Skip to main content
x
‹ካልደፈረሰ አይጠራም!›

‹ካልደፈረሰ አይጠራም!›

ሰላም! ሰላም! እንዴት ነው ሰሞኑን ቅፅበታዊ እብደቶች አልበዙባችሁም? ግብር በግምት እንደ መብረቅ እየባረቀብን እንዳትሉኝ ብቻ? ክፍት የሥራ ቦታ እብደትና ልመና ብቻ የሆኑ እስኪመስለን ድረስ ጎዳናው እያደር የከሰሩ ዜጎች ይበዙበት ጀምሯል። “ሌላው መስክማ እንዴት ይገባበታል? በመንግሥትና በግል ሌቦች ቁጥጥር ሥር ወድቆ!” ብሎ ያለው አንድ ስሙን የማልነግራችሁ ወዳጄ ነው። ሲፈጥረው ‘ሐመሩሐ’ እግር ሥር ያልጣለው ግብር ከፋይ እንዴት የታደለ ነው የሚባልበት ጊዜ ላይ እንድረስ? ምንድን ነበር የምናወራው? ሳንጀምረው የሚጠፋን ነገር ኧረ በረከተ እኮ? አዎ ሰሞኑን እንዲሁ በየሄድኩበት ጨርቁን የጣለ በዛብኝ እያልኳችሁ ነበር። እኔም ጨርቄን እንዳልጥል መፍራቴን ለውዷ ማንጠግቦሽ ብነግራት፣ ‹‹መጀመርያ ደህና ጨርቅ ሲኖርህ አይደል?›› ብላ ስትመልስልኝ ፀጥ ብዬ ወጣሁ፡፡ ምን ይባላል ታዲያ?

አንድ ወዳጄን “ምንድነው ነገሩ?” ብዬ ጠየኩት። እሱም ምን አለኝ፣ “እንኳን ሰው ውሻም የለመደውን ሲነሱት ይነክስ የለ ወይ?” ብሎ የኑሮን ማሻቀብ አማልኝ። ልማታዊው መንግሥታችን ‹ሐሜት ልማት አይሆንም› ቢልም ሐሜት የዋጋ ንረትን ተከትሎ እየገሸበ እንጂ፣ እየቀነሰ ሲመጣ ልናይ አለመቻላችን ያስደንቃል። ምክንያቱም እስኪ አስቡት፣ በዚህ የውጥረት ኑሮ ቢያንስ ችግሮቻችንን ቢበዛ ችግር ፈጣሪዎቻችን ካላማን እንዴት ይሆናል? ሁላችንም ተያይዘን አብደን የእብድ ከተማ ሆኖ እርፍ። አገሩ በሙሉ! ‘ችግሩን ያልተናገረ መድኃኒት አይገኝለትም’ አይደል የሚባለው? ግን ለአብዛኛው ሰው ሲያብድ እንዳንነቃበት ያደረገን ነገር ምን መሰላችሁ? ተስፋ። ደግሞ ይኼን ሰምተው ተስፋችንን በ ‘ሐ’ ሥር እንዳይመዘግቡት አደራ ለሰው አታውሩ!

እናላችሁ፣ “ሸክም ተሸክሜ ያለቅጥ ቢከብደኝ. . .” አለ አሉ አዝማሪው “. . .ሸክም ተሸክሜ ያለቅጥ ቢከብደኝ፣ ከድካሜ በቀር የለም ያዋረደኝ፤” በአገር ቅኝት እንፍሰስ ብዬ  ነው ጣል ጣል የማደርግባችሁ። በነሲብ ግምት የቀን ገቢ ከሚተመንባችሁ ባላንጣ መቼስ እኔ እሻላችኋለሁ። ጣል የሚያደርግብን ሲገኝ ለቀም። እንኳን ይህን የአቦ ሰጡኝ ግብር እንከፍል የለ እንዴ? ጥሎ ለረጋጭ የሚሰጥ እንጂ በአለን ላይ የሚጨምር የት ይገኛል በዚህ ጊዜ? ዋሸሁ? ቆይ ግን ደላላና ፖለቲከኛ ውሸታም ነው ብሎ የነዛው ማን ነው? በእርግጥ ፖለቲከኛ ሆኖ አልዋሽም ባይ ካለ የልጅ ልጅ ዓይታ ድንግል ነኝ የምትል አለች ማለት ነው። ባሻዬ መቼ ዕለት በዚሁ ዙሪያ አደባባይ ስንዞር ምን አሉን መሰላችሁ? “ሕዝብ እኮ ከፖለቲከኞች ጋር በውሸት ተጣልቶ አያውቅም፤” ብለው ዝም አሉ።

“እንዴት ነው ነገሩ? ስንት አላየንም እንዴ ከጫካ እስከ ከተማ፣ ከከተማ እስከ መልከ ብዙ አብዮት?” ስላቸው፣ “ነገርኩህ! በአወሻሸት ሒደት ላይ፣ ቴክኒክና ታክቲኩ ላይ፣ ወይ አነጣጡ አጠቋቆሩ ላይ ካልሆነ የትኛውም ሕዝብ ዋሻችሁ ብሎ ፖለቲከኞቹን አኩርፎ አያውቅም። የዓለምን ታሪክ በጥንቃቄ ደግመህ አንብብ፤” አይሉኝ መሰላችሁ? ለራሴ የግራ እጄ መዳፍ ሰበዛ ሰበዙ አሁን ዓይቼው አሁን እየተዘበራረቀ አስቸግሮኛል ባሻዬ ዓለምን ጨብጣት እያሉ ያሳቅቁኛል። ለራሴ፣ “እኔማ ዘንድሮ ሆኛለሁ ጀርጀርቱ፣ ቢጠሩኝ አልሰማ ጨርቄን ካልጎተቱ፤” እያልኩ ሲሸጡ ስሸጥ፣ ሲያከራዩ ሳከራይ፣ ሲለውጡ ሳለዋውጥ እውላለሁ ባሻዬ ጭራሽ ‘ከጋርዮሽ ሥርዓት ምሥረታ አንስተህ እስከ ስምተኛው ሺሕ ድረስ ተቀምጠህ አንብብ’ ይሉኛል። እንኳን ተቀምጠን ቆመንስ ቻልነው እንዴ? ምኑን?. . . እንጃላችሁ! 

እግረ መንገዴን 15 ሚሊዮን ብር የሚባልለት ቤት ሳሻሽጥ ያጋጠመኝን ልንገራችሁ። ይገዛሉ የተባሉት ሀብታም የመጡት በሁለት ቪ8 መኪኖች በአጃቢ ነው። የአጃቢዎቻቸውን ብዛት ስመለከት ወይ አዲስ አበባ ለዚህም በቃሽ? ሳልል አልቀረሁም። እንደ እኔ ያለው ምስኪን እንኳን ከባለፀጋ ጋር ሊጣላ ለሰላምታም አልደራረስ ባለበት ዘመን፣ በጋርድ እስከ መንቀሳቀስ የሚያደርስ ምን ጉዳይ ይሆን እያልኩ ማውጠንጠኔን ተያያዝኩት። ሰውዬው ቤቱን የሚገዙት ለልጃቸው ስለሆነ ስለወደዱት በጣም ተደሰቱ። ወዲያውኑ ካልከፈልኩ ብለው ተገለገሉ። የሀብታም ነገር ብር ካለ ሁሉም ነገር ዛሬ ቀላል ነው። የክፍያ አፈጻጸም ራሱን የቻለ ሥርዓትና ወግ እንዳለው አስረድተናቸው፣ ባለቤቱም ለጊዜው እንዲያዩት ብቻ መክረዋቸው ተለያዩ። በሚቀጥሉት ቀናት ሁሉም ነገር ተፈጻጸመና ግብዣና ፈንጠዝያ ካላደረግኩ ብለው እኔም ጭምር አንድ ጉደኛ የዘመኑ ሥጋ ቤት ተሄደ። መቼም የእኛ ነገር ኪሳችን ሞላ ብለን ሥጋ መጨርገድ የምናቆም አንመስልም። ይኽም የዘመኑ ፀባይ ስለሆነ ምንም ማድረግ አይቻል። የገባው ገብቶታል!

በቀደም ደግሞ እንደ ቀልድ ‘ሐበሻ ጥበቡን የጥበብ ቀሚስ ላይና ምሳሌ ላይ ጨረሰው’ ስል ባሻዬ ሰምተውኝ ኖሮ፣ “ወሬስ የት ሄዶ?” ብለው ቀብ አደረጉኝ። እሳቸው ደግሞ ሲመጣባቸው አንዴ ቀጨም ያደረጉትን ነገር በዋዛ አይለቁም። እናም ቀጠል አድርገው (ተቀጣጣይ እሳት እንጂ የማልወደው ነገር ሲቀጣጠል በጉጉት ደሜ ትግ ትግ እንደሚል የታወቀ ነው) “ይመስለናል እንጂ ይኼ ሳይለፉ ማካበት፣ ተቀምጦ መብላት፣ በተቆራጭ ገንዘብ መነዛነዝ የመጣው እኮ ማልደን ተነስተን ላብ ስናፈስ ከዋልን ለወሬ ለምንቀንሰው ሰዓት በውስጠ ታዋቂነት እረፍት ስለሚነሳን ይመስለኛል። አይመስልህም? ‘ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው’ ይባላል በአገራችን፤” ብለው ነገሩን ወደ እኔ መሩት። እንኳን በ ‘ይመስለኛል! አይመስልህም?’ ዴሞክራት ሆነው ነገሩን ወደ እኔ መሩት እያልኩ በውስጤ “ልክ ነው!” ብዬ ዝም አልኩ። ታዲያ እንደ እኔ በቤተ ሙከራ የማይለካ፣ የማይረጋገጥ፣ የማይመሳከርን ነገር እየደመደሙ ነገር ከማስረዘም ማሳጠር ይልመድባችሁ። ሌላ ምን እላለሁ? ዘንድሮ ነገርና ኳስ የሚያስረዝሙት ናቸው ከዋንጫ ፉክክር ሲርቁ ያየናቸው። ነው እኔ ብቻ ነኝ የሚታየኝ? አይ እናንተ!

‹መሃረቤን ዓያችሁ አላየንም. . .› ከመጫውታችን በፊት የባሻዬን ጨዋታ ልጨርስላችሁ። ምናሉኝ፣ በአንድ ቀዬ ትዳራቸው የሚያስቀና አካላቸው ቢያረጅም፣ ከሚስታቸው ጋር ያላቸው ፍቅር እያደር የወጣት የሆነ አዛውንት ነበሩ አሉ። መቼም አበባ ካለ ንብ ያንዣብባል። ስኬታችሁና ደስታችሁ እያደር ምቀኛ ሲያፈራ ስታዩ ፅጌሬዳ ጉያ እሾህ ጠፍቶ እንደማያውቅ አስታውሱ። ምነው ስንት መርሳት የሚገባንን ነገር አንረሳም እያል በጎሳ እያበርን? የማይገነባ ነገር ከማስታወስ በሜዳ ሳር ጤዛ መመሰጥ ለኑሮ የሚበጅ ሚስጥር ያካፍላል ይባላል። እና አንድ ቅናተኛ የአዛውንቱን ጎጆ ማፍረሻ መላ ሲፈልግ (መቼም ኑሮ ያልተወደደበት መሆን አለበት የቻፓ መላ ትቶ ፍቅር ማፍረሻ መላ ሲፈልግ ጊዜ የሚያጠፋው) ሰነባብቶ ማምለጫውንም አዘጋጅቶ (የቀናተኛም ብሩህ አለው ማለት ነው? ይታያችሁ እንግዲህ?) ጠጋ ብሎ “አንቱ! ኧረ ይህቺ ሚስትዎ ትሄዳለች። ምን ሆና ነው?” ይላቸዋል። “ዓይተሃታል?” ይላሉ በቸልታ። “በዓይኔ በብረቱ፤” ይመልሳል። ሰውዬው ሚስታቸውን ወዲያው ጠርተው፣ “ሰማሽ ስምሽን? ሂያጅ ነች ይሉሻል። ይኼው ወሬኛው ፊት ጠየቅኩሽ፤” ሲሏቸው ሚስታቸውን ወሬኛው ጣልቃ ገብቶ፣ “አንቱ! እንዴት ያሉ ሰው ነዎት ግን? ትሄዳለች ስልዎ በሐሳብ ትነሆልላች ማለቴ እንጂ ትወሰልታለች መቼ ወጣኝ?” ብሎ ሲቆጣ፣ “በል ተወው ወንድሜ። ያለዛሬም ሐሳብ ሲዎሸም አልሰማሁ፤” ብለው አባረሩት። ላልደረሰበት የቃላት ጨዋታ አይመስልም አሁን ይኼ ታሪክ? እንዲያው እኮ!

አሁን ብንበተን ምን ይመስላችኋል? አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አሁንም ሥራ ላይ መሆኑን ትዘነጉታላችሁ ልበል? አይ ጊዜ እንዲህ እንደ ዘበት አዋጅና ፍቅርን የሚያስረሳ ዘመን ይምጣ? ትዝ ይለኛል ያኔ ጓድ መንግሥቱ ግንባሬ ሳይበተን ኢትዮጵያ አትበተንም ብለው ሲዝቱ። ይኼው የእሳቸውም ግንባር ሳይበተን አገራችንም ይኼው እስካሁን አለች፡፡  መሰንበት ደጉ እያረሳሳም ቢሆን ያስተዛዝበናል። የዘንድሮው ደግሞ ባሰ። ትናንት አገር እንዳይበተን ነበር ጭንቁ። ዛሬ ግን ቤት ለቤት ሆኗል። በዚያ በኩል ትዳር ይፈርሳል። በዚያ በኩል በውኃ፣ በመብራትና በኔትወርክ እየተመሀኘ ቢዘነስ ይቆማል። በዚህ ወር ብቻ የልጆች የትምህር ቤት ወጪ መሸፈን አቅቷቸው ለመጪው የትምህርት ዘመን ማስመዝገቢያ የተበደሩኝ ወዳጆቼ ቁጥር አራት ደርሷል።

መንገዱ እንደምታውቁት በመሰናክል ታጥሯል። ሠርቶ መቋጠር ፍዳ በሆነበት በዚህ ጊዜ እንኳንም ዘንቦብሽ ዓይነት የሚያሸንፈን እንቅፋት ለቁጥር ይታክታል። አሯሯጮቻችን መጠጥና ጫት ሆነዋል። መተንፈሻችን ሺሻና ትምባሆ ሆኗል። ሥጋችን በጭስና በአልኮል ሲገረጣ መንፈሳችን ባልተፈጸሙ የኪዳን ቃሎች ተጎሳቁሎ ይሰበራል። ዓመት ዓመት የምናዝንበት፣ የምንተክዝበት ነገር አያጣንም። እናላችሁ ይኼ ሁሉ እያሳሰበኝ እኔም የጎዳናው አባል ነኝና የተለመደችዋ ግሮሰሪ ታድሜ ጉሮሮዬ ሳርስ አንዱ ምን ሲል ሰማሁት መሰላችሁ? “ቤት ሠራሁ ብለሽ አትንገሪ ለሰው፣ አሞራሽ እኔ ነኝ የማፈራርሰው፤” ቅኔ ነጋሪና ቅኔ ተቀባይ የጥልቅ ተሃድሶ አባል በሆኑ አያሰኝም እስኪ? አንዱ ከወዲያ ማዶ ‹‹ተቀበል. . .›› ብሎ፣ ‹‹አማረብኝ ብለሽ አትበይ ደንበር ገተር፣ እኛም አንድ ሰሞን እንዲህ አርጎን ነበር፤›› ሲል ሳቅ እንደ ውኃ ፈሰሰ፡፡ በቀን ገቢ ግምት ጡዘት ላይ የሙስና ተጠርጣሪዎች እስር ተጨመረበት የሚባለው ርዕስ ሲጨመርማ፣ ሁሉም እንዳሻቸው የወሬ ወፍጮውን አንቀሳቀሱት፡፡ ‹ካልደፈረሰ አይጠራም› ያለው ማን ነበር?  መልካም ሰንበት!