Skip to main content
x
‹‹በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ›› የኢትዮጵያ ቡና ክለብ ጅምሮች

‹‹በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ›› የኢትዮጵያ ቡና ክለብ ጅምሮች

  • 350 ሚሊዮን ብር በጀት የተያዘለት ስታዲየም የመጀመሪያው ምዕራፍ ግንባታ በ2010 ይጀመራል

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ክለቦች ከጊዜ ወደ ጊዜ ስፖርታዊ እንቅስቃሴያቸው እየተዳከመ መምጣቱ እሙን ቢሆንም፣ በፋይናንስና በደጋፊዎች ብዛት ግን ለውጥና ዕድገት በማሳየት ላይ ይገኛሉ፡፡ በተለይ ደግሞ የደጋፊዎች ብዛትን በአግባቡ በመጠቀም የበለጠ ውጤት ማስመዝገቡ ላይ ክለቦች የዳዴ ጉዞ እንደሚታይባቸው ይገለጻል፡፡ በእግር ኳሱ የቅርብ ጊዜ ታሪክ ብሎም በደጋፊዎች ብዛት የተነሳ ራሱን ‹‹ሕዝባዊ ክለብ›› ብሎ የሚጠራው የኢትዮጵያ ቡና እግር ኳስ ክለብ ለዚህ ተጠቃሽ ነው፡፡

ክለቡ ሐምሌ 9 ቀን 2009 ዓ.ም. ለሁለተኛ ጊዜ የሚያከናውነው ዓመታዊ የቤተሰብ ሩጫ ‹‹ሜዳችን በራሳችን›› በሚል መሪ ቃል ነው፡፡ በዕለቱ በጀሞ አካባቢ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለስታዲየም ማስገንዘቢያ በተረከበው 35 ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ የመሠረት ድንጋይ እንደሚያስቀምጥ፣ የግንባታው አስተባባሪ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ይስማሸዋ ሥዩም ረቡዕ ሐምሌ 4 ቀን  የቤተሰብ ሩጫውንና የመሠረት ድንጋይ የማኖሩን ሥርዓት አስመልክቶ በአዲስ አበባ ሒልተን በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቀዋል፡፡

በርካታ የኢትዮጵያ ቡና እግር ኳስ ክለብ የቦርድ አባላትና ደጋፊዎች በተገኙበት በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ክለቡ የቱንም ያህል የደጋፊ ብዛት ቢኖረውም ከደጋፊዎቹ ተገቢውን የማቴሪያልና የገንዘብ ድጋፍ በማግኘቱ በኩል ብዙ እንደሚቀረው የሚናገሩ አሉ፡፡ ከዚሁ ባልተናነሰ ከደጋፊዎቹ አንዳንዶቹ ክለቡ በተለይም በአሁኑ ወቅት አቅም ፈጥሮ እያንዳንዱን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ የሚከታተል የአሠራር ሥርዓት ዘርግቶ ባለበት ሰዓት ሳይቀር ጣልቃ የሚገቡ እንዳሉና ለምን እንዲህ ታደርጋላችሁ? ሲባሉ ደግሞ የሚያኮርፉ መኖራቸው የክለቡ ቦርድ ሊቀመንበር የመቶ አለቃ ፈቃደ ማሞ ተናግረዋል፡፡

የክለቡ ‹‹በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ›› ጅምሮች

በደጋፊዎች ብዛት በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ ቡና እግር ኳስ ክለብ በ2007 ዓ.ም. የጀመረውን ዓመታዊ የቤተሰብ ሩጫ ባለፈው ዓመት በተለያዩ ምክንያቶች ሳያከናውን መቅረቱ ይታወሳል፡፡ ክለቡ ዛሬ ለሁለተኛ ጊዜ የሚያካሂደው የቤተሰብ ሩጫ መነሻውን ከ67 ቁጥር አውቶቡስ ማዞሪያ በለቡ መብራት ኃይል አድርጎ፣ በጀርመን አደባባይና በጀሞ ሚካኤል በኩል የክለቡ ስታዲየም ግንባታ የመሠረት ድንጋይ የሚጣልበት ሜዳ ፍጻሜውን እንደሚያደርግ አስተባባሪ ኮሚቴው ገልጿል፡፡

‹‹ሜዳችን በራሳችን›› በሚል መሪ ቃል ከ10,000 በላይ ደጋፊዎችና ቤተሰቦች እንደሚታደሙበትም ተነግሯል፡፡ በዕለቱ በባርሴሎና ኦሊምፒክ በ10,000 ሜትር ድሏ ለሴቶች ተሳትፎ በፈር ቀዳጅነት የምትታወቀው ደራርቱ ቱሉን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች በተገኙበት የሩጫውም ሆነ የስታዲየሙ የመሠረት ድንጋይ የሚከናወነው፡፡ በሥነ ሥርዓቱ የአምቡላንስ አገልግሎትን ጨምሮ የተለያዩ ዝግጀቶች የሚቀርቡ ስለመሆኑ ጭምር አስተባባሪ ኮሚቴ ይፋ አድርጓል፡፡

የቤተሰብ ሩጫውን ስፖንሰር ካደረገው የሐበሻ ቢራና ከደጋፊ ማኅበሩ ከ2.5 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ እንደሚሰበሰብ፣ የክለቡ ቦርድ በወሰነው መሠረትም የቀድሞ የኢትዮጵያ ቡና ተጨዋች የነበረው የአሸናፊ በጋሻው 12 ቁጥር ማሊያ ሌሎች ተጨዋቾች እንዳይለብሱት በማድረግ ቁጥሩ ለክለቡ የደጋፊዎች ማኅበር መለያ ሆኖ መሰየሙ ተገልጿል፡፡

በጋዜጣዊ መግለጫው እንደተገለጸው፣ በ350 ሚሊዮን ብር በጀት በ2010 ዓ.ም. የግንባታው የመጀመሪያው ምዕራፍ እንደሚጀመር የተነገረለት የስታዲየም ግንባታ የክለቡ ውጤት እያሽቆለቆለ በመጣበት በዚህ ወቅት መሆኑ ለምን? ሲሉ ጥያቄ ያነሱ ደጋፊዎች ነበሩ፡፡ የአስተባባሪ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ይልማሸዋ ለቀረበው ጥያቄ በሰጡት ማብራሪያ መሠረት፣ የቡድኑ ውጤት ማሽቆልቆል የደጋፊው ብቻ ሳይሆን ለቦርዱም፣ ‹‹የውስጥ እግር እሳት›› መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ይህ ለኢትዮጵያ ቡና እግር ኳስ ክለብ መሠረተ ልማት ከማሟላት ጋር መያያዝ እንደሌለበትም አስረድተዋል፡፡

ለቡድኑ ውጤት ማሽቆልቆል የችግሩ መሠረታዊ መንስኤና ኃላፊነቱን የሚወስደው አካልን አስመልክቶ ግን፣ ተጨማሪ መድረክ እንደሚኖር ገልጸዋል፡፡ በጋዜጣዊ መግለጫው ዕለት ሌላው እንደ ችግር የቀረበው ክለቡ በጀመረው ዓይነት ሌሎች በርካታ ክለቦች የራሳቸውን ስታዲየም መገንባት የሚያስችል የመሠረት ድንጋይ ከማኖር ያለፈ ነገር እንዳልሠሩ ለአብነት በማንሳት፣ ‹‹ሜዳችን በራሳችን›› የሚለው የኢትዮጵያ ቡና ዕቅድስ ዕውን የመሆኑ ጉዳይ እንዴት ይታያል? የሚለው ይጠቀሳል፡፡

ለጥያቄው ማብራሪያ የሰጡት አቶ ይስማሸዋ፣ ‹‹ኢትዮጵያ ቡና ደጋፊውም ሆነ የክለቡ ቦርድ የሚስማሙበት አንድ ብቸኛ ክፍተት ቡድኑ ደጋፊው በሚፈልገው ልክ ውጤት እያስመዘገበ አይደለም፡፡ ለዚህ ራሱን የቻለ መድረክ ይኖረዋል፡፡ ነገር ግን ከሜዳ ውጭ በዕቅድ ተይዞ ያልተፈጸመ ነገር ካለ መነጋገር እንችላለን፤›› ብለው ይህ ክለቡ ሊያስገነባው ያቀደው ስታዲየም ይጠናቀቃል ተብሎ በዕቅድ የተያዘው በአምስት ዓመት ጊዜ ውስጥ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ቡና የሜዳ ውስጥ ችግር ለምን?

በጋዜጣዊ መግለጫው ከታደሙት የክለቡ ደጋፊዎች ለቡድኑ ውጤት ማጣት ብለው ካስቀመጧቸው ነጥቦች ክለቡን የማይመጥኑ ተጨዋቾች መካተትና የዝውውር ፖሊሲው በምክንያትነት ቀርቧል፡፡

የክለቡ የቦርድ ሊቀመንበር የመቶ አለቃ ፈቃደ፣ ከኢትዮጵያ ቡና የተጨዋቾች ዝውውር ፖሊሲ ጋር ተያይዞ ለቀረበው ቅሬታ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ እንደ ቦርድ ሊቀመንበሩ፣ አገላለጽ ‹‹የኢትዮጵያ  ቡና እግር ኳስ ክለብ እንዲህ እንዳሁኑ ከፋይናንስ ጀምሮ የተለያዩ አደረጃጀቶችን ባልፈጠረበት ወቅት፣ በተለይ የክለቡ ደጋፊዎች ጊዜያቸውንና ገንዘባቸውን ጭምር እያወጡ ተጨዋቾች ለኢትዮጵያ ቡና እንዲጫወቱ በማድረግ መቻላቸው በወቅቱ የማይተካ ሚና ነበራቸው፡፡ ‹‹ክለቡ በእነዚያ ጊዜያት አቅም ስላልነበረው ደጋፊዎች ለክለባቸው ከነበራቸው ከልብ የመነጨ ድጋፍና ክትትል ሊመሰገኑ ግድ ነው፤ ያሉት ሊቀመንበሩ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ቡና ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በአደረጃጀትም በፋይናንስም አቅም መፍጠሩን፣ የተጨዋቾችን ዝውውር ከሚመለከተው አደረጃጀት ጀምሮ የማርኬቲንግ፣ የፋይናንስ እንዲሁም ክለቡ በቀጣይ እንዴት ውጤታማ መሆን እንደሚችል የተለያዩ ስትራቴጂካዊ ዕቅዶችን ማዘጋጀት የሚችል ጠንካራ የአሠራር ሥርዓት መፍጠሩን አውስተዋል፡፡ አያይዘውም ‹‹ይህ ማለት ደግሞ በክለቡ ማን ምን ዓይነት የሥራ ድርሻ እንደሚኖረው ስለሚያመላክት፣ ደጋፊዎች ጭምር በዚህ ሥርዓት ማለፍ ግድ ይላቸዋል፤›› ቢሉም በአሠራሩ አንዳንዶች ማኩረፋቸውን ግን ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

እንደ ሊቀመንበሩ ከሆነ፣ ‹‹ከእንግዲህ የኢትዮጵያ ቡና ነን የምንል ከሆነ ለኢትዮጵያ ቡና በሚበጀው ሥርዓት ማለፍ የውዴታ ግዴታ ነው፡፡ የምንሠራውን እያንዳንዱን ነገር ለደጋፊዎቻችን እያቀረብን መተቸትም ሆነ መጠየቅ ካለብን አምነንና ተቀብለን እንቀጥላለን፡፡ ይህ ማለት ደግሞ ቀደም ሲል እንደነበረው ከተጨዋቾች ዝውውር ጀምሮ ‘እከሌን አስገቡ እከሌን አስወጡ’ በሚለው አሠራር አንቀጥልም፡፡ ይህንን ውሳኔ ለማስቀልበስ የሚሞክሩ ካሉ የሞተን ሰው እንደማስነሳት ይቆጠራል፤›› ብለዋል፡፡

ለውጤቱ ማሽቆልቆል ምክንያት ያሉት ደግሞ፣ ‹‹በክለቡ ውስጥ የክለቡ ነን›› የሚሉ አንዳንድ ወገኖች ምክንያታቸው ምን እንደሆነ ባይታወቅም፣ ተጨዋቾች ወደ ቡና እንዳይገቡ የሚቀሰቅሱና የሚያሳድሙ እንዳሉ በመናገር ነው፡፡ በእነዚህና በሌሎችም መሰል ችግሮች ኢትዮጵያ ቡና ውጤት ማግኘት እየቻለ ውጤት እንዲያጣ የሆነበት አጋጣሚም ብዙ እንደሆነ ጭምር አስረድተዋል፡፡

እነዚሁ አካላት በሌሎች ስም በተለያዩ ማኅበራዊ ድረ ገጾች ሳይቀር የክለቡንና የአመራሮች ሰብዕና የሚያብጠለጥሉ ማንነታቸው በግልጽ የታወቀ መሆኑንና ይህንኑ በሕግ አግባብ ለመጠየቅ ክለቡ መብት ያለው መሆኑንም  ተናግረዋል፡፡

በመጨረሻም የቦርድ ሊቀመንበሩም ሆነ አቶ ይስማሸዋም እንደጠቀሱት፣ በአገሪቱ እግር ኳስ ከፍተኛ የፋይናንስ አቅም ካላቸው ክለቦች በተሻለ በአነስተኛ ፋይናንስ የተሻለ ውጤት ያስመዘገቡ ክለቦች የመገኘቱ ትልቁ ምስጢር ተጨዋቾቹ ለብሰው የሚጫወቱት ማሊያ ከጨርቅ ያለፈ ትርጉም ያለው መሆኑን አምነው መጫወታቸው ነው፡፡

የኢትዮጵያ ቡና እግር ኳስ ክለብም ከእንግዲህ ቅድሚያ የሚሰጠው መጀመርያ በአገሪቱ ካሉት ተጨዋቾች መካከል ‹‹ጨርቅና ማሊያን›› ለይተው የሚያውቁና የሚጫወቱ ተጨዋቾችን ለይቶ እንደሚያስፈርምም በመግለጫው ይፋ አድርገዋል፡፡