Skip to main content
x
ፀረ ሙስና ዘመቻው አሉታዊ ጎኖችን አይዘንጋ!

ፀረ ሙስና ዘመቻው አሉታዊ ጎኖችን አይዘንጋ!

በየትኛውም የሥራ ዘርፍ ውስጥ ከሙስና ጋር ንክኪ ያላቸው መጠየቅ አለባቸው፡፡ በየትኛውም ኃላፊነትና ደረጃ ላይ የሚገኙ የሙስና ተጠርጣሪዎች ለሕግ መቅረባቸው ተገቢ ነው፡፡ መቼም ቢሆን ተጠያቂነት መኖር አለበት፡፡ የተጠያቂነት መኖር የሕግ የበላይነት መገለጫ ሲሆን፣ አለመጠየቅ ሲሰፍን ደግሞ አገር በነቀዝ ትበላለች፡፡ በሙስና የተዘፈቁም ሆኑ በማቀባበል ሰንሰለት ውስጥ ያሉ ሲጠየቁ ሥርዓት ይኖራል፡፡ ማናለብኝነት ይከስማል፡፡ ሕገወጥነት አደብ ይገዛል፡፡ አሁን የተያዘው የፀረ ሙስና ዘመቻ ግቡን ሊመታ የሚችለው ደግሞ በተጠናና በማያወላዳ አኳኋን ሲከናወን ብቻ ነው፡፡ መንግሥት ይህንን ፀረ ሙስና ዘመቻ የጀመረው ቀደም ሲል ባደረገው ጥናት ላይ ተመሥርቶ እንደሆነ ተገልጿል፡፡ ምን ጊዜም ቢሆን በጥናት ላይ የተመሠረተ ሥራ በአዋጭ ዕቅድ ሲታገዝና አፈጻጸሙ ሲሰምር አመርቂ ውጤት ይገኝበታል፡፡ ‹‹ሲሮጡ የታጠቁት ሲሮጡ ይፈታል›› የሚባለው ፈሊጣዊ አነጋገር እንዳይደርስ ደግሞ ከባድ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም በኔትወርክ የተሳሰረው የሙስና ኃይል ጉልበቱ ጠንካራ ነውና፡፡

ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ሥር ውለው ፍርድ ቤት ሲቀርቡም ሆነ ንብረቶች ዕግድ ሲጣልባቸው በጥናት ላይ የተመሠረተ አሠራር ተግባራዊ መደረግ ይኖርበታል፡፡ የፀረ ሙስና ዘመቻው የመንግሥት ተሿሚዎችንና የንግድ ማኅበረሰቡ አባላት ላይ ሲከናወን፣ የንግድና የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎችን ማወክ የለበትም፡፡ ሙስና ውስብስብና ሰንሰለቱም የተራዘመ በመሆኑ በርካታ ጉዳዮች በሚስጥር የሚያዙ ቢሆንም፣ ‹‹ከኑግ ጋር የተገኘህ ሰሊጥ. . .›› ዓይነት ድርጊቶች ብዙዎችን ያስበረግጋሉ፡፡ ተጠያቂነት ያለባቸው ግለሰቦች ለሕግ ሲቀርቡም ሆነ ንብረቶች ዕገዳ ሲጣልባቸው፣ በሥራ አማካይነት የሚገናኙ ሌሎች ሰዎች ግራ መጋባት ውስጥ እንዳይወድቁ ጥንቃቄ ያስፈልጋል፡፡ ንግድና ኢንቨስትመንት በተፈጥሯቸው ሰላምና መረጋጋትን የሚፈልጉ በመሆናቸው፣ መንግሥት ሥጋት የገባቸውን በማረጋጋትና ሕጋዊውን ከሕገወጡ የመለየት ኃላፊነቱን መወጣት ይኖርበታል፡፡ ይህ ሳይሆን ሲቀር ግን ችግር ያለበት እየተደናበረ ከአገር ሲሸሽ ጤነኛውም ‹‹ጎመን በጤና›› እያለ መከተሉ አይቀርም፡፡ በዚህ አጋጣሚ ደግሞ የግብይት መቀዛቀዝ ይፈጠራል፡፡ ይህንን ተከትሎ ለዋጋ ግሽበት የሚዳርጉ ክስተቶች ያጋጥማሉ

በሙስና ምክንያት የተጠረጠሩ ሰዎች ቀደም ብሎ ጥናት የተደረገባቸው ከሆኑና ከእነሱ ጋርም ተያያዥነት ያላቸው ግለሰቦችም ሆነ ተቋማት ሲጠየቁም ሆነ፣ መረጃ በማሰባሰብና በማጠናቀር ወቅት የተለያዩ ሥራዎች ሲከናወኑ የሕዝብን አስተያየት እንደ ግብዓት መጠቀም ተገቢ ነው፡፡ ሕዝብ በተለያዩ አካባቢዎችና ዘርፎች ውስጥ የሚከናወኑ ድርጊቶችን ስለሚያውቅ፣ ተጨማሪ መረጃዎችና ማስረጃዎችን እንዲሰጥ ማድረግ የሚቻለው መንግሥት አሠራሩን ግልጽ ሲያደርግ ነው፡፡ ግልጽነት ከሌለ ግን ምርመራው የተንዛዛ ይሆናል፡፡ መሰላቸትን ይፈጥራል፡፡ አፋጣኝ ፍትሕ ከማግኝት ይልቅ በተራዘመ የውጣ ውረድ ሒደት ዓላማው ገጽታውን ይቀይራል፡፡ አገሪቱን እንደ ነቀዝ እየበላ ያለው ሙስና ከሥር መሠረቱ ሊገነደስ የሚችለው በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት ያገኘ አሠራር ተግባራዊ ሲሆን ነው፡፡ ተጠርጣሪዎች በአፋጣኝ ሕግ ፊት ቀርበው በሥርዓቱ ሲከራከሩና ዓቃቤ ሕግም አለኝ የሚላቸውን ማስረጃዎች ይዞ ሲሟገት፣ በንግድና ኢንቨስትመንት ውስጥ የሚሳተፉ ዜጎችም ተረጋግተው ሥራቸውን ያከናውናሉ፡፡

ንግድና ኢንቨስትመንት በተረጋጋ ከባቢ ውስጥ እንዲከናወን የማድረግ ኃላፊነት የመንግሥት ነው፡፡ መንግሥት ሕግ በማስከበርና ዜጎችን ከማናቸውም ጥቃቶች በመጠበቅ  በተሰማሩባቸው ዘርፎች ውጤታማ እንዲሆኑ ማገዝ አለበት፡፡ እንዲህ ባለው ወቅት ደግሞ ሕገወጦች ክፍተቶችን እየተጠቀሙ ሌላ የሙስና መስኮት በመክፈት በንግድና በኢንቨስትመንት ውስጥ የሚሳተፉ ዜጎችን ይረብሻሉ፡፡ እነዚህ በኔትወርክ የተደራጁ ሐሰተኛ መታወቂያና ማንነት በመያዝ ሰላማዊ ዜጎችን በማሸበር የዘረፋ ተግባር ይፈጽማሉ፡፡ መንግሥት አሠራሩ ግልጽ ሲሆንና ዜጎችም በዚህ የሚተማመኑ ከሆኑ ግን፣ ወቅት ጠብቀው ክፍተቶችን በመጠቀም ሕገወጥ ድርጊት የሚፈጽሙ ወረበሎች ከድርጊታቸው ይቆጠባሉ፡፡ በአሁኑ ጊዜ ሥጋት የገባቸው ከአገር ወጣ ብለው ሁኔታዎችን የሚከታተሉ አሉ፡፡ እነዚህ የመጣው ደራሽ ውኃ ጠራርጎ ይወስደናል በማለት የሚሸሹ፣ የተወሰኑት ደግሞ ሥራቸውን አውቀው የኮበለሉ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን አለመረጋጋት በሚያመጣው ፍራቻ ብቻ በየቦታው ንግድ ሲቀዘቅዝ ግብይቱ ይናጋል፡፡ ኢንቨስትመንት ሲጓተት ሥራ ይቆምና በርካቶች ሥራ አጥ ይሆናሉ፡፡ ይህንን ለመከላከል ብርቱ የሆነ ጥረት ያስፈልጋል፡፡

ተጠያቂነት መኖር ያለበት በዙር ወይም በዘመቻ አይደለም፡፡ ሙስናን መከላከልም ሆነ ከመሠረቱ መንግሎ ለመጣል ሥርዓቱ ራሱን በራሱ መቆጣጠር አለበት፡፡ ሕግ አውጪው፣ ሕግ አስፈጻሚውና ሕግ ተርጓሚ እርስ በርስ እየተናበቡ መሥራት ከቻሉ ሙስናም ሆነ ሌሎች ብልሹ አሠራሮች ሥፍራ አይኖራቸውም ነበሩ፡፡ የሦስቱን አካላት አሠራር መቆጣጠር ያለበት ጠንካራ ሚዲያ ቢኖርና ከለላ ቢሰጠው ደግሞ በሙስና የሰከሩ አገር አይበጠብጡም ነበር፡፡ ሙስና ተቋማዊ እስኪመስል ድረስ የአገር አንጡራ ሀብት እየበላ ዜጎችን በድህነት ሲያማቅቅ፣ ጥቂት ቅንጡዎች ያለፉበትን እንዳሻቸው ሲያጋብሱና በዜጎች መካከል ኢፍትሐዊ ግንኙነት ሲሰፍን እንደ አገር ለምን መባል ነበረበት፡፡ በእርግጥ በተደጋጋሚ ሙስና አገር የሚያፈርስ ክፉ ደዌ መሆኑ ቢነገርም ድፍረት በመታጣቱ በርካታ ጉዳቶች ደርሰዋል፡፡ በአንድ ሌሊት ሚሊየነሮች የሚፈለፈሉበት ሙስና ረጃጅምና ጠንካራ መዳፎች ያሉዋቸው ጀብደኞችን ፈጥሯል፡፡ እነዚህን የፈረጠሙ ጡንቸኞችን በቁጥጥር ሥር ማዋል ከባድ መሆኑም ታይቷል፡፡ ነገር ግን አገሪቱም ሆነች ሕዝቡ ከዚህ ዓይነቱ ቀውስ ውስጥ የሚወጡት ሀቀኞች የበላይነት ሲይዙ ብቻ ነው፡፡ ያኔ ሕዝቡም ከእነሱ ጎን ይሠለፋል፡፡ ለሕገወጥነት የሚያሰፈስፉም ይገታሉ፡፡

እስከዚያው ግን አሁን ባለው ሁኔታ ብርቱ ጥንቃቄ የሚፈልጉ ጉዳዮች እንዳሉ ማስታወስ ተገቢ ነው፡፡ ከደጋ እየተንደረደረ እንደሚመጣ ደራሽ ጎርፍ ፀረ ሙስና ዘመቻው ሲከፈት በሙሰኞች ተጠልፎ ተሰነካክሎ እንዳይቀር ያሠጋል፡፡ በመንግሥት ተቋማት ውስጥ ያሉ ሀቀኛ ተሿሚዎችም ሆኑ በአግባቡ ሥራቸውን የሚያከናውኑ የንግዱ ማኅበረሰብ አባላት እንዳይበረግጉ መደረግ አለበት፡፡ ተጠያቂነት ያለባቸው በአግባቡ ሕግ ፊት ቀርበው መዳኘት ያለባቸውን ያህል፣ በጥናት ላይ ያልተመሠረተና ማስረጃ ያልተገኘባቸውም በፍጥነት መለየት ይኖርባቸዋል፡፡ አንዱ ተጠያቂ የሆነበትን ጉዳይ ሌላ ሳይጠየቅበት ከቀረም የፍትሐዊነት ጥያቄ ይነሳል፡፡ ሕዝቡ በበኩሉ አሁን የተጀመረው ፀረ ሙስና ዘመቻ የበለጠ የተሳካ እንዲሆንና ውጤት እንዲያስመዘግብ መተማመኛ ይፈልጋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በንግድና በኢንቨስትመንት ውስጥ ያሉ ዜጎች ደግሞ ከመጠራጠርና ምን ይመጣ ይሆን ከሚሉ ሥጋቶች መላቀቅ ይፈልጋሉ፡፡ አገሪቱም እንደ ወትሮው ተረጋግታ መቀጠል ስላለባት ሕጋዊና ሕገወጥ ድርጊቶች መለየት አለባቸው፡፡ ከምንም ነገር በላይ ደግሞ የሕግ የበላይነት ሊኖር ይገባል፡፡ ለዚህም ሲባል ፀረ ሙስና ዘመቻው አሉታዊ ጎኖችን መዘንጋት የለበትም!