Skip to main content
x

‹‹እንዳያማህ ጥራው እንዳይበላ ግፋው›› የመሰለው የ40/60 ነገር

  ባለፈው ሳምንት ትኩረቴን ከሳቡ ዘገባዎች አንዱ የ40/60 ኮንዶሚኒየም ቤቶች ፕሮጀክትን በማስመልከት የሚመለከታቸው ኃላፊዎች የሰጧቸው መግለጫዎች ይገኙበታል፡፡

      የ40/60 ኮንዶሚኒየም የቤቶች ፕሮጀክት ተግባራዊ ከሆነበት ከ2006 ዓ.ም. ወዲህ ሲነገሩን ከነበሩ መረጃዎች አንፃር፣ ሰሞኑን የሰማናቸው መረጃዎች የ40/60 ቤቶች ፕሮጀክት ብዙ የተምታቱ ነገሮች እንደነበሩበት አመላካች ሆነውብኛል፡፡ ፕሮጀክቱን በተመለከተ ሲነገር እንደነበረው፣ ከሌሎች የኮንዶሚኒየም ቤቶች ግንባታ በተሻለ ጥራትና አፈጻጸም እንደሚተገበር ነበር የሰማነው፡፡

በዚህ ፕሮግራም የሚታቀፉ ዜጎችም የዕድሉ ተጠቃሚ ለመሆን በማሰብ ቤቶቹ የተተመነላቸውን ዋጋ መቶ በመቶ ቀድመው ለመክፈል ከተሽቀዳደሙበት ምክንያቶች መካከል ስለፕሮጀክቱ ሲቀርቡ የነበሩ አማላይ ማብራሪያዎች ዋነኞቹ ናቸው ማለት ይቻላል፡፡

      በተመረጡ የከተማው አካባቢዎች ግንባታቸው በ18 ወራት ተጠናቀው ለቤት ባለቤቶች እንደሚተላለፉ በአደባባይ ሲነገር ከርሞ ነበር፡፡ ከሰሞኑ ግን የከተማው አስተዳደር ቤቶች ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ኃላፊዎች የሰማነው ግን ለግንባታው የተሰጠው ጊዜ እንደማይበቃ ነው፡፡

ጊዜው አይበቃም የተባለው ቤቶቹ አልቀውና ለዕድለኞች ተላልፈው ሌላ የግንባታ ፕሮጀክት መገባደድ በነበረበት ወቅት መሆኑን ልብ እያልን፤ በተስፋ ሲጠበቁ የከረሙትንም ቤቶች በተባለው ጊዜ ማስረክብ አልተቻለም፡፡ በኮንዶሚኒየም ቤቶች የግንባታ ሒደት የታየው ዘገምተኛነት በእነዚህኞቹም ተደግሟል፡፡ ይህም አገልግሎቱን ለመስጠት ኃላፊነት በወሰደው በቤቶች ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤትና በአገልግሎቱ ተቀባይ መካከል ንፋስ እንዲገባ አድርጓል፡፡

      ጽሕፈት ቤቱ ቃሉን መጠበቅ አለመቻሉ የሚያበሳጭ ብቻ ሳይሆን ደጋግሞ የታየው የብቃት ችግር፣ ‹‹መንግሥትም በአደባባይ ቃለአባይ ከሆነ ማን ይታመናል?›› ያሰኛል፡፡ መቼስ ነው ቃል በተገባው መሠረት ነገሮችን መፈጸም የሚቻለው? በማለት  ጥያቄ እንድንጠይም ያስገድደናል፡፡ በተባለው ጊዜ ግንባታው ስላለመጠናቀቁ ሲቀርቡ የነበሩ ምክንያቶች በሙሉ ከነባራዊው እውነታ ውጭ እንደነበሩም ታይቷል፡፡

የ40/60 ቤቶች ፕሮጀክትን በተመለከተ የተሰጠውን ማብራሪያ የበለጠ በብስጭት ንፍር እንድንል የሚያደርገው፣ ግንባታዎቹን ለማጠናቀቅ ከኃላፊዎች የተሰጠው ዜንጠኛ ምክንያት ነው፡፡ ‹‹የ40/60 ቤቶችን ገንብቶ ለመጨረስ የሰጠነው የ18 ወራት ጊዜ ትክልል አልነበረም፤›› የሚለውን አስገራሚ የኃላፊዎችን አንደበት የሰማንበት አግባብ፣ እስከዛሬ ከሰማናቸው ሁሉ የተለየ ነበር፡፡

የ40/60 ቤቶች ዓይነት ዲዛይን ያላቸውን የ12 ወለል ሕንፃዎች ገንብቶ ለመጨረስ 18 ወራት አይበቃም ነበር የተባለው፣ ‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ ባለ12 ወለል ሕንፃዎች በ18 ወራት ውስጥ ተጠናቀው ስለማያውቁ ጽሕፈት ቤቱም በ18 ወራት ጊዜ ውስጥ አጠናቅቃለሁ ማለቱ ተገቢ አልነበረም፤›› በማለት ለአዲሱ ምክንያት ተጨማሪ የምክንያት ማብራሪያ ተሰጥቶበታል፡፡  

ይሁንና እንዲህ ያለው ምክንያት ፈጽሞ ተቀባይነት አይኖረውም፡፡ ምክንያቱም ጽሕፈት ቤቱ ከዚህ ቀደም በኮንዶሚኒየም ቤቶች ግንባታ የተፈጠሩ ችግሮች እንዳይደገሙ ለማድረግ ተግቼ እሠራለሁ በማለት ሲምል ሲገዘት በመቆየቱ ነው፡፡ ከዚህ ቀደሙ የተሻለ አሠራርና አፈጻጸም ይተገበራል ባለበት አንደበቱ፣ ሳይሳካለት ሲቀር ግን የእናቴ መቀነት አደናቀፈኝ ዓይነት ምክንያት መስጠቱ ቀድሞውንስ ግንባታዎቹን በትክክል መች አስቦ ገባበትና ወደሚል መደምደሚያ ይወስደናል፡፡

ተዓማኒነት ያለው መስጠት ይቻል ዘንድ የጠራ፣ በተግባር የሚተረጎም ዕቅድ ቀርፆ የመሥራት ልምድና ሥርዓት አለማዳበራችን የሚፈጥረውን ችግር ወደ ሌላ አካል የማላከክ ክፉ አመላችንን ለማስወገድ እንደማንሠራ የሚያሳይ መሆኑን ሰሞኑን የተደመጡት የመንግሥት ገለጻዎች ይነግሩናል፡፡ በጣሙን የሚያናድደው ሌላው ጉዳይ ደግሞ በትክክል ባለመታቀዱ ሰበብ የተፈጠረውን ክፍተትና ጉዳት ቤት ፈላጊው እንዲሸከመው መደረጉ ነው፡፡

የግንባታ ማጠናቀቂያ ጊዜው ካለፈ በኋላ የግንባታ ወጪ እንዲጨምር መደረጉ ይታወቃል፡፡ የግንባታ ጊዜ በተጓተተ ቁጥር የሚጠየቀው ተጨማሪ የግንባታ ወጪ  ዞሮ ዞሮ ቤት ፈላጊው ላይ ያርፋል፡፡ ቤት ለማግኘት ከመንግሥት ጋር ተዋውሎ ገንዘቡን ከከፈለ በኋላ ከተስማመበት ዋጋ በላይ ጭማሪ መክፈል አለብህ የተባለበት ምክንያትም ቀድሞውኑ በአግባቡ ካለማቀድ የሚመጣ ችግር ነው፡፡ 

የግንባታውን የሚያካሂደው አካል ሥራው በ18 ወራት ውስጥ ይጠናቀቃል ብሎ ሲነሳ፣ ውል ተቀባይ ተቋራጮችም በዚሁ አግባብ ተስማምተው ውል ፈርመዋል፡፡ ስለዚህ ችግሩ በአንድ ወገን ላይ ብቻ የተንጠለጠለ እንዳይደለ ይጠቁማል፡፡ ምክንያቱም ተቋራጮቹ የግንባታ ውሉን ሲዋዋሉ በ18 ወራት እንደማያልቅ ከተገነዘቡ፣ ይህንን አለማሳወቃቸው ስህተት ብቻ ሳይሆን፣ ነገሩ ሁሉ በጥርጣሬ እንዲታይ የሚጋብዝ ነው፡፡ ሁለቱም እምነት አጉድለዋል፡፡  ከዚህ በመለስ ብናየው እንኳ በ18 ወራት ውስጥ ለማጠናቀቅ የማያስችል አቅርቦት ቢኖርም፣ ባወጣው ያውጣው ብለው የገቡበት ሥራ ነው ያስብላል፡፡ ግንባታውን ለማከናወን ውለታ የገቡት ተቋራጮች ሙያቸው እስከሆነ ድረስ የተሰጣቸው የግንባታ ጊዜ ገደብ  እንደማያስኬዳቸው ቀድመው አልተረዱም ማለት ስለሚከብድ፣ ይህ በሆነበት ወቅት ቀድመው የማሳወቅ ሙያዊ ግዴታቸው አልነበረም ወይ? ብለን ብንጠይቅም ተገቢ ይሆናል፡፡

ስለዚህ ሁሉም ወገኖች ኃላፊነቱን መውሰድ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ከሁሉም በላይ ልንጠቅሰው የሚገባን ጉዳይ፣ የቤቶች ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት በተለያዩ ጊዜያት የ40/60 ቤቶች ግንባታ ሒደት ይህን ያህል በመቶ ደረሰ፣ ሊጠናቀቅ ይህንን ያህል ቀረው ወዘተ. ሲባል የነበረው የፕሮጀክቱ ግንባታ በ18 ወራት እንደሚጠናቀቅ ታስቦ አልነበረም ወይ? ይህም መፈተሽ አለበት፡፡ በአጠቃላይ የግንባታዎቹ መዘግየት በውለታ መሠረት ለባለቤቶቹ በወቅቱ አለማስረከብ ያስከተለው ጫና ሳያንስ፣ በሌሎች ጥፋት ቤት ገዥው ተጨማሪ ክፍያ እንዲከፍል መገደዱ አግባብ አይደለም፡፡ እንደውም ቤት ሻጩ መንግሥት፣ ቤት ፈላጊውን ሊክሰው በተገባው ነበር፡፡

ከውለታ ውጪ የግንባታ መዘግየት ያስከተለው ጉዳት ተሰልቶ ሊከፈለው ይገባ ነበር፡፡ ሙሉ ክፍያውን ፈጽሞ ከመቼ ቤቴ በገባለሁ እያለ በሚጠባበቅበት ወቅት፣ ሰበብ እየደረደሩ ቤት የማግኘት ተስፋውን ማጠውለግ ደግ አይደለም፡፡ ተጓዳኝ ወጪዎችና ጉዳቶቹም ሊታዩለት፣ የሞራል ካሳና ማካካሻ በታሰበለት ነበር፡፡ እንዲህ ያሉ እውነታዎች እያሉ ጭርስኑ ዋጋ ካልጨመርክ ቤትህን አትረከብም ማለት የመልካም መንግሥትነት መገለጫ አይደለምና መታረም አለበት፡፡ እንዲህ ቀስ በቀስ ሕዝቡ መንግሥት ላይ ያለውን እምነት የሚሸረሽሩ ስህተቶችን በአግባቡና ተቀባይነት ባላቸው ዕርምጃዎች በማስተካከል ሕዝባዊነቱን ካላሳየ፣ ‹‹እንዳያማህ ጥራው እንዳይበላ ግፋው›› የሚለው የአገራችን አባባል መገለጫው እንዳይሆን ይጠንቀቅ፡፡