Skip to main content
x

‹‹የኢትዮጵያ ሕዳሴ የሱዳንም ሕዳሴ ነው፡፡ የሱዳንም እንደዚሁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ነው፡፡››

    የሱዳን ፕሬዚዳንት ኦማር ሐሰን አልበሽር፣ 12ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በአፋር ክልል ሲከበር ከተናገሩት የተወሰደ፡፡ በዓሉ ‹‹በሕገ መንግሥታችን የደመቀ ህብረ ብሔራዊነታችን ለሕዳሴያችን” በሚል መሪ ቃል ኅዳር 29 ቀን 2010 ዓ.ም. በሰመራ ከተማ ሲከበር በክብር እንግድነት የተገኙት የሱዳኑ ፕሬዚዳንት አልበሽር፣ ዕለቱ የሁለቱን አገሮች ሕዝቦች ግንኙነት የምናድስበት ነው በማለት ተናግረዋል።

‹‹አክሱም ወደ አደገኛ ሁኔታ እየሄደ ነው፡፡ ልክ እንደ ስሜን ተራራ ብሔራዊ ፓርክ ለአደጋ የተጋለጠ ተብሎ ከፋይል እንዳይወጣ ያሠጋል፡፡››

የኢትዮጵያ አርኪዮሎጂ ባለሙያዎች ማኅበር ፕሬዚዳንትና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአርኪዮሎጂ ረዳት ፕሮፌሰር ተክሌ ሐጎስ፣ በዩኔስኮ የዓለም ቅርስ ሆኖ ከ37 ዓመት በፊት የተመዘገበው አክሱም ሐውልቶቹና መካነ ቅርሶቹ ለከፋ አደጋ መጋለጣቸውን በማመልከት ለሪፖርተር ከተናገሩት የተወሰደ፡፡

‹‹…ዴሞክራሲው መስፋት አለበት! የመቻቻል፣ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ፣ ከመሸማቀቅ ወጥቶ ሰው በነፃነት የሚከራከርበትና እነዚህ የመሳሰሉ ነገሮች መፍጠር አለብን ብዬ አምናለሁ፡፡››

የቀድሞው የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከል ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ በረከት ስምዖን፣ በጎንደር ከተማ በቅርቡ በተደረገው የአማራና የትግራይ የሕዝብ ለሕዝብ መድረክ ላይ የተናገሩት፡፡ አቶ በረከት በዲስኩራቸው ምሁራን በውጪ ያሉት ኢትዮጵያውያን ጭምር፣ ‹‹በመድረኩ ማሳተፍ አለብን›› ብለው የተንደረደሩት ‹‹ከዚህ ከደረስንበት ወደሚቀጥለው እንዴት ነው የምንሄደው ብለን አሳታፊ በሆነ መንገድ መመለስ አለበት›› በማለትም ነው፡፡ በቅርቡ ከመንግሥታዊ ሥልጣናቸው በፈቃዳቸው የለቀቁት አቶ በረከት፣ መንግሥት ለውጦችን አጠናክሮ መቀጠል እንደሚኖርበት፣ የተመዘገቡ ለውጦች ላይ የሚሰነዘሩ ጥቃቶችን ማስቆም አለበት ብለዋል፡፡ ‹‹ፖሊሲዎች ላይ የሚሰነዘሩትን ያልተገቡ ተፅዕኖዎችን መቋቋም የሚችል መንግሥት መሆን አለበት፡፡ በዚህ ደረጃ ብዙ ችግሮች ናቸው ያሉት፤›› በማለትም አስረግጠው ተናግረዋል፡፡

‹‹እያንዳንዱ ቤተሰብ አንድ ልጅ በጉዲፈቻ ቢያሳድግ የጎዳና ተዳዳሪነትን መቅረፍ ይቻላል፡፡››

ዩኒሴፍ ኢትዮጵያ የዓለም የሕፃናት ቀንን አስመልክቶ በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ባዘጋጀው መርሐ ግብር ብሌን ገመቹ የተባለች ታዳጊ የተናገረችው ነው፡፡ ኅዳር 11 ቀን 2010 ዓ.ም. የተካሄደው መርሐ ግብሩ የሕፃናት ፓርላማ አባላት የተለያዩ  ሚኒስትሮችን እንዲወክሉ የተደረገበት ነበር፡፡

‹‹ከኤርትራ ጋር ለረጅም ጊዜ የዘለቀ ከባድ የድንበር ጦርነትና ግጭት ተከስቶ ነበር፡፡ ይህንን ችግር ለመፍታት የአሜሪካ መንግሥት ቁርጠኛ ነው፡፡››

በኢትዮጵያ የቀድሞ የአሜሪካ አምባሳደርና በውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የአሁኑ የአፍሪካ ጉዳዮች ተጠባባቂ ምክትል ኃላፊ ዶናልድ ያማማቶ፣ ሰኞ ህዳር 4 ቀን 2010 ዓ.ም. ከዋሺንግተን ዲሲ በስልክ ከሰጡት መግለጫ የተወሰደ

‹‹አያቴ የዛሬ 50 ዓመት በረገጣት መሬት ታሪክን በመድገሜ ደስተኛ አድርጎኛል፡፡››

ኢትዮጵያን እየጎበኙ ያሉት የኖርዌይ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት አልጋ ወራሽ ልዑል ሃኮን ማገኑስ፣ ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ በብሔራዊ ቤተመንግሥት ጥቅምት 28 ቀን 2010 ዓ.ም. የክብር አቀባበል ባደረጉላቸው ጊዜ የተናገሩት፡፡

ፍሬከናፍር

«የፊልም ባለሞያዎች ዝርዝርን በአማርኛ ለመጻፍ የመረጥኩበት ምክንያት፤ አማርኛ እጅግ ጥንታዊ ከሆኑ የዓለማችን የጽሑፍ ቋንቋዎች አንዱ በመሆኑ ነው። በዓለም እንዲህ ዓይነት ቋንቋዎች ጥቂት ናቸው። ይህ ውብ ፊደላት ያሉት ቋንቋ በኢትዮጵያና በጥቂት ሰዎች በኤርትራ ይነገራል።»

‹‹የግብር ከፋዩን ገንዘብ እያነሳችሁ ማንንም መሸለም አትችሉም፡፡››

የገንብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትሩ አብርሃም ተከስተ (ዶ/ር)፣ የዩኒቨርሲቲዎችና የፌደራል ባለበጀት መሥሪያ ቤቶች ኃላፊዎችን ለሁለት ቀናት ጠርተው ባነጋገሩበት ወቅት ስለ ወጪ ቅነሳ በቀረበው መመሪያ ውስጥ ከተካተቱት አንዱ በስፖንሰርሲፕ፣ በሽልማትና በመሰል ድጋፎች መልክ የሕዝብ ገንዘብ እያነሱ መስጠት እንደማይቻል፣ እንዲህ ያለው ልማድ መቅረት እንደሚገባው ከገለጹት የተወሰደ፡፡

 

 

‹‹በማንኛውም ጊዜ የኑክሌር ጦርነት ሊጀመር ይችላል፡፡››

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የሰሜን ኮሪያ ምክትል አምባሳደር ኪም ኢን ርዩንግ፣ ለተመድ ጠቅላላ ጉባዔ የጦር መሣሪያ ቅነሳ ኮሚቴ ካደረጉት ንግግር የተወሰደ፡፡ ዋሽንግተን ፖስት ይዞት በወጣው ዘገባ መሠረት፣ ምክትል አምባሳደሩ የኮሪያ ልሳነ ምድር አጠቃላይ ሁኔታ ለኑክሌር ጦርነት መቀስቀስ ጫፍ ላይ ደርሷል ብለዋል፡፡

ድሮ እና ዘንድሮ

የመስቀል ደመራ በዓልን ለማክበር የሕንድ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ካቶሊኮስ (ርዕሰ ሊቃነጳጳሳት) አዲስ አበባ ከተገኙና ካከበሩ በኋላ ኢትዮጵያን በይፋ የጎበኙት የሕንዱ ፕሬዚዳንት ራም ናት ኮቪድ ናቸው፡፡ በሸራተን አዲስ ከፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ ጋር በመሆን የንግድ ማኅበረሰቡን አግኝተው ነበር፡፡