Skip to main content
x
ድጋፍ የሚሹት የኩላሊት ሕሙማን

ድጋፍ የሚሹት የኩላሊት ሕሙማን

‹‹መቼም ገንዘቡ ካለቀ እኛም አለቅን ማለት ነው፤›› አሉ የሆስፒታሉ አልጋ ላይ ጋደም እንዳሉ፡፡ በግምት በ60ዎቹ መጀመርያ ላይ የሚገኙት እኚህ ሰው ኩላሊታቸው ሥራውን ካቆመ ዓመታት አስቆጥሯል፡፡ ኩላሊታቸውን ተክቶ የሚሠራው ከጎናቸው የቆመው ማሽን ነው፡፡ በክንዳቸው ላይ በተጠመጠመው ቀጭን ቱቦ ደማቸው ወደ ማሽኑ ሲገባ ይታያል፡፡

ጤናማ ኩላሊት ላላቸው ሰዎች የሕክምናው ሒደት የሚያሳቅቅ ዓይነት ነው፡፡ ይሁንና እንደእሳቸው ላሉ በዕድሜያቸው ላይ ተጨማሪ ሰዓታት የሚጨመርላቸው ነውና ጭንቀትን ሳይሆን ዕፎይታን ይሰጣቸዋል፡፡ በአጠቃላይ ህልውናቸው የተመሠረተው በማሽኑ ላይ ነው፡፡ ሕክምናው ግን በጣም ውድና በአብዛኛዎቹ ኢትዮጵያውያን አቅም የማይደፈር ዓይነት ነው፡፡ አቅሙ ካላቸው ውጪ ለድሃው የኅብረተሰብ ክፍል ሞትን ከመጠባበቅ ባለፈ ሌላ አማራጭ የለም፡፡ ሕክምናውንም በሳምንት ሦስት ጊዜ መውሰድ ግድ ይላቸዋል፡፡

እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ለአንድ እጥበት ብቻ ከ2,000 ብር በላይ እንዲከፍሉ ይደረግ ነበር፡፡ አማካይ ክፍያውም የተለያዩ መድኃኒቶችን ወጪ ሳይጨምር 1,500 ብር እንደነበር የኩላሊት እጥበት በጎ አድራጎት ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን አሰፋ ይናገራሉ፡፡ አንድ ሰው በሳምንት ለሦስት ጊዜያት ያህል ኩላሊቱ እንዲታጠብለት በትንሹ 4,500 ብር ያስፈልገዋል፡፡

ይህ የብዙዎችን ኢኮኖሚ ያናጋ፣ ሕይወታቸውን እንዳልነበር አድርጎ የቀየረ፣ ባለፀጎችን ሳይቀር ተመፅዋች ያደረገና እያደረገ የሚገኝ በሽታ ነው፡፡ ናሽናል ኪድኒ ፋውንዴሽን ባወጣው መረጃ መሠረት አሥር በመቶ የሚሆነው የዓለም ሕዝብ በኩላሊት አለመሥራት በሽታ ይሰቃያል፡፡ ሕክምናውን በተመጣጣኝ ዋጋ የማያገኙ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በየዓመቱ ሕይወታቸው ያልፋል፡፡ ሁለት ሚሊዮን የሚሆኑም በሕይወት ለመቆየት የኩላሊት እጥበትና ንቅለ ተከላ ሕክምና ይደረግላቸዋል፡፡

በሽታው እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ታዳጊ አገሮች አስከፊ ጉዳት እያደረሰ ይገኛል፡፡ ሕክምናውን ለማግኘት አቅሙ የሌላቸው ብዙዎች ሕይወታቸው እንደዋዛ አልፏል፡፡ በኩላሊት ሕመምተኞች እጥበት በጎ አድራጎት ድርጅት አባል የነበሩ ነገር ግን ከሞት የሚታደጋቸው ጠፍቶ ያለፉን በምሳሌነት ማንሳት ይቻላል፡፡ ስለበሽታው ብዙም ግንዛቤ ባልነበረበት ወቅት ነበር የኩላሊት ሕመምተኞች እጥበት በጎ አድራጎት ድርጅት በ43 ታማሚዎች የተመሠረተው፡፡

አባላቱ የሕክምናቸውን ወጪ ለመሸፈን ቤት ንብረታቸውን የሸጡና ባዶ እጃቸውን የቀሩ ነበሩ፡፡ በሳምንት ሁለትና ሦስት ጊዜ ማግኘት የሚገባቸውን ሕክምና በወጉ ለማግኘት ይቸገሩ የነበሩ፣ ሕይወታቸውን ለማቆየት በየቤቱ ዞረው ዕርዳታ የሚለምኑ፣ እስከ መጨረሻው የሚታደጋቸው ያጡ ነበሩ፡፡ በአሁኑ ወቅት ከአቶ የሱፍ አብዱልሀሚድ በስተቀር 42ቱ የድርጅቱ መሥራች አባላት በሕይወት የሉም፡፡ ሕክምናው እንደዛሬው በመንግስት ሆስፒታል መሰጠት ሳይጀምር፣ አማካይ የሕክምና ዋጋውም 1,500 ብር በነበረበት ወቅት ነበር ሕይወት የቀደመቻቸው፡፡

ከጥቂት ጊዜያት በፊት በግል የሕክምና ተቋማት ብቻ ይሰጥ ነበረው የኩላሊት እጥበት ሕክምና በአሁኑ ወቅት በዘውዲቱ፣ በጥቁር አንበሳ፣ በጴጥሮስና በምኒልክ ሆስፒታሎች እንዲሁም በተለያዩ በክልል ከተሞች በሚገኙ ሆስፒታሎች በቅናሽ ዋጋ በመሰጠት ላይ ይገኛል፡፡ ከዚህ ቀደም በአገር ውስጥ የማይሰጠው የኩላሊት ንቅለ ተከላ ሕክምና በአገር ውስጥ መጀመሩ ጨልሞ የነበረው የመዳን ተስፋቸው እንደገና እንዲያቆጠቁጥ አድርጓል፡፡

የንቅለ ተከላ ሥራው ከተጀመረ እስካሁን ለ48 ሰዎች ሕክምናው ሜዲካል ተደርጎ 47ቱ በስኬት መጠናቀቃቸውን በቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ የሕክምና ዘርፍ ፕሮቨስት ዶክተር ብርሀኔ ረዳኢ ተናግረዋል፡፡ የንቅለ ተከላ ሕክምናው በወር አንድ ጊዜ የሚሠራ ሲሆን በቅርቡም በየቀኑ መሥራት እንደሚጀምሩ ዶክተር ብርሀኔ ተናግረዋል፡፡ ‹‹የንቅለ ተከላ ሕክምናው ከእጥበት ጋር ሲተያይ በጣም ርካሽ ነው፡፡ ዲያሌሲስ በጣም ውድ ነው፡፡ ነገር ግን የንቅለ ተከላ ሕክምናው እስኪደረግላቸው ታማሚዎች በዲያሌሲሰ መቆየት አለባቸው፤›› ይላሉ፡፡

በተደረጉ ጥረቶች ሕክምናው በተለያዩ የመንግሥት የሕክምና መስጫ ተቋማት መሰጠት መጀመሩ በተደራሽነቱ ላይ ትልቅ ለውጥ ቢያመጣም ችግሩ አሁንም አሳሳቢ ነው፡፡ ለአንድ ሕክምና እስከ 750 ብር መክፈል ይኖርባቸዋል፡፡ ስንቱ ይህንን ከፍሎ መታከም ይችላል የሚለው አጠያያቂ ነው፡፡ በተለያዩ የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራሞች ከሕዝቡ በተገኘ ገቢ የኩላሊት ሕመምተኞች እጥበት በጎ አድራጎት ድርጅት የአባላቱን ወጪ ሲጋራ ቆይቷል፡፡ በየሳምንቱ 600 ብር እንደሚሰጣቸውም አባላቱ ይናገራሉ፡፡ እንደዚህም ሆኖ የተቀረውን ለመክፈል የሚቸገሩ ብዙ ናቸው፡፡

ሌላው ፈተና ደግሞ የድርጅቱ መክፈል አቅም እየተዳከመ መምጣቱ ነው፡፡ አቶ የሱፍን እረፍት የነሳቸውና ገንዘቡ ካለቀ እኛም አለቀልን ያስባላቸውም ይኸው ጉዳይ ነው፡፡ ረቡዕ ነሐሴ 3 ቀን 2009 ዓ.ም. በጁፒተር ሆቴል ተዘጋጅቶ በነበረው ፕሮግራም ላይ የችግሩን አሳሳቢነት የሚያሳይ ዘጋቢ ፊልም ተዘጋጅቶ ነበር፡፡

በፊልሙ ከአቅም በላይ የሆነ ፈተና እንደተጋረጠባቸው ሁሉ ዓይናቸውን መሬት ላይ ተክለውና ጣቶታቸውን እያፍተለተሉ በሐሳብ ጭልጥ ያሉ ሰዎች ይታያሉ፡፡ በሐዘን ተኮራምተው የተቀመጡ ወጣቶችና አዋቂዎችን ለተመለከተ ችግራቸው ባይገባውም አብሮ መጨነቁ ማዘኑ አይቀርም፡፡ ሳግ እየተናነቃቸው ችግራቸውን ሲያወሩ ደግሞ አብሮ ከማዘን ባለፈ ነገ በእኔ ሊደርስ ይችላል ብለው ሥጋት ይገባዎታል፡፡

በበሽታው ምክንያት የደረሰባቸውን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም አካላዊ እንግልት ታማሚዎቹና የታማሚ ቤተሰቦች ሳግ እየተናነቃቸው ያወራሉ፡፡ ‹‹በሕመሙ ምክንያት ሥራ መሥራት ባለመቻሌ ከሥራ ገበታዬ ቀረሁ፡፡ ቤቴን፣ መኪናዬን ሸጥኩኝ፡፡ በአሁኑ ወቅት በኪራይ ቤት ነው የምኖረው፤›› አሉ አንደኛው ታማሚ፡፡

በሕክምናው ላይ የሚያውቋቸው ሌሎች እንደሳቸው ያሉ ታካሚዎች መሞታቸውን ሲሰሙ ሐዘናቸው እንደሚበረታና በተደጋጋሚ እንደሚያጋጥም ሳግ እየተናነቃቸው ተናገሩ፡፡ ሌላኛው ደግሞ ‹‹ለእኛ ሁሉም ገንዘብ ዋጋ አለው፡፡ ሕይወታችንን የምናቆየው በገንዘብ ኃይል ነው፡፡ ያገኘነውን ለሕክምና ነው የምናውለው፡፡ እንደ ድሮ ካፌ ገብተን ሻይ እንኳን አንጠጣም፤›› በማለት በሽታው ያላቸውን ሁሉ እንዳሟጠጠ ተናገሩ፡፡

 የተደላደለ ኑሮ ይኖሩ የነበሩ በበሽታው እንዳልነበሩ ሆነዋል፡፡ ባለፀጋ ነበርኩኝ ብሎ ስለነበራቸው የተደላደለ ኑሮ ትዝታቸውን ከማጋራት ባለፈ ተመፅዋች የሆኑ ብዙ መሆናቸውን ከፊልሙ መገንዘብ ይቻላል፡፡

በአዳራሹ የነበሩ አንዳንዶች ፊልሙን እየተመለከቱ ያለቅሱ ነበር፡፡ በተለይ ወይዘሮ ጂጂ ዳዊት ለቅሧቸው ያሳዝን ነበር፡፡ በበሽታው የቅርብ ዘመድ ወይም ልጃቸውን አጥተው እንደሆነ ጠየቅናቸው፡፡ በሕመሙ የሚሰቃዩት እሳቸው ራሳቸው መሆናቸውን አንባቸውን እየጠራረጉ ነገሩን፡፡ ኩላሊታቸው ሥራ ካቆመ ስምንት ዓመት ሊሞላቸው ቀናት ቀርተዋል፡፡ በእነዚህ ዓመታት በሕይወታቸው ላይ የሰማይና የምድር ያህል ልዩነት ተፈጥሯል፡፡

ጥሩ ገቢ የሚያገኙ ነጋዴ ነበሩ፡፡ ቤትና ትልልቅ ዋጋ ያላቸው የተለያዩ ንብረቶች ባለቤትም ነበሩ፡፡ ባለትዳና የአንድ ልጅ እናት የሆኑት ወይዘሮ ጂጂ የተደላደለ ኑሮ ይኖሩ ነበር፡፡ ይህንን የሚያውቁት ግን እሳቸውና ሌሎች በቅርበት የሚያውቋቸው ሰዎች እንጂ አሁን ያለውና ያሉበት ፈጽሞ ከዚህ የተለየ ነው፡፡

በሕመሙ ምክንያት ሥራ መሥራት ትተው ቤት ከዋሉ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ በሳምንት ሦስት ጊዜ የሚደረግላቸው ሕክምናም ያጠራቀሙትን እንዲጨርሱ አደረጋቸው፡፡ ይህም ለትዳቸው መፍረስ ምክንያት ሆነ፡፡ ቤትና ንብረት ተካፍለውም ነበር፡፡ ይሁንና የሕክምናውን ወጪ ለመሸፈን ሲሉ ቤቱንና ሌሎች ንብረታቸውን ለመሸጥ ተገደዱ፡፡ ልጃቸውን ይዘው ከወላጆቻቸው ጋር አብሮ መኖርም ጀመሩ፡፡ ንብረት ሸጠው ያገኙት ጠቀም ያለ ገንዘብ ግን ብዙም ሳይቆይ በሕክምናው አለቀ፡፡

‹‹እኔን ለማሳከም እናቴ ቤቷን መሸጥ ነበረባት፡፡ እሱ ሲያልቅ ደግሞ ሌሎች ንብረቶችን መሸጥ ተያያዘች፡፡ አሁን ሁሉም አለቀ፡፡ ጥሩ ኑሮ ትኖር የነበረችው እናቴም በእኔ ምክንያት ችግር ላይ ወድቃለች፤›› በማለት በአሁኑ ወቅት የሕክምና ወጪያቸውን የሚሸፍኑት የሚያውቋቸውን ሰዎች ትብብር በመጠየቅ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ በሳምንት ሦስት ጊዜ መታከም ሲኖርባቸው ገንዘብ በማጣት ሳይታከሙ የሚያልፉባቸው ቀናት እንዳሉም ይናገራሉ፡፡

ንቅለ ተከላ መጀመሩ ትልቅ ዕፎይታ የሰጣቸው ቢሆንም ኩላሊት ማግኘት አልቻሉም፡፡ የቅርብ ዘመዶቻቸው ሊሰጧቸው ፈቃደኛ ነበሩ፡፡ ይሁን እንጂ ኩላሊታቸው የስኳር በሽታ ምልክት ስለሚያሳይ የቤተሰቦቻቸውን መጠቀም አልቻሉም፡፡ ‹‹ሌላ ማንም አይሰጠኝም፡፡ ብዙ ሞክሬያለሁ፤›› በማለት በንቅለ ተከላ የመዳን ተስፋቸው መጨለሙን ይናገራሉ፡፡

እንደሳቸው ያሉ ሕመምተኞችን ሕይወት ለማቆየት የሚሆን የመታከሚያ ወጪ ለመሸፈን የኅብረተሰቡና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ድጋፍ ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ ቀደም የነበረው የሕዝቡ ትብብር አብሯቸው እንዲቀጥል ግድ ነው፡፡ ባለፈው ረቡዕ በጁፒተር ሆቴል ተዘጋጅቶ በነበረው ፕሮግራም የበጎ አድራጎቶች ኤጀንሲ ለሥራ መርጃ የሚሆን ተሽከርካሪ የለገሳቸው ሲሆን፣ ኬኬ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት ደግሞ የአምስት ሚሊዮን ብር የገንዘብ ድጋፍ አድርጎላቸዋል፡፡

በደም ግፊት፣ በስኳር በሽታ የሚከሰተውን የኩላሊት ሥራ ማቆምን በቀን ውስጥ የሚያስፈልገውን በቂ ውኃ በመጠጣት የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በማድረግና የአኗኗር ሁኔታን በመቀየር በቀላሉ መከላከል ይቻላል፡፡ ይሁንና በማኅበረሰቡ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን በማድረግ ጤና መጠበቅ፣ ጤናማ አመጋገብና ሌሎችም ከጤና ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያላቸው ነገሮችን የማዘውተር ባህሉ ዝቅተኛ ነው፡፡ ሰዎች የእነዚህ ነገሮች ጥቅም ጎልቶ የሚታያቸው ጅብ ከሄደ ውሻ ጮኸ እንዲሉ ከታመሙ ነገሮችን ወደ ነበሩበት ለመመለስ አስቸጋሪ ደረጃ ላይ ከደረሱ በኋላ ነው፡፡