Skip to main content
x
‹‹ግብፅ ሩጫዋን ስትጨርስ በተቀመጠው ማዕቀፍ መሠረት ወደ ንግግር መምጣቷ አይቀርም››

‹‹ግብፅ ሩጫዋን ስትጨርስ በተቀመጠው ማዕቀፍ መሠረት ወደ ንግግር መምጣቷ አይቀርም››

አቶ አበበ ዓይነቴ፣ በውጭ ግንኙነት ስትራቴጂካዊ ጥናት

ኢንስቲትዩት የጂኦፖለቲካ ጉዳዮች ተመራማሪ

አቶ አበበ ዓይነቴ በኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ስትራቴጂካዊ ጥናት ኢንስቲትዩት የጂኦፖለቲካ ጉዳዮች ተመራማሪ ናቸው፡፡ በጋዜጠኝነትና ኮሙዩኒኬሽን የትምህርት መስክ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመጀመርያ ዲግሪ አግኝተዋል፡፡ በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የዘመን መጽሔት አዘጋጅ ሆነውም ሠርተዋል፡፡ ከዚያ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኢንስቲትዩት በሴኩሪቲ ስተዲ የማስተርስ ዲግሪያቸውንም ሠርተዋል፡፡  ከ2002 ዓ.ም. ጀምሮ እስካሁን ድረስ ባለፉት ሰባት ዓመታት በውጭ ግንኙነት ስትራቴጂክ ጥናት ኢንስቲትዩት ከተመራማሪነት እስከ ዲፓርትመንት ኃላፊነት አገልግለዋል፣ እያገለገሉም ይገኛሉ፡፡ በዛሬው ቆይታቸውም በምሥራቅ አፍሪካ አገሮች መካከል፣ በተለይም በዓባይ ወንዝ ተፋሰስ አገሮች መካከል ስላለው ወቅታዊ ሁኔታና በቀጣናው ስላለው አሠላለፍ በተመለከተ ከዘመኑ ተናኘ ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በቅርቡ በሱዳን ይፋ የሥራ ጉብኝት አድርገዋል፡፡ ጉብኝቱ በሁለቱ አገሮች መካከል ከሚኖረው የኢኮኖሚ ትስስር ይልቅ፣ በዓባይ ዲፕሎማሲ ላይ የተሻለ ውጤት ያስመዘግባሉ የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ ከዚህ አንፃር የሱዳን ሚና በዓባይ ዲፕሎማሲ ምን ሊሆን ይችላል?

አቶ አበበ፡- ላለፉት አሥራ ሰባት ዓመታት በተለይም ደግሞ ከኢትዮ ኤርትራ ጦርነት በኋላ ኢትዮጵያ ባዘጋጀችው የውጭ ግንኙነትና አገራዊ ደኅንነት ስትራቴጂ ዶክመንት ላይ፣ እያንዳንዱን አኅጉር በተለይ ጎረቤት አገሮችን ጨምሮ ምን ዓይነት ፖሊሲ እንደምትከተል፣ ምን ዓይነት ፀጋዎች እንዳሉ፣ ተግዳሮቶችስ ምን እንደሆኑ በደንብ ተለይቶ ተቀምጧል፡፡ ከዚህ አንፃር አንዱ ተለይቶ የተቀመጠው የወደብ አገልግሎት ነው፡፡ ምክንያቱም ፑንትላንድንና ሶማሌላንድን እንደ አገር ከወሰድናቸው ወደ ዘጠኝ አገሮች ናቸው በኢትዮጵያ ማዕከል ያሉት፡፡ እነዚህ ሁሉም አገሮች ከአንድና ከሦስት በላይ ወደቦች አሏቸው፡፡ ለምሳሌ ሶማሊያ ብቻዋን አሥር ወደቦች ናቸው ያሏት፡፡ ኢትዮጵያ ግን የላትም፡፡ ኢትዮጵያ ለብዙ ጊዜ ከጂቡቲ ነበር የወደብ አገልግሎት ስትጠቀም የቆየችው፡፡ አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ሲታይ በእርግጥም የጂቡቲ የወደብ አገልግሎት ሽፋን የሰፋ ስለሆነ፣ አሁንም ቢሆን በአገልግሎት ላይ ክፍተቶች እንዳሉ በተለያዩ ጊዜ ተገልጋዮች በተለይ አስመጪዎችና ላኪዎች የሚያነሱት ነው፡፡ ቀልጣፋና ፈጣን አገልግሎት ከመስጠት አንፃር የሚታየው አንዱ ነገር ነው፡፡ ሌላው ኢትዮጵያ እንደ ስትራቴጂ ያስቀመጠችው፣ በሁሉም ጎረቤት አገሮች ያሉትን ወደቦች በእኩል ደረጃ መጠቀም ነው፡፡ ከመርህ አንፃር ካየኸው የእኩል ተጠቃሚነት የሚለው መርህ ነው፡፡ እነዚህ አገሮች ወደብ ነው ያላቸው፡፡ ኢትዮጵያ ካልተጠቀመች የእነዚህን አገሮች ወደብ በስፋት ሊጠቀም የሚችል የለም፡፡ አንዱ ጥቅም ይኼ ነው፡፡ ከመርህ አንፃር የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዕድገት ከጎረቤት አገሮች ጋር ባለው የኢኮኖሚ ትስስር ይለካል፡፡ ኢትዮጵያ ኢኮኖሚዋ በጣም ካደገና የወደብ ፍላጎቷ በጨመረ ቁጥር የአገሮችን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ይጨምራል የሚለው ነው፡፡ በዚህ ረገድ ለተወሰነ ጊዜ ሙሉ በሙሉ በጂቡቲ ላይ ብንቆይም፣ አሁን በሁሉም አገሮች ላይ የወደብ አገልግሎትን ማስፋት እንደ ስትራቴጂ እየታየ ነው፡፡ ምንም እንኳ በቀጣናውና በመካከለኛው ምሥራቅ ከተፈጠረው ሁኔታ ጋር ለማያያዝ ቢሞከርም፣ እንደ ስትራቴጂ የተቀመጠው ከሁሉም አገሮች የወደብ አገልግሎት ማግኘት የሚለው መርህ ነው፡፡ ስለዚህ ያ ነው ወደ ተግባር እየተመነዘረ ያለው፡፡ በአጠቃላይ አንዳንድ ሰዎች የራሳቸውን ትርጓሜ ወይም ፍቺ ሊሰጡ ይችላሉ፡፡ ግን ይኼ የወደብ አጠቃቀም ስትራቴጂ ዶክመንቱ ያስቀመጠው ነው፡፡ ኢትዮጵያም ለረዥም ጊዜ መከተል አለብኝ ብላ ካስቀመጠችው አንፃር ሊታይ ይችላል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ፍላጎት ሁል ጊዜ ገደብ የለውም፡፡ ጂቡቲ 90 በመቶ በወደቦቿ ብንጠቀም ደስታዋ ነው፣ ሱዳንም እንዲሁ፡፡ ሁሉም አገሮች የኢኮኖሚ ጥቅማቸውን ከፍ ማድረግ ነው የሚፈልጉት፡፡ ሶማሌላንድም 90 በመቶ በዚያ በኩል ብናደርግ ደስ ነው የሚላት፡፡ ሌሎችም አገሮች እንደዚህ ዓይነት ፍላጎት ይኖረዋል፡፡ ዋናው ጉዳይ የኢኮኖሚ ጥቅማቸውን ማሳደግ ስለሆነ አሁን ኢትዮጵያ ከምትከተለው መርህ አንፃር የተጣጣመ፣ የኢኮኖሚ ዕድገት ለማምጣትና ከተያዘው ዕቅድ አንፃር በቀጣናው ትስስር ከመፍጠር አንፃር ሊታይ ይችላል፡፡ ቀጣናዊ ትስስርና ውህደት አንዱ በመሠረተ ልማት ነው የሚገለጸው፡፡ የመንገድ፣ የኤሌክትሪክ ኃይልና የወደብ አገልግሎት እነዚህ ሁሉ ቀጣናዊ ትስስሩን የሚያፋጥኑ ነገሮች ናቸውና ከዚህ አንፃር መታየት ይችላሉ፡፡

ስለዚህ ይኼ የኢኮኖሚ ትስስሩ መጨረሻ ላይ ሁሉን አቀፍ ወደ ሆነ ፖለቲካዊ ትስስር ነው የሚሄደው፡፡ የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት (ኢጋድ) ካስቀመጠው መርህ አንፃርም አንዱ አቅጣጫ ነው፡፡ የአፍሪካ ኅብረት ለ2063 ካስቀመጠው መርህ አንፃርም ኢትዮጵያ እየሄደችበት ያለው አቅጣጫ ከዚያ ጋር ተያይዞ ሊታይ የሚችል ነው፡፡ በዋናነት በቀጣናው ሰላም ማምጣት፣ ልማት ማምጣት፣ ሁሉን አቀፍ ተጠቃሚነትና ፍትሐዊ የሆነ የሀብት  አጠቃቀም አዝማሚያ አቅጣጫ መገለጫ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ ኢትዮጵያ ሱዳን ላይም ላትቆም ትችላለች፡፡ ሞምባሳ ልትሄድ ትችላለች፡፡ ወደ በርበራም ልትሄድ ትችላለች፡፡ በሶማሊያ ካሉ በርካታ ወደቦች ወደ አንዱ መሄድ ትችላለች፡፡ ይኼ በሱዳን ብቻ የሚገታ አይሆንም፡፡ በጂቡቲ ወደብም የሚገታ አይደለም፡፡ ሁኔታዎች የሚቀየሩ ከሆነ ደግሞ የአሰብ ወደብን የማንጠቀምበት ምክንያት የለም፡፡ ከሁሉም አገሮች ጋር ጤናማ የሆነ ግንኙነት የመፍጠር አዝማሚያ ወይም ሰላምንና ብልፅግናን የማረጋገጥ አቅጣጫ ስለሆነ፣ ያንን የመመንዘርና የመተግበር አካሄድ አድርጌ ነው የምወስደው፡፡

ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ ፊቷን ወደ ሱዳን ማዞሯ ተገዳ ነው የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ በተለይ በዓባይ ዲፕሎማሲ ሱዳን ከኢትዮጵያ ጎን እንድትቆም ለማግባባት ነው የሚባለው ይህንን እንዴት ነው የሚያዩት?

አቶ አበበ፡- ይኼ አመለካከት ሊኖር ይችላል፡፡ ኢትዮጵያ ፖርት ሱዳንን መጠቀም ሳትጀምር ነው እኮ ከሱዳን ጋር በዓባይ ጉዳይ ላይ አንድ ዓይነት አቋም የያዘችው፡፡ በእርግጥ አሁን የተጀመረው የበለጠ መተማመኑን ያጠናክረዋል እንጂ ኢትዮጵያን ሊያስገድድ የሚችል ነገር የለም፡፡ ቅድም እንዳልኩህ ያለውን ሀብት በፍትሐዊ አጠቃቀም ላይ ለመመርኮዝ ነው፡፡ የዓባይ ውኃ ፍትሐዊ አጠቃቀም ስንል ዓባይ ተፋሰስ ውስጥ ወደ አሥር አገሮች አሉ፡፡ ሁሉም አገሮች የራሳቸውን ድርሻ እንዲጫወቱ የማድረግ ነው፡፡ እኛ ደግሞ የሌለንን ነገር ነው የጠየቅናት፡፡ ይኼ የኃይል አቅርቦቱ ወይም ደግሞ የህዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያ ብቻ አይደለም፡፡ ለሁሉም ጎረቤት አገሮች የሚከፋፈል ሀብት ነው፡፡ ለዚህም ነው ካምፓላ ላይ የተደረሰው ስምምነት ሁሉም አገሮች ያላቸውን ተፈጥሮ ሀብት ፍትሐዊ በሆነ መንገድ መጠቀም አለባቸው የሚለው፡፡ ስለዚህ ግድቡ ለኢትዮጵያ ብቻ አይደለም ለሱዳንም፣ ለግብፅም፣ ለሌሎችም አገሮች ጠቃሚ ስለሚሆን እየተሄደበት ነው፡፡ በሌላ በኩል ሱዳን ያላት ሀብት ወደብ ነው፡፡ ይኼ ወደብ ለኢትዮጵያ አገልግሎት መስጠት፣ ኢትዮጵያ ደግሞ ፍላጎቷ የወደብ አገልግሎት ከጎረቤት አገሮች ማግኘት ነው፡፡ አሁን በወቅቱ በሱዳን የተመቻቸው ሁኔታ እንጂ ኢትዮጵያን ሊያስገድድ የሚችል ሁኔታ አይደለም፡፡ ሁለቱም ተማምነውበት የሚሄዱበት ስለሆነ ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን ካርቱም ውስጥ የደረሱበት ስምምነትም አንዳችን የሌላችን ጉዳት ሳንፈልግ ያለንን ፀጋ በእኩል ደረጃ እንጠቀማለን ከሚለው አስተሳሰብ የመነጨ ነው፡፡ 

ሪፖርተር፡- በቀደሙት ጊዜያት ኢትዮጵያና ሱዳን የሚለያዩባቸው ጉዳዮች እንደነበሩ ይታወቃል፡፡ ከህዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ ደግሞ ሱዳን የተለሳለሰ አቋሟን ለኢትዮጵያ እያሳየች ትገኛለች፡፡ ከዚህ አንፃር በዓባይ ዲፕሎማሲ፣ በተለይም የህዳሴ ግድቡ ዕውን እንዲሆን ሱዳን ቁልፍ አገር ነች ብሎ መቀበል ይቻላል?

አቶ አበበ፡- በህዳሴ ግድቡ ሱዳን ብቻዋን ወሳኝ ወይም ቁልፍ አገር ልትሆን የምትችልበት አይደለም፡፡ አሁን ያለው ማዕቀፍ የሚያመላክተው ኢትዮጵያም ብቻዋን ወሳኝ አይደለችም፡፡ ሁሉም የተፋሰስ አገሮች እኩል ሚና እንዲኖራቸው ነው የሚፈለገው፡፡ ቀደም ሲል የነበረው እ.ኤ.አ. የ1959 እና የ1929 ስምምነት ግብፅን ወሳኝ አገር አድርጎ ነው ያስቀመጠው፡፡ ካምፓላ ላይ እ.ኤ.አ. በ2010 የተደረሰው ስምምነት ነው ያንን የቀየረው፡፡ ስለዚህ ማንም አገር ብቻውን ወሳኝ እንዳይሆን የሚያደርግ ነገር ነው አዲሱ ስምምነት፡፡ ይህንንም ተከትሎ ኢትዮጵያ፣ ሩዋንዳና ታንዛኒያ በአገራቸው ሕገ መንግሥት መሠረት አፅድቀዋል፡፡፡ ስለዚህ ሱዳን ቀደም ሲል የያዘችውን አቋም ቀይራ የህዳሴ ግድቡ አካል ሆናለች፡፡ የኢትዮጵያን አቋም ማራመድ ጀምራለች፡፡ የሚባለው ነገር ለሁሉም በሚጠቅም መንገድ የተሄደበት ነው እንጂ፣ በተባለው አይደለም መታየት ያለበት፡፡

ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ በተናጠል ከምታደርገው የኢኮኖሚ ግንኙነት ይልቅ በጋራ መርህ ላይ ያተኮረ ፖሊሲ የምትከተል አገር መሆኗ ነው የሚገለጸው፡፡ ነገር ግን ሌሎች አገሮች ከዚህ ጋር በተያያዘ የተለያዩ ስሜቶችን ሲያሳዩ ተስተውሏል፡፡ ለምሳሌ ኢትዮጵያ ወደ ፖርት ሱዳን ስትሄድ ጂቡቲ ኢትዮጵያ አሳንሳ እንዳየቻት ልታስብ ትችላለች ይባላል፡፡ ይህ ፖሊሲ ትክክል ነው ብለው ያስባሉ? የህዳሴ ግድቡን ዕውን ከማድረግ አኳያ ተግዳሮቶች ሊኖሩት አይችልም?

አቶ አበበ፡- ቅድም እንደጠቀስኩት ሁሉም አገሮች ወደብ ለኢትዮጵያ በበቂ ሁኔታ ማቅረብ የሚችሉ ናቸው፡፡ አሁን ጥያቄው ማን ነው ኢትዮጵያ በምትፈልገው ፍጥነት የተሻለ የወደብ አገልግሎት ለመስጠት ራሱን ያዘጋጀ የሚለው ነው፡፡ አጋጣሚ ሆኖ ጂቡቲ ቀዳሚ ሆና ተገኝታለች፡፡ ጂቡቲ ያለው የወደብ አገልግሎት ከጊዜ ወደ ጊዜ  እየተሻሻለ ቢመጣም የራሱ ችግሮች አሉት፡፡ ከጂቡቲ ተነስተህ ወደ ሰሜን ኢትዮጵያ ከመሄድ፣ ከሰሜን ኢትዮጵያ አካባቢ በተለይ ትግራይ፣ ጎንደርና አማራ አካባቢ ላለው ከሰሜን በተለይም ከፖርት ሱዳን መነሳቱ ተነፃፃሪ የሆነ ጠቀሜታ አለው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ከጂቡቲ ተነስተህ ሰሜን ኢትዮጵያ ጎንደር ድረስ ለመሄድ የምታወጣው የነዳጅ ወጪ ተነፃፃሪ ጠቀሜታ ነው፡፡ በተለይም በተወሰነው ምዕራብ ክፍል ከጂቡቲ ተነስተህ በቀላል ልትደርስ ትችላለህ፡፡ እንደዚህም ወደፊት ነገሮች የሚቀየሩ ከሆነ አሰብ ነው፡፡ የመጨረሻው ለኢትዮጵያ ቅርብ የሚባለው አሰብ ነው፡፡ ከአዲስ አበባ በ650 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ነው ያለው፡፡ ከዚያ ቀጥሎ ጂቡቲ ነች፡፡ 910 ኪሎ ሜትር ነው፡፡ ከዚያ ቀጥሎ በረበራ ነው፣ ሶማሌላንድ 930 ኪሎ ሜትር፣ ከዚያ ቀጥሎ ፖርት ሱዳን ነው፡፡ ከዚያ ቀጥሎ ሞቃዲሾ አለ፡፡ ከዚያ ሞምባሳ ወደብ፡፡ ይህ እንግዲህ ከአዲስ አበባ ከተነሳ ነው፡፡ በቅርብ ካሉ ክልሎች ብንነሳ ደግሞ ቅርብ ናቸው፡፡ አንደኛ እዚያ አካባቢ ያለውን የሀብት ብክነትም ትቀንሳህ፡፡ ለጎረቤት ቀጣናዊ ትስስርም የራሱን አስተዋጽኦ ያበረክታል፡፡ ሁለተኛ የሀብት ብክነቱንም ይቀንሳል፡፡ ስለዚህ ከኢኮኖሚ ጠቀሜታው አንፃር ነው መታየት ያለበት፡፡    

ሪፖርተር፡- በቀይ ባህር አካባቢ ከኢኮኖሚያዊ ትስስሩ ይልቅ ፖለቲካዊ ፋይዳው እያየለ የመጣ ነው የሚመስለው፡፡ ለምሳሌ ሳዑዲ ዓረቢያና ግብፅ በተደጋጋሚ ጊዜ በወደብ ስም ፊታቸውን ወደ ኤርትራ ሲያዞሩ ይስተዋላል፡፡ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ደግሞ ወደ በርበራና ሌሎች አካባቢዎች እየተሳበች ነው፡፡ ኢትዮጵያ ደግሞ በአሁኑ ጊዜ ከጂቡቲ ወደ ሱዳንና ሶማሌላንድ እየሄደች ነው፡፡ ስለዚህ በተለይ በቀይ ባህርና በመካከለኛው ምሥራቅ አካባቢ የአገሮች በወደብ ስም መምጣት ከኢኮኖሚያዊ ፋይዳው በተለየ ሌላ ፖለቲካዊ አንድምታ የለውም ብለው ያስባሉ?

አቶ አበበ፡- እንግዲህ አሁን የተፈጠረውን ከዓለም ሥርዓት አንፃር ሰፋ አድርገን ነው ማየት ያለብን፡፡ አጥብበን ከመካከለኛው ምሥራቅ ፖለቲካ አንፃር ካየነው ትንሽ ሥዕሉን ሊያዛባብን ይችላል፡፡ የዓለም ሥርዓት በተለያየ ጊዜያት ሲቀያየር ነው የነበረው፡፡ እስከ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማብቂያ ድረስ የነበረው የዓለም ሥርዓት ‹‹ባላንስ ኦፍ ፓወር›› በሚባለው ነው ሲመራ የነበረው፡፡ አውሮፓውያን ለረዥም ጊዜ ጦርነት ውስጥ ቆይተው ከዚያ በጦርነት የተጎዱ አገሮችን፣ አንዱ ሌላውን እንዳያጠቃና እንዳይጎዳ በማለት ነው ስምምነት የደረሱት፡፡ ማጣጣም ወይም ተስማምቶ መኖር ማለት ነው፡፡ ያንን የቀየረው ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ በተለይም እ.ኤ.አ. ከ1945 በኋላ የመጣው ቀዝቃዛው የዓለም ጦርነት የሚባለው ሥርዓት ነው፡፡ ይኼ ቀዝቃዛው የዓለም ጦርነት በምዕራቡና በምሥራቁ ጎራ በሁለት የዓለም ኃያላን መንግሥታት መካከል የነበረ ነው፡፡ እ.ኤ.አ. ከ1990 በኋላ ዓለም ይመራ የነበረው ደግሞ ግሎባላይዜሽን የሚባለው አስተሳሰብ ነው፡፡ ይኼን አስተሳሰብ ያመጣው ነገር ቢኖር ዓለም ወደ አንድ መንደር ተቀይራለች፡፡ ዓለምን የሚገዛው የዴሞክራሲና የኢኮኖሚ ትስስር ነው በሚል አስተሳሰብ ተተካ፡፡ 

እ.ኤ.አ. ከ2011 በኋላ በመካከለኛው ምሥራቅ ሌላ ፖለቲካ ተፈጠረ፡፡ በዚህ ጊዜ በአብዛኛው የኤምሬቶችንና የሼኮችን (የዓረብ ንጉሦችን) የሚገዳደር ሆነ፡፡ በተለይ ቱኒዚያ ላይ የተጀመረው የሥራ አጦች ጥያቄ፣ የፍትሕ ጥያቄ፣ በአጠቃላይ የአገዛዝ ጥያቄ፣ ከዚያ ተነስቶ ሥርዓት ቀየረ፡፡ ግብፅ ተሻገረ ሥርዓት ቀየረ፡፡ መካከለኛው ምሥራቅን አመሳት፡፡ ከዚያ በኋላ የእነዚህ ኤምሬቶችና የመካከለኛው ምሥራቅ ንጉሦች ሥርዓታቸውን ለማቆየት ሌላ ዘዴ ፈየዱ፡፡ የአገዛዝ ሥርዓቶቹ ጥያቄዎችን ወደ ማፈን ውስጥ ገቡ፡፡ ይህ ማፈን ወደ ጎራ መለያየት ወሰዳቸው፡፡ ጎራው ደግሞ አንዱ ሌላውን በልጦ ለመገኘት ሩጫ ሆነ፡፡ ይህን ክፍተት የፈጠረው አሜሪካ ቀድሞ የነበራትን ሚና መቀነሷና ሌሎችም፣ እነ ቻይናና ሩሲያ ወደ ዓለም ፖለቲካ ሥርዓት ውስጥ መቀላቀላቸው ነው፡፡ ይህም አሜሪካ በመካከለኛው ምሥራቅ አካባቢ ያላትን ሚና እንድትቀንስ አደረገ፡፡ በሌላ በኩል በመካከለኛው ምሥራቅ የተፈጠረው በኢራቅና በአካባቢው የተፈጠረው ቀውስ የባህር ላይ ወንብድና እንዲስፋፋ አደረገ፡፡ ሽብር በጣም እንዲስፋፋ አደረገ፡፡ ይህንንም ተከትሎ መንግሥታት በተለይም ቀይ ባህርንና በህንድ ውቅያኖስ አካባቢ ያላቸው ገንዘብ ለብክነት ተዳረገ፡፡ ይህንን ለመከላከል ትብብር ወሳኝ መሆኑን ሁሉም አመኑ፡፡

በተለይ በሳዑዲ ዓረቢያና በአካባቢዋ እነ ኳታር፣ ኢራንና ሌሎችም አካባቢዎች ያለው ሁኔታ መልኩን እየቀየረ መጣና ወደ እርስ በርስ ሽኩቻ ወሰደው፡፡ እነዚህ ነገሮች ተደማምረው የመካከለኛው ምሥራቅ ፖለቲካ ውጥንቅጡ እንዲወጣ ሆነ፡፡ ከዚያ አይኤስኤስ የሚባለው ተፈጠረ፡፡ በመጨረሻ የየመን ጦርነት መጣ፡፡ በዚህ ጦርነት የቪዓና የሱኒ ጦርነት ግልጽ ብሎ ወጣ፡፡ ግልጽ ብሎ ሲወጣ 34 የሱኒ እምነት ተከታዮች በሳዑዲ ዓረቢያ ጋሻ ጃግሬነት አንድ ኅብረት ፈጠሩ፡፡ መሀል ሠፋሪዎቹ እንደተጠበቁ ሆኖ ሌሎች በሌላ ጎራ ቆሙ፡፡ ሳዑዲ ዓረቢያ ለህልውናዋ በጣም አሥጊ ስለነበር ሱኒዎችን አሰባሰበችና የመን ላይ ያለውን መዋጋት ፈለገች፡፡ ለዚህም ለሳዑዲ ዓረቢያ አመቺ ሆኖ የተገኘው ቦታ አሰብ ሆነ፡፡ በአሰብ ወታደራዊ ቤዝ ለማቋቋም ኤርትራ ወደቧን ሰጠች፡፡ በዚህ ምክንያት ጂኦፖለቲካ ፍላጎቱ እየጨመረ መጣ፡፡ ይኼንን በአንድ በኩል የምታየው ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ጂቡቲ ላይ ያለውን ኃይል ታያለህ፡፡ ጂቡቲ ለመጀመርያ ጊዜ ቻይና ወታደራዊ ቤዝ ስታቋቁም፣ ጃፓን እንደዚሁ አቋቋመች፡፡ ሩሲያ እንደዚሁ ፍላጎት እያሳየች ነው፡፡ አሜሪካ አላት፡፡ አውሮፓ አለው፡፡ እዚያ የሌለው አገር የለም፡፡ ሁሉም አገሮች በተለይ የባብኤል መንደብ የሚባለውን መስመር ለመቆጣጠር ውድድር ውስጥ ገቡ፡፡ ይህንን ለማስታገስ ፖለቲካዊ ወሳኝ ሚና ያላቸው መንግሥታት አልነበሩም፡፡ ከመንግሥት ባሻገር "ነን ስቴት አክተር" የሚባሉ ናቸው ፖለቲካው ላይ ሚና የነበራቸው፡፡ ይህ "ነን ስቴት አክተር" የሚባለው ወደ ሽብርተኝነትና መንግሥት በኃይል የመገልበጥ እንቅስቃሴ ውስጥ ሲገባ፣ መንግሥታት ህልውናቸውን ለማስጠበቅ ሚና ውስጥ በመግባት ስትራቴጂካዊ ቦታዎችን በመያዝ መከላከል ወደሚለው መጡ፡፡ አንዱም ስትራቴጂካዊ ቦታዎች ላይ የመሮጡ ጉዳይ የውስጥ ችግርን ውጫዊ ለማድረግ ይጠቅማቸዋል፡፡ ሁለተኛው ይህን የውስጥ ፖለቲካ ለራሳቸው ይጠቀሙና የውጭ ኃይሎችን ለማዳከም፣ ጠላት የሆነውን ለመደምሰስም እንደ መጠቀሚያ ሥልት ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ቀይ ባህርና ህንድ ውቅያኖስ አካባቢ ያለው አሠላለፍ ሌላ ገጽታ እየያዘ መጣ፡፡ ጂቡቲ በኩል ያለው አሠላለፍ ሌላ ነው፡፡ በቀይ ባህር በኩል ያለው አሠላለፍ ሌላ ነው፡፡

ስለዚህ ኤርትራ ለዚህ ሁሉ መጫወቻ ሜዳ አመቻቸች ማለት ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ነው አሁን ያለው የዓለም ሥርዓት እየተቀየረ ያለው፡፡ በዚህ መሠረት በአፍሪካ ቀንድና በኢጋድ አባላት አገሮች መካከል ያለው የፖለቲካ ሥርዓት "መርካንታይል ቢዝነስ" የሚባለው ዓይነት ቅርፅ እየያዘ መጣ፡፡ ፖለቲካውን በገንዘብ ነው የምትሠራው፡፡ ለአገር ጥቅም ሳይሆን ለፖለቲካ ጥቅም፡፡ ለምሳሌ የሶማሊያን ምርጫ ውሰድ፡፡ በዚህ ምርጫ ሳዑዲ ዓረቢያ 80 ሺሕ ዶላር ለፎርማጆ (አዲሱ የሶማሊያ ፕሬዚዳንት) አቀረበች፡፡ ሌላው ቀደም ሲል የነበራት ፕሬዚዳንትም በራሳቸው ሲደገፉ ነበር፡፡ ደቡብ ሱዳን ውስጥ ያለውም ሁኔታ ይኼው ነው፡፡ ኤርትራ የአሰብ ወደብን ለዓረቦች ስትሰጥ የምታገኘው ገንዘብ፣ ዓረቦች እዚያ አካባቢ ከመጡ አንድም የኃይል ሚዛኑን ለማየት ነው፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያ እዚህ ጋ አለች፡፡ አንዱ እሱ ነው፡፡ ሁለተኛው ኤርትራ ለዓረቦቹ ያንን ነገር ስትሰጥ ኤ.ኤ.አ. ከ2009 ጀምሮ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የጣለባት ማዕቀብ አለ፡፡ በዚህ ምክንያት ኢኮኖሚዋ በከፍተኛ ደረጃ ተጎድቷል፡፡ ዋና ተዋናዮች አሉ፡፡ መካከለኞች አሉ፡፡ አሻንጉሊቶች አሉ፡፡ የእነዚህ ድምር ውጤት ነው በዚህ በቀይ ባህር አካባቢ ያለውን የፖለቲካ ሁኔታ የሚያሳየው፡፡   

ሪፖርተር፡- በዚህ ሁሉ አሠላለፍ ውስጥ የኢትዮጵያ ሚና ምንድነው መሆን ያለበት?

አቶ አበበ፡- ኢትዮጵያ መጀመርያ የቤት ሥራዋን ነው መሥራት ያለባት፡፡ እንግዲህ ኢትዮጵያ ውስጥ ሁሉንም እኩል የሚያደርግ ሥርዓት ነው የተፈጠረው፡፡ የዚህ ዋነኛ ማጠንጠኛ ሕገ መንግሥቱ ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱን የመተርጎም ክፍተቶች እዚያም እዚህም ይገኛሉ፡፡ በቅርቡ የተከሰቱ ጥያቄዎች ሕገ መንግሥቱን በትክክል ወደ መሬት ካለማውረድ ጋር የተያያዙ ነገሮች ናቸው፡፡ ሕገ መንግሥቱን የመረዳትና ያለውን ጠባይ በሚገባ ከመረዳት ተያይዞ የሚመጡ ነገሮች ናቸው፡፡ ሕገ መንግሥቱ ላይ የተቀመጡ ነገሮች በትክክል ወደ መሬት ሲወርዱ ሁሉም ችግሮች ይፈታሉ፡፡ ለዚህ ሁሉም ሰው ለሕገ መንግሥቱ ያለውን ግንዛቤና ዕውቀት ከፍ ማድረግ አለበት፡፡ ሕገ መንግሥቱም በትክክል መተርጎም መቻል አለበት፡፡

ሁለተኛው ከሕገ መንግሥቱ ቀጥሎ እያንዳንዱ ሰውና መንግሥት መሥራት የሚገባው የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነትና አገራዊ ደኅንነት ፖሊሲው ላይ ነው፡፡ ከሕገ መንግሥቱ ቀጥሎ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ፣ እያንዳንዱ ባለድርሻ አካል በዚህ ላይ ግልጽ የሆነ ግንዛቤና መረዳት ሊኖረው ይገባል፡፡ የኢትዮጵያ ህልውና የሚወሰነው ኢትዮጵያ ከሌሎች ጋር በምታደርገው ግንኙነት ነው፡፡ ሁል ጊዜ ለዘመናት ኢትዮጵያ ጠላቶቿ ከውጭ ሲመጡ የነበሩት የውስጥ ችግሮቿን በአግባቡ ማስተናገድ ባለመቻሏ ነው፡፡ የውጭ ፖሊሲ ማለት ደግሞ ያለህን ነገር ወይም ፍላጎት ለሌላው የምትገልጽበት መንገድ ነው፡፡ ሌላው ዓለም አንተን የሚያይበት መነጽር ነው፡፡  የምትከተለው የውጭ ፖሊሲ የአንድን አገር ግንኙነት ጥንካሬና ጉድለት የሚያሳይ ነው፡፡ ስለዚህ እያንዳንዱ ሰው ተገቢውን ሥራ መሥራት አለበት፡፡ በሦስተኛ ደረጃ ኢትዮጵያ ሁልጊዜ ራሷን ለመከላከል አቋሟን ጠንካራ ማድረግ አለባት፡፡ የተጋላጭነት ደረጃዋን እጅግ ዝቅ ማድረግ አለባት፡፡ በታሪክ አጋጣሚ ሁሉንም ኢትዮጵያ ላይ የተቃጡ ጦርነቶች ስታይ፣ ሁልጊዜ ኢትዮጵያ ያላትን ድክመቶች እየተጠቀሙ ነው የተከፈቱት፡፡ በአራተኛ ደረጃ አሁን የተፈጠረው የፖለቲካ ሁኔታ መሠረት እንዲይዝ የፀረ ሙስና ትግሉ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት፡፡ የሙስና ትግሉ ፈታኝ ነው፡፡ በአንድ ጊዜ ሊፈታ አይችልም፡፡ በመንግሥት በኩል ያለው ክፍተት በአገሪቱ ሙስና ችግር እንዲሆን አድርጓታል፡፡

በአምስተኛ ደረጃ ኢትዮጵያ እስከ ዛሬ ድረስ ስትከተለው የነበረው በውስጥ ጉዳይ ላይ ማተኮር ነው፡፡ ኢትዮጵያ በውስጥ ጉዳይዋ ላይ ትኩረት ካደረገች፣ በልማትና በዴሞክራሲ ጉዳይ ላይ ትኩረት ካደረገች፣ ኢኮኖሚዋን ካበለፀገችና ካሳደገች ለጎረቤቶቿ መልካም የገበያ ዕድል ይፈጠራል፡፡ የኢኮኖሚ ትስስር ይኖራል፡፡ የሥራ ዕድል ይፈጠራል፡፡ ሌሎች ጎረቤት አገሮችም ከዚህ ትሩፋት ተጠቃሚ ይሆናሉ ከሚል አስተሳሰብ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ትልቅ አገር ነች፡፡ መቶ ሚሊዮን የሚደርስ ሕዝብ ያላት በመሆኗ፣ በአፍሪካ ውስጥ ጠንካራ የሚባል መከላከያ ያላት በመሆኗ፣ በዲፕሎማሲውም ረገድ በዓለም ታሪክ ጠንካራ ዲፕሎማሲ የገነባች ከመሆኗ አንፃር፣ እነዚህ ሁሉ ተደምረው ሥጋት ላይ አይጥላትም፡፡ አሁን ባለው የዓለም ሥርዓትና በመካከለኛው ምሥራቅ ያለውን ሁኔታ ስናይ ጎረቤት አገሮች ፈልገው አይደለም ለዚህ እየተጋለጡ ያሉት፡፡ ጎረቤት አገሮች ይሁን ብለው የኢትዮጵያን ጥቅም ለመንካት ፈልገው አይደለም፡፡ ከእነሱ ቁጥጥር ውጪ ፖለቲካው ወደነሱ እየመጣ ነው፡፡ ከዚህ መልካም አጋጣሚ ለመጠቀም የሚያደርጉት ጥረት ነው፡፡ 34 የሙስሊም አባል አገሮች ኅብረት ሲመሠረት የኢጋድ አባል የነበሩት ሱዳን፣ ጂቡቲና ሶማሊያ በአንድ ቃል ነው በሳዑዲ ዓረቢያ ለሚመራው ኅብረት ድጋፋቸውን የገለጹት፡፡ የተቀሩት አገሮች ሃይማኖታዊ ጉዳይ ስላለ ብዙም አልተሳቡም፡፡ በመካከለኛው ምሥራቅ የሚከሰት ማንኛውም ነገር ኢትዮጵያን ይነካል፡፡ በአፍሪካ ቀንድ ያሉ አገሮችን በሙሉ ይነካል፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያ ማድረግ ያለባት አሁን ባለው አሠላለፍ ከውስጥ ጉዳይዋ እኩል ለውጭ ግንኙነቷም ትኩረት መስጠት ነው፡፡ ሁልጊዜ ኢትዮጵያ ተንኳሽ አይደለችም፡፡ ሁልጊዜ ኢትዮጵያ የሰላም ደሴት ነች ብለን በመናገር ኢትዮጵያን ከማንኛውም ከሚመጣው ነገር ማዳን አይቻልም፡፡ ተዘጋጅቶ መጠበቅ ያስፈልጋል፡፡ ከተቻለም መውሰድ ያለባቸውን ጉዳዮች አስቦ ስተራቴጂካዊ በሆነ መንገድ ቀድሞ ተዘጋጅቶ ዕርምጃ መወሰድ አለባት፡፡ የውጭ ፖሊሲው በተወሰነ ደረጃ መሻሻል አለበት፡፡       

ሪፖርተር፡- ከዚህ ወቅታዊ ትኩሳት አንፃር ኢትዮጵያ ጂቡቲ ላይ ወታደራዊ ቤዝ ሊኖራት ይገባል የሚሉ አሉ፡፡ እርስዎ በዚህ ይስማማሉ?

አቶ አበበ፡- ኢትዮጵያ በጂቡቲ ወታደራዊ ቤዝ ቢኖራት ደስ ይለኛል፡፡ ያስፈልጋታልም፡፡ ኢትዮጵያ በቀጣናው ውስጥ ካላት ሚና አንፃር፣ እንደ ሌሎቹ አገሮች ራሱን የቻለ ባህር ኃይል ከሌሎች አገሮች ቀድመን የነበረን ነን፡፡

ሪፖርተር፡- ወደ ጂቡቲና ሱዳን ልመልስዎትና ባለፈው ሳምንት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ወደ ሱዳን ሄደው ነበር፡፡ በቆይታቸውም ለሱዳኑ ፕሬዚዳንት ኢትዮጵያ 50 በመቶ ገቢ ንግዷን በፖርት ሱዳን ለመጠቀም ፍላጎት እንዳላት ፍላጎታቸውን እንደገለጹላቸው ሲነገር ነበር፡፡ ከዚህ አንፃር ጂቡቲ ምን ዓይነት ስሜት ሊያሳድርባት ይችላል ብለው ያስባሉ?

አቶ አበበ፡- ሁለቱም አገሮች የወደብ አገልግሎት አቅራቢ ናቸው፡፡ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ፖርት ሱዳን 20 በመቶ የሚሆነው ነበር የሚሸፍነው፡፡ አሁን ካለው ከአገልግሎትና ስትራቴጂ በተለይ ለሰሜን ኢትዮጵያ ካለው ቅርበት አንፃር ይህንን መጠን ከፍ ማድረጉ ክፋት የለውም፡፡ ግን ጂቡቲን ደስ ላይላት ይችላል የሚባለው አይገባም፡፡ ጂቡቲ ሉዓሏዊ አገር ነች፡፡ ኢትዮጵያም ነፃ ፍላጎት ያላት አገር ነች፡፡ በአጠቃላይ ከጎረቤት አገሮች ጋር የምታደርገው ግንኙነት በኢጋድ ማዕቀፍ መታየት አለበት፡፡ ጂቡቲ ውስጥ የሚበላውና የሚጠጣው ሁሉ የሚቀርበው ከኢትዮጵያ ነው፡፡ በእርግጥ የኢትዮጵያ መንግሥት ከጂቡቲ መንግሥትና ሕዝብ ጋር ሳይመካከርበት እንደዚህ ዓይነት ውሳኔ ላይ የደረሰ አይመስለኝም፡፡

ሪፖርተር፡- የግብፅ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ ከሳምንት በፊት ወደ ሩዋንዳና ታንዛኒያ ጉብኝት አድርገው ነበር፡፡ እነዚህ አገሮች ደግሞ ሁሉን አቀፍ የናይል የትብብር ማዕቀፍ (ሲኤፍኤ) የፈረሙ አገሮች ናቸው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ወደ ሱዳን ሄደው ነበር፡፡ ይህ የሁለቱ አገሮች መሪዎች ጉብኝት የተካሄደው በአንድ ሳምንት ውስጥ ነው፡፡ በእነዚህ አገሮች እነዚህ መሪዎች ጉብኝት የማድረግ ፖለቲካዊ አንድምታ ምንድነው?

አቶ አበበ፡- ግብፅ ለብዙ ጊዜ ከኢንቬቲቩ ራሷን አግልላ ቆይታ ባለፈው ሩዋንዳ በተካሄደው ስብሰባ ነው እመለሳለሁ ብላ ድምጿን የሰጠችው፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በተለያዩ መድረኮች የመቀራረቡና ጉዳዩን የማጤን ሁኔታ እየተስተዋለባት ነው፡፡ ይህ ማለት ግን ግብፅ ቀድሞ የያዘችውን አቋም በቀላሉ ትቀይራለች ማለት አይደለም፡፡ ግብፅ የተቻላትን ሁሉ ማድረግ ነው የምትፈልገው፡፡ የህዳሴ ግድብን ኢትዮጵያና ሌሎቹ የተፋሰስ አገሮች ካምፓላ ላይ በደረሱት ስምምነት መሠረት የስምምነቱ መነሻ አድርጋ ኢትዮጵያ ሒደቱን እያስቀጠለች ነው ያለችው፡፡ ግብፅ ደግሞ ራሷን አግልላ የማለሳለስ ፍላጎት እያሳየች ነው ያለችው፡፡ እነዚህ አገሮች ዘንድ ስትሄድ ሌላ ምንም የተለየ ፍላጎት የላትም፡፡ በኢትዮጵያ ላይ ተፅዕኖ እንዲያደርጉ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ላይ ግፊት እንዲያደርጉ ነው፡፡

በግብፅ በየትኛውም ዘመን ወደ ሥልጣን ለሚመጣ ባለሥልጣን የሕዝብ ካርድና የሕዝብ ቅቡልነት የሚያጠናክርበት የዓባይ ጉዳይ ነው፡፡ የዓባይ ጉዳይ የሕዝቡን ድጋፍ ለማግኘትም ሆነ ለማጣት እንደ ትልቅ ካርድ የሚጠቀሙበት ስለሆነ፣ የግብፅ ሚዲያዎችና ፖለቲከኞች በየጊዜው የሚያቀርቡት ዘገባ የሕዝቡን ስሜት የሚጎዳ ነው፡፡ ይህንን ለማስታገስ የግብፅ መሪዎች የተቻላቸውን ሁሉ ይሞክራሉ፡፡ ከዚህ አንፃር ግብፅ ወደ እነዚህ አገሮች ያደረገችው ጉብኝት በዋናነት ኢትዮጵያ ላይ ተፅዕኖ እንዲያደርጉ ነው፡፡ ግብፅ የምታራምደውን አስተሳሰብ ኢትዮጵያ እንድትደግፍላት ተፅዕኖ ለመፍጠር ነው፡፡ ይኼ ደግሞ በኢትዮጵያ በኩል የማይታሰብ ነገር ነው፡፡

በሌላ በኩል ሱዳን ከተከዜ ግድብ ትልቅ ጥቅም አግኝታለች፡፡ ኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል በማመንጨቷ ሱዳን ተጠቃሚ ሆናለች፡፡ እነዚህን ነገሮች ስናይ ሱዳን በህዳሴ ግድቡ ላይ የምታስመዘግበውን ከራሷ ጥቅም አንፃር ነው እያየች ያለችው፡፡ ለዘመናት ምንም ጥቅም ስላላገኘች ሱዳን ራሷን አግልላ ቆይታለች፡፡ አሁን የአቋም ለውጥ አድርጋለች፡፡ እንዲያውም በግብፅና በኢትዮጵያ መካከል ሸምጋይ ነው የሆነችው፡፡ ግብፅ ሩጫዋን ስትጨርስ በተቀመጠው ማዕቀፍ መሠረት ወደ ንግግር መምጣቷ አይቀርም፡፡ የግብፅ ሩጫ አሁን የተያዘውን የህዳሴ ጉዞ ያደናቅፈዋል የሚል ነገር አይታይም፡፡  

ሪፖርተር፡- በሱዳን፣ በግብፅና በኢትዮጵያ መካከል ያለውን ግንኙነት እንዴት ነው የሚያዩት? በተለይ በዓባይ ወንዝ ላይ ካላቸው ፍላትና ከህዳሴ ግድቡ አንፃር?

አቶ አበበ፡- የኃይድሮ ፖለቲክስ ባለሙያ አይደለሁም፡፡ ግን ከኢኮኖሚና ከፖለቲካ አስተሳሰብ ስናይ የእነዚህ የሦስቱ አገሮች ፍላጎት የሚቀራረብበትም አለ፡፡ የሚለያይበትም አለ፡፡ የሁለቱ አገሮች ፍላጎት የሚጣጣምበትም አለ፡፡ በአብዛኛው የኢትዮጵያና የሱዳን ፍላጎት ይጣጣማል፣ ይቀራረባል፡፡ ሌላው እነዚህ አገሮች የጋራ መከላከያ ስምምነት የፈረሙ ናቸው፡፡ ስትራቴጂካዊ ግንኙነቱ ከፍ ያለ ነው፡፡ በድንበር ጉዳይ፣ በፀጥታ ጉዳይ እነዚህ አገሮች ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰ ግንኙነት አላቸው፡፡ የግብፅ ፍላጎት ከሁለቱም ይለያል፡፡ የግብፅ ፍላጎት ውኃውን አትንኩት ነው፡፡ ስለዚህ የሦስቱ አገሮች ግንኙነት በመርህ ደረጃ ካየነው ከአንድ ወንዝ የሚጠጡ ሕዝቦች ናቸው፡፡ የምንመሳሰልባቸውና የምንለያይባቸው ነገሮች አሉ፡፡ በሒደት ግን እየጠሩ ይመጣሉ፡፡ በታሪክ እነዚህ ሦስቱ አገሮች በአንድ ወንበር ላይ የተነጋገሩበት አጋጣሚ የለም፡፡ አሁን ግን ተቀራርበው የመነጋገር ባህል አዳብረዋል፡፡ የናይል ፖለቲካ ጉዳይ ለዘመናት የቆየ በመሆኑ በአንድ ሌሊት ተፈትቶ ግብፅ ወደ ኢትዮጵያ ጉንጉን አበባ ይዛ ትመጣለች ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው፡፡