Skip to main content
x

‹‹ተኩስ አለያ ስሜን መልስ!››

 

በአነስተኛ ነጋዴዎች ወይም በደረጃ ‹‹ሐ›› ግብር ከፋዮች ላይ የተጣለው የቀን ገቢ ግምት ላይ የሚታየው ብዥታ አሁንም ድረስ የጠራ መስመር አልያዘም፡፡ ያልተገባ ግምት ተጣለብኝ በሚሉ የንግዱ ኅብረተሰብ አባላትና በግብር ሰብሳቢው ተቋም መካከል  ያለው እሰጥ አገባ አላቆመም፡፡ እርግጥ ግብር በዛብን፣ የተጣለብን ገቢ ግምት አግባብ አይደለም በማለት ካመለከቱት ውስጥ ጥያቄያቸው ተቀባይነት አግኝቶ የግብር መጠን ያስቀነሱ እንዳሉም ተሰምቷል፡፡

ሌሎች ነጋዴዎች ደግሞ ባቀረቡት የግብር በዛብን አቤቱታ መሠረት የተደረገላቸው ማስተካከያ እዚህ ግባ የማይባል፣ በመቶና ሃምሳ ብር ደረጃ የተወሰነ እንደሆነ በመግለጽ፤ አሁንም አርኪ ምላሽ እንዳላገኙ ሲናገሩ ይደመጣሉ፡፡ እንዲህ የሚናገሩት ነጋዴዎች ‹ቅሬታችሁን ይዛችሁ ወደ ላይኛው አካል አቤት ማለት ትችላላችሁ› እየተባሉ እንደሚመለሱም ይገልጻሉ፡፡ ቅሬታ ቢያቀርቡም የተጣለባቸው ግብር የፀናባቸው እንዳሉም የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን አስታውቋል፡፡ እንዲህ ባለው ሒደት የገቢ ግብር ትመናው ላይ የሚታዩ ጉራማይሌ አሠራሮች ጉዳዩን አንዛዝተውታል ማለት ይቻላል፡፡

በሺዎች የሚቆጠሩ ነጋዴዎች አቤት ያሉበት የቀን ገቢ ግምት ላይ የተመሠረተው የግብር ጥያቄ፣ ከአዲስ አበባ ጀምሮ በየክልል ከተሞችም አሠራሩ እየተቀዳ መዳረሱም ልብ ሊባል ይገባል፡፡ ጠብ ሲያስነሳ መታየቱም የጉዳዩን ክብደት ያሳያል፡፡ የንግዱ ኅብረተሰብ ጩኸት ከአቅጣጫው ሲነሳ፣ ነገሩን ረጋ ብሎ በመፈተሽ መፍትሔ ሊገኝ የሚችልበትን መንገድ በጥንቃቄ መመልከት እንደሚገባ አመላካች ነው፡፡       የግብር ጥያቄው አነሰ ወይም በዛ የሚለው ነጥብ ላይ የገለልተኛ ወገን ጥናትና ስሌት ቢደመጥ፣ የግብር ትንተና የሚሰጡ ተቋማት ቢኖሩ ምንኛ በጠቀመ ነበር፡፡ ለጊዜ የግብር መጠኑ ማነስና መብዛቱን ከመተቸት እንቆጠብና በሚነሱት ጥያቄዎች ላይ የመፍትሔ አፈላላጊነት ሚና በሚኖራቸው አካላት ላይ እናተኩር፡፡

እንዲህ ያሉ የነጋዴው ጥያቄዎች ሲነሱ፣ ነገሩን በቅርብ ተከታትለው መፍትሔ ለማመላከት መጣጣር ከሚጠበቅባቸው ተቋማት መካከል የንግዱን ኅብረተሰብ የሚወክሉት ዋነኞቹ ይሆናሉ፡፡ የንግድ ኅብረተሰቡን ለጥያቄ የሚያነሳሳው ጉዳይ ሲከሰት፣ የጠራና የተደራጀ መረጃ እንዲኖረው የማድረግ፣ ተደራጅቶ ሐሳቡን እንዲያቀርብና እንዲያሰማ የማድረግ ኃላፊነት ካለባቸው አካላት ውስጥ በነጋዴው ስም የተሰባሰቡና የተቋቋሙ የንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች በመጀመርያው ረድፍ ይሰለፋሉ፡፡

የንግድ ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች ሲመሠረቱ፣ የንግዱን ኅብረተሰብ መብትና ጥቅም ማስጠበቅ ቀዳሚ ዓላማቸው እንደሆነ በምሥረታ ሰነዳቸው ውስጥ አስፍረዋል፡፡ በሁሉም ንግድ ምክር ቤቶች መመሥረቻ ጽሑፍ ውስጥ በንግዱ ኅብረተሰብና በመንግሥት መካከል ድልድይ ሆነው ያገለግላሉ የሚለው አንቀጽ በጉልህ ይነበባል፡፡ ስለ ንግድ ምክር ቤቶች ዓላማ በየመድረኩ ሲገለጽ የምንሰማውም ይኼንኑ ነው፡፡ ለነጋዴው ጥቅምና መብት መከበር እንተጋለን ይላሉ፡፡ የንግዱን ኅብረተሰብ ላይ ጫና የሚፈጥር ጉዳይ ሲፈጠር የተደራጀ መረጃ ይዞ፣ ጥናት ላይ የተመሠረተ ማስረጃ አጣቅሶ በመቅረብ ከመንግሥት ጋር በምክክርም ሆነ በክርክር መፍትሔ ማምጣትና እንዲመጣ ማድረግ፣ መንግሥት ተሳስቶም ከሆነ እንዲስተካከል ጫና የማድረግ ተግባር የሥራ ድርሻቸው ነው፡፡

ከሰሞኑ የቀን ገቢ ግምትን መሠረት ካደረገው የግብር ጥያቄ አኳያ፣ የአገሪቱ ንግድ ምክር ቤቶች ሚና ቢመዘን፣ የሥራቸው ውጤት ባዶ ሊሆን ይችላል፡፡ ነጋዴው ግብር በዛብኝ እያሉ ሲጮህ በስሙ የተቋቋሙት ንግድ ምክር ቤቶች ድምፃቸው መጥፋቱ ትዝብት ላይ ይጥላቸዋል፡፡ እየጮሁ ከሚገኙት ነጋዴዎች መካከል በንግድ ምክር ቤቶቹ ውስጥ በአባልነት የተመዘገቡ እንደሚኖሩበት አይጠረጠርም፡፡ አባሎቻቸውም ባይሆኑ የንግድ መስኩን የሚመለከት ጉዳይ ሲያነታርክ በር ዘግቶ መቀመጥ ያስተቻል፡፡

ይህም ቢቀር ለአባሎቻቸው ሲሉ ጉዳዩን በመፈተሽ መፍትሔ ለመሻት ስለመሞከራቸው አለመስማታችን ምን እየሠሩ ነው ያሰኛል፡፡ አለያ ግን  ቀድሞውንስ መች ለንግዱ ኅብረተሰብ ጥብቅና ቆሙና? የሚል ትዝብት ውስጥ ስለሚጥላቸው ሁኔታው ራሳቸውን እንዲፈትሹ የሚያስገድዳቸው ነው፡፡ በእርግጥ አብዛኞቹ የንግድ ምክር ቤቶች አቅምና ብቃት እንዲህ ላለው ጉዳይ በመነሳት መንግሥትን የሚሞግቱበትን አቋም እንዳጡ የሚያሳዩ አጋጣሚዎችን አሳልፈዋል፡፡ ይህ ሲባልም መንግሥት ተቋማቱን የማግለል ሥራ አልሠራም ብሎ አለመናገርም ሞኝነት ነው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የንግድ ምክር ቤቶች ከመንግሥት ጋር ባላቸው የግንኙነት ሒደት እንዲህ ያሉ መድረኮች እየደበዘዙ እንደመጡ መታዘብ ይቻላል፡፡ እንደቀደመው ጊዜ መንግሥት ነጋዴውን ለሚወክሉ ተቋማት መድረኩን ሲሰጥ፣ ራሱን ለትችትና ለክርክር ሲያዘጋጅ ማየት ብርቅ እየሆነ መጥቷል፡፡

ይህም ሆኖ ከሰሞኑ አቧራ ያስነሳው የቀን ገቢ ግምት ላይ የተመሠረተው የግብር ጥያቄ ጉዳይ ንግድ ምክር ቤቶቹ ያለቀስቃሽ ነገሩን እንዲመለከቱት የሚጋብዛቸው ይመስለናል፡፡ የንግዱ ኅብረተሰብ ጥያቄ ምንድነው ብለው በመነሳት ጉዳዩን መገምገም በተገባቸው ነበር፡፡

የንግድ ምክር ቤቶቹን የአመራር ቦታ ለመቆናጠጥ የሚያሳዩትን ትጋት፣ በስሙ ለሚጠሩበት፣ ድምፁን እያሰማ ላለው ነጋዴ ጥያቄዎች ምላሽ ለማስገኘት ጥረት ማድረጋቸውን እስካላሳዩ ድረስ፣ ኃላፊነታቸውን ተወጥተዋል ብሎ ለመናገር አይቻልም፡፡

በመሠረቱ የንግድ ምክር ቤቶቹ በግምት የተጣለው ግብር ስለበዛ መንግሥት ይቀንስ ብለው እንዲያስተጋቡ አይጠበቅም፡፡ ነገር ግን ችግሩን ፈትሾ፣ ጉድለቱና ስህተቱ የቱ ጋ እንዳለ በመመርመር መፍትሔ ማመላከት ይጠበቅባቸው ነበር፡፡ ይኼንን ኃላፊነታቸውን ስላልተወጡ ነው የሚወቀሱት፡፡ ጉዳዩን በማስጠናት በቂ መረጃ ይዘው ሊያስማማ የሚችል መፍትሔ ከማምጣት መስነፍ አልነበረባቸውም፡፡ ተመኑ ተገቢ ሆኖ ከተገኘም ችግሩ የነጋዴው ከሆነም ይህንኑ ለማስረዳት መጣጣር ነበረባቸው፡፡

አሁንም ቢሆን ለሁሉም ወገን ሲባል የቀን ገቢ ግምቱን የተመለከቱ ጥናቶች ተካሂደው ለከርሞም ችግር እንዳይፈጠር፣ የተፈጠረውም እንዳይባባስ ከምክር ቤቶቹ ብዙ ይጠበቃል፡፡ ንግድ ምክር ቤቶች ከተኙበት ይንቁ፡፡ ኃላፊነታቸውንም ይወጡ፡፡ አለያ ግን ናፖሊዎን ቦናፓርት ከጦር ሜዳ ሲሸሽ ያገኘው ሞክሼውን የተናገረው ነገር ለእነሱም ሊጠቀስባቸው ይችላል፡፡ ንጉሡ የሚሸሸውን ወታደር ወደ ጦር ሜዳው ተመልሶ እንዲዋጋ በማሳሰብ፣ ‹‹ተኩስ አለያ ስሜን መልስ›› እንዳለው ሁሉ ንግድ ምክር ቤቶቹም ስለነጋዴው ችግሮች የሚጠበቅባቸውን በአግባቡ ይሥሩ አለያ ግን ነጋዴውን በመወከል በየአገሩ እየዞሩ አበል ሲበሉ መኖር ከንቱነት መሆኑን ይረዱ፡፡