Skip to main content
x

ዲላ ዩኒቨርሲቲ አልሞተም!

  ቀዳሚ የመረጃ ምንጭ ነኝ የሚለው አዲስ ቴሌቪዥን መስከረም 13 ቀን 2010 ዓ.ም. በዕለታዊ የዜና ማስታወሻ ፕሮግራሙ በምሥልና በጽሑፍ አስደግፎ ካቀረባቸው ዜናዎች መካከል “የጂማ፣ የባህር ዳርና የመቀሌ ዩኒቨርሲቲዎች በመምህራን የትምህርት ልቀት ማዕከላት እንዲሆኑ ተመረጡ” የሚለው አንዱ ነበር፡፡

      የጽሑፍ ዜናውን ሳነብ ዓይኔ የሚፈልገው ዲላ የሚለውን ስለነበር ዜና አንባቢው በድምፅ የተናገረውንና ከዚሁ ዜና ጋር በተያያዘ እንዲያስረዱ የቀረቡት የትምህርት ሚኒስትሩ ጥላዬ ጌቴ (ዶ/ር) የተናገሩትን በደንብ አልሰማሁም፡፡

      የጽሑፍ ዜናውን ግን ከአንዴም ሁለቴ፣ ሦስቴ ስላነበብኩት ተመረጡ ከተባሉት ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ዲላ ዩኒቨርሲቲ እንዳልተካተተ እርግጠኛ ነበርኩ፡፡ ዲላ ዩኒቨርሲቲ ለምን አልተመረጠም? ለመሆኑ የመምረጫ መስፈርቱ ምን ቢሆን ነው ዲላ ዩኒቨርሲቲ ዝቅተኛ ውጤት ያገኘው? ለመሆኑ በደቡብ ክልል ለተሰባሰቡ ዩኒቨርሲቲዎች ለመምህራን ትምህርት የልቀት ማዕከልነት ከዲላ ዩኒቨርሲቲ ውጪ ተመረጡ ከተባሉት ከሦስቱ የትኛው እንዲሆን ታስቦ ነው? ጂማ ዩኒቨርሲቲ ከሆነ የታሰበው፣ በምዕራብና በደቡብ ለሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች እንዴት ማዕከል ሊሆን ይችላል? በመሀል ኢትዮጵያ ዙሪያ ለሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲንና የኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ የትኛው ዩኒቨርሲቲ የመምህራን ትምህርት የልቀት ማዕከል ሊሆን ነው? በምሥራቅ ኢትዮጵያ ለሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎችስ? ኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ በቀጥታ በትምህርት ሚኒስቴር ሥር ሳይሆን፣ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳድር ትምህርት ቢሮ ሥር የሚተዳደር በመሆኑ ሊሆን ይችላል ያልተመረጠው፡፡ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ግን እንዴት አልተመረጠም? የሚሉ ጥያቄዎችን አከታትዬ ሳነሳ ስጥል ብቆይም፣ ወደ መጨረሻ ላነሳኋቸው ጥያቄዎች እኔን ማን ነው ጠያቂና መልስ አፈላላጊም ያደረገኝ? በማለት ትኩረቴን ዲላ ዩኒቨርሲቲ ለምን አልተመረጠም? ወደሚለው አደረኩ፡፡

      ለአንድ የሥራ ባልደረባዬ እንዲህ የሚል የስልክ መልዕክት ጻፍሁ፡፡ “እንዲህ ዓይነት ዜና ሰምቼ በጣም ተረብሼና አዝኜ ነው ይኼን የስልክ መልዕክት የላኩልህና ስለ ጉዳዩ ምን የምታውቀው ነገር አለ?”፡፡ ላቅርበኩለት ጥያቄም በስልክ ያወጋኝ ለዲላ ዩኒቨርሲቲ አለመመረጥ ምክንያት ሊሆኑ የሚችሉ ጥርጣሬዎችን ነበር፡፡ ዲላ ዩኒቨርሲቲ ላመመረጡ ምናልባት ለአምስት ቀናት በተካሔደው ውይይታችን ወቅት በዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት፣ በትምህርትና ሥነ ባህርይ ተቋም ኃላፊ ወይም ዳይሬክተሩ መካከል አለመግባባት እንደነበረ በውይይቱ ካደረጉት ጭቅጭቅና ክርክር መረዳት ችለናል፡፡

      በመጨረሻ የዩኒቨርሲቲያችን መምህራን ትምህርቱ ከሞተ እንደቆየ ፕሬዚዳንቱ ብቻ ሳይሆኑ ሌሎች የስብሰባው ተሳታፊዎችም ገልጸው፣ ዲላ ዩኒቨርሲቲ የመምህራን የትምህርት ልቀት ማዕከል ለመሆን እንደማይችልና እንደማይገባው ስምምነት ላይ ባይደረስም፣ ይኼን ሐሳብ የሚያራምዱ በርካቶች ስለነበሩ በአብላጫ ድምፅ ተወስኖ ሊሆን ይችላል የሚል ማብራሪያ ሲሰጠኝ የበለጠ ተናደድኩ፡፡ አዘንኩ፡፡ በዚህ የስህተት ውሳኔ ምክንያት እኔ ብቻ ሳልሆን፣ ሁሉም የዲላ ዩኒቨርሲቲ ምሩቃን አብዛኛው የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ እንዲሁም ስለ ዲላ ዩኒቨርሲቲ ዝና በተለይም በመጀመርያዎቹ አሥር ዓመታት የትምህርት ጥራትን ጠብቆ አቅም ያላቸው፣ ተወዳዳሪ ምሩቃንን ያፈራ ተቋም ስለመሆኑ የሚያውቁ ሁሉ  ሊያዝኑ እንደሚችሉ እርግጠኛ ነኝ።

      ካነሳኋቸው ጥያቄዎች በተጨማሪ እንዴት በግለሰቦች አለመግባባትና ጭቅጭቅ ምክንያት ለዘመናት የተደከመበትና ሲገነባ የቆየ ተቋም በአንዴ መልካም ሥራውንና ስሙን ያጣል? ዕውቅና ይነፈጋል? እንዲፈርስ ይደረጋል? እንዴት ዩኒቨርሲቲውን የሚጎዳ ታሪካዊ ስህተት ይሠራል? የሚሉ ጥያቄዎችን በማንሳት እንቅልፍ አልወስድ ስላለኝ፣ ይኼን በጣም ትልቅ ስህተት እንደ ዜጋ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ይፋ ማድረግ እንዳለብኝ በማመን፤ ትምህርት ሚኒስቴርም የማስተካከያ ዕርምጃ ይወስድ ይሆናል በሚል ተስፋ ይኼን ለመጻፍ ተነሳሁ፡፡

      በአገሪቱ የመምህራን ትምህርት ሥልጠና ታሪክ በግንባር ቀደምትነት ከሚጠቀሱ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በኋላም ወደ ዩኒቨርሲቲ ደረጃ ካደጉት የቀድሞው የኮተቤ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ የአሁኑ የኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ የሚጠቀስ ነው፡፡ የባህር ዳሩ የመምህራን ትምህርት ኮሌጅ (ፔዳጎጂ) በአጭሩ ፔዳ በመባል የሚታወቀውና የአሁኑ ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ በቀደምትነት ይጠቀሳሉ፡፡

      ከእነዚህ ቀደምት ኮሌጆች በመከተል ከሁለት አሥርታት በፊት በ1989 ዓ.ም. በሁለት ፋኩልቲዎች (የመምህራን ትምህርት ፋኩልቲና የጤና ሳይንስ ፋኩልቲ) በመምህራን ትምህርት ፋኩልቲ በዲግሪ መርሐ ግብር በስምንት የተለያዩ የትምህርት መስኮች መምህራንን ማሠልጠን የጀመረው የቀድሞው የዲላ መምህራን ትምህርትና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ፣ የአሁኑ ዲላ ዩኒቨርሲቲ ነው፡፡ ይህ ኮሌጅ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ በርካታ መምህራንን በመደበኛውና በተከታታይ የትምህርት ፕሮግራሞች በማሠልጠን አገሪቱ የነበረባትን የሰው ኃይል ችግር በተለይም የሁለተኛ ደረጃ መምህራንን እጥረት በመቅረፍ ረገድ ኃላፊነቱን ተወጥቷል፡፡ እየተወጣም ይገኛል፡፡

      በ2000 ዓ.ም. በአሶሳ ከተማ በተካሄደው የትምህርት ጉባዔ፣ ዲላ ዩኒቨርሲቲ በመምህራን ትምህርት ምርጥ ተብሎ መመረጡና መሸለሙ ይታወሳል። በቅርቡ በአገሪቱ ‹‹Post Graduate Diploma Training›› ማለትም በሌላ መስክ የመጀመርያ ዲግሪያቸውን ካገኙ በኋላ አስተማሪ መሆን የሚፈልጉትን በመቀበል የማስተማር ዘዴ መሠረት ኮርሶችን በመስጠት የመምህርነት ማረጋገጫ ሰርተፍኬት ከሚሰጡ ስድስት ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ ዲላ ዩኒቨርሲቲ መሆኑም ኃላፊነቱን በሚገባ እየተወጣ እንደሚገኝ ያሳያል፡፡

      የትምህርትና ሥነ ባህርይ ኢንስቲትዩቱም ከአሥር በላይ ሦስተኛ ዲግሪ (PhD) ያላቸው መምህራን የሚገኙበት በመሆኑ፣ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን መምህራን በመደበኛውና በተከታታይ የትምህርት ፕሮግራሞች በድኅረ ምረቃ ፕሮግራሙ በሁለተኛ ዲግሪ ተቀብሎ በማስተማር አስመርቋል፡፡ እያስተማረም ይገኛል፡፡ የዲላ ዩኒቨርሲቲ የመምህራን ትምህርት እንዲህ እየተጠናከረና እየተስፋፋ ባለበት ወቅት ነው እንግዲህ የሞቱ ዜና እየተናፈሰ የሚገኘው፡፡

      ለመሆኑ የዲላ ዩኒቨርሲቲ መምህራን ትምህርት ሞቷል የሚሉት መቼ እንደሞተ፣ እንዴት እንደሞተ፣ ማን እንደገደለው፣ አሟሟቱ በድንገተኛ አደጋ ወይስ በባለሙያዎችና በዩኒቨርስቲው ከፍተኛ ኃላፊዎች እገዛ ሲደረግለት ቆይቶ ከአቅም በላይ በመሆኑ ይሆን የሞተው? ለእነዚህ ጥያቄዎች ወንጀል መርማሪ ፖሊስ ሳይሆን፣ የትምህርት ባለሙያዎችና የሚመለከተው ትምህርት ሚኒስትር ሊመረምሩ፣ ሊፈትሹ፣ ሊያጣሩና በተለይ ሊሞት የማይችለውን፣ እየተሟረተበት የሚገኘውን ነገር በአስቸኳይ በማጣራት ዲላ ዩኒቨርሲቲ የመምህራን ትምህርት አንድ የልቀት ማዕከል ሆኖ እንዲቀጥል በመታደግ ከታሪካዊ ተወቃሽነት እንዳን እላለሁ፡፡

      ግለሰቦች ከኃላፊነት ሊነሱ በሌሎችም ሊተኩ ይችላሉ፡፡ ለዘመናት ከፍተኛ መዋዕለ ነዋይ ፈሶበት፣ በብዙዎች ጥረት የተገነባ ተቋም ግን በግለሰቦች አለመግባባትና ፍላጎት ወይም ተቃውሞ ምክንያት በድምፅ ብልጫ አይዘጋም፡፡ አይናድም፡፡ በሌላ ተቋምም አይተካም፡፡ የሚገባውን ዕውቅናም ሊነፈግ አይችልም፡፡ ለምናደርገውና ለምንወስነው ሁሉ ምክንያታዊ እንሁን እንጂ ስሜታዊ አንሁን!! 

(ተሰማ፣ ከዲላ ዩኒቨርሲቲ)