Skip to main content
x
የፖላንድ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ የትራክተርና የሶፍትዌር ገበያዎች ውስጥ እየተንቀሳቀሱ ነው

የፖላንድ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ የትራክተርና የሶፍትዌር ገበያዎች ውስጥ እየተንቀሳቀሱ ነው

  • ትራክተር አምራቹ ኡርሱስ 1,500 ትራክተሮቹ በሜቴክ መገጣጠማቸውን ይፋ አድርጓል
  • የፖላንድ ፕሬዚዳንት ለፀጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባልነት የአፍሪካን ድጋፍ ጠይቀዋል

በፖላንድ ፕሬዚዳንት አንድሬ ዱዳ የተመሩ ኩባንዎች ከኢትዮጵያ አቻዎቻቸው ጋር የንግድ ትስስር ለመፍጠር ፍላጎት እንዳላቸው ሲያስታውቁ፣ በተለይም በትራክተርና በሶፍትዌር አምራችነት የሚታወቁ ሁለት ኩባንያዎች ላለፉት ሦስት ዓመታት ሲያደርጉ የቆዩትን እንቅስቃሴ እንደሚያጠናክሩ አስታውቀዋል፡፡

እ.ኤ.አ. በ2013 ወደ ኢትዮጵያ ከመጡና ከኢትዮጵያ አቻዎቻቸው ጋር የንግድ ግንኙነት ከፈጠሩ መካከል ኡርሱስ ኤስ.ኤ. የተባለው ትራክተር አምራች ኩባንያ አንዱ ነው፡፡ ከሦስት ዓመታት በፊት ከብረታ ብረትና ኢንጂነሪግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ጋር ባደረገው ስምምነት መሠረት የ90 ሚሊዮን ዶላር ዋጋ ያላቸውን የ3,000 ትራክተሮች አቅርቦት ስምምት ማድረጉን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ የሁለቱ ኩባንያዎች ስምምነት ከትራክተር አቅርቦት ባሻገር የአቅም ግንባታና የቴክሎጂ ሽግግርን ያካተተ በመሆኑ በሺሕ የሚቆጠሩ የኮርፖሬሽኑ ባለሙያዎች ፖላንድ በሚገኘው የኡርሱስ ትራክተር ማምረቻ ፋብሪካ ሥልጠና እንደተሰጣቸው፣ በኡርሱስ ኩባንያ የውጭ ገበያዎች ትብብር ምክትል የንግድ ዳይሬክተር ሚካል ኒዮርስኪ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

እንደ ሚስተር ሚካል ማብራሪያ፣ ኡርሱስ ለሜቴክ ባቀረቸው ትራክተሮች ብዛት 1,500 ደርሰዋል፡፡ ቀሪዎቹን ጨምሮ በሺዎች የሚቆጠሩ ተጨማሪ ትራክተሮች አገር ውስጥ እንዲገጣጠሙ ለማቅረብ የሚያስቸለው የገበያ ዕድል እንዳለ አስታውቀዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ሜቴክ በዓመት 500 ትራክተሮችን የመጋገጠም አቅም እንዳለው ሲታወቅ ይህ ቁጥር ግን እንደገበያው ሁኔታ ከዚህም በላይ ሊጨምር ወይም ዝቅ ሊል የሚችልባቸው አጋጣሚዎች እንደሚኖሩም ተጠቅሷል፡፡

ትራክተር አምራቹ ከሜቴክ ባሻገር ከስኳር ከርፖሬሽን ጋር ባደረገው ስምምነት መሠረትም እስካሁን እስከ 280 የፈረስ ጉልበት ያላቸው 200 ትራክተሮችን እንዳቀረበ ኃላፊው ገልጸዋል፡፡ ለስኳር ልማት ሥራዎች እንዲስማሙ ተደርገው የተፈበረኩት ትራክተሮች ቁጥር ወደ ፊት እንደሚጨምርም ሚካል ጠቅሰዋል፡፡ ከትራክተሮቹ በተጨማሪ ለጭነት ተግባር የሚውሉ 400 የሸንኮራና የስኳር ውጤቶች ማመላሻዎችን ለስኳር ኮርፖሬሽን ማቅረቡን አስታውቀዋል፡፡

እ.ኤ.አ. በ1893 በመመሥረት ከ120 ዓመታት በላይ ያስቆጠረው ኡርሱስ፣ በፖላንድ የስቶክ ገበያ ውስጥ ከተመዘገቡ ትላልቅ ኩባንያዎች ውስጥ ይመደባል፡፡ በፖላንድ ብቻ ከ1.5 ሚሊዮን በላይ ትራክተሮችን ለገበያ ማቅረብ እንደቻለና የመለዋወጫ መሣሪዎችንም እንደሚያቀርብ ሲታወቅ፣ በአማካይ እስከ 25 ዓመታት ለማገልገል የሚችሉ ትራክተሮችን በማምረት በአውሮፓ ከሚጠቀሱ ኩባንያዎች መካከል እንደሚመደብ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

ከኡርሱስ ባሻገር ከሦስት ዓመታት በፊት ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት የሶፍትዌር ምርቶችና አገልግሎቶቹን ለብሔራዊ የመረጃ መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ (ኢንሳ) እያቀረበ የሚገኘው ሌላኛው ኩባንያ አሴኮ ፖላንድ ግሩፕ የተባለው ሶፍትዌር አምራች ነው፡፡ ኩባንያው በአሁኑ ጊዜ ከኢትዮ ቴሌኮምና ከሌሎች መንግሥታዊ ድርጅቶች ጋር አብሮ ለመሥራት እንቅስቃሴ እያደረገ እንደሚገኝ ለሪፖርተር ያብራሩት፣ በአሴኮ ፖላንድ ኩባንያ የካፒታል ልማት ዘርፍ የኮርፖሬት ኃላፊው ሲዛሪ ሚክሳ ናቸው፡፡ እንደ ሚስተር ሲዛሪ ገለጻ፣ አሴኮ ወደ ኢትዮጵያ ገበያ ለመግባት በመዘግየቱ ምክንያት እንደ ኮር ባንኪን ያሉ የባንክና የመድን ድርጅቶች የሚጠቀሙባቸውን ሶፍትዌሮች የማቅረብ ዕድል ለጥቂት አምልጦታል፡፡ ይሁንና በሌሎች የቴክኖሎጂ ዘርፎች አገልግሎት ላይ የሚውሉ ምርቶችን ለማቅረብ በጨረታዎች እየተሳተፈ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

ከፖላንዱ ፕሬዚዳንት ዱዳ ጋር አብረው የመጡ ሌሎችም ኩባንያዎች ከኢትዮጵያ የንግድ ማኅበረሰብ አባላት ጋር የንግድ ግንኙነት ለመፍጠር የሚረዳቸውን ውይይት አካሂደው ወደ አገራቸው ተመልሰዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ፕሬዚዳንት ዱዳ ኢትዮጵያን ጨምሮ የአፍሪካ አገሮች በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ለፀጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባልነት፣ ፖላንድ ለምታደርገው ቅስቀሳ ድጋፍ እንዲሰጡ መጠየቃቸው ታውቋል፡፡ ከፕሬዚንት ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር) እንዲሁም ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ጋር ከኢንቨስትመንት ጉዳዮች ባሻገር ኢትዮጵያ ስለምትሰጣቸው ድጋፍ ከመነጋራቸውም ባሻገር፣ በተመድ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን እንዲሁም ከአፍሪካ ኅብረት ኃላፊዎችም ጋር ስለዚሁ ጉዳይ መነጋገራቸውን ከአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የተገኘው መረጃ ይጠቁማል፡፡

ፕሬዚዳንት ዱዳ ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ ያደረጉትን የሦስት ቀናት የሥራ ጉብኝት በሳምንቱ መጀመሪያ ቀናት አጠናቀው ለፖላንድ ድጋፍ ሊሰጡ ወደሚችሉ ወደ ሌሎች የአፍሪካ አገሮች ማቅናታቸው ታውቋል፡፡