Skip to main content
x
‹‹እሳቸው አልሞቱም››

‹‹እሳቸው አልሞቱም››

እናንተ ልጆች…አትጋፉ እስኪ…! በሩን ልትገነጥሉት ነው እንዴ?

እትዬ ጥሩወርቅ ሁሌ ደጇ ላይ ተሰብስበን በባለሁለት ተካፋች በሯ መሃል መላጣ ጭንቅላቶቻችንን ወደቤት ለማስገባት ስንንጠራራ ትቆጣናለች፤ የቤቷ ምንጣፍ በባዶ እግር ነው የሚረገጠው፤ ከቤት ውስጥ የሚወጣው ደስስ የሚል ሽታ አሁን ድረስ አፍንጫዬ ውስጥ አለ፤..ቤቷ ውስጥ ደግሞ ሌላ ቦታ የማይገኝ ውድ ነገር አለ...እሱን ፍለጋ ነው የምንመጣባት፡፡

በሯ ላይ የምንሰበሰበው የሠፈር ልጆች ደግሞ ስንራገጥ ውለን ስለምንመጣ ‘ጋዴ’ በሚባለው መጫሚያችን ውስጥ አፈትልከው የሚታዩት ጣቶቻችን ውስጣ ውስጥ ጭምር ጭቃና አፈር አይጠፋም፤ ስንንፏቀቅበት ቂጥና ጉልበቱ የተቀዳደደና የተጣጣፈ ሱሪያችን ለዚያ ባለምንጣፍ ቤት አይመጥንም፡፡

እግሮቻችን የያዙት ቆሻሻም ወደዚያ ቤት የመግባት ፈቃድ አያሰጥም ...ሁሌ በቁጣ ብታባርረንም አትጨክንብንም፤ ከገበያ ስትመጣ ዘንቢሏን ተሽቀዳድመን እየተቀበልን እናግዛታለን...ወደ ሱቅ ሰው ለመላክ ሳትጣራ በፊት ገና ብቅ ስትል፣ አንዳችን በአንዳችን ላይ እየተገፋፋንና እየወዳደቅን ሁሉ ልንላካት እንሟሟታለን፤...ስማችንን ስለማታውቀው ሁላችንንም ልጆች ብላ ነው የምትጠራን፤

ከጊዜያት በኋላ እትዬ አንድ ሕግ አወጣች፡፡

እሷ መጥቶ በራፏ ላይ ለማጮለቅ የሚችለው ልጅ፣ እግሩን የታጠበና ፊቱ ላይ ንፍጥ የሌለው፣ እንዲሁም የማይለፈልፍና ጮክ ብሎ የማይስቅ ልጅ ብቻ ነው፡፡…ከዚያ በሩ ይከፈታል..በረንዳ ላይ ተቀምጠን በፀጥታ እናያለን፣ የማይረሳ ትዝታ እንሰንቃለን፡፡

በዘመናችን እንደዚህ ሕግ ያከበርነውና ሳናሠልስ በተግባር የተረጎምነው ሕግ የለም…፤

የቤተሰቦቻችንን ትዕዛዝም ቢሆን እንዲህ ጎሽ ብለን ተቀብለን አናውቅም፡፡

በቃ እትዬ ጥሩወርቅ በራፍ ላይ የምንሰበሰበው ባለጥቁርና ነጭ ቴሌቪዥኗን ለማየት ነው፡፡ በሳምንት አንድ ቀን ብቻ …አባባ ተስፋዬን ለማየት ብቻ…አባባ ተስፋዬን ሳናይ ከሚያልፈን ብንሞት ሁሉ ይሻለን ነበር…ምንም ትበለን ምንም ታድርገን እትዬ ጥሩወርቅ ንግሥታችን ናት…ገዢያችን ናት…እሷ ከተጣላችን “ደህና ናችሁ ልጆች? እንደምን ናችሁ ልጆች? የዛሬ አበባዎች የነገ ፍሬዎች…”

የሚለው የአባባ ተስፋዬ ቃል ያመልጠናል፤…እሱ ሳያመልጠን ኖርን…ዛሬ አባባ ተስፋዬ አሳድገውን ኖረው በሞት አመለጡን…ከትዝታቸው በቀር ዳግም በአካል አናያቸውም!

ነፍስዎትን በገነት ያኑር የልጅነታችን አስታዋሽ…መካሪያችን…፤

በርስዎ የተሠራው ትውልድ ስንት ቁምነገር እንደሠራ ቆመው አይተዋልና ...የሞቱት ለቁምነገር ኖረው ነውና አይቆጨንም....ሁሌም በሁሉም፣ በሁላችንም ውስጥ አሉ!

አባባ ተስፋዬ አልሞቱም!!

  • መላኩ ብርሃኑ በፌስቡክ ገጹ ያሠፈረው      
  • ***

ሞትን መጠበቁ ስለተሳነኝ

ሞትን መጠበቅ ስለተሳነኝ፤

በበጎ ፈቃዱ ቆሞ ጠበቀኝ፤

ሠረገላውም ላይ የተሳፈርነው

ከኛ በቀር ሌላ አልሞት ባይነት ነው፡፡

ዝግ ብለን ነዳን፤ ጥድፊያ የሚሏትን አያውቃት ፈጽሞ፤

እኔም ሥራዬን ተውኩ ዘረገፍኩት ደግሞ

ኧረ ከናካቴው የዕረፍት ጊዜዬንም፤

ትሁት ስለሆነ ተውኩለት ሁሉንም፡፡

አልፈነውም ሄድን ትምህርት ቤቱንም፤ ልጆች ሲጫወቱ፤

ሳያገባድዱ ጥናት ሳይጨርሱ፤

ማሳዎቹን አልፈን እህል የሞላውን፤

እንዲሁም አለፍነው ጠላቂ ጅምበርን፡፡

እንዲያውም እሱ ነው አልፎን የሄደው፤

ያም ጤዛ ሲንዛዛ እያሽቆጠቆጠ ብርዱን ሲያወርደው

ቀሚሴ የሳሳ የሸረሪት ድር፤

ሸማዬም ዓይነርግብ ሻሽ ስለነበር፡፡

አንዱ ቤት ዘንድ ስንደርስ ቆም ብለን ስናየው

የምድር መጎርበጥ ነበር የሚመስለው፤

የቤት ክዳኑንም ማየት ያዳግታል፤

ጣራውም እንደሆነ ያፈር ክምር መስሏል፡፡

ከዚያም እስከዛሬ አልፏል ዘመናት፤

ሆኖም አንዷ ዘመን ስላጠረች ከለት

ለካስ መጀመሪያ ሳየው ሳስበው

የፈረሶቹ ራስ ወደዘላለም ነው ያዘነበለው፡፡

  • ከኤሚሊ ዲክንሰን፣ ስድ ትርጉም በከበደ ዳግማዊ

**

‹‹ደህና ሁኑ ልጆች›› የሚለው የማሳረጊያ ድምፅ አሸለበ

በአበው መልካም ዘይቤ ነፍስ ይማር!

በደርግ ዘመን ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ስሠራ ነው ከአባባ ተስፋዬ ጋራ የተዋወቅነው። ሰላምተኛና ሰው አክባሪ፤ ተጨዋችና ቀልደኛ እንደነበር ትዝ ይለኛል። ለዛ ካለው ቀልዱ መካከል፤ በአንድ ወቅት ዕድሜውን በፔርሶኔል ሲጠየቅ በማሳነሱ ‹‹ምነው አባባ ተስፋዬ? ኧረ እርግጡን ይናገሩ!›› ሲባል፤ ‹‹አውላቸው ደጀኔ ከፊቴ ተገትሮ እንዴት ልለፍበት›› ብሎ አቶ አውላቸውም ዕድሜውን ቀንሶ መናገሩን በዘዴ አጋልጧል ሲባል ሰምቻለሁ። ሁለቱም ለቴአትር ሙያ ባለውለታዎች ናቸው!

የቴአትር ቤት አካባቢ ጨዋታና ቀልድ ሲነሳ ትዝ ከሚለኝ አንዱ ‹‹የጭራ ቀረሽ›› /ዘነበች/ እና የኢዮኤል ዮሐንስ  ነው! እንደ አባባ ተስፋዬ ጭራ ቀረሽም ዕድሜዋን አሳንሳ ‹‹20 ዓመቴ ነው!›› በማለቷ፤ አለቃዋ የሀገር ፍቅር ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ኢዮኤል ዮሐንስ እንዲመሰክር ፔርሶኔሉ ይጠይቀዋል።

‹‹ዕድሜዋን በትክክል አላውቅም! ግን አብረን ስንሠራ 30 ዓመት ሆኖናል!›› ብሎ  እርፍ! ከዚህ በተረፈ እነጌታቸው አብዲ፣ ዓለምፀሐይ ወዳጆ፣ ታማኝ በየነና ሌሎቹም የፈገግታ ቀልዶች ቢያጫውቱን አይከፋም!

  • አሰፋ ገብረማርያም ተሰማ (የቀድሞው የኢትዮጵያ ሕዝብ መዝሙር ደራሲ)