Skip to main content
x
‹ይኼም ቀን ያልፍና. . .›

‹ይኼም ቀን ያልፍና. . .›

ሰላም! ሰላም! “ይህ ሕይወት ካለፈው የቀጠለ ነው። አሁን የምትኖረው ያለምከውን ነው፤” አለኝ አንዱ በቀደም። አንዱ የምለው ወድጄ እንዳይመስላችሁ። አንድ አንድ እያልን ካልነጣጠልነው የዘንድሮ ቅዠት ተደራጅቶ ገና ጉድ ይሠራናል። አስቡት እስኪ? ለቁጠባ ቤት ዕጣ እንዲወጣልን ያበራነው ጧፍ ሳይጠፋ፣ ከአመድ መጣችሁ ወደ አመድ ትመለሳላችሁ ሲሉን፡፡ ሰው ዓይኑ እያየ የሚድርበት ታዛ ሳይኖረው ከገዛ ሐሳቡ በታች ውሎ እያደረ ልፋቱ ሁሉ ህልም ነው ሲባል። ኧረ ህልምና ራዕይ አይምታታብን ተው ተው። እኔ እኮ የምለው ይኼ አሸባሪነት የሚሉት ነገር መልኩን ቀይሮ አንድ በአንድ መለመለን እንዴ? እንዴት ማለት ጥሩ። አንድ በአንድ የመተንተን ችሎታ የምሁሩን የባሻዬ ልጅ ያህል ባላዳብርም ነገር መበተን በደም የወረስኩት ነው። ምነው የሚወራ የሚሠራው ሁሉ ‹ደም ደም› ይላል እያሉ የሚያስፈራሩ እያሉላችሁ፣ በእኔ ደም የማጥለል ሥልት ተገረማችሁ? እሺ እሱን ልተወው ይቅር፡፡

ምን እያልኩ ነበር? አዎ ሽብርና የሽብር ውሎ መልኩን ሳይቀይር አልቀረም ነበር ወሬያችን፡፡ እንግዲህ እንደምታውቁት ጎዳናው በሁለት ምድብ ከተከፈለ ቆይቷል። ተስፋ በቆረጡና ተስፋ በቀጠሉ፡፡ በነገራችን ተስፋ መቀጠልና መቁረጥ ወሬ ቆርጦ እንደ መቀጠል ቀላል አይደለም፡፡ ስላልሆነ ምን ሆነ? ‹ማን አቀርቅሮ ማን ተዝናንቶ ይኖራል› የምትል ነገር ተወልዳለች፡፡ ስለዚህ የትም ሳታውቁት አንዱ ቀረብ ብሎ ‹ዘመኑ አልቋል ንስሐ ግቡ› ሲላችሁ፣ ዕውን ስለእናንተ መዳን ተጨንቆ መሆኑን መጠራጠር አለባችሁ። እኔማ እንዴት አልጠራጠር? ያ አንዱ ያልኳችሁ ተስፋ አስቆራጭ ከቀበጣጠረ በኋላ ምን እንዳለኝ አልገርኳችሁም ለካ? “ያለህን ሁሉ ሸጠህ ለመንግሥት ግብር አስገባ፡፡ ከዚያ ወደ ቀድሞ ሕይወትህ ዞረህ ተንፍስ፤” አይለኝ መሳለችሁ? ካፒታሊስቶች ይቺን ቢሰሙ አስቡት በታደሰና ባልታደሰ ኦክስጂን ሲበዘብዙን። ኧረ ኡኡ!

ስለቤትና ቤተኛ እያሰብኩ ቤት ላሻሽጥ ደፋ ቀና እላለሁ። ቡልቡላ አካባቢ 175 ካሬ ላይ ያረፈች ቅልብጭ ያለች ‹ጂፕላስ ዋን› ካልገዛችሁ ብዬ መቆሚያ መቀመጫ ያሳጠኋቸውን ደንበኞቼ ጠየቁኝ። አዲስ ደንበኛ ማፍራት እንደሆነ ድሮ ቀርቷል። ምክንያቱማ ጊዜው የሞኖፖሊስቶች ነዋ፡፡ እና ከአሁን አሁን አንዱ ደወለ እያልኩ ስቁነጠነጥ ስልኬ ይጮሃል፡፡ “ሃሎ?” ስል “አንበርብር አውጣኝ፣ የዘንድሮን አውጣኝ፤” አለኝ ከወዲያ፡፡ “ማን ነህ? ለምን አትረጋጋም?” እላለሁ ዕርጋታ የዘመኑ ታርጋ ይመስል፡፡ “እንዴት ብዬ ልረጋጋ ፊልሜ ተሰርቆ?” አይለኝ መሰላችሁ? ቀስ ብዬ ሳጣራ እውነትም ፊልሙ ተሰርቆ አንበርብር ዘንድ ደውል ተብሎ ነው የደወለው፡፡ የዘመኑ ባለፀግነት የሕዝብ ሀብት በመመዝበርበር ላይ የተመሠረተ ይመስለኝ ነበር፡፡ ለካ ፊልም መስረቅም ይጨምራል። ቆም ብዬ ሳስበው ያበሽቀኝ ጀመር።

እኔ ደላላው አንበርብር ምንተስኖት ገዥና ሻጭ የማገናኝ ፕሮፌሽናል ደላላ እንጂ ሌባና ፖሊስ የምጫወት ሕገወጥ ደላላ ነኝ እንዴ? ብዬ ራሴ ላይ ጮህኩ፡፡ ውሎ አድሮ ከባሻዬ ልጅ ጋር ስናወራው፣ “ይቀልዳል እንዴ? ሰው ኑሮውን፣ ቤተሰቡን፣ አገሩን፣ ማንነቱን በቁሙ በሚዘረፍበት አገር ፊልሜ ተሰረቀ ብሎ ለአንተ ሲደውል ትንሽ አያፍርም?” ነበር ያለኝ፡፡ ‹የተማረ ይግደለኝ› ብዬ ሳልጨርስ የባሻዬ ልጅ የዘረዘራቸው ነገሮች ሌላ ራስ ምታት ሆኑብኝ። “የት ሄጄ ልሰደድ?” አለ ስደተኛው። ቆይ እኔ ምለው ህልምና ሐሳብ አልቆ ነው ሰው ፊልም ወደ መሰራረቅ የዞረው? ቢሆንስ እኔን የመሰለ ስመ ጥር ደላላ እዚህ ውስጥ ምን አገባው? አቤት ሰው። በፎቅ ላይ ፎቅ መሥራት የሚያቅተውን ተውት። ችግኝ ላይ ችግኝ ደርቦ የሚተክለውን ፊልመኛ ማን ይሆን ግን የሚሰርቀው? ያልተያዘ ግልግል ያውቃላ!

ግልግል ስል በቀደም ከአንድ ለማኝ ጋር በገላጋይ ተለያየሁ። እንጃ ዘንድሮ አመሌ ከፋ። ሆድ አልሰፋ ሲል ምን ይሁን? መታሰቢያ ማጣትም እኮ አንዱ ችግር ነው። በአፍ ሁላችንም እኩል ሆነን። ዕድሜ ለገንዘብ፡፡ ሐውልት የሚቆምለት ትልቅ ሰው ጠፋ፡፡ እና ምን ይመጣ ከዚህ በላይ? ለማኙ፣ ‹‹በነሐሴ!›› ይለኛል፡፡ ወር አያልቅም ብሎ፡፡ በኋላ፣ “አንተ ሰውዬ ከእኔ ምን አለህ?” ስለው እጁን ዘርግወቶ ያራግበው ጀመር። ልመና መሆኑ ነዋ፡፡ “በነሐሴ ጋሼ። አንድ ነሐስ ይጣሉልኝ፤” ይለኛል። ደግሞ ብለው ብለው በአባባሉ መጥተዋል (ጥልቅ ተሃድሶ እንዳይሆን ብቻ? እኔ አላልኩም ልብ አድርጉ)፡፡  ከማንጠግቦሽ ጋር ሳወራ፣ “ገና የቤተሰብህን ታሪክ አጥንተው በአያትህ ሙት ዓመት ይመጣሉ፤” አለችኝ። አሰብኩት። ቁጭ ብዬ ሳስበው የአያቴ አሟሟት ትዝ አለኝ፡፡የአሟሟቷን ሁኔታ እያሰብኩ የሚታየኝ የእኔ አኗኗር ነው።

አንድ ቀን ማልዳ ተነስታ እንደ ለመደችው አፏን ሳታሟሽ ቤተ ክርስቲያን ተሳልማ ስትመጣ መንገድ ላይ ‹‹እእ ወጋኝ. . .›› አለች በቃ በዛው ቀረች። ምን የለ ምን የለ። ጣር የለ ሕመም የለም፡፡ የባሻዬ ልጅ የአያቴን አሟሟት ባስታወሰ ቁጥር፣ ‹‹እግዜር አንዳንዴ ልክ እኛ ቴሌቪዥን ሲሰለቸን በሪሞት ኮንትሮል ድርግም እንደምናደርገው፣ በቅዝበት እልም ሲያደርግህ ምነኛ መታደል ነው፤›› እያለ የአሟሟቱ ጉዳይ ያስጨንቀዋል። እኔ አሁን ይኼን ሁሉ የማወራው ለምንድነው? በየየቀኑ መሞት ሰልችቶኝ ነዋ። ቆይ ግን እኔ ብቻ ነኝ ወይስ እናንተም አላችሁበት? ድሮ ድሮ ናፍቆትና ብርድ ይመስሉኝ ነበር በቁም የሚቀብሩት። ያኔ እንዳሁኑ ኑሮ ጣራ አልነካማ። ዛሬ ይኼውላችሁ በቀኝ በግራ ወጪ እያንዣበበኝ እኖራለሁ። ጭራሽ አሁንማ (መቼም እኔ ላይ የማይበረታ የለም) በመድኃኔዓለም ማለቱን ትቶ፣ “በነሐሴ ነሐስ” ዓይነት በአባባልና በምሳሌ የሚፈልጡኝም መተዋል። እኔስ ያለማውጣት አዋጅም ናፈቀኝ ጎበዝ!

ካነሳሁት አይቀር ስለገንዘብና አያያዙ ብዙ እንድንጫወት ፈልጌያለሁ። እኛና ገንዘብ እንዲሁ አሁን አሁን አይጥና ድመት ከመሆናችኔ በፊት እንዲያው ማን ይሙት የሠራነው ግፍ አይቆጠርም። በአጭሩ ‹ጢባ ጢቤ ተጫወትንበት› በተባለው ዓይነት ብንይዘው ይቀላል። ሌላ ገላጭ የለውም። ዛሬ እሱ በተራው ይኼው ያንቀረቅበናል። እኛም አያያዙን አንችልበት እሱም አንጠባጠቡን አብዝቶት፣ አዳሜ አግኝቶ በማጣት ተውኔት ሰማይ ነክቶ ሲፈርጥ የአልፎ ሂያጅ መሳቂያ ሆኗል። ከአወዳደቅ መማር ለእኛ አልተፈጠረምና የሳቅንም በዓመቱ ሊሳቅብን ተራ እንይዛለን። ኧረ አጀብ ነው። አጀብ ብለን ጀምረን ሳንጨርስ ደግሞ መስቀረም ሊጠባ ነው። ሌላ አጀብ። ታዲያ ምን ሆነ መሰላችሁ? ያቺን ቤት አሻሽጨ ኮሚሽኔን ተቀበልኩና ባሻዬ አስጠርተውኝ ወደ እሳቸው ሄድኩ። ከገጠር አንድ ዘመዳቸው ታማ እሳቸው ዘንድ አርፋ እየታከመች ነው።

“አንበርብር እስቲ አምስት ሺሕ ብር አበድረኝ። የዚህች ልጅ ነገር ትቼ ማልተወው ነው። ቶሎ አሳክሜ አገሯ ልስደዳት. . .፤” ሲሉኝ አንጀቴ ተንቦጫቡጮ፣ ኮሚሽኔን ዘረገፍኩላቸው። የልጅቷ ሕመም ቀላል ቢሆንም ባሻዬ ለምን ይጨናነቁ? የገዛ ቧሏ ሲደበድባት ኩላሊቷ ተበላሽቶ መሆኑን ባሻዬ ናቸው ያጫወቱኝ። እኔ ግን ይኼን እያየሁ መፈላሰፍ ያምረኛል። ገንዘቤ ናት። ሰጥቻቸውም በላችኝ። በፍልስፍና ካልሆነ በምኔ ልወጣው? የዚያን ሕገወጥ ሰው ሸክም ባሻዬ በምን ዕዳቸው ይሸከማሉ? ሕይወት ግን የምትጫወተው ቁማር ምን ዓይነት ነው? እያልኩ ሳወጣ ሳወርድ ኮሚሽኔን ረሳኋት። እኔ መስመር ስስት ገጠር የሚኖር ምስኪን ወገኔ ለምን ጎብጦ ይኖራል? የአንዱ የጥጋብ ግሳት ለምድነው ለሌላው እንደ ጦር ነጋሪት ድምፅ ሆኖ የሚሰማው? እያልኩ ጭልጥ እያለለሁ። ‹በደንባራ በቅሎ ቃጭል ተጨምሮ› ሆኖ ነገሩ፣ አንዱን ሳነሳው አንዱን ስጥለው ያለሁበትን ረስቼ ሥራ ፈትቼ የማታ ራቴ ለቁርስ ተሸጋግሮ አገኘዋለሁ። እም ነው እንጂ ሌላ ምን ይባላል?!

በሉ እንሰነባበት። ማለቱን እንላለን እንጂ መኖሩን ከተውን ቆይተናል። ንግግር የበዛው ለምን መሰላችሁ ታዲያ? እውነቴን ነው። ሰሞኑን ታዲያ እኔና የባሻዬ ልጅ በጊዜ ተገናኝተን በጊዜ ተጎንጭተን በጊዜ ወደ ቤታችን መሯሯጥ ይዘናል። የባሻዬ ልጅ  በችኮላ ወጥተን በችኮላ ስንገባ፣ እያየ ‹‹አወይ ኃላፊነትን መዘንጋት?›› ይላል። ‹‹የምን ኃላፊነት?›› ስለው፣ ‹‹አታይም እንዴ እያንዳንዳችን የገዛ ኃላፊነታችንን እየረሳን በሰላማችን፣ በህልውናችን ላይ የመጣውን ችግር። ‹ሳይቃጠል በቅጠሉን› ረስተን ይኼው እንደ ፖንፔ ሕዝብ ገሞራው ከፈንዳ በኋላ የሞት የሽረት ጨዋታ ስንጫወት፤” ሲለኝ ግራ ገብቶኝ ዝም አልኩ። እኔ እምልህ አልኩት ቀስ ብዬ። እ አለኝ። “ፖንፔ ማን ናት?” ስለው ከት ብሎ ስቆ፣ “አይ አንበርብር አረጀህ እኮ?” ብሎ ይስቅብኛል። እሱ የዓለምን ታሪክ ጠጥቶታልና እኔ ማስታወስ ሲያቅተኝ አረጀህ እባላለሁ። ወይ ዘንድሮ አለ ዘፋኙ። እናላችሁ ምሁሩ በየባሻዬ ልጅ በትንሹ ያጫወተኝ የፖንፔ ታሪክ መሰጠኝ። የፖንፔ ሕዝብ በአሁኒቷ ጣሊያን ግዛት ከዛሬ 2,000 ዓመት በፊት ይኖር የነበረ ሕዝብ ነው። ማሲቩየስ የሚባል ታላቅ ተተራ አጠገቡ አለ። ይኼ ተራራ ያልበረደ የእሳት ውኃ ውስጡ እያራገበ ከቀን ቀን ቅራኔው ሲጨምር የፖንፔ ሕዝብ ይበላ፣ ይጠጣ፣ ይዘፍንና ይዳራ ነበር።

አንድ ቀን አገር አማን ብሎ ሕዝቡ የዕለት ተዕለት ኑሮውን ሲያከናውን ያ እሳተ ጎሞራ ወጥቶ ፈሰሰበት። ወደ እኛ ፖንፔ ስዞርላችሁ እኔና የባሻዬ ልጅ ጥቂት እንደተያየን ለአፍታ አንገቴን ባዞር ከየት መጣ ያላልኩት ጠርሙስ በግንባሬ ትይዩ ይምዘገዘጋል። እንዴት እንደሳተኝ አምላክ ያወቃል። ቤቱ በአንድ እግሩ ቆመ። ስድብና ቡጢ እንደ ሆያ ሆዬ ተዛዝለው አበዱ። ምንም በማናውቀው ነገር በተቀመጥንበት ተቸክለን ቀረን። ፖሊስ መጣ። ታፍሰን ፖሊስ ጣቢያ። ማንጠግሽ ስትሰማ አሉ ጨርቋን ጥላ ልታብድ ምንም አልቀራት። መርማሪው ፀበኛውንና ሰላማዊውን ከለየ በኋላ የፀቡ መነሻ ሲጣራ ስም ሆኖ አረፈው። ስም እንዴት ያጣላል የምትሉ ጠይቁና ድረሱበት። እኮ ከዚህ በላይ ምን እሳተ ጎሞራ አለ ጎበዝ? ኧረ ‹ሳይቃጠል በቅጠል?› ብለን ብለን በስም እንጣላ? ዋ ‹ይኼም ቀን ያልፍና. . .› አለ ዘፋኙ። እስኪ ልብ እንግዛ። መልካም ሰንበት!