Skip to main content
x

ፌዴራላዊ ሥርዓትና ዴሞክራሲያዊ ልማታዊ መንግሥት በኢትዮጵያ ያላቸው ተመጋጋቢነት

በኃይለየሱስ ታየ (ዶ/ር)

በአገሮች የሚነደፉ የመንግሥታት አወቃቀር ሥርዓቶች የየአገሩን ተጨባጭ ችግሮች የሚፈቱና በአገሮች ሰላም የሚያሰፍኑ፣ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታና ለልማት መሠረት የሚጥሉ መሆን እንዳለባቸው የተለያዩ ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡ በተለይ ብዙ ጊዜ ከወሰዱ የእርስ በርስ ግጭት ለመውጣት የሚጥሩ አገሮች የሚፈጥሩዋቸው ተቋማት ከችግሩ የሚያወጡ መሆን እንዳለባቸው ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ሥርዓትም ከመነሻው እነዚህን ሁኔታዎች መሠረት ያደረገ መሆኑ የመንግሥት ማኅበረሰብ ግንኙነቶቸ (State Society Relations) ከመሠረቱ በመለወጥ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ሰፍኖ የኖረውን ኅብረ ብሔር ማኅበረሰብ አሃዳዊ መንግሥት (Federal Society Unitary State) መካከል የነበረ ተቃርኖ ለመፍታት የተቀየሰና ራስን በራስ የማስተዳደርና በጋራ ጉዳዩች ላይ በጋራ የመወሰን (Self Rule and Shared Rule) ልዩነትን ከማስተናገድ (Accommodation of Diversity) ጋር አጣምሮ የያዘ ፌዴራላዊ ሥርዓት ነው፡፡

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ሥርዓት መነሻው ይኼ ሆኖ የልማታዊ መንግሥት አስተሳሳብ ከምንም ዓይነት የመንግሥት አደረጃጀት ተቃርኖም ሆነ ተመሳሳይነት የሌለው ሲሆን፣ የልማታዊ መንግሥት የተወሰኑ ባህሪያት በተለያዩ መንግሥታዊ አደረጃጀቶች የታዩ ናቸው፡፡ ለምሳሌ በ18ኛው ክፍለ ዘመን በአውሮፓ በነበሩ የንጉሣዊ ሥርዓቶች መንግሥታት በኢኮኖሚው ውስጥ ጣልቃ እየገቡና በአገሮቻቸው በማቆጥቆጥ ላይ የነበሩ ኢንዱስትሪዎች በተለያዩ መንገዶች በመደገፍ፣ በዓለም ገበያ ተወዳደሪ ሆነው እንዲወጡ ለማድረግ አሁን በዘመናችን የልማታዊ መንግሥት አስተሳሰብ በምንለው በሚመስል አግባብ የተንቀሳቀሱ ናቸው፡፡ ከ1950ዎቹ ጀምሮ ልማታዊ መንግሥት የሚለው አስተሳሰብ ጎልቶ እንዲወጣ፣ አንድ የልማት ማስፈጸሚያ አማራጭ ተደርጎ እንዲታይና በልማታዊ ኢኮኖሚክስ ተመራማሪዎች የጥናትና ምርምር መነሻ እንዲሆን ያደረጉት በምሥራቅ እስያ የሚገኙ አገሮች ናቸው፡፡ እንደ ደቡብ ኮሪያና ታይዋን የመሳሰሉት በዚህ አቅጣጫ ተጉዘው "ተዓምራዊ" ኢኮኖሚያዊ ለውጥ አምጥተዋል፡፡

እነዚህ የምሥራቅ እስያ አገሮች ያልተማከለ የአስተዳደር ሥርዓት የሚከተሉና ከመነሻቸው አሁን ወደሚገኙበት የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ደረጃ ያልደረሱና አምባገነናዊ መንግሥታት ነበሩ፡፡ በተለምዶ ልማታዊ መንግሥታትን ካልተማከሉና ዴሞክራሲያዊ ካልሆኑ መንግሥታት ጋር ማያያዝና ልማታዊ መንግሥት ዴሞክራሲያዊና ፌዴራላዊ ሊሆን እንደማይችል፣ በመሀላቸውም የማይታረቅ ተቃርኖ እንዳለ የእያንዳንዱን ጽንሰ ሐሳቦች አጠቃላይ ባህሪያትና በየአገሮቹ ሊኖራቸው የሚችለውንና ያላቸውን አንድምታ በተገቢው ሳይዳሰስ ድምዳሜ ላይ ለመድረስ ሲከጀል ይታያል፡፡  በመሆኑም በዚህ ዙሪያ ያለውን ብዥታ በተወሰነ መልኩም ቢሆን ለመግለጽ ዴሞክራሲያዊ ልማታዊ መንግሥትና የፌዴራል ሥርዓቱ በኢትዮጵያ ሁኔታ ተመጋጋቢነት እንደሚከተለው ለማብራራት ተሞክሯል፡፡

የልማታዊ መንግሥት አንዱና ትልቁ መነሻው ኅብረተሰቡ የሚጋራው ልማታዊ ራዕይ ያለው መሆንና ኅብረተሰቡን ለዚህ ራዕይ መሳካት በተደራጀ መልኩ ማንቀሳቀስ ነው፡፡ አሁን ኢትዮጵያ ከምትገኝበት አገራዊ ሁኔታ አኳያ አገሪቱን ከድህነት ማውጣትና ወደ መካካለኛ ገቢ ያላቸው አገሮች ተርታ ማሠለፍ የሚቻለው፣ ሕዝቦች በየአካባቢያቸው ወደ ልማት ማስገባት ሲቻል ነው፡፡ ኅበረ ብሔር በሆኑ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች በየአካባቢው ላሉ ማንነቶች ዕውቅና ሰጥቶ ራሳቸውን በራሳቸው የሚያሰተዳድሩበት ሥርዓት ፈጥሮ ከመንቀሳቀስ ውጪ የማኅበረሰቡን ይሁንታ ያገኘና የጋራ የሆነ ራዕይ ይዞ መቀጠል የሚቻልበት ነባራዊና ኅሊናዊ ሁኔታ አለመኖሩ ከኢትዮጵያ የቅርብ ጊዜና አሁንም ሙሉ በሙሉ ካልተሻገርነው የድህነትና የሰቆቃ ታሪክ መገንዘብ አያዳግትም፡፡ በመሆኑም የፌዴራላዊ ሥርዓቱ ከልማት አኳያም ሲቃኝ የራስ አስተዳደርን በመጠቀም፣ አካባቢያዊ ፍላጎቾችና አቅሞችን መሠረት አድርጎ አካባቢን ማልማትና ተጠቃሚ መሆን ከጋራ አስተዳደር አኳያም በአገራዊ ልማት ላይ በተመጣጣኝ ደረጃ ተሳታፊና ተጠቃሚ መሆንን የሚያመቻች ፌዴራላዊ ሥርዓት ነው፡፡

ስለሆነም ፌዴራል ሥርዓቱ ኅበረተሰቡን በየአካባቢው ለልማት ለማሠለፍና በኅብረተሰቡ ሙሉ ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎ ልማቱን በማከናወን የልማቱ ባለቤት በማድረግ፣ የልማታዊ መንግሥት አንዱና መሠረታዊ ባህሪን የሚደግፍ እንጂ ከልማታዊ መንግሥት ጋር ተቃርኖ ያለው አይደለም፡፡ ይልቁንም የኅብረተሰቡን ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎና የልማቱን ባለቤትነት መነሻ ያደረገ ማኅበረሰባዊ የሆነ የጋራ ራዕይ መሠረት አደርጎ የሚፈጸም የልማት ተግባር፣ ኅብረተሰቡ በየአካባቢው የራሱን ጉዳይ በራሱ የሚወስንበት ነው፡፡ ቀጣይነት ላለው ልማትም ሆነ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ መሠረት የሚሆነው ማኅበራዊ ካፒታል እየተገነባ የሚሄድበት ፌዴራላዊ የመንግሥት አወቃቀር፣ የዴሞክራሲያም ልማታዊ መንግሥት ባህሪን አጣምሮ የሚሄድ ካልሆነ ውጤታማ ሊሆን አይችልም፡፡

ሌላው የልማታዊ መንግሥት መገለጫ ከሆኑት ቁልፍ ጉዳዮች አንዱ፣ የመንግሥትና የቁልፍ አመራሩ ለልማት መሳካት ያለው ቁርጠኝነትና ቁርጠኝነቱ በሚያወጣቸው ፖሊሲዎችና የፖሊሲ አፈጻጸሞች የሚገለጽ መሆን ነው፡፡ የፌዴራላዊ አደረጃጀቱ በየደረጃው የሚገኙ መንግሥታትና ቁልፍ አመራሮች አካባቢያዊና አገራዊ ልማትን አስተሳስሮና አናቦ በአካባቢያዊ ልማት መገኘት የሚችለውን ውጤት አሟጦ ማግኘት የሚስችል፣ አገራዊ ልማቱን የሚመግብ ፖሊሲ ቀርፆ አገራዊ ልማቱ የሚፈለግበት ግብ ማድረስ የሚያስችል ፖሊሲ ተይዞ፣ ሁለቱ ፖሊሲዎች እየተናበቡና እየተቀናጁ እስከተፈጸሙና አለመግባባቶች ሲያጋጥሙም ተቋማዊ በሆነና መተንበይ በሚቻል የመንግሥታት ግንኙነት አግባብ እየተፈቱ መሄድ አለባቸው፡፡ ይህ እስካሁን ድረስ የፌዴራላዊ ሥርዓቱ በየደረጃው ያለው አመራር በየሚገኝበት የአመራር እርከን ልማትን ለማረጋገጥ ቁርጠኝነት ወስዶና ቁርጠኝነቱ በተግባር እየተገለጸ እስከተንቀሳቀሰ ድረስ፣ ዴሞክራሲዊ ልማታዊ መንግሥትና የፌዴራል ሥርዓቱ ተመጋጋቢ ሆነው የአካባቢያዊ ልማትን ከአገራዊ ልማት ጋር ያስተሳሳረ የዳበረ ልማት ለማምጣት ምሰሶና ማገር ናቸው፡፡

የልማታዊ መንግሥት ሌላው ዋና መለያ ባህሪው በተለምዶ በማንኛውም መንግሥት ከሚሠሩ በዋናነት ሕግና ሥርዓትን ከማስከበር ጋር የተያያዙ ሥራዎች ወጣ ባለ መንገድ በተመረጠ አቅጣጫ በኢኮኖሚ ውስጥ ጣልቃ በመግባት፣ ለልማት ቁልፍ የሆኑ መሠረተ ልማቶችን ማሟላትና ገና በጅምር ላይ ባለ የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ያለውን የገበያ ክፍተት መሙላት ተገቢ ነው፡፡ ይህ ማለት በባለሀብቱ ሊቀርቡ የማይችሉና ለልማት ቁልፍ የሆኑ ምርቶችንና አገልግሎቶችን በማቅረብ ለታዳጊ አገሮች ልማት ቁልፍ በሆኑ ዘርፎች ማለትም በቴክኖሎጂ አቅም ግንባታ፣ በሰው ኃይል ሥልጠና፣ በትልልቅ መሠረተ ልማቶች ግንባታ፣ ወዘተ . . . መሳተፍ ነው፡፡ ባለሀብቱ አዋጭና ለአገር ኢኮኖሚ ግንባታ ወሳኝ በሆኑ የኢንቨስትመንት መስኮች ላይ እንዲሰማራ ከመሠረተ ልማት ጀምሮ፣ ብድርና የሠለጠነ የሰው ኃይል ማቅረብ ተገቢ ነው፡፡ አንፃራዊ ነፃነቱን በጠበቀ ሁኔታ በልማታዊ አግባብ በአገሪቱ የኢኮኖሚ ልማት አቅጣጫ የሚንቀሳቀሰውን ባለሀብት በመደገፍ፣ ለአገሪቱ ኢኮኖሚ መሠረት የሆኑ ዘርፎች ላይ በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ የሆኑ አምራች ኢንዱሰትሪዎችን ማስፋፋት ነው፡፡ ይህን ዓላማ ለማሳካት በየደረጃው ብቁ አገልግሎት የሚሰጥና ፌዴራላዊ የሆነ ያልተማከለ አስተዳደርን የሚተገብር የመንግሥት አወቃቀር፣ ልማታዊ ባለሀብቱ ልማትን ለማፋጠን የሚያስችሉት ምቹ ሁኔታዎችን በየአስተዳደር እርከኑ አካባቢውን መሠረት አድርጎ መፍጠር አለበት፡፡ ግብዓቶችን በየአካባቢው በማቅረብ ለዴሞክራሲያዊ ልማታዊ መንግሥት አሠራር ብርቱ መሠረት እንጂ ተቃርኖ የሚሆንበት አግባብ የለም፡፡ በተግባራዊ እንቅስቃሴ ከፌዴራላዊ አመለካከትና ከዴሞክራሲያዊ ልማታዊ መንግሥት የአስተሳሰብ ጥራት፣ ከዚህም ከዚያም የሚታዩ ክፍተቶች ካልሆኑ በቀር፡፡

የሕዝብ አገልጋይነት ሰብዕና የተላበሰ፣ የተቀላጠፈ፣ ውጤታማ የሆነና የሚተነበይ አገልግሎት የሚሰጥ ልማትን ማሳካት የሕዝብ አገልጋይነቱና ሙያዊ መገለጫው አድርጎ የሚንቀሳቀስ ሲቪል ሰርቫንት ገንብቶ ማንቀሳቀስ የልማታዊ መንግሥታት አንዱ መለያ ባህሪ ነው፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ባለብዙ ብሔርና ባህል ባለቤት በሆኑ አገሮች አገራዊ መሥፈርቶችና ስታንዳርዶች እንደተጠበቁ ሆነው፣  የየአካባቢውን ማኅበረሰብ አካባቢያዊ መሠረቶችና ዕድሎች መሠረት አድርጎ ከላይ በተገለጸው ሁኔታ በማገልገል የማኅበረሰቡን ልማት የሚያፋጥን ሲቪል ሰርቫንት በየደረጃው ለመፍጠር፣ የፌዴራል ሥርዓቱ ለዴሞክራሲያዊ ልማታዊ መንግሥቱ መሠረት እንጂ ተቃርኖ ሊሆን አይችልም፡፡ መሠረታዊ ችግሩ ፌዴራላዊና ልማታዊ ሲቪል ሰርቪስ በሚፈለገው ደረጃ አለመገንባቱ ካልሆነ በቀር፡፡

 ዞሮ ዞሮ የፌዴራሊዝም አስተሳሰብና የፌዴራላዊ ሥርዓት የሚታሰበው በዴሞክራሲያዊ አግባብ  እንደ አገር አብሮ የመቀጠል ሐሳብ ሲኖርና እንደ አገር ያሉ አንድነቶችና ትስስሮችን በአዲስ መሠረት ማስቀጠል ሲፈለግ ነው፡፡ በመሆኑም ለፌዴራል ሥርዓቱ መፈጠርና በሒደትም እየተጠናከረ ለመሄድ የሚያስችሉ

  • ተቋማት (Institutions)
  • ፌዴራላዊ ሒደቶች (Federal Process)
  • ፌዴራላዊ አመራር (Federal Leadership)
  • ፌዴራል እሴቶች (Federal Values)
  • ባለብዙና ተመጋጋቢ የሆነ ማንነት (Multiple and Complementary or Nested identity)

   መገንባት የሚያስችል ሥርዓት መፍጠርና እየገነቡ መሄድ ሲቻል ነው፡፡  

እነዚህ መሠረታዊ የሆኑ ፌዴራል ሥርዓቱ መሠረቶችን መገንባት የሚቻለው፣ ዴሞክራሲያዊና ልማታዊ አሰተሳሰብና ተግባር የተላበሰ አመራር፣ ሲቪል ሰርቫንት፣ ባለሀብትና የፌደራላዊ ሥርዓቱና የልማቱ ተጠቃሚና ባለቤት የሆነ ማኅበረሰብ መፍጠር ሲቻል ነው፡፡ በኢትዮጵያ ሁኔታ ልማታዊ መንግሥትና የፌደራላዊ ሥርዓት ዴሞክራሲያዊ ከመሆን ባለፈ ተመጋጋቢና ተደጋጋፊ ሆነው መሄድ የሚችሉና ያለባቸው መንግሥታዊ አደረጃጀትና ልማታዊ እሳቤ ናቸው፡፡ ፌዴራላዊ ሥርዓት ያለዴሞክራሲ ሊታሳብ የማይችልና ቢታሰብም ውጤታማ የማይሆን የመሆኑን ያህል፣  በፌዴራል ሥርዓት ውስጥ የሚተገበር ልማታዊ መንግሥት ዴሞክራሲያዊ ልማታዊ መንግሥት ሊሆን የግድ ይለዋል፡፡ ሕገ መንግሥትን መሠረት ያደረገ የሥልጣን ክፍፍልና ሁለትና ከዚያ በላይ መንግሥታትንና ከዚሁ ጋር ተያይዞ ብዙ የልማት ማዕከላትን መፍጠር በራሱ የዴሞክራሲው ሥርዓት ግንባታ አንዱ አቅጣጫ ሲሆን፣ ልማታዊ መንግሥቱም ዴሞክራሲያዊ መሆን እዳለበት አስገዳጅ የሆነ መነሻ ሁኔታ ነው፡፡

ሲጠቃለል በፌዴራላዊ ኢትዮጵያ ሁኔታ እንደ መሠረታዊ ችግር ተደርጎ መወሰድ አለበት ብዬ የማስበው የሁለቱ ጽንሰ ሐሳቦች መቃረን ሳይሆን፣ ሁለቱም ጽንሰ ሐሳቦች (ፌዴራላዊ ሥርዓትና ዴሞክራዊ ልማታዊ መንግሥት) ለአገራችን አዲስና በአገራችን ሥርዓተ ትምህርትም የአገራችንን ተጨባጭ ሁኔታና የልማትና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ዕድል መሠረት ተደርጎ በሚገባና በበቂ ሁኔታ ገና ያልተዳሰሱ ናቸው፡፡ በመሆኑም ጽንስ ሐሳቦቹን በሚገባ ተረድቶና ከአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ጋር በሚገባ ተንትኖ ከተግባር ጋር አመጋግቦ በመፈጸም ዙሪያ የሚያስፈልገው አቅም በየደረጃው ወቅቱ በሚፈለገው ደረጃ አዳጊ ሆኖ እየተገነባ አለመሄድ፣ በጉዳዩ ዙሪያ በማኅበረሰብ ደረጃ በቂ ውይይት አለመደረግ፣ አደረጃጀቱና አስተሳሰቡ ገና ያልተሻገሩት ችግርና በቀጣይ በተከታታይ፣ በተደራጀና በተቀኛጀ መንገድ መሥራት ያለበት ወሳኝ ጉዳይ ሆኖ ይታያል፡፡   

   

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው በፌዴራሊዝም ጥናት ረዳት ፕሮፌሰር ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡