Skip to main content
x
‹‹ግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ መሞታቸውን ባላምንም ሐውልታቸውን የማቆም ሥራ ግን ከሚቀጥለው ዓመት አያልፍም››

‹‹ግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ መሞታቸውን ባላምንም ሐውልታቸውን የማቆም ሥራ ግን ከሚቀጥለው ዓመት አያልፍም››

አቶ ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ፣ የቀድሞ ፕሬዚዳንትና የለም ኢትዮጵያ የበላይ ጠባቂ

‹‹ወደ ኋላ መለስ ብለን ስናስብ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን ልዩ የሚያደርጋቸው ከመንገሣቸው በፊት በሕዝብ የሚመረጡ እንደራሴዎች ከመሳፍንት ተመርጠው የሚሾሙ ሴናተሮችን የያዙ ሁለት ምክር ቤቶችን መመሥረታቸው፣ የመጀመርያውን ሕገ መንግሥት ማውጣታቸው፣ አገሪቱን የሊግ ኦፍ ኔሽን አባል እንድትሆን ማድረጋቸው፣ የፋሺስት ኢጣሊያ ጦር ኢትዮጵያን ሲወር በዚሁ ሊግ ኦፍ ኔሽን ስብሰባ ላይ ያደረጉት ንግግር ዓለምን ማስነደቁ፣ እንዲሁም የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን (የአፍሪካ ኅብረት) በማቋቋም አፍሪካን አንድ ማድረጋቸው፣ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማብቂያ ላይ በዓለም ኃያላን ነገሥታት ዘንድ የነበራቸው ክብር ከፍተኛ መሆን፣ ፕሬዚዳንት ሩዝቬልት፣ ዊኒስተን ቸርችልና ስታሊን በጥቁር ባህር ያልተወደበ መርከብ ላይ ስብሰባ ሲያደርጉ በክብር እንግድነት መገኘታቸው ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ለእኝህ ታላቅ መሪ መታሰቢያ ሐውልት እንዲቆምላቸው ቢፈቀድ የግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ መታሰቢያ ማኅበር ኃላፊነቱን ወስዶ እንደሚያሠራ አምናለሁ፤›› ይህ ጥቅስ የተወሰደው የቀድሞ ፕሬዚዳንትና የለም ኢትዮጵያ የበላይ ጠባቂ አቶ ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ ጥር 15 ቀን 2009 ዓ.ም. በቁጥር የቀኢፌዴሪፕ 899/2009 ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ከጻፉት ማስታወሻ ተቀንጭቦ ነው፡፡ በዋናነት መታሰቢያ ሐውልት የማቋቋሙን ጉዳይ፣ እንዲሁም በስማቸው ይጠራ የነበረው የቀድሞ በጎ አድራጎት ድርጅትን ንብረት ማኅበሩ እንዲመለስለት ያቀረበውን ጥያቄና ከንጉሠ ነገሥቱ ጋር የነበራቸውን መቀራረብ በተመለከተ የቀድሞውን ፕሬዚዳንት ታደሰ ገብረ ማርያም አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መታሰቢያ ማኅበር ሊቋቋም የቻለው አፅማቸውን ወደ ተዘጋጀላቸው መካነ መቃብር በክብር ለማሳረፍ ሲባል ነበር፡፡ ይህም ከተከናወነ በኋላ በትምህርት ዘርፍ እንደ አንድ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት መሥራት የሚያስችለውን ሕጋዊ ዕውቅና ጉዳዩ ከሚመለከተው መንግሥታዊ አካል ተሰጥቶታል፡፡ ለሥራው እንዲረዳው በስማቸው ይጠራ የነበረውንና በቀድሞ ሥርዓት የተወረሰው የበጎ አድራጎት ድርጅት ንብረት እንዲመለስለት ጠይቆ እስካሁን የተፈጸመ ነገር የለም፡፡ እርስዎ በአባልነትዎ የማስመለሱን ሥራ እንዴት ያዩታል?

አቶ ግርማ፡- ማኅበሩ መኖሩን አውቃለሁ፡፡ መቼ እንደተቋቋመ ግን አላውቅም፡፡  ግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ መሞታቸውንም አላምንም እንደ ጃማይካዎች፡፡ በተረፈ የማኅበሩ አባል ከሆንኩ ገና ሦስት ዓመት ሆኖኛል፡፡ በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ንብረቶቹን ለማስመለስ እየተካሄደ ባለው እንቅስቃሴ አልተሳተፍኩም፡፡ ከእንግዲህ በኋላ ግን እታገላለሁ፡፡ የግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴን መታሰቢያ ሐውልት የማቆም እንቅስቃሴን ግን እንደ ግል ጉዳዬ አድርጌ ነው የያዝኩት፡፡ ይህንንም ያደረግኩት የማኅበሩ አባል ስለሆንኩ አይደለም፡፡ ግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ በእውነት ትልቅ ሰው ናቸው፡፡ አንዳንዴም ጃማይካዎች የሚሉት እውነታቸውን ነው፡፡ ቅዱስነትም ይኖራቸዋል፡፡ ምክንያቱም የአውሮፓ አገሮች አንዱ በሌላው ቢጠቃ የማንገራገሪያ መንገድ ሲፈልጉ ‹‹ሊግ ኦፍ ኔሽን›› የሚባል ተቋም መሥርተዋል፡፡ በዚያን ጊዜ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አልነበረም፡፡

ኢትዮጵያ በፋሺስት የኢጣሊያ ጦር ከመወረሯ በፊት ጄኔቭ ሄደው በእነ ብላታ ሎሬንሶ ረዳትነት የሊግ ኦፍ ኔሽን አባል እንድትሆን አድርገዋል፡፡ ይህም የሚያሳየው  ቢኖር ምን ያህል አርቆ አስተዋይ እንደነበሩ ነው፡፡ ሲነግሡም እንደማንኛውም ሌላ ንጉሥ አንድ ቄስ አስቀምጥተውና አስባርከው ዘውዱን መድፋት ይችሉ ነበር፡፡ እሳቸው ግን በቅድሚያ የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚተዳደርበትን ሕግ ወይም ሕገ መንግሥት አውጥተው፣ እንዲሁም የሚሾሙ ሴናተሮቸና በሕዝብ የሚመረጡ እንደራሴዎችን የያዙ ሁለት ምክር ቤቶች (አፐር ኤንድ ሎወር ሐውስ) አቋቁመው ነው ዘውድ የጫኑት፡፡ ይህም ከተጠናቀቀ በኋላ ሞአ አንበሳ ዘ እምነ ይሁዳ  ኃይለ ሥላሴ ሥዩመ እግዚአብሔር ንጉሠ ነገሥት ዘ ኢትዮጵያ ተባሉ፡፡ ከዚህ በፊት አገሪቷ ሕገ መንግሥት አልነበራትም፡፡ የመጀመርያው የሕገ መንግሥት ሥራ የግርማዊ ቀዳማዊ አፄ አኃይለ ሥላሴ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ሞአ አንበሳ ዘ እምነ ነገደ ይሁዳ ምን ማለት ነው?

አቶ ግርማ፡- የይሁዳ አንበሳ ሲባል የሳባ ልጅ ምኒልክን ነው የሚያመላክተው፡፡ ንጉሥ ምኒልክ የንጉሥ ሰለሞን ልጅና የመጀመርያው የኢትዮጵያ ንጉሥ ነው፡፡ ሞአ አንበሳ ዘ እምነ ነገደ ይሁዳ ማለት ከዚያ ሥርዓት የመጣ እንደ ማለት ነው፡፡ 

ሪፖርተር፡- የቀድሞው በጎ አድራጎት ድርጅት ንብረት የተወረሰው በአዋጅ ወይም በሕግ ነው፡፡ በዚህ መንገድ የተወረሱ ንብረቶችን ለማስመለስ ደግሞ ያለው ብቸኛ አማራጭ የፖለቲካ ውሳኔ ነው፡፡ በማስመለሱ ሥራ ላይ እስከ ዛሬ ድረስ ባይሳተፉም በፖለቲካ ውሳኔው ላይ ያለዎት አስተያየት ምንድነው?

አቶ ግርማ፡- የበጎ አድራጎት ድርጅቱ ንብረቶች በመጀመርያውኑ ሊወረሱ አይገባም ነበር፡፡ ማኅበሩ ንብረቶቹ እንዲመለሱለት የሚፈልገው እኮ ለሌላ ተግባር ለማዋል ፈልጎ ሳይሆን፣ ከደሃ ደሃ ቤተሰብ ለወጡና በትምህርታቸው ከፍተኛ ውጤት ላመጡ ችግረኛ ተማሪዎች የመጀመርያ ዲግሪ እስከሚያገኙ ድረስ ስኮላርሽፕ በመስጠት የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ፣ በዚህ ዓይነቱ ድጋፍ የሚማሩ ተማሪዎችን ቁጥር ከፍ ለማድረግ ነው፡፡ ከዚህም ባለፈ የተጠናከረና በሚገባ የተደራጀ ቤተ መጻሕፍት ለማቋቋም ነው፡፡ ማኅበሩ በትምህርት ዘርፍ ለመሥራት ያነሳሳው ዋናው ምክንያት የግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴን ፈለግ በመከተል ወይም ለትምህርት መስፋፋት ያበረከቱትን አስተዋጽኦ ከግምት ውስጥ በማስገባት ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ሲታይ ማኅበሩ ለበጎ አድራጎት ሥራ የተቋቋመ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት መሆኑ መታወቅ ይኖርበታል፡፡ ንብረቶቹም እስካሁን ያልተመለሱት አስታዋሽ በመጥፋቱ ነው፡፡ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ይህንን ቢያውቁ ኖሮ ያስመልሱት ነበር፡፡ ምክንያቱም ለግል ሳይሆን ኅብረተሰቡ የሚጠቀምበት ነው፡፡ ከዚህ አንፃር የተወረሱት ንብረቶች ይመለሳሉ የሚል የፀና እምነት አለኝ፡፡

ሪፖርተር፡- ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ንብረቶቹን በማስመለስ ላይ ያተኮሩ ተከታታይ ደብዳቤዎች ማኅበሩ ጽፏል፡፡

አቶ ግርማ፡- መጻፍ ብቻ በቂ አይደለም፡፡ ማንኳኳት፣ መጎትጎትና መከታተል  ይጠይቃል፡፡

ሪፖርተር፡- ሐውልቱን የማቆም ሥራ ግን እንደ ግል ሥራዎ አድርገው እንደያዙት ነው የነገሩን፡፡ ታዲያ አሁን ምን ደረጃ ላይ ደርሷል?

አቶ ግርማ፡- የግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ሐውልት መሠራት አለበት፡፡ የሚሠራውም ወይም የሚተከለውም የቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ሕንፃ ፊት ለፊት ባለውና የአፍሪካ መሪዎች በተከሏቸው የዛፍ ችግኞች ውስጥ በሚገኘው መናፈሻ ነው፡፡ ይህ መናፈሻ የሌሊን ሐውልት ቆሞበት በነበረው ሥፍራ ነው፡፡ ፓርኩ ውስጥ በመሪዎቹ የተተከሉት የዛፍ ችግኞች በአሁኑ ጊዜ አድገው አካባቢው ተጨማሪ ውበት እንዲጎናፀፍ አድርገዋል፡፡ በዚህ መናፈሻ ሐውልታቸው መቆሙ ብዙ ትርጉምና ታሪካዊ አንድምታዎችን ይይዛል የሚል መልዕክት ያለበትን የጽሑፍ ማስታወሻ ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ አቀረብኩ፡፡

ሪፖርተር፡- መልሱ ምን ሆነ?

አቶ ግርማ፡- እንቢም እሺም አላሉም፡፡ ጉዳዩ እንዲያው በእንጥልጥል ላይ ነው ያለው፡፡ ግን ያቀረብኩት ሐሳብ በየት በኩል እየገፋ እንደሄደ ባላውቅም፣ በአፍሪካ ኅብረት ግቢ ውስጥ የግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ሐውልትና የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ መታሰቢያ እንዲቆሙ ተወስኗል፡፡ ይህንንም ስሰማ በጣም ደስ አለኝ፡፡ ምክንያቱም ሐውልት እንዲቆም በመፈቀዱ ብቻ፡፡ የት እንደሚቆም ግን የአፍሪካ ኅብረት ኃላፊዎች አይደሉም ቦታ የሚመርጡልን፣ እኛ መምረጥ አለብን፡፡ እንዴት እንደሚቆምና ምን ዓይነት እንደሆነም መምረጥ ያለብን እኛው ነን፡፡

ሪፖርተር፡- የአፍሪካ መሪዎች የወሰኑት የአፍሪካ ኅብረት ቅጥር ግቢ ውስጥ ነው፡፡

አቶ ግርማ፡- የእነሱን ድርሻ በተጠቀሰው ግቢ ውስጥ ሊያሠሩ ይችላሉ፡፡ እኛ ግን የራሳችንን ድርሻ የምናቆመው የቀድሞው አፍሪካ አንድነት ድርጅት (አፍሪካ አዳራሽ) ፊት ለፊት ነው፡፡ ይህም ደረጃውን የጠበቀ፣ ኢትዮጵያዊነታቸውን አጉልቶ የሚያሳይና የኢትዮጵያን ገጽታ የተላበሰ ነው መሆን ያለበት፡፡

ሪፖርተር፡- ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የጻፉት ማስታወሻ መልስ ሳይገኝበት በእንጥልጥል ላይ እንዳለ ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ አፍሪካ አዳራሽ ፊት ለፊት ወይም የሌኒን ሐውልት ቆሞበት በነበረው ሥፍራ ላይ ማሠራት እንዴት ይቻላል?

አቶ ግርማ፡- ማስታወሻውን የጻፍኩላቸው ለአፍሪካ ኅብረት ከመወሰኑ በፊት ነው፡፡ እርግጥ ነው እስካሁንም ለጽሑፉ መልስ አልሰጡኝም፡፡ ይህም ቢሆን ግን እንደገና አንጠይቃቸውም፡፡ ምክንያቱም ጉዳዩ ከእሳቸው ውጪ ሆኗል፡፡ ስለዚህ አቅም ካለ ማቆም ይቻላል፡፡ የቀረው ነገር ቢኖር የሐውልቱን ዓይነት የመምረጥ ጉዳይ ነው፡፡ ይህም ጉዳይ የማኅበሩ የሥራ ድርሻ ነው የሚሆነው፡፡

ሪፖርተር፡- ሐውልቱን ለማስቆም የሚያስችል ገንዘብ ከየት ይገኛል?

አቶ ግርማ፡- ምንም ችግር የለም፡፡ በአንድ ቀን ወይም በ24 ሰዓት ውስጥ ገንዘብ እናገኛለን፡፡ በዚህም ሙሉ ለሙሉ እተማመናለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ሐውልቱን የማቆም ሥራ ከስንት ዓመት በኋላ ይጀመራል ብለው ያስባሉ?

አቶ ግርማ፡- ለነገሩማ ሐውልታቸው አለ ለማለት ይቻላል፡፡ ይኼውም የአፍሪካ መሪዎች የመጀመርያ ስብሰባ ያካሄደበት ቤት ወይም አዳራሽ ሐውልታቸው ነው ለማለት ይቻላል፡፡ አጠገቡ ሥዕላቸው ይቁም ለማለት ነው እንጂ ቤቱ የራሳቸው ነው፡፡ በውስጡ ያሉት ሥዕሎችና ፓርኩ ውስጥ የተተከሉ ዛፎች ሁሉ የእሳቸው ነው፡፡ ከዚህ አንፃር የእሳቸው ገጽታ ያልሆነ ነገር የለም፡፡ ይህም ሆኖ ግን የትክክለኛው ሐውልታቸው ግንባታ ወይም የማቆሙ ሥራ ከሚቀጥለው ዓመት በላይ አያልፍም፡፡

ሪፖርተር፡- ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን በደንብ ያውቋቸዋል፡፡ በትውውቃችሁ ወቅት ካከናወኗቸው ተግባራት መካከል እስከ ዛሬ ድረስ ሲያስቡት የሚያስደስትዎት ወይም ረክቼበታለሁ የሚሉት የትኛው የልማት ሥራ ነው? በዚህስ ሒደት ያጋጠመዎት ፈተና ምን ይመስላል? እንዴትስ ተወጡት?

አቶ ግርማ፡- ግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴን በደንብ አውቃቸዋለሁ፡፡ ቅርበትም ነረበኝ፡፡ የማውቃቸውም እንደ ንጉሥ ብቻ ሳይሆን እንደ ማንኛውም ሰው ነው፡፡ አንዳንዴም ይጣሉኛል፡፡ እኔም ደፋርና ተናጋሪ ነበርኩ፡፡ አቀራረቤን ከተገነዘቡና የምሰጣቸው መልሶች ካረካቸው ወዲውያውኑ ከቁጣ ወይም ከንዴት መለስ ይሉና ይመርቁኛል፡፡ በትውውቃችን ዘመን ሠራሁ ብዬ እስካሁን ድረስ የምኮራባቸው ከልማት ተግባራት መካከል አንዱና ዋነኛው በተለያዩ ክልሎች (ጠቅላላ ግዛቶች) 34 የአውሮፕላን ማረፊያዎችን ማሠራቴ ይገኝበታል፡፡ ይህንንም ላሠራ የቻልኩት የሲቪል አቪዬሺን ዳይሬክተር በነበርኩበት ወቅት ነው፡፡ ሁኔታው እንዲህ ነው፡፡ በአንድ ወቅት ግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ 35 የአውሮፕላን ማረፊያዎች እንዲሠሩ ዙፋናዊ ትዕዛዝ ሲሰጡ፣ ሥራውንም ለማስፈጸም ከዓለም ባንክ ብድር ተጠየቀ፡፡ ያን ጊዜ የትራንስፖርትና መገናኛ ሚኒስትር የነበሩት ክብር ደጃዝማች ገብረ ሥላሴ (ዶ/ር) ወደ አሜሪካ አቅንተው ከዓለም ባንክ ብድሩን አገኙ፡፡ አውሮፕላን ማረፊያዎቹን የሚያሠራው ‹‹አማን ኤንድ ዊትኒ›› የተባለ የአሜሪካ ኩባንያ ስለሆነ፣ ሥራውን ለማስጀመር የኩባንያው ዳይሬክተር ሚስተር ሄደን መጥቶ ግዮን ሆቴል ተቀመጠ፡፡ ብድሩም ቢገኝ መንግሥት ካላፀደቀው በስተቀር ሥራውን ለማስጀመር አልተቻለም ነበር፡፡ ዳይሬክተሩም ያለሥራ መቀመጣቸው ታከታቸው፡፡

ሪፖርተር፡- ሥራው እንዲጀመር ምን አደረጉ?

አቶ ግርማ፡- የሚኒስትሮች ምክር ቤት ኃላፊ ለነበሩት ለአቶ ተፈራ ወርቅ ኪዳነ ወልድ ይህንን ነገር ፍቀዱልኝና ሥራውን ልጀምር ብዬ ጠየኩዋቸው፡፡ ሲያዩኝ የሚጠሉኝ ሰው ስለነበርኩ ‹‹ገና አጀንዳ ተይዞ ነው›› አሉኝ፡፡ እንደገና በሳምንቱ ተመልሼ ስመጣ ራስ አበበ አረጋይ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሰብሳቢ ሆነው አገኘኋቸው፡፡ ጉዳዩንም ነገርኳቸው፡፡ ‹‹ደህና እንግዲህ እናየዋለን›› አሉኝ፡፡ ሁኔታውን እንደገና ስገምግመው ተፈራ ወርቅ ኪዳነ ወልድ ስለማይወዱኝ ጉዳዩን ወደ ኋላ ሊያጓትቱብኝ ሆነ፡፡ ራስ አበበ ደግሞ አርበኛ ናቸው እንጂ፣ ጉዳዩን ይህን ያህል ልብ ሊሉት እንደማይችሉ ተገነዘብኩ፡፡ በዚህም የተነሳ ለምን እኔ ራሴ አንድ ቀን መንግሥት አልሆንም? ብዬ አሰብኩ፡፡ አስቤም አልቆምኩም፡፡ የሚኒስትሮች ምክር ቤትን ለውጬ ራሴ አሠራዋለሁ ብዬ ወሰንኩ፡፡

ሪፖርተር፡- ውሳኔውን ተግባራዊ በማድረግዎ የተነሳ ከቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ጋር አልተጋጩም?

አቶ ግርማ፡- በመጀመርያ አማካሪዬ ደብዳቤ እንዲያረቅልኝ አደረግኩ፡፡ የደብዳቤውም ረቂቅ ሥራው እንዲከናወን ትዕዛዝ ለመስጠት የሚያስችለኝ ነው፡፡ የኩባንያውንም ዳይሬክተር አስጠራሁትና መንግሥት የአውሮፕላን ማረፊያዎችን ግንባታ ስለረሳው እኔ መንግሥትን ተክቼ ልሠራ ነው፡፡ ስለዚህ ቀጥል ሥራህን ብዬ ብልህ ትቀጥላለህ ወይ? ብዬ ጠየኩት፡፡ ‹አንተ ካልክ እቀጥላለሁ› አለኝ፡፡ ወዲያውኑ ከ35 አውሮፕላን ማረፊያዎች ውስጥ 34ቱን አሠርተን አጠናቀቅን፡፡ ይህም ከተጠናቀቀ በኋላ አቶ ተፈራ ወርቅ ኪዳነ ወልድ እኔን ከማይወዱኝ ሰዎች ጋር ሆነው፣ ከአየር ኃይል የመጣ አንድ መቶ አለቃ ግርማ የሚባል እብድ መንግሥት ያልፈቀደውን ሥራ ያሠራል በማለት አጉረመረመብኝ፡፡ ይህም ጉዳይ ግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ዘንድ ደረሰ፡፡ በጣም ተቆጡ፣ ቤተ መንግሥት አስጠሩኝ፡፡ እሳት ለብሰው እሳት ጎርሰው ጠበቁኝ፡፡  ገባሁና እጅ ነሳሁ፡፡ ‹‹መንግሥት ያልፈቀደውን ሥራ ታሠራለህ?›› አሉኝ፡፡ እርስዎ ደጃዝማች ዘውዴ ገብረ ሥላሴን ወደ ዓለም ባንክ ልከው ገንዘብ እንዲበደሩና በዚህም ገንዘብ 35 የአውሮፕላን ማረፊያዎች እንዲሠሩ ራስዎ በፈረሙት ደብዳቤና በገቡትም መተማመኛ መሠረት ነው የሠራሁት ብዬ መለስኩላቸው፡፡ እሳቸውም ይህን ከሰሙ በኋላ ወደ ተፈራ ወርቅ ኪዳነ ወልድ ዞር ብለው ‹‹ለምን ሠራ ብላችሁ ነው የከሰሳችሁት?›› አሏቸው፣ ነገሩም ተገለባበጠ፡፡ እኔንም ተባረክ አሉኝና ተመርቄ ወጣሁ፡፡ ከገጠሙኝ ፈተናዎች አንዱ ይህ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- 34 የአውሮፕላን ማረፊያዎች የት አካባቢ ነው የተሠሩት?

አቶ ግርማ፡- ከአሮጌው አውሮፕላን ማረፊያና ከቦሌ ኤርፖርት በስተቀር በሁሉም ክልሎች (ጠቅላይ ግዛቶች) የሚገኙ ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- የሲቪል አቪዬሽን ዳይሬክተር ተብለው የተሾሙት እንዴት ነበር?

አቶ ግርማ፡- መጀመርያ ተሹመው የነበሩት አቶ ተፈራ ደግፌ ናቸው፡፡ በዚያን ወቅት እኔ አስመራ ነበርኩ፡፡ አቶ ተፈራ ደግሞ እኔ የገንዘብ እንጂ የአየር ሰው አይደለሁም፡፡ ለዚህ ቦታ ተስማሚ ሰው መቶ አለቃ ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ ናቸው ብለው በጠቆሙት መሠረት ከአስመራ ተጠርቼ ነው የተሾምኩት፡፡

ሪፖርተር፡- ከሲቪል አቪዬሽን እንዴት ለቀቁ?

አቶ ግርማ፡- አልሠራም ብዬ ወጣሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ከዚያ ወዴት ሄዱ?

አቶ ግርማ፡- ፓርላማ ተመረጥኩና ወዲያውኑ የፓርላማው ሊቀመንበር ሆንኩ፡፡ አሁንም እንደገና ደግሞ ከጃንሆይ ጋር በድጋሚ ተገናኘሁ፡፡ ውሎ አድሮ ‹‹መሬት ላራሹ›› የሚል መጣ፡፡ ሆኖም ግን አንዳንድ ወገኖች ይህ ሕግ ሆኖ እንዳይመከርበት የሚል ሐሳብ ለጃንሆይ አቀረቡ፡፡ በመካከሉ ደግሞ ጃንሆይ ያስጠሩኝና ‹‹በባላገር ችግር ተፈጥሯል፡፡ በዚህም ሰው ይገዳደላል አሉ፡፡ ኧረ ይኼ ነገር እንዴት ነው?›› ሲሉ ጠየቁኝ፡፡ እኔም አይ ግርማዊ ሆይ! መቼም ሰው ካልተረዳና ካልገባው ብዙ ነገር ያደርጋል፡፡ ማስረዳት ነው ያለብን እንጂ ማቆም አይደለም፡፡ የታሰበውን ጥሩ ነገር ተግባራዊ ለማድረግ ፀንተን መሟገት አለብን አልኳቸው፡፡ ተረዱኝ፡፡ እሺ እስኪ እናንተም አስቡበት አሉና ተመለስኩ፡፡

ሪፖርተር፡- ፓርላማ ውስጥ ለንስት ዓመት ያህል አገለገሉ? በቆይታችሁ ዓመታት  በሐሳብ ሳትግባቡ ስትቀሩ ምን ዓይነት ዕርምጃ ነበር የምትወስዱት?

አቶ ግርማ፡- ፓርላማ የቆየሁት ለአራት ዓመታት ነው፡፡ በሐሳብ ካልተግባባን ያን ያልተግባባንበትን ነገር አስበን እንደገና ልናየው እንድንችል የምናደርገው ነገር ቢኖር፣ የተወሰኑ እንቢተኞች ይፈጠሩና ይወጣሉ፡፡ በዚህም ኮረም ይጎድላል፡፡ ቤቱ ይበተናል፡፡ እንደገና ሌላ ስብሰባ አድርገን ነው የምናየው፡፡

ሪፖርተር፡- ይህን ዓይነቱን አካሄድ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ እንዳልወደዱትና እንደተበሳጩ ነበር ያለኝ መረጃ፡፡ እስኪ ዝርዝር አድርገው ቢያብራሩልኝ?

አቶ ግርማ፡- አዎ፡፡ በአንድ ወቅት ከፍ ብሎ በተጠቀሰው ምክንያት ምክር ቤቱ ተበትኖ ነበር፡፡ በዚያን ወቅትም ግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ከምፅዋ ተመልሰው ነበር፡፡ መቶ አለቃ ግርማ የተባለ በጥባጭ ምክር ቤቱን በተነው፡፡ ደግሞ ይኼን ያደረገው የአፍሪካ መሪዎች በሚሰበሰቡበት አካባቢ ኢትዮጵያን ለማውረድ ነው ብለው ይነግሩዋቸዋል፡፡ በዚህም የተነሳ እኔና ምክትሌ ቤተ መንግሥት ተጠራን፡፡ ቤተ መንግሥት ግቢ ውስጥ ከምትገኝ አንድ ክብ ቤት አጠገብ ቆመው ጠበቁን፡፡ መቼም ያስፈራሉ፡፡ እኛም ለጥ ብለን እጅ ነሳን፡፡ ‹‹ለመሆኑ ምንድናችሁ?›› ሲሉ ጠየቁን፡፡ ግርማዊ ሆይ! አማካሪዎች ነን አልኳቸው፡፡ የተጠራንበት ጉዳይ ምክር ቤትን የሚመለከት ከሆነ ሁሉንም መመለስ እችላለሁ አልኳቸው፡፡ ‹‹በቀደም ዕለት ምክር ቤቱ ለምን እንዲበተን አደረግክ?›› ሲሉ ጠየቁኝ፡፡ ይኼማ በውስጥ ደንባችን መሠረት አንድ ነገር ቢበላሽ ያንን ለማስተካከል ከምንወስዳቸው ዕምርጃዎች መካከል አንዱ፣ ለጊዜው መበተንና እንደገና መመለስ ነው አልኳቸው፡፡

‹‹የሶማሌ ሬዲዮ ያንተን ስም እየጠራች ስትናገር ሰምትሃል?›› አሉኝ፡፡ እኔ በቀጥታ አልሰማሁም፡፡ ግን ሰዎች ነግረውኛል ስል መለስኩላቸው፡፡ ይህም ሆኖ ግን በሰማሁት እኔ ደስ ብሎኛል አልኳቸው፡፡ ‹‹እንዴት?›› ሲሉ ጠየቁኝ፡፡ የኢትዮጵያ ፓርላማ ጠንክሯል፡፡ ይሠራል እያሉ ከሆነ በኢትዮጵያ መንግሥት ያምናሉ፣ ያከብሩናልም አልኳቸው፡፡ ‹‹በል ተባረክ ውጣ›› አሉኝ፡፡ ተረግሜ ገብቼ ተመርቄ ወጣሁ፡፡ ሌላው ያጋጠመኝ ፈተና ይኼ ነበር፡፡ እኔን እስር ቤት ሊወስድ ይጠባበቅ የነበረውም መኪና ወዲያውኑ ወደ መጣበት ባዶውን ተመለሰ፡፡ አማካሪዎቹ ደግሞ በሁኔታው ተደናግጠው የሚከተለውን ዕርምጃ ለማየት እዚያ ድረስ ተሠልፈው መጥተው ነበር፡፡ በመጨረሻም ‹ካባ ልበስ በሞቴ› ብለው ተሸክመው ወሰዱኝ፡፡

ሪፖርተር፡- በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ላይ ያለዎትን ገጠመኝ በአጭሩ ቢገልጹልኝ?

አቶ ግርማ፡- አንድ ወቅት ጄኔቭ ሲዊዘርላንድ ለስብሰባ ሄጄ ከሆቴል ወጣ ብዬ አውቶብስ እጠብቅ ነበር፡፡ የአገሬን ባንዲራ አሽቆጥቁጦ የለበሰ አንድ ሰው ወደ እኔ መጣ፡፡ ሰላምታ ከተለዋወጥን በኋላ ‹‹ከየት ነው?›› አለኝ፡፡ ከኢትዮጵያ አልኩት፡፡ ‹‹የእናንተ ንጉሥ እኮ የኛ እግዚአብሔር ነው፤›› አለኝ፡፡ እኔ ደግሞ ጉልበተኛ ነበርኩና እሳቸው እግዚአብሔራችሁ ከሆኑ እኔ ደግሞ ቅዱሳችሁ (ሴንት) ነኝ አልኩት፡፡ በዚህ ጊዜ ተቆጣ፡፡ አይ እንግዲህ ምክንያታችሁን ካስረዳኸኝ ቅዱስነቴን እሰርዝ ይሆናል አልኩት፡፡ በጣም የሚገርም ነገር አስተማረኝ፡፡

‹‹ከፋሺስት ኢጣሊያ ወራሪ ጦር ጋር በምትዋጉበት ጊዜ ጃማይካ ውስጥ የሚታተም አንድ ጋዜጣ ራስ ተፈሪ የጥቁር ጦር እየመራ ከጣሊያን ጋር ይዋጋል፡፡ ነጭን የሚወጋ ጥቁር ሰው ካለ ያ ጥቁር ሰው መሲህ ነው የሚል ጽሑፍ ይዞ ወጥቶ ነበር፡፡ ብሎ ነገረኝ፡፡ እኔም ይኼንን በአግራሞት ከሰማሁ በኋላ በል እንግዲህ ቅዱስነቴን አንስቻለሁ አልኩት፡፡ አፄ ኃይለ ሥላሴን እግዚአብሔር ናቸው ብለው የሚያምኑት ጃማይካውያን ‹ራስ ተፈሪያንስ› ይባላሉ፡፡ ለእነሱና በኢጣሊያ ወረራ ጊዜ ከጎናችን ቆመው ወረራውን ለተከላከሉ ኤርትራውያን ‹‹ስመጥር ሐማሴን›› በሚባል መጠሪያ ሻሸመኔ አካባቢ ቦታ ተሰጥቷቸው ኑሯቸውን እንዲመሠርቱ ተደርጓል፡፡