Skip to main content
x
‹‹ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎችን ከማንጋጋት ይልቅ ለአገልግሎት ጥራት ቅድሚያ መስጠቱ ይመረጣል››

‹‹ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎችን ከማንጋጋት ይልቅ ለአገልግሎት ጥራት ቅድሚያ መስጠቱ ይመረጣል››

አቶ ቢንያም ብሥራት፣ የአዲስ አበባ ሆቴል ባለንብረቶች የዘርፍ ማኅበር የቦርድ ሰብሳቢ

አቶ ቢንያም ብሥራት በሆቴልና ቱሪዝም መስክ ከአሥር ዓመታት በላይ በኢትዮጵያ ተሞክሮ አላቸው፡፡ የአዲስ አበባ ሆቴል ባለንብረቶች የዘርፍ ማኅበር ቦርድ ሰብሳቢ በመሆን ሲያገለግሉ ከአምስት ዓመታት ያላነሱ ጊዜያት አሳልፈዋል፡፡ የጁፒተር ኢንተርናሽናል ሆቴል ዋና ሥራ አስኪያጅም ናቸው፡፡ ከተቋቋመ ከሦስት ዓመታት በላይ ባስቆጠረው በቱሪዝም ትራንስፎርሜሽን ምክር ቤት ባለሆቴሎችን በመወከል ይሳተፋሉ፡፡ የቱሪዝም ቦርድ አባልም ናቸው፡፡ በአገሪቱ ሲካሄድ በቆየው በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሥር በሚንቀሳቀሰው የዓለም ቱሪዝም ድርጅት መሥፈርት አውጭነትና ደረጃ መዳቢነት የአዲስ አበባ ሆቴሎች የኮከብ ደረጃ ሲወጣላቸውም፣ የአዲስ አበባ ሆቴል ባለንብረቶች ማኅበር ከጅምሩ ጀምሮ ተሳታፊ እንደነበር የሚገልጹት አቶ ቢንያም፣ በውጤቱም ሆቴሎች ተጠቃሚ መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የኢትጵያ ቱሪዝም ዘርፍ የተደቀነበትን አደጋ ብቻ ሳይሆን፣ በአገሪቱ ተክስቶ በነበረው ሕዝባዊ ተቃውሞ ሳቢያ በተለይ የከተማው ሆቴሎች ስለደረሰባቸው ጉዳትም አቶ ቢንያም ይፋ አድርገዋል፡፡ ባለፈው ሳምንት ማኅበሩ ጠርቶት በነበረው ጋዜጣዊ መግለጫ ወቅትም፣ የአዲስ አበባ ሆቴል በ2009 የመጀመሪያው ሩብ ዓመት ብቻ ከ380 ሚሊዮን ብር በላይ ኪሳራ እንደደረሰባቸው አቶ ቢንያም አስታውቀዋል፡፡ ይህም የሆነው ሕዝባዊ ተቃውሞን ተከትሎ በተከሰተው ግጭት፣ ያንንም መነሻ በማድረግ በርካታ አገሮች ወደ ኢትዮጵያ የሚደረጉ ጉዞዎችን እንዲሰርዙና ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ የሚያሳስቡ የጉዞ ክልከላዎችንና ዕገዳዎችን በማውጣታቸው ምክንያት የገበያ መቀዛቀዝ በመፈጠሩ የደረሰ ኪሳራ ነው፡፡ ለወትሮው በአማካይ 67 በመቶ የሆቴል ክፍሎች ዓመቱን ሙሉ ደንበኛ የሚስተናገዱባቸው ቢሆንም፣ ከብጥብጡ ማግሥት ጀምሮ እስካሁን ድረስ ግን የ20.5 በመቶ ቅናሽ ተመዝግቦ እንደሚገኝ አቶ ቢንያም አስታውቀዋል፡፡ የኪሳራው መጠን በሦስኛው ሩብ ዓመትም ጭምር እየታየ በመሆኑ መንግሥት ለሆቴሎች ድጋፍ መስጠት እንዳለበት፣ የድጋፍ መንገዶቹም በንግድ ገቢ እፎይታ መልክ፣ የባንክ ብድር መክፈያ ጊዜ ማራዘሚያን የመሳሰሉ ሌሎችም የመፍትሔ አማራጮች እንዳሉ በመጥቀስ መንግሥት የደረሰባቸውን ኪሳራ ለማካካስ የሚችሉበት ዕድል እንዲሰጣቸው መጠየቃቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ በዚህ ወቅት ከሪፖርተር ጋር ቆይታ ያደረጉት አቶ ቢንያም የአገሪቱ የቱሪዝም መስክ እያደገ፣ የሆቴል ኢንዱስትሪውም በየሦስት ወሩ ሁለት ሆቴሎች የሚገነቡበት እየሆነ እንደመጣ ይጠቁማሉ፡፡ እነዚህን ጨምሮ በሆቴል ንግድ መስክ ስለሚታዩ የሰው ኃይል ችግሮች፣ ወደፊት ስለሚገነባው የሆቴል ባለሙያዎች ማሠልጠኛ ተቋምና ስለሌሎች ጉዳዮች ብርሃኑ ፈቃደ አቶ ቢንያምን አነጋግሮ የሚከተለውን ቃለ ምልልስ አጠናቅሯል፡፡

ሪፖርተር፡- ቀደም ሲል በሆቴል ዘርፍ በተካሄደ ጥናት ኢትዮጵያ በሆቴሎች ግንባታ ከአሥር የአፍሪካ አገሮች ተርታ ተመድባ ነበር፡፡ ግንባታቸው እየተካሄዱ የሚገኙና ወደ ግንባታ ለመግባት የሚያስችላቸውን ስምምነት ያደረጉ የሆቴል ፕሮጀክቶች ለዚህ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያ አሁንም ከአሥሩ ዋና ዋና የአፍሪካ አገሮች ምድብ ውስጥ ትካተታለች ማለት ነው?

አቶ ቢንያም፡- ባለፉት ስምንት ወይም ዘጠኝ ዓመታት ውስጥ በየወሩ አንድ ሆቴል መክፈት ችለናል፡፡ ወደፊትም በወር ከአንድ በላይ ሆቴል (በስታትስቲክስ አገላለጽ 1.5 ሆቴል) እየከፈትን እንደምንሄድ ይጠበቃል፡፡ ከመቶ በላይ ሆቴሎች በመስመር ላይ ናቸው፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ከ20 እስ 25 በመቶውን የሚሸፍኑት ደግሞ ዓለም አቀፍ ደረጃ ያላቸው የውጭ ሆቴሎች ናቸው፡፡ በአሁኑ ወቅት 8,000 አልጋዎች ያሏቸው ሆቴሎች በሥራ ላይ ሲሆኑ፣ በሦስት ዓመታት ውስጥ ይህ ቁጥር በእጅጉ እንደሚጨምር ግልጽ ነው፡፡ ስለዚህ ከአሥሩ አገሮች ተርታ ውስጥ እንገኛለን ወይ? ለሚለው አዎን እንደዚያው እንደሆነ እገምታለሁ ነው ምላሼ፡፡ 

ሪፖርተር፡- ወደ መስተንግዶው ወይም በጥቅል ወደ ሆቴል አገልግሎት ስንመለከት በርካቶች ግራ የሚጋቡበት ሆኖ ይገኛል፡፡ ዘርፉ የሚያቀርባቸውን አገልግሎቶች እንዴት ይመለከቷቸዋል?

አቶ ቢንያም፡- መመልከት ያለብን ከየትኛው ደረጃ እየተነሳን እንደሆነ ነው፡፡ በሆቴል ሥራ ውስጥ ያሉና የማስፋፊያ ግንባታ እያካሄዱ የሚገኙ የሆቴል ባለንብረቶች አሉ፡፡ ዓለም አቀፍ ሆቴሎችን የሚያስተዳድሩትም እየገቡ ነው፡፡ በዘርፉ ያልነበሩ በሌላ የሥራ ዘርፍ ውስጥ የነበሩ አዳዲስ የሆቴል ባለንብረቶችም፣ ነባሮቹንና ከውጭ የመጡትን እየተቀላቀሏቸው ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ነገር ግን ሆቴሎች የሚሰጡት አገልግሎትና እየተስፋፉ ያሉትን የሆቴል ግንባታዎች እንዴት ይመለከቷቸዋል? በሆቴል አገልግሎት አሰጣጥ መስክስ በምን ደረጃ ልንመዘን እንችላለን?

አቶ ቢንያም፡- እስካሁን የተወያየነው በሆቴሎች የምርት ይዘት ላይ ነው፡፡ እየተከፈቱ ያሉ ሆቴሎች፣ የተገነቡት ሕንፃዎችና ንብረቶች የሆቴል ምርትን የሚወክሉ ናቸው፡፡ ምርት በማምረት ረገድ ተዋጥቶልናል ማለት እችላለሁ፡፡ በጣም የሚያማምሩ፣ ቅንጡና ደረጃቸው ከፍ ያሉ ሆቴሎችን በመገንባት ላይ እንገኛለን፡፡ ምቹና ውድ ክፍሎች በሆቴል ንግድ ውስጥ እየተስፋፉ መጥተዋል፡፡ ይሁንና የአገልግሎት ዘርፉን ስናይ ብዙ መሥራት የሚጠበቅብን መስክ ሆኖ ይገኛል፡፡ በተፈጥሯችን እንግዳ ተቀባዮች ነን፡፡ ይህ የኢትጵያውያን የተፈጥሮ ጠባያችን በመሆኑ ትልቅ እሴታችን ነው፡፡ ሆኖም በአግባቡ በሙያ ክህሎት የጎለበተና የሠለጠነ የአገልግሎት አሰጣጥ አላዳበርንም፡፡ ማኅበራችን የአጭር ጊዜ ሥልጠናዎችን በመስጠት በሆቴል መስተንግዶ በኩል ያሉትን ክፍተቶች ለመፍታት እየሞከረ ነው፡፡ ወደፊትም በርካቶችን በማሠልጠን ለውጥ ለማምጣት የሚያስችል ትልቅ የሥልጠና አካዴሚ ለመመሥረት እየተንቀሳቀስን እንገኛለን፡፡ ይህንን በማድረግም ከምርቱ እኩል የሚቀርበውን አገልግሎትና መስተንግዶ ለማጣጣም እንሞክራለን፡፡ ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎችን ከማንጋጋት ይልቅ ለአገልግሎት ጥራት ቅድሚያ መስጠቱ ይመረጣል፡፡   

ሪፖርተር፡- እየመጡ ያሉትን ሆቴሎች ተከትሎ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዓለም ቱሪዝም ድርጅት ሆቴሎችን በደረጃ በመመደብና በኮከብ አሰጣጥ በመለየት፣ ላለፉት ሦስት ዓመታት ሲሠራበት የቆየውን ፕሮግራም አጠቃሎ ወጥቷል፡፡ በመሆኑም የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ፕሮጀክቱን በራሱ መምራት እንደጀመረ ይታወቃል፡፡ ይህ ማለት አገሪቱ ደረጃዎችን ለማውጣት ወይም በኮከብ ደረጃ ሆቴሎችን ለመመደብ የሚችሉ ባለሙያዎችን አፍርታለች ማለት ነው?

አቶ ቢንያም፡- የደረጃ ምደባውም ሆነ የኮከብ ደረጃ አወጣጡ በብዙ መንገድ ጠቃሚ ነው፡፡ ማኅበራችን የኮከብ ደረጃ የሚሰጥበትን ፕሮግራም ከጅምሩ ሲደግፍ ቆይቷል፡፡ ፕሮግራሙ ጥራትን ለማስጠበቅ በእጅጉ ጠቅሞናል፡፡

ሪፖርተር፡- ጥያቄው ግን የዓለም ቱሪዝም ድርጅት ሰዎች ፕሮግራሙን አጠናቀው የወጡት ባለፈው ዓመት በመሆኑ፣ በራስ ሰዎች ደረጃ ማውጣት ተጀምሯል ወይ የሚል ነው፡፡

አቶ ቢንያም፡- ምላሼ ሁለት ነው፡፡ አዎን፣ አይደለም የሚል ነው፡፡ የሚደረጉት ዳሰሳዊ ምዘናዎች ከጅምሩ በዓለም ቱሪዝም ባለሙያዎች የሠለጠኑ ከሆኑ አዎን እንችላለን የሚል እምነት አለኝ፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ሰዎች ከጅምሩ በምዘናው ሥራ ውስጥ ተሳታፊ ስለነበሩ ፕሮግራሙን በደንብ ያውቁታልና ነው፡፡ እኔ በራሳችን ሰዎች እንደምንወጣው አምናለሁ፡፡ እዚህ ላይ ልነግርህ የምፈልገው ነገር አለ፡፡ በራሳችን አቅምና እዚህ ባገኘነው እውቀት ተጠቅመን ከዲዛይን፣ ከጽሑፍና ከምሥል ይዘት እስከ መጨረሻው ኅትመት ድረስ ያለውን ሥራ በራሳችን የተወጣንበት ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የቱሪዝም መጽሔት ለአዲስ አበባ ከተማ ማዘጋጀት ችለናል፡፡ ለዓለም መሠራጨት የሚችል ጥራት ያለው ነገር ማዘጋጀት እንደሚቻል አሳይተናል፡፡ በመሆኑም የሥልጠና ጉዳይ በመሆኑ ምዘናውን የሚሠሩትን ሰዎች በማሠልጠን የሚፈለገውን ውጤት ማግኘት እንደሚቻል አስባለሁ፡፡ የውጭ ሰዎችን በየጊዜው እያመጣን ምዘና እንዲያካሂዱ በማድረግ መቀጠል አንችልም፡፡ ወጪውም ከፍተኛ ነው፡፡ ስለዚህ በአገር ውስጥ ባለሙያዎች መሥራት የሚቻልበትን መንገድ መፍጠር ይጠበቅብናል፡፡

ሪፖርተር፡- ከሁለት ዓመታት በፊት በርካቶች ኢትዮጵያ በቱሪዝምና በሆቴል መስተንግዶ ዘርፍ ጥሩ ዕድል እንዳጋጠማት ይስማሙ ነበር፡፡ ይኸውም የሆነው አገሪቱ ከዓለም የቱሪዝም መዳረሻዎች ተርታ ተመራጭ ተደርጋ በቱሪዝም ደረጃ አውጭ ድረ ገጾች ዘንድ በመታወቋና ለዓለም ይፋ በማድረጋቸው ነበር፡፡ ይሁንና ዘርፉ በሚጠበቀው ደረጃ ለዓለም ሕዝብ አለመተዋወቁን የሚተቹ አካላት የሚያቀርቡት፣ አገሪቱ ያላትን አቅምና ልታገኝ የምትችለውን ጥቅም በማውሳት ነው፡፡ እንደ ግብፅ፣ ኢንዶኔዥያ፣ ስሪላንካ የመሳሰሉት አገሮች ሳይታክቱ በዓለም አቀፍ ሚዲያዎች የቱሪዝም ዘርፋቸውን ያስተዋውቃሉ፡፡ ይህን እዚህ ማድረግ ለምን አልተቻለም?

አቶ ቢንያም፡- ይህንን ማድረግ እንችላለን፡፡ በቅርቡ ይፋ የተደረገው ‹ኢትዮጵያ ምድረ መገኛ› የሚለው የቱሪዝም መለያም ይጠቀሳል፡፡ የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅት አገሪቱ በዓለም መድረክ እንድትታወቅና በዘርፉም እንድትወከል እየጣረ ነው፡፡ እንደሚገባው መጠን ሠርተናል ወይ ካልክ ገና ብዙ መሥራት እንደሚኖርብን ግልጽ ነው፡፡ ይሁንና የማስተዋወቅ ሥራ ብቻም ሳይሆን ሌሎችም የሚጎድሉን ነገሮች ምን እንደሆኑ ማየት ይኖርብናል፡፡ ሁሉም ነገር አብሮ ተያይዞ መቅረቡን ማረጋገጥ ይኖርብናል፡፡ የምናቀርባቸው አገልግሎቶች፣ ፋሲሊቲዎችና የመሳሰሉት ሁሉ በእሴት ሰንሰለቱ ውስጥ በሚገባ መገኘታቸውን እርግጠኞች መሆን ይጠበቅብናል፡፡ መቼም ብልሽት ወይም ችግር ያለበትን ምርትና አገልግሎት ይዘህ በመውጣት ለመሸጥ አታስተዋውቅም፡፡ በቅድሚያ ያለህ ነገር በገበያው ውስጥ ያለ ምንም ችግር ሊሸጥ እንደሚችል ልበ ሙሉ መሆን መቻል ይኖርብሃል፡፡ ይህ ሲባል ግን ያሉንን ምርቶችና አገልግሎቶች ማስተዋወቅ የለንብም ማለትም አይደለም፡፡ ያሉን የቱሪዝም፣ የሆቴል አገልግሎቶችና ምርቶች በዓለም የቱሪዝም ገበያ በጥሩ ሁኔታ መሸጥ የሚችሉ መሆናቸው ግልጽ ነው፡፡ ሆኖም ለውጦችን ማሳየት አለብን፡፡ ሁሉም የዘርፉ ሥነ ምኅዳር ተሟልቶ እስኪለማ መጠበቅም አንችልም፡፡ ነገሮችን ጎን ለጎን ማስኬድ ይቻላል፡፡

ሪፖርተር፡- መንግሥት የአሥር ዓመት መሪ ዕቅድ ለዘርፉ ይፋ አድርጓል፡፡ ዕቅዱ ከብዙው በጥቂቱ ከሚገልጻቸው ነገሮች መካከል የቱሪዝም ዘርፉ የኢኮኖሚ ድርሻ በእጥፍ እንደሚጨምር ማስፈሩ አንዱ የሚጠቀስ ነጥብ ነው፡፡

አቶ ቢንያም፡- ዕቅዱ ስለመውጣቱ አውቃለሁ፡፡ እንዲህ ያለው ዕቅድ መዘጋጀቱም ዘርፉን ለመምራት የሚያስችል ሰነድ በመሆኑ መልካም ነው፡፡ ይሁንና የሚወጡትን ዕቅዶች በተግባር መለወጡ ነው ተፈላጊው ነገር፡፡ በወረቀት ላይ የሚቀር ከሆነ ምን ይፈይዳል? በወረቀት ያሰፈርናቸውን በተግባር በመቀየሩ ላይ ልንበረታ ይገባናል፡፡

ሪፖርተር፡- ቱሪዝም ውስብስብና ተጋላጭ ዘርፍ መሆኑ ዕሙን ነው፡፡ በቅርቡ በተከሰተው ሕዝባዊ አመፅ ሳቢያም ዘርፉ መጎዳቱ እየታየ ነው፡፡ ይሁንና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ያሳደራቸው ተፅዕኖዎችም እያሉ እርስዎ ግን በአፋጣኝ አገግሞ እንደ ቀድሞው እንደሚጓዝ ተስፋ ያደርጋሉ፡፡

አቶ ቢንያም፡- እንዳለመታደል ሆኖ አጋጣሚዎቹ ተከስተዋል፡፡ የትኛውም ኢኮኖሚ የሚያልፍባቸው መዘውሮች አሉት፡፡ የዓለም ማኅበረሰብ በአሜሪካ ላይ የተፈጸመውን የ9/11 የሽብር ጥቃት፣ በለንደንና በፓሪስ ከተሞች የተፈጸሙ የቦምብ ጥቃቶችንም ተመልክቷል፡፡ በምዕራቡ ዓለም አሁንም አስከፊ ነገሮች እየተፈጸሙ ነው፡፡ እነሱ ላይ እየደረሱ እንዳሉት ዓይነት የከፉ ጥቃቶች ሰለባ አይደለንም፡፡ መጥፎው ነገር ግን ሕዝባዊ ተቃውሞው በእኛ አገር ሲከሰት የጉዞ ዕገዳና ማስጠንቀቂያ ወደ እኛ አገር በሚጓዙ ዜጎቻቸው ላይ ማውጣታቸው ነው፡፡ እኔ ምንም ዓይነት ተቀባይነት ያለው ምክንያታዊ አገላለጽ ያጣሁለት፣ በእኛ የደረሰውንና በእነሱ እየደረሰ ያለውን ነገር በምን ዓይነት ሚዛን በእኩል ለማየት እንደሚቻል ነው፡፡ በእነሱ እየደረሰ ያለው ከእኛ የከፋም ቢሆን፣ ከእነሱ ይልቅ እኛ ላይ ነው የጉዞ እገዳዎችና ማስጠንቀቂያዎች የወጡት፡፡ አንዳንድ አገሮች ያወጧቸውን የጉዞ ክልከላዎች ቢያነሱም፣ አሁንም ድረስ ግን የጥንቃቄ መልክዕቶችን አላነሱም፡፡    

ሪፖርተር፡- ይህንን በሚመለከት መንግሥት አገሮች ላወጧቸው የጉዞ ክልከላዎች ከፍተኛ ትኩረት እንዲሰጥ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመሩት የቱሪዝም ትራንስፎርሜሽን ምክር ቤት ስብሰባ ወቅት ማንሳትዎን አስታውሳለሁ፡፡ አገሮች እያወጡ ያሉትን ማስጠንቀቂያና ክለከላ በማስመልከት ያቀረቡት ጥያቄ የተነሳው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተግባራዊ ሊደረግ ገና ጅምር ላይ በነበረበት ወቅት ነበር፡፡

አቶ ቢንያም፡- ቱሪዝም ብቻም ሳይሆን መላው የአገሪቱ ኢኮኖሚ ነው ንዳዱ የሚሰማው፡፡ የውጭ ኢንቨስትመንትን፣ የውጭ ዕርዳታንና ሌሎችንም ለማስተናገድ ፈታኝ የሚሆነው አገሮች ያወጡብን የጉዞ ክልከላ እስካለ ድረስ ይመስለኛል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩና አመራራቸው ስለጉዳዩ በደንብ ያውቃሉ፡፡ አጥብቀው እየሠሩ እንደሆነም እናውቃለን፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረ ማርያም የቱሪዝም ቦርድ ሰብሳቢ እንደመሆናቸው ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተሉት ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩም በሚገባ እንደሚከታተሉት እርግጠኛ ነኝ፡፡

ሪፖርተር፡- ከመንግሥት አኃዛዊ መረጃዎች በመነሳት እያሽቆለቆለ ከመጣው የወጪ ንግድ አኳያ ሲታይ፣ ቱሪዝም ዋነኛ የአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ አስገኚ እየሆነ መምጣቱን ማየት ይቻላል፡፡ ይሁንና እንዲህ አስተዋጽኦ እያደረገ ላለ ዘርፍ መንግሥት ተመጣጣኙን ትኩረት ሰጥቶታል ብለው ያስባሉ?

አቶ ቢንያም፡- እንደማስበው መንግሥት ለዘርፉ ትኩረት እየሰጠ ነው፡፡ ቱሪዝም ብቻም ሳይሆን የአገልግሎት ዘርፉ በጠቅላላው በአገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ ከፍተኛው የሥራ ዕድል ፈጣሪ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ከግብፅ የፀደይ አብዮት በፊት ከግብፅ ሕዝብ ውስጥ ከ20ዎቹ አንዱ ግብፃዊ በቱሪዝም መስክ የሥራ ዕድል ያገኝ ነበር፡፡ ቱሪዝም በአገሮች ኢኮኖሚ ውስጥ ትልቅ ሚና ይጫወታል፡፡ እንደማስበው የኢትዮጵያ መንግሥት የቱሪዝም ትራንስፎርሜሽን ምክር ቤት በመመሥረት በጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲመራ በማድረግ የሰጠውን ትኩረት ያህል ሌሎች አገሮች የሚሰጡ አይመስለኝም፡፡ የቱሪዝም ምክር ቤት ቦርድ የሚመራውም በአየር መንገዱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ነው፡፡ ይህ ቦርድ የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ አጋርነት የሚንፀባረቅበት ነው፡፡ በአብዛኛው በቱሪዝም ገበያ፣ በቱሪዝም መዳረሻዎች፣ በብራንድ አወጣጥና በመሳሰሉት ጉዳዮች ላይ ይመክራል፡፡ መንግሥት ለዘርፉ ትልቅ አትኩሮት የሰጠው ይመስለኛል፡፡

ሪፖርተር፡- በሆቴል ዘርፍ ካለፉት አምስት ዓመታት በፊትና አሁን ያለውን ለውጥ እንዴት ይገልጹታል?

አቶ ቢንያም፡- ቀደም ብዬ እንደጠቀስኩት ፈጣን ለውጥ እየታየበት የሚገኝ ዘርፍ ነው፡፡ ከተማውን አይተህ የምትገነዘበው ነገር ነው፡፡ በየሦስት ወሩ ሁለት ሆቴል እየተገነባ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ጥሩ ተንቀሳቅሰናል፡፡ ከዚህ ቀደም ከነበረው ይልቅ ብዙ የሥራ ዕድል መፍጠር ችለናል፡፡ ሆኖም በሌላ አቅጣጫ ያለውንም መመልከት ይኖርብናል፡፡ ፍላጎትና አቅርቦትን ማጣጣም ይጠበቅብናል፡፡ መንግሥት ብዙ ሥራ እንደሚያመጣልን ብቻ መጠበቅም ያለብን አይመስለኝም፡፡ ወደ ከተማችን ቢዝነስ እንዲመጣ የማድረግ እኩል ኃላፊነትም አለብን፡፡ ይህም ምናልባት ቶሎ ቶሎ የሚካሄዱ የንግድ ዓውደ ርዕዮችን በማዘጋጀት ሊሆን ይችላል፡፡ ወይም የቱሪዝምና የሆቴል አግልገሎትን የሚያሳዩ ዝግጅቶች ወይም ሌሎችም ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ እነዚህን በማዘጋጀት ሊሆን ይችላል ሰዎች እንዲመጡ ማድረግ ያለብን፡፡ የመሰብሰቢያና የትርዒት ማዘጋጃ ማዕከላትን መገንባት ይኖርብናል፡፡ ጥሩ ደረጃ የሚሰጠው አየር መንገድ አለን፡፡ ይህም በቱሪዝም እሴት ሰንሰለት ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ግብዓት ነው፡፡ የንግድ እንቅስቃሴ በብዛት የሚካሄድባቸው የስብሰባና ተዛማጅ ዝግጅቶች ያስፈልጉናል፡፡ እነዚህ ለቱሪዝም ዘርፍ ከፍተኛ ውጤት የሚያስገኙ እንቅስቃሴዎች ናቸው፡፡ እንዲሁ መቀመጥ አንችልም፡፡ በመሆኑም እንዲህ ያሉት ተግባራት ውስጥ እየተሳተፍን ለውጦችን ለማምጣት እየጣርን ነው፡፡ በአዲስ አበባ ሊገነባ እንቅስቃሴ የሚደረግበት ዓለም አቀፍ የስብሰባና የልዩ ልዩ ዝግጅቶች ማካሄጃ ኮንቬንሽን ሴንተር፣ በግሉና በመንግሥት ዘርፍ አጋርነት የሚካሄድ እንደመሆኑ መጠን የመጨረሻ ውጤቱን ለማየት እንጠባበቃለን፡፡

ሪፖርተር፡- በቱሪዝም መስክ እየታዩ ያሉ ለውጦችን ለመግለጽ ደጋፊ ማስረጃዎችን ማጣቀስ ግድ አይልም፡፡ እንዲሁ የሚታይ ነው ለማለት ነው፡፡ ይሁንና ዘርፉ ከጠቅላላው ኢኮኖሚ አኳያ ያለው ድርሻ ሲታይ በጣም ዝቅተኛ ነው፡፡ ድርሻው ከሦስት በመቶ በታች ነው፡፡ አዳዲስ ትንበያዎች እንደሚያሳዩት ወደ አምስት በመቶ የሚደርሰው ከአሥር ዓመት በኋላ እንደሚሆን ነው፡፡

አቶ ቢንያም፡- እውነቱን ለመናገር እነዚህ ትንበያዎች የሉኝም፡፡ ይሁንና ዘርፉ ከዚህም የበለጠ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ግን አምናለሁ፡፡ በርካታ የሥራ ዕድሎችን እየፈጠርን ነው፡፡ ኢንዱስትሪውም እያደገ ነውና አስተዋጽኦውም በዚያው መጠን ትልቅ እንደሚሆን አስባለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- የሥራ ዕድል ፈጠራውም አሁን ካለበት ይልቅ ወደ አምስት ሚሊዮን ገደማ እንደሚደርስ ተንበያዎቹ ይጠቁማሉ፡፡

አቶ ቢንያም፡- እዚህም ላይ ልል የምችለው ባይኖርም ይኸው እንተ እንደምትገልጸው ከሆነ አስደሳች ዜና ነው፡፡ ምናልባትም በዘርፉ ከፍተኛ የሥራ ዕድል ፈጣሪዎች ሳያደርገን አይቀርም፡፡ ከዚህም በላይ እንደምናድግ እናምናለን፡፡

ሪፖርተር፡- እርስዎ ወደፊት በቱሪዝም መስክ ስለሚሆነው ነገር ቀና ተስፋ አለዎት፡፡ ነገር ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለዱር እንስሳት መጠለያዎችና ፓርኮች ጥፋት ሥጋታቸውን በይፋ ሲገልጹ ቆይተዋል፡፡ የአገሪቱ ፓርኮች አስተዛዛቢ ጥበቃና ክብካቤ በወደፊት ህልውናቸው ላይ አደጋ ደቅኗል፡፡

አቶ ቢንያም፡- ጠቅላይ ሚኒስትሩ በግልጽ እንደተናገሩት እነዚያ ኃላፊዎችም ሆኑ ይህ ትውልድ ወደፊት የታሪክ ተጠያቂነት ይኖርበታል፡፡ እሳቸው ስላስቀመጧቸው ሥጋቶችና ወደፊት ሊመጡ ስለሚችሉት አደጋዎች የተናገሩትን እጋራለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ለእኔ ይህ ማለት የአገሪቱ የአስጎብኝነት ሥራዎች ይጎዳሉ፡፡ ያሉትን ሀብቶች መጠበቅና መንከባከብ በተሳነ ቁጥር እንዲህ ያሉ ዘርፎች ብቻም ሳይሆኑ፣ የታሪክ ተጠያቂነቱም እንዳለ ሆኖ እንደ ሕዝብ ከፍተኛ ጉዳት ይደርሳል ማለት ነው?

አቶ ቢንያም፡- ሁሉም ነገር ያለህን በመጠበቅ፣ በመንከባከብና በማክበር ነው የሚገለጸው፡፡ የተፈጥሮ ፀጋው አለን፡፡ ለቱሪዝም ኢንዱስትሪው በሁሉም መስክ ምቹ የሆኑና የሚስቡ ነገሮች አሉን፡፡ የባህል ብዝኃነታችን የበለፀገ ነው፡፡ ያለንን መንከባከብና መጠበቅ መቻላችን ነው ስለእኛ ብዙ እንዲናገር የሚያደርገው፡፡

ሪፖርተር፡- አሁን በዘርፉ እየታዩ ካሉት ነገሮች አኳያ መንግሥት ያስቀመጣቸው ዕቅዶች ሊሳኩ ይችላሉ ብለው ያምናሉ? ለአብነት ያህል አገሪቱ ከአፍሪካ አምስት ዋና ዋና የቱሪዝም መዳረሻዎች አንዷ ትሆናለች መባሉ ሊሳካ ይችላል?

አቶ ቢንያም፡- እንዲህ ያሉ ግቦች እንዴት እንደሚሳኩ ተለይቶና በየትኛው መስክ እንደሆነ ግልጽ ተደርጎ መቀመጥ አለባቸው፡፡ ለምሳሌ እንዴት ነው ከአምስቱ ዋና ዋና መዳረሻ አገሮች አንዷ ኢትዮጵያ የምትሆነው? ሲባል በሆቴል ብዛት ነው? በሚመጡት ቱሪስቶች ልክ ነው? ለኢኮኖሚው በሚደረግ አስተዋጽኦ ነው? በየትኛው መመዘኛ ነው? የሚለው ተለይቶ መታየት ያለበት ይመስለኛል፡፡

ሪፖርተር፡- ይሁንና ዘርፉ በመጪዎቹ አምስት ወይም አሥር ዓመታት ውስጥ የተቀመጡትን ግቦች ለማሳካት በሚያስችል አቅጣጫ እየተጓዘ ነው ማለት ይቻላል?

አቶ ቢንያም፡- ይህንን የማሳካት ብቃቱ ይኖረናል፡፡ መንግሥት በመሠረተ ልማት ግንባታ መስክ ኢንቨስት እያደረገ ነው፡፡ የባቡር መስመሮች እየተፋጠኑ ነው፡፡ የአየር ትራንስፖርቱም ሆነ የአየር ትራንስፖርት መሠረተ ልማቱም እያደጉ ናቸው፡፡ አየር መንገዱ በየጊዜው እያደገ የበረራ መዳረሻዎቹም እየተስፋፉ ናቸው፡፡ መንግሥት በብዙ መንገዶች እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል፡፡ የቱሪዝም መዳረሻዎች እየተስፋፉ ነው፡፡ የግሉ ዘርፍ ብዙ መሥራት ይጠበቅበታል፡፡ የድርሻችንን መወጣት አለብን፡፡ የመንግሥትን ፋና መከተል ይገባናል፡፡ ይህ እንዲሆን ለማድረግ የሚረዳው አንደኛው መንገድ መንግሥት የሚሰጠው የኢንቨስትመንትና የታክስ ማበረታቻ ነው፡፡ የግሉን ዘርፍ ለማሳተፍ ይህ አንዱ መንገድ ቢሆንም፣ የሚሰጠው ማበረታቻ ግን መታየት አለበት፡፡ በከተማ ኢንቨስት የሚያደርገው ባለሀብት በገጠራማ አካባቢዎች ከሚደረጉት ጋር እኩል ከሆነ፣ ከከተማ ርቀው የሚገኙ ገጠራማ አካባቢዎች በመሄድ ኢንቨስት የሚያደርገው ባለሀብት ለመሄድ አይነሳሳም፡፡ ምክንያቱም በእነዚህ አካባቢዎች የሚያደርገው ኢንቨስትመንት ወጪውን ለማስመለስ ረጅም ጊዜ ስለሚወስድበት ነው፡፡ ይህ በመሆኑም ነው አብዛኞቹ ሆቴሎች በአዲስ አበባና በሌሎች ትልልቅ ከተሞች የተበራከቱት፡፡ ወደ ገጠራማና አብዛኞቹ የቱሪስት መዳረሻዎች በሚገኙባቸው ቦታዎች ሄዶ ኢንቨስት ለማድረግ የሚሰጡት ማበረታቻዎች መሻሻል ብቻም ሳይሆን ለአልሚው ተስማሚና የሚያበረታቱ መሆን ይኖርባቸዋል፡፡