Skip to main content
x
‹‹በየት በኩል ልውጣ?››

‹‹በየት በኩል ልውጣ?››

ደንበል ሲቲ ሴንተር ጀርባ አውራ መንገዱ በመቆፈሩ ምክንያት ከግቢ መውጣት ያልቻለችው ተሽከርካሪ   

ያላነጋው ቀን

ነጋ ስንል ቀኑ ጠራ፣

ፈካ ስንል ፀሐይ በራ፣

መንገዳችን መቼ ፀና? 

ልባችንስ መቼ ቀና?

ገና . . .

ገና . . .

ገና . . .

ገና . . .

ሰለሞን ሞገስ (ፋሲል) ‹‹የተገለጡ ዓይኖች›› (ሐምሌ 2009 ዓ.ም.)
*****

የሕዝቡ ዕውቀትና ሀብት ሲያድግ የመንግሥቱ ሀብትና ሐሳብም ይሰፋል

እስቴር ሶምሎ የሚባል የጀርመን ሊቅ እንዲህ ይላል፣ እያንዳንዱ ሰው ሌላውን ሰው ሁሉ አጥቅቶ ለብቻው እንደ ፈቃዱ እንዲኖር ይወዳል፡፡ መንግሥት ግን በግዛቱ ውስጥ የሚኖሩትን ኃይለኞች ሁሉ እርስ በርሳቸው እንዲተፋፈሩ የግድ ይላቸዋል፡፡ የመንግሥት ጥረቱ ሕዝቡን ሁሉ አስማምቶ በመካከላቸው ሰላም ለማድረግ ነው፡፡ ስለዚህም መንግሥት የተሻለውን ሥርዓት እያወጣ፣ ያወጣውንም ሥርዓት እንዳይፈርስበት ባለቤቱ ይጠብቃል፡፡ ሥርዓት አውጪውም ዳኛም መንግሥት ራሱ ነው፡፡ ከዳኝነቱ በቀር ሕዝቡን ከፍ ወዳለው የዕውቀትና የሀብት ደረጃ እንዲደርስ የማስተዳደሪያ ደንብ እያወጣ ባወጣውም ደንብ ሕዝቡን በሥርዓት ያስተዳድራል፡፡ ሕዝቡንም ማስተዳደር ማለት ጥንት የቆየውን የሕዝብ ጥቅም እንዳይጠፋ መጠበቅ ነው፡፡ ሌላውንም አዲስ ጥቅም አዘጋጅቶ አውጥቶ በግድ ማስፈጸም ነው፡፡ የሕዝብ ሐሳብና ሀብት ሲሰፋ መንግሥት ሐሳቡን ለማስፈጸም የበለጠ ኃይል ያገኛል፡፡

እንግዲህ እንደ ሊቁ ቃል ከሄድን ዘንድ፣ በመንግሥቱ ውስጥ የሚያድር ሕዝብ ዕውቀት የሌለውና ደሃ የሆነ እንደሆነ መንግሥቱ ኃይል ሊያገኝ አይችልም፡፡ እንኳን በውጭ አገር ሊታፈር የገዛ ሕዝቡም ቢሆን አያፍሩትም፡፡ በአገሩ ውስጥ ሽፍታ፣ ወንበዴና ሌባም ይበዛበታል፡፡ ሕዝቡ ዕውቀት ሲያድርበት ግን መንግሥት አዋቂዎች፣ ሠራተኞችንና ሹማምንቶችን ያገኛል፡፡ ሕዝቡም ሲበለፅግ መንግሥት በግብር የሚያገኘው ገንዘብ እየበዛ ይሄዳል፡፡

ገብረሕይወት ባይከዳኝ ‹‹መንግሥትና የሕዝብ አስተዳደር›› (1916)
*******

ፓሽን ፍሩት

ፓሽን ፍሩት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገራችን እየተስፋፋ የመጣ ተክል ነው፡፡ ከዚህ ተክል ግንድ ልክ እንደ ሐረግ የሚመዘዝ ነው፡፡ አበባና ፍሬ አለው፡፡ ለመድኃኒትነት የሚያገለግሉት አበባውና የፍሬው ልጣጭ ናቸው፡፡ የአበባው ቅመማ ውስብስብ በመሆኑ የፍሬውን ልጣጭ ጠቀሜታ መቃኘቱ ይበጃል፡፡ ፍሬውን /ሁለትና ሦስት ፍሬ/ ትኩሱን መመገብ ይቻላል፡፡ የፍሬውን ልጣጭ በመውቀጥ፣ አንድ የሻይ ማንኪያ /ድርበብ/ አንድ ብርጭቆ ውስጥ በጥብጦ ጠዋትና ማታ መጠጣት የፈውስ ረድኤቱን መቀራመትም ይቻላል፡፡

ፓሽን ፍሩት የነርቭ ዕውክታን በማስተካከል፣ የእንቅልፍ ችግርን በመክላት፣ ግልፍተኝነትንና ንክነትን የመሳሰሉ የአዕምሮ ችግሮችን በማረም በኩልም ምስጉን ነው፡፡ ፍሬው ለሚያገግሙ በሽተኞችና ላረጡ ሴቶችም ጠቀሜታ አለው፡፡ ፓሽን ፍሩት ለትኩሳትም ይበጃል፡፡ ፍሬው ሱስ ባያስይዝም፣ የዕፅ ሱሰኞችን ባህርይ ለማረም ይረዳል፡፡ ነርቮችን በማለሳለስ በብስጭት ሳቢያ ከፍ የሚል የደም ግፊትን ያወርዳል፡፡ የነርቭ ችግር ላለበት ሁሉ የፈውስ ረድኤትን ይፈነጥቃል፡፡ በአዕምሮ ውጥረት ሳቢያ ለሚከተል የራስ ምታትም ፓሽን ፍሩት መድህን ነው፡፡ በስሜት መገንፈል ሳቢያ በሚነሳ አስም /ስፓስሞዲክ አስማ/ ለሚሰቃዩም እፎይታን ይሰጣል፡፡

ዶክተር ቤዲ ‹‹ዳየት-ክዩር›› ጥንቅር በሻለቃ ዓባይነህ አበራ ‹‹ካዘና››
*******

በቀን የ10 ደቂቃ የእግር ጉዞ የሚጨመረው ዕድሜ

      የጤና ነገር ሲነሳ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ሁሌም አብሮ ይነሳል፡፡ በተለይ ብዙውን የሥራ ጊዜያቸውን ቁጭ ብለው የሚሠሩ ሰዎች ከተለያዩ በሽታዎች ይጠበቁ ዘንድ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ ይመከራሉ፡፡ በስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራ መሄድ ባይችሉ የእግር ጉዞ በማድረግ ሰውነታቸውን እንዲያፍታቱም ይመከራሉ፡፡

      ቢቢሲ ይዞት የወጣው ዘገባ ደግሞ፣ በተለይ ዕድሜያቸው ከ40 እስከ 60 ያሉ ሰዎች በቀን ለ10 ደቂቃ ያህል ፈጠን ፈጠን ያለ የእግር ጉዞ በማድረግ ያለ ዕድሜ ሞትን 15 በመቶ መቀነስ ይችላሉ ብሏል፡፡ ለ10 ደቂቃ የሚደረገው የእግር ጉዞም በየቀኑ መሆን እንዳለበት አስፍሯል፡፡

*****

በምጥ የተያዘች እናቱን ያዳነ የአሥር ዓመት ታዳጊ

አሸሌይ ሞሪው የመውለጃዋ ጊዜ እየታቀረበ ቢሆንም፣ በ34ኛ ሳምንቷ ላይ እወልዳለሁ ብላ አልገመተችም ነበር፡፡ ሆኖም በመፀዳጃ ቤት ባለችበት ሰዓት ድንገት ምጥ ይመጣና ሽንት ውኃ ይፈሳታል፡፡ ወዲያውም ምጥ አፋፍሟት ደም ይፈሳታል፡፡ የእናቱን ሲቃ የሰማው የአሥር ዓመታት ታዳጊ እናቱን ሲያይ ከመደናገጥ ይልቅ ከጎረቤት ያሉት አያቱ ለፖሊስ እንዲደውሉ ነግሮ እናቱን ምን ማድረግ እንዳለበት እንድትነግረው ብቻ ነበር የጠየቃት፡፡

እናቱ ጨቅላው የ34 ዓመት ሳምንት ስለሆነ መተንፈስ ሊቸግረው እንደሚችል፣ ስለሆነም እሷ ስትገፋ እሱ በፍጥነት ጨቅላውን ስቦ ማውጣት እንዳለበት ትነግረዋለች፡፡ የአሥር ዓመቱ ጄይደን ፎንቴኖት እናቱ ባለችው መሠረት ጨቅላውን ቢያዋልዳትም ትንፋሽ አልነበረውም፡፡ በመሆኑም ቤት ውስጥ የነበረውን በአፍንጫ ለመተንፈስ ሲቸገር (አስም ያለባቸው ሰዎች የሚጠቀሙት) የሚረጭ መድኃኒት አምጥቶ የሕፃኑን አፍንጫ እንዲከፈት ይረጫል፡፡ ወዲያውም የሕክምና ባለሙያዎች ደርሰው ጨቅላውንም እናቲቱንም ወደ ሕክምና በመውሰድ የሁለቱም ሕይወት ሊተርፍ ችሏል፡፡ ፎንቴኖት የእናቱንና የጨቅላውን ሕይወት በማትረፉም በአሜሪካ በሉዊዛና ግዛት ከንቲባ ዕውቅና ተሰጥቶታል፡፡

*******

የናይጄሪያው ፕሬዚዳንት ቢሮ በዓይጥ መወረር

ዓይጦች በተለይም የመንገድ ፍሳሽ ማስወገጃ ዝግ ትቦዎች ባሉባቸው ሥፍራዎች ተራብተው ድንገት መንገድ ማጥለቅለቃቸው ከዚህ ቀደም ተነግሯል፡፡ አሁን ደግሞ የናይጄሪያው ፕሬዚዳንት ሙሃማዱ ቡሃሪ ቢሮ በዓይጥ መወረሩን ዚስዴይ ዘግቧል፡፡

‹‹ድመቱ ሲሄድ ዓይጦች ይጫወታሉ›› እንዲሉ የፕሬዚዳንት ቡሃሪ ቢሮ በዓይጦች የተወረረው፣ ለሕክምና ወደ ለንደን ባቀኑበት ወቅት ነው፡፡

የፕሬዚዳንቱ ከፍተኛ የሚዲያና ፐብሊሲቲ ረዳት ጋራባ ሺሁ እንዳሉት፣ ዓይጦቹ የቢሮውን ሶፋዎችና የአየር ማመጣጠኛ መቆጣጠሪያ ክፍሉን ቁሳቁሶች አውድመዋል፡፡ ቢሮው በጠጋኝ ኩባንያ እየታደሰ ቢሆንም ፕሬዚዳንቱ ከዓይጥ ነፃ ከሆነው ቤታቸው ሆነው ለመሥራት ተገደዋል፡፡