Skip to main content
x
‹‹በአገሪቱ አካባቢያዊ ዴሞክራሲ ለማስፈን የአካባቢያዊ አስተዳደሮችን ሥልጣንና ተግባር በግልጽ ማስቀመጥ የግድ ይላል››

‹‹በአገሪቱ አካባቢያዊ ዴሞክራሲ ለማስፈን የአካባቢያዊ አስተዳደሮችን ሥልጣንና ተግባር በግልጽ ማስቀመጥ የግድ ይላል››

ዶ/ ዘመላክ ዓይነተው፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፌዴራሊዝም ጥናት ማዕከል መምህር

ዶ/ር ዘመላክ ዓይተነው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፌዴራሊዝም ጥናት ማዕከል ተባባሪ ፕሮፌሰር ሲሆኑ፣ በዌስተርን ኬፕ ዩኒቨርሲቲ ዱላህ ኦማር ኢንስቲትዩት ኤክስትራኦርዲናሪ ተባባሪ ፕሮፌሰር ናቸው፡፡ ዶ/ር ዘመላክ በአካባቢያዊ አስተዳደር ላይ ትኩረት ያደረጉ የሕገ መንግሥት ኤክስፐርት ናቸው:: የመጀመርያ ዲግሪያቸውን በሕግ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ያገኙ ሲሆን፣ ሁለተኛና ሦስተኛ ዲግሪያቸውን ደቡብ አፍሪካ ከሚገኘው የዌስተርን ኬፕ ዩኒቨርሲቲ ኮሙዩኒቲ ሎው ሴንተር አግኝተዋል:: በተለያዩ ጆርናሎችና ኮንፈረንሶች ላይ በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ የመንግሥት አወቃቀር ከፌዴራል መንግሥቱና ከብሔራዊ ክልላዊ መንግሥቶች ሥር የሚገኙትን እንደ ወረዳ፣ ልዩ ወረዳና ቀበሌ ያሉ አካባቢያዊ አስተዳደሮችን የተመለከቱ የጥናትና ምርምር ሥራዎችን አሳትመዋል፣ አቅርበዋል:: “Local Government in Ethiopia: Advancing Development and Accommodating Ethnic Minorities” በሚል ርዕስ መጽሐፍ አሳትመዋል:: ሰለሞን ጎሹ በቅርቡ በሚካሄደው አካባቢያዊ ምርጫና በአጠቃላይ በአካባቢያዊ አስተዳደሮች ሚና ላይ ዶ/ር ዘመላክን አነጋግሯቸዋል::

ሪፖርተር፡- ያለፉት አምስት አካባቢያዊ ምርጫዎች የተከናወኑት ያለ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተሳትፎ ነው ማለት ይቻላል፡፡ አገሪቱ በዚህ ዓመት ሌላ አካባቢያዊ ምርጫ ታካሂዳለች፡፡ በዚህኛው ዙር የተለየ ነገር ልናይ እችላለን?

ዶ/ር ዘመላክ፡- በመሠረቱ ቀጣዩ አካባቢያዊ ምርጫ ካለፈው የተለየ እንደሆነ እንድናስብ የሚያስገድድ አዲስ ነገር አልተፈጠረም፡፡ እርግጥ ነው ገዥው ፓርቲና ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቀጣዮቹ ምርጫዎች ለሁሉም ዜጎች የሚያጓጉ እንዲሆኑ የማድረግ ዓላማ ይዘው በመደራደር ላይ ናቸው፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ ላይ መሠረታዊ የሆነ ማሻሻያ ለማድረግ መስማማታቸውም ተዘግቧል፡፡ ገዥው ፓርቲ የአገሪቱን የምርጫ ሥርዓት ለማሻሻል፣ በዚህም የተነሳ ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያ ለማድረግ መስማማቱም እንዲሁ ተነግሮ ነበር፡፡ ይኼ በእውነቱ የሚያበረታታ ነው፡፡ ይሁንና አጠቃላይ ትኩረቱ በብሔራዊ ወይም ጠቅላላ ምርጫ ላይ ይመስላል፡፡ በድርድሩም ላይ እየተሳተፉ ያሉት አገር አቀፍ ፓርቲዎች ብቻ ናቸው፡፡ ክልላዊና አካባቢያዊ ፓርቲዎች የድርድር ሒደቱ አካል አይደሉም፡፡ እኔ እስከማውቀው ድረስ አካባቢያዊ ፓርቲዎችና አካባቢያዊ ምርጫዎች የድርድሩ ሒደቱ አካል አይደሉም፡፡ ፓርቲዎቹ በጠቅላላ ምርጫ ላይ የሚደርሱበት ስምምነት ለአካባቢያዊ ምርጫዎች ተፈጻሚ ስለመሆኑ እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ ድርድሩም ሆነ የማሻሻያ ሐሳቡ ታሳቢ ያደረገው በ2012 ዓ.ም. የሚካሄደውን ጠቅላላ ምርጫ በመሆኑ፣ ማሻሻያዎቹን በአካባቢያዊ ምርጫዎች ለመፈተሽ በቂ ጊዜ ያለ አይመስለኝም፡፡

ሪፖርተር፡- ከመቼውም ጊዜ በባሰ ሁኔታ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከገዥው ፓርቲ ጋር ተወዳድረው በአካባቢያዊ ምክር ቤቶች ወንበሮችን ለማሸነፍ የሚያስችል ቁመና እንደ ሌላቸው ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ የእርስዎ የጥናት ሥራዎች ግን ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአካባቢያዊ ምርጫዎች የመሳተፍ ፍላጎት እንኳን እንደሌላቸው ያሳያሉ፡፡ ይህ ፍላጎት ማጣት የመጣው በምን ምክንያት ነው?

ዶ/ር ዘመላክ፡- ከጥያቄህ ከራሱ ማንበብ እንደሚቻለው በምርጫው የማሸነፍ ዕድል የሌላቸው መሆኑን መገንዘባቸው በምርጫ የመሳተፍ ፍላጎት እንዲያጡ ያደርጋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ አሁን ብዙ እርከኖች ያሉት የመንግሥት ሥርዓት ነው ያለን፡፡ ሦስት ራሳቸውን የቻሉና ነፃነት ያላቸው የመንግሥት እርከኖች ማለትም የፌዴራል መንግሥት፣ የክልል መንግሥታትና አካባቢያዊ አስተዳደሮችን የማዋቀር ሥልጣን በሕገ መንግሥቱ የተቀመጠ ቢሆንም፣ ይህ ልዩነት በእያንዳንዱ ዜጋ አዕምሮ ውስጥ የሰረፀ አይመስልም፡፡ ካለፈው አሀዳዊ የመንግሥት ሥርዓት የወረስነው የሚመስለኝ አንድ አስተሳሰብ አለ፡፡ ይህ አስተሳሰብ ማዕከላዊውን ወይም የፌዴራል መንግሥቱን መቆጣጠር ወሳኝ እንደሆነና ከማዕከሉ ርቀው የሚገኙ አካባቢያዊ አስተዳደሮችን ወዲያውኑ ለመቆጣጠር ያበቃል በሚል ያስቀምጣል፡፡

ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች በተለይ ብሔራዊና ወይም አገር አቀፍ የሆኑት ማዕከላዊው ወይም ፌዴራል መንግሥቱ ላይ ትኩረት ማድረግን እንደ ጥሩ ስትራቴጂ ይወስዱታል፡፡ በጠቅላላና በአካባቢያዊ ምርጫዎች ላይ ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ይገጥሙናል የሚሏቸው ለሥራና ለውድድር ምቹ ያልሆነ የሕግ ማዕቀፍና የፖለቲካ ጭቆናን ጨምሮ፣ የተለያዩ ተቋማዊና ፖለቲካዊ ጫናዎች ከሞላ ጎደል ተመሳሳይ ናቸው፡፡ ይሁንና እነዚህ ጉዳዮች በጠቅላላ ምርጫ ላይ ከመሳተፍ አላገዷቸውም፡፡ ነገር ግን በአካባቢያዊ ምርጫዎች ላይ የመጀመርያው ችግር ምልክት እንደታየ ከምርጫው ራሳቸውን ያገላሉ፡፡

ሪፖርተር፡- ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች የድጋፍ መሠረት ከመቼውም ጊዜ ይልቅ ደካማ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ ይሁንና በአካባቢያዊ ምርጫዎች ለመሳተፍ ማቅረብ የሚጠበቅባቸው የዕጩ ቁጥር ከሦስት ሚሊዮን በላይ ነው፡፡ ይህና በድኅረ ምርጫ 97 የተወሰዱ ሌሎች የሕግ ማሻሻያዎች አካባቢያዊ ምርጫዎች ላይ ምን ያህል ተፅዕኖ ፈጥረዋል?

ዶ/ር ዘመላክ፡- በቀበሌ፣ በወረዳ፣ በከተማና በዞን ደረጃ ያሉ አካባቢያዊ ምክር ቤቶች ወንበሮች ቁጥር ከ600,000 ወደ 3.6 ሚሊዮን እንዲጨምር ያደረገው ማሻሻያ በአገሪቱ ላይ በከፍተኛ ሁኔታ አሉታዊ ተፅዕኖ ከፈጠሩ የድኅረ ምርጫ 97 የሕግ ማሻሻያዎች አካል ነው፡፡ በ2000 ዓ.ም. ሥራ ላይ ውሏል፡፡ ገዥው ፓርቲ ይህን ማሻሻያ ያደረገው “የሕዝቦችን የፖለቲካ ውክልናና ተሳትፎ ለማሳደግ” እንደሆነ ይገልጻል፡፡ ነገር ግን ገዥው ፓርቲ ይህን ለማድረግ ሐሳብ የሌለው እንኳን ቢሆን፣ ሦስት ሚሊዮን ዕጩዎችን የሚያንቀሳቀስ  አደረጃጀትና የገንዘብ አቅም ያለው ገዥው ፓርቲ ብቻ በመሆኑ፣ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአካባቢያዊ ምርጫዎች የማሸነፍ ዕድላቸውን ፍፁም የማይቻል በማድረግ ይህ ማሻሻያ ግልጽ ተፅዕኖ ፈጥሯል፡፡

አንድ የኢሕአዴግ ከፍተኛ ባለሥልጣን እንደነገሩኝ ከሆነ፣ ኢሕአዴግ አካባቢያዊ ምክር ቤቶችን የሚወስዳቸው ለቀጥተኛ ሕዝባዊ ተሳትፎ መድረክ እንደሆኑ ነው እንጂ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚቀናቀኑባቸው መድረኮች አድርጎ አይደለም፡፡ ይህ አመለካከት በአካባቢያዊ አስተዳደሮች ደረጃ መድበለ ፓርቲ አስፈላጊ እንዳልሆነ ያመለክታል፡፡ እርግጥ ነው አካባቢያዊ አስተዳደሮች የሚሠሩት “ዳቦና ቅቤ” ላይ በመሆኑ ከመድበለ ፓርቲ ፖለቲካ ሊፀዳ ይገባል በማለት የሚከራከሩ ምሁራን አሉ፡፡ ይህ የገዥው ፓርቲ ሐሳብ ከሆነ፣ ምናልባትም በፓርቲ ደረጃ ሳይሆን ግለሰቦች ገለልተኛ ዕጩ ሆነው አካባቢያዊ ምክር ቤቶች መቀመጫዎች የምረጡኝ ዘመቻ የሚያደርጉበትና የሚወዳደሩበት ምርጫ ማካሄድ እንደ አማራጭ መታየት አለበት፡፡ ይህን በቻይና ተግባራዊ የሚያደርጉ ይመስለኛል፡፡ ነገር ግን ይህን ማድረግ ደግሞ የራሱ ችግሮች ይኖሩታል፡፡ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከገዥው ፓርቲ ጋር እያደረጉ ባለው ድርድር የአካባቢያዊ ምክር ቤቶች ወንበሮች ቁጥር እንዲቀንስ ጥያቄ ያቀረቡ አይመስለኝም፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ማሻሻያ ማድረግ ያስፈልጋል ብዬ የማምነው ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲች በአካባቢያዊ ምክር ቤቶች ውስጥ የተወሰኑ መቀመጫዎችን እንዲያሸንፉ ለማስቻል ብቻ ሳይሆን፣ ለአካባቢያዊ ዴሞክራሲ ጤናማ ከባቢ ሁኔታ ለመፍጠርም ነው፡፡

ሪፖርተር፡- አካባቢያዊ ምርጫዎች ገዥው ፓርቲ የሕዝብ መተማመኛ የሚያገኝባቸው መሣሪያዎች እንጂ በራሳቸው ዴሞክራሲያዊ ምርጫ የሚደረግባቸው አይደሉም የሚሉ አሉ፡፡ በዚህ ግምገማ ይስማማሉ?

ዶ/ር ዘመላክ፡- ቀደም ብዬ እንዳልኩት አካባቢያዊ ምርጫዎችን የሚገዛው ተቋማዊ ማዕቀፍ ገዥው ፓርቲን ይበልጥ ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው፡፡ ይህ አሠራር የሚቀጥል ከሆነ የተለየ ውጤት መጠበቅ አይቻልም፡፡

ሪፖርተር፡- እንደ ኢሕአዴግ ያሉ አውራ ፓርቲዎችን ለማሸነፍ ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች አካባቢያዊ አስተዳደሮችን ከመቆጣጠር መጀመር እንዳለባቸውና ቀስ በቀስ ፌዴራል መንግሥቱን የመቆጣጠር አቅም እየዲገነቡ የሚመክሩ ኤክስፐርቶች አሉ፡፡ በሌላ በኩል እርስዎም በምርምር ሥራዎች እንደሚከራከሩት፣ ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች በቅድሚያ የፌዴራል መንግሥትን መቆጣጠር በእርግጠኝነት አካባቢያዊ አስተዳደሮችን ለመቆጣጠር ያስችላል የሚል ስትራቴጂ ነው ያላቸው:: እርስዎ የትኛው የተሻለ ነው ብለው ያስባሉ?

ዶ/ር ዘመላክ፡- እኔ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች የፌዴራል መንግሥቱን ለመቆጣጠር በማሰብ ወደ ውድድር ከመግባታቸው በፊት፣ ከዚያ በመለስ ያሉ የመንግሥት እርከኖች ላይ በማተኮር ጠንካራ የፖለቲካ መሠረት እንዲፈጥሩ ከሚከራከሩት ውስጥ አንዱ ነኝ፡፡ ሌሎች ምክንያቶችን ገለል በማድረግ ሙሉ በሙሉ ምርጫ ላይ ብቻ ካተኮርን ኢሕአዴግ የፌዴራል መንግሥቱን የተቆጣጠረው የአካባቢያዊ ምክር ቤቶችን ስለተቆጣጠረ ነው፡፡ በተገላቢጦሽ ምክንያት አይደለም:: በ2005 ዓ.ም. አካባቢያዊ ምርጫ ከመደረጉ ጥቂት ጊዜ በፊት ጋዜጣ ላይ በጻፍኩት አንድ አስተያየት ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች አካባቢያዊ አስተዳደሮችን መቆጣጠራቸው የፖሊሲያቸውን ውጤታማነት ለመፈተሽ፣ የአስተዳደር ልምድ እንዲቀስሙ፣ እንዲሁም ከሕዝቡ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት እንዳይፈጥሩ የሚከለክሏቸው ጨቋኝ አካባቢያዊ ባለሥልጣናትን ጨምሮ፣ በምርጫ ስኬት እንዳያስመዘግቡ እንቅፋት ሆነውብናል የሚሏቸውን ሌሎች ችግሮች ለማስወገድ እንደሚያስችል ተከራክሬያለሁ::

እርግጥ ነው ይህ አስተያየት ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአካባቢያዊ ምርጫዎች ለመወዳደርና ለማሸነፍ በጣሩበት መጠን እንዲያሸንፉ የሚያስችሉ ተቋማዊና ፖለቲካዊ ከባቢ ሁኔታዎች አስቀድመው መሟላታቸውን ታሳቢ ያደርጋል፡፡ ስለዚህ የአካባቢያዊ ምክር ቤቶች ዕጩዎች ቁጥርን መቀነስ ጨምሮ ከላይ የጠቀስኳቸው ችግሮች ካልተቀረፉ፣ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአካባቢያዊ ምርጫዎች ላይ ለመሳተፍና ውጤታማ ለመሆን ማትጊያ የማግኘት ዕድላቸው በጣም ዝቅተኛ ነው፡፡ ለዚህም ነው ከላይ እንደተናገርኩት ከገዥው ፓርቲ ጋር እየተደራደሩ ያሉት ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች የአካባቢያዊ አስተዳደሮችንና አካባቢያዊ ምርጫዎችን ጉዳይ ወደ ውይይት ጠረጴዛው ማምጣት ያለባቸው፡፡

ሪፖርተር፡- የአካባቢያዊ ምርጫዎች ይዞታ በአገሪቱ እንዲሻሻል ብሔራዊ ምርጫ ቦርድና ሚዲያው ምን ማድረግ ይችላሉ?

ዶ/ር ዘመላክ፡- በአገራችን አካባቢያዊ ምርጫዎች የሚካሄዱት በፀጥታና ያለ ብዙ ድራማ ነው፡፡ አሁን ቀጣዩ አካባቢያዊ ምርጫ ሊካሄድ የቀረው ከአንድ ዓመት ያነሰ ጊዜ ነው፡፡ ይሁንና ፓርቲዎችና ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለምርጫው እያደረጉ ያለውን ዝግጅት በተመለከተ የተሠራ አንድም የሚዲያ ሪፖርት አላየሁም፡፡ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በዚሁ ጉዳይ ላይ ስለሰጠው አንድም መግለጫ አልሰማሁም፡፡ በእውነቱ የቦርዱን ድረ ገጽ ሳይም በምርጫው ላይ ምንም የተባለ ነገር የለም፡፡ የሚካሄደው ጠቅላላ ምርጫ ቢሆን ኖሮ በዚህ ወቅት ሚዲያው ምርጫውን በተመለከተ ዜናና ሪፖርት ተጥለቅልቆ ነበር፡፡ ይኼ በአገራችን አካባቢያዊ ምርጫዎችና አካባቢያዊ ዴሞክራሲ ያላቸውን ዝቅተኛ ደረጃ ያሳያል፡፡

አካባቢያዊ ዴሞክራሲ በአገሪቱ አጠቃላይ የዴሞክራሲ ሽግግር ሒደት ላይ ሊጫወት የሚችለው ግዙፍ ሚና ላይ ያለው ግንዛቤ በጣም ጥቂት ነው፡፡ የአሜሪካን ዴሞክራሲ በጥንቃቄ ያጠኑት ፈረንሣዊው ፈላስፋ አሌክሲስ ዲቶክቪሌ አሜሪካ በዋነኛነት ዴሞክራሲያዊ አገር የሆነችው፣ አካባቢያዊ ዴሞክራሲን በቅድሚያ በማረጋገጧ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ በሌላ በኩል በአገራችን አካባቢያዊ አስተዳደር ሲነሳ ወደ አዕምሮ የሚመጣው ትንሽ ፈላጭ ቆራጭ ሰው ነው፡፡ ስለዚህ አካባቢያዊ አስተዳደሮችን ዴሞክራሲያዊ ለማድረግ ብዙ መሥራት ይጠበቅብናል፡፡ በአካባቢያዊ ዴሞክራሲ ጠቀሜታ ላይ ግንዛቤ ከመፍጠር አንፃር ሚዲያው ሊሠራ ይገባል፡፡

ሪፖርተር፡- ከዚህ አንፃር የፌዴራል መንግሥትና የክልል መንግሥታት ምን ዓይነት ሚና ይኖራቸዋል?

ዶ/ር ዘመላክ፡- ማዕከላዊውን መንግሥት የሚመሩ አካላት አካባቢያዊ አስተዳደሮችንና አካባቢያዊ ባለሥልጣናትን እንደ ዴሞክራሲያዊ ተቋማት ከመቀበል ይልቅ የሥልጣን መሣሪያ አድርገው ነው የሚያዩዋቸው በዚህ ረገድ ብዙ ነገር አልተለወጠም፡፡ እርግጥ ሕገ መንግሥቱ አካባቢያዊ አስተዳደሮች ራሳቸውን የቻሉ የአስተዳደር እርከኖች መሆናቸውን በግልጽ አይደነግግም:: አካባቢያዊ አስተዳደሮች ነፃነት ያላቸው፣ በዴሞክራሲያዊ መርህ የሚመራ አመራር ያላቸው መሆናቸውን የሚጠቁሙ ድንጋጌዎች ግን አሉ፡፡ አካባቢያዊ አስተዳደሮች ዴሞክራሲያዊ ተቋማት እንዲሆኑ ለማድረግ የፌዴራል መንግሥቱና የክልል መንግሥታት ሊወስዷቸው የሚችሏቸው የተወሰኑ ዕርምጃዎች አሉ፡፡ አካባቢያዊ አስተዳደሮች የሁለቱ የመንግሥት እርከኖች አስተዳደራዊ ወኪሎች ሳይሆኑ፣ ራሳቸውን የቻሉ የመንግሥት እርከኖች እንደሆኑ ዕውቅና ሊሰጡ ይገባል፡፡ የሕገ መንግሥቱ ንባብ አካባቢያዊ አስተዳደሮች ራሳቸውን የቻሉና ነፃነት ያላቸው መዋቅሮች እንደሆኑ ቢያመለክትም፣ በኢትዮጵያ አካባቢያዊ አስተዳደሮች ጠንካራ ሕገ መንግሥታዊ ድጋፍ የላቸውም፡፡

ስለዚህ የፌዴራል መንግሥት የሕገ መንግሥት ማሻሻያ በማድረግ ይህ በሕገ መንግሥቱ በግልጽ ዕውቅና እንዲያገኝና እንዲካተት ማድረግ አለበት፡፡ የወረዳዎችና የቀበሌዎችን የፖለቲካ ነፃነት እንዲሸረሸር፣ በዚህም ዴሞክራሲያዊ ባህሪያቸው እንዲጠፋ ያደረጉ ሕጎችን የማስተካከል ዕርምጃ የክልል መንግሥታት ሊወስዷቸው ከሚችሉ የተወሰኑ ዕርምጃዎች የሚካተት ነው፡፡ ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነው የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት እ.ኤ.አ. በ2006 ያወጣው አዋጅ ቁጥር 116 ነው፡፡ ይህ አዋጅ በክልሉ ውስጥ የሚገኙ የከተማ ምክር ቤቶች የራሳቸውን ከንቲባ የመምረጥ ወይም የመሾም ሥልጣን ይከለክላቸዋል፡፡ በአዋጁ ይህ ሥልጣን ወደ ክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ተሸጋግሯል፡፡ በእኔ እምነት ይህ አዋጅ ያለ ምንም ዓይነት ሕገ መንግሥታዊ ተግዳሮት የፀደቀው አካባቢያዊ አስተዳደሮች ነፃነት ያላቸው የመንግሥት መዋቅሮች መሆናቸው በፌዴራሉ ሕገ መንግሥት በግልጽ ዕውቅና ስላልተሰጠው ነው፡፡ የክልል መንግሥታት በሕገ መንግሥታቶቻቸው ላይ ማሻሻያ በማድረግ የአካባቢያዊ አስተዳደሮችን ሥልጣንና ተግባር በግልጽ ማስቀመጥና በቂ የገቢ ምንጭ እንዲኖራቸው ማድረግ አለባቸው::

ከዚህ አንፃር በፍጥነት ማሻሻያ ሊደረግበት የሚገባው ጉዳይ የክልል መንግሥታት ለወረዳዎች እንዲሁም በተወሰነ መልኩ ለከተማዎች የሚያስተቅላልፉት ቅድመ ሁኔታ የሌለውን የበጀት ድጋፍ (Block Grant) አስገዳጅ ማድረግ ነው፡፡ በትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ሕገ መንግሥት በተወሰነ ደረጃ ከተቀመጠው በስተቀር፣ የወረዳዎች ተግባር ምን እንደሆነ የክልል ሕገ መንግሥታቶች በግልጽ አያስቀምጡም፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ክልሎች ለወረዳዎች የሚያስተላልፉት እንዲሁም በተወሰነ መልኩ ለከተማዎች የሚያስተቅላልፉት ቅድመ ሁኔታ የሌለው የበጀት ድጋፍ ከ70 በመቶ በላይ የወረዳዎቹን ወጪ የሚሸፍን ቢሆንም፣ እንደ ስጦታ የሚወሰድ በመሆኑ ይህን ማግኘት የወረዳዎች መብት አይደለም፡፡ በአገሪቱ አካባቢያዊ ዴሞክራሲ ለማስፈን የአካባቢያዊ አስተዳደሮችን ሥልጣንና ተግባር በግልጽ ማስቀመጥ የግድ ይላል፡፡ አለበለዚያ አንድ ፓርቲ ሥልጣንና ተግባሮቻቸው በግልጽ የማይታወቁ አካባቢያዊ አስተዳደሮችን ለመቆጣጠር፣ በአካባቢያዊ ምርጫዎች የመሳተፍ ፍላጎት አይኖረውም፡፡ የክልል መንግሥታት ለአካባቢያዊ አስተዳደሮች ቅድመ ሁኔታ የሌለው የበጀት ድጋፍ እንዲያደርጉ የሚያስገድድ ሕግ ማውጣት ሌላ የሚሰጠው ጥቅም፣ አንድ የክልል መንግሥት ክልሉን ከሚመራው ፓርቲ ውጪ በሆነ ሌላ ፓርቲ ለመመራት ለመረጠ ወረዳ ወይም ከተማ በጀት አላስተላልፍም እንዳይል የሚከለክል መሆኑ ነው፡፡