Skip to main content
x
‹‹የስደትን አደጋ ለመቀነስና ጥቅሙንም ለማስፋት የፖለቲካውን አጥር እንደምንም አስወግዶ መነጋገር ያስፈልጋል››

‹‹የስደትን አደጋ ለመቀነስና ጥቅሙንም ለማስፋት የፖለቲካውን አጥር እንደምንም አስወግዶ መነጋገር ያስፈልጋል››

አቶ ዮርዳኖስ አልማዝ ሰይፉ፣ የማኅበራዊ ጉዳዮች ተመራማሪ

አቶ ዮርዳኖስ አልማዝ ሰይፉ በጂማ ዩኒቨርሲቲ የመጀመርያ ዲግሪያቸውን በምጣኔ ሀብት (ኢኮኖሚክስ) ዘርፍ ይዘዋል፡፡ ከዚያ በኋላ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሁለተኛ ዲግሪያቸውን በሥነ ሕዝብ፣ እንዲሁም ጀርመን በሚገኘው ኦልድንበርግ ዩኒቨርሲቲ ሌላ ሁለተኛ ዲግሪ በስደትና የባህል ግንኙነት (Migration and Intercultural Relations) ላይ ወስደዋል፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽንን ጨምሮ ከተለያዩ ዓለም አቀፍና የአገር ውስጥ ድርጅቶች ጋር በማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ በአማካሪነትና በተመራማሪነት ሠርተዋል፡፡ የምርምር ሥራዎቻቸው የሚያተኩሩት በሥነ ሕዝብ፣ በአካባቢ ጥበቃ፣ በወጣቶችና በስደት ላይ ሲሆን፣ በእነዚህ ጉዳዮች ከዚህ ቀደም ሁለት መጻሕፍትንና የተለያዩ ጥናታዊ ጽሑፎችን በእንግሊዝኛ ቋንቋ ለንባብ አብቅተዋል፡፡  በቅርቡ የመመረቂያ ጽሑፋቸውን መነሻ በማድረግ ‹መንገደኛ› በሚል ርዕስ ያዘጋጁት መጽሐፍ በስደት ጉዳይ ላይ መወያያ አጀንዳዎችን ከማስፋቱም በላይ፣ አቀራረቡ በጣም ቀለል ያለና በሥነ ጽሑፋዊ ለዛ የተዋዛ በመሆኑ ተወዳጅ ለመሆን ችሏል፡፡ ሰለሞን ጎሹ በመጽሐፋቸውና ከስደት ጋር በተገናኙ ጉዳዮች ላይ አቶ ዮርዳኖስን አነጋግሯቸዋል::

ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ በእናት ስም መጠራት ብዙም አልተለመደም፡፡ አቶ ዮርዳኖስ አልማዝ በእናትዎ ስም መጽሐፉን ለማሳተም ለምን መረጡ?

አቶ ዮርዳኖስ፡- ፓስፖርቴ ላይ ያለው ስም ዮርዳኖስ ሰይፉ እስጢፋኖስ ነው የሚለው፡፡ የልደት ሰርተፍኬቴም ሆነ የትምህርት ማስረጃዎቼም ላይ ያለው ይኼው ስም ነው፡፡ መጽሐፉ ላይ አልማዝን ያስገባሁት እናቶችን ለማክበርና የምሥጋና መልዕክት ለማስተላለፍ ነው፡፡ እንዲያውም በአንድ ወቅት አንድ ትልቅ ሰው ‘እንዴት በእናትህ ስም ትጠራለህ?’ ብለው ጠየቁኝ፡፡ ‘ልጅ በአባቱስ ስም ይጠራ የለም እንዴ’ ስላቸው ስቀው አለፉት፡፡ እናቶች ግን ከዚህም በላይ ዋጋ ይገባቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ‹መንገደኛ› የሁለተኛ ዲግሪ ማሟያ ጥናትዎን መነሻ በማድረግ የጻፉት መጽሐፍ ነው፡፡ ነገር ግን መጽሐፉ ከአካዳሚያዊ ጽሑፍ በተቃራኒ እጅግ ቀለል ብሎና በሥነ ጽሑፋዊ ለዛ ተዋዝቶ የተዘጋጀ ነው፡፡ በጥናትዎና በመጽሐፉ መካከል ያለው መሠረታዊ ልዩነት ምንድን ነው?   

አቶ ዮርዳኖስ፡- ጥናቱን ለመሥራት ብዙ መንገድ ተጉዣለሁ፣ ብዙ ውጣ ውረዶች አልፌያለሁ፡፡ በስደት ላይ ትምህርቴን የተከታተልኩት ጀርመን ቢሆንም አንድ ኮርስ ኖርዌይ ወስጃለሁ፡፡ ተማሪዎች ለኢንተርንሽፕ ወደ ተለያዩ የዓለም ክፍሎች እንበታተን ነበር፡፡ ብዙዎቹ የክፍል ጓደኞቼ አውሮፓን፣ አሜሪካን እንዲሁም የምሥራቅ አፍሪካ አገሮችን የመረጡ ሲሆን፣ እኔ ግን ጥናቴንና ኢንተርንሺፔን አንድ ላይ ለማድረግ የተሻለ ሆኖ ያገኘሁት ደቡብ አፍሪካን ነው፡፡ ክፍል ውስጥ ከምታገኘው ዕውቀት ይልቅ በጉዞ ሒደት የምታገኘው ብዙ ነው፡፡ ሁለቱ አንድ ላይ ሲቀናጁ የበለጠ ውጤታማ ይሆናሉ፡፡ መጽሐፉ የጉዞ ገጠመኞቸንና የጥናት ውጤቴን አንድ ላይ አጣምሮ የያዘ ነው፡፡ አብዛኛው ሰው ሲጓዝ የሚገጥመውንና ብዙም የማይነገረውን የባህል ግጭትን ጨምሮ የተለያዩ ገጠመኞችን ያቀርባል፡፡ ከዚያው በተጓዳኝ የተጠቀምኩት የጥናት ሒደት ሰውኛ (Ethnographic) ነበር፡፡ ይህን መንገድ ስትጠቀም ዝም ብለህ የምትፈልገውን መረጃ ለማግኘት ወደ ቃለ መጠይቅ አትገባም፡፡ መጀመርያ ከምታነጋግራቸው ሰዎች ጋር ማኅበራዊ ግንኙነት በመፍጠር እንዲቀበሉህና እምነት እንዲጥሉብህ ማድረግ አለብህ፡፡

ይኼ ትክክለኛ መረጃ ለማግኘት አስፈላጊ ነው፡፡ ደቡብ አፍሪካ አጠቃላይ የቆየሁት ለሦስት ወራት ነው፡፡ የመጀመርያውን አንድ ወር ይህን ቅድመ ዝግጅት ስፈጥር ነው ያሳለፍኩት፡፡ ይህ መረጃ እንዳታገኝ መንገድ የሚዘጉብህና ወደ መረጃ ቋት እንዳትዘልቅ የሚያግዱህ  እንደ መረጃ በር ጠባቂዎች (Gatekeepers) ያሉ ግለሰቦችን እምነት ማግኘትን ይጨምራል፡፡ በዚህ ሁሉ ሒደት የሰበሰብኩት መረጃ ተጠቃሎ ሲታይ ለሁለተኛ ዲግሪ ማሟያ ጥናት ከሚያስፈልገው በላይ ሆነ፡፡ ጥናቱ ሁለተኛው ምርጥ ጥናት ተብሎ ቢመረጥም፣ ሦስት አካዳሚያዊ አርቲክሎችም ጥናቱን መሠረት አድርገው ቢታተሙም፣ ዋናው ጥናት እዚያው ጀርመን ሼልፍ ላይ ነው ቁጭ ያለው፡፡ እርግጥ በቅርቡ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ታትሞ ለዓለም አቀፍ ገበያ ቀርቧል፡፡ ይኼ መረጃ ግን እዚህ ላለው ማኅበረሰብ፣ ፖሊሲ አውጪዎችና አንባቢያን መድረስ አለበት በሚል ተነሳሽነት ነው መጽሐፉን ያዘጋጀሁት፡፡ ስለሆነም ጥናቱ በአካዴሚክ ዓለምና በመደበኛ አንባቢያን፣ እንዲሁም በአካዴሚክ ዓለምና ፖለቲካዊ ውሳኔ ሰጪዎች መካከል ያለውን የግንኙነት ክፍተት ያጠባል የሚል ግምትም አለኝ።

ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያም ሆነ በውጭ በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች በአንገብጋቢ ወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ጥናትና ምርምር የሚያደርጉ ኢትዮጵያዊያን ጥናታቸው ሼልፍ ላይ ተቀምጦ እንዳይቀር ለመታደግ መጠነኛ የአርትኦት ሥራ ሠርተው በእንግሊዝኛ ቋንቋ በመጽሐፍ ሲያሳትሙ ቢስተዋሉም፣ ለአገር ውስጥ አንባቢያን እንዲስማማ በማድረግ በአማርኛ ቋንቋ ሲያሳትሙ አይታዩም፡፡ እርስዎ ይህንን ልማድ ለመስበር ያነሳሳዎት ስደት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገራችን ላይ እያስከተለ ያለው ጉዳት ትልቅ የመወያያ አጀንዳ መሆኑ ነው? ወይስ ይህን ልማድ ለመቀየር ያለዎት የግል ፍላጎት? 

አቶ ዮርዳኖስ፡- በከፊል በሁለቱም ምክንያቶች ነው፡፡ ስደት በጣም አንገብጋቢ ጉዳይ ነው፡፡ አሁን ያለው ጊዜ የስደት ዘመን እስከ መባል ደርሷል፡፡ ከአፍሪካም ሆነ ከተለያዩ የዓለም አካባቢዎች እንደ አሁን ዘመን ስደት ተባብሶ አያውቅም፡፡ ሁኔታውንም ስታይ ቀጣይነት አለው፡፡ ሆኖም የእኔ ጥናት ወደ ኅብረተሰቡ ስለደረሰ ስደትን እቀይራለሁ ማለት ውኃ አያነሳም፡፡ ከችግሩ ስፋት፣ ጥልቀትና ብዛት አንፃር ስደት በተቋም ደረጃ ነው ሊጠናና ውይይት ሊደረግበት የሚገባው፡፡ ይኼ ጥናት ምናልባትም እንደ መነሻ ሊሆን ይችላል፡፡ ሜሪ አርምዴ በአንድ ዘፈኗ፣ ‹‹ተምሮ ተምሮ ቤት ካልሠሩበት፣ እንዴት ያሳዝናል ሲባክን ዕውቀት›› ብላለች፡፡ ሁለት ዓመት ስለስደት ተምሬያለሁ፡፡ ለዚሁ ሥራ በተለያዩ ቦታዎች ተዘዋውሬያለሁ፡፡ በጉዳዩ ላይ ከብዙ ሰዎች ጋር ተነጋግሬያለሁ፡፡ በዚህ ሁሉ ሒደት ያገኘሁትን ዕውቀት ይዤው ቁጭ ካልኩ ምንም ጥቅም የለውም፡፡ ሜሪ ‹ቤት› ያለችው አገርና ማኅበረሰብ ለማለት ይመስለኛል፡፡ ስለዚህ መጽሐፉን ያሳተምኩት በዋነኛነት ያገኘሁትን ዕውቀት ለመወርወር ነው፡፡ ነገር ግን ከእኔ በላይ የተጓዙ፣ የተማሩ፣ ብዙ ዕውቀት ያላቸውና ሕይወት ያስተማራቸው በርካታ ሰዎች አሉ፡፡ እነሱ ያንን ዕውቀት ይዘውት ቁጭ ብለዋል፡፡ ሌላው ተቆስቁሶና ተነሳስቶ ታሪኩንና ዕውቀቱን ለማድረግም ነው ይህን ሥራ የሠራሁት፡፡ እነዚህ ሰዎች በስደት ላይ ብቻ ሳይሆን በሌላውም ዘርፍ ያላቸውን ዕውቀት ቢያካፍሉ አዲስ አዝማሚያ ይሆናል፡፡ የተሻለ ዕውቀት፣ ማኅበረሰብና አገር ለመገንባት ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡   

ሪፖርተር፡- በመጽሐፉ ወደ ደቡብ አፍሪካ ስለሚደረገው ስደት፣ የሚያስከትላቸው ተፅዕኖዎችና ጉዳቶች ከብዙ አቅጣጫ በጥልቀት ተዘርዝረው ቀርበዋል፡፡ በሦስት ወራት ጊዜ ውስጥ እነዚህን ታሪኮችና መረጃዎች በዚህ መጠን ማግኘት አዳጋች አልነበረም?

አቶ ዮርዳኖስ፡- መጀመርያ ለማጥናት ሳስብ ሰፊ የጥናት ማዕቀፍ (Framework) ነው ያዘጋጀሁት፡፡ ማዕቀፉን የምታዳብረው በርዕሰ ጉዳዩ ላይ የተጻፉ የምርምር ሥራዎችን በማንበብ ነው፡፡ በንባቤ አንድ የጥናት ማዕቀፍ ጎልቶ ወጥቶ ታየኝ፡፡ ይህም ፖለቲካል ኢኮኖሚ ነው፡፡ በዓለም ላይ ያሉትን ስደተኞች የፖለቲካና የኢኮኖሚ ስደተኛ ብሎ መመደብ የተለመደ ነው፡፡ እሱን ደግሞ የሚቃወሙ አካላት አሉ፡፡ ከአማካሪዬ ጋር በመመካከር ፖለቲካል ኢኮኖሚ ለጥናቴ የተሻለ ማዕቀፍ ይሰጠኛል የሚል ድምዳሜ ላይ ደረስኩ፡፡ የፖለቲካል ኢኮኖሚ ማዕቀፍ፣ ስደት እንዴት እንደሚከናወንና የትኞቹ አካላት ተዋንያን እንደሆኑ ሰፋ አድርገህ እንድታይ ያደርግሃል፡፡ ይኼ እንዳለ ሆኖ ስለሰዎች ስለማጠና አቀራረቡ ሰውኛ እንዲሆን አድርጌዋለሁ፡፡ ሰውኛ የጥናት ሒደት ራሳቸው ስደተኞቹን፣ ደላሎቹንና ሌሎች ተዋንያንን እንድታገኛቸው ያደርግሃል፡፡ ይበልጥ ለማዳበር ደግሞ ታሪካዊ ገጽታውን ወደ ኋላ ተመልሼ ለማየት ሞክሬያለሁ፡፡

ለምሳሌ የደርግ መንግሥት መውደቅና የኢሕአዴግ መንግሥት መምጣት አንድ ታሪካዊ ክስተት ነው፡፡ በደርግ ጊዜ እንኳን ከአገር መውጣት አገር ውስጥ መንቀሳቀስ ራሱ ከባድ ነበር፡፡ በአንፃሩ የኢሕአዴግ መንግሥት ደርግን ሲተካ የመንቀሳቀስ መብት ተፈቀደ፡፡ በደቡብ አፍሪካ በኩልም በአፓርታይድ ጊዜ የነፃነት ታጋዮች ራሳቸው ስደተኞች ነበሩ፡፡ በዚህም የተነሳ ታግለው የአፓርታይድን ሥርዓት ከገረሰሱ በኋላ ወደ ሥልጣን ሲመጡ በጣም ሊበራል የሆነ የስደት ፖሊሲ ነው የተቀረፀው፡፡ እነዚህ ሁለት ግጥምጥሞሾች ስደትን እንዴት እንደሚቀርፁት ያሳይሃል፡፡ ይኼ በንባብ ሲታገዝ የተሻለ ሥዕል ይሰጥሃል፡፡ በዚህ ውስጥ ለተለያዩ ተዋንያን የምታቀርባቸው ጥያቄዎች ይበልጥ ግልጽ ይሆኑልሃል፡፡ ሌላ እንዲሁ የምትረዳው ነገር አንድ ስደተኛ ከኢትዮጵያ ተነስቶ ደቡብ አፍሪካ ሲገባ በሒደት የተለያየ ዓይነት የባህሪ ለውጥ እንደሚያመጣ ነው፡፡ እሱም ሌላ ግኝት ይሰጥሃል፡፡ ሌላው በዚህ መጽሐፍ ለመመለስ ያልቻልኩት ጥያቄ ደግሞ ግሎባላይዜሽን ወይም አሁን ዓለም የምትመራበት የፖለቲካል ኢኮኖሚ አቀራረብ እንዴት ነው ሥራ ላይ የሚውለው? እንዴት ስደተኞችንና ደላሎችን ይፈጥራል? የሚለው ነው፡፡ በግሎባላይዜሽን ማዕቀፍ ውስጥ ደግሞ የሕግ፣ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማዕቀፎች አሉ፡፡ የእነዚህ ማዕቀፎች ቅንጅት ሌላ ሥዕል ይሰጥሃል፡፡ እና እነዚህ በመጽሐፉ ውስጥ የተካተቱት ጉዳዮች በዚህ ሰፊ ማዕቀፍ ውስጥ የተጣሉ ናቸው፡፡   

ሪፖርተር፡- መጽሐፍዎን አንብቤ ስጨርስ በደቡብ አፍሪካ አፓርታይድ አሁንም እንዳለ ነው የተሰማኝ፡፡ ደቡብ አፍሪካ ከመሄድዎ በፊት ስለኔልሰን ማንዴላ አስተዋጽኦ፣ ስለአገሪቱ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ሥርዓት፣ እንዲሁም ስለጥቁር ዜጎች አሠፋፈርና የኑሮ ደረጃ የነበረዎት መረጃና ዕውቀት በተግባር ካገኙት እውነታ ጋር ምን ያህል የተራራቀ ነበር?

አቶ ዮርዳኖስ፡- ደቡብ አፍሪካ ከመሄዴ በፊት የማንዴላን መጽሐፍ ‹‹A Long Walk to Freedom›› አንብቤ ነበር፡፡ በጣም ደስ በሚል ቋንቋ የተጻፈ አማላይ መጽሐፍ ነው፡፡ ማንዴላን እንድትወደው፣ እንድታከብረውና እንድታደንቀው፣ ከዚያም አልፈህ እንድታመልከው የሚያደርግህ ዓይነት መጽሐፍ ነው፡፡ ይኼ ስለደቡብ አፍሪካ ሙሉ በሙሉ የተሳሳተ ሳይሆን ሚዛኑን ያልጠበቀ ሥዕል ይሰጥሃል፡፡ ያንን ሥዕል ይዘህ ነው የምትሄደው፡፡ አፓርታይድ ማለት በቀለምና በኢኮኖሚ ጀርባ ተከፋፍለው የሚኖሩ ሰዎች ማለት ነው፡፡ በአፓርታይድ ጊዜ ጥቁሮች ለብቻ ነበር የሚኖሩት፡፡ ይኼ አሁንም አለ፡፡ የማንዴላን ስኬት ለማንኳሰስ አይደለም፡፡ እሱ ብቻውን ታግሎ የሆነ ነገር አምጥቷል፡፡ ማንዴላም በመጽሐፉ ላይ ‹አንዱን ተራራ ከወጣችሁ በኋላ ሌላ ተራራ ይጠብቃችኋል› ብሏል፡፡ ነፃነት የትግሉ መጨረሻ እንዳልሆነ፣ እንዲያውም ነፃነት አደጋ እንዳለውና ከነፃነት በኋላም ነፃነት ያስፈልጋል የሚል መደምደሚያም ሰጥቷል፡፡ ስለማንዴላ አስተዋጽኦ ምሁራን ለሁለት ተከፍለው ይከራከራሉ፡፡ በዚህ መጽሐፍ ላይ ግን ሁለት የጎዳና ተዳዳሪዎች ናቸው እነዚህን የሚጋጩ ዕይታዎች የሚያንፀባርቁት፡፡

ከነፃነት በኋላ ቃል የተገቡ ብዙ ነገሮች ነበሩ፡፡ ለምሳሌ በጥቁሮችና በነጮች መካከል ያለው የኑሮ ደረጃ እንዲቀንስ ማድረግ አንዱ ቃል የተገባ ጉዳይ ነው፡፡ መሬት ላይ ስታየው ይኼ አልተደረገም፡፡ ጥቂት በገዥው ፓርቲ አፍሪካን ናሽናል ኮንግረስ (ኤኤንሲ) ዙሪያ ያሉ ጥቁር ደቡብ አፍሪካውያን የኢኮኖሚ አቅማቸው ጨምሮ፣ አብዛኛው ጥቁር ደቡብ አፍሪካዊ ግን የኢኮኖሚ አቅሙ ከመጀመርያው በታች ሆኗል፡፡ አሁን በነጮችና በጥቁሮች መካከል ብቻ ሳይሆን በጥቁሮችም መካከል የኢኮኖሚ አፓርታይድ ተፈጥሯል፡፡ በየመንገዱ በሱስ የተጠመዱ፣ ሥራ ያጡና በልመና የሚተዳደሩ ወጣቶችና ጎልማሶች ጥቁር ደቡብ አፍሪካዊያንን ስታይ ትደነግጣለህ፡፡ አሁን ድረስ ‹ታውንሺፕ› የሚሏቸው ቦታ ስትሄድ የሚኖሩት ጥቁሮች ብቻ ናቸው፡፡ ድህነቱ በጣም አሰቃቂ ነው፡፡ ሕገወጥ መሣሪያና አደንዛዥ ዕፅ አለ፡፡ የጥቁሮች ሥራ አጥነት የትየለሌ ነው፡፡ የፖለቲካ ነፃነት ያግኙ እንጂ የኢኮኖሚ ነፃነታቸው አሁንም ድረስ የነጮች የበላይነት ነው ያለው፡፡ ጥቁሮች አሁንም አገልጋይ ሆነው ነው የቀጠሉት፡፡ የባንቱ የትምህርት ሥርዓት ጥቁሮችን አገልጋይ እንዲሆኑ አድርጎ ነው የሚቀርፃቸው፡፡ ከፍ ብለው በጊዜ ሒደት እየተሻሻሉ ከኢኮኖሚ አንፃር የሆነ ቦታ የሚያገኙ ጥቁር ደቡብ አፍሪካዊያን ቁጥር በጣም አናሳ ነው፡፡ ከእነሱ ይልቅ ስደተኞች የተሻለ የኢኮኖሚ ደረጃ አላቸው፡፡ ለዚህም ነው ኢትዮዽያዊያን ደቡብ አፍሪካ በገቡ በሁለተኛና በሦስተኛ ዓመታቸው ጥቁር ደቡብ አፍሪካዊያንን፣ እንዲሁም ከጎረቤት አገሮች የሚመጡ ጥቁር አፍሪካውያን እህቶቻቸውንና ወንድሞቻቸውን በሥራቸው ቀጥረው የሚያሠሩት፡፡

ስለማንዴላም ሆነ ስለደቡብ አፍሪካ ፊት የያዝከውን ዕውቀት መሬት ላይ ካለው እውነታ ጋር ለማመዛዘን ስትሞክር ማንዴላን የናቅህ ያስመስልሃል፡፡ በተለይ ስለማንዴላ እውነቱን ስታቀርብ የተዛባ እውነት የያዘ ሰው ቅር ይለዋል፡፡ ደቡብ አፍሪካን ከማያባራ ብጥብጥ እንደታደጋት በስፋት የሚነገርለትና የጥቁር ደቡብ አፍሪካውያን ታጋይና የነፃነት ቀንዲል ተደርጎ የሚወሰደው ማንዴላ፣ መሀል ጆሃንስበርግ ላይ በስሙ ትልቅ ድልድይ ተሰይሞለታል። በድልድዩ ላይ ነጭ ዲታዎች ውልውል መኪናቸውን ያሽከረክራሉ። ከድልድዩ ሥር ደግሞ ጥቁር ደቡብ አፍሪካውያን በጎዳና ተዳዳሪነት ሕይወታቸውን ይመራሉ። ቪላካዚ ስትሪት የምትባል ቦታም አለች፡፡ የማንዴላና የዴዝሞንድ ቱቱ ቤቶች እዚያ ነው የሚገኙት፡፡ ለዚህም ነው ሁለት የሰላም ኖቤል ሽልማት ያሸነፉ ሰዎች የሚኖሩባት ብቸኛው መንገድ ተብሎ በጊነስ ቡክ ኦፍ ሪከርድስ ላይ የሠፈረው፡፡ እዚያ ቦታ ስትሄድ ግን ሰላም የሚባል ነገር የለም፡፡ መሬት ላይ ይኼ ተቃርኖ አለ፡፡ በዚህ ምክንያት ለውጥ ቢኖርም አፓርታይድ አሁንም ያበቃ አይመስለኝም፡፡ 

ሪፖርተር፡- በመጽሐፍዎ ችግሩ አስቀድሞ እንደነበር ቢገልጹም ጥቁር ደቡብ አፍሪካዊያን በስደተኞች ላይ የሚፈጽሙት ዘግናኝና ኢሰብዓዊ የሆነ ጥቃት የዓለምን ትኩረት ያገኘው በቅርብ ዓመታት ነው፡፡ አሁን ላሉበት ችግርና መከራ የዳረጓቸውን ነጭ ደቡብ አፍሪካዊያኑን ሳይነኩ ጥቁር ወንድሞቻቸው ላይ እንዲህ ዓይነት ሰውን በሕይወቱ እስከማቃጠል የሚያደርስ ግፍ ለመፈጸም ያነሳሳቸው ምንድነው?

አቶ ዮርዳኖስ፡- ባህል ከባድ ነገር ነው፡፡ በአፓርታይድ ጊዜ የነበሩ አሠራሮች በጊዜ ሒደት ባህል እየሆኑ መጥተዋል፡፡ ለምሳሌ በአፓርታይድ ጊዜ መብታቸውን ለማስከበር ያደርጉት የነበረው አንዱ ነገር ሰላማዊ ሠልፍ ነው፡፡ እየጮሁ የሚፈልጉትን ነገር ይናገራሉ፡፡ ይኼ ነገር አፓርታይድ ካበቃ በኋላ ባህል ሆኖ ቀጥሏል፡፡ በአፓርታይድ ጊዜ ጠላቴ ነው ብለህ የምታስበውን ሰው አንገቱ ላይ እንደ ሀብል ጎማ አንጠልጥለህ ጋዝ አድርገህ ማቃጠል የተለመደ ነበር፡፡ ነጮች ላይ ይደረግ የነበረው አመፅ አንድ አካል ነበር፡፡ ዊኒ ማንዴላ በተግባር ፈጽማዋለች፡፡ ይህ ድርጊት ባህል ሆኖ በተለያዩ ታውንሺፖች ይደረጋል፡፡ አንድ ኢትዮጵያዊ ስደተኛ ላይ ጎማ ተደርጎ ሲቃጠል የሚያይ ሰው እዚህ ሊደነግጥና ሊያር ይችላል፡፡ ግን ፊት የነበረና ሲንከባለል የመጣ ባህላቸው ነው፡፡ አገራችሁ ሀብታም ናት፣ ነፃ ወጥታችኋል የተባሉ ጥቁር ደቡብ አፍሪካዊያን ሲያገለግሉት የቆዩትን ዓይነት ሕይወት የመኖር ጉጉት አድሮባቸው ነበር፡፡ ኤኤንሲ ወደ ሥልጣን ሲወጣ የትምህርትና የሥራ ዕድል ለመፍጠር፣ ቤት ለመሥራትና ሌላ ሌላም ቃል ገብቶ ነበር፡፡ ይህን ባለው መጠን አላከበረም፡፡ በሰው ፍላጎትና ባለው ሀብት መካከል አለመመጣጠን ተፈጠረ፡፡

ከዚህም በላይ አሁን ሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት አገሪቷ ላለባት ረዥም ጊዜ ሲንከባለል ለኖረ ችግር የውስጥ ዲያቢሎሶቹን በመዘንጋት ስደተኞችን እንደ ማስቀየሻ ይጠቀምባቸዋል፡፡ ላለው የሥራ አጥነት ተጠያቂዎቹ ስደተኞች ናቸው፤ ለወንጀል መበራከትም ተጠያቂዎቹ ራሳቸው ናቸው በማለት ያስቀይሳል፡፡ ይኼን የሰሙ የዋህ ጥቁር ደቡብ አፍሪካዊያን ስደተኞች ላይ ዓይናቸውን ማፍጠጥ ጀመሩ፡፡ ሰላማዊ ሠልፉ በጣም ደስ በሚል ሁኔታ ነው የሚጀምረው፡፡ ኅብረ ዝማሬው በጣም ደስ ይላል፡፡ ድንገት ግን ተቀይሮ ወደ ብጥብጥና ግጭት ይሸጋገራል፡፡ ይህ ሲፈጠር ያን ሁሉ ጉዳት ያደረሱባቸው ነጮችና ያን ሁሉ ቃል የገቡላቸው ባለሥልጣናት አጠገባቸው የሉም፡፡ አጠገባቸው ያሉት ሕይወታቸውን ለማሻሻል ከተለያዩ የአፍሪካ አገሮች የመጡ ስደተኞች ናቸው፡፡ እነዚህ ስደተኞች የተሻለ የኢኮኖሚ ደረጃ ላይ እንደሆኑ ሲያዩ ዕቃቸውን መዝረፍና ጉዳት ማድረስ ጀመሩ፡፡ 

ሪፖርተር፡- በአንድ በኩል ስደትን የሚያቀሉ ሁኔታዎች እየተበራከቱ መምጣታቸው፣ በሌላ በኩል ስደትን ለመግታት እየተወሰዱ ካሉ ዕርምጃዎች ጋር ተቃርኖ መፍጠሩን በመጽሐፍዎ ላይ ገልጸዋል፡፡ ይህ ተቃርኖ እንደት ሊፈጠር ቻለ?

አቶ ዮርዳኖስ፡- በዚህ መጽሐፍ ልመልሰው ያልቻልኩት ትልቁ ጥያቄ ይኼ ነው፡፡ አሁን የምነግርህ መላምቴን ነው፡፡ ግሎባላይዜሽን ወይም ሉላዊነት የሚለውን ማዕቀፍ ብትወስድ አራት ዘለላዎች ልታወጣለት ትችላለህ፡፡ የመጀመርያው ዘለላ የኢኮኖሚ ገጽታ ነው፡፡ እዚህ ውስጥ በዋነኛነት የተፈጥሮ ሀብቶችና ገንዘብ ታገኛለህ፡፡ ምዕራብ አፍሪካን እንደ ምሳሌ ብንወስድ የአውሮፓ ኅብረትና ምዕራብ አፍሪካ በተለይም ሴኔጋል ባደረጉት ስምምነት መሠረት፣ የአውሮፓ የአሳ ኩባንያዎች በምዕራብ አፍሪካ የውቅያኖስ ዳርቻዎች ላይ ያለውን የዓሳ ሀብት በዘመናዊ መንገድ እያጠመዱ ይጠቀማሉ፡፡ እዚያ የዓሳ ሀብት ላይ ሕይወታቸውን የመሠረቱ በርካታ ወጣት ሴኔጋላዊያን ነበሩ፡፡ በዚህ ውሳኔ ሕይወታቸው የተናጋው እነዚህ ወጣቶች ባህላዊ በሆነ መንገድ ዓሳ ያጠምዱባቸው የነበሩ ጀልባዎቻቸውን እየነዱ ስፔን ደረሱ፡፡ እዚያ ሲደርሱ ግን ‹ሕገወጥ ስደተኞች› ተባሉ፡፡ ይኼ አንድ ኢኮኖሚያዊ ተቃርኖ ነው፡፡

ሁለተኛው የሉላዊነት ዘለላ ቴክኖሎጂ ነው፡፡ አሁን ከሉላዊነት መስፋፋት ጋር ተያይዞ መረጃ እንደ ልብ ይገኛል፡፡ በፊልም ስለምዕራባዊያን የኑሮ ዘይቤ ስታይ ሳታስበው ስለእነዚያ አገሮች አዎንታዊ የሆነ ሥዕል ይጭርብሃል፡፡ የትራንስፖርት ዋጋም ቀንሷል፡፡ ይኼም የመሰደድ ፍላጎትህን ይጨምረዋል፡፡ ሌላው የሉላዊነት ዘለላ ባህል ነው፡፡ ዋናውና ከስደት ጋር የሚያያዘው የሉላዊነት ዘለላ ፖለቲካ ነው፡፡ ብሊጅ የተባሉ የኔዘርላንድ ሶሻል ሳይንቲስት ‹ዓለም እንዳሁኑ አጥራም ሆና አታውቅም› ብለዋል፡፡ በተለያዩ ቦታዎች ስደተኞችን ለመከላከል አጥር እየበዛ ነው፡፡ ሌላው አጥር በየአገሩ የሚገኙ ኤምባሲዎች ናቸው፡፡ አሳማኝ ባልሆኑ ምክንያቶች ቪዛ ይከለክሉሃል፡፡ ጉዞዎች ላይ ሸንቋጭና በጣም ከባድ የሆኑ ገደቦችን የሚጥሉ ሕጎችም እየተረቀቁ ነው፡፡ በነፃነት መንቀሳቀስን የሚገድቡ ዕርምጃዎች ሲበዙ ደግሞ ስደተኞች በሕገወጥ መንገድ ለመንቀሳቀስ ያስገድዳሉ፡፡ አገር ውስጥ ደግሞ የተለያዩ ግፊቶች አሉ፡፡  የኑሮ ደረጃ ዝቅ ማለት ወይም ድህነት ሊሆን ይችላል፡፡ ፖለቲካም ሊሆን ይችላል። . . .ስለዚህ የተሳበና የተገፋ ግን ለመሰደድ ያልተፈቀደለት ሕዝብ አለ፡፡ የምዕራባዊያን የስደት ፖሊሲን እኔ እስከተረዳሁት ድረስ ምርጥ ምርጡን በስኮላርሽፕና በሌላውም መንገድ ለመውሰድ የተዘጋጀና የማያስፈልጉትን ግን እዚያው ባሉበት ስደተኛ ካምፕ በማቋቋምና ዕርዳታ በመላክ እዚያው ለማስቀረት ያለመ ነው፡፡ እንደ ምዕራብ አፍሪካ ወጣቶች ኑሮህ ከተናጋ በኋላ አትፈለግም ትባላለህ፡፡

ሪፖርተር፡- አንድን ስደተኛ የፖለቲካ ወይም የኢኮኖሚ ስደተኛ ብሎ መከፋፈል አስቸጋሪ መሆኑን በመጽሐፍዎ ላይ ቢገልጹም፣ በአብዛኛው ስደተኞች በተሰደዱበት አገር የመኖሪያ ፈቃድ ለማግኘት ሲሉ ራሳቸውን የፖለቲካ ስደተኛ አድርገው ያቀርባሉ፡፡ ለፖለቲካ ስደተኞች የተሻለ ጥበቃ የመስጠት መነሻ ምንድነው?

አቶ ዮርዳኖስ፡- እ.ኤአ. በ1951 ስደተኞችን የሚመለከተው የጀኔቫ ኮንቬንሽን ተፈርሞ ነበር፡፡ ስምምነቱ ከመውጣቱ በፊት ሁለተኛው የዓለም ጦርነትና የናዚ ንቅናቄ ነበሩ፡፡ ሒትለር ብዙ ሰዎችን ስለጨፈጨፈ በፖለቲካ አመለካከታቸው የተነሳ ጥቃትና ቅጣት ሊደርስባቸው ሲል አምልጠው የሄዱ ሰዎች ላይ የተመሠረተ ኮንቬንሽን ነው፡፡ ስለዚህ ከኢኮኖሚና ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር የተያያዙትን ጨምሮ ሌሎች ምክንያቶችን ብዙም ቦታ አልሰጣቸውም ነበር፡፡ ኮንቬንሽኑ ለረዥም ጊዜ ሳይሻሻል ቆይቷል፡፡ ከአንድ ታዳጊ አገር ወደ አደጉ አገሮች የሚሄዱ ሰዎች ብዙ ጊዜ ጥገኝነት ሲጠይቁ ፈቃድ የሚሰጣቸው የፖለቲካ ስደተኛ ከሆኑ ነው፡፡ የአደጉ አገሮችም ከየት አገር ስደተኛ መቀበል እንዳለባቸው ይለያሉ፡፡ ለምሳሌ ከአፍሪካ ሶማሊያና ኤርትራን መጥቀስ ይቻላል፡፡ በዚህም የተነሳ በድህነት ወይም በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ወደ አውሮፓ ያቀና አንድ ኢትዮጵያዊ ስደተኛ አውሮፓ ሲገባ ፈቃድ እንደማይሰጠው ስለሚያውቅ የሶማሊያ ወይም የኤርትራ ፓስፖርት ይፈልጋል፡፡ ወይም የውሸት ፖለቲካዊ ተረክ ይፈጥራል። ደቡብ አፍሪካም ያለው እውነት ይኼ ነው፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት አሸባሪ ብሎ ከፈረጃቸው ድርጅቶች መካከል የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) አንዱ ነው፡፡  በኦነግ ስም ሄዶ ጥገኝነት የሚጠይቅ ስደተኛ ተቀባይነት ያገኛል፡፡ ብዙዎቹ እኔ ያገኝኋቸው ስደተኞች እዚያ እስኪደርሱ ድረስ ኦነግ እስከነመፈጠሩም የማያውቁ ቢኖሩም፣ ወረቀታቸውን ያገኙት ወይም የሚያሳድሱት በኦነግ ስም ነው፡፡ ይኼን ‹ኬዝ መጋገር› ይሉታል፡፡ አንድ ‹ኬዝ የሚጋግር› ልጅ አግኝቼ ነበር፡፡ የሚያቀርቧቸው ማመልከቻዎች አንድ ዓይነት ናቸው፡፡

አብዛኛው ከሆሳዕና የሄዱ ስደተኞች ደግሞ በፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ የሚመራው ተቃዋሚ ፓርቲ አባል ነን ይላሉ፡፡ ይኼ ማለት የፖለቲካ ስደተኞች የሉም ማለት አይደለም፡፡ የተወሰኑ ጋዜጠኞች፣ የፖለቲካና የመብት አቀንቃኞች ይኖራሉ፡፡ አብዛኛው የደቡብ አፍሪካ ስደተኛ ግን የኢኮኖሚ ስደተኛ ቢሆንም ጉዳዩ የሚያሳየው ግን የፖለቲካ ስደተኛ እንደሆነ ነው፡፡ ይኼ የስደተኞቹ ጥፋት አይመስለኝም፡፡ ዓለም አቀፉ ሥርዓት የፈጠረው ችግር ነው፡፡ አሌክሳንደር ቤትስ የተባሉ ምሁር የስደቱ መነሻ ምንም ይሁን ምንም ጥገኝነት ሊሰጥ ይገባል ሲሉ ይከራከራሉ፡፡ በድህነት፣ በኢኮኖሚና በማኅበራዊ ጫና ምክንያት ለሚሰደዱ ሰዎች የተሻለ ጥበቃ ለመስጠት የጀኔቫ ኮንቬንሽን ሊሻሻል ይገባል፡፡ የስደቱ መነሻ የምዕራባዊያን ኩባንያዎች በታዳጊ አገሮች ከፈጠሩት ችግር ጋር የሚያያዝ ከሆነ፣ እነዚህ አገሮች ስደተኞቹን የመቀበል ግዴታቸው የሞራል ብቻ አይደለም፡፡ ኢኮኖሚያዊ ኃላፊነትም አለባቸው፡፡ ከዚህ ሁሉ የተሻለ የሚሆነው ግን ስደትን የሚፈጥሩ መንስዔዎች ላይ ማተኮርና መሥራት ነው።

ሪፖርተር፡- በመጽሐፍዎ ላይ የብዙ ሰዎች የሕይወት ታሪክ ቢካተትም የኢዛናን የሕይወት ተሞክሮ በጣም አስደሳች ሆኖ አግኝቸዋለሁ፡፡ የኢዛናን ስደት የወለደው የኢትዮጵያና የኤርትራ ግጭት ነው፡፡ በኢዛና ዓይን የኢትዮ-ኤርትራን ግንኙነት እንዴት መዘኑት? 

አቶ ዮርዳኖስ፡- የአንድ ድርጊት ውጤት ጣጣና መዘዙ ምን እንደሆነ ድርጊቱን የፈጸሙ ወይም ውሳኔ ያሳለፉ ሰዎች ላያውቁት ይችላሉ፡፡ የኢዛናን ታሪክ ያካተትኩበት አንዱ ዓላማ ይኼን ለማሳየት ነው፡፡ በርካታ ኢዛናዎች አሉ፡፡ ለካ ያኔ የወሰድኩት ውሳኔ ይኼን ሁሉ መዘዝ አምጥቷል ብለው እነዚህ ሰዎች እንዲቆጩና እንደዚያ ዓይነት የግዴለሽነት ውሳኔ እንዳይወስኑ ሁለተኛ ጊዜ እንዲያስቡ ለማድረግ ነው፡፡ ይኼ ፖለቲከኞቹ ላይ ብቻ የተገደበ አይደለም፡፡ ኢዛና የፖለቲካ ስደተኛ ነው፡፡ ኢዛና ድንገት ማንነቱን የተነጠቀ ሰው ነው፡፡ ከዚያ በኋላ በኬንያ፣ በታንዛኒያ፣ በዛምቢያ፣ በሞዛምቢክና በደቡብ አፍሪካ ብዙ ስቃይ ደርሶበታል፡፡ የኢትዮ-ኤርትራ ጉዳይ በመግባባትና በመነጋገር መፈታት ያለበት ነው፡፡ በጥቂት ፖለቲከኞች አለመግባባት በሚፈጠር ጠብ ሰፊው ሕዝብ ላይ የሚያስከትለው ተፅዕኖ ግንዛቤ ውስጥ ሊገባ እንደሚገባ የኢዛና ታሪክ ያሳይሃል፡፡ በምዕራፍ ሦስት የቀረበውን የቢኒያምን ታሪክ ካየህ እሱ ደግሞ የማኅበራዊ ግፊት ስደተኛ ነው፡፡ ሠፈር ውስጥ ያሉ ሰዎች በሚያወሩት ወሬ፣ በእናትና አባት ግፊት ደቡብ አፍሪካ የገባ ነው፡፡ እንደ ፖለቲከኖቹ ሁሉ እነዚህ የሠፈር ሰዎችም ለስደት የዳረጓቸው ወጣቶች በምን ዓይነት የሕይወት ውጣ ውረድ ውስጥ እምደሚያልፉ ያሳያል የሚል እምነት አለኝ።

ሪፖርተር፡- እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገሮች ከስደት ጋር በተገናኘ ላሉት መጠነ ሰፊ ችግሮች ዋነኛ ተጠያቂ የሚያደርጉት ሕገወጥ ስደተኞችን የሚያሸጋግሩ ግለሰቦችን ነው፡፡ ይኼ አቋም አገሮቹ ሌሎች የችግሩ መንስዔዎችን እንዳያዩ አድርጓቸዋል ብለው ያምናሉ?

አቶ ዮርዳኖስ፡- ያደረጋቸው አገሮች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ሆን ብለው እዚህ ላይ የሚያተኩሩም አሉ፡፡ ለምሳሌ የአውሮፓ ኅብረት ብዙ ነገር ቢያውቅም፣ በግዙፍ ዓለም አቀፍ የሚዲያ አውታሮች የሚያስተላልፉት መልዕክት ግን የአውሮፓ ኅብረት ዋና ዓላማው ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርን መረብ መሰባበር እንደሆነ ነው፡፡ ዋነኛው መነሻ ምክንያት ሌላ እንደሆነ ያውቃል፡፡ በአገር አቀፍና በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታይ የኢኮኖሚ ፍትሕ ጥያቄ አንዱ እንደሆነ የምዕራብ አፍሪካ ወጣቶች ላይ የአውሮፓ የዓሳ ኩባንያዎች ካደረሱት ማፈናቀል መረዳት ይቻላል፡፡ ይህን መረብ ለመበጣጠስ አንዱ ወስደውት የነበረው ዕርምጃ ከሞሮኮ መንግሥት ጋር በመተባበር ስዌታና ሚሊላ የሚባሉ የስፔን ድንበሮች ላይ ትልቅ አጥር መሥራት ነበር፡፡ ከዚያ በተጨማሪ ለሞሮኮ ፖሊሶች የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ ከምዕራብ አፍሪካ ወደ አውሮፓ የሚሄዱ ስደተኞችን ለመገደብ ጥረት ተደርጎ ነበር፡፡ በዚህ ምክንያት ወደ ስፔን የሚገቡ ስደተኞች ቁጥር ቀነሰ፡፡ ነገር ግን እነዚህ ስደተኞች በግሪክና በጣሊያን በኩል መሄድ ጀመሩ፡፡ ይኼ የስደተኞችን ስቃይ ጨመረ እንጂ ስደትን አልገታም፡፡

ደቡብ አፍሪካም ደላሎችን ተጠያቂ ታደርጋለች፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥትም በተመሳሳይ ሕገወጥ ደላሎችን ዋና ተጠያቂ ያደርጋል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር 100 ሚሊዮን ደርሷል፡፡ ከዚህ ውስጥ 70 በመቶ የሚሆነው ዕድሜው ከ35 በታች ነው፡፡ በየዓመቱ ከዩኒቨርሲቲ እየተመረቀ ያለውን ጨምሮ ሥራ የሚፈልገው ወጣት ቁጥር በጣም ብዙ ነው፡፡ በየዓመቱ ከሚፈጠረው የሥራ ዕድል ቁጥር ጋር አለመመጣጠን አለ፡፡ ከዚያ በተጨማሪ ሠራተኞችን የሚቀንሱ ከፍተኛ የሆነ ካፒታል የሚጠይቁ ቴክኖሎጂዎች ወደ አገር ውስጥ እየገቡ ነው፡፡ ስለዚህ ወደ ሥራው የሚገባውን የሰው ኃይል የሚያስተናግድ አቅም አልፈጠርንም፡፡ እንግዲህ እነዚህ ‹‹ትርፍ›› የሆኑ ሰዎች (Excess Population) ሊሆኑ ይችላሉ ደላሎችን እየፈለጉ አሻግሩን የሚሉት፡፡ ሕገወጥ ስደተኞችን የሚያሸጋግሩ ግለሰቦች ለስደተኞች ፍላጎት ምላሽ ይሰጣሉ እንጂ ለስደት መፈጠር መነሻዎች አይደሉም፡፡ ነገር ግን አሁን ካለው የድንበሮች መጥበቅ፣ እንዲሁም የተዛባ የዓለም የኢኮኖሚና የፖለቲካ ግንኙነት ውስጥ የራሳቸውን ጥቅም ማሳደግ የሚፈልጉ ሕገወጥ ስደተኞችን የሚያሸጋግሩ ግለሰቦች በየቦታው ብቅ ብቅ ይላሉ፡፡ በጊዜ ሒደት በሥራው የሚገኘው ገንዘብ እየበዛ ሄዷል፡፡ ስለዚህ በመካከለኛና በከፍተኛ ቦታ ያሉ ትልልቅ ሰዎችም በዚህ ሒደት የሚሳተፉት ለገንዘቡ ነው፡፡ ስለዚህ ደላሎች ተጠያቂ አይደሉም ማለት አይደለም፡፡ በጊዜ ሒደት አቅማቸው እየፈረጠመ ብዙ ገንዘብ ሲያገኙ እየጎተጎቱና እያማለሉ ጭምር የሚወስዱ ደላሎች አሉ፡፡ በዓለም ደረጃ የኑሮ ልዩነት እየጨመረ ነው፡፡ እዚህ ኢኮኖሚ ቢያድግም የተሻለ የኑሮ ደረጃ ትፈልጋለህ፡፡ በርካታ የተገፋና ለመሰደድ የተሳበ ሰው አለ፡፡ እነዚህ ሰዎች እንዳይሄዱ የሚያግዳቸው ሕግ ብቻ አይደለም፡፡ የገንዘብ አቅምም ያግዳቸዋል፡፡ ኢኮኖሚው ባደገ ቁጥር የእነዚህ ሰዎች የገንዘብ አቅም አብሮ ያድጋል፡፡ ስለዚህ ደላሎች እንዲፈጠሩና እንደ ልባቸው እንዲንቀሳቀሱ ከባቢ አየሩን ምን ፈጠረው የሚለው ላይ ማተኮር አለብን፡፡ ስደት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየከፋና የሚጠይቀው ገንዘብ እየጨመረ ቢመጣም ራሱን ወደ ቻለ ኢንዱስትሪ ደረጃ ግን ደርሷል፡፡ ለዚያም ነው የደላሎችን መረብ መሰባበር ችግሩ እሰካለ ድረስ የስደተኞችን ስቃይ ያጎላው እንደሁ እንጂ፣ ከመሠረቱ ችግሩን አይቀርፈውም ያልኩት፡፡

ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ ስደት እያስከተለ ያለውን ችግር ለመቅረፍ የሕግ ማዕቀፍ ማዘጋጀትና ተቋማትን ማደራጀትን ጨምሮ ባለፉት ጥቂት ዓመታት የተለያዩ ዕርምጃዎችን ወስዳለች፡፡ ነገር ግን በስደት ጉዳትና ችግሮች ላይ በቂ መረጃና ግንዛቤው ያለው ጭምር የመሰደድ ፍላጎቱ አለመቀነሱ እነዚህን ጥረቶች ትርጉም አልባ አያደርግም?

አቶ ዮርዳኖስ፡- ይኼ ራሱን የቻለ ሰፊ ጥናት የሚጠይቅ ጥያቄ ነው፡፡ ባህላችንን ጨምሮ ወደ ውስጥ ገብተን ራሳችንን እንድንፈትሽ የሚያስገድድ ነው፡፡ ‹‹እኔ ካልሞትኩኝ ሌላው አያልፍለትም›› የሚል ባህል አለን? ‹‹እዚህ በረሃብ ከምሞት እየሄድኩ ልሙት›› ነው? ወይስ ከሞት የከፋ ድህነት አለብን? እዚህም እዚያም የሚሰሙ ግን በጥናቴ ያላረጋገጥኳቸው መላምቶች ናቸው፡፡ ሌላውና ጎልቶ የወጣው ደግሞ የዓይን መጋረድና የአዕምሮ መዘጋት ነው፡፡ ለምሳሌ ከኢትዮጵያ ወደ ደቡብ አፍሪካ የሚሄዱ ስደተኞች እዚያ የሚደርሱት ብዙውን ጊዜ በለጋ ዕድሜያቸው ነው፡፡ አደጋው እንዳለ ሆኖ የሞተው ሞቶ የሚኖረው በጊዜ ሒደት ብዙ ብር ያገኛል፡፡ ወንድ ወጣቶች ብዙ ጊዜ አገር ቤት ያለች ሴት ነው ማግባት የሚፈልጉት፡፡ በአብዛኛው የሠርግ ሥነ ሥርዓቶች የሚከናወኑት በጆሐንስበርግ ወይም በተለያዩ የደቡብ አፍሪካ ክፍሎች ውስጥ በሚገኙ ማራኪ ፓርኮች ነው፡፡ በመቶዎች በሚቆጠሩ መኪናዎችም ይታጀባሉ፡፡ እነዚህ የሠርግ ሥነ ሥርዓቶች በቪድዮ ይቀረፁና አገር ቤት ለቤተሰብ ይላካሉ፡፡ ይህን ያዩ ሰዎች ለደቡብ አፍሪካ ከፍ ያለ አዎንታዊ ሥዕል ይኖራቸዋል፡፡ ከደቡብ አፍሪካ የሚመለሱ ወጣቶች ያላቸው አካላዊና የኑሮ ዘይቤ ለውጥም ሌላ ጥሩ ሥዕል ይፈጥርባቸዋል፡፡ አገር ቤት ያልተመለሱት ደግሞ ለቤተሰቦቻቸው ብዙ ብር ይልካሉ፡፡ በዚህ እልም ያለ ገጠር ውስጥ ከባህላዊ ጎጆ አጠገብ እኔ ነኝ ያለ ዘመናዊ ቪላ ቤት ተሠርቶ ታያለህ፡፡ በሁለቱ መካከል የኑሮ ልዩነቱ አፍጦ ታየዋለህ፡፡ ስለዚህ ሰው ሲሞት ብታይም እሱ አይታይህም፡፡ የሚታይህ መኪና የሚነዳው ጓደኛህ፣ አምሮበት ያየኸው አብሮ አደግህ ወይም ቪላ የሠራው ጎረቤትህ ነው፡፡ ማንዴላ ‹‹የተዘጋን ጭንቅላት ለመክፈት በጣም አስቸጋሪ ነው፤›› ይላል፡፡

ሪፖርተር፡- በተቋም ደረጃ ስደት ላይ የሚሠሩ አካላት በቂ ሥራ እየሠሩ ነው ማለት ይቻላል?

አቶ ዮርዳኖስ፡- ስደት የሚያስከትላቸው ተፅዕኖዎች ላይ መረጃ እዚህም እዚያም አለ፡፡ ዶክመንተሪዎች፣ ጥናቶችና የተለያዩ ሥራዎች አሉ፡፡ ነገር ግን እነዚህን ሁሉ አንድ ላይ አጠቃሎ የሚይዝ ትልቅ ተቋም የሚያስፈልግ ይመስለኛል፡፡ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ መልቲ ዲሲፕሊነሪ የሆነ አንድ ተቋም መኖር ነበረበት፡፡ ምክንያቱም ስደት ከሳይኮሎጂ፣ ከኢኮኖሚ፣ ከፖለቲካ፣ ከሕግ፣ ከአንትሮፖሎጂ፣ ከታሪክና ከመሳሰሉት ዘርፎች አንፃር ያለው ተፅዕኖ በዝርዝር ሊጠና ይገባል፡፡ ሌላው ስደትን በመጥፎ ጎኑ ብቻ ማየት አያስፈልግም፡፡ ከስደት ጥሩ ነገር አለ፡፡ በየቦታው እየተሰቃዩ ወደ አገር ቤት ገንዘብ የሚልኩ በርካታ ኢትዮጵያዊያን አሉ፡፡ ባሉበት መብታቸውን ለማስከበር መጣር እንጂ ስደት አትወጡም ብሎ መከልከል ጥሩ አይመስለኝም፡፡ ስለዚህ የስደትን አደጋ ለመቀነስና ጥቅሙን ለማስፋት የፖለቲካውን አጥር እንደምንም አስወግዶ መነጋገር ያስፈልጋል፡፡ በየአገሩ ያሉ የኢትዮጵያ ኮሙዩኒቲ ማኅበሮችን ማነጋገርና የኤምባሲዎችንና ቆንስላ ጽሕፈት ቤቶችን አቅም ማዳበር ቢቻል ለውጥ ማምጣት የሚቻል ይመስለኛል፡፡