Skip to main content
x
‹‹ለፖሊስ ፈታኙ ጊዜ አሁን ነው››

‹‹ለፖሊስ ፈታኙ ጊዜ አሁን ነው››


ረዳት ኮሚሽነር አበበ ለገሰ፣ የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሌጅ ዋና ዳይሬክተር

ረዳት ኮሚሽነር አበበ ለገሰ የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሌጅ ዋና ዳይሬክተር ናቸው፡፡ ከኢትዮጵያ ፖሊስ ኮሌጅ በዕጩ መኰንንነት ተመርቀዋል፡፡ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሕግ ትምህርት የመጀመሪያ፣ እንዲሁም ከሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ በዓለም አቀፍ ሕግ ትምህርት ሁለተኛ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል፡፡ በሥራ ዓለምም የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽንን በማደራጀትና በአምቦ ሰንቅሌ ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት በመምህርነት አገልግለዋል፡፡ ከዚህም ሌላ የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ሆነው ሠርተዋል፡፡ በኦሮሚያ ፖሊስ ኮሌጅ እንቅስቃሴና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ዋና ዳይሬክተሩን ታምራት ጌታቸው አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ኮሌጁ መቼ ነው የተቋቋመው? ዓላማውስ ምን ነበር

ረዳት ኮሚሽነር አበበ፡- ኮሌጁ እንደ ኮሌጅ ከመመሥረቱ በፊት የኦሮሚያ ፖሊስ ማሠልጠኛ ማዕከል በሚል መጠሪያ በ1984 ዓ.ም. በጅማ ዞንና በአዳማ ከተማ ተመሠረተ፡፡ ከዚያም በ1985 ዓ.ም. አምቦ ሰንቅሌ ማሠልጠኛን በማዋሃድ አምቦ ሰንቀሌ በሚባል ቦታ ላይ ኦሮሚያ ፖሊስ ማሠልጠኛ በመባል አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቷል፡፡ በዚህ ግን መቀጠል አልቻለም፡፡ ምክንያቱም በየጊዜው እያደገ የመጣው የኅብረተሰቡ የፖሊስ አገልግሎት ፍላጎት በዘመናዊ መልክ መስጠት በማስፈለጉ እንዲሁም የምናሠለጥነው ፖሊስ ከዘመኑ ጋር መራመድ እንዲችል ከማሠልጠኛ ወደ ኮሌጅ ማሳደግ ግድ ሆኗል፡፡ በዚህም የተነሳ ቀድሞ ናዝሬት ሕፃናት ማሳደጊያ ይባል በነበረው ቦታ ላይ የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሌጅን በ2002 ዓ.ም. ለማቋቋም ተችሏል፡፡ ኮሌጁ በርካታ ዓላማዎች ያሉት ሲሆን፣ ከነዚህም መካከል ከክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ጋር በመተባበር ጥናትና ምርምር ማካሄድ ተደጋጋሚ ወንጀሎችን የሚፈቱበትን ጥናት ማድረግ፣ ወንጀሎች ከመከሰታቸው በፊት ምርምር ማካሄድና መፍትሔዎችን ማበጀት ተጠቃሾች ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- ወደ ኮሌጁ የሚገባ አንድ ሠልጣኝ ምን ምን መሥፈርት ነው ማሟላት ያለበት? ኮሌጁስ በምን መስክ ሥልጠና ይሰጣል? የመቀበል አቅሙስ ምን ያህል ነው?

ረዳት ኮሚሽነር አበበ፡- ወደ ኮሌጁ የሚገባ አንድ ሠልጣኝ በሁለት ዓይነት መንገድ ነው፡፡ አንደኛው ከትምህርት ቤት ጀምሮ በትንሹ አሥረኛ ክፍልን ያጠናቀቀ፣ ሙሉ ጤንነቱ በሕክምና የተረጋገጠ፣ ዕድሜው ከ18 እስከ 25 ዓመት የሆነና የፀባዩ ሁኔታ ምንም ወንጀል እንደሌለበት ከቀበሌ ጀምሮ ትምህርት ቤቱ የተመሰከረለት መሆን ይገባዋል፡፡ ለዚህም በኦሮሚያ ክልል ባሉ ከ7,000 በላይ ቀበሌዎች ማስታወቂያዎችን በመለጠፍ በመመልመል ብቁ የሆኑት የሚገቡበት ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ከፖሊስ ሠራዊት ውስጥ የሚመለመሉ ሲሆን፣ ይህም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መግቢያ ፈተና ወይም በመሰናዶ ትምህርት መልቀቂያ ፈተና ውጤታቸው ቢያንስ 2.2 ለወንድ፣ ለሴት ደግሞ 2 ነጥብና ከዚያ በላይ ያላቸው፤ የአገልግሎት ዘመናቸው ከአምስት ዓመት በላይ የሆናቸውና የመግቢያ ፈተናውን ያለፉ በዲፕሎማ ፕሮግራም በመመልመል የፖሊስ ሳይንስ ትምህርት ይሰጣል፡፡ ኮሌጁ የሚሰጣቸው የትምህርት ዓይነቶች በርካታ ሲሆን፣ ከነዚህ ውስጥ የመደበኛ ፖሊስ፣ ትራፊክ፣ አድማ ብተና፣ የወንጀል ምርመራ፣ በፖሊስ ሾፌርና እንዲሁም በየጊዜው በሚቀያየረው የፖሊስ ሳይንሳዊ ትምህርቶችን ይሰጣል፡፡ በአሁኑ ሰዓት የመቀበል አቅሙም ከ6,000 እስከ 7,000 ደርሷል፡፡   

ሪፖርተር፡- ኮሌጁ ከዘመኑ ጋር የሚራመድ ፖሊስ በማፍራት ደረጃ ምን እየሠራ ነው?

ረዳት ኮሚሽነር አበበ፡- የፖሊስ አገልግሎት በአሁኑ ሰዓት በጣም ፈታኝ ሥራ ውስጥ ይገኛል፡፡ ምክንያቱም ወንጀል በተለምዶ የሚከናወን አይደለም፡፡ ዛሬ ደግሞ ዘመኑ የረቀቀ ወንጀል በረቀቀ መሣሪያ የሚፈጸምበት ነው፡፡ ማኅበረሰቡንም ከነዚህ የረቀቁ ወንጀሎች ለመጠበቅ ፖሊስ ከሁሉም ቀድሞ መገኘት መቻል ግዴታ ነው፡፡ ለፖሊስ ፈታኙ ጊዜ አሁን ነው፡፡ ይህንን ካልተወጣን የሕግ የበላይነት ይጠፋና የኅብረተሰብ ያለመረጋጋት ይመጣል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ከዚህ ቀደም በተመሠረተው የኢትዮጵያ ፖሊስ ኮሌጅ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመሆን ለሠልጣኞቻችን በቴክኒክ ሙያ፣ በኮምፒውተር ጥቃት ላይ እየሠራን ሲሆን፣ ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ በአመራር፣ በኮምፒውተር ላቦራቶሪ፣ በረቂቅ ወንጀሎች አፈታት ዙሪያ ከውጪ ባለሙያዎችን በማስመጣት ሥልጠና እንጀምራለን፡፡ ይህም ሆኖ ግን ኅብረተሰቡ በሚፈልገው ልክ ዘመናዊ ፖሊሲ የማውጣት ሥራ ሠርተናል ማለት ግን አንችልም፡፡ ይህን ችግር ለመቅረፍ ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ ከ10,000 በላይ የሚሆኑ የፖሊስ አባላትን በመቀበል ችግሩን ከተጠቀሰው ቁጥር ለመቀነስ ግብ ጥለን እየሠራን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ከሌሎች የትምህርት ተቋማት ጋር ያላችሁ ግንኙነት ምን ይመስላል?

ረዳት ኮሚሽነር አበበ፡- በዚህ ዙሪያ ጥሩ ሥራ እየሠራን እንገኛለን፡፡ እነሱ ከእኛ የሚፈልጉት አለ፡፡ እኛም ከነሱ የምንፈልገው አለ፡፡ ለምሳሌ እነሱ የጥበቃ አገልግሎት የትምህርት ቤቶች ደኅንነት እንዴት እንደሚጠበቁ እንዲሁም ከሌሎች ጉዳይ ልምድ ይፈልጋሉ፡፡ እኛ ደግሞ አንድ ሠልጣኝ በፖሊስ ሳይንስ ትምህርት ብቻ በቂ ይሆናል ብለን አናምንም፡፡ ለምሳሌ በሕግ፣ በኮምፒውተር፣ በዲሲፕሊንና በድኅረ ምረቃ አስተማሪዎቻችን እንዲያሠለጥኑልን እንፈልጋለን፡፡ ምክንያቱም በአንድ ተቋም ብቻ ፖሊስ አሠልጥኖ ማውጣት ስለማይቻል በጋራ መሥራት የግድ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት በክልሉ ካሉ 15 ዩኒቨርስቲዎች ጋር ለመሥራት ደብዳቤ እየተጻጻፍን ሲሆን፣ ለጊዜው ከአርሲ፣ ከአምቦና ከአዳማ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ሥራ ጀምረናል፡፡  

ሪፖርተር፡- ፖሊስ ኮሌጅ ሰሞኑን የቀድሞ ፖሊሶች (በሥራ ላይ የነበሩትን) እየጠራ እንደ አዲስ እያሠለጠነ ይገኛል፡፡ ለምንድነው? ባለፈው ረብሻ የታዩ ክፍተቶች ስለነበሩ ነው?

ረዳት ኮሚሽነር አበበ፡- በእርግጥ መነሻው እሱ ባይሆንም በአገሪቱ በተለያዩ ቦታዎች የተከሰተው ችግር በእኛም ክልል ነበር፡፡ ለምሳሌ በዚህ ወቅት በፖሊስ ሠራዊቱ ላይ የታየው ክፍተት በጥናት ስናይ ሕዝቡ በፖሊስ አባላት ላይ የነበረውን ችግር፣ እንዲሁም በክልሉ የትራፊክ አደጋ ለምን እንደሚጨምር ለየንና እንዚህንና ሌሎች በአጠቃላይ በፖሊስ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ በተደረገው ጥናት የተገኘው ውጤት የፖሊስ አባሎቻችንን እንዲሁም በየትኛውም እርከን ያሉ አመራሮች እንደ አዲስ መሠልጠንና ተሃድሶ ማግኘት እንዳለባቸው በመታመኑ ነው ሥልጠና እንዲገቡ የተደረገው፡፡

ሪፖርተር፡- በጥናቱ የተገኘው ውጤት ምንድነው?

ረዳት ኮሚሽነር አበበ፡- በመሠረቱ አንድ የፖሊስ አባል በፖሊስ ሳይንስ ተመርቆ ወጣ ማለት ሁሌም ብቁ ሆኖ ነው የሚሠራው ማለት አይደለም፡፡ በየዘመኑ ከኅብረተሰቡ ፍላጎት አንፃር እየታየ መታደስ ያስፈልገዋል፡፡ እኛ ይህንን ሳናደርግ ቆይተናል፡፡ በዚህም በፖሊስ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ከታየው የግንዛቤ ክፍተት፣ ፖሊሳዊ ዲሲፕሊኖች መጥፋት፣ በተወሰኑ አባሎች ላይ ደግሞ የኪራይ ሰብሳቢነት መፈጠር፣ የተደራሽነት ችግር እንዲሁም ሕዝቡ ያነሳቸው የነበሩ የመርማሪዎች ማነስ ከተለዩት ችግሮች በጥቂቱ ሲሆኑ፣ በፖሊስና በፍትሕ አካላት ላይ በሕዝቡ ሲነሱ የነበሩ ጥያቄዎችን ለመመለስ የተሰጠ ሥልጠና ነው፡፡ ሥልጠናው የሚሰጣቸው እንደየሥራ ክፍሎቻቸው ሲሆን፣ በተከታታይም የማብቃት ሥራ በየደረጃው ኮሌጁ በአምቦ ሰንቅሌ፣ በአዳማ እንዲሁም በትውስት በወሰድነው አላጌ ግብርና ባሉት ካምፖች ይሰጣል፡፡

ሪፖርተር፡- በኮሌጁ ውስጥ እንደ ችግር የሚያነሱት ምንድነው?

ረዳት ኮሚሽነር አበበ፡- ኮሌጁ ያለበትን ችግር በማጥናት ለመንግሥት አቅርበን መልስ እየጠበቅን ቢሆንም፣ በአሁን ሰዓት ከፍተኛ የአቅርቦት ችግር አለበት፡፡ የቅበላ አቅማችን ከዓመት ዓመት እያደገ ቢመጣም ያሉት የመማሪያ ክፍሎች፣ በከባድ ሁኔታ ደግሞ የመኝታ ክፍሎች እጥረት፣ ቀድሞ ሜዳ የነበሩ በአሁኑ ሰዓት ባሉን ኮሌጆች አካባቢ ሁሉ ከተማ መስፋፋት፣ ኢላይብረሪ፣ አለመኖር አጋዥ የሆኑ የመማሪያ ቁሳቁሶች እጥረት እነዚህ ከፍተኛ ችግሮቻችን ናቸው፡፡ በትንሹ እነዚህ ችግሮች ቶሎ መፈታት ካልቻሉ ለሚቀጥለው ዓመት ለምንቀበላቸው ሠልጣኞች ጋር እንኳን ከባድ ነው የሚሆንብን፡፡

ሪፖርተር፡- ኮሌጁ በሚቀጥሉት ዓመታት ምን ለመሥራት አስቧል?

ረዳት ኮሚሽነር አበበ፡- ኮሌጁ ሲቋቋም ዓላማ እና ተልዕኮ አለው፡፡ ከተልዕኮው ደግሞ ዕቅዱ ይመነጫል፡፡ በዚህም ከ2010 ዓ.ም. የፖሊስ ሳይንስ ትምህርት በትንሽ ተማሪዎች የዲግሪ ፕሮግራም መጀመር፣ የቅበላ አቅሙን በማሳደግ 10,000 አዳዲስ የፖሊስ አባላትን ለማሠልጠን ዝግጅቱን ያጠናቀቀ ሲሆን፣ በተለይ ደግሞ በክልሉ የሚታየውን የመረጃ ሰብሳቢ ባለሙያ እጥረትን ለመቅረፍ የሚሠራ ይሆናል፡፡ ሌላው በአባሎች ላይ የሚታየውን የሕክምና አገልግሎት ችግር ለመቅረፍ በአቅራቢያቸው ቀላል ሕክምና የሚሰጧቸውን ባለሙያዎች በሚቀጥለው ዓመት ማስተማር ለመጀመር ለመንግሥት ያቀረብነው ጥያቄ ቃል በተገባልን መሠረት ቶሎ የሚፈጸም ከሆነ በክልሉ ያሰብነውን ዘመናዊና ተደራሽ የፖሊስ እንዲሁም የፍትሕ አሰጣጥ አገልግሎት በሰፊው ለመሥራት ዝግጁ ሆነን እየጠበቅን እንገኛለን፡፡

ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ ፖሊስ ቀን ለሁለተኛ ጊዜ እየተከበረ ይገኛል፡፡ ለእርሶ ምን ስሜት ይሰጥዎታል?

ረዳት ኮሚሽነር አበበ፡- ፖሊስ 365ቱንም ቀን በሥራ ነው የሚያሳልፈው፡፡ ከዚህ ቀን ውስጥ ደግሞ አንዱ ፖሊስ የሚታሰብበት ቀን ሲሆን፣ ለሞራልም ለሥራም ተነሳሽነት ደስ ይላል፡፡ ሌላው ፖሊስ ማለት ሕዝብ ነው፡፡ ወንጀልን የሚፀየፍ ሕዝብ ፖሊስ እንዲፈጠር ያደርጋል፡፡ ይህ ባህል የሁላችንም ማለት ነው፡፡ ስለዚህ መልካም በዓል ለሁላችንም ለማለት እወዳለሁ፡፡ ግሮጠ