Skip to main content
x
‹‹ዕቅድን ከአፈጻጸም ጋር ብቻ አይቶ ማለፉ ኢቫሉዌሽን ሳይሆን ክትትል ነው››

‹‹ዕቅድን ከአፈጻጸም ጋር ብቻ አይቶ ማለፉ ኢቫሉዌሽን ሳይሆን ክትትል ነው››

አቶ ዮሐንስ በልሁ፣ የኢትዮጵያ ኢቫሉዌሽን አሶሲዬሽን ፕሬዚዳንት

ምዘና (ኢቫሉዌሽን) በአሠራር ውስጥ ለውሳኔ የሚረዱ ሐሳቦች ከአቅም፣ ከችሎታ፣ ከጥራት፣ ወዘተ አኳያ የሚመነጭበት ሒደት ነው፡፡ በኢትዮጵያ ባለሙያዎች ሙያዊ የምዘና/ግምገማ ዕውቀትና ክህሎት እንዲኖራቸውና የአቅም ግንባታ ሥራዎችን ለማከናወን ከስምንት ዓመታት በፊት የተቋቋመው የኢትዮጵያ ኢቫሉዌሽን አሶሲዬሽን 200 አባላት አሉት፡፡ ማኅበሩ ስለሙያው ግንዛቤ በመፍጠር አርኣያ የሆነ ሳይንሳዊ የምዘና ሥራ እንዲስፋፋ ለማድረግ እየሠራ መሆኑን ይናገራል፡፡ በማኅበሩ እንቅስቃሴ ዙሪያ ፕሬዚዳንቱን አቶ ዮሐንስ በልሁን ሻሂዳ ሁሴን አነጋግራቸዋለች፡፡

ሪፖርተር፡- ማኅበሩ ከተቋቋመ ስምንት ዓመታት አስቆጥሯል፡፡ በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ምን ሠርቷል?

አቶ ዮሐንስ፡- ባለሙያዎችን የማሰባሰቡ ሥራ ረዥም ጊዜ ፈጅቶብናል፡፡ ሙያው ገና አዲስ ነው፡፡ እስከአሁን በዚህ ሙያ የሠለጠኑ ብዙ ባለሙያዎች የሉም፡፡ ሙያው  እያደገ ቢመጣም፣ በደንብ ማሳወቅ አልቻልንም፡፡ የማስተዋወቅ ችግር አለ፡፡

ሪፖርተር፡- ማኅበሩ ሥራውን ከመሥራት የሚያግዱት ሌላ ችግሮች አሉበት?

አቶ ዮሐንስ፡- የሙያ ማኅበራት በግለሰብ በጎ ፈቃደኝነት ላይ የተመሠረቱ ናቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች በተለያየ ኃላፊነት ላይ የሚገኙ ናቸው፡፡ ከመደበኛ ሥራቸው ጊዜ ወስደው ለማኅበር ማድረግ ይቸግራቸዋል፡፡ እነዚህን ሰዎች ማግኘት ትልቅ ችግር ነው፡፡ ሌላኛው ችግር የገቢ ነው፡፡ ገቢያችን የተመሠረተው በአባላት መዋጮ ላይ ነው፡፡ የአባላት መዋጮ ደግሞ አነስተኛ ነው፡፡ እኛ በዓመት 300 ብር ነው እናስከፍላለን፡፡ ይኼንንም የሚከፍሉት መክፈል የሚችሉት ብቻ ናቸው፡፡ 200 አባሎቻችን በሙሉ ከፈሉ ብንል እንኳን፣ በዓመት የሚገኘው በጣም አነስተኛ ነው፡፡ በመሆኑም የተለያዩ ወጪዎችን ሸፍኖ ማኅበሩን ለማንቀሳቀስ አይበቃም፡፡ ቢሮውን የሚያንቀሳቅሱ ሠራተኞችም የሉንም፡፡ የቦርድ አባላትን ሐሳብና ውሳኔ ወደ መሬት አውርዶ የሚያስፈጽም ቋሚ ሰው የለንም፡፡ 

ሪፖርተር፡- ምዘና እንደ ሙያ እንዴት ይገለጻል?

አቶ ዮሐንስ፡- ኢቫሉዌሽን ማለት በጥቅሉ ለውሳኔ የሚረዱ ሐሳቦችን የሚያመነጭ ሥራ ነው፡፡ ከቤት፣ ከግለሰብ ጀምሮ እስከ አገር ድረስ ውሳኔዎችን የሚጠይቁ ብዙ ጉዳዮች አሉ፡፡ ትክክለኛ ውሳኔ ለመወሰን ጥሩ ኢቫሉዌሽን ማካሄድ ያስፈልጋል፡፡ ሰዎች ግን ኢቫሉዌሽንን ወይም ግምገማና ምዘናን በአሉታዊ ጎኑ ይረዱታል፡፡ ግምገማ ሲባል የአንድን ግለሰብ መጥፎ ጎን ብቻ ለይቶ ማውጣት እንደሆነ አድርገው የሚያስቡም አሉ፡፡ ይኼ ግን የተሳሳተ ሐሳብ ነው፡፡ ኢቫሉዌሽን ተጠያቂነትን ያካተተ ነው፡፡ ተጠያቂነት ያለውን ሥራ ከመሥራት ባሻገር ስህተቶች በድጋሚ እንዳይከሰቱ ትምህርትን እንወስድበታለን፡፡ የግምገማ ሪፖርቶች ለሚቀጥሉት ሥራዎች መንገድ የሚከፍቱ ናቸው፡፡ ኢቫሉዌሽን የተሠሩ ፕሮጀክቶችንና ፖሊሲዎችን የሚመዝንና ለቀጣይ ውሳኔ በቂ የሆነ መረጃ የሚሰጥ መሣሪያ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ድርጅቶች የኢቫሉዌሽን ባለሙያ ይቀጥራሉ ወይ? ሳይንሱን የተማረ ሰውስ ማግኘት ይቻላልን?

አቶ ዮሐንስ፡- ለዚህ ማኅበር መመሥረት ዋናው ምክንያት ይኼ ነው፡፡ በሙያው ላይ የሠለጠኑ ሰዎች በቁጥር ናቸው፡፡ ግምገማ ወይም ምዘና ግን በእያንዳንዱ መሥሪያ ቤቶች ቁልፍ ሥራ ነው፡፡ ይኼንን ሥራ የሚሠሩት ሰዎች እነ ማን ናቸው? ብለን ስናይ ትክክለኛ የኢቫሉዌሽን ትምህርት ያልወሰዱ ከተለያየ ሙያ የተሰባሰቡና በልምድ የሚሠሩ ናቸው፡፡ ሙያው ግን ራሱን የቻለ ሳይንስና ሥልቶች ያሉት በዚያው ሙያ የሠለጠኑ ሰዎችን የሚፈልግ ነው፡፡

ሪፖርተር፡በምዘና ሥራ የተሰማሩ በልምድ የሚሠሩ ሰዎች መሆናቸው  ምን ዓይነት ችግሮችን ያስከትላል፡?

አቶ ዮሐንስ፡- ኢቫሉዌሽን ለውሳኔ የሚያንደረድሩ ውሳኔዎች እንዲሰጡ የሚያደርጉ ሐሳቦችን ይዞ ይመጣል፡፡ አንድን ነገር ከብዙ አቅጣጫ ለማየት ያስችላል፡፡ ትክክለኛውን መንገድ የማይጠቁም ውሳኔ  የት እንደሚያደርስ ይታወቃል፡፡ የኢቫሉዌሽን ትምህርትና ክህሎት በሌለው ሰው የሚሠራ ከሆነ በኪራይ ሰብሳቢነት መጠቃቱ አይቀርም፡፡ ሙያው የእኔ ነው በሚል ባለሙያ ከተሠራ ግን ዋጋ ይኖረዋል፡፡ ትክክለኛ ውሳኔ መስጠትም አይከብደውም፡፡ ሁሉም በልምድ የሚሠሩ ሰዎችን እንዲህ ያደርጋሉ ማለት ባይቻልም አልፎ አልፎ የሚታይ ነው፡፡ ምዘናን ሙያዊ ማድረግ ሰው ለሙያው ሲል የተስተካከለ ሐሳብ እንዲያቀርብ ይረዳዋል ብዬ አስባለሁ፡፡

ሪፖርተር፡የተለያዩ አካላትና ሠራተኞች የሚመዘኑበት ወጥ የሆነ ደረጃ አለ?

አቶ ዮሐንስ፡- የምዘና ሥራ የራሱ የሆነ መሥፈሪያ አለው፡፡ እኛም ይኼንን መሥፈርት እንደ ደረጃ ሆኖ እንዲሠራበት ረቂቅ አዘጋጅተናል፡፡ መንግሥትና የተለያዩ ባለድርሻዎች አውቀውትና አስተያየት ሰጥተውበት እንዲወጣ ትግል እያደረግን ነው፡፡ ለምዘና ደረጃ በጣም ወሳኝ ነገር ነው፡፡ በብዛት ጥቅም ላይ የሚውሉ የተለያዩ አምስት መሥፈርቶች አሉ፡፡ እነሱ ትክክል ናቸው፡፡ ሆኖም ከዚያም በላይ ቢጨመርበት ውጤታማ ያደርጋል፡፡

ሪፖርተር፡- አምስቱ የትኞቹ ናቸው?

አቶ ዮሐንስ፡- አምስቱ የምንላቸው ስኬታማነት፣ አፈጻጸም፣ ቀጣይነት፣ ውጤታማነትና አስፈላጊነት የሚባሉት መሥፈርቶች ናቸው፡፡ ለምሳሌ ወፍጮ ለሴቶች አስፈላጊ ነው ብላ የምታምን፣ እንሰት በብዛት በሚበላበት አካባቢ ወፍጮ ወስዳ ተከለች፡፡ ወፍጮው አስፈላጊ ቢሆንም መተከል የነበረበት ግን ሌላ ቦታ ነበር፡፡ ይኼ ለማኅበረሰቡ ምን ያህል አስፈላጊ ነው? የሚል ጥያቄ ያስነሳል፡፡ ከንድፈ ሐሳብ ጀምሮ እስከ ክንውኑ ድረስ እነዚህን አምስት መሥፈርቶች መሠረት አድርጎ የሚሠራ ሥራ ምዘና (ኢቫሉዌሽን) ይባላል፡፡

ሪፖርተር፡- የምዘና ደረጃ ምን ምን ነገሮችን ይዟል?

አቶ ዮሐንስ፡- የተለያዩ ነጥቦችን ይዟል፡፡ ለምሳሌ የምዘና ሥራ ለመሥራት መሟላትና መከተል ያለባቸውን አካሄዶች አካቷል፡፡ ሌሎችም ተመሳሳይ ነጥቦችን ያካተተ ረቂቅ አዘጋጅተናል፡፡ የመንግሥት አካላት እንዲያዩትና ሐሳብ እንዲጨምሩበት ይደረጋል፡፡

ሪፖርተርግለሰቦችና ድርጅቶች የሚመዘኑት በተመሳሳይ መሥፈርት ነው ወይስ የተለያየ ነው?

አቶ ዮሐንስ፡- የተለየ ነገር የለም፡፡ ሁሉም ተመሳሳይ ነው፡፡ ትልቁ ነገር አምስቱ መለኪያዎች መሟላታቸው ነው፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚሠራበትና በየትኛውም ቦታ መሣሪያ ሆነው ማገልገል የሚችሉ ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- በተለያዩ የሙያ መስኮች በምዘና ዘርፍ የሚሰማሩ ከሚሠሩበት መሥሪያ ቤት ለምሳሌ የሕክምና ተቋም ከሆነ ለሕክምና መዛኞች ተብሎ የሚሰጥ ተጨማሪ ትምህርት አለወይስ የምዘና ትምህርት መማራቸው ብቻ በቂ ነው?

አቶ ዮሐንስ፡- በየሴክተሩ የሞኒተሪንግና ኢቫሉዌሽን ኮርስ ይኖራል፡፡ ለምሳሌ እኔ ዴቨሎፕመንት ኢኮኖሚክስ ተምሬያለሁ፡፡ በዴቨሎፕመንት ኢኮኖሚክስ ፕሮጀክት ማኔጅመንት፣ ፕሮጀክት ሞኒተሪንግ ኤንድ ኢቫሉዌሽን የተባሉ ኮርሶች ይሰጣሉ፡፡ በጤናውም እንደዚሁ ጤናውን የሚከታተሉበትና የሚቆጣጠሩበት መንገዶች ይኖራሉ፡፡ የተሟላ ነው ማለት ባይቻልም አንዳንድ ጥሩ ጅምሮች አሉ፡፡ ለምሳሌ ጅማ ዩኒቨርሲቲ የጤናን ሥራ በተመለከተ ብቻ ሞኒተሪንግ ኤንድ ኢቫሉዌሽን በማስተርስ ዲግሪ ፕሮግራም ጀምሯል፡፡ አንድ ሴክተር መሆኑ እንጂ ጅምሩ መልካም ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በአገሪቱ የኢቫሉዌሽን ትምህርት የሚሰጥባቸው ተቋማት አሉ?

አቶ ዮሐንስ፡- ዩኒቨርሲቲዎቻችን ከሌሎች ጎረቤት አገሮች በተለየ ለሙያው አነስ ያለ አመለካከት እንዳላቸው ታዝቤያለሁ፡፡ ለምሳሌ በኬንያ ሰባት ዩኒቨርሲቲዎች በሞኒተሪንግና ኢቫሉዌሽን ብቻ በድኅረ ምረቃ ትምህርት ይሰጣሉ፡፡ ዮጋንዳ፣ ታንዛኒያና ደቡብ አፍሪካ በዲግሪና ማስተርስ ፕሮግራም ያስተምራሉ፡፡ ይኼ ምን ያህል ለጉዳዩ ትኩረት እንደሰጡት የሚያሳይ ነው፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ስንመጣ ግን በጣም ወደ ኋለ ቀርቷል፡፡ በኢቫሉዌሽን ሙያ ትምህርት የሚሰጥ የትምህርት ተቋም ከጅማ ዩኒቨርሲቲና ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በስተቀር የለም፡፡ ይኼ ዘርፍ ግን ትልቅ ዋጋ አለው፡፡ ስለዚህ ዩኒቨርሲቲዎቻችን ነቃ ማለት አለባቸው፡፡ እያንዳንዱ ድርጅት የግድ በዚህ ሙያ የሠለጠነ ሰው ያስፈልገዋል፡፡ ይኼ ሙያ ለአንድ ወንበር አራተኛ እግር ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ዩኒቨርሲቲዎቻችን ይኼንን አስበው ትኩረት ቢሰጡት እላለሁ፡፡ አንድ አገር ከዚህ ደረጃ ተነስታ እዚህ ደረሰች ለማለት መመዘን ያለባቸው ነገሮች አሉ፡፡ በአገሪቱ ያለው ፈጣን ዕድገትም ፈጣን የሆነ ምዘና ያስፈልገዋል፡፡ ስለዚህ የመንግሥትም ሆኑ የግል የትምህርት ተቋማት የኢቫሉዌሽን ትምህርት ማስተማር መጀመር አለባቸው፡፡ ሙያው በጣም ተፈላጊ ነው፡፡ ለምሳሌ አንዱ በሞኒተሪንግና ኢቫሉዌሽን ሙያ የተማረ አይደለም እንበል፡፡ የሚሠራው ግን የሞኒተሪንግና ኢቫሉዌሽን ሥራ ነው፡፡ ይኼ የሚሆነው የባለሙያ የእጥረት ስላለ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በልምድ በሚሠሩና ትምህርቱን ተምረው ሳይንሱን አውቀው በሚሠሩ መካከል ያለው ልዩነት ምንድነው?

አቶ ዮሐንስ፡- ሙያው የራሱ የሆነ ዲሲፕሊን አለው፡፡ ፕሮግራሞች የሚታዩት በተለየ መነፅር ነው፡፡ በምሠራበት ድርጅት ውስጥ የፕሮግራም ሰዎች አሉ፡፡ የሞኒተሪንግና ኢቫሉዌሽን ሰዎችም አሉ፡፡ እኛ ፕሮራሞችን የምናይበትና እነሱ የሚያዩበት ዓይን የተለያየ ነው፡፡ እነሱ ይኼንን ያህል ሥራ ሠራን ይላሉ፡፡ እኛ ደግሞ እዚያ ጋር አንቆምም ከዚያስ ምን ለውጥ መጣ እንላለን፡፡ ስለዚህ እኛና ሌላው ነገሮችን የምናይበት መንገድ በጣም የተለያየ ነው፡፡ ሳይንሱን ተምረው የሚሠሩ ሰዎች ደግሞ ከእኛ የተሻሉ ይሆናሉ፡፡ የእኛም ጥረት ሴክተሩ ሳይንሱን ባጠኑ ባለሙያዎች እንዲመራ ማድረግ ነው፡፡ 

ሪፖርተር፡- ሙያው በልምድ በሚሠሩ ሰዎች መመራቱ አገሪቱን ምን ያህል ዋጋ  እያስከፈላት ይገኛል?

አቶ ዮሐንስ፡- ይኼንን ያህል የገንዘብ ኪሳራ እያደረሰ ይገኛል ለማለት ጥናት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ነገር ግን በሚታየው ነገር ላይ ተመሥርቶ መናገር ይቻላል፡፡ ለምሳሌ በየዓመቱ የመንግሥት ፕሮጀክቶች ይገመገማሉ፡፡ የሚገመገሙበት መንገድ ግን  ትክክለኛ ሳይንሱን የተከተለ ነው አልልም፡፡ ዕቅድን ከአፈጻጸም ጋር ብቻ አይቶ ማለፉ ኢቫሉዌሽን ሳይሆን ክትትል ነው፡፡ ክትትልና ግምገማ ደግሞ ይለያያሉ፡፡ ግምገማ ይኼ ነገር ተከናውኗል፣ ግን ምን ለውጥ አመጣ? የሚለውን ማየት ነው፡፡ ለምሳሌ የመንገድ ችግር ባለበትና መኪኖች በሚጨናነቁበት አካባቢ መንገድ መገንባት ሲገባ ብዙ ተጠቃሚ በሌለው ቦታ ላይ መንገድ ቢገነባ ሥራው ተከናውኗል ነገር ግን ኅብረተሰቡን ጠቅሟል ወይ? ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል ወይ? አስፈላጊ ነው ወይ? የሚሉት ጥያቄዎችም መነሳት አለባቸው፡፡ የማኅበረሰቡ ፍላጎት ያልሆኑ ፕሮጀክቶች እየተፈጸሙ ሊሆን ይችላል፡፡ እነኚህን ማየት የሚችለው ጥሩ የሆነ የኢቫሉዌሽን ዕይታ ያለው ባለሙያ ሲኖር ነው፡፡ ነገር ግን ይኼ በሌለበት በሚካሄድ ግምገማና በሚወጣ ሪፖርት ላይ ተመሥርቶ ይኼ ፕሮጀክት ይቀጥል! ይቋረጥ! ብሎ መወሰን ስህተት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ግምገማ በየምን ያህል ጊዜ መደረግ አለበት ብለው ያምናሉ?

አቶ ዮሐንስ፡- ግምገማ መካሄዱ በጣም ጥሩ ነገር ነው፡፡ ምን ሠራሁ? ምን አመጣሁ? ከተያዘው ዕቅድ አንፃር ምን ያህሉን ሠራሁ? ብሎ መመዘን የሚቻልበት ነው፡፡ ነገር ግን ቃሉ ይሁን ሌላ በማኅበረሰቡ ውስጥ ስለ ግምገማ ጥሩ አመለካከት የለም፡፡ ግምገማ በመጥፎ ጎኑ መታየት የለበትም ምን እየሠራሁ ነው? ለምን? እና የመሳሰሉትን መሠረታዊ ነገሮች የምናሳይበት ነው፡፡ በበጎ ጎኑ አለመታየቱ ያሳዝነኛል፡፡ ይኼ እንዲሆን ያደረግነው እዚያ ውስጥ ያለን ሰዎች ልንሆን እንችላለን፡፡ ይሁንና ካለው ጠቀሜታ አንፃር ግምገማ በየዓመቱ ቢደረግ ጥሩ ነው፡፡ ነገር ግን ከዋጋ አንፃር በጣም ውድ ሊሆን ይችላል፡፡ ስለዚህም የአምስት ዓመት ዕቅድን በሁለት ዓመት ተኩል ላይ መገምገም ከዋጋም ከዕቅዱም አፈጻጸምም አንፃር አዋጭ ነው፡፡