Skip to main content
x
‹‹ሚኒስትርም ቢሆን በሙስና ውስጥ እጁ ካለበት ማንም ሰው አይታለፍም››

‹‹ሚኒስትርም ቢሆን በሙስና ውስጥ እጁ ካለበት ማንም ሰው አይታለፍም››

ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር)፣ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ

ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር) የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር ናቸው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በጥቅምት 2009 ዓ.ም. አዲሱን ካቢኔያቸውን ሲያዋቅሩ ወደ ሥልጣን ከመጡ አመራሮች አንዱ ሲሆኑ፣ የቀድሞውን ኃላፊ አቶ ጌታቸው ረዳን በመተካት ጽሕፈት ቤቱን እየመሩ ይገኛሉ፡፡ ለጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ ሆነው ከመመደባቸው በፊት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙዩኒኬሽን ትምህርት ክፍል ዲን ነበሩ፡፡ ነአምን አሸናፊ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- በቅርቡ 37 የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ ነጋዴዎችና ደላሎች በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን መንግሥት አስታውቋል፡፡ ነገር ግን ከዚህ ጋር በተያያዘ የሚሰጡ አስተያየቶች አሉ፡፡ ይህም መንግሥት ግለሰቦቹን በቁጥጥር ሥር ያዋለው ሙስናን የምር ለመታገልና ለመግታት ሳይሆን የትኩረት አቅጣጫ ለማስቀየር ነው ይባላል፡፡ ለእነዚህ አስተያየቶች የእርስዎ ምላሽ ምንድነው?

ዶ/ር ነገሪ፡- ይህ የተሳሳተ ግምት ነው፡፡ እውነት ነው በተለይ በማኅበራዊ ሚዲያም እንደዚህ የሚሉ አሉ፡፡ እኛም እንዲህ ያሉትን አስተያየቶች ዓይተናል፡፡ ይህ ከምን የመነጨ ነው? ሁልጊዜ መንግሥት የሚያደርጋቸውንና የሚወስዳቸውን ዕርምጃዎች፣ ሕዝቡ በጥርጣሬ እንዲመለከት ሥራዬ ብለው የተያያዙ ቡድኖች እንዳሉ ነው የሚያሳየው፡፡ በተለይ በሚያገኙት የመረጃ አውታር በማኅበራዊ ሚዲያም ሆነ ከውጭ በሚሠራጩ የሳተላይት ሬዲዮና ቴሌቪዥን ፕሮግራሞች ሁልጊዜ በዚች አገር ውስጥ የተረጋጋ የፖለቲካ ሥርዓት እንዳይኖር፣ ሕዝቡም የተረጋጋ ሕይወት እንዳይመራና ቢቻል ደግሞ ብጥብጥ እንዲፈጠር፣ በሕዝብና በመንግሥት መካከል ጥርጣሬ እንዲኖር ለማድረግ የተያያዙት የሥነ ልቦና ጦርነት ነው፡፡ ነገር ግን መንግሥት ይህን ዕርምጃ እየወሰደ ያለው ለዚህ ዓላማ አይደለም፡፡ ምክንያቱም መንግሥት አንድም ሰው ቢሆን ከዚህ ወንጀል ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ሥር በሚያልበት ጊዜ አጥንቶና ጊዜ ወስዶ ነው፡፡ 

አንደኛ በፌዴራል ደረጃ ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ያከናወናቸው ሥራዎች አሉ፡፡ ይህ ደግሞ ከዓመት ያላነሰ ጊዜ የወሰደ ነው፡፡ ከግብር ጋር የተያያዘው ነገር የቅርብና የሳምንት ጉዳይ ነው፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ይህ እንዴት ሰውን ያሳምናል? የሙስና ወንጀል በጣም ውስብስብ የሆነ ወንጀል ነው፡፡ በቁጥጥር ሥር የዋሉት ሰዎች መንግሥት አምኗቸው እኔን ወክለው ሕዝቡን ይመራሉ፣ ለፕሮጀክቶች የተመደቡ በጀቶችን በተገቢው መንገድ ያስተዳድራሉ ብሎ ኃላፊነት የሰጣቸው፣ አንዳንዶቹ ደግሞ ለበርካታ ዓመታት በሥልጣን ላይ የቆዩና በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ሲያንቀሳቅሱ የነበሩ ናቸው፡፡ ታዲያ እንዴት እንዲሁ ለታይታና ያለውን ሁኔታ አቅጣጫ ለማስቀየር ብሎ መንግሥት እንዲህ ያለ ዕርምጃ ይወስዳል? ይህ ማንንም አያሳምንም፡፡ መነሻው ይታወቃል፡፡ ቀደም ሲል እንደገለጽኩት ነው፡፡ መንግሥት የሚወስዳቸውን ዕርምጃዎች ሁሉ ተከታትለው ራሳቸው የሚፈልጉትን ትርጉም እየሰጡ፣ ያንን ትርጉም ደግሞ ሕዝቡ እንዲገዛላቸው በማድረግ ፊት ለፊት በፖለቲካ መድረክ ላይ ወጥተው በሰላማዊ መንገድ ተከራክረው መንግሥትን ወይም ገዥውን ፓርቲ ማሸነፍ ያልቻሉ አካላት፣ ያገኙትን ዕድል በመጠቀም ይህ አገር እንዲተራመስ የሚያደርጉት ጥረት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ነገር ግን እንዲህ ያለ አስተያየት የሚሰጡ ግለሰቦች ለመከራከሪያነት የሚያነሱት ነጥብ፣ እስካሁን ድረስ መንግሥት በሙስና የተጠረጠሩ የመንግሥት ኃላፊዎችን በቁጥጥር ሥር ሲያውል ብዙውን ጊዜ የሚያዙት ግለሰቦች መካከለኛ ደረጃ የሥልጣን እርከን ላይ ያሉት ናቸው፡፡ መረቡ ትልልቅ ዓሳዎችን አይዝም ይባላል፡፡ ስለዚህ የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናትና ሚኒስትሮች ሙስና አልፈጸሙም ማለት ነው? ወይስ እነሱን መያዝ አይቻልም ነው? አይነኬዎች ናቸው ነው? በዚህ ላይስ ምን ይላሉ?

ዶ/ር ነገሪ፡- ይህም በልኩ ነው መታየት ያለበት፡፡ እስካሁን የታሰረ ሚኒስትር የለም ብለው የሚከራከሩ ከሆነ ሐሰት ነው፡፡ በኢሕአዴግ የአመራር ዘመን በከፍተኛ የሥልጣን ደረጃ ላይ ያሉ ግለሰቦች አልታሠሩም ብለው የሚያስቡ ሰዎች ካሉ፣ ቅድም የጠቀስኩትን ነው የሚያመላክተው፡፡ መንግሥት የሚወስዳቸው ዕርምጃዎች እንዲሁ በጥርጣሬ እንዲታዩ ከማድረግ የተነሳ ነው፡፡ ሌላው መታወቅ ያለበት ደግሞ በመካከለኛ ደረጃ ያሉ ባለሥልጣናት የሚባሉት ከሚኒስትሮች ጋር በሚወዳደሩበት ጊዜ፣ ለመንግሥትና ለሕዝብ ሀብት በጣም ቅርበት ያላቸው እንደሆኑ መታወቅ አለበት፡፡ እንዲያውም አንዳንዶቹ ከሚኒስትር በበለጠ በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ የሚያንቀሳቅሱ ናቸው፡፡ እነሱ እነማን ናቸው የሚለውን ሕዝቡ በግልጽ ማወቅ አለበት፡፡ ስለዚህ በቅርበት ገንዘብ እንዲያንቀሳቅሱ፣ እንዲቆጣጠሩና እንዲከታተሉ ኃላፊነት የተሰጣቸው ሰዎች ትልልቅ ባለሥልጣናትና ከፍተኛ ኃላፊዎች እንደሆኑ ሕዝቡ ማወቅ አለበት፡፡ ሚኒስትርም ቢሆን በሙስና ውስጥ እጁ ካለበት ማንም ሰው አይታለፍም፡፡ መታወቅ ያለበት ይህ ነው፡፡ በክልል ደረጃም ሆነ በፌዴራል ደረጃ፣ ሚኒስትርም ይሁን አይሁን ከሕግ በላይ የሚሆንበት ምክንያት የለም፡፡ የሕግ አግባብን በመከተል ዕርምጃ ይወሰዳል፡፡

ሪፖርተር፡- አገሪቱ አሁን የምትገኘው በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ ነው፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ደግሞ ከሳምንት በኋላ ይጠናቀቃል፡፡ ከዚህ አንፃር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ይቀጥላል ወይስ ይነሳል? በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በተከናወኑ ሥራዎች አገሪቱ ምን አተረፈች?

ዶ/ር ነገሪ፡- እንደሚታወቀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲታወጅ ኢትዮጵያ የነበረችበትን ሁኔታ መለስ ብሎ ማስታወስ ይገባል፡፡ በሰላማዊ መንገድ ጥያቄያቸውን ለመንግሥት ለማቅረብ የተነሳሱ ዜጎች ነበሩ፡፡ በተለይ በኦሮሚያ፣ በአማራና በደቡብ ክልሎች አንዳንድ አካባቢዎች የተነሱ ጥያቄዎች ነበሩ፡፡ መጀመርያ እነዚህ ጥያቄዎች በሚነሱበት ጊዜ ትልቅ ሥጋት ተደርጎ አልታየም ነበር፡፡ ነገር ግን ከተወሰኑ ሒደቶች በኋላ አቅጣጫውን የቀየረበትና በአጠቃላይ ለአገር ሥጋት የፈጠረበት አጋጣሚ ነበረ፡፡ በዚህ ውስጥ ሌሎች ተዋንያን እንዳሉ ይታወቃል፡፡ በአንድ በኩል መንግሥት ይህንን ችግር በሚያይበት ጊዜ ራሱ ከሁለት ዓመት ቀደም ብሎ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ስላሉ፣ ገዥው ፓርቲ ውስጡን ማጥራት እንዳለበትና ከዚያም ባሻገር ከፌዴራል እስከ ክልሎች ድረስ ራሳቸውን ማጥራት እንደነበረባቸው ታምኗል፡፡ ሕዝባችን ብዙ ሮሮ አለበት በማለት መንግሥት ራሱ ግንባር ቀደም ሆኖ ችግር ስላለብን መፍታት አለብን ብሎ፣ ከችግሩ በፊት ነበር አቋም የተወሰደው፡፡ እንዲያውም መቐለ ላይ በተደረገው የኢሕአዴግ ስብሰባ ተገልጾ ነበር፡፡ ያኔ ይህ ሁከት አልነበረም፡፡ ስለዚህ ቀደም ብሎ ችግሩን የለየው መንግሥት ነበር፡፡ ከሕዝብ ጋር ሆኖ ዕርምጃ ለመውሰድ እንቅስቃሴ በጀመረበት ወቅት በአንዳንድ አካባቢዎች ለየት ያሉ ጥያቄዎች ተነሱ፡፡ በመጨረሻ ደግሞ የኢሬቻ በዓል ላይ የደረሰው አሰቃቂ አደጋ ደረሰ፡፡

መንግሥት ይህን መቆጣጠር ነበረበት፡፡ ምክንያቱም በዚህ ተጎጂ የነበረው እያንዳንዱ የአገሪቱ ሕዝብና ቤተሰብ ነው፡፡ ተማሪዎች በአግባቡ ትምህርት ቤት የማይሄዱበት ሁኔታ ተፈጠረ፡፡ የንግድ ሥራዎችን ለማከናወን አልተቻለም፡፡ ከቦታ ወደ ቦታ መንቀሳቀስ አልተቻለም፡፡ ትክክለኛ ዓላማ ያላቸው ዜጎቻችን ጥያቄውን አነሱ፡፡ ነገር ግን የራሳቸው የጥፋት ዓላማ ያላቸው ደግሞ ጥያቄውን ከእነሱ በመንጠቅ ለራሳቸው ዓላማ ሲጠቀሙበት ነበር፡፡ ስለዚህ ያ መቅረት ነበረበት፡፡ ያንን በመግታት የሕዝባችንን ትኩረት ወደ ልማት እንዲሆን ነው የተደረገው፡፡ ውጤቱን በምናይበት ጊዜም ከዚህ አኳያ ነው የምንመዝነው፡፡

በዚህ መሠረት ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አገኘን የምንለው ጥቅም ሕዝባችን በሥነ ልቦና ደረጃ ተረጋግቶ የዕለት ተዕለት ሥራውን ማከናወን መቻሉ ትልቅ ነገር ነው፡፡ ተማሪዎቻችን ትምህርታቸው ላይ ትኩረት አድርገው መማራቸው፣ በንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩ ግለሰቦችም በንግድ ሥራቸው ላይ ትኩረት አድርገው የአገር የኢኮኖሚ እንዲቀጥል መደረጉ ትልቅ ስኬት ነው፡፡ ይነሳል ወይስ ይቀጥላል የሚለውን በተመለከተ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ኮማንድ ፖስት የዘጠኝ ወራት ሪፖርቱን ይፋ አድርጓል፡፡ በሪፖርቱ መሠረት በአገሪቱ ያለው ሁኔታ በጣም በጥሩ ደረጃ ላይ ነው ያለው፡፡ የኮማንድ ፖስቱ ሴክሬታሪያት ኃላፊ በገለጹት መሠረት በአብዛኛው ወደ ፌዴራል ተዛውሮ የነበረው የሕግ አግባብ መያዝ እንደሚቻል ስለታመነበት፣ ኃላፊነቱ ወደ ክልል የፀጥታ ኃላፊዎችና አስተዳደሮች እየተመለሰ እንደሆነ ታይቷል፡፡ ስለዚህ ይህ የሚያመለክተው ሒደቱ በዚህ የሚቀጥል ከሆነ የሚመለከተው አካል ሪፖርቱን ያቀርብና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመጨረሻውን ውሳኔ ይሰጣል፡፡

ሪፖርተር፡- የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ግን ዓመታዊ እረፍት ላይ ነው፡፡ ስለዚህ አስቸኳይ ስብሰባ ይጠራል? ወይስ መስከረም ይጠበቃል?

ዶ/ር ነገሪ፡- ካስፈለገ አስቸኳይ ስብሰባ ይኖራል፡፡ ምንም ችግር የለውም፡፡ ሥራ ሲኖር እረፍት ተብሎ አይተውም፡፡ አስቸኳይ ስብሰባ ተጠርቶ በዚህ ላይ ውሳኔ እንዲሰጥ ይደረጋል፡፡ ስለዚህ ብንጠብቅ ይሻላል፡፡

ሪፖርተር፡- ሌላው በቅርቡ ከግብር አወሳሰን ጋር በተያያዘ ውጥረት ነበር፡፡ በተለይ የደረጃ ‹‹ሐ›› ግብር ከፋዮች ከፍተኛ የሆነ የግብር ጫና ተደርጎብናል የሚል ቅሬታ እያሰሙ ነው፡፡ ከመጀመሪያው የግብር ትመናው በግልጽ ያልተከናወነው ለምንድነው? የነጋዴውን ቅሬታ ለመፍታት መንግሥት ምን እየሠራ ነው?

ዶ/ር ነገሪ፡- የገቢ ተመንን በተመለከተ በአጠቃላይ ከመጀመሪያው ግልጽ አይደለም ብለን መደምደም አስቸጋሪ ነው፡፡ ምክንያቱም የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላትና ተቋማት ጊዜ ወስደውና ጥናት አድርገው ነው የሠሩት፡፡ የአዲስ አበባ አስተዳደርንም የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥትንም ችግሮች ለይቶ ነው የተሠራው፡፡ ለምሳሌ የኦሮሚያን የወሰድን እንደሆነ ነጋዴዎች ሲከፍሉ የነበረው ከዘጠኝ ዓመት በፊት በተደረገ የግብር ተመን ነበር፡፡ የአዲስ አበባ ደግሞ ከስድስት ዓመት በተደረገ ተመን ነበር፡፡ ለማንም ግልጽ እንደሚሆነው በእነዚህ ዓመታት ውስጥ አገሪቱ ትልቅ ለውጥ አስመዝግባለች፡፡ ስለዚህ ከመጀመሪያው ግልጽ ነው፡፡ ለውጥ ያስፈልጋል፡፡ አገራዊ ዕድገቱ በየደረጃው ባሉ ተቋማዊና ግለሰባዊ ዕድገት ከሌለ ከየት ነው የመጣው? አመክንዮው የሚነሳው ከዚህ ነው፡፡ ነገር ግን ሰዎች ኃላፊነት ተሰጥቷቸው ወደ ሥራ በሚገባበት ጊዜ፣ አንዳንድ ይህን ሥራ የወሰዱ አካላት በስንፍናም ይሁን በአመለካከት ችግር ትክክለኛ ሥራ እንዳላከናውኑ ይታያል፡፡

ግልጽነት የተባለው እኔ እንደሚገባኝ የሚመለከታቸው አካላት ቀደም ብለው የነጋዴውን ማኅበረሰብ ማወያየት አስፈላጊ ነበር፡፡ ውይይት የተደረገባቸው አካባቢዎች ይኖራሉ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ በዚያ ላይ ግን ቀደም ብሎ ግልጽነት ተፈጥሯል አንልም፡፡ ግልጽነት ቢፈጠርና አሁን የተፈለገው ይህ ነው፣ ምክንያቱ ይህ ነው፣ አካሄዱ ደግሞ ይህን ይመስላል ተብሎ ቢሠራ የተሻለ ይሆን ነበር፡፡ ከዚህ አንፃር ሒደቱ ከመጀመርያው እንዳለ ችግር አለበት ብለን መደምደም አስቸጋሪ ቢሆንም፣ ነገር ግን በመሀል ደግሞ ይህ ሥራ በሚከናወንበት ጊዜ የተንፀባረቀ ችግር አለ፡፡ ያንን ለመፍታት ግን መንግሥት ምን አደረገ የሚለው ትልቅ ትርጉም ሊሰጠው ይገባል፡፡ በዚህም መሠረት ቅሬታ ካቀረቡ በሺዎች የሚቆጠሩ ነጋዴዎች መካከል ቅሬታቸው ትክክል እንደሆነ መንግሥት አውቆ ምላሽ እየሰጠ ነው፡፡ ይህ ማለት ግመታው ትክክል እንዳልሆነ የሚያሳይ ነው፡፡ ይህ ምንድነው የሚያሳየው? ግመታው ውስጥ የተሰማሩ ኃላፊዎች ወይ ከአመለካከት ወይ ደግሞ ከመረጃ እጥረት ትክክለኛ ግንኙነት በነጋዴውና በእነሱ መካከል ስላልነበር፣ ትክክለኛ ያልሆነ ግመታ ይዘው መጥተዋል፡፡ መንግሥት የፈለገው ግን ይህን አይደለም፡፡ መንግሥት የፈለገው ምንድነው? አገራችንን ማልማት አለብን ነው፡፡ ፍላጎታችን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋ ነው፡፡ ሕዝቡን በትክክል ለማገልገል መንግሥት ከየትም አያገኘውም፡፡ በዕርዳታ ላይ ተደግፈን ለዘለዓለም መኖር አንችልም፡፡ በታክስ በኩል መስተካከል አለበት የሚል ዓላማ ነው የመጣው፡፡ ለዚህ ሁሉ ችግር የዳረገን ደግሞ ዘመናዊ ሥርዓት መጠቀም አለመቻላችን እንደሆነ መታወቅ አለበት፡፡

ሪፖርተር፡- የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶችን መጀመርያ ለመገንባት ሲታቀድ ከነበረው ውል በተለየ ባለ አንድ መኝታ ቤት ለማግኘት የተመዘገቡ ወደሚቀጥለው ዙር ተላልፈዋል፡፡ እንዲሁም በውሉ ላይ ያልነበረ ባለአራት መኝታ ቤት ተሠርቷል፡፡ ከዚህ አንፃር እንዲህ ያሉ ክፍተቶች ለምን ተፈጠሩ? ሕዝቡስ ከዚህ በኋላ መንግሥትን ሊያምን ይችላል ወይ? ለዚህ ችግርስ ኃላፊነት የሚወስድና የማጠየቀው ማን ነው?

ዶ/ር ነገሪ፡- መንግሥት የምንለው ማን ነው? የሚለውን ጥያቄ በመጀመርያ ደረጃ መመልከት አለብን፡፡ በጣም የሚያሳዝነው አንዳንድ ጊዜ እምነት የተጣለባቸው ሰዎች ታማኝ ሳይሆኑ ሲቀሩ፣ በአጠቃላይ የመንግሥት ስም ነው የሚጠፋው፡፡ በዚህ ሒደት ውስጥ እንግዲህ የሚጣራው እንዳለ ሆኖ ባለሦስት መኝታ ክፍል ይገነባል ተብሎ አራት መኝታ ቤት መገንባት፣ ባለአንድ መኝታ ክፍል ይገነባል ተብሎ ሕዝብ ተመዝግቦ ገንዘብ እንዲያጠራቅም ተደርጎ ግንባታው ከተጠናቀቀ በኋላ እንዲህ መሆኑን መንግሥትም የሚቀበለው አይደለም፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ተጠያቂ መሆን ያለባቸው ተጠያቂ ይሆናሉ፡፡ መታወቅ ያለበት ግን ይህን ነገር መንግሥት ፈልጎት አይደለም የተደረገው፡፡ በጣም የሚገርመው ይህ መረጃ እስከ መጨረሻው ድረስ ግልጽ ያለመሆኑ ነው፡፡ በተለይ ለአንዳንድ ኃላፊዎች ፕሮጀክቱ መሀል እስከሚደርስ ድረስ ግልጽ አልነበረም ነው የሚባለው፡፡ እንደዚህ መሆኑ ክትትሉ ላይም ክፍተት እንዳለ ያሳያል፡፡ ይህ መሆን አልነበረበትም፡፡ ለወደፊት ግን ትልቅ ትምህርት ይሆናል፡፡ በመንግሥትና በሕዝብ በኩል እንዴት መተማመን ይኖራል ለሚለው፣ አንደኛ መንግሥት ፈልጎት እንዳልሆነ መታወቅ አለበት፡፡ ኃላፊነት የተሰጣቸው ሰዎች ኃላፊነታቸውን ሳይወጡ ቀርተዋል፡፡ እነርሱ ደግሞ ተጠያቂ የሚሆኑበት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡ በዚህ ውስጥ ጥቅማቸው የተጓደለና የተጎዱ ዜጎቻችን ደግሞ የሚካሱበት ሁኔታ መኖር አለበት፡፡ ግዴታ ነው፡፡ ሕግ አለ፡፡ ያጠፉ በሕግ አግባብ ተጠያቂ መሆን አለባቸው፡፡ መካስ ያለባቸውም መካስ አለባቸው፡፡ መንግሥት ይህንን በቁርጠኝነት ይሠራል፡፡

ሪፖርተር፡- ከዚህ የመንግሥትና የሕዝብ እምነት ጉዳይ ጋር በተያያዘ የሚነሳው ደግሞ የቤቶቹ ዋጋ መጀመርያ ከተተመነበት አንፃር በከፍተኛ መጠን መጨመሩ ነው፡፡ በግለሰቦችና በድርጅቶች መካከል ስምምነት ሲኖር ወደ ፍርድ ቤት አምርተው መፍትሔ ያገኛሉ፡፡ ነገር ግን አሁን ውሉ በመንግሥትና በሕዝብ መካከል ከመሆኑ አንፃር፣ የመንግሥትንና የሕዝብን መተማመን አያወሳስበውም?

ዶ/ር ነገሪ፡- የዚህ ዝርዝር እኔ ዘንድ የለም፡፡ ለምንድነው ዋጋው የተጨመረው የሚለው ዝርዝሩ የሚመለከታቸውና በዚህ ጉዳይ ላይ የሚሠሩ አካላት አሉ፡፡ ነገር ግን እኔ እንደምረዳው አሁን ተጨማሪ ገንዘብ የተጠየቀው ያለምክንያት አይደለም፡፡ ጥያቄ የሚያመጣው ጊዜ ነው ወይ? ከመጀመርያው ግምቱ ትክክል አልነበረም፡፡ ምክንያቱም ጥራት ከተፈለገ ጥራት ያለው ሥራ ነው መከናወን ያለበት፡፡ አንዳንዶቹ ግብዓቶች ከውጭ የሚገቡ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ የውጭ ምንዛሪ የሚጠይቁ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ የውጭ ምንዛሪ በምንመለከትበት ጊዜ ባለበት ቦታ አይደለም የቆየው፡፡ ሥራው ደግሞ በሒደት ነው እየተከናወነ የመጣው፡፡ ስለዚህ ይህንን በቅርበት የሚሠራው የመንግሥት ተቋም መሬት ላይ ያለው እውነታ ያስገደደው ይመስለኛል፡፡ የሚፈለገውን ጥራት ለማምጣት የሚወጣው ወጪ በሚታይበት ጊዜ መንግሥትን ኪሳራ ውስጥ የሚከት ከሆነ እንደገና የሚታይበት ሁኔታ ሊኖር ይችላል፡፡ እኔ ከዚያ የመጣ ነው ብዬ ነው የምገምተው፡፡

ሪፖርተር፡- ሆኖም ፕሮጀክቱ ሲታቀድ በ18 ወራት እንደሚጠናቀቅ ቢገለጽም አራት ዓመታት ፈጅቷል፡፡ ፕሮጀክቱ የዘገየው በመንግሥት የአፈጻጻም ችግር እንጂ በተመዝጋቢዎች ምክንያት አይደለም፡፡ ስለሆነም ተመዝጋቢዎቹ ችግሩን እንዲጋሩ ማድረግ ለምን አስፈለገ?

ዶ/ር ነገሪ፡- ጊዜውን በተመለከተም ቢሆን መንግሥት በማጓተት የሚያተርፈው ነገር አለ ብዬ አልገምትም፡፡ ሆን ብሎ ተጓቷል ብዬ አላምንም፣ ምክንያቶች አሉ፡፡ አንዳንድ ጊዜ ፍላጎትና አቅም የማይመጣጠኑበት ጊዜ አለ፡፡ ሲታቀድ ችግሩን መሠረት አድርጎ ነው የታቀደው፡፡ ምክንያቱም ቤት ፈላጊዎች ብዙ ናቸውና፡፡ ስለዚህ ችግሮች ያለምክንያት የመጡ ናቸው አንልም፡፡ በአዲስ አበባ አስተዳደር በኩልም ግልጽ መሆን አለበት፡፡ መንግሥት ለምን ተሳሳተ? ወይ ደግሞ ለምን ዋጋ ጨመረ? ለምን በተያዘው ጊዜ ውስጥ አልጨረሰም? ሳይሆን ትልቁ ጥያቄ ምክንያቶቹ ለሕዝብ ግልጽ መሆን አለባቸው፡፡ የሚያሳምኑ መሆን አለባቸው የሚለው ነው፡፡