Skip to main content
x
‹‹ወጣቶች ተነሱ ተብሎ የሚደረገው ነገር ለእኔ እሳት የማጥፋት አሠራር ነው››

‹‹ወጣቶች ተነሱ ተብሎ የሚደረገው ነገር ለእኔ እሳት የማጥፋት አሠራር ነው››

ዶ/ር ወልዳይ አመሐ፣ የኢኮኖሚ ባለሙያ

ዶ/ር ወልዳይ አመሐ በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚጠቀሱ የኢኮኖሚ ምሁራን መካከል አንዱ ናቸው፡፡ በኢኮኖሚ ሙያቸው ከዩኒቨርሲቲ ጀምሮ በተለያዩ ተቋማት ውስጥ ተሳትፈዋል፡፡ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ባለሙያዎች ማኅበርን በፕሬዚዳንትነት ከማገልገላቸው በተጨማሪ፣ አያሌ መጻሕፍትን አሳትመዋል፡፡ በአገር ውስጥና በዓለም አቀፍ ጆርናሎችም የኢኮኖሚ ትንታኔዎች የሰጡባቸውን በርካታ የምርምር ሥራዎች አሳትመዋል፡፡ በተለይም በአገሪቱ ማይክሮ ፋይናንስ ዘርፍ ላይ በማተኮር መሥራት ከጀመሩ ዓመታትን አስቆጥረዋል፡፡ የኢትዮጵያ አነስተኛ የፋይናንስ አቅራቢ ድርጅቶች የመሠረቱትን ማኅበር በሥራ አስፈጻሚነት የሚመሩት የኢኮኖሚክስ ምሁሩ፣ በማክሮ ኢኮኖሚ መስክ በተለይ ከሰሞኑ ለየት ያሉ አዝማሚያዎች መከሰት ጋር በተያያዘ ከሪፖርተር ጋር ባደረጉት ቆይታ ትንታኔ ሰጥተዋል፡፡ መንግሥት የሕዝብ ተቃውሞ ከተነሳበት በኋላ እየወሰዳቸው ከሚገኙ ዕርምጃዎች መካከል አንዱ ለወጣቶች ተዘዋዋሪ ፈንድ በማለት ያቀረበው የአሥር ቢሊዮን ብር ፈንድ ይጠቀሳል፡፡ ይህ ፈንድ በአገሪቱ ይፋ ሲደረግ በማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ላይ ደቅኖት ስለነበረው ሥጋትና አስፈጻሚዎች ሳይቀሩ ስለነበራቸው የግንዛቤ ችግር አብራርተዋል፡፡ በክልል መንግሥታት ከሰሞኑ ይፋ የተደረጉ የኩባንያ ምሥረታ እንቅስቃሴዎች በግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ ላይ ስለሚያሳድሩት ጫና ተጠይቀው ገለጻ አድርገዋል፡፡ መንግሥት የአገሪቱን የወደፊት ልማት ዘላቂ ለማድረግ ካስለፈገው የግሉ ዘርፍ እንዲያድግ መሥራት አለበት ያሉት ዶ/ር ወልዳይ፣ ለወጣቶች የቀረበውን ፈንድ ጨምሮ ከሰሞኑ የታዩትን እንቅስቃሴዎች ‹‹እሳት ማጥፊያ›› በማለት ገልጸዋቸዋል፡፡ በማክሮ ኢኮኖሚያዊ ችግሮችና መፍትሔዎቻቸው ላይ በማተኮር ብርሃኑ ፈቃደ ከዶ/ር ወልዳይ አመሐ ጋር ያደረገው ቃለ ምልልስ እንዲህ ተጠናቅሯል፡፡

ሪፖርተርየአንድ መንግሥት ተልዕኮ ከሆኑ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች መካከል የተረጋጋ ማክሮ ኢኮኖሚ እንዲኖር ማድረግ ዋናው ነው። መንግሥት በዚህ አኳኋን መወጣት ከሚጠበቅበት ሥራዎች መካከል ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል እንዲኖር ማድረግ ነው። የሥራ ዕድሎችን በመፍጠር ሥራ አጥነትን መቀነስ ሌላው የማክሮ ኢኮኖሚ ተልዕኮው ነው። የዋጋ ግሽበትን መከላከልና የመሳሰሉትም ይጠቀሳሉ። መንግሥት በፍትሐዊ የሀብት ክፍፍልና በሥራ አጥ ቅነሳ በኩል ስላከናወናቸው ሥራዎች የእርስዎ ምልከታ ምንድነው?

ዶ/ር ወልዳይ:- እኔ ወደ መሠረታዊ ጉዳዮች አዘነብላለሁ፡፡ መንግሥት ለህልውናው ሲል ወይም ለታይታ በማለት ሊሠራቸው የሚችላቸው ነገሮች ይኖራሉ። በአገሪቱ የሚታየውን የውጭ ምንዛሪ እጥረት በቀላሉ ለመቅረፍ የስኳር አቅርቦት ችግርን በመፍታት ማንበሽበሽ ይቻል ይሆናል። አገሩን ስኳር በስኳር ማድረግ እንዳለ ሆኖ ሚዛናዊነቱን መጠበቅ ግን ተገቢ ነው። ሥራ ፈጠራው አምራች ወይም ምርታማነትን መሠረት ያደረገ መሆን አለበት። ምርታማነትን ካላመጣ ግን ችግር ይኖረዋል። ለጊዜው ለችግር ማስተንፈሻ ሊፈጠሩ፣ ሊሠሩ የሚችሉ ነገሮች ይኖራሉ። እነዚህን ወጣቶች ተቀብላችሁ ቅጠሯቸው፣ ሥራ ስጧቸው የሚባል አሠራር ሊመጣ ይችላል። ነገር ግን ለኢኮኖሚ ዕድገት መሠረታውያን የሆኑ ነገሮች መምጣት አለባቸው። ኬኩ ሳይኖር  ሥርጭቱን እንዴት መዳረስ እንዳለበት ማውራቱ ዋጋ የለውም። ይህም ቢሆን ይቅር፣ አይደረግ ማለትም አይደለም። ሚዛኑን መጠበቅ ግን ይኖርበታል። ቅድሚያ የሚሰጣቸው ጉዳዮችም መታየት አለባቸው። ለእኔ የሚቀጥሉት አሥርት ዓመታት ጥሩ ነገር የሚታይባቸው ጊዜያት ይመስሉኛል። ለምንድነው? ከተባለ አሁን ላይ ወገብ የሚያጎብጡ የመሠረት ማውጣት ሥራዎችን እየሠራን ስለሆነ ነው። መሠረቱ ምንድነው? ለዕድገት መሠረት የሆኑ ግብዓቶችስ አሉ ወይ? ለእንዲህ ያለው ጥያቄ ምላሽ ለማግኘት የመንግሥትን ፖሊሲ መቃኘት ያስፈልጋል። ፖሊሲው ሲቃኝ በመዋቅራዊ ለውጥ ላይ ያተኮረ፣ ስትራክቸራሊስት አካሄድ የሚከተል ሥርዓት እየሆነ መምጣቱን ታያለህ። ኢንዱስትሪ መገንባት አለብኝ ይላል። ኢንዱስትሪ መገንባት አዲስ ነገር አይደለም። ጥያቄው ግን ኢንዱስትሪ እንዴት ይገነባል? የሚለው ነው። ካለህ የሀብት ክምችት ጋር የሚሄድ ሥራ እየሠራህ ነው ወይ? ከአቅምህ ጋር የሚጣጣም ነገር እየሠራህ ነው ወይ? የሚለውን እያየን መሄድ አለብን።

መዋቅራዊ ለውጥ የማምጣት ንድፈ ሐሳብ ድሮም ኩዝኔት በተባለ የኢኮኖሚ ምሁር ጀምሮ ሲተነተን የኖረው ከዝቅተኛ ምርታማነት ወደ ከፍተኛ ምርታማነት መሻገር፣ ከዝቅተኛ የግብርና ዘርፍ ወደ ከፍተኛ አምራች ኢንዱስትሪ መሸጋገር ማለት ነው። ይህ ነው መዋቅራዊ ለውጥ ወይም ትራንስፎርሜሽን የሚባለው፡፡ ግብርናው ራሱ ከዝቅተኛ ወደ ከፍተኛ አምራችነትና ምርታማነት በመሸጋገር ትራንስፎርሜሽን ማምጣት አለበት። ይህንን መሠረት አድርገው በርካታ አገሮች ተለውጠዋል። የአፍሪካ አገሮችም ሞክረዋል። ከዚህ በፊት “የዋሽንግተን ኰንሰንሰስ” እየተባለ በሚጠቀሰው ስምምነት መሠረት ትክክለኛ ፖሊሲ ማውጣትና ትክክለኛ ተቋማትን መመሥረት ለኢኮኖሚው የተስተካከለ ዕድገት እንደሚያመጣ ይታመን ነበር። ከዋሽንግተን ‘ኮንሰንሰስ’ በፊት ወይም ከቅኝ ተገዥነት ከወጡ በኋላ የአፍሪካ አገሮች እንዳደጉት አገሮች ለመሆን ተነሱ፡፡ እንደ አደጉት አገሮች እንሆናለን፣ ቶሎ እናድጋለን ማለት ጀመሩ፡፡ በዚህ ምክንያት የተጋነኑ ዕርምጃዎችን መውሰድ ቢጀምሩም ውጤታማ መሆነ አልቻሉም፡፡ ውድቀት ነበር ያተረፉት፡፡ አንዳንዶቹ አቅማቸውን ያገናዘበ ዕርምጃ መውሰድ አልቻሉም ነበር፡፡ እንዲሁ በተስፋ የተለጠጠ ፍላጎት ብቻ ነበር የነበራቸው፡፡ የኤሌከትሪክ ኃይል ሳይኖርህ ኢንዱስትሪ ልታስፋፋ አትችልም፡፡ እንዲሁ የምኞት ሐሳብ ብቻ ሆኖ ይቀራል፡፡ ስለዚህ ካለህ ነባራዊ ሁኔታ ጋር የመጣጣም ነገር እየሠራህ ሲያስፈልግም እያየህ ወደ ግል መዛወር ያለበትን ታዛውራለህ፡፡ ተገቢው ግብዓት ሲኖርህ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፉን ታሳድጋለህ፡፡ ሲኖርህ ከውጭ ላምጣ ወይስ ወደ ውጭ ልላክ? ብለህ ለመወሰን የሚያስችልህን ውሳኔ ታሳልፋለህ፡፡ የአፍሪካ አገሮች ግን መዋቅራዊ ለውጥ ማምጣት አለብን፣ ኢንዱስትሪ መስፋፋት አለብን ብለው ሲነሱ ተፈላጊው ግብዓት አልነበራቸውም ነበር፡፡

በመሆኑም ‹የዋሽንግተን ኮንሰንሰስ› ሲመጣ ፖሊሲን ማስተካከል፣ የግሉን ዘርፍ ማሳደግ፣ ወደ ግል የሚዛወሩ ተቋማትን ማዛወር፣ ኢኮኖሚውንም ከመንግሥት ይዞታ ማውጣት የመሳሰሉትን የሚያቀነቅን ነው፡፡ አሁንም ግን ፖሊሲን መስተካከል አስፈላጊ ሆኖ እንደሚገኝ ግልጽ ነው፡፡ አሁንም ቢሆን የግሉ ዘርፍ የኢኮኖሚው ሞተር መሆን አለበት፡፡ ይኼ ምንም ጥያቄ የለውም፡፡ ነገር ግን ምንድነው የምንሠራው? የሚለው መታወቅ አለበት፡፡ ይህ ባለበት ወቅት የእስያ አዲስ አስተሳሰብ ብቅ አለ፡፡ እስያዎቹ ጥርመሳ ነው ያመጡት፡፡ ለመቶ ዓመታት ያህል የምዕራቡ ዓለም ኢኮኖሚ በዓመት ከአንድ በመቶ በላይ ማደግ ሳይችል ቆይቶ ነበር፡፡ ይህም ቢሆን ከኢንዱስትሪ አብዮት በኋላ የመጣ ነው እንጂ ከዚያ በፊትማ ከዜሮ በታች ድረስ የወረደ ነበር፡፡ የምሥራቅ እስያ አገሮች ግን አዲስ የመዋቅረዊ ለውጥ ንድፈ ሐሳብ አስተዋወቁ፡፡ ይህን መጥቀስ ያስለፈገኝ ለምንድነው? የእኛን አገር ለውጥ በምን መልኩ እየቃኘነው ነው? የሚለውን ለመመልከት ነው፡፡ የልማት ንድፈ ሐሳብ አለን ወይ? የሚለውን ስንመለከት ወደ መዋቅራዊ ኢኮኖሚያዊ ለውጥ እንደሚያመራ እናስተውላለን፡፡ በመዋቅራዊ ለውጡ ግን እውነተኛው የኢኮኖሚ ዘርፍ ማደግ መቻል አለበት፡፡ አምራች የኢኮኖሚው ክፍል ማደግ መቻል አለበት፡፡ ኢንዱስትሪ ማደግ ይጠበቅበታል፡፡ ይህ ሁሉ እንዲሆን ግን የመንግሥት ሚና ምን መሆን አለበት የሚለውን በደንብ መመልከቱ ተገቢ ነው፡፡ ብዙ የሚያጨቃጭቀውም ይኸው ነው፡፡ እኔ ከእስያ ተሞከሮ ተነስቼ ለኢትዮጵያ የትኛው ይጠቅማታል የሚለውን ማስቀመጥ እፈልጋለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ ውስጥ መንግሥት መዋቅራዊ አኮኖሚያዊ ለውጥ አመጣለሁ በሚልበት ወቅት ለወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠር ፈተና ሆኖበታል፣ ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል ማስፈን ከብዶታል ተብሎ ይታመናል?

ዶ/ር ወልዳይ፡- እዚህ ላይ እንመጣበታለን፡፡ መጀመርያ ስለ ኬኩ መነጋገር አለብን፡፡ ኬኩን እንዴት እንጋግረው? እንዴት ነው ትልቁን ኬክ መሥራት የምንችለው? የሚለውን እንይና ከዚያ በኋላ ስለፈታኝ ሁኔታዎቹ እንነጋገራለን፡፡ እኔ እያሰብኩ ያለሁት የመንግሥት የመዋቅራዊ ለውጥ ዕቅድ ምን ያህል አሳታፊ ነው? ምን ያህል ሰው ጠቅሟል? እነ ማንን ጠቅሟል? ጠቅሞስ ከሆነ ቀጣይነት አለው ወይ? የሚለውን ለማየት እፈልጋለሁ፡፡ ይሁንና በጥያቄ ያነሳሀቸውን የሥራ አጥነትና የሀብት ክፍፍል ጉዳዮችን እናያቸዋለን፡፡ በመጀመርያ ግን ስለኢኮኖሚ ዕድገትና ስለመንግሥት ሚና እንነጋገር፡፡ ምክንያቱም ለእኔ ይህ ዋናው ቁልፍ ነጥብ ነው፡፡ በፊስካል ፖሊሲ አማካይነት ገንዘብ ከታክስም ከሌላ የገቢ ምንጭም ሰብስበህ የምትሠራቸው ሥራዎች ይኖራሉ፡፡ ይህ እንግዲህ ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል እንዲኖር ለማድረግ ይረዳል፡፡ ፖሊሲዎቹንም መመልከት ያስፈልጋል፡፡ እኔ አጽንኦት መስጠት የምፈልግበት ነጥብ ይህች አገር ለዕድገት የሚበጁ መሠረቶችን ማበጀት አለባት የሚለው ላይ ነው፡፡ ዕድገትን የሚገቱና የሚገድቡ አስገዳጅ ችግሮች ምንድን ናቸው? የሚሉትን መፈለግና የት ላይ ችግሮቹ እንዳሉ መቃኘት ይገባል፡፡ ለምንድነው ግብርናው እንደሚፈለገው ማደግ ያልቻለው? ለምንስ ነው ማኑፋክቸሪንግ እንደሚጠበቀው ያላደገው? የሚሉትን ጥያቄዎች መመለስ ግድ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የሥራ አጥነትና ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል ችግሮች ላይ ማተኮር የፈለግኩት መንግሥት በጣም ጠንካራ ሚና ያለው በመሆኑ ባለፉት 20 ዓመታት ውስጥ ልዩ ልዩ ፖሊሲዎችን ሲሞክር ቆይቷል፡፡ ግብርና መር የኢንዲስትሪ ልማት ከሚለው ጀምሮ ድህነት ቅነሳ ላይ ያተኮሩ ፖሊሲዎችና አሁን እስከመጡት የትራንስፎሜሽን ዕቅዶች ድረስ መንግሥት ያሳካቸው ነገሮች እንዳሉ ሆነው የሚተችባቸው በርካታ ጉዳዮች አሉ፡፡ የመንግሥት ሚና ግን ምን ያህል ነው መሆን ያለበት?

ዶ/ር ወልዳይ፡- አዲስ መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ለውጥ ለማምጣት የሞከሩና የተሳካላቸው አገሮች መንግሥታት ሚና ምን ይመስል ነበር? ብለን ማየቱ ይጠቅመናል፡፡ የመንግሥት ሚና በብዙ አገሮች ዘንድ ትልቅ ነው፡፡ እነ አሜሪካን እያየን ነው፡፡ አሁን እንደ ቀድሞው ነፃ ኢኮኖሚ መሆናቸው ቀርቶ ከለላ የሚሰጡ ወይም ‹ፕሮቴክሽኒስቶች› ሆነዋል፡፡ ይኼን ትተን በልማታዊ መንግሥትነት የሚጠቀሱ መንግሥታት ሚና ምን እንደሆነ ለማየት ብንሞክር ‹ከኒዮ ክላሲካል› ጀምሮ እስከ ‹ዋሽንግተን ኮንሰንሰስ› የተንሸራሸሩ ሐሳቦችን ብናይ የመንግሥት ሚና አነስተኛ መሆን አለበት በሚለው ሲስማሙ እናያለን፡፡ ክርክሩ ግን የመንግሥት ሚና ምን ያህል ነው መሆን ያለበት? የሚለው ላይ ነው፡፡ ለዚህ ግን የግሉ ዘርፍ ምን ያህል ጠንካራ ነው? የሚለውን መመለስ መቻል አለብን፡፡ የግሉ ዘርፍ እየጠነከረ ሲሄድ የመንግሥት ሚና እየቀነሰ መሄድ አለበት ነው የሚባለው፡፡ እንዳልከው ኢንቨስትመንቱንና ሌላውንም ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ስናየው የግሉ ዘርፍ ድርሻውን ይዞ እየተጓዘ እንዳልሆነ ግልጽ ነው፡፡ መንግሥት መንገድ ይገነባል፡፡ የሚጠቀምበት የግል ዘርፍ ከሌለ ግን ዋጋ የለውም፡፡ የኤሌክትሪክ ኃይል ይዘረጋል ተጠቃሚ ከሌለ ዋጋ አይኖረውም፡፡ እርግጥ ለውጭ ገበያ ይቀርባል የሚለው እንዳለ ሆኖ ማለት ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው መንግሥት በጣም ጠንካራ ነው፡፡ በተለይ በኢንቨስትመንት በኩል የመንግሥት ድርሻ ከፍተኛ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የመንግሥት መስፋፋት የግሉን ዘርፍ እያቀጨጨ ነው፡፡ ከኢኮሚኖው እያስወጣ ነው የሚሉ ክርክሮችም አሉ፡፡

ዶ/ር ወልዳይ፡- የመንግሥት ድርጅቶች ጫና ያደርጋሉ፣ የግሉን ዘርፍ ያስወጣሉ የሚለውን መቀበል ይከብደኛል፡፡ እርግጥ አንዳንድ የመንግሥት ፕሮጀክቶች እኮ እንዲቆዩ፣ መደርደሪያ ላይ እንዲቀመጡ የዓለም ባንክ እየወተወተ ነው፡፡ ለእኔ የቱንም ያህል ይራበን እንጂ የኤሌክትሪክ ኃይል ማስፋፋት ሥራዎች መሠረታዊ ናቸው፡፡ ኢንዱስትሪ ልገንባ፣ ወዘተ. ለሚለው ጥያቄህ ምላሽ የሚሰጡ ናቸው፡፡ ባይሆን ብቃት ያለው አመራር ተመሥርቶ ፕሮጀክቶቹን በአግባቡ ማስፈጸም መቻል ይጠበቅበታል እንጂ፣ መንግሥት ከኃይል ማስፋፊያ ግንባታ ሥራዎች ይውጣ ብንል የግሉ ዘርፍ ተስቦ መግባት እስካልቻለ ድረስ የማይሆን ነው፡፡ መንግሥት በመሠረተ ልማት መስክ ሚናውን ይዞ መገንባት ካልቻለ ሁሉ ነገር ዋጋ አይኖረውም፡፡ በዚህ እንስማማ፡፡ የግሉ ዘርፍ የኢኮኖሚ ዕድገት ሞተር መሆን አለበት፡፡ በተለይም ኢትዮጵያዊው የግል ባለሀብት የኢኮኖሚው መዘውር መሆን አለበት የሚለው ግልጽ ነው፡፡ የውጭው እየመጣ ቢሆንም እንኳንና የውጭ ገንዘብ ሊያመጣልን ያለንን እየወሰደው በመሆኑ መንግሥት ቆም ብሎ ማሰብ የጀመረ ይመስለኛል፡፡ አሁን ያለው ሁኔታ በፋይናንስ መስኩም ብታየው የመንግሥት ድርጅቶች ናቸው ትልቁን ድርሻ የሚይዙት፡፡ የግሉ ዘርፍ ድርሻ 25 በመቶ ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን መገንዘብ ያለብን የመንግሥት ዓላማ የግሉን ዘርፍ ለማቀጨጭ ወይም ለማስወጣት እንዳልሆነ ነው፡፡ እርግጥ ክፍተት አለ፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ግን የግሉ ዘርፍ የኢኮኖሚው ሞተር በመሆን መዋቅራዊ ለውጥ ያመጣል ማለት የሚቻል አይደለም፡፡

ወደ ማኑፋክቸሪንግ ስንመጣ እንደ ንግድ ባንክ ያሉት ብቻም ሳይሆኑ ትልልቅ የሚባሉት ማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ሳይቀሩ የሚጠየቁት ብድር በአብዛኛው ከማኑፋክቸሪንግ ውጪ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ በማኑፋክቸሪንግ መስክ ብድር ተጠይቆበት ውድቅ ያደረጉት ፕሮጀክት እንደሌለ ገልጸውልኛል፡፡ ፍላጎት የለም እያሉ ነው፡፡ በማኑፋክቸሪንግ መስክ የግሉ ዘርፍ ለመግባት ትልቅ ክፍተት እያሳየ ነው፡፡ መሠረተ ልማት ዝቅተኛ በሆነበት፣ የግሉ ዘርፍ ሚና አነስተኛና ደካማ በሆነበት የኢኮኖሚው ክፍል ሁሉ መንግሥት ይገባል፡፡ ይህ በሌሎችም አገሮች ዘንድ የሚደረግ፣ እየተደረገም ያለ ነው፡፡ በመሆኑም የመንግሥት ሚና ትክክል ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ መንግሥት አቅርቦት እየፈጠረ ነው፡፡ የግሉ ዘርፍ ሊሠራው ይችል ነበር? የግሉ ዘርፍ ኢንቨስትመንት የደከመ በመሆኑ የግዴታ መንግሥት በመግባት መሥራት ይኖርበታል፡፡ ይኼም ሆኖ መንግሥት በማኑፋክቸሪንግ መስክ የሚጠቅሳቸው ዘርፎች ምን ያህል ወሳኝ ናቸው? የሚለውንም መመልከት ይበጃል፡፡ በዕቅዱ ውስጥ ያሉት ሲታዩ እንደ ቆዳና ጨርቃ ጨርቅ የመሳሰሉት ቦታ አግኝተዋል፡፡ ግን እነዚህ ብቻ ናቸው ወይ የሚያስፈልጉን? እያልኩ አስባለሁ፡፡ በዚህ አገር ውስጥ አንድ መቶ ወሳኝ የሚባሉ ማኑፋክቸሩንግ መስኮች ቁልፍ የምንላቸው ተለይተው ቢወጡ የትኞቹ ይሆኑ ብዬ አስባለሁ፡፡ ጃፓኖቹ፣ ቻይኖቹና ሌሎቹም የሩቅ ምሥራቅ አገሮች ማኑፋክቸሪንግ ሲሉ ምን ማለታቸው ነው? ሲባል ካላቸው ለሥራ ግብዓት ከሚሆን ምንጭ ጋር አብሮ የሚሄድ ነው፡፡ ነገር ግን በጣም ወሳኝ ናቸው፡፡ እነዚህን ካልያዛችሁ፣ ካላለማችሁ መቀጠል አትችሉም የሚያስብሉት የትኞቹ ናቸው? የሚለውን ማየት ይጠቅመናል፡፡ በማኑፋክቸሪንግ መስክ አብዛኞቹ እየመጡ ያሉት ኢትዮጵያውያን አይደሉም፡፡ በመሆኑም የግሉ ዘርፋችን አቅም ትንሽ ነው እናሳድገው ካልን ከዚህ ውጪ አማራጭ ያለን አይመስለኝም፡፡ በመሆኑም መንግሥት የግሉን ዘርፍ እያስወጣ ነው የሚለው ብዙም የሚያስኬድ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ደካማ የግል ዘርፍ ይዘን ለመኩራራት እየሞከርን ይመስለኛል፡፡

ይልቁንስ ስለሌለን እንዴት እንፍጠረው? ለዚህስ መንግሥት ምን መሥራት አለበት? ማለት አለብን፡፡ የመንግሥት ፖሊሲን አንብቤያለሁ፡፡ ከሰዎች ጋርም ተወያይቼበታለሁ፡፡ መንግሥት የግሉን ዘርፍ የማስወጣት ወይ የማቀጨጭ ዓላማ የለውም፡፡ ትክክለኛ ክርክር ከሆነ መንግሥት ኢትዮጵያውያን ኢንቨስትሮችን እንዴት መፍጠር አለበት የሚለው ላይ ማተኮር የሚገባ ይመስለኛል፡፡ አብዛኛው የግሉ ዘርፍ በአገልግሎት መስክ ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ብድር የሚጠየቀው ለሆቴል ግንባታ ነው፡፡ መኪና ለማስመጣት ነው፡፡ ውስን ሀብት ባለበት እንዲህ ያሉ ጥያቄዎችን እስከ ወዲያኛው ማስተናገድ ከባድ ነው፡፡ የግሉ ዘርፍ በሌሎች ትልልቅ የማኑፋክቸሪንግ መስኮች ላይ ለመሳተፍ ፋይናንስ እየጠየቀ እንዳልሆነ እየታየ ነው፡፡ ስለዚህ እንዲህ ባሉት መስኮች ላይ መሳተፍ የሚችል፣ ኢንቨስት የሚያደርግ የግል ዘርፍ እንዴት ይፈጠር? የሚለውን መመለስ መቻል አለብን፡፡ ውጤታማ እንደሆኑ ያመነው የኮሪያ መንግሥት ለኢንቨስተር ዜጎቹ ፋብሪካ ሠርቶ አድሏል፡፡ ከዚያ አንፃር የእኛስ እንዴት ይታያል? የሚለውን መመካከር ያስፈልጋል፡፡ መንግሥት አሁን ባለው ሁኔታ የግሉ ዘርፍ የገባበት ቦታ ውስጥ እየገባ ሊወዳደረው ቀርቶ ለራሱም በጣም ተወጥሯል፡፡ የግሉን ዘርፍ ለመወዳደር የሚችልበት ወቅት አይደለም፡፡ የጀመራቸውን ትልልቅ ፕሮጀክቶች መጨረስ አቅቶት ትኩረቱ እዚያ ላይ ነው፡፡ እነ ዓለም ባንክ ትልልቅ ለመንግሥት ከባድ የሆኑ ፕሮጀክቶች እንዲገቱ፣ በዚህም መሠረት ለግዙ ዘርፍ የሚውል ፋይናንስ እንዲሁም የውጭ ምንዛሪ ይገኛል የሚል ክርክር እያሰሙ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- መንግሥት መሠረተ ልማት እየገነባ ነው? አዎ እየገነባ ነው፡፡ ትልቁ ጥያቄ ግን መንግሥት የሚሠራው ሥራና በአገሪቱ እየተከሰተ ያለው ነገር ቆም ብሎ እንዲያስብ ያደረገው ይመስላል፡፡ የወጣቶች ተዘዋዋሪ ፈንድ ብሎ እንዲያመጣ ያስገደደው ሁኔታ የተፈጠረው፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የክልል መንግሥታት የአክሲዮን ኩባንያዎችን እንዲመሠርቱ የሚያደርጉ ክስተቶች የመጡት ከሕዝባዊ ተቃውሞው ማግሥት ነው፡፡ በኦሮሚያ፣ በአማራና በደቡብ ክልሎች ሕዝብ እንዲጠቀም እናደርጋለን በማለት በትራንስፖርትና በተለያዩ መስኮች በመንግሥት ሥር አክሲዮን ኩባንያዎች ሲመሠረቱ እያየን ነው፡፡ ‹የኢኮኖሚ አብዮት› የሚባሉ እንቅስቃሴዎች ተጀምረዋል፡፡ ይህ ሁሉ ከመምጣቱ በፊት መንግሥት በሥራ አጥነትና በፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል ላይ ምን ሲሠራ ነበር የሚል ጥያቄ እንድናነሳ ያስገድዳል?

ዶ/ር ወልዳይ፡- ይኼ ለእኔ እሳት የማጥፋት አሠራር ነው፡፡ ወጣቶች ተነሱ፣ ወዘተ. ተብሎ የሚደረገው ነገር ጊዜያዊ ችግርን ለመፍታት የሚወሰድ ዕርምጃ ነው፡፡ እንደጠቀስከው ያለ ዓይነት ነገር የሚሠራ ከሆነ ለእኔ ‹የፖፑሊስት› ወይም የሕዝባዊነት ስሜት ያነገበ አካሄድ ነው፡፡ ለዘለቄታው ያሉብን ችግሮች እንዴት ይፈቱ? የሚለው ነው የእኔ ትኩረት፡፡ ችግሮችን ለማርገብና ለማረጋጋት የሚወሰዱ ዕርምጃዎች ይኖራሉ፡፡ እኔ ግን ዘላቂ ሥራዎች ላይ ማተኮሩን እመርጣለሁ፡፡ በወጣቶች ላይ ለመሥራት እኮ አሁንም አንዱ መፍትሔ የግሉን ዘርፍ ማሳደግ ነው፡፡ የግሉ ዘርፍ ደካማ ነው ካልን እንዴት አድርገን ነው ጠንካራ እንዲሆን መሥራት ያለብን የሚለውን ማጤን ይኖርብናል፡፡ በአገሪቱ የታየውን ሁኔታ እንዴት ትተረጉመዋለህ ካልከኝ እንደ የፍጥነት ማገጃ ወይም የፍጥነት መወሰኛ እመለከተዋለሁ፡፡ ለወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠር በጣም ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡ እዚህ ሠልጥነው ወደ ውጭ ሄደው የሚሠሩ፣ በሁለተኛ ደረጃ ራሳቸውን በራሳቸው ቀጥረው መሥራት የሚችሉ ወጣቶችን መፍጠር፣ በሦስተኛ ደረጃ በመንግሥት ቀጣሪነት የሥራ ዕድል መፍጠር ተገቢ ነው፡፡ አንዳንዱ የራሱን ሥራ መሥራት ይፈልጋል፣ አንዱንዱ ተቀጥሮ መሥራት ይፈልጋል፡፡ አንዳንዱ የመንግሥት ሥራ ላይ ያተኩራል፡፡ ከእነዚህ በተለየ ደግሞ መሥራት እየቻለ ሥራ ፈት የሚሆንም አለ፡፡ ዘመድ ገንዘብ ይልክልኛል ብሎ የሚጠብቅ ወይም ወደ ወጪ እሄዳለሁ ብሎ በተስፋ የሚቀመጥ አለ፡፡ ከዚህ ውጭ ግን አሳሳቢ የሥራ አጥነት አለ፡፡ ሥራ እየፈለገው ማግኘት ያልቻለ ብዙ ነው፡፡ በተለይ በገጠር አካባቢ ያለው የሥራ አጥነትነት ላይ አልተሠራም፡፡ ይኼ ነገር እንዴት ይፈታል? ካልን እኔ የምለው ከረዥም ጊዜና ዘላቂነት ካለው አካሄድ እንጂ እንደታየው እሳት የማጥፋት ነገር ብዙም አያስኬድም፡፡

መንግሥት ከራሱ በጀት ቀንሶ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሚያስተዳድረው ተዘዋዋሪ ፈንድ ተዘጋጅቷል፡፡ በወጣቶች ሥራ ማጣት ላይ ባደረግነው ጥናት መሠረት ሥራ የመስጠትና የመፍጠር ኃላፊነት የመንግሥት ብቻ እንዳልሆነ ተገንዝበናል፡፡ ዘላቂነት ያለው የሥራ ዕድል መፍጠር የሚችለው የግሉ ዘርፍ ነው፡፡ ስለዚህም መንግሥት የወጣቱን ሥራ አጥነት ችግር እፈታለሁ የሚለውን አካሄድ አልቀበለውም፡፡ ወላጆችም ኃላፊነት አለባቸው፡፡ ወልደህ አሳድገህ በኋላ ላይ ሂድና ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ሥራ ይስጥህ ብለህ አትልከውም፡፡ የግሉ ዘርፍ የቅጥር ምንጭ መሆን መቻል አለበት፡፡ በተቃውሞ ወቅት ጉዳት የደረሰባቸውን አንዳንድ ባለሀብቶች አነጋግሬ ነበር፡፡ እነሱም ሥራ መስጠት የመንግሥት እንደሆነ ነው የሚያስቡት፡፡ ‹‹ወጣቶቹን አሠልጥኜ ቀጥሬ ነገ ትቶ የሚደሄድ ከሆነ እኔ ማሠልጠኛ ነኝ እንዴ?›› የሚሉ፣ ‹‹ወጣት መቅጠር ሥጋት ብቻ ነው ትርፉ፤›› ያሉኝም ነበሩ፡፡ መንግሥት የሚሠራቸው ፕሮጀክቶች እንዳሉ ሆነው የግሉ ዘርፍ ግን ትልቁ የሥራ መስክ ነው፡፡ እነዚህ ባለሀብቶች የችግሩ መፍትሔ አካል መሆን አለባቸው፡፡ መንግሥት የግሉ ዘርፍ ለሚፈጥራቸው የሥራ ዕድሎች ማበረታቻ መስጠት ይችላል፡፡ አንዳንድ አገሮች ይህ አላቸው፡፡ ለምሳሌ ለሁለት ዓመት ቢቀጥር ግማሹን የደመወዝ ወጪ መንግሥት እየተጋራ፣ ቀስ በቀስ እየቀነሰ በመጨረሻም ባለሀብቱ ወጪውን መሸፈን የሚችልበት አሠራር አለ፡፡

በመሠረቱ እኮ አሁን ለወጣቶች ሥራ ተብሎ የተመደበው በጀት ከሌላ የመንግሥት ፕሮጀክት ተቀንሶ የመጣ ነው፡፡ አንዱን ለማጥፋት የወሰድከው ዕርምጃ በሌላ ጎኑ የኢኮኖሚው መረጋጋት ላይ ችግር ሊያመጣ ይችላል፡፡ መንግሥት የበጀት ጉድለት ሊመጣበት ይችላል፡፡ ይህንን ለመሙላት ገንዘብ ሊያትም ይችላል፡፡ ይህ ደግሞ የዋጋ ግሽበትን በማስከተል ኢኮኖሚውን ያናጋል፡፡ በመሆኑም የአጭርና የረዥም ጊዜ ጉዳዮችን በአግባቡ ማየት ያስፈልጋል፡፡ መንግሥት በአሁኑ ወቅት እያደረጋቸው ያሉት ነገሮች እሳት የማጥፋት እንጂ በደንብ ታስበውበት የተደረጉ አይመስለኝም፡፡ ለጊዜው ለማብረጃ ተብለው የተወሰዱ ናቸው፡፡ መንግሥት ለዘለቄታው በሚበጁ ሥራዎች ላይ ማተኮር አለበት፡፡

ሪፖርተር፡- ከወጣቶች የሥራ ዕድል ጋር በተያያዘ በፊት እርስዎ ራስዎ አበክረው የሚከራከሩበት ነጥብ ነበር፡፡ መንግሥት ማይክሮ ፋይናንስን ለወጣቶች የሥራ መፍጠሪያነት ሲያስበው፣ ወጣቶቹን በቡድን እያደረጀ ገንዘብ ያለ ውጣ ውረድ እንዲያገኙ ያደርግ ነበር፡፡ ይህንን እርስዎ ሲቃወሙ ቆይተዋል፡፡ ወጣቶቹ የመሥራት ፍላጎት ሳይኖራቸው፣ ውጤታማ ሥራ ለመሥራት ሳይነሳሱ ገንዘብ መስጠት ትክክል አይደለም ይሉ ነበር፡፡ ይህ እኮ ነው አሁንም የመጣው?

ዶ/ር ወልዳይ፡- አሁንም ትክክል አይደለም፡፡ በቅርቡ ለምርምር ፊልድ ወጥቼ ነበር፡፡ ተዘዋዋሪ ፈንድ የሚባለው ይፋ ሲደረግ የግንዛቤ ችግር ተፈጥሮ ነበር፡፡ በወረዳ ደረጃ የነበሩ አመራሮች የነበራቸው አመለካከት የተሳሳተ ነበር፡፡ ገንዘቡን አምጡትና ለወጣቶቹ አሳልፈን እንስጣቸው ነው የሚሉት፡፡ ይህ ስህተት ነው፡፡ በአስፈጻሚዎቹና በወጣቶቹ ዘንድ የተሳሳተ ነገር ታይቷል፡፡ እንዲሁ እንደ ዕርዳታ የሚሰጥ ነገር መስሏቸው ነበር፡፡ መጀመርያ ራሳቸው ፈጻሚዎቹ እንዲገባቸው መደረግ አለበት፡፡ አለበለዚያ እስካሁን ስንሠራ የቆየነውን በባዶ የሚያስቀር ነው፡፡ ይኼ ነገር ከተነገረ በኋላ በጥሩ ደረጃ እየሠሩ ብድራቸውን በአግባቡ ይከፍሉ የነበሩ ወጣቶች ማቆም ጀምረዋል፡፡ መንግሥት ለጋስ መሆን ከጀመረማ ምናለበት ለእኛም የሚል አመለካከት ይታይባቸው ነበር፡፡ የፋይናንስ ዘርፉ በወሬ የሚነዳ መሆኑን መገንዘብ አለብን፡፡ በየትኛውም ዓለም ይህ እውነታ ነው፡፡ ፕሬዚዳንት ትራምፕ የመሰላቸውን በተነፈሱ ቁጥር ስቶክ ገበያው ይዋዥቃል፡፡ እኛም ጋ እንዲሁ ነው፡፡ መንግሥት ያመጣው የተዘዋዋሪ ፈንድ አደገኛ ሁኔታ የሚፈጥር ነው፡፡ ቀስ በቀስ ግን አለመግባባቱ እየሰከነ እየመጣ ነው፡፡ በአማራ፣ በደቡብ፣ በትግራይና በኦሮሚያ ክልሎች የሚያስደግጥ ነገር ዓይተን ነበር፡፡ እስካሁን የለፋንበት ሥራ ገደል ገባ ብዬ ነበር፡፡ አስፈጻሚዎቹ ራሳቸው ነገሩ ከገባቸው በኋላ ቀስ በቀስ ነገሮች መልክ መያዝ ጀመሩ፡፡ አነስተኛና ጥቃቅን ኩባንያዎች የሚፈለፈሉት በማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ድጋፍ ነው፡፡ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ወጣቶች ሥራ እንዲፈጥሩ፣ ሥራ እንዲያገኙ የሚያግዝ ነው፡፡ ከ75 በመቶ ያላነሰው ከቁጠባ በሚገኝ ገንዘብ ነው ፋይናንስ የሚደረገው እንጂ ከመንግሥት በጀት አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- ከአነስተኛና ጥቃቅን እያደጉ ወደ መካከለኛ አምራችነት ለሚሻገሩት ድጋፍ የሚሰጡ አሠራሮች አልነበሩም፡፡ እንዲህ ዓይነቱን ችግር የሚፈጥሩ ደግሞ በጣም ትልልቅ የሆኑ ጥቂት የመንግሥት፣ የፖለቲካ ፓርቲ ሰዎች፣ እንዲሁም በጣት የሚቆጠሩ የግል ኩባንያዎች ሌሎች እንዳያድጉና እንዳይስፋፉ እንቅፋት ሆነዋል የሚል ጥናት በዓለም ባንክ ሳይቀር የወጣው እ.ኤ.አ. በ2010 ነበር፡፡

ዶ/ር ወልዳይ፡- ይህ አባባል ፖለቲካዊ ስሜት እንዳይላበስ ነው የምፈራው፡፡ አብዛኛውን ጊዜ የፖለቲካ ሚዲያው ላይ የሚንፀባረቅ ነገር ነው፡፡ እንደ እኔ ግን ኢኮኖሚያዊ በሆነ ቅኝት እነዚህ ኩባንያዎች ሥራቸው ምንድነው? የሚሉ ነጥቦችን እያነሳሁ እንደ ኢኮኖሚ ባለሙያ መፈተሽ ነው የሚገባኝ፡፡ ለፖለቲካ ፍጆታ የፓርቲ ድርጅቶች ናቸው እየተባለ ሊወራ ይችላል፡፡ እንደ ኢኮኖሚ ባለሙያ ግን እነዚህ ኩባንያዎች በመላው ኢኮኖሚ ላይ ያላቸው ተፅዕኖ ምን ያህል ነው? የሚለው መታየት አለበት፡፡ ለምሳሌ እኔ በሰላም ባስ ውስጥ ለሁለት ዙር በቦርድ አገልግያለሁ፡፡ ይህ ኩባንያ ሲመሠረት ከኢትዮ ኤርትራ ጦርነት በኋላ ብታምንም ባታምንም ወደ ትግራይ የሚጓዝ የሕዝብ ማመላለሻ አውቶቡስ አልነበረም፡፡ መንገዱ ተበለሻሽቷል፡፡ ለመኪኖች ጠንቅ ነበር፡፡ በዚህ ሁኔታ የግል ድርጅቶች ለመሥራት አያዋጣቸውም ነበር፡፡ መኪኖቹ ቢሄዱ እንኳ ተበላሽተው ስለሚያስቸግሩ የሚመጣ አልነበረም፡፡ በዚህ ምክንያት ሰላም ባስ የሚባል ድርጅት ተፈጠረ፡፡ አሁን ተልዕኮውን አሳክቷል፡፡ አሁን ሰላም ባስ የሚያመነጨው ገንዘብ የሚፈለገው ቀላሚኖ የሚባለውን ትምህርት ቤት እንዲደጉም ነው፡፡ ሕንፃ እንዲገነባና ሌሎች መተዳደሪያዎችን እንዲፈጥር ነው፡፡ ሰላም ባስ ኩባንያ አገልግሎቱን በመስጠቱ አሁን እኮ በርካታ የአክሲዮን ድርሻው ተሸጧል፡፡ በእኔ አመለካከት እነዚህ ድርጅቶች የግሉን ዘርፍ ከጨዋታ የሚያስወጡ ከሆኑ መሸጥ አለባቸው፡፡ ፖለቲካውን ፖለቲከኞቹ እንዲጨነቁበት ትቼ እኔ ግን በኢኮኖሚ ጉዳዮች ላይ ማተኮሩን እመርጣለሁ፡፡ እነዚህ የፓርቲ ኩንያዎች የሚባሉት ምን ያህል ናቸው? ከጠቅላላው ኢኮኖሚ አኳያ ያላቸው ካፒታል ምን ያህል ነው? የገበያ ድርሻቸው ምን ያህል ነው? ወዘተ. ያሉትን ነጥቦች መመልከቱ ነው ለእኔ ትርጉም የሚሰጠኝ፡፡

ሪፖርተር፡- የኦሮሚያና  የአማራ ክልሎች የአክሲዮን ኩባንያዎች በአንድ ጊዜ እየመሠረቱ ነው፡፡ አመጣጣቸው በአንድ ጊዜ መሆኑ ግን አያሠጋዎትም?

ዶ/ር ወልዳይ፡- በእኔ አመለካከት በረዥም ጊዜ ሒደት ለውጥ ማምጣት የሚችለውና የኢኮኖሚ ዕድገት ሞተር የሚሆነው የግሉ ዘርፍ ነው፡፡ ይህ በምንም ሁኔታ የምደራደርበት ሐሳብ አይደለም፡፡ ምክንቱም ለለውጥ ይኸው ነው መንገዱ ብዬ አምናለሁ፡፡ ቅድም እንዳልኩት ግን ለጊዜያዊ መፍትሔ ሲባል የሚሠሩ ነገሮች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ይህ ለእኔ ውጤታማ አያደርግም፡፡ በወሳኝነት ለውጥ ለማምጣት የግሉ ዘርፍ በማይገባበት መስክ ስትገባ አሳይተህ እንዲከተልህ ማድረግ ነው፡፡ መንግሥት በአንድ በኩል ‹ፕራይቬታይዝ› እያደረገ እንደሚገኝም ማየት ያስፈልጋል፡፡ የነበሩትን እየሸጠ እየወጣ ነው፡፡ እንደ አዲስ እየገባ ነው ካልንም የግሉ ዘርፍ መግባት ባልቻለባቸው ቦታዎች እየገባ መንግሥት ከሠራ የሚደገፍ ነው፡፡ የመንግሥት ሚና በጉልህ መለየት አለበት፡፡ በምንም ዓይነት ተዓምር የግሉን ዘርፍ ከኢኮኖሚው እያስወጣን ዘላቂ ዕድገትና ለውጥ ልናመጣ አንችልም፡፡ የግሉን ዘርፍ ከጨዋታ እያስወጣን በሄድን ቁጥር የሩሲያ ዓይነት ችግር ውስጥ ነው የምንገባው፡፡ ወይም ደግሞ በደርግ መንግሥት ወቅት እንደነበረው ዓይነት ከባድ ውድቀት ውስጥ ነው የምንወድቀው፡፡ ይህ የሚሆን አይመስለኝም፡፡ ይልቅ አሁንም ቢሆን የሚያስደግጠው ነገር ምንድነው? ካልን መንግሥት በአብዛኘው ኢንቨስተር መሆኑ፣ በፋይናንስ ዘርፉም ትልቁን ድርሻ መያዙ ነው፡፡ ወደ ማኑፋክቸሪንግ መስክም የግሉን ዘርፍ ማምጣት ትልቅ ሥራ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የማኑፋክቸሪንግ መስኩን ካነሳን መንግሥት የሥራ ቦታዎችን ወይም ሼዶችን ገንብቶ፣ የፋይናንስ አቅርቦትም አመቻችቶ እየሰጠ እንደሚገኝ ቢገልጽም የግሉ ዘርፍ ግን ፍላጎት ያለው አይመስልም፡፡

ዶ/ር ወልዳይ፡- ወሳኙ የጠፋው ነገር የምልህ እሱን እኮ ነው፡፡ እንደገለጽኩልህ ለባንክ ብድር የሚቀርቡት ፕሮጀክቶች በአብዛኛው ለሆቴልና ለሌሎች አገልግሎቶች ነው፡፡ ይህ ግን ዘላቂ ለውጥ አያመጣም፡፡ ስለዚህ እኮ ነው በጣም አሳሳቢ ችግር ውስጥ ነን የምለው፡፡ አሁን የምንችልበት ጊዜ አይደለም፡፡ ባለሀብት በአግባቡ ታክስ መክፈል አለበት፡፡ መንግሥት ተቋማትን ማፅዳትም አለበት፡፡ ሙስናውን፣ የቢሮክራሲ አሠራሩን መፈተሽና ማስተካከል አለበት፡፡ የአገልግሎት ዘርፉ በቀላሉ ገንዘብ ለማግኘት ምቹ ከሆነ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉም ልክ እንደዚያው እንዲሆን ለማድረግ ነው ማሰብ የሚገባን፡፡ አብዛኛው ሰው ቀዳዳ እየፈለገ ለራሱ ጥቅም ብቻ የሚሯሯጥ ከሆነ ጉዳት ነው ትርፉ፡፡ መንግሥት የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ባለሀብቶችን ለማፍራት፣ ተገቢውን ማበረታቻ ብቻ ሳይሆን ስለጥቅሙም በአግባቡ ማስተማር ይጠበቅበታል፡፡

ሪፖርተር፡- ባለሀብቶች መንግሥት እያቀረባቸው ባሉ የማኑፋክቸሪንግ መሠረተ ልማቶች ውስጥ አለመግባታቸው በረዥም ጊዜ እንደሚያሳካቸው በሚያልማቸው የልማት ፍላጎቶቹ ላይ ጫና አያሳድሩበትም?

ዶ/ር ወልዳይ፡- የግሉ ዘርፍስ እንዲህ ባሉት መስኮች ላይ ለመሰማራት አቅም አለው ወይ? የሚለውን መመለስ ያስፈልጋል፡፡ መሠረተ ልማት መገንባቱ ጥያቄ ውስጥ የሚገባ አይደለም፡፡ ጥያቄ ውስጥ የሚገባው መሠረተ ልማቶቹ እንዴት እየተገነቡ እንደሆነ፣ ወጪ ቆጣቢ መሆናቸው፣ ምርታማ ያደርጉናል ወይ? የሚለው ጉዳይ ነው፡፡ የእስያ አገሮች መሠረተ ልማት ገነቡ፣ ፋይናንስ አቀረቡ፣ ትምህርትና ሥልጠና ሰጡ፡፡ በተለይ የቴክኒክ ክህሎት ሥልጠና ሰጥተዋል፡፡ ከዚያም ቴክኖሎጂን አቀረቡ፡፡ የግሉ ዘርፍ በኢንዱስትሪው ውስጥ ጉልህ ሚና መጫወት እንዲችል እንዲህ ያሉት ነገሮች ተሟልተው መቅረብ አለባቸው፡፡