Skip to main content
x
የ29ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ ውሳኔዎች ፋይዳ

የ29ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ ውሳኔዎች ፋይዳ

ሃምሳ አምስት አገሮችን በውስጧ የያዘችው አፍሪካ በድህነትና በኋላቀርነት ከሚታወቁት መካከል አንዷ ነች፡፡ ለዘመናት በአውሮፓውያኖች እጅ የቆየችው አፍሪካ የተፈጥሮ ሀብቷን በእነዚህ ቅኝ ገዥዎች እንደተዘረፈች ብዙ ተብሎበታል፡፡ አብዛኛው ሕዝብ በእርሻ ሥራ እንደሚተዳደሩ መረጃዎች ቢጠቁሙም፣ በኋላቀር አስተራረስ ሳቢያ የአኅጉሪቱን ዓመታዊ ዕድገት ከ3.4 በመቶ ከፍ ማድረግ አልተቻለም፡፡

አፍሪካ በቅኝ ገዥዎች ቀንበር ሥር ውላ በነበረበት ዘመን የአኅጉሪቷ ሕዝብ ጉልበት ከመበዝበዙ ባሻገር፣ የተፈጥሮ ሀብቷ ተዘርፏል፡፡ አፍሪካውያንም  በኢትዮጵያ አነሳሽነትና መሥራችነት በአኅጉሪቷ ውስጥ ያሉ አገሮች አንድ ድምፅ እንዲኖራቸውና ተሰሚነታቸው ከፍ እንዲል፣ የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን (አአድ) አቋቁመዋል፡፡ ‹‹አፍሪካ ስትበታተን ለባሰ ችግር ይዳርጋታል፣ አንድ ስንሆን ግን ድምፃችን ይሰማል፤›› ብለው ንግግር አድርገው የነበሩት የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ለአፍሪካ አንድነት ድርጅት ለአሁኑ የአፍሪካ ኅብረት መመሥረት ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል፡፡ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ድምፅ አንድ እንዲሆንና ተሰሚነት እንዲኖረው የተጫወተችው ሚናም ከፍተኛ ነው፡፡

አፍሪካ በኢትዮጵያ ዋነኛ አንቀሳቃሽነትና በጥቂት የአፍሪካ መሪዎች ደጋፊነት ድምጿን ለማሰማት የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን እ.ኤ.አ. በ1963 መሥርታለች፡፡ በወቅቱ የድርጅቱ መመሥረት ዋነኛ ዓላማ የነበረው የአፍሪካ አገሮች ዳግመኛ በቅኝ ገዥዎች እጅ እንዳይወድቁና አንድ የጋራ ድምፅ በመፍጠር ተሰሚነታቸውን ከፍ ለማድረግ ያለመ ቢሆንም፣ ከዚያን ጊዜ ወዲህ አኅጉሪቱ በማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ትስስር በመፍጠር አንድ የጋራ አኅጉራዊ ማኅበረሰብ ለመፍጠር እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

አገሮችን በጋራ በማስተሳሰር ችግሮችን ለመፍታት አሁንም ደፋ ቀና እያለ እንደሆነ የሚናገረው የአፍሪካ ኅብረት፣ በአኅጉሪቱ ውስጥ ለሚከሰቱ ችግሮች ዘላቂ መፍትሔ በማምጣቱ በኩል ውስንነቶች እንዳሉበት የዘርፉ ባለሙያዎች ሲናገሩ ይደመጣል፡፡ ለዚህ ችግር ዋነኛ መንስዔ ደግሞ የአፍሪካ መሪዎች የሥልጣን ጥም መሆኑን እንደ አንድ ምክንያት ያስቀምጣሉ፡፡ አኅጉሪቱን እንደ አውሮፓና ሌሎች አኅጉሮች በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊና በፖለቲካዊ ጉዳዮች ማፈርጠም ያልተቻለው፣ በውስን አምባገነን መሪዎች ሳቢያ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡

‹‹ለአንድ አገር ዕድገት ዋነኛ መሠረት የሆነው ዴሞክራሲ በአፍሪካ አይከበርም፤›› ሲሉ ናይጄሪያዊው ምሁር አካችኖ አካቾ እ.ኤ.አ. በ2004 ባቀረቡት ጥናታዊ ጽሑፍ ገልጸዋል፡፡ ‹‹አፍሪካ በተፈጥሮ ሀብት የታደለች ብትሆንም ወደ ሥልጣን የሚመጡ መሪዎቿ የሥልጣን ጥም ያለባቸው በመሆኑ ብቻ የዴሞክራሲን ፋይዳ ያቀጭጩታል፡፡ የዴሞክራሲ ፋይዳ ሲቀጭጭ ደግሞ ዕድገት ማስመዝገብ አይቻልም፡፡ ከአርባ ዓመት በላይ በሥልጣን ላይ መቆየት አንድ አገር የተለየ አስተሳሰብና አሠራር እንዳትከተል በሩን ይዘጋባታል፡፡ አፍሪካ ውስጥ የተለመደው ይህ ነው፤›› ሲሉ የአፍሪካ መሪዎች ለሥልጣን ያላቸውን ጥም ኮንነዋል፡፡

አፍሪካ ከጊዜ ወደ ጊዜ ችግሮቿ እየቀለሉና እየተቀረፉ እየሄዱ እንደሆነ እየተገለጸ ቢሆንም፣ በዚህ ግሎባላይዜሽን ዘመን አሁንም ማከናወን የሚገባት በርካታ የቤት ሥራዎች እንዳሉ ይነገራል፡፡ በደቡብ አፍሪካ ጆሃንስበርግ ዩኒቨርሲቲ የሚያስተምሩት ፕሮፌሰር ኒኮላስ ባቫኞ፣ ‹‹አፍሪካ ከውድድሩ ጋር አብራ መሮጥ ካልቻለች ዕጣ ፈንታዋ በእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ መውደቅ ነው፤›› ይላሉ፡፡

የአፍሪካን ድምፅ በአንድ አድርጎ በኃያላኑ ዘንድ የበለጠ ተሰሚነትን ለመፍጠር የተቋቋመው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ከዓመታት ወዲህ የአፍሪካ ኅብረት እየተባለ የሚጠራ ሲሆን፣ የአፍሪካን ችግር ለመፍታት የተቋቋመው ይህ ኅብረት ዋና መቀመጫው ኢትዮጵያ ነች፡፡ በአፍሪካ የነፃነት ተምሳሌት ሆና የምትቆጠረው ኢትዮጵያ የሃምሳ አምስት አገሮች ድምፅ ማረፊያና ዋነኛ መቀመጫ ነች፡፡

የአፍሪካ ኅብረት በመሪዎች ደረጃ በዓመት ሁለት ጊዜ ጉባዔ የሚያካሂድ ሲሆን፣ በጥር ወር የሚካሄደውን የኅብረቱ ጉባዔ ዘወትር ኢትዮጵያ ነው የምትስተናገደው፡፡ በሐምሌ ወር ላይ የሚካሄደውን ደግሞ መሪዎች በጥር ወር በሚያደርጉት ስብሰባ ላይ የሚወስኑት እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በሐምሌ ወር የሚካሄውን የዘንድሮውን ጉባዔ ታንዛኒያ እንደምታስተናግደው በጥር ወር አዲስ አበባ ላይ በተካሄደው ጉባዔ ላይ የተወሰነ ቢሆንም፣ ዝርዝር ጉዳይ ግልጽ ባይሆንም ኢትዮጵያ እንድታስተናግድ ተደርጓል፡፡

29ኛው የአፍሪካ ኅብረት ጉባዔ ለዘጠኝ ቀናት የዘለቀ ቢሆንም፣ በመሪዎች ደረጃ የተካሄደው ጉባዔ ግን ለሁለት ቀናት የቆየ ነበር፡፡ ከሰኞ ሰኔ 26 እስከ 27 ቀን 2009 ዓ.ም. በመሪዎች ደረጃ የተካሄደው 29ኛው የኅብረቱ ጉባዔ አዲስ አበባ በሚገኘው የኅብረቱ አዳራሽ ነው የተካሄደው፡፡ ከሃምሳ አምስት አባል አገሮች ሃያ አራት ፕሬዚዳንቶችን ብቻ ያሳተፈው የዘንድሮው ጉባዔ በተሳትፎ ደረጃ ዝቅ ብሎ መታየቱን በሥፍራው የነበሩ ባለሙያዎች ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ ከታንዛኒያ የመጣው ጋዜጠኛ ኢማኑኤል ፓማርኖ በ29ኛው የኅብረቱ የመሪዎች ጉባዔ ላይ አብዛኛዎቹ የአፍሪካ መሪዎች ባለመገኘታቸው ይኼኛው ክብደት ሊሰጠው እንደማይችል ተናግሯል፡፡

ከኬንያ እንደመጣች የምትናገረዋ ጋዜጠኛ   ቼቪሪቾ ኮኮቪያ ደግሞ፣ ‹‹የግብፅ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ የት አሉ?›› በማለት አስተያየቷን በጥያቄ ጀምራለች፡፡ የራሷን አገር ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታን ጨምሮ፣ የደቡብ አፍሪካ፣ የናይጄሪያና ሌሎች ተሰሚነት ያላቸው የአፍሪካ አገር መሪዎች ባለመገኘታቸው የአሁኑን ጉባዔ በተለየ መንገድ እንደምታየው ሐሳቧን ለሪፖርተር አጋርታለች፡፡

29ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ ላይ በአፍሪካ ትልቅ አቅም አላቸው የሚባሉ አገሮችን ፕሬዚዳንቶች አላሳተፈም፡፡ በአካባቢው ተሰሚነት አላቸው ከሚባሉት አገሮች መካከል አንዷ ግብፅ ስትሆን፣ የፕሬዚዳንቱ በጉባዔው ላይ አለመሳተፍ በምሥራቅ አፍሪካ ያለውን ቀውስ ለመፍታት በሚደረገው ጥረት ላይ የራሱ አሉታዊ ተፅዕኖ ሊኖረው እንደሚችል ተነግሯል፡፡ የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ጃኮብ ዙማ አለመገኘትም ጥያቄ አጭሯል፡፡ ሳዑዲ ዓረቢያ ኳታርን ከዓረብ ባህረ ሰላጤ አገሮች ስብስብ ማስወጣት ተከትሎ የሥጋት ምንጭ እየሆነ የመጣው የኤርትራና የጂቡቲ ጉዳይ ላይ እልባት ይሰጣሉ ተብለው ከሚጠበቁ አገሮች መካከል ኬንያ፣ ግብፅና ኢትዮጵያ ይገኙበታል፡፡ የኬንያና የግብፅ ፕሬዚዳንቶች በዚህ ጉባዔ ላይ አለመሳተፍ ኅብረቱ ይህንን ችግር ለመፍታት በሚንቀሳቀስበት ጊዜ እክሎች ሊገጥሙት እንደሚችሉ ግምቶች ተሰንዝረዋል፡፡

ባለፋ ሳምንት ሰኞ ዕለት ጉባዔው በተጀመረበት ወቅት የሃያ አራት የአፍሪካ አገሮች ፕሬዚዳንቶች፣ የፍልስጤሙን ራስ ገዝ አስተዳደር መሐሙድ አባስንና የሳዑዲ ዓረቢያን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጨምሮ የተለያዩ ክፍላተ አኅጉር ዲፕሎማቶች፣ ተወካዮችና ጋዜጠኞች ተገኝተዋል፡፡ 29ኛው የኅብረቱ ጉባዔ ‹‹ሀርነሲንግ ዘ ዲሞግራፊክ ዲቫይድድ ስሩው ኢንቨስትመንትስ ኢን ዘ ዩዝ›› በሚል መሪ ቃል ተካሂዷል፡፡

በመክፈቻው ዕለት የየአገሮች ፕሬዚዳንቶችና ተወካዮች ፕሮግራሙ ከመጀመሩ በፊት ዝግ ስብሰባ አድርገዋል፡፡ በወጣው ፕሮግራም መሠረት በአምስት ሰዓት መሪዎች ዝግ ስብሰባቸውን ጨርሰው በዋናው አዳራሽ በመገኘት 29ኛው የኅብረቱ የመሪዎች ጉባዔ በንግግር እንደሚከፈት ቢገለጽም፣ የመሪዎች ዝግ ስብሰባ የተጠናቀቀው ስድስት ሰዓት ተኩል ላይ ስለነበር በተጋባዥ እንግዶችና ጋዜጠኞች ዘንድ ከፍተኛ መዳከምና መሰላቸት ታይቶ ነበር፡፡

መሪዎች በወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ዝግ ስብሰባቸውን መጨረስ ያልቻሉት፣ ኅብረቱ ያለበትን የገንዘብ እጥረት ለመቅረፍ በሩዋንዳ ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ ሰብሳቢነት ተቋቁሞ የነበረው ቡድን ሪፖርት በሚቀርብበት ጊዜ በመሪዎች መካከል ስምምነት ላይ መድረስ አለመቻሉ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ሪፖርቱን ያቀረቡት የሩዋንዳ ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ ሲሆኑ፣ የአፍሪካን ኅብረት የፋይናንስ ችግር ለመቅረፍና የኅብረቱን የአሠራር ሥርዓት ለማሻሻል በቀረበው ሪፖርት ላይ  ውይይቶችና ክርክሮች መካሄዳቸውን ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡ በጣም ዘግይቶም ቢሆን የመሪዎች ዝግ ስብሰባ ተጠናቆ በ6፡45 ሰዓት ላይ የአገሮቹ ፕሬዚዳንቶችና ተወካዮቻቸው ወደ አዳራሹ መጥተዋል፡፡

በመክፈቻው ላይ ንግግር ያደረጉት የኅብረቱ ኮሚሽነር ሙሳ ፋቂ መሃማት፣ ‹‹አፍሪካን ካለባት ችግር እንታደግ እያልን ዘወትር እንናገራለን፡፡ እስከ ዛሬ ግን ተጨባጭ ለውጥ አላስመዘገብንም፡፡ ስለሆነም በዚህ ጉባዔና ወደፊት በምናደርጋቸው ውይይቶችና ስብሰባዎች የሚወሰኑ ውሳኔዎችን ቁርጠኛ ሆነን ልንተገብር ይገባል፤›› በማለት መሪዎች ከወሬ ያለፈ ተጨባጭ ለውጥ ሊያመጣ በሚችል ደረጃ መሥራት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2020 የጥይት ድምፅና ኮሽታ የማይሰማባትን አኅጉር ለመፍጠር የተሻለ ሥራ ማከናወን፣ በአጀንዳ 2063 ወጣቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ የተቀረፁ ፕሮግራሞችና የዘላቂ ልማት ግቦች ዕውን እንዲሆኑ መሥራት እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡ በአፍሪካ ዘላቂ የሆነ የሰላምና መረጋጋት እንዲኖር መሥራት ተገቢ እንደሆነ አክለዋል፡፡ ኮሚሽነሩ ከኳታር ቀውስ ጋር ተያይዞ በኤርትራና በጂቡቲ መካከል የተፈጠረው ውጥረትና የደቡብ ሱዳን ወቅታዊ ሁኔታ ኅብረቱን እንደሚያሳስበው ተናግረዋል፡፡

የጊኒ ፕሬዚዳንትና የአፍሪካ ኅብረት የወቅቱ ሊቀመንበር አልፋ ኮንዴ በበኩላቸው፣ በአፍሪካ ዋነኛ ችግር የሆነውን የወጣቶችን የሥራ ዕድል ፈጠራ አገሮች ትኩረት ሰጥተው መሥራት እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡ ‹‹አፍሪካውያን በአንድነት ከቆምን ሁሉን ማድረግ እንችላለን፡፡ ከአፍሪካችን የወጡት ኢትዮጵያዊው ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ደግሞ ለዚህ ምሳሌ ናቸው፤›› ብለዋል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ምክትል ዋና ጸሐፊ አሚና መሐመድ በበኩላቸው፣ ‹‹ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎች አገሮች ለስደተኞች በሮቻቸውን ክፍት በማድረግ ላከናወኑት ተግባር ምሥጋና ይገባቸዋል፤›› በማለት ኢትዮጵያ ስደተኞችን በማስጠለል እያደረገች ያለችውን ተግባር አሞካሽተዋል፡፡ ሌሎች የአፍሪካ አገሮችም የእሷን ተሞክሮ በመውሰድ በሰብዓዊነት ሥራቸውን እንዲያከናውኑ አሳስበዋል፡፡

በጉባዔው ላይ የፍልስጤም ራስ ገዝ አስተዳደር ሙሐመድ አባስ ባደረጉት ንግግር፣ አፍሪካ ከእስራኤል ጋር ያላትን ግንኙነት ከፍልስጤም ጋርም እንዲኖራት ተማፅነዋል፡፡ ፍልስጤምና እስራኤል ለበርካታ ዓመታት ቀውስ ውስጥ መሆናቸው ይታወቃል፡፡ የፍልስጤም ፕሬዚዳንት በኅብረቱ ጉባዔ ላይ እንደናገሩት፣ ከእስራኤል ጋር ያለውን ግጭት አፍሪካ እንድታሸማግልና ገለልተኛ ሆና ችግሩ እንዲፈታ ከፍተኛ ሚና መጫወት እንዳለባት ጠይቀዋል፡፡

29ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ በአዲስ አበባ ሲካሄድ ብዙ አንድምታዎች እንዳሉት የፖለቲካ ተንታኞች ይናገራሉ፡፡ ኢትዮጵያ ከአንድ ዓመት በላይ ከቆየችበት ሁከት ተረጋግታ ረብሻ ነፃ ሆና ይህንን አኅጉር አቀፍ ጉባዔ ማካሄዷ ትልቅ እመርታ እንደሆነ የተናገሩ ነበሩ፡፡ በተለይ በአስቸኳይ አዋጅ ሥር ሆና ይህንን ጉባዔ መወጣቷ አሁን በትክክለኛ መንገድ ላይ የምትገኝ መሆኗ ማሳያ እንደሆነ፣ አንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከፍተኛ ባለሙያ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ ‹‹ከዚህ ቀደም በነበረብን ቀውስ የእኛ ጠላት የነበሩ አገሮች በደስታ ተውጠው ኢትዮጵያ ትፈርሳለች ይሉ ነበር፡፡ እኛ ግን ሁሌም ባለን የጠራ ፖሊሲ ወደፊት እንጂ ወደኋላ የማንሄድ አገር ሆነናል፤›› ብለዋል፡፡

ለዘጠኝ ቀናት በአዲስ አበባ ሲካሄድ የነበረው የአፍሪካ ኅብረት ጉባዔ ማክሰኞ ሰኔ 27 ቀን 2009 ዓ.ም. ከሰዓት በኋላ ሲጠናቀቅ ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት የኅብረቱ ኮሚሽነር ሙሳ ፋኪ መሃማት፣ የአሁኑ የአፍሪካ ኅብረት ጉባዔ በሦስት ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ያተኮረ እንደነበር ገልጸዋል፡፡ የመጀመሪያው አጀንዳ ኅብረቱን እንደገና ማደራጀት የተመለከተ ሲሆን፣ ይህንን ጉዳይ ተፈጻሚ ለማድረግ በዋና ሰብሳቢነት ተሰይመው የነበሩት የሩዋንዳ ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ በኅብረቱ የመሪዎች ጉባዔ ላይ ፕሮግራሙ በይፋ ከመጀመሩ በፊት የየአገሮች ፕሬዚዳንቶች ባካሄዱት ዝግ ስብሰባ ላይ ሪፖርታቸውን አቅርበዋል፡፡ ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ በሪፖርታቸው ካቀረቡት የማሻሻያ ፕሮግራም አንዱ፣ ኅብረቱ ዓመታዊ በጀቱን አባል አገሮች በሚያዋጡት ገንዘብ እንዲሸፈን የሚል ውሳኔ እንደሆነ መረጃዎች አመልክተዋል፡፡  የአፍሪካ ኅብረት በበጀት ራሱን አለመቻሉና የሌሎች ጥገኛ መሆኑ፣ የአባል አገሮች መዋጮ አለመክፈልና ዳተኝነት ለህልውናው አሥጊ እንደሆነ በተደጋጋሚ ተነግሯል፡፡

በዚህ ርዕስ ውስጥ ትኩረት ተሰጥቶት የነበረው ሌላው ጉዳይ በአኅጉሪቱ ውስጥ ነፃ የንግድ ቀጣና እንዲኖር የሚፈቅድ ሪፖርት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ግን ሳትቀበለው ቀርታለች፡፡ የነፃ ንግድ ቀጣናውን የሚመሩት የኒጀር ፕሬዚዳንት ማሃማዱ ኢሱፍ በሰጡት መግለጫ፣ ድርድሩ በአባል አገሮች የንግድ ሚኒስትሮችና በመሪዎች ደረጃ ሲካሄድ መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡ ድርድሩ አገሮች እስከ 90 በመቶ የሚደርሱ የሌሎች አገሮችን ምርቶች ከቀረጥ ነፃ ወደ አገራቸው እንዲያስገቡ ለማስቻል የሚደረግ መሆኑንም አውስተዋል፡፡ የአገሮችን ምርቶች ወደ አባል አገሮች ያለቀረጥ እንዲገባ የሚያደርገው የኅብረቱ ዕቅድ ግን፣ ሳይቀረጥ በነፃ ይገባል በተባለው የምርት መጠን ላይ ከተለያዩ አገሮች ተቃውሞ እንደገጠመው ለማወቅ ተችሏል፡፡ ተቃውሞ ካነሱ አገሮች መካከል አንዷ ኢትዮጵያ እንደሆነችም ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ማክሰኞ ሰኔ 27 ቀን 2009 ዓ.ም. ከጉባዔው መጠናቀቅ በኋላ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቀዋል፡፡ ኢትዮጵያ፣ ሱዳን፣ ጂቡቲና ሌሎች ሰባት አገሮችን ጨምሮ ይህንን ውሳኔ እንደተቃወሙት ለማወቅ ተችሏል፡፡ በአገሮች መካከል ተመጣጣኝ ኢኮኖሚ አለመኖርና የተሻለ ኢኮኖሚ ያላቸው አገሮች የሚጭኑትን ሸክም ለመሸከም የሚከብድ በመሆኑ፣ ላለመስማማታቸው እንደ ምክያት ሆኖ መቅረቡን ለማወቅ ተችሏል፡፡

ሁለተኛው አጀንዳ የአፍሪካ ወጣቶች ከስደት ይልቅ በአገራቸው ውስጥ ሠርተው የሚያድጉበትን ሁኔታ ለማመቻቸት የቀረበ የውሳኔ ሐሳብ ነው፡፡ ይህንን የውሳኔ ሐሳብ ሁሉም ተሳታፊ አገሮች በሙሉ ድምፅ እንዳፀደቁት ታውቋል፡፡ አፍሪካ በተፈጥሮ ሀብቷ የታደለች ብትሆንም፣ የተፈጥሮ ሀብቷን በአግባቡ በመጠቀም ወጣቶችን ተጠቃሚ በማድረግ በኩል ክፍተቶች እንዳሉ ተጠቁሟል፡፡ አፍሪካ የወጣቱን ዕውቀትና ኃይል በመጠቀምና ተገቢ የሆነ አመራር በመስጠት፣ የወጣቶችን ችግር መፍታት እንደሚገባት ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡

ሦስተኛው አጀንዳ ደግሞ በአፍሪካ የሚስተዋለውን የፀጥታ ችግር መፍታትን የተመለከተ ነው፡፡ እ.ኤ.አ. በ2020 አፍሪካ ምንም ዓይነት የተኩስ ድምፅ የማይሰማባት አኅጉር ለማድረግ ስምምነት ላይ መደረሱ ታውቋል፡፡ የኅብረቱ ኮሚሽነር በመክፈቻ ንግግራቸው ላይ ትኩረት ሰጥተው የተናገሩት አፍሪካን ከሽብርተኞችና ከእርስ በርስ ጦርነት፣ እንዲሁም ከጎረቤት አገሮች ጋር የሚፈጠር ግጭት የአኅጉሪቱ ዋነኛ መገለጫ መሆኑን ነው፡፡ የኅብረቱ አባል አገሮች ትኩረት ሰጥተውት መፍታት እንደለበትም አሳስበዋል፡፡ ኮሚሽነር ሙሳ ፋኪ እንደገለጹት፣ ኅብረቱ በመጨረሻ በአኅጉሪቱ ያለውን ግጭት ለመከላከል የሚያስችል አዲስ አሠራር መዘርጋቱን ገልጸዋል፡፡

በተደጋጋሚ የአፍሪካ ፈተና እንደሆነ የሚገለጸው የደቡብ ሱዳን፣ የሶማሊያ፣ በአሁኑ ወቅት ደግሞ የኤርትራና ጂቡቲ ጉዳይ ኅብረቱ ትኩረት ሰጥቶ የሚሠራባቸው እንደሆኑ ተገልጿል፡፡ በእነዚህ አገሮች የሚታየውን ግጭት ለመፍታት ግብረ ኃይል መቋቋሙንም አስታውቀዋል፡፡

የዓረብ ባህረ ሰላጤ አገሮች በኳታር ላይ በጣሉት ዕግድ የተነሳ ኳታር በኤርትራና በጂቡቲ መካከል አሰማርታው የነበረውን ጦር አስወጥታለች፡፡ የኳታር ጦር ሁለቱ አገሮች ይወዛገቡበት ከነበረው አካባቢ መውጣት ደግሞ ኤርትራንና ጂቡቲን አፋጥጧል፡፡ በአፍሪካ ኅብረት ሥር ሆኖ ይህንን ችግር ለመፍታት ተሰይሞ የነበረው የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት (ኢጋድ) እውነታ አፈላላጊ ቡድን ወደ ሥፍራው አቅንቶ ሁኔታውን ለማጣራት ቢሞክርም፣ ኤርትራ እሺ አለማለቷን የኢጋድ የወቅቱ ሊቀመንበር የሆነችውን ኢትዮጵያ በመወከል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡ የኢጋድ አባል አገሮች ውሳኔ ወደ አፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ ሄዶ በአፍሪካ ደረጃ መፈታት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

በኅብረቱ የመሪዎች ጉባዔ ላይ የተገኘችው ጂቡቲ አፍሪካ በሁለቱ አገሮች መካከል ባለው ድንበር ተጠባባቂ ኃይል እንዲያሰማራ ጠይቃለች፡፡ የአፍሪካ ኅብረት የሰላምና ደኅንነት ኮሚሽነሩ ኢስማኤል ቼሪጉዊ በሁለቱ አገሮች መካከል ያገረሸውን ቀውስ ለመፍታት፣ የሁለቱን አገሮች ፕሬዚዳንቶች በተናጠል ለማነጋገር መወሰናቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡ በሁለቱ አገሮች መካከል ያለው ውዝግብ ሥር የሰደደና ከአፍሪካ ውጪ ካሉ አገሮች ጋር የሚያያዝ በመሆኑ፣ በቀላሉ መፍትሔ ለማበጀት እንደሚከብድ የፖለቲካ ተንታኞች ይናገራሉ፡፡

በኅብረቱ 29ኛው የመሪዎች ጉባዔ ላይ የተገኙት የሳዑዲ ዓረቢያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አደል ቢን አህመድ አል ጁቤር የአፍሪካ አገሮች ከአገራቸው ጎን እንዲቆሙ ቅስቀሳ ሲያደርጉ መሰንበታቸውን ምንጮች ጠቁመዋል፡፡ ሳዑዲ ዓረቢያ የአፍሪካ አገሮች ከኳታር ጋር ያላቸውን ግንኙነት በይፋ እንዲያቋርጡ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሲያግባቡ መሰንበታቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡

ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) ጋር እንደመከሩና ኢትዮጵያ ከኳታር ጋር ያላትን ግንኙነት እንድታቋርጥ በይፋ መጠየቃቸውን ምንጮች ጠቁመዋል፡፡ ኢትዮጵያ ከዚህ በፊት ከኳታር ተመሳሳይ ጥያቄ ቀርቦላት፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ዳሳለኝ ኢትዮጵያ ሁለቱ ወገኖች በውይይት የተፈጠረውን ችግር እንዲፈቱ ማሳሰባቸው ይታወሳል፡፡ የኢትዮጵያ አቋም ከውጭ ግንኙነት ፖሊሲዋ እንደሚመነጭ መናገራቸው አይዘነጋም፡፡

የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርም በጉባዔው ላይ ተገኝተው ሃማስን እየረዳች ነው ያሏትን ኳታርን ለማግለል የአፍሪካ አገሮችን ሲያግባቡ መሰንበታቸውን ምንጮች ገልጸዋል፡፡ በኢትዮጵያ በኩል፣ ኢትዮጵያ ሁሌም በውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ላይ ተመሥርታ ከሌሎች አገሮች ጋር የሁለትዮሽ ግንኙነት እንደምትፈጥር የተገለጸ ሲሆን፣ ከኳታር ጋር ያለውን ግንኙነት ከማቋረጥ ይልቅ ኢትዮጵያ ሁለቱን ወገኖች ለማግባባት እንደምትንቀሳቀስ መገለጹ ተጠቁሟል፡፡

በቀይ ባህር በኩል ባለው ውዝግብ በአሁኑ ወቅት በቀጣናው የተለየ አሠላለፍ እየተፈጠረ መምጣቱ እየተገለጸ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ አጣብቂኝ ውስጥ መሆኗም ይሰማል፡፡ ኢትዮጵያና ኳታር ግንኙነታቸውን ካደሱ አጭር ጊዜ ቢሆንም፣ የሳዑዲ ዓረቢያ መንግሥት ግን በተደጋጋሚ ለኢትዮጵያ ጥያቄ ማቅረቡን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ኢትዮጵያ ደግሞ ገለልተኛነትን መምረጧ ነው የሚነገረው፡፡

29ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ ይህንን ሁሉ ችግር የመፍታት ኃላፊነት የተጣለባት ቢሆንም፣ የአሁኑ ጉባዔ በብዙ ነገሮች ለየት ያለ እንደነበር ሪፖርተር በቦታው ተገኝቶ ለማረጋገጥ ችሏል፡፡ የኅብረቱ ኮሚሽነር፣ ‹‹ጊዜው ከአሁን በኋላ የምናወራበት ሳይሆን የምንሠራበትና ተጨባጭ ለውጥ የምናመጣበት መሆን አለበት፤›› በማለት የኅብረቱን የዘንድሮ ጉባዔ ፋይዳ ገልጸዋል፡፡ ‹‹በአኅጉራችን ያለውን የሰላምና የፀጥታ ችግር ዛሬ መፍታት ካልቻልን ስማችንን ማደስ አንችልም፤›› በማለት፣ በአኅጉሪቱ የተጋረጡ ችግሮችን ጊዜ ሳይሰጥ መፈታት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

በበዚህ ጉባዔ ላይ ኢትዮጵያ ከተለያዩ የአፍሪካ አገሮች ጋር ከኅብረቱ ስብሰባ ጎን ለጎን የሁለትዮሽ ግንኙነት ያደረገች ሲሆን፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ከፍልስጤም ራስ ገዝ አስተዳደር ፕሬዚዳንት መሐሙድ አባስ ጋር ያደረጉት ውይይት የብዙዎችን ቀልብ ስቦ ነበር፡፡ በዝግ የተካሄደውን የሁለቱ አገር መሪዎች ስብሰባ ሪፖርተር የተከታተለ ሲሆን፣ የፍልስጤም ፕሬዚዳንት ኢትዮጵያ ከእስራኤል ጋር ባላት ግንኙነት ብዙም ደስተኛ እንዳልሆነች ለመገንዘብ ተችሏል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም፣ ‹‹እኛ ከአገሮች ጋር ግንኙነት የምንፈጥረው በውጭ ግንኙነት ፖሊሲያችን መሠረት ነው፡፡ የውጭ ፖሊሲያችን ደግሞ ከአንዱ ጋር ወዳጅ ስንሆን ከሌላው ጋር ጠላት እንድንሆን አያዝም፡፡ ይህ ችግር በእናንተ መካከል እንጂ የእኔ አገርና ሕዝብ ከእስራኤልም ሆነ ከእናንተ ጋር ያለንን ግንኙነት አያሻክርም፡፡ ይህን ላረጋግጥልዎት እወዳለሁ፤›› በማለት ምላሽ ሰጥተዋቸዋል፡፡

በዚህ ጉባዔ ላይ እንደ አዲስ ሆኖ በማጠቃለያ ላይ የተበሰረው ለቀድሞዎቹ የኢትዮጵያ መሪዎች ለቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴና ለቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ፣ በአፍሪካ ኅብረት ቅጥር ግቢ ውስጥ የመታሰቢያ ሐውልት ለማቆም ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡ ይህንንም ሐሳብ ያቀረበችው ጋና ናት፡፡

29ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ በአኅጉሪቱ በተለይም በምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ያለውን ችግር ለመፍታት ቃል የተገባበት እንደሆነ ተገልጿል፡፡ የአፍሪካን ችግሮች ጊዜ ሳይሰጡ በመፍታት አኅጉሪቱን እ.ኤ.አ. በ2063 ያቀደችውን ዕቅድ ግብ ለመምታት ቁርጠኛ አቋም መያዟ ተጠቁሟል፡፡

የኅብረቱ ከፍተኛ አመራሮች ይህን ይበሉ እንጂ የአፍሪካ መሪዎች በሰላማዊ መንገድ ከሥልጣን እየወረዱና ለወጣቱ አርዓያ እየሆኑ ካልመጡ፣ አሁንም ውኃ ቅዳ ውኃ መልስ ነው የሚሆነው እያሉ የሚሞግቱ አሉ፡፡ አፍሪካውያን ለአፍሪካውያን በመቆም በመካከላቸው ያለውን እሴት በመጨመርና ለችግሮች በጋራ በመቆም ወደፊት መራመድ እንደሚቻል ግን ከመግለጽ አልተቆጠቡም፡፡

በአፍሪካ ኅብረት አዳራሽ የተገኙ ዲፕሎማቶች፣ ጋዜጠኞች፣ የፖለቲካ ተንታኞችና ሌሎች በአብዛኛው ሲናገሩ የተደመጡት አፍሪካ ከመቼውም ጊዜ በላይ ትልቅ ነገር እንደሚያስፈልጋት ነው፡፡ በአኅሪቱ ውስጥ የሚታየው ድህነት፣ ግጭት፣ ሽብርተኝነትና የመሳሰሉት አሁንም ጥያቄ እያስነሱ ነው፡፡ አፍሪካ ወደፊት ተስፋ ያላት አኅጉር እንድትሆን ከተፈለገ የዴሞክራሲና የሰብዓዊ መብት ጉዳይም ትልቅ ትኩረት እንደሚሻ ተደምጧል፡፡ ከዚህ አንፃር የመሪዎች ጉባዔ ምን ያህል ተሳክቶለታል መባል እንዳለበትም ተወስቷል፡፡ አፍሪካዊያን ለዘመናት ከቆዩበት ድህነትና ኃላቀርነት ለማላቀቅ፣ አኅጉሪቱን ደግሞ የወደፊቷ ተደማጭ ኃይል ለማድረግና በኢኮኖሚ ለማበልፀግ ጠንካራና ትክክለኛ ዕርምጃዎች መውሰድ እንዳለባቸው የብዙዎች ሐሳብ ነው፡፡