Skip to main content
x
‹‹መደራጀትን ጨምሮ የጤንነትና የሥራ ላይ ደኅንነት ችግርን ማስተካከል ካልተቻለ ተጎጂ ዜጎች ወደ ልመና ነው የሚገቡት››

‹‹መደራጀትን ጨምሮ የጤንነትና የሥራ ላይ ደኅንነት ችግርን ማስተካከል ካልተቻለ ተጎጂ ዜጎች ወደ ልመና ነው የሚገቡት››

አቶ ካሣሁን ፎሎ፣ የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) ፕሬዚዳንት

በሠራተኞች የመደራጀት መብትና በሙያ ደኅንነት ዙሪያ ያሉ ችግሮች እየተባባሱ እንደመጡ በተለያዩ መንገዶች እየተገለጸ ነው፡፡ አገሪቱን ወደ ተሻለ የዕድገት ደረጃ ያራምዳሉ የተባሉ ኢንዱስትሪዎች እያቆጠቆጡ መሆናቸው ደግሞ፣ የሠራተኞችን መብት ከማስጠበቅ አንፃር ሥጋት ሊሆኑ የሚችሉ አጋጣሚዎችን ሊፈጥር ይችላል የሚል አመለካከትም እየተንፀባረቀ ነው፡፡ በተለይ የውጭ ኩባንያዎች በመደራጀት መብት ላይ ያላቸው አመለካከት ብዙ እያነጋገረ ሲሆን፣ የሥራ ላይ አደጋዎችም የሠራተኞች ወቅታዊ ችግር እየሆኑ ነው፡፡ እነዚህን ጉዳዮች በተመለከተ ዳዊት ታዬና ዮናስ ዓብይ የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) ፕሬዚዳንት አቶ ካሣሁን ፎሎን አነጋግረዋቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ከተለያዩ አገሮች ከመጡ የውጭ ኩባንያዎች አብዛኞቹ የሠራተኞች የመደራጀት መብትን እንደሚቃወሙ ይነገራል፡፡ እናንተም ይህንን ችግር ስትናገሩ ቆይታችኋል፡፡ አሁንም ችግሩ መባባሱ ይነገራልና በዚህ ላይ ምን እያደረጋችሁ ነው?

አቶ ካሣሁን፡- በአሁኑ ጊዜ ካለው የኢንዱስትሪ መስፋፋት ጋር ተያይዞ ብዙ ዜጎች ወደ ሥራ እየገቡ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር የሠራተኞች የመደራጀት መብትን በተመለከተ አሁንም የተፈታ ችግር የለም፡፡ ሆኖም በዚህም ችግር ውስጥ ሆነን ሠራተኛውን ለማደራጀት በተለያዩ መንገዶች ጥረት እናደርጋለን፡፡ ከአሠሪዎች፣ ከክልል ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮዎችና ከመንግሥት ኃላፊዎች ጋር በመነጋገር ሠራተኞችን ለማደራጀት ጥረት እያደረግን ነው፡፡ ነገር ግን አሁንም በርካታ ችግሮች አሉብን፡፡ አንዳንድ ኩባንያዎች ሠራተኞች እንዲደራጁ አይፈልጉም፡፡ አንዳንድ የውጭ ኩባንያዎች ሠራተኞችን ወደ ማኅበር እንዳትገቡ በማለት ክልከላ ያደርጋሉ፡፡ እኛ ሠራተኞችን የምናደራጀው መጀመሪያ ኩባንያዎቹን ጠይቀን ነው፡፡ ካልፈቀዱልን በራሳችን መንገድ በሠራተኛው የዕረፍት ቀን ሰብስበን እናደራጃለን፡፡ ይህንን ስናደርግ ግን የተለያዩ ጫናዎች ያጋጥሙናል፡፡ ለምሳሌ እኛ በዕረፍት ሰዓት ሠራተኛውን ለማደራጀት ስንጠራ አሠሪዎች ሠራተኞችን በ‘ኦቨርታይም’ ሥራ ግቡ ይላሉ፡፡ በተለይ በዱከም ኢንዱስትሪ ዞን ያጋጠመን ነገር አለ፡፡ በዚህ ዞን ውስጥ ያሉ የዘጠኝ ኢንዱስትሪዎችን ሠራተኞች ለማደራጀት ሞክረን ነበር፡፡ በእርግጥ በዘጠኙም የሠራተኞች ማኅበራት አሉ፡፡ ከዘጠኙ አንዱ መደራጀቱን ደግፎ ከማኅበሩ ጋር የኅብረት ስምምነት ድርድር ላይ ነው፡፡ ሥልጠና ስንጠራም ሠራተኞችን ይልካል፡፡ ቢሮም ሰጥቷቸዋል፡፡

በስምንቱ ኢንዱስትሪዎች ውስጥ ግን ሠራተኞች ተደራጁ እንጂ ማኔጅመንቶቹ ዕውቅና አልሰጧቸውም፡፡ ለማደራጀት ስንነሳ አንዳንዶቹ ኩባንያዎች ቀድሞ ከሚከፍሉት በላይ ‘ኦቨርታይም’ ከፍለው ሠራተኞች ወደ ስብሰባው እንዳይሄዱ ለማድረግ ይሞክራሉ፡፡ ሠራተኞች ግን ከፍተኛ ‘ኦቨርታይም’ ይከፈላል የሚለውን ማማለያ ትተው ለመደራጀት ወደ ስብሰባ አዳራሽ ነበር የመጡት፡፡ በዚህ መንገድ ካደራጀን በኋላም ያጋጠሙን ችግሮች ነበሩ፡፡ የሠራተኞቹን መደራጀት የሰማ አንድ ኩባንያ በማግሥቱ፣ ‹‹ትናንት የተደራጃችሁ ሠራተኞች ከማኅበሩ ካልወጣችሁ የሥራ ውላችሁን እናቋርጣለን›› ብሎ በይፋ ማስታወቂያ የለጠፈ አለ፡፡ ይህንን ማድረግ ወንጀል መሆኑን ከከተማው ሠራተኛና ማኅበራዊ ቢሮ ማስጠንቀቂያ ሲሰጠው ይቅርታ ጠይቆ ማስታወቂያውን አነሳው፡፡ ነገር ግን ማስታወቂያው ከተነሳ በኋላም ውስጥ ለውስጥ የሚደረግ ነገር ነበር፡፡ የሁለት የኢንዱስትሪ ዞኑ ኩባንያዎች የማኅበሮቹን ሊቀመንበርና ምክትል ሊቀመንበር አባረዋል፡፡ በሌሎቹ ኩባንያዎች ሠራተኞች ከማኅበር እንዲወጡ ግፊት ያደርጋሉ፡፡ ሌሎች ጫናዎችም ያሳድራሉ፡፡ በአንዱ ኩባንያ ውስጥ ደግሞ የሠራተኛ ማኅበር መሪውን ‘ኦቨርታይም’ እንዳይሠራ ይከለክሉታል፡፡ ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞችንም እንዳያገኝ ማኔጅመንቱ ሲገድበው፣ ሠራተኞች በነገሩ ተቆጭተው ‘ኦቨርታይም’ እንዳይሠራ የተከለከለውን የማኅበሩ መሪ በትርፍ ሰዓት ሥራ ሠርቶ ከሚያገኘው ጥቅማ ጥቅም በላይ የሚሆን ክፍያ እያዋጡ እየሰጡት ነው፡፡ ይህ ሠራተኛው ይህንን ያህል ኃላፊነት ያለበት መሆኑን ያሳያል፡፡ እንዲህ የሚያደርጉት አብዛኞቹ ወጣቶች ናቸው፡፡ መብታቸውን በደንብ ያውቃሉ፡፡ ስለዚህ መሪዎቻቸውን እንዲህ እየታደጉ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የሠራተኞች የመደራጀት መብትን የሚጫኑት የአገር ውስጥ ኩባንያዎች ናቸው? የውጪዎቹ? በየትኛው ይብሳል?

አቶ ካሣሁን፡- በየዘርፉ ይለያይ፡፡ ለምሳሌ ዱከም ኢንዲስትሪ ዞን ውስጥ ሠራተኞችን ለማደራጀት ፈቃደኛ የሆነ አንድ ኩባንያ ብቻ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- እነዚህ የውጭ ኩባንያዎች ሠራተኞች እንዳይደራጁ የሚፈልጉበት ዋነኛ ምክንያት ምንድነው ተብሎ ይታሰባል?

አቶ ካሣሁን፡- ሠራተኛው መብቱን ይጠይቀናል የሚል ነው፡፡ አሠሪዎቹ ለሙያ ደኅንነትና ጤንነት መስጠት ያለባቸውን ላለመስጠትና ይህንን ይጠይቀናል በማለት ነው፡፡ ሠራተኛው ሌላ አዲስ ጥቅማ ጥቅም ይጠይቀናል ብቻም ሳይሆን፣ በአዋጁ ላይ ያለው መብት እንዲከበርለት ይጠይቃል ከሚል የመነጨ  ነው፡፡ ለምሳሌ ደመወዛቸው አነስተኛ ስለሆነ መደራደራቸው አይቀርም፡፡ ይህንን ደግሞ አይፈልጉም፡፡ እንዲሁም በዱከም ከተማ በተደረገ አንድ ስብሰባ ላይ አንዱ የአሠሪ ተወካይ ተነስቶ ‘እኛ ከነኦቨር ታይሙ 13 ሰዓት ነው የምናሠራው’ አለ፡፡ ‘እንኳን ተደራጅተው አሁን ስምንት ሰዓት ካልሠራን እያሉ ሕገወጥ የሥራ ማቆም አድማ ያደርጋሉ’ ብሎ ተናገረ፡፡ ከመደበኛው የሥራ ሰዓት ሌላ አምስት ሰዓት ‘ኦቨርታይም’ ይጨምራሉ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ሠራተኛው 13  ሰዓት ሠርቶ ምን ያህል ጊዜ አርፎ ተመልሶ በማግሥቱ ወደ ሥራ እንዴት እንደሚገባ ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ ፋብሪካ ላይ እንዲህ ባለ ሁኔታ ረዥም ጊዜ መሥራት ከባድ ነው፡፡ እንደ ሌላ ሥራ አይደለም፡፡ ስለዚህ በዱከም በተደረገው ስብሰባ ላይ እንዲህ ያለ ነገር ሁሉ ተነስቶ ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- እናንተ ምን ምላሽ ሰጣችሁ? በሕግ የተቀመጠ የሥራ ሰዓት ያለ መሆኑንን አሠሪዎቹ አያውቁም?

አቶ ካሣሁን፡- እኛ የመለስንላቸው መጀመሪያ ሕገወጥ ሥራ የሠራው ማነው? ከሚለው ጥያቄ ተነስተን ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ሕገወጥ ሥራ የሠራው አሠሪው ነው፡፡ ከነኦቨርታይሙም ቢሆን ኢትዮጵያ ውስጥ ከአሥር ሰዓት በላይ አይሠራም፡፡ በሕጉ አሥር ሰዓት ነው ማሠራት የሚችሉት፡፡ ከዚያ በላይ ለማሠራት ሕጉ አይፈቅድም፡፡ አሠሪዎቹ 13 ሰዓት አንሠራም ብለው ሥራ ካቆሙ ማኅበር ሲመሠርቱ ደግሞ ከዚህ የበለጠ ሥራ ያቆማሉ የሚል አመለካከት አላቸው፡፡

ሪፖርተር፡- እነዚህ የውጭ ኩባንያዎች በአብዛኛው ከኢትዮጵያ የተሻለ ኢኮኖሚ ካላቸው አገሮች እንደመጡ ይታመናል፡፡ ከሠራተኞች መብትና አያያዝ ጋር በተያያዘ  ምናልባትም የተሻለ ሕግና አፈጻጸም ካላቸው አገሮች የመጡ ናቸው፡፡ እዚህ ሲመጡ ግን እዚያ አገራቸው የሚያከብሩትን ሕግና ደንብ ይተገብሩታል? ወይም በአገራቸው ለሠራተኞቻቸው የሚሰጡትን ክብር ያህል እዚህ ላሉት ይሰጣሉ?

አቶ ካሣሁን፡- አገራቸው ላለው የሚሰጡትን ያህል የሚለውን አይሰጡም፡፡ በኢትዮጵያ ሕግ መሠረት ለሠራተኛው የሚሰጠውን መብት መስጠትም አይፈልጉም፡፡ የእኛ ሕግ ከእነሱ የተሻለ ሆኗል፡፡ እንዲያውም አብዛኞቹ የመጡት በማደግ ላይ ካሉ አገሮች ነው፡፡ ካደጉ አገሮችም የመጡ አሉ፡፡ በአብዛኛው ግን በማደግ ላይ ናቸው ከሚባሉና ከኢትዮጵያ በተሻለ ደረጃ ላይ ካሉ አገሮች የመጡ ናቸው፡፡ ሆኖም ሠራተኛን በተመለከተ የእነሱን አገር ‘ስታንዳርድ’ ይቅርና የኢትዮጵያን ሕግ አክብረው አይሠሩም፡፡ ፍላጎታችን ይህን ሕግ አክብረው እንዲሠሩ ቢሆንም ይህንን አያከብሩም፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ለምሳሌ ቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ዞን ውስጥ ያለው ችግር አሠሪዎች ግንዛቤ የሌላቸው መሆኑ ነው፡፡ ሠራተኞች ቢደራጁ ፍርኃት ያለባቸው መሆኑን ተረድተናል፡፡

በቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ዞን ውስጥ ካሉ ኩባንያዎች የሠራተኞች መደራጀት ፍርኃት ያሳደረባቸው ምንድነው ብዬ በግሌ ሄጄ ጠይቄያቸው ነበር፡፡ የሰጡኝ ምላሽ ‘በሌሎች አገሮች ልክ የሠራተኛ ማኅበር ሲቋቋም የተለመደው የኅብረት ስምምነት ድርድር ከመጠየቁ በፊት የሥራ ማቆም ዕርምጃ ይወሰዳል፡፡ ሠራተኛው ማንኛውንም ጥያቄ ሲያቀርብ በሥራ ማቆም ነው የሚጀምረው፡፡ አሁንም እኛ እንዲህ እንዳይሆንብን ፈርተን ነው’ በማለት ገልጸውልኛል፡፡ እንደገናም ‘እኛ ብዙ ደንበኞቻችን ብዙ የምርት ጥያቄዎች ያቀርቡልናል፣ ይህንን በአግባቡ አምርተን ማስረከብ ስላለብን ሥራ አቁመው ይህ እንዳይስተጓጎልብን ነው የምንፈራው’ ብለው ይሠጋሉ፡፡ እነሱ ዘንድ ያሉ ሠራተኞችም ሥጋት አለባቸው፡፡ አንዳንድ ሠራተኞችን ሳናግር ስለመደራጀት የምንነጋገረው ከግቢ ከወጣን በኋላ ነው ብለውኛል፡፡ ይህንን ግቢ ውስጥ ብንነጋገር አሠሪው ያባርረናል ብለን እንፈራለን ይላሉ፡፡ ስለዚህ ሁለቱም ዘንድ ሥጋት አለ፡፡

ነገር ግን እኛ ደግሞ ሥራ ማቆም ሊፈጠር የሚችለው በድርድር መስማማት ሳይቻል እንጂ፣ ዝም ብሎ አይደለም ብለን በደንብ አስረድተናቸዋል፡፡ ድርድር ሲጀመር ሁለት ሦስት ቀን ሥራ ይቁም የሚል ሕግ የለንም፣ ሳትስማሙ ስትቀሩ ብዙ ውይይት አድርጋችሁ ልትስማሙ ካልቻላችሁ ብቻ ሊፈጠር የሚችል ነገር ነው ብለን አስረዳን፡፡ በእርግጥ በአንዳንድ አገሮች የኅብረት ስምምነት ድርድር ለመጀመር ሲሉ ሥራ ያቆማሉ፡፡ እዚህ ግን እንዲህ የለም፡፡ መጀመሪያ የኅብረት ስምምነት ትጠይቃለህ፡፡ በተደጋጋሚ ትደራደራለህ፡፡ መጨረሻ ላይ ተደራድረው አሠሪዎች የፈረሙትና ይሰጣል የተባለውን ከከለከሉ እስከ ሥራ ማቆም ትሄዳለህ፡፡ በዚህ ከተስማማን በኋላ ነገሩን በመገንዘብ ይህ ከሆነ መደራጀት ይችላሉ ችግር የለብንም ብለው፣ አሁን አንድ አምስት ማኅበራት ተደራጅተዋል፡፡ ማደራጀቱን እንቀጥላለን፡፡ ይለያል የምንለው ለዚህ ነው፡፡ ለምሳሌ ዱከም ኢንዱስትሪ ዞንና ቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክን አታወዳድርም፡፡ ተነጋግረን መግባት ትችላለህ፡፡ ወደ ዱከም ኢንዱስትሪ ዞን ስትሄድ እዚያ ያሉ የቻይና ኩባንያ አሠሪዎች ለአንተ ሲሆን ቋንቋ አንችልም ይሉሃል፡፡ አማርኛም እንግሊዝኛም አልችልም ይሉሃል፡፡ ለራሳቸው ሲሆን ግን አማርኛ ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ በዱከም በተደረገ ስብሰባ ላይ የቻይናዎቹ አሠሪዎች ተወካዮች አስተርጓሚ ይምጣላችሁ ስንል አማርኛ ይችላሉ ተባልን፡፡ ስለዚህ በቅን ልቦና መነጋገር ይቻል ነበር፡፡ እነዚህ ስምንት የቻይና ኩባንያዎች ለመግባባት ጥረት አያደርጉም፡፡

ሪፖርተር፡- ከኢንዱስትሪ ፓርኮች መስፋፋት ጋር ተያይዞ ለምሳሌ በቅርቡ ወደ ሥራ የገባው የሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ የሠራተኞች የመነሻ ደመወዝ ዝቅተኛ ነው ተብሎ እየተተቸ ነው፡፡ እናንተም ይህንን ጉዳይ ይዛችሁታል፡፡

አቶ ካሣሁን፡- በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ የሚሠሩ ሠራተኞች መነሻ ደመወዝ 650 ብር ነው፡፡ በፓርኩ 42 ከሚሆኑት ውስጥ 17 ኩባንያዎች ወደ ሥራ ገብተዋል፡፡ ግን የሁሉም ኩባንያዎች መነሻ ደመወዝ 650 ብር ነው፡፡ የቤት አበል 400 ብር አላቸው፡፡ ይህንን መነሻ ደመወዝ የተከሉት ደግሞ በኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ያሉ ኩባንያዎች ተሰባስበው በመሠረቱት ማኅበር አማካይነት ነው፡፡ ኩባንያዎቹ ማኅበር ሲኖራቸው የሠራተኞች ማኅበር ግን የለም፡፡ ኩባንያዎቹን በአባልነት የያዘው ማኅበር መነሻ ደመወዙን በተመሳሳይ 650 ብር ያደረገው፣ በፓርኩ ውስጥ ያሉ ሠራተኞች ከአንዱ ኩባንያ ወጥተው ወደ ሌላኛው ኩባንያ እንዳይገቡ ለማድረግ ነው፡፡ ነገር ግን ሠራተኞች እስካሁን አልተደራጁም፡፡ ለማደራጀት ከኢንቨስትመንት ኮሚሽን ጋር ተወያይተናል፡፡ የኢንዱስትሪ ፓርኩንም ሄደን ጎብኝተናል፡፡ ሠራተኞችንም አነጋግረናል፡፡ አንደኛ ብዙ ሠራተኞች ከሐዋሳ ወጣ ካሉ ገጠሮች የሚመጡ ናቸው፡፡ ሐዋሳ ደግሞ በትንሹ የቤት ኪራይ የሚጠየቁት አምስት መቶና ስድስት መቶ ብር ነው፡፡ የኢንዱስትሪ ፓርኩን በጎበኘንበት ወቅት የተወሰኑ ሴት ሠራተኞችን አነጋግረን ነበር፡፡ አንዷ ወደ ዓረብ አገር ለመሄድ በሒደት ላይ ላይ መሆኗን፣ በዚህ ደመወዝ ቤት ኪራይ ከፍላና ምግብ በልታ ልትኖር እንደማትችል ተናግራለች፡፡ ነገር ግን ከገጠር ስለመጣችና አማራጭ ስለሌላት የዓረብ አገር ጉዞዋ ሒደት እስኪያልቅ እዚያ እየሠራች እንደምትጠባበቅ ነው መልስ ያገኘነው፡፡ ስለዚህ አሁን ከፓርኩ ከማኅበርና ከኢንቨስትመንት ኮሚሽን ጋር እንነጋገርና ሠራተኞችን እናደራጅ የሚል ሐሳብ ነበረን፡፡ እስካሁን መፍትሔ አላገኘንም፡፡ ሠራተኞች ግን የእንደራጅ ጥያቄ እያቀረቡልን ነው፡፡ ሌሎች ወገኖችም እንዲደራጁ ይፈልጋሉ፡፡

በነገራችን ላይ ሠራተኞችን ስናደራጅ እንደ ቀድሞ አይደለም፡፡ አሠራራችንን ቀይረናል፡፡ የአካባቢውን ሕዝብ በማነጋገር ማደራጀቱን አብረውን እንዲሠሩ እናደርጋለን፡፡ የክልሉ ወጣቶችና ሴቶች ማኅበራትም በዚህ የማደራጀቱ ሥራ ላይ እንዲካተቱ አድርገናል፡፡ አሁን ከትናንት [ማክሰኞ ነሐሴ 2 ቀን 2009 ዓ.ም.] ጀምሮ ወደማደራጀቱ ገብተናል፡፡ ምክንያቱም እኛ ብቻችንን ዝም ብለን ብንገባ የሆነ ነገር ቢፈጠር ድርጅቱን ማወክ እንዳይመስል፣ ሁሉም ማኅረሰብ ይህንን እንዲቀበለውና እንዲያግዘን ለማድረግ ነው፡፡ ከአሁን በኋላም የማደራጀት ሥራ ስናከናውን እንዲህ ያለውን መንገድ ተጠቅመን ነው የምንሠራው፡፡

ሪፖርተር፡- መንግሥት ቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንት ለመሳብ የውጭ ኩባንያዎች ገብተው እንዲሠሩ የተለያዩ ማበረታቻዎችን ይሰጣል፡፡ ምናልባት የውጭ ኢንቨስትመንቶችን ከመሳብና ለእነሱ ነገሮችን ከማመቻቸት አንፃር መንግሥት ሠራተኛው ላይ ጫና ሲደርስ ቀዝቀዝ ያለው እነሱን ለመደገፍ ተብሎ ነው ይባላል፡፡ ስለዚህ መንግሥት የሠራተኞችን መብት ማስጠበቅ ሲገባው ቸልተኛ ሆኗል? ለሠራተኞች ቅድሚያ አልሰጠም?

አቶ ካሣሁን፡- ቅድሚያ ብቻ አይደለም፡፡ የሠራተኞች መነሻ ደመወዝ 650 ብር ነው ብለን ስናነሳ፣ አንዳንድ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች እንዴት ኢሠማኮ ስለዚህ ደመወዝ ጉዳይ ያነሳል? ስለደመወዙ ከማንሳት ሠራተኞቹ ምን ያህል ምርታማ ናቸው ብላችሁ በቅድሚያ ለምን አትጠይቁም? ይላሉ፡፡ ነገር ግን ምርታማነትና ደመወዝ ተለያይተው አይሄዱም፡፡ በልቶ ያላደረ ሰው ሊሠራ አይችልም፡፡ ምርታማ አይሆንም፡፡ የምትነጋገረው በልተህ እንጂ ሳትበላ አይደለም፡፡ ስለዚህ እንኳንስ ለዚህ ቅድሚያ ለመስጠት ቀርቶ የደመወዙን አነስተኝነት ስናነሳ እንዲህ ያለ መልስ የሰጡን አንዳንድ ባለሥልጣናት አሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች ለምን ኢሠማኮ ይህንን ጥያቄ ያነሳል ብለው ይሞግቱናል፡፡ 650 ብር ደመወዝ ሆኖ 400 ብር የምግብ አበል ይከፈላቸዋል ይላሉ፡፡ አዎ ይከፈላል፡፡ ነገር ግን በቂ አይደለም ብለን ነው የምንከራከረው፡፡ የቤት ኪራዩን ጉዳይ ስናነሳ ደግሞ የፓርኩ ሠራተኞች በአነስተኛ ዋጋ እንዲያገኙ ከክልሉ መንግሥት ጋር ተነጋግረን ቤት እየተሠራ ነው ይላሉ፡፡ ይህም ቢሆን በነፃ ቤቱ አይሰጥም በኪራይ ነው፡፡ ይኼም ሆኖ ከ50 ዶላር በታች የሚያገኝ ሰው ከድህነት ከተቀመጠው ወለል በታች ነው፡፡ የደሃ ደሃ ሆኖ ሥራ ያለው ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ኢሠማኮ ይህንን ማንሳት ግዴታው ነው፡፡ 

ሪፖርተር፡- በነገራችን ላይ ኩባንያዎች ተሰባስበው ደመወዝ ይህንን ያህል ነው በማለት ዋጋ ተምነው ማስቀመጥ ይችላሉ? በሕግ አንተ ከዚህ በላይ አትክፈል፣ እኔም ከዚህ በታች አልከፍልም ማለት ይቻላል?

አቶ ካሣሁን፡- ይኼ የማኅበር ስምምነት ነው፡፡ በሕግ የተቀመጠ ነገር አይደለም፡፡ ይኼ ትክክል አይደለም ብሎ ሌላ ወገን ካልተነሳ አስቸጋሪ ነው፡፡ እነሱ ይህንን ሲወስኑ እንደ አሠሪ ነው፡፡ በጽሑፍ አድርገው ተፈራርመው ላይሆን ይችላል፡፡ ማኅበራቸው ግን ይህንን  ወስኗል፡፡ ግን ደመወዙ እንዴት እኩል ሆነ? ይህንን ውሳኔ የተገበረው እንዴት ነው? ማኅበሩ ሕጋዊ ሰውነት አለው ወይም የለውም የሚለውን ባላውቅም ሠራተኞቹ መደራጀት አለባቸው፡፡ ሲደራጁ ደግሞ ሊነጋገሩ የሚችሉት በዚህ ጉዳይ ነው፡፡ አንዳንድ የመንግሥት ኃላፊዎች ይህንን ለምን ትጠይቃላችሁ እንደሚሉን አላውቅም፡፡ ኢሠማኮ ይህንን ካላነሳ ማን ሊያነሳ ነው ታዲያ?

ሪፖርተር፡- የሠራተኞች መብት ሲነሳ በትክክል መብቱ እንዲጠበቅና እንዲከበር ይጠበቃል፡፡ እናተም ስለመብቱ መሞገታችሁ ትክክል ነው፡፡ በሌላ በኩል ግን አሁን ለአገር ጠቃሚ ይሆናሉ የተባሉ ኢንዱስትሪዎች ውስጥ ያሉ ሠራተኞች ከእነዚህ ኢንዱስትሪዎች አቅም ጋር እንዲራመዱና ምርታማ እንዲሆኑ ለማስቻል ምን ያደረጋችሁት ነገር አለ? ለሠራተኛው መብት ብቻ እንቁም ማለት ብቻ ሳይሆን፣ እንዲህ ያሉ ጠቃሚ ኩባንያዎች ውስጥ ያሉ ሠራተኞችን በማብቃት ረገድ ምን ሠርታችኋል?

አቶ ካሣሁን፡- በጣም ጥሩ፣ በመጀመርያ ደረጃ ይህንን ለመሥራት ማኅበር መኖር አለበት፡፡ የተበታተነ ሠራተኛ ዘንድ ሄደን መነጋገር አንችልም፡፡ እኛ ከምንሠራቸው አንዱ የሠራተኛውን አመለካከት እንለውጥና በጋራ ምርታማ እናድርግ ነው፡፡ ተገቢው ክፍያ ይከፈለው፣ ለምርታማነቱ ደግሞ ከመንግሥትና ከአሠሪው ጋር በጋራ እንሥራ ነው፡፡ በእኛ በኩል ሠራተኛው የሥራ ባህሉን እንዲያሻሽል፣ ስለኢንዱስትሪና ስለመብቱም እንዲያውቅ ማድረር አለብን፡፡ መብቱን ብቻ ሳይሆን ግዴታውንም ጭምር ነው እኛ የምናስተምረው፡፡ ይኼንን ለማስተማር ደግሞ መጀመሪያ ሠራተኛው መደራጀት አለበት፡፡ ካልተደራጀ በምን ሁኔታ እናገኘዋለን? ስለዚህ እኛ እንዲያውም እንደ ሌሎች አገሮች በውይይት ሊመለሱ በሚችሉና በቀላል ጥያቄዎች ሰበብ የኢንዱስትሪው ሰላም እንዳይረበሽ ለማድረግ በመጀመሪያ በውይይት እንዲፈታ ነው የምንፈልገው፡፡ ኢንቨስትመንት ኮሚሽንን የምንጠይቀውም ከማኅበሩ ጋር እንዲያገናኘን ነው፡፡ ሠራተኛው ቢደራጅ ሥጋታቸው ላይ መነጋገር እንፈልጋለን፡፡  

ግን ደግሞ ስንነጋገርና የሠራተኞችን መብት ስንጠይቅ ዝም ብለን ከልክ በላይ የሆነ ጥያቄ ይዘን አይደለም፡፡ ድርጅቱ ሊሸከም የማይችለውን ጥያቄ አይደለም የምንጠይቀው፡፡ ነገር ግን መነሻ ደመወዙ 650 ብር ሆኖ መሥራት አይችልም ነው፡፡ ኩባንያዎቹም ምርታማ አይሆንም ነው፡፡ ሠራተኞች በዚህ ደመወዝ በመሥራታቸው ለሥራ ላይ አደጋ ይጋለጣሉ ነው የምንለው፡፡ በዚህ ደመወዝ እየሠራ ማታ ለእራት ስለሚከፍለው ገንዘብና ስለቤት ኪራይ ክፍያ ያስባል? ወይስ ስለሥራው? እጁ ይቆረጣል፣ ዓይኑ ይጠፋል፡፡ ስለዚህ ሠራተኛውም ሆነ ድርጅቱ በማይጐዱበት ሁኔታ ተባብረን እንሥራ ነው ያልነው፡፡ ይህ የማይሆን ከሆነ አስቸጋሪ ነው፡፡ አንዳንዶቹ ኩባንያዎች የኢንዱስትሪ ሰላም ከተናጋባቸው እንደ ባንግላዴሽ ካሉ አገሮች ነቅለው የመጡ ናቸው፡፡ ከባንግላዴሽ እንዴት መጡ? እኛ እናውቃቸዋለን፡፡ ሠራተኛው ጥያቄ ስለሚያነሳና ሁልጊዜ የሥራ ማቆም አድማ ዕርምጃ ስለሚወሰድ ነው የመጡት፡፡ እዚህም ይህ እንዳይሆን ምን መተማመኛ አለ? 

ሪፖርተር፡- በአነስተኛ ደመወዝ ተቀጠረ የሚባለው የፋብሪካ ተቀጣሪውን ብቻ አይደለም፡፡ በሌሎች የግልና የመንግሥት ተቋማት ውስጥ ሊከሰት ይችላል፡፡ በሌላ በኩል ሲታይ ደግሞ አነስተኛም ሆነ ከፍተኛ ደመወዝ ተከፋይ የሆነው ሠራተኛ በኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛውን ደረጃ የሚይዝ ግብር ከፋይ ነው፡፡ ከፍተኛ ግብር የሚሰበስበውም ከሠራተኛው ሆኖ ሳለ መንግሥት ለዚህ ሠራተኛ በታክስ የሚያስገባውን ገቢ ያህል መብቱን በማስጠበቅ ረገድ ውለታውን እየመለሰ ነው? የውለታውን ያህል እየደገፈው ነው?

አቶ ካሣሁን፡- አይደለም፡፡ ምንም ክርክር የለውም፡፡ አሁን የኢንዱስትሪ ፓርኮችን አነሳን እንጂ የውጭም ሆነ የአገር ውስጥ ኩባንያዎች ሆቴሎችን ጨምሮ መደራጀትን እንቢ ያሉ አሉ፡፡ ሌላው ቀርቶ በአዲስ አበባ ዙሪያ ሆቴሎችን ጨምሮ ወደ 92 ድርጅቶችን ለይተናል፡፡

ሪፖርተር፡- የሠራተኛ ማኅበር መደራጀት ያልፈቀዱ ማለት ነው?

አቶ ካሣሁን፡- አዎ! 92 ለይተናል፡፡ መንግሥት እነዚህን ድርጅቶች ስለሕጉ እንዲያሳውቅልን እንፈልጋለን፡፡ የአዋጁን አስፈጻሚ አካል ጠርቶ ቢያንስ መደራጀት ሕጋዊና ሰብዓዊ መብት ነው፣ መደራጀት የሰብዓዊ መብት አካል ነው በማለት ድርጅቶቹን እንዲያሳምንልን ነው፡፡ የእኛ ጥያቄ መንግሥት ያደራጅልን አይደለም፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያ ደግሞ እነዚህን የሰብዓዊ መብቶች ተቀብላለችና ይህንን እንዲቀበሉ ቢያንስ ግንዛቤ ስጧቸው በማለት ነው የአዋጁን አስፈጻሚ አካል የምንጠይቀው፡፡ ይህንን መንግሥት ካላደረገ ድጋፍ እየሰጠ ነው የምንለው እንዴት ነው? ሠራተኛው ግን አንድ ብር ታክስ ቢያስቀር በሕግ ይጠየቃል፡፡ ማድረግም አይችልም፡፡ ምክንያቱም በፔሮል ስለሚከፈለው ግብሩን ይከፍላል፡፡ ይህ ለመንግሥት ትልቁ አጋዥ ነው፡፡ የውጭም ሆነ የአገር ውስጥ የግል ድርጅቶች የሠራተኞቻቸው ደመወዝ በጨመረ ቁጥር የመንግሥት ገቢ ይጨምራል፡፡ ይህ ምንም ጥያቄ የለውም፡፡

ሪፖርተር፡- ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሠራተኞች ቅጥርን በተመለከተ አዲስ አሠራር እየተተገበረ ነው፡፡ አንዳንድ ኩባንያዎች ሠራተኞችን ከኤጀንቶች ይወስዳሉ፡፡ እነዚህ ሠራተኞች የፋብሪካው ወይም የኩባንያው ቀጥተኛ ተቀጣሪዎች አይደሉም፡፡ በኤጀንቱ የተቀጠሩ በመሆናቸው መብታቸውን ለማስከበር እያስቸገረ ነው፡፡ ለምሳሌ በቅርቡ የዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ ሠራተኞች በኤጀንቶች ተቀጥረው የገቡ በመሆናቸው ምክንያት በተጠፈረ ችግር ሥራ አቁመው ነበር፡፡ እንዲህ ያለው የቅጥር ሁኔታ እንዴት ይታያል? እንዲህ ዓይነት ቅጥር ላይ ኤጀንቱ ከፋብሪካው በሚሊዮኖች የሚገመት ገንዘብ ተቀብሎ ለሠራተኞቹ የሚከፍለው በጣም ጥቂት ነው እየተባለ ነውና በዚህ ላይ ምን አስተያየት አላችሁ?

አቶ ካሣሁን፡- ይህ እንዲያውም የተሻለ ነው፡፡ ከዚህም የባሰ አለ፡፡ እናንተ ያያችሁት የተሻለውን ነው፡፡ የተሻለ ስል ‘አውትሶርስ’ የሆነውን ነገር ነው፡፡ አንዱ ኤጀንት ይወስድና ሠራተኛ ቀጥሮ ያሠራል፡፡ ከድርጅቱ ገንዘብ ይወስዳል፡፡ ለሠራተኞቹ ደመወዝ ይከፍላል፡፡ ስታመዛዝን የተሻለ ነው ያልኩበት ምክንያት ኤጀንቱ ራሱ ሥራውን ይመራል፡፡ ኤጀንቱ ካርቶን የመጫንና የማውረድ ሥራውን ሊሆን ይችላል የወሰደው፡፡ ወይም ደግሞ ኦፕሬተር ሊሆን ይችላል፡፡ ይህንን ሥራ ራሱ ይወስድና ሰው ቀጥሮ ደመወዝ እየከፈለ ያሠራል፡፡ ግን ከድርጅቱ የሚቀበለው ገንዘብ ከፍተኛ ነው፡፡ ለሠራተኞቹ የሚከፍለው ግን ዝቅተኛ ነው፡፡ ይኼንን ጥሩ ነው ያልኩት ቃሊቲ አካባቢ ሠራተኛ ስናደራጅ ያጋጠመ ነገር ስላለ ነው፡፡ ኤጀንቱ ሥራውን አይመራም፡፡ ዝም ብሎ 20 ሰዎች ይይዝና ለአንድ ኩባንያ ይሰጣቸዋል፡፡ ሥራውን የሚቆጣጠረው ኩባንያው ነው፡፡ ቅጥሩ ግን ሌላ ኤጀንሲ ጋ ነው፡፡ ኤጀንሲው ሥራ የለውም፡፡ በሰጣቸው ሰዎች ቁጭ ብሎ ኮሚሽን ይባላል፡፡

በ20 ሠራተኞች ስም በነፍስ ወከፍ አራት ሺሕ ብር ትወስድና ለሠራተኞቹ ሁለት ሁለት ሺሕ ብር ትከፍላለህ፡፡ ያለ ምንም ችግር 40 ሺሕ ብር አገኘህ ማለት ነው፡፡ እንዲህ ያለው ሥራ በሰው መነገድ ነው፡፡ አንዳንድ ኤጀንሲዎች ሥራውን ነው ‘አውትሶርስ’ አድርገው የሚወስዱት፡፡ ጥበቃ ከሆነ የጥበቃ ሥራውን ጠቅልለው ይወስዱና ራሳቸው ይቆጣጠሩታል፡፡ ራሳቸው ይመሩታል፡፡ ደመወዙንም ከዚያ ተቀብለው ይሰጣሉ፡፡ መደራጀት ላይ ስትመጣ ይህንን እነሱን መጠየቅ ትችላለህ፡፡ አሁን የተቸገርነው ‘አውትሶርስ’ ወስዶ ከሆነ ኤጀንሲው ነው ተጠያቂ የሚሆነው፡፡ ማደራጀትም ያለበት እሱ ነው፡፡ መደራደርም ካለበት ሥራ ስላለው ይችላል፡፡ ይኼንን ፋብሪካውን ስትጠይቀው ‘ሥራ ላይ ልመራቸው እንጂ ለእነሱ ፈቃድ መስጠት አልችልም፡፡ ይደራጁ አይደራጁ የማውቀው ነገር የለም፣ አያገባኝም’ ይላል፡፡ ኤጀንሲው ዘንድ ስትሄድ ደግሞ እንዳንዴ ቢሮዋቸውንም አታገኝም፡፡ ቢሮዋቸውን አግኝተህ ስትጠይቃቸው ደግሞ ‘እኔ አንድ ጊዜ ሥራ እንዲያገኙ ቀጥሬ ለኩባንያዎቹ ሰጠኋቸው እንጂ ከዚያ በኋላ የእኔ ጉዳይ አይደለም፡፡ እኔን አያጋባኝም፣ ሂዱና ኩባንያውን ጠይቁ’ የሚሉም አሉ፡፡ ይልቁንስ አዲስ በሚወጣው ረቂቅ አዋጅ ላይ ይህንን ሕጋዊ ለማድረግ እየተሞከረ ነው፡፡ ዝም ብሎ ሠራተኛ ቀጥሮ ለአንዱ ኩባንያ ለመስጠት በአሠሪና በሠራተኛ አዋጅ ላይ እንዲካተት ረቂቅ ቀርቧል፡፡ እኛ ግን አልተቀበልነውም፡፡

ሰው እተተበዘበዘ ነው፡፡ ከኩባንያው አራት ሺሕ ብር ወስዶ እሱ ላስቀጠረው ሠራተኛ ሁለት ሺሕ ብር እየከፈለ ሥራውን እየመራ የሚኖር ሞልቷል፡፡ የእሱ ብዝበዛ እንዳለ ሆኖ አሁን ደግሞ የባሰው ምንም ሥራ ሳይኖረው ለሚሠራው ኤጀንት ሕግና ዕውቅና ለመስጠት እየተሞከረ ነው፡፡ ስለመደራጀት ሲነሳ ኩባንያው እኔ አላውቅህም ይላል፡፡ ከእኔ ጋር የቅጥር ውል ስለሌለህ ሥራህን ሠርተህ መሄድ እንጂ፣ ምንም የምትጠይቀኝ መብት የለህም ይባላል፡፡ የእኛ ጥያቄ ይህ ነው፡፡ ሠራተኞቹ የት ይሂዱ? አሁን በተጨባጭ ይዘን ያለነው ጉዳይ በመሆኑ በቅርቡ በኢሠማኮ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ውሳኔ ይሰጥበታል ብዬ አስባለሁ፡፡ ዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ አካባቢ የተፈጠረውንም እናውቀዋለን፡፡ ይህን ጉዳይ ስንመለከት ፈቃድ የተሰጠው ኤጀንት ከፋብሪካው ጋር ባለው ስምምነት መሠረት ሠራተኞችን አሰባስቦ በራሱ ቅጥር ፈጽሞ ለፋብሪካው ያቀርባል፡፡ ፈቃዱን የሰጠው የኦሮሚያ ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ስለሆነ ሠራተኞችን እየበዘበዘና በደል እየፈጸመባቸው በመሆኑ ሠራተኞቹ ሲያመለክቱ ስለነበር፣ የክልሉ ቢሮም ዕውቅናውን (ፈቃዱን) ቀማው፡፡ ሠራተኞቹን ስሞታቸውን ለፋብሪካው ቢያቀርቡም እኔ አይደለሁም የቀጠርኳችሁ ኤጀንታችሁን ጠይቁ ስላላቸው ነው ውዝግቡ የተፈጠረው፡፡ በዚህ የተነሳ ነው ክልሉም ፈቃዱን ወደ ማገድ ዕርምጃ የገባው፡፡

ሪፖርተር፡- ስለዚህ ሠራተኞች በደል ስለደረሰባቸው የቢሮውን ዕርምጃ ኢሠማኮ ሙሉ ለሙሉ ደግፎታል?

አቶ ካሣሁን፡- ይህን ዕርምጃ በአንድ በኩል ስናየው ትክክለኛ ዕርምጃ ነው፡፡ ምክያቱም ቢሮው ኤጀንቱን ሠራተኛ እየበደልክ ነው፣ ሠራተኞችን በትክክል እያስተዳደርክ አይደለም ብሎ ነው ዕርምጃውን የወሰደው፡፡ ምንም እንኳን እነሱ (ቢሮው) በኋላ የሚመጣውን ክስተት ስላላዩት ቢሆንም፣ ዕርምጃው ትክክል ነው ብለን የወሰድነው፡፡ ችግሩን በጥልቀት ስንመለከተው ሊነሱ ከሚችሉት ጥያቄዎች ውስጥ ከድርጅቱ ደመወዝ ተቀብሎ ማን ያከፋፍል? ወይም የሠራተኞችን ደመወዝ ማን ይቀበልላቸው? የሚሉት ይገኙበታል፡፡ እንዲያው ችግሩ በመከሰቱ ደመወዛቸውን ማኅበሩ ተረክቦ ያከፋፍል የሚል ሐሳብ ተነስቶ ነበር፡፡ የሚመራቸው እስኪገኝ ድረስ ማኅበሩ ወስዶ እንዲያከፋፍል የሚል ሐሳብ ነበር፡፡ የሚመራቸው እስኪገኝ ድረስ ሥራ ሊያቆሙ ሆነ፡፡ ወዲያውም አቆሙ፡፡ በአንፃሩ ደግሞ ፋብሪካው ሥራውን ሊያቆም አይገባም፡፡ ማኅበር ስላላቸው ደመወዛቸውን ወስዶ ያከፋፍል የሚል አቋም ያዘ፡፡ ማኅበሩ በበኩሉ ከኤጀንቱ ጋር ይህን በተመለከተ ውል የሌለኝ በመሆኑ፣ ይህን ለማስተዳደር ሳይሆን የቆምኩት የሠራተኛውን መብት ለማስከበር ነው የሚል ምላሽ ነው የሰጠው፡፡

በዚህ ውዝግብ ውስጥ ሌላ ኤጀንት ደግሞ ሊገባ ይፈልጋል፡፡ ይኼ ደግሞ ሌላ የራሱን ችግር ይዞ ነው የሚመጣው፡፡ አዲሱ ኤጀንት እንዲገባ ቢደረግ ደግሞ ነባሩን ሠራተኛ በትኖ የራሱን አዲስ ሠራተኛ ይዞ ሊመጣ ነው፡፡ ይህ በእንዲህ እያለ ተጨማሪ ሐሳብ ቀርቦ ወደ በለጠ ውስብስብ ደረጃ ሄዶም ነበር፡፡ በተለይ በጥቃቅንና በአነስተኛ በኩል ለፋብሪካው ሠራተኛ ቢቀርብ ተብሎም ነበር፡፡ እኛ እንደ ሠራተኛ ኮንፌዴሬሽን አቋም ለመውሰድ አጣብቂኝ ውስጥ ገብተናል፡፡ ምክንያቱም የሠራተኛ ማኅበሩ ደመወዝ ያከፋፍል የሚለውን ሐሳብ ቢደገፍ ፋብሪካው ለጊዜውም ቢሆን ሥራ ሊያቆም ሆነ፡፡ የአዲስ ኤጀንሲ መምጣትም ሆነ የጥቃቅንና አነስተኛ የሚለውን ሐሳብ እንዳንቀበል ደግሞ በሠራተኛው ላይ የሥራ ዋስትና ማጣትን ያስከትላል፡፡ የሥራ ውሉ ዕውቅና ከተነፈገው ኤጀንት ዘንድ የነበረ በመሆኑ፣ ሠራተኞቹ ዳንጐቴን በሕግ መጠየቅ አይችሉም፡፡ ኤጀንቱም አሁን ዕውቅና ያጣ በመሆኑ እሱንም መክሰስ አይቻልም፡፡ ለዚህም ነው ኮንፌዴሬሽናችን የመጨረሻ ሐሳብ አድርጎ የተቀበለው ባለው ሁኔታም ቢሆን ለጊዜው ማኅበሩ ከፋብሪካው ደመወዝ በቀጥታ ተቀብሎ እንዲያከፋፍል፣ በሒደትም አቅሙን በማጠናከር ምን መሆን እንዳለበትም እየተወያየን መፍትሔ መፈለግ ይገባል የተባለው፡፡ እንዲሁም እዚያው በሥራው ቦታ እንደገና በኢንተርፕራይዝ መልክ እንዲደራጁ የሚል ሐሳብ አቅርበን ለጊዜው በፌዴሬሽኑ በኩል ክትትል እየተደረገበት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ሌላው በአገሪቱ ከሠራተኞች ጋር በተመለከተ በስፋት የሚነሳው ችግርና እናንተም ትኩረት እንደምትሰጡ የምትገልጹት የሠራተኛውን የሥራ ላይ ደኅንነት የተመለከተ ጉዳይ አንዱ ነው፡፡ አሁን ያለው ነባራዊ እውነታና የችግሩ ጥልቀት ምን ያህል ነው?

አቶ ካሣሁን፡- በትክክል ችግሩ አለ፡፡ ይህንን ሁኔታ በተመለከተም ጉዳዩ ሰፊና ጥቅጥቅ በመሆኑ በዝርዝር ለማውራት ቢያስቸግርም ብዙ የሚነሱ ጉዳዮች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡

ሪፖርተር፡- ጥቂት ማሳያዎችን ብቻ በማንሳት ሊታዩ የሚችሉና በቅርቡ እየተነሱ ያሉት፣ በአበባ እርሻዎች ውስጥ በኬሚካል በመመረዝ በርካታ ሴቶችና ወጣት ሠራተኞች ራሳቸውን በመሳት ለሆስፒታል የተዳረጉ አሉ፡፡ በተለያዩ ፋብሪካዎችም የአካል ጉዳት እየደረሰባቸው በግልጽ እየታየ ነው፡፡ እነዚህና መሰል ተመሳሳይ ችግሮች እንዴት ይገለጻሉ?

አቶ ካሣሁን፡- የሙያ ደኅንነትና ጤንነትን በተመለከተ ያለው ትልቁ ችግር እነዚህ የጠቃቀሳችሁዋቸው ዓይነት አደጋዎች እየተከሰቱ መሆኑ ነው፡፡ እንደሚታወቀው አሠሪው አካል በማምረቻም ሆነ ተመሳሳይ በሆነ ዘርፍ ሲገባ ከመጀመርያው ጀምሮ በሕግ የሚጣልበት ግዴታና ኃላፊነት አለ፡፡ አሠሪው ላይ አዋጁ የሚጥለው ግዴታ የሚጀምረው፣ አሠሪው ሠራተኛን ወደ ሥራ ከማስገባቱ በፊት ነው፡፡ መጀመርያ ማድረግ (ማሟላት) ያለበትን አስረድቶ ነው ሠራተኛን ወደ ሥራ የሚያሰማራው፡፡ መንግሥትም አሠሪው ለሠራተኛው አግባብ ያለው ሥልጠና እንዲሰጥ ግዴታ ይጥልበታል፣ ቁጥጥርም እንዲያደርግ ግዴታ ይጥልበታል፡፡ ነገር ግን እነዚህ ግዴታዎች እየተፈጸሙ ባለመሆናቸው የተባሉት ጉዳቶች በበርካታ ሠራተኞች ላይ እየደረሱ ነው፡፡ ጥንቃቄ ስለማይደረግና ሥልጠና ስለማይሰጥ መድረስ የማይገባቸው ጉዳቶች እየደረሱ ነው፡፡ በቅርቡ የደረሱ ጉዳቶችን ለአብነት ማንሳት ይቻላል፡፡ ለምሳሌ ሐምሌ 17 ቀን 2009 ዓ.ም. በሆለታ አካባቢ በሚገኝ የአበባ እርሻ ውስጥ 31 የሚሆኑ ሠራተኞች በተመሳሳይ ጊዜ ራሳቸውን ስተው ወደቁ፡፡ ልክ ሥራ እንደገቡ ነበር በኬሚካል ምክንያት ራሳቸውን የሳቱት፡፡

ሪፖርተር፡- ኬሚካሉ አደጋ እንዳያደርስባቸው መከላከያ ስላልነበራቸው ነው? ወይስ ሌላ ምክንያት ነበር ለዚህ የዳረጋቸው?

አቶ ካሣሁን፡- መከላከያ ያልነበራቸው መሆኑ አንዱ ምክንያት ነው፡፡ በተጨማሪም ኬሚካሉ በራሱ ገና ያልተመረመና ትክክለኛነቱ ያልተረጋገጠ ከመሆኑ ጋር ይያያዛል፡፡ በሰው ላይ ጉዳት እንደማያደርስ ተመርምሮ ነው ወይ? ኬሚካሉ በትክክለኛው መንገድ ወደ አገር ቤት የገባ ነው? ወይስ ሌላ ምክንያት ሊኖር ይችላል የሚሉ ጥያቄዎች አሉ፡፡ እንዲሁም በምርት ክፍሉ ውስጥም ጥንቃቄ ሊወሰድባቸው በሚያስፈልጉ ጉዳዮች ሁሉ ለሠራተኞች በአግባቡ መገለጽ ይገባል፡፡ ሰላሳ አንድ ሰዎች በአንድ ቀን መውደቃቸው አስደንጋጭ ነው፡፡ እንዲያውም አሁን ይህ ቁጥር አሻቅቧል፡፡ ለጊዜው ለእኔም ሆነ ለድርጅታችን በደብዳቤ ገና ያልተገለጸ ቢሆንም፣ በደረሰኝ መረጃ የተጎጂዎች ቁጥር ረቡዕ ነሐሴ 3 ቀን 2009 ዓ.ም. ድረስ ወደ 56 ደርሷል፡፡ ሁሉም በዚሁ ኬሚካል የተጎዱ ናቸው፡፡ እንግዲህ ከአንድ የአበባ እርሻ ይህን ያህል ጉዳት በጥቂት ቀናት ውስጥ ከደረሰ በሌላው ላይ ምን ሊደርስ እንደሚችል ማሰብ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ጉዳቱ ምን ያህል ነው? ከዚያ በኋላ የደረሰ ጉዳት አለ?

አቶ ካሣሁን፡- ለጊዜው ያለው መረጃ በአንድ ጊዜ ይወድቃሉ፡፡ ከዚያ ለተጨማሪ ሕክምናና ምርመራ ወደ ሆስፒታል እየተላኩ ነው የሚል ነው፡፡ ሌላው በቀጣይ የሚታይ ይሆናል፡፡ ችግሩ የአበባ እርሻው በሚገኝበት ብቻ የተወሰነ አይደለም፡፡ ለምሳሌ በዝዋይ ተመሳሳይ ችግር ያለበትን መጥቀስ ይቻላል፡፡ በዝዋይ ያለው የአበባ እርሻ ጭራሹን ሠራተኞች በኬሚካል የተጎዱ መሆናቸው እየታየ፣ በሐኪም ማስረጃም ተረጋግጦ፣ ሕክምና እየተከታተሉ መሆናቸው እየታወቀና ይህም በሐኪም ማስረጃ ጭምር ተረጋግጦ፣ ሠራተኞችም በአካል እዚህ አዲስ አበባ ኢሠማኮ ቢሮ ድረስ በአካል መጥተው አመልክተው፣ ነገር ግን ተጨማሪ የተሻለ ሕክምና እንዲያገኙ አልተፈቀደላቸውም፡፡ እንግዲህ ወደዚህ መጥተው ማመልከት የቻሉት እንኳ አሥር ናቸው፡፡ እነሱና ሌሎቹ ሠራተኞች በኬሚካሉ የተነሳ በደረሰባቸው የጤና ጉዳት ግማሾቹ ወደ ካንሰር ደረጃ ደርሶባቸው ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የጨረር ሕክምና የጀመሩ አሉ፡፡ ሁለት ሠራተኞች ኩላሊታቸው በመጎዳቱ ዲያሌሲስ ላይ ያሉ አሉ፡፡ አንዱ ኩላሊታቸው ብቻ የተጎዳባቸውም እንዲሁ ዲያሌሲስ ላይ ናቸው፡፡ ሌሎች ደግሞ ፊታቸውን በኬሚካል የተጎዱና ያበጠባቸውም ሕክምና ላይ ይገኛሉ፡፡ ይኸው ድርጅት ወይም የአበባ እርሻው ባለቤት በፊት እዚህ አዲስ አበባ ቤት ስለነበረው፣ እዚህ መጥተው የሚታከሙትን ሠራተኞች ያቆይበት ነበር፡፡ አሁን ግን እንደ ማቆያ የሚጠቀምበትን ቤት ትቶት ጉዳት የደረሰባቸውን ሠራተኞች በዝዋይ ክሊኒክ ስላቋቋምኩ እዚሁ ተከታተሉ እንጂ፣ ወደ አዲስ አበባ ሄዳችሁ አትታከሙም ብሏቸዋል፡፡ ‘ሪፈር’ ካልተጻፈላችሁ በስተቀር አዲስ አበባ ድረስ ልኬ አላሳክማችሁም ብሏቸዋል ተብሎ ነበር፡፡ ነገር ግን በቀጥታ ሪፈር የተጻፈላቸውንም አላሳክምም ብሏቸዋል፡፡ መቼም ዝዋይ የጨረር ሕክምና አይሰጥም፡፡ ለካንሰርም ሆነ ለዲያሌሲስ ሕክምና ሊሰጥበት አይችልም፡፡ በተጨማሪም ዝዋይ ያለው የክሊኒክ ዶክተር ቢሆንም ‘ሪፈር’ በመጻፍና ችግሩ ከራሱም ሆነ ከክሊኒኩ አቅም በላይ መሆኑን ቢገልጽም፣ የድርጅቱ ዳይሬክተር ግን ወደ አዲስ አበባ መሄድ የፈለገ ካለ በራሱ ወጪ መታከም እንደሚችል ነው የገለጸላቸው፡፡ ሌላው ቢቀር እንኳ ወደ አዲስ አበባ ሄደው ለመታከም ፈቃድም ሊሰጣቸው አልቻለም፡፡ ችግሩ እስከዚህ ድረስ ይገለጻል፡፡

ሪፖርተር፡- የሰው ሕይወት እየጠፋና የአካል ጉዳት በከፋ ሁኔታ እየደረሰ መሆኑ በግልጽ ከታወቀ ከችግሩ ግዝፈት አንፃር እናንተ ምን እየሠራችሁ ነው? ችግሩ እንዳይስፋፋ፣ እንዲሁም ጉዳት የደረሰባቸው እንዲረዱ ለማድረግ ምን ያህል ተጉዛችኋል? የሠራተኞች ጉዳትን በምን ያህል እንዲታወቅ ጥራችኋል? መንግሥት የችግሩን ጥልቀት በአግባቡ ያውቀዋል? እናንተስ አሳውቃችኋል?

አቶ ካሣሁን፡- ችግሩን ለማሳወቅ የአቅማችንን ያህል እየሠራን ነው፡፡ መንግሥትም ቢሆን ችግሩን በደንብ ያውቀዋል፡፡ እንደሚታወቀው በዚህ ዘርፍ መንግሥትን የሚወክለው የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በዋነኝነትና የየክልል ቢሮዎች ናቸው፡፡ የክልል ቢሮዎች የተወሰኑ ዕርምጃዎችን እየወሰዱ ነው ያሉት፡፡ ለምሳሌ በሆለታ አካባቢ ለደረሰው ጉዳት ኦሮሚያ እየተንቀሳቀሰ የተወሰኑትን የድርጅት ኃላፊዎች የማሰር ዕርምጃና በሌሎችም ክትትል እያደረገ ነው፡፡ በአንዳንዶቹ የውጭ ኩባንያዎች ላይ ክትትሉን ይጀምራል፡፡ ነገር ግን ከእዚህ ጋር በተያያዘ አንድ የሚጋጭ ጉዳይ ሲነሳ ይስተዋላል፡፡ ክልሎች የውጭ ኩባንያዎች ላይ ክትትል ወይም ምርመራ ለማድረግ ሲሞክሩ፣ ‹‹እኛ ከፌዴራል መንግሥት ፈቃድ ያወጣን በመሆኑ ክልል ምን ያገባዋል?›› የሚሉ ጥያቄዎችን ያነሳሉ፡፡ ፌዴራል መንግሥት ደግሞ ሲጠየቅ ‘ጉዳዩ በሒደት ነው የሚስተካከለው፣ ፖሊሲ እስካሁን አልነበረንም፣ አሁን ፖሊሲውን አውጠተን ለማስፈጸም የግንዛቤ ፈጠራ እየሠራን ነው’ የሚሉ የተለመደ ዓይነት መልሶች ከመስጠት ውጪ በተግባር ዕርምጃ እየተወሰደ አይደለም፡፡ ሰው እየሞተ ነው ብለህ ብትጠይቅ በተግባር የሚታይ ይህ ነው የሚባል መልስ አይሰጥም፡፡

ሪፖርተር፡- ነገር ግን እስካሁን ያነሷቸውን ምሳሌዎች ጨምሮ በርካታ ጉዳቶች በጤና ላይ ከመድረስ ባለፈ ዜጎች እየሞቱ መሆኑን በዝርዝር አሳውቃችሁ፣ መንግሥት በአግባቡ ተገንዝቦታል ነው የሚሉት?

አቶ ካሣሁን፡- አዎ በትክክል ያውቁታል፡፡ በሆለታም ሆነ በሌሎች ቦታዎች ያለውን እውነታ በደንብ ያውቁታል፡፡ የዝዋዩን በተመለከተ በእኛም በኩል ቢሆን ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ነው በደንብ የተረዳነው፡፡ ችግሩ ግን ሰፊ በመሆኑ በበርካታ ቦታዎች ተመሳሳይ ጉዳቶች እንዳሉም ይታወቃል፡፡ አንድ ሌላ ሞጆ አካባቢ ያለ ቆዳ ፋብሪካን ማንሳትም ይቻላል፡፡ ፍሬንድሺፕ ቆዳ ፋብሪካ ይባላል፡፡ ለምን እንደሆነ አላውቅም ይህ ፋብሪካ ያለ ሰው ደም የሚንቀሳቀስ አይመስለኝም፡፡ ፋብሪካው ማሠራት የማይችል ከሆነ ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ መሥራት የሚችልበት ደረጃ እስከሚደርስ ድረስ የማገድ ሥልጣን አለው፡፡ ወይ አልተዘጋ፣ ወይ አልተስተካከለ ጉዳት ማድረሱን እንደቀጠለ ቢሆንም ይሠራል፡፡ የዚህ ፋብሪካ አንድ ሠራተኛ ጉዳት ደረሰበት ብለን ደብዳቤ ጽፈን ሳንጨርስ፣ ሌላው ሠራተኛ ላይ ደግሞ ጉዳት ደረሰ የሚል ሪፖርት ይደርሰናል፡፡ ለምሳሌ ዛሬ ወጪ ያደረግኩት ደብዳቤ ከዚሁ ፋብሪካ ጋር በተያያዘ ለኦሮሚያ ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ የጻፍኩት ነው፡፡ በአንድ ፋብሪካ ውስጥ እየደረሰ ያለን ጉዳት ነው እንግዲህ በተደጋጋሚ ደብዳቤዎች እየጻፍን ያለነው፡፡ የሚገርመው ነገር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሰኞ አንድ ሰው ጉዳት ደረሰበት ተብሎ ይነገረናል፡፡ በቀጣዩ ማክሰኞ ደግሞ ሁለት ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱ ይገለጽልናል፡፡ እንዲህ ዓይነት የጉዳት ሪፖርቶችን እያደረገልን ያለው የፋብሪካው ሠራተኞች ማኅበር ሊቀመንበር ነው፡፡ ባለፈው ሳምንት ወደ ጅማ ሄጄ ነበርና እዚያ ሆኜ ይኸው የማኅበሩ ሊቀመንበር ደውሎ የነገረኝ ደግሞ፣ ሌላ ሠራተኛ ስለመጐዳቱ ሳይሆን የራሱ የማኅበሩ ሊቀመንበር እጅ መሰበሩን ነው ሪፖርት ያደረገው፡፡ እንግዲህ በዚህ ፋብሪካ ብቻ የሚታየው የሚገርም ክስተት ነው፡፡ ድሮ የሚደርሰን መረጃ ብዙ የሚባል አልነበረም፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን በርካታ ሪፖርትና መረጃዎች መምጣታቸውን በማየት ጉዳት እየጨመረ መሆኑን ነው የተገነዘብነው፡፡ ከፋብሪካዎች ጋር በተያያዘ የሚቀርብ ጉዳት ጨምራል፡፡ በተለይ ሞጆ አካባቢ ካሉ ፋብሪካዎች በብዛት ችግሮች ይከሰቱባቸዋል፡፡ ይህ ደግሞ ፍሬንድሺፕ ከተባለው ፋብሪካ ሌላ ማለት ነው፡፡ ነገር ግን ፍሬንድሺፕ ብዙ ጉዳቶች የሚደርሱበት ፋብሪካ ሲሆን፣ ተጎጂዎችም ብዙ ካሣ የማያገኙበት ፋብሪካ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ይህንን በተመለከተ ሠራተኛው ለሚደርስበት የአካል ጉዳትም ሆነ ሌላ የጤና ችግር የካሣ ጥያቄው በምን ዓይነት መንገድ ነው የሚስተናገደው?

አቶ ካሣሁን፡- ጉዳትን በተመለከተ የሕክምና ቦርድ ነው የሚወስነው፡፡ ቦርዱ የጉዳቱን መጠን በመቶኛ አስልቶ ከደመወዝ ጋር በመቀመር ጉዳቱ ሙሉ የአካል፣ ወይም ከፊል ጉዳት በማለት ለይቶ በሚያቀርበው መሠረት ማስፈጸም ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ይህ አሠራር ግን ፍትሐዊነቱ ምን ያህል ነው? ለምሳሌ ቀደም ሲል ከተገለጸው ድርጅት ጋር በተያያዘ ተከፈለ የተተበለውን የካሣ አከፋፈል ብንመለከት፣ አንዲት ሁለት እጆቿን ላጣች ሴት የሁለት ሺሕ ብር ካሣ ያስፈልጋታል ብሎ የሚወሰን ከሆነ ፍትሐዊ ነው? ምን ዓይነት ቦርድ ነው ይህን የሚወስነው? ከፋዩስ ማን ነው?

አቶ ካሣሁን፡- ተጎጂዎች ካሣውን የሚያገኙት ከድርጅቱ ነው፡፡ ነገር ግን ምን ያህል ደመወዝ እንደሚከፍል የማይገልጽ ድርጅት ላይ ደመወዝን አስልቶ እንዴት መከራከር ይቻላል? ለማስላት መሞከር በራሱ ትልቅ ችግር ነው የሆነብን፡፡ ለዚህም ነው የመደራጀት ጉዳይ፣ የሙያና ጤንነት ጉዳይ ትልቅ ጉዳይ የሆነው፡፡ ይህ ደግሞ ለኢሠማኮ ብቻ ሳይሆን ለአገሪቱም ትልቅ ችግር ነው፡፡ ሲጀመር እነዚህ የተጠቀሱትን የአካል ጉዳቶችና ከኬሚካል ጋር ተያይዘው የተፈጠሩ ጉዳቶች ወዲያው የሚታዩ በመሆኑ አየን እንጂ፣ ኬሚካሎች በረዥም ጊዜ ሊያደርሱ የሚችሉት ጉዳት እኮ በደንብ የታየ አይደለም፡፡ ስለዚህ በአገር አቀፍ ደረጃ አስፍተን ካየነው ደግሞ ችግሮቹ በጣም በርካታ ናቸው፡፡ ስለዚህ ይህንን ችግር መከላከልና መቀነስ እንዲቻል በጋራ መሥራት ካልተቻለ፣ መንግሥትም ማስፈጸም ካልቻለ፣ ጉዳት እየደረሰባቸው ያሉትን ዜጎች መሸከም የሚያስችል የኢኮኖሚ አቅም አይኖርም፡፡ በአጠቃላይ መደራጀትን ጨምሮ የጤንነትና የሥራ ላይ ደኅንነት ችግርን ማስተካከል ካልተቻለ ተጎጂ ዜጎች ወደ ልመና ነው የሚገቡት፡፡ ሁለት እጅ ያጣ ሰው ምን ሊሠራ ይችላል? በተለይ የጉዳቱ ሰለባዎች በአብዛኛው ወጣት ሴቶች ናቸው፡፡ ገና ትዳር ያልመሠረቱና ያልወለዱ፡፡ ገና ብዙ ቦታ ይደርሳሉ ተብለው የሚጠበቁና የየራሳቸው ህልም ያላቸው ናቸው፡፡ ከመንገድ ሲቀሩ የሚደርስባቸው አንዱ የሞራል ስብራት ነው፡፡ ሁለተኛ በአካል ሠርተው አለመብላታቸው የሚያደርስባቸው የሥነ ልቦና ጫና ነው፡፡ ለዚያም ነው ቤተሰቦቻቸው እነሱን ማስተዳደር ስለማይችሉ ወደ ልመናና ወደ ከፋ ሕይወት የሚዳረጉት፡፡