቶ እውነቱ ብላታ ደግሞ በአምባሳደርነት ተሹመዋል፡፡

ከእነዚህም መካከል ከሹመታቸው በፊት አቶ ካሳ ተክለ ብርሃን የፌዴራልና አርብቶ አደር ጉዳዮች ሚኒስትርና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቦርድ ሰብሳቢ፣ ዶ/ር ሽፈራው ተክለ ማርያም የትምህርት ሚኒስትር፣ አቶ ዓሊ ሱሌይማን የፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር፣ ፕሮፌሰር መርጋ በቃና የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ፣ አቶ እውነቱ ብላታ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ፣ እንዲሁም ፕሮፌሰር አድማሱ ፀጋዬ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ነበሩ፡፡ ወ/ሮ አስቴር ማሞ ደግሞ ፌዴራል መንግሥቱን፣ ኦሮሚያ ክልልንና ኦሕዴድን በተለያዩ ኃላፊነቶች ያገለገሉ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስትርና የመልካም አስተዳደር ክላስተር አስተባባሪ ተጠቃሽ ናቸው።

ለገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ በሚኒስትር ደረጃ ያሉትን ጨምሮ ከፍተኛ ባለሥልጣናቱን ከኃላፊነታቸው በማንሳት በአምባሳደርነት መሾም አዲስ ነገር አይደለም። ለአብነት ያህል ከዚያ ቀደም የቀድሞ የአማራ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ አያሌው ጐበዜ፣ የማዕድን ሚኒስትሯ ወ/ሮ ስንቅነሽ እጅጉ በኢሕዴድ መሥራችነትና ታጋይነት የአዲስ አበባ ከንቲባነትን ጨምሮ በተለያዩ የመንግሥት ተቋማትና የክልል ፕሬዚዳንትነት ያገለገሉት አቶ ኩማ ደመቅሳ፣ እንዲሁም ለ15 ዓመታት ገደማ የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር የነበሩት ወ/ሮ ሳሚያ ዘካሪያ በአምባሳደርነት ተሹመዋል::  

ይህ ዓይነት አሠራር አሁን በሥራ ላይ በሚገኘው ‹‹የውጭ ግንኙነት አገልግሎት አዋጅ ቁጥር 790/2005›› ሕጋዊ መሠረት ያለው ነው፡፡ አዋጁ በአንቀጽ ስምንት የዲፕሎማቲክ አገልግሎት ዘርፎችን ከፍተኛ፣ መካከለኛ፣ መጀመሪያ ደረጃና የቆንስላ አገልግሎት ምድብ በማለት በአራት ደረጃ ይከፍላቸዋል፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ የዲፕሎማቲክ አገልግሎት ምድብ ሁለተኛና ሦስተኛ ጸሐፊዎችና አታሼዎች የሚገኙበት ነው፡፡ በከፍተኛው ደረጃ ላይ ደግሞ አምባሳደሮች፣ ልዩ መልዕክተኞችና ሁለገብ አምባሳደሮች የሚመደቡበት ነው፡፡

የውጭ ግንኙነት አገልግሎት የፖለቲካ ሹመቶች ልዩ መልዕክተኞችንና ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደሮችን፣ አምባሳደሮችንና ሁለገብ አምባሳደሮች ያካታል፡፡ ልዩ መልዕክተኞችና ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደሮችና አምባሳደሮች በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 71(3) መሠረት በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት በፕሬዚዳንቱ ይሾማሉ፡፡

ይሁንና የፖለቲካ ሹመት አምባሳደሮችን ለመሾም ዋነኛ መንገድ እንዳልሆነ ከአዋጁ አጠቃላይ መንፈስ መረዳት ይቻላል፡፡ በአዋጁ መግቢያ እንደተገለጸው ይህ ሕግ የወጣው የውጭ ግንኙነት አገልግሎቱን ወጥነት ባለውና በተቀናጀ ተቋማዊ የአሠራር ሥርዓት ለማስተዳደር የሚያስችል የሕግ ማዕቀፍ መዘርጋት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፣ የተለያዩ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የሚያከናውኗቸውን ከውጭ ግንኙነት አገልግሎት ጋር የተያያዙ ተግባራትን በተቀናጀ መንገድ ለማከናወን የሚያስችል ሥርዓት መዘርጋት ጠቃሚ መሆኑ ስለታመነበትና ሙያዊ አቅሙ፣ ብቃቱና ክህሎቱ የዳበረና የተጣለበትን አገራዊ ተልዕኮ በታማኝነትና በቁርጠኝነት የሚወጣ ጠንካራ የሰው ኃይል ለማፍራት የሚያስችል፣ የሥራ ተነሳሽነትን የሚፈጥር፣ ግልጽነትና ተጠያቂነት የሰፈነበት ሙያዊ የውጭ ግንኙነት አገልግሎትን ዕውን ለማድረግ የሚያስችል ቀልጣፋና ውጤታማ የአደረጃጀት፣ የአሠራርና የአስተዳደር ሥርዓት መዘርጋት በማስፈለጉ ነው፡፡

በአንቀጽ ሦስት ላይ ከተዘረዘሩት የውጭ ግንኙነት አገልግሎት ሥልጣንና ተግባራት መካከል በሁለትዮሽና በባለብዙ ወገን ግንኙነቶች አማካይነት የፖለቲካ፣ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ትብብሮችን መፍጠርና ማጠናከር፤ በተለይም ቴክኖሎጂን በማሸጋገር፣ ንግድና ኢንቨስትመንትን በማስተዋወቅ፣ የባህል ግንኙነትና የቱሪዝም አድማስን በማስፋፋትና በማጠናከር የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅሞች ማረጋገጥና ማስከበር፣ ከልማት አጋሮች የሚገኙ አዳዲስ የፋይናንስ፣ የቴክኒክና የአቅም ግንባታ ድጋፎችን ማፈላለግ፣ በውጭ አገር የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንን መብቶችና ጥቅሞች ማስጠበቅ፣ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮዽያዊያንና የውጭ ዜግነት የያዙ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸውን ትስስር እንዲያጠናክሩና በኢትዮጵያ የልማትና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሒደት በንቃት ተሳትፈው ራሳቸውንና አገራቸውን እንዲጠቅሙ ማስቻል፣ የአገሪቱን መልካም ገጽታ በቀጣይነት ለመገንባትና ለልማት የተመቻቸ ሁኔታን ለመፍጠር በውጭ አገር የፐብሊክ ዲፕሎማሲና የሕዝብ ግንኙነት ሥራዎችን ማስተባበርና ማካሄድ ተጠቃሽ ናቸው፡፡

እነዚህን የውጭ ግንኙነት አገልግሎት ሥልጣንና ተግባራት በብቃት ለመወጣት በአብዛኛው ባለሙያ ዲፕሎማቶችን መጠቀም እንደሚመረጥ የፖለቲካ አዋቂዎች ይመክራሉ፡፡ አዋጁ ራሱ የዲፕሎማቲክ አገልግሎት ሠራተኞች ምልመላ ዕውቀትና ችሎታን መሠረት ባደረገ ግልጽ ውድድር መሠረት እንደሚፈጸም ይደነግጋል፡፡

ከዚህ አንፃር የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በተለይም በአፈጻጸማቸው ጥያቄ የሚቀርብባቸው በአምባሳደርነት መሾም መቀጠላቸውን ብዙዎች እየተቹት ይገኛሉ፡፡ እርግጥ መንግሥት ይህን ዕርምጃ አሁን ለመውሰድ ምን አነሳሳው? ወይም አስገደደው? ለሚለው እስካሁን በይፋ የተሰጠ መግለጫ የለም። ነገር ግን ኢሕአዴግ በአንድ ሚኒስቴር የአቅም ችግር የተስተዋለበት ሰው በሌላ ቦታ ስኬታማ ሥራ ማከናወን አይችልም ማለት አይደለም ሲል መከራከሪያ ያቀርባል።

በፖለቲካ ሹመት አማካይነት ዲፕሎማቶችን መመደብ በኢትዮጵያ ለበርካታ ዓመታት ይከናወን የነበረ ቢሆንም፣ ይህ ተግባር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተስፋፋ መምጣቱን የፖለቲካ ተንታኞች ይናገራሉ::

በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት በዕውቀታቸውና በችሎታቸው የላቁ ባለሙያዎች እየተመለመሉ በዲፕሎማትነት እንዲሠሩ የማድረጉ ዕርምጃ ተጠናክሮ፣ የአገሪቱን ገጽታ ለመቀየር ቁልፍ ሚና መጫወቱን የታሪክ ሰነዶች ያትታሉ፡፡ በንጉሡ ዘመን የውጭ ግንኙነት ትምህርትን በተለያዩ የውጭ አገሮች እንዲቀስሙ ተልከው የተመለሱ ኢትዮጵያውያን የተደራጀ የዲፕሎማሲ ሥራ ይከውኑ እንደነበር፣ በአሁኑ ወቅት በጡረታ ላይ የሚገኙ አምባሳደሮች ይናገራሉ::

የዲፕሎማሲ ሥራ በዕውቀትና በልምድ የተጠናከረ በመሆኑም በወታደራዊው ሥርዓት ወቅት ምንም እንኳን የርዕዮተ ዓለም መሠረታዊ ለውጥ ቢኖርም፣ አብዛኛዎቹ አምባሳደሮች በአገልግሎታቸው ቀጥለዋል፡፡ የእነዚህ አንጋፋ ዲፕሎማቶች አገልግሎት የኢሕአዴግ መንግሥት ወደ ሥልጣን ከመጣ በኋላ ግን ሙሉ በሙሉ መቀጠል አልቻለም፡፡ በምትኩ በደርግ አገዛዝ ተገፍተው በውጭ ይኖሩ የነበሩ ኢትዮጵያውያንና በኢሕአዴግ ትግል ውስጥ የተሳተፉ በአብዛኛው መመደባቸውን አንዳንድ ጽሑፎች ያስገነዝባሉ፡፡ በተለይ ከ1997 ዓ.ም. በኋላ በዲፕሎማሲ ሥራ ውስጥ የፖለቲካ ተሿሚዎች እየተበራከቱ መምጣታቸውንም ያሳያሉ፡፡ በዚህም ኢሕአዴግ በፓርቲ ሥራ ላይ እንዲሁም በመንግሥት ሥራ አስፈጻሚነት ለረዥም ጊዜ ያገለገሉ ግለሰቦች በዲፕሎማሲ ሥራው ላይ መመደብ ቀጥሏል::

ተንታኞች በአብዛኛው የዲፕሎማቶች አመዳደብ በዕውቀት፣ በችሎታና በውድድር ላይ የተመሠረተ እንዲሆን ያሳስባሉ፡፡ ኢትዮጵያ የፖለቲካ ሹመትንም በዲፕሎማሲ ሙያ ላይ የቆዩትንም በውጭ አገልግሎት ላይ ትመደባለች፡፡ ይሁንና በከፍተኛ የመንግሥት ሥልጣን ላይ የነበሩ ተሿሚዎች ከ‹‹ኬርየር ዲፕሎማት›› (የረዥም ጊዜ የዲፕሎማሲ አገልግሎት፣ ልምድና ዕውቀት ያላቸው) በተቃራኒ የአጭር ጊዜ ሥልጠናዎችን አግኝተው ወደ ሥራ ይገባሉ፡፡

የቀድሞው የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጌታቸው ረዳ በአንድ ወቅት፣ ‹‹በፖለቲካ የሚመደቡ አምባሳደሮች ለረዥም ጊዜ የመንግሥትን ፖሊሲ ሲያስፈጽሙ የቆዩ በመሆናቸው የአጭር ጊዜ የዲፕሎማሲ ሥልጠና ወስደው እንዲመደቡ ይደረጋል፡፡ ምክንያቱም የፖሊሲ ሥልጠና በአጭር ጊዜ ሰጥቶ አምባሳደር ማድረግ ስለማይቻል፤›› በማለት ለሪፖርተር ተናግረው ነበር፡፡

ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባልደረባ፣ ‹‹ኬርየር ዲፕሎማቶች በተለይ ጥልቅ የሆነ የዲፕሎማሲ ሥራ የሚጠየቅባቸው እንደ ተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በሚገኙባቸው አገሮች ይሾማሉ:: የመንግሥት ፍላጐት ለምሳሌ ዳያስፖራውን ማንቀሳቀስ ከሆነ በፖለቲካ ሹመት የሚመደብ አምባሳደር ይኖራል፤›› በማለት ያስረዳሉ::

ነገር ግን የፖለቲካ ተሿሚዎች ጥራትና ብዛት ላይ በርካታ ቅሬታዎች ይሰማሉ፡፡ ለአንዳንዶች አምባሳደርነት የተከበረ ሙያ ቢሆንም ከንጉሡ ዘመን ጀምሮ ቦታው ሰዎችን ገለል ማድረጊያ፣ የደከመን፣ ያኮረፈን ማባበያና ጡረታ ማውጫ ሆኖ ማገልገሉ አሳዛኝ እንደሆነ የሚናገሩ አሉ፡፡

የመድረክ የወቅቱ የውጭ ግንኙነት ኃላፊ ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ፣ ‹‹በሌሎች አገሮች የአምባሳደሮች ሹመት አገር የሚወክሉ ከፍ ያለ ብቃት ያላቸው ሰዎች የሚመለመሉበት ነው፡፡ በእኛ አገር ግን የፓርላማን እንኳን ይሁንታ የማያገኝ ነው፡፡ ሥልጣን ላይ ያለው ጠቅላይ ሚኒስትር ሰዎችን እንደፈለገ ወዲያ ወዲህ የሚያደርግበት ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ የአምባሳደርነት ሹመት መጦሪያና የውለታ መክፈያ ሆኗል፡፡  ከሥልጣን ማዕከል ገለል ማድረጊያ መሣሪያም ነው፤›› በማለት ለሪፖርተር  ተናግረዋል፡፡

የኢዴፓ መሥራችና የቀድሞ ሊቀመንበር አቶ ልደቱ አያሌውም የአምባሳደርነት ሹመት በአግባቡ ሥራ ላይ እየዋለ እንደማይገኝ ያምናሉ፡፡ ‹‹ብዙ ጊዜ በዲፕሎማት ደረጃ የሚሾሙ ሰዎች ጥሩ የሥራ ብቃት የሌላቸው፣ በጤናና በሌሎች ምክንያቶች ገለል እንዲሉ የሚፈለጉና ለሰጡት አገልግሎት እንደ ውለታ መክፈያ የሚቆጠሩላቸው ናቸው፡፡ ይኼ የሚያሳዝንና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየባሰበት የመጣ ችግር ነው፡፡ በዲፕሎማትነት የሚመደቡ ሰዎች በሙያው ብቃት ያላቸው መሆን አለባቸው፤›› ሲሉ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

አቶ ልደቱ ኢሕአዴግ ሁሌም ችግር በመጣ ቁጥር ባለሥልጣናቱን ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ማዛወሩ መፍትሔ አድርጎ ማየቱን በመተው ዘላቂ መፍትሔ እንዲሻ መክረዋል፡፡ ‹‹የፖለቲካ ሹመት አስፈላጊ እንደሆነ እገነዘባለሁ፡፡ ነገር ግን የፖለቲካ ታማኝነትና ወገንተኝነት ለሁሉም ነገር መሥፈርት መሆን የለበትም፡፡ ኃላፊነት በዕውቀትና በሥነ ምግባር መመዘን አለበት፡፡ ግለሰቦችን መቀያየር መፍትሔ  አይሆንም፡፡ አጠቃላይ ሥርዓቱ መዋቅራዊና የአስተሳሰብ ችግር ነው ያለበት፤››  ብለዋል፡፡

ለሌሎች አስተያየት ሰጪዎች ደግሞ የአምባሳደሮቹ ሹመት ከጥቂት ወራት በፊት የነበረውን ሹምሽር ያልተጠና ያስመሰለ ነው፡፡ ፕሮፌሰር በየነም በተመሳሳይ ዕርምጃው የተረጋጋ መንግሥት አለመኖሩን የሚያሳይ ነው ነው ሲሉ ተከራክረዋል፡፡ ‹‹የካቢኔ ሚኒስትሮቹ በቅርቡ የተሾሙ ናቸው፡፡ በወራት ውስጥ ሌላ ብወዛ መደረጉ በአገሪቱ የተረጋጋ መንግሥት እንደሌለ ማረጋገጫ ነው፤›› ብለዋል፡፡

የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መርጋ በቃና በአምባሳደርነት መሾማቸው በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ላይ ለሚነሳው የገለልተኝነት ጥያቄ ማረጋገጫ አድርገው ያዩትም አሉ፡፡ ፕሮፌሰር በየነ፣ ‹‹ፕሮፌሰር መርጋ ገለልተኛ እንዳልነበሩ በጉልህ ይታይ ነበር፡፡ ፍርደ ገምድል ውሳኔ ሲያሳልፉና በደንታ ቢስነት ብዙ ጥፋት ሲያጠፉ የነበሩ ናቸው፤›› ብለዋል፡፡

አቶ ልደቱ ግን የምርጫ ቦርድ ችግር ከአንድ ግለሰብ ጉዳይ የዘለለ እንደሆነ በማስታወስ፣ የፕሮፌሰር መርጋ ሹመትን የገለልተኝነት መለኪያ ማድረግ ስህተት ነው ሲሉ ሞግተዋል፡፡ ‹‹በእኔ አመለካከት የምርጫ ቦርድ ጉዳይ የአንድ ግለሰብ ጉዳይ አይደለም፡፡ እንዲያውም የምርጫ ቦርድ ዋና ኃላፊ አጠቃላይ ምርጫውን በማስፈጸም ረገድ ያላቸው ሚና ያን ያህል አይደለም፡፡ የምርጫ ቦርድ የገለልተኝነት ጉዳይ ከላይ እስከ ታች ያለ ነው፡፡ ችግሩ ተቋማዊ ነው፤›› ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡

አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች የትምህርት ሚኒስትሩ፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንትና የቦርድ ሰብሳቢው አንድ ላይ መነሳት የትምህርት ዘርፉ በአጠቃላይ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ደግሞ በተለይ ችግር እንዳለባቸው ማሳያ እንደሆነ ይጠቅሳሉ። ፕሮፌሰር በየነ፣ ‹‹አንጋፋው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሒሳቡን ባለማወራረዱ በከፍተኛ ሁኔታ ተጠያቂነት ያልሰፈነበትና በዚህ ረገድ ብቃት ያጣ ነበር፡፡ የቦርዱ ሰብሳቢ፣ፕሬዚዳንቱና ሚኒስትሩ መነሳታቸው ከዚህ ጋር የተያያዘ ይመስለኛል፡፡ ለዚህም የተሰጣቸውን አዲሱን ኃላፊነት ሹመት አድርጌ አልቆጥረውም፡፡ ችግሩ ግን በሌሎች ዩኒቨርሲቲዎችም የሚስተዋል ነው፤›› ሲሉ ከዚሁ ግምገማ ጋር እንደሚስማሙ አመልክተዋል፡፡

አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች ግን አገሪቱ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአስተዳደር ረገድ ከገጠማት ዘርፈ ብዙ ችግሮች አኳያ ማን ተነሳ ሳይሆን ማን ነው የሚተካው የሚለው ይበልጥ አሳሳቢ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡