Skip to main content
x

ድኅረ መለስ ኢትዮጵያ በመስቀለኛው መንገድ ላይ

በቶፊቅ ተማም   

ኢትዮጵያን ለ21 ዓመታት የመሩት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስተር መለስ ዜናዊ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት ከአምስት ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ነው፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ሕልፈት ተከትሎ የኢትዮጵያን መፃኢ ዕድል አስመልክቶ በተለያዩ አካላት አገሪቱ የብተና ሥጋት ይገጥማታል ተብሎ ቢታሰብም፣ ከዚህ በተቃራኒ አገሪቱ ወደ ብተና ሳትገባ በአንፃራዊ ሰላም እንደ አገር መቀጠል ችላለች፡፡

በዚህ ጽሑፍ ድኅረ መለስ ኢትዮጵያን ወሳኝ በሆኑ ዋና ዋና አገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ፣ የታዩ ድክመቶችና ጥንካሬዎችን በወፍ በረር ቅኝት ለማየት እሞክራለሁ፡፡

ስለአንድ አገር ሲታሰብ በዋነኛነትና ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው የሰላምና የፀጥታ ጉዳይ ሲሆን፣ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ሕልፈት በኋላ በተለይ ባለፈው ዓመት በአብዛኛው የአገሪቱ ክፍሎች የተቀሰቀሰውና ከመቶ በላይ ዜጎችን ሕይወት የቀጠፈውን ከማስተር ፕላን ጋር ተያይዞ የተቀሰቀሰው ሁከት፣ እንዲሁም በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የወሰንና የማንነት ጥያቄዎች መሠረት ያደረጉ ግጭቶች ተቀስቅሰዋል፡፡ ግጭቶቹ የአገሪቱን ሰላምና ፀጥታ አደጋ ላይ የጣሉ ከመሆናቸውም በላይ፣ መንግሥትም ባልተለመደ ሁኔታ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲያውጅ አስገድደውታል፡፡ ከዚህ ባለፈ ካለፈው የሰው ሕይወትና ከወደመው ንብረት በተጨማሪ፣ የአገሪቱ ኢኮኖሚ የሚደጉመው የቱሪዝም ዘርፍ ማስገኘት የነበረበትን ገቢ በአግባቡ ማስገኘት ሳይችል ቀርቷል፡፡ ከዚህም በአጭሩ ለመረዳት የሚቻለው ድኅረ መለስ ኢትዮጵያ በሰላምና በፀጥታ በኩል ተፈትና እንደነበር ነው፡፡

በሌላ በኩል ዋነኛውን ኢኮኖሚያዊ ጉዳይ ስንመለከት በዚህ አጭር ጽሑፍ በአግባቡ ማስፈር ቢያዳግትም፣ ድኅረ መለስ ኢትዮጵያ በተለይ የወጪ ንግድ (Export) ገቢ ከወትሮ በተለየ ሁኔታ የቀነሰ መሆኑ በተለያዩ ሚዲያዎች ተዘግቧል፡፡ አገሪቱ አሁንም በተለይ የዋጋ ግሽበት (Inflation)፣ የብር የመግዛት አቅም በእጅጉ መዳከም እንዲሁም የወጪ ንግዷ መቀዛቀዝን ተከትሎ የገጠማት የውጭ ምንዛሪ እጥረት፣ የድኅረ መለስ ኢትዮጵያ አሉታዊ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ውስጥ  ከብዙዎቹ ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ በግብርናው መስክ ደግሞ በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የሥልጣን ዘመንም ቢሆን መለስ ቀለስ የሚለው የድርቅ አደጋ በድኅረ መለስ ኢትዮጵያም ከአየር ንብረት ለውጥና የዝናብ ወቅት መዛባትን ተከትሎ ተከስቷል፡፡

ከኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ በአገሪቱ እተፋፋመ የሚገኘው የኮንስትራክሽን አብዮት ካሉበት ተግዳሮቶችም ጋር ቢሆን በድኅረ መለስ ኢትዮጵያ ተጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን፣ ከዚህም በተጨማሪ በአገሪቱ የተጀመሩ ትላልቅ ፕሮጀክቶች በተለያየ ደረጃ ተጓተዋል፡፡ ከዚህ በተቃራኒ አገሪቱ የውጭና የአገር ውስጥ ባለሀብቶችን ለመሳብ፣ እንዲሁም የወጪ ንግዷን ለማገዝና ከግብርና መር ወደ ኢንደስትሪ መር ኢኮኖሚ ለመግባት ለምታደርገው ጥረት የሚያግዙ ተግባራትን እየተከናወነ ነው፡፡

ለዚህም ዋነኛው ማሳያ የሚሆነው በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች እየተገነቡ ያሉ  የኢንዱስትሪ ፓርኮች ናቸው፡፡ ለዜጎች የሥራ ዕድል በመፍጠርና የዕውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግርን በማስገኘት ለአገር ዕድገት ሰፊ ጥቅም እንደሚሰጡ ይጠበቃል፡፡ እነዚህም የኢንዱስትሪ ፓርኮቸ  የትላልቅ ዓለም አቀፍ አምራች ድርጅቶችን ቀልብ መሳብ ችለዋል፡፡ ለአብነት ያህል እንደ ሐዋሳና ቦሌ ለሚ ባሉ የኢንደስትሪ ፓርኮች ሥራ ጀምረው፣ የተለያዩ አገሮች ኩባንያዎችም ምርታቸውን ለውጭ ገበያ ማቅረብ የጀመሩ መሆኑ ሲታይ አገሪቱ የጀመረችው የኢንደስትሪ ፓርኮች አብዮት በድኅረ መለስ ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ ረገድ በአዎንታዊ መልኩ የሚታይ አገራዊ ጉዳይ ነው፡፡

ሌላው ከኤሌክትሪክ ኃይል ጋር ተያይዞ የሚጠቀሰው ጉዳይ ቢኖር፣ በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የሥልጣን ዘመን ግንባታው የተጀመረውና በተለያዩ የውጭ አካለት ተፅዕኖ ሥር ወድቆ የነበረው የግልገል ጊቤ ሦስት የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት፣ በድኅረ መለስ ኢትዮጵያ ዕውን መሆን የቻለ ነው፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን ሊጠቀስ የሚገባው ዋነኛ ጉዳይ ቢኖር የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ግንባታውን ያስጀመሩት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ነው፡፡ ግድቡም በድኅረ መለስ ኢትዮጵያም ግንባታው ተጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን፣ ግድቡ ግንባታው ተጠናቆ የታለመለትን ግብ ይመታ ዘንድ ሌላ አምስት ዓመታትን እንዳንጠብቅ ዘንድ እንመኛለን፡፡

ሌላው በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የሥልጣን ዘመንም ይሁን በድኅረ መለስ ኢትዮጵያ ለአገሪቱ ዕድገት እንቅፋት የሆነው ሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነት ነው፡፡ ሙስናን ለመታገል መንግሥት ከዓመታት በፊት ‹‹ትልልቅ ዓሶች›› ያላቸውን ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትና ባለሀብቶች ለሕግ ያቀረበ ቢሆንም፣ ይህንም ተግባር አጠናክሮ ይቀጥላል ተብሎ ሲጠበቅ መቀዛቀዝ አሳይቶ ነበር፡፡ ሰሞኑንም ለመታዘብ እንደቻልነው ዓመታትን እየጠበቁ የተወሰኑ ባለሥልጣናትንና ሌሎችን በዙሪያቸው ያሉ ሰዎችን በቁጥጥር ሥር የማዋል ዘይቤን እየተከተለ ይገኛል፡፡

ድኅረ መለስ ኢትዮጵያም ሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነትን በፅኑ መታገል ላይ ድክመት እያሳየች ትገኛለች፡፡ ለዚህም ማሳያ በቅርቡ በሪፖርተር አንድ ጸሐፊ ያቀረቡት ጽሑፍ እንደሚያትተው ለፀረ ሙስና ትግሉ መዳከም ዋነኛ መነሻው፣ በፌዴራል ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ይከናወን የነበረው የሙስና ወንጀል ምርመራ በዋናነት ለፌዴራል ፖሊስ መሰጠቱ መሆኑ ይጠቀሳል፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን የፌዴራል ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን አሁን ያለበትን ሕንፃ ለቤቶች ኮርፖሬሽን እንዲያስረክብ መታዘዙ፣ በራሱ ለኮሚሽኑ የተሰጠው ዋጋ እየወረደ መሆኑን መገንዘብ ያስችላል፡፡

በእርግጥ አንድን ሰው ለፍርድ ለማቅረብ ማስረጃ ዋነኛ ጉዳይ ቢሆንም፣ ‹‹ከልብ ካለቀሱ እንባ አይገድም›› እንዲሉ አሁንም ቢሆን መንግሥት በውስጡ ያሉትንም ሆነ ሌሎች ከደሃው ሕዝብ ላይ እየነጠቁ የግል ኪሳቸውን የሚያደልቡትን በአግባቡ እየተከታተለ ለፍርድ ሊያቀርብ ይገባል፡፡ አገራዊ ሙስናን መከላከል የሚቻለው ዓመታትን እየጠበቁ 30 እና 40 ሰዎቸን በቁጥጥር ሥር ማዋል ብቻ አይደለም፡፡ ሙስናን በአግባቡ ለመዋጋትም አገሪቱ ወጥ የሆነ የፀረ ሙስና ትግል ስትራቴጂ ቀርፃ መንቀሳቀስ የሚገባት ሲሆን፣ አሁን የተጀመረው ሙሰኞችን የመዋጋት ዘመቻ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል፡፡ ሙስናን መዋጋት እንደ ገና ዳቦ ከላይም ከታችም እየለበለባት በምትገኘው ኢትዮጵያ፣ እንደ ገና መብራት ብልጭ ጥፍት የሚሆን መሆን የለበትም፡፡

በአገሪቱ ያለው ሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነት በቁጥር ከሚገለጸው በላቀ በአስተሳሰብና በባህል ደረጃ በማደግ ላይ የሚገኝ ነው፡፡ ይኼም አገሪቱ ከምትገኝበት የሙስና አረንቋ ለማውጣት አዳጋች ያደርገዋል፡፡ በአገሪቱ በተንሰራፋው ሙስና ምክንያት የዜጎች የሀብት ክፍፍል ሊመጣጠን ያልቻለ ሲሆን፣ አገሪቱም በተለይ የጥቂቶች ብቻ የመሆን አዝማሚያ እያሳየች ትገኛለች፡፡

በአገሪቱ ለሚታየው የዜጎች የሀብት ክፍፍል አለመመጣጠን ዋነኛ ምክንያትም ጥቂቶች በተመቻቸላቸው ‹ኔትወርክ› አማካይነት የዕድገትና የብልፅግና መንገዱ አልጋ በአልጋ ሲሆንላቸው፣ አብዛኛው ሕዝብ ግን በተቃራኒው የዕድገትና የብልፅግና መንገዱ አሜኬላ የበዛበት እየሆነበት ይገኛል፡፡ ከላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው በአገሪቱ የተንሰራፋው ሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነት ጥቂቶችን ብቻ የድህነትን ድልድይ እንዲሻገሩ ሲያስችል፣ አብዛኛውን ኅብረተሰብ ከድህነት ለመውጣትና የድህነትን ድልድይ ለመሻገር እንዲሳነው አድርጓል፡፡ ዛሬ አገሪቱን የዘረፉ ግለሰቦች ያላግባብ የተመቻቹላቸውን  ዕድሎች ተገን አድርገው  የድህነትን የድልድይ  የተሻገሩ ሲሆን፣ እነዚህ ሰዎች ሌሎች ዜጎችም ሆኑ አገሪቱ በአጠቃላይ የድህነትን ድልድይ እንዳይሻገሩ እንዲህ ብለው የሚዘባበቱ ይመስለኛል፡፡

                ‹‹ሌላው መንገደኛ አልፎ እንዳይመጣበት፣

                ካንተ ጋር እንደ አቻ እንዳይኩራራበት፣

                የአደጋ ምልክት ቀይ አንጠልጥልበት፣

               ስበረው አፈንዳው አመድ አድርገው ትቢያ፣

               ምን ያደርጋል ድልድይ አንተ ካለፍክ ወዲያ፤››     

የድኅረ መለስ ኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ክራሞትን ስንመለከት ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ሕልፈት ወዲህ አገሪቱ ያደረገችው አምስተኛው አገር አቀፍ ምርጫ በገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ሙሉ በሙሉ የመቶ በመቶ አሸናፊነት የተጠናቀቀ ነው፡፡ ይኼም የአገሪቱን የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት በእጅጉ ያዳከመ ክስተት ነው፡፡ በተለይ ምርጫ 97ን ተከትሎ ተቃዋሚዎች ባገኙት ድምፅ መሠረት በፓርላማ የነበራቸው መቀመጫ ጥሩ የሆነ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት፣ እንዲሁም የሐሳብ ብዝኃነት በተለይ ከ1998 እስከ 2002 ዓ.ም. በነበረው የፓርላማ የሥራ ዘመን ላይ የነበረ ሲሆን፣ ይህንን ሥርዓት በአሁኗ ድኅረ መለስ ኢትዮጵያ መመለስ አልቻለም፡፡

ከዚሁ ጎን ለጎን የፓርላማ ክራሞትን ስንመለከት ድኅረ መለስ ኢትዮጵያ በተለይ ሚኒስትሮችን በተመለከተ ከሌላው ጊዜ የተለየ መንገድ ተከትላለች፡፡ የትምህርት ዝግጅታቸውንና ያላቸውን የሥራ ልምድ መሠረት በማድረግ በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲሾሙላቸው ያቀረቡዋቸውን ሚኒስትሮች ሹመት በማፅደቅ፣ የአገሪቱን የተለያዩ ተቋማትን የሚመሩ ሚኒስትሮች በዘርፉ ምሁራን እንዲመሩ መደረጉ በድኅረ መለስ ኢትዮጵያ የፓርላማ የሥራ ወቅት የታየ አዎንታዊ ጉዳይ ነው፡፡

ከዚሁ በተቃራኒ ፓርላማው የተለያዩ ተቋማትን ዕቅድ አፈጻጸም በቋሚ ኮሚቴ በኩል የክትትልና ግምገማ ተግባራት እያከናወነ ቢገኝም፣ የቢሊዮን ብር ጥያቄ የሆነውን የኦዲት ግኝት ሪፖርቶችን መሠረት አድርጎ ለሚነሱ ችግሮች ዕርምጃ የመውሰድ ክፍተቶች ከዓመት ዓመት ሊሻሻልና ራስን ከመውቀስ ባለፈ ተጨባጭ ለውጥ መምጣት አለመቻሉ፣ ፓርላማውን ጥርስ የሌለው አንበሳ እየተባለ እንዲወቀስ አድርጎታል፡፡ 

ከዚሁ ከዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ጋር ተያይዞ ሊጠቀስ የሚገባው ጉዳይ ቢኖር፣ የአገሪቱ የነፃ ፕሬስ ጉዳይ ነው፡፡ አገሪቱ በተለይ በሕገ መንግሥቱ የተረጋገጠውን ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ተከትሎ በ1980ዎቹ እና 1990ዎቹ የነበረው የነፃ ፕሬስ ጥቂት በሕዝብ ካላገጡ ነፃ ፕሬሶች ውጪ፣ ይህንን ጉዳይ በቅርቡ ‹‹የዘመኑ ሴራ›› የሚል መጽሐፉን ለንባብ ያበቃው ጸሐፊ ገልጾታል፡፡ እንዲሁም በሚያወጧቸው ከባህል ጋር የማይዛመድ ጽሑፎችና ምሥሎች ምክንያት በሕዝብ ግፊት ከኅትመት ከወጡ ጋዜጦችና መጽሔቶች በመለስ፣ በወቅቱ የነበሩት ጋዜጦች በብዛትም በሚኖራቸው ይዘትና በነበራቸው ተፅዕኖ የተሻሉ የነበሩ ናቸው፡፡ ለዚህም ማሳያ የሚሆነው በተለይ በ1997 ዓ.ም. በነበረው ምርጫ ተቃዋሚዎች የተሻለ ድምፅ ያገኙ ዘንድ የተጫወቱት ሚና ለአብነት ይጠቀሳል፡፡

ይሁን እንጂ ከሚሊንየም መባቻ አንስቶ በአገሪቱ የነበሩ አብዛኛዎቹ ፕሬሶች በተለያዩ ምክንያቶች ቁጥራቸው ቢቀንስም፣ ከዚያ በኋላ የኅትመት ብርሃን ማግኘት የቻሉ ፕሬሶች የራሳቸውን ተፅዕኖ መፍጠር የቻሉና ላቅ ያለ ሚና መጫወት የቻሉ ነበሩ፡፡ ተፅዕኖ ፈጣሪ የነበሩ ጥቂት ፕሬሶች ከፊሎቹ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ሕልፈት በፊት፣ እንዲሁም ከፊሎቹ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ሕልፈት በኋላ በተለያዩ ምክንያቶች ከገበያ ውጪ ሆነዋል፡፡ የነፃው ፕሬስ ማበብ ለአገሪቱ ዴሞክራሲያዊ  ሒደት የሚጫወተው ሚና ላቅ ያለ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ በመሆኑም  መንግሥትና ነፃው ፕሬስ አይጥና ድመት ከመሆን፣ እንዲሁም በማይታረቅ ሁለት ጽንፍ ላይ ከመቆም ይልቅ ለአገር ሊጠቅም የሚችል የጋራ አቋም በመያዝ በጋራ ጥቅም መርህ (Mutualistic Approach) በቅርበት ሆነው ሊሠሩ ይገባል፡፡ ያም ሆነ ይህ ከላይ እንደተጠቀሰው በቋፍ ላይ የነበረው የአገሪቱ ነፃ ፕሬስ በድኅረ መለስ ኢትዮጵያ ዳግም ማንሰራራት አልቻለም፡፡ ከአፍሪካ በሕዝብ ብዛቷ ሁለተኛ የሆነችው ኢትዮጵያ አሁን በነፃው ፕሬስ  በኅትመት ላይ ያሏት ጋዜጦችና መጽሔቶች ቁጥር፣ እንዲሁም የኅትመት መጠን እዚህ ግባ የማይባል በመሆኑ በተለይ በነፃው ፕሬስ ረገድ ከጎረቤት አገሮች ጋር ስትነፃፀር በእጅጉ መፎካከር ተስኗታል፡፡

የድኅረ መለስ ኢትዮጵያን ክራሞት በዚህ አጭር ሐሳብ በአግባቡ መግለጽ አይቻልም፡፡ አሁን ትኩረት የሚሻው ዋናው ጉዳይ ቢኖር ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ አገሪቱን የሚመራ ፓርቲ እንደመሆኑ፣ በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የአመራር ዘመን የነበሩ ጠንካራ ጎኖችን በአግባቡ አጠናክሮ መቀጠል ተገቢ ነው፡፡ እንዲሁም በድኅረ መለስ ኢትዮጵያ የታዩ ከላይ የተጠቀሱና ሌሎችንም ችግሮች መቅረፍ ይገባል፡፡ አገሪቱ አሁን በተጨባጭ ካለችበት መስቀለኛ መንገድ ወደ የልማት፣ የሰላምና የዴሞክራሲ መንገድ በመመለስ የተሻለች ኢትዮጵያን ለመፍጠር በቁርጠኝነት መትጋት የውዴታ ግዴታ ነው፡፡

ለማጠቃለል ያህል ይህ ጽሑፍ ከጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ እረፍት በኋላ የኢትዮጵያ ክራሞትን በጣም በአጭሩ ለማስቀመጥ የሞከረ ሲሆን፣ ይህን ጽሑፍ በማሰናዳበት ወቅት በቅርቡ በሆሄ የሥነ ጽሑፍ ሽልማት በረዥም ልቦለድ ዘርፍ ዕጩ የሆነውና በዶ/ር ዓለማየሁ ዋሴ የተጻፈው ዘጎራ መጽሐፍ በገጽ 40 ላይ የሰፈረው ሐሳብ ጽሑፌን ያጠናክርልኝ፣ እንዲሁም ያጠቃልልኝ ዘንድ ሁነኛ ሆኖ በማግኘቴ ከመጽሐፉ ጥቂት ላካፍል፡፡

የመጽሐፉ ደራሲ ከዓይኑ የእንባ ዘለላዎችን እያረገፈ እንዲህ ይላል፡፡ ‹‹. . . በደላችን በዝቶ ተቀይመኸን ተለያይተን ጉራማይሌ ሆንብህ፣ ከመካከላችን ሙሴን አስነሳና ወደ ተራራው አውጥተህ ንገረው፣ የተባረከ በትር ስጠውና የድህነቱን ባህር ከሁለት ከፍሎ ያሻግረን እባክህ፡፡ ቁስላችንን የሚቀርፍ ሳይሆን የሚያክም፣ ትናንት ጦማችንን አደርን ስንለው ዛሬም ድገሙ የማይለንን ተቆነጠጥን ስንለው የማይኮረኩመንን፣ ከፋን ስንለው የማያስከፋንን፣ የምንፈራው እሱም የሚፈራን ሳይሆን፣ ሁላችን እንደ አባት  የምናየው አንድ ሙሴ ስጠን፡፡ የአድባራቱንና የገዳማቱን ቡራኬ የሚቀበል፣ የአዛውንቶችና የሸሆችን ምርቃት የሚያከብር፣ የምዕራብን ካፒታሊስት የምሥራቅን ሶሻሊስት ርዕዮት እንደ ወረደ ተግቶ ኑ ልጋታችሁ የማይል የዚህችን ድንቅ አገር ሚስጥር የሚፈታ አንድ ሙሴ ስጠን. . .››

በመጨረሻም ከአሥራዎቹ መጨረሻ ዕድሜአቸው ጀምሮ በትጥቅ ትግል እንዲሁም ከድል በኋላ ለ21 ዓመታት አገሪቱን ያለ አንዳች በቂ ዕረፍት የመሩት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሕልፈት ተከትሎ፣ በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የሚጻፉ ደብዳቤዎች ግርጌ እንዲህ የሚል ቃል እንዲያሰፍሩ ታዘው እየተገበሩት ይገኛሉ፡፡ እኔም ሐሳቤን በዚህ ቃል ላብቃ፣ ‹‹መለስ ዜናዊ ለሕዝብ የተፈጠረ፣ ለሕዝብ የኖረ፣ ለሕዝብ የተሰዋ ታላቅ መሪ ሌጋሲህም ይቀጥላል፣ ራዕይህ በትውልድ ቅብብሎሽ ይሳካል፤›› ሰላም!

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡