Skip to main content
x
‹‹በጋምቤላ ማማረጥ ካልሆነ ሥራ ተፈልጎ የሚታጣባት አይደለችም››

‹‹በጋምቤላ ማማረጥ ካልሆነ ሥራ ተፈልጎ የሚታጣባት አይደለችም››

በ​ ታምራት ጌታቸው

አቶ ኦካኔ ኡጋዳ ኡፓዲ፣ የጋምቤላ ከተማ ዋና ከንቲባ

በጋምቤላ ከ345 ሺሕ በላይ ስደተኞች በተለያዩ የስደተኛ ካምፖች ተጠልለው ይገኛሉ፡፡ ከተማዋ በመሠረተ ልማት ለውጥ እያስመዘገበች ቢሆንም፣ ከስደተኞች ጋር በተያያዘ የሚከሰቱ አለመግባባቶች ክልሏን በተለያዩ ጊዜያት ለፀጥታ ችግር ሲያጋልጧት ተስተውለዋል፡፡ አቶ ኦካኔ ኡጋዳ ኡፓዲ የጋምቤላ ከተማ ዋና ከንቲባ ናቸው፡፡ ጋምቤላ ስላለችበት ሁኔታና በክልሉ የተጠለሉ ስደተኞች ስላሳደሩት ተፅዕኖ ታምራት ጌታቸው ከንቲባውን አቶ ኡካኔ አነጋግሯቸዋል፡፡  

ሪፖርተር፡- ጋምቤላ በምን ያህል ወረዳዎችና ቀበሌዎች የተከፋፈለች ናት? የሕዝቦች አሠፋፈርስ ምን ይመስላል?

አቶ ኦካኔ፡- ጋምቤላ ትንሿ ኢትዮጵያ ነች ማለት ይቻላል፡፡ ከሁሉም ክልል የመጡ ነዋሪዎች ከተወላጁ ጋር የሚኖርባት ነች፡፡ ይህም ለየት ያደርጋታል፡፡ አኗኗሯርን በተመለከተ ይህን ያህል የተደራጀና ዘመናዊ አሠፋፈር የተከተለ አይደለም፡፡ ጋምቤላ ከተማ በአምስት ቀበሌዎች የተከፋፈለች ስትሆን በቅርቡ ግን ወደ ሦስት ወረዳዎች ለማሳደግ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ከመሠረተ ልማት አኳያ ያለው እንቅስቃሴ ምን ይመስላል?

አቶ ኦካኔ፡- ጋምቤላ ከዚህ በፊት ምንም ያልነበራት ከተማ ነበረች፡፡ ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች የአስፋልት መንገድ፣ የተለያዩ መሠረተ ልማቶች አለመኖር ብዙም እንቅስቃሴ የማይታይባት ከተማ አድርጓት ቆይቷል፡፡ ከሆቴል አቅም እንኳን የዛሬው ባሮ ሆቴል ብቻ ነበር ያለው፡፡ እንግዲህ ከተማዋ ትልቅ ለውጥ ያመጣችው 11ኛው የብሔር ብሔረሰቦች በዓል በክልሉ እንዲከበር ከተወሰነ በኋላ ነው፡፡ በተሰጠን በስምንት ወር ጊዜ ውስጥ ከማኅበረሰቡ ጋር በመሆን ጠንካራ አመራር በመፍጠር ስታዲየም፣ የመሰባሰቢያ አዳራሽ፣ የመንግሥት ቢሮዎች፣ የአስፋልት መንገዶች፣ ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች፣ በመንግሥትና በግል የተገነቡ ሲሆን ዛሬ እንደ ሌሎች ከተሞች መሆን ጀምራለች፡፡

ሪፖርተር፡- በወቅቱ የነበረው ከተማዋን የማልማት እንቅስቃሴ ዛሬ ቀዝቅዟል ይባላል፡፡ ለምንድነው?

አቶ ኦካኔ፡- 11ኛ የብሔር ብሔረሰቦች በዓል በክልሉ መከበሩ ካስተማረን አንዱ በአጭር ጊዜ የተለያዩ ማኅበረሰቦችን በማስተባበር አገር መለወጥ እንደሚቻል ነው፡፡ ይህን ለማድረግ ግን ቁርጠኛ አመራር፣ ሠርቶ የሚያሠራ ያስፈልጋል፡፡ ዝም ብሎ ሊሠራ አይችልም፡፡ በመሀል የተፈጠረው ችግር፣ የአመራሮች እየተዳከሙ መምጣትና በአገሪቱ ተከስቶ የነበረው ችግር ጋምቤላም ውስጥ በመታየቱና አመራሮች በዚህ ችግር ውስጥ በመዘፈቃችን ሊቀዘቅዝ ችሏል፡፡

ሪፖርተር፡- በከተማዋ ከፍተኛ የወጣት ሥራ አጥ መኖር እንደ ችግር ይነሳል፡፡ እዚህ ላይ ምን እየሠራችሁ ነው መንግሥት በመደበው ፈንድ እየተጠቀማችሁ ነው?

አቶ ኦካኔ፡- የወጣት አጀንዳ የሞት ሽረት አጀንዳ ነው፡፡ በቅርቡም በተደረገው የተሃድሶ ለውጥ ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶት እየሠራንበት ነው፡፡ በከተማዋ የሚገኙትን ከ2,111 በላይ ሥራ አጥ ወጣቶች ቤት ለቤት በመሄድ መዝግበን ወደ ሥራ ገብተናል፡፡ እነዚህን ወጣቶች ወደ ሥራ ካስገባናቸው ትርፍ እናገኝበታለን፡፡ ሥራ ካልሰጠን ደግሞ ኪሳራ ነው፡፡ በከተማዋ ተመዝግበው የነበሩ ሥራ አጦችን በማኅበር በማደራጀት እስከ አራት ሚሊዮን ብር ብድር በመስጠት በኮብልስቶንና በተለያዩ መስኮች ሥራ ላይ እንዲሰማሩ አድርገናል፡፡ ከአራት ሺሕ በላይ የሚሆኑ ወጣት አባወራዎች በከተሞች የምግብ ዋስትና ተጠቃሚ ናቸው፡፡ ክልሉም በመደበው በጀት ሥራ እየተሠራ ይገኛል፡፡ ከተማዋ ሥራ ፈልገህ የምታጣባት አይደለችም፡፡ ምናልባት አሁን የሚታየው የሥራ ማማረጥ ካልሆነ በስተቀር ሥራ አጥ አለ ለማለት ያስቸግረኛል፡፡

ሪፖርተር፡- ከተማዋ የጎርፍ ተጠቂ እንደሆነች ይታወቃል፡፡ አምና የተከሰተው ጎርፍ የሰው ሕይወት እስከመንጠቅ ደርሷል፡፡ ዘንድሮስ ይህን ለመቀነስ ምን ሠርታችኋል?

አቶ ኦካኔ፡- ከተማዋን የሚያጠቃት ጎርፍ በሁለት ይከፈላል፡፡ አንደኛው ቀድሞ የጎርፍ መውረጃ የነበሩ ቦታዎች ላይ ሰዎች ግንባታ ማካሄዳቸው፣ ሁለተኛው ደግሞ ቀድሞ የተሠሩ የፍሳሽ ቱቦዎች በመዘጋታቸውና ውኃው መንገዱን ለቆ በመውጣቱ በከተማዋ ላይ ጉዳት አድርሷል፡፡ ከዚህም ችግር በመነሳት በተለይ በባሮ ወንዝ ዳርና ዳር ሕገወጥ ግንባታ ሠርተው ለአደጋ ተጋላጭ የነበሩ ከ400 በላይ እማወራዎችና አባወራዎችን በማንሳት ወደ ሌላ ሥፍራ አስፍረናል፡፡ የከተማው አስተዳደርም ከአራት ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ የተዘጉ ቱቦዎችን ከመክፈት ጀምሮ አዳዲስ የጎርፍ መውረጃ ቱቦዎችን እየሠራ ይገኛል፡፡ ሌላው ማኅበረሰቡ ወንዝ ዳር ግንባታዎችን እንዳያካሂድ ቁጥጥር በማድረጋችንና ቆሻሻዎችን በአግባቡ እንዲጥል ትምህርት እየተሰጠ በመሆኑ በዘንድሮ ችግሩ ይቃለላል ብለን እንጠብቃለን፡፡

ሪፖርተር፡- የባሮ ወንዝ ብክለቱ እየጨመረ እንደሚገኝ ይነገራል፡፡ መንስዔው ምንድነው?

አቶ ኦካኔ፡- ባሮ ወራጅ ወንዝ ስለሆነ በባህሪው ሊበከል አይችልም፡፡ ተበከሉ የሚባሉት መጋቢዎቹ ናቸው፡፡ በከተማዋ ካሉ አምስቱም ቀበሌዎች ባሮን የሚቀላቀሉ ወንዞች አሉ፡፡ በተለይ ከአራት ኪሎ ሜትር አካባቢ የሚመጣው ጀጀባ ወንዝ የሚባል አለ፡፡ ይህ ወንዝ ሰዎች በብዛት የሚኖሩበት በመሆኑ፣ የሞቱ እንስሳት ከመኪና ማጠቢያዎች የሚወጣው ዘይት፣ ቆሻሻና ሌሎች በርካታ በካይ ነገሮችን ይዞ ባሮን ይቀላቀላል፡፡ ባሮ ለሰውና ለከብቶች መጠጥ ይውል የነበረ ቢሆንም አሁን ከባድ ሆኗል፡፡ ችግሩን ለመቅረፍ ከአካባቢ ጥበቃና ከከተማ ግብርና ቢሮዎች ጋር በመተባበር ባሮን በሚመግቡት ወንዞች ላይ ጉዳት የሚያደርሱትን ችግሮች ማስወገድ በመሆኑ ከነዋሪዎቹ ጋር እየሠራንበት ይገኛል፡፡ ከከተማ ግብርና ቢሮ ጋር በመሆን ደግሞ የከተማ ግብርናን ለወጣት የሥራ ዕድል ፈጠራ በማዋል በወንዞቹ ዳርቻ የመስኖ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማድረግ ሠፋሪዎች በተነሱበት ቦታ ደግሞ ችግኞችን በመትከል ችግሩን ለመቀነስ እየተሠራ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በከተማዋ እየጨመረ በመጣው የቤት ኪራይ ክፍያ ነዋሪዎች እየተማረሩ ይገኛሉ፡፡ ይህን ችግር ለመቅረፍ ምን እየሠራችሁ ነው?

አቶ ኦካኔ፡- በእኛ በኩል ለጊዜው ቤት የመሥራት ፕሮግራም የለም፡፡ ነዋሪዎች እየኖሩበት ያለው መኖሪያ ቤት ደረጃውን የጠበቀ አይደለም፡፡ እነዚህ ሰዎች ግን በማኅበር ተደራጅተው ቢመጡ መሬት እናቀርባለን፡፡ ሌላው ከተማዋ እንደ ዕድል ሆኖ ለመኖሪያ ምቹ የሚያደርጋት በርካታ ነገሮች አሉ፡፡ አንደኛው ከተማዋን ለሁለት የሚከፍለው ባሮ ወንዝ ነው፡፡ ይህ በራሱ ውበት ነው፡፡ ባደጉት አገሮች እንደምናየው የጀልባ ትራንስፖርትና ሌሎች መዝናኛዎችን የአካባቢውን ሥነ ምኅዳር በመጠበቅ መሥራት ይቻላል፡፡ ያለንን ምቹነት በማስተዋወቅ የሪል ስቴት አልሚዎች እንዲገቡ በማድረግ ችግሩ እንዲቀረፍ እኛም የጀመርነው ሥራ አለ፡፡ እዚህ ላይ የግል ባለሀብቶች እንዲሳተፉበት እያበረታታን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በጋምቤላ የፀጥታ ጉዳይ ሥጋት መሆኑን ነዋሪዎች ይገልጻሉ፡፡ ችግሩ ምንድነው?        

አቶ ኦካኔ፡- ጋምቤላ የድሮዋ ከተማ አይደለችም፡፡ ከቀን ቀን እየጨመረ የመጣ የከተማ ነዋሪዎች ብዛት አለ፡፡ ይህም ችግሮች ይዞ ይመጣል፡፡ ችግሩ በሁለት መንገድ የነበረ ነው፡፡ ከጥልቅ ተሃድሶው በፊት የነበረው አንድ ሰው ሲጣላ ችግሩን ከብሔር ጋር በመውሰድ ብሔር ለብሔር እንዲጋጭ ማድረግ አመራሩ ጭምር የሚሳተፍበት ነበር፡፡ ከተሃድሶው በኋላ ግን አንድ  ሰው ከሌላ ጋር ቢጋጭ ተጠያቂው ሰውየው ብቻ እንዲሆን በመደረጉ ይህ አሁን ተቀርፏል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ከተሞች ሲስፋፉ አብሮ የሚመጣው የመዝናኛ ቦታዎች መስፋፋት ነው፡፡ በዚህ የሚደረጉ ፀቦች፣ የመንገዶች ጉራንጉር መሆን፣ የውስጥ ለውስጥ መብራት ባለመኖሩ ጨለማን ተገን በማድረግ ዘረፋ ማካሄድ፣ ሞባይል መንጠቅና  ሌሎች ችግሮች ይታዩ ነበር፡፡ እነዚህ በተደራጀ መልኩ ሳይሆን ዕለታዊ ነበሩ፡፡ ችግሮቹ ላይ ኅብረተሰቡን በማወያየትና መፍትሔዎችም ራሱ ኅብረተሰቡ እንዲሆን በማድረግ፣ የከተማ አስተዳደር ደግሞ የውስጥ ለውስጥ መብራቶችን በማስተካከል ከአጎራባቻችን ኦሮሚያ ክልል ጋርም በመተባበር ችግሮችን መፍትሔ በማስቀመጥ ችግሩ ቀንሷል፡፡

ሪፖርተር፡- ከጎረቤት ደቡብ ሱዳን ከ345 ሺሕ በላይ ስደተኞች በክልሉ ተጠልለው ይገኛሉ፡፡ ይህ በከተማዋ ላይ ጫና አልፈጠረም?

አቶ ኦካኔ፡- ስደተኞች በከተማዋ ስለማይኖሩ ይህ ጥያቄ በእርግጥ እኛን አይመለከትም፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ከተማዋ ተጠቃሚ ነኝ ነው የምትለው፡፡ በአጎራባች ወረዳዎች አኝዋ፣ ጃዊ፣ ያሉ አሉ፡፡ እነዚህ ስደተኞች በታሪክ አጋጣሚ በብሔር ደረጃ በከተማዋ የሚኖሩ፣ በዜግነት ደረጃ ደግሞ የደቡብ ሱዳን ስደተኛ በመሆን የተሰደዱ ናቸው፡፡ ባህላችንና አኗኗራችን አንድ በመሆኑ ምንም ዓይነት የባህል መበረዝ አይመጣም፡፡ ምግባችንም አንድ ነው፡፡ ለከተማዋ ትልቅ አጋጣሚም ናቸው፡፡ እነዚህ ስደተኞች በተቀመጡበት ቦታ ኑሮአቸውን ለማሻሻል አንዳንድ ሥራ ይሠራሉ፡፡ ለምሳሌ ምግብ ቤት ከፍተው በብዛት ይሠራሉ፡፡ ለእነዚህ ደግሞ ሸቀጥ የሚቀርበው ከከተማ ነው፡፡ በተፈቀደላቸው ጊዜና ሰዓት ከተማዋ ውስጥ መጥተውም ተዝናንተው፣ አልባሳት ሸምተው ይመለሳሉ፡፡ ይህም ከተማ ያሉትን እየጠቀመ ነው፡፡ ፀጥታን በተመለከተ ግንኙነታችን ቤተሰባዊ ነው፡፡ እንደነገርኩህ አብዛኛው ነገሮቻችን ይመሳሰላሉ፡፡ ወደ ከተማ ምን ያህል ሰው እንደመጣ ስለሚታወቅና የሚመጣበትም ሰዓት ውስን በመሆኑ በእነሱ ምክንያት የፀጥታ ችግር አይታይም፡፡ በአጠቃላይ በእነሱ ተጠቃሚ ነን እንጂ ጫና አልተፈጠረብንም፡፡

ሪፖርተር፡- በቀጣይነት ምን መሥራት አስባችኋል?

አቶ ኦካኔ፡- ጋምቤላ ሥራ እየተጀመረባት ያለች ከተማ ነች፡፡ በሁሉም መስክ ገና ጅማሮው ነው ያለው፡፡ በርካታ ሥራዎች ይጠበቁብናል፡፡ እንደ ቅድሚያ የሰጠነው ማስተር ፕላን በማዘጋጀት ከተማዋን ከተማ አድርጎ ለማስጀመር ነው፡፡ ከፍተኛ የመንገድ ችግር አለ፡፡ በሚቀጥሉት ጊዜያት ሰፋፊ መንገዶች ለመገንባት አቅደናል፡፡ አረንጓዴ ልማትን ማስቀጠልም ሌላው ሥራ ነው፡፡ ጋምቤላ እንደሚታየው አረንጓዴ ነች፡፡ በርካታ ወንዞች ያሉባትም ነች፡፡ ስለዚህ ከአካባቢ ብክለት ነፃ ሆና የምታድግበትንም እየሠራን ነው፡፡