Skip to main content
x
በድጋሚ ያንሰራራው የኪምና የትራምፕ ውይይት ተስፋ
የሰሜን ኮሪያ የቀድሞ የስለላ ድርጅት ኃላፊ ኪም ዮንግ ቾል የሁለቱን አገሮች መሪዎች ውይይት ለማመቻቸት ወደ አሜሪካ አቅንተዋል

በድጋሚ ያንሰራራው የኪምና የትራምፕ ውይይት ተስፋ

በደቡብ ኮሪያ ዋና ተዋናይነት ተጠንስሶ ሊካሄድ እ.ኤ.አ. ለሰኔ 12 ቀን 2018 ቀነ ቀጠሮ ተይዞለት ሲንጋፖር ላይ ለመካሄድ ጫፍ ከደረሰ በኋላ ብዙዎችን ግራ በማጋባት፣ በፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ደብዳቤ እንዲሰረዝ የተደረገው የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡንና የትራምፕ ግንኙነት ለኮሪያ ልሳነ ምድር ሰላምን ለማምጣት ትልቅ ተስፋ የተጣለበት ክስተት ነበር፡፡

በምን ጉዳይ ላይ ውይይቱ ሊካሄድ እንደሚችልና የት እንደሚካሄድ ዝግጅቶች እየተደረጉ እንደሆነ በማሰብ፣ ውይይቱን ሲጠባበቁ የነበሩት የሩቅ ምሥራቅ አገሮችንም በድንጋጤ ያደረቀ ውሳኔ ነበር መሰረዙ፡፡

ውይይቱ እንዲሰረዝ ዋነኛ ምክንያት አድርገው ፕሬዚዳንት ትራምፕ ያቀረቡት ከሰሜን ኮሪያ በኩል ለግንኙነቱ የሚደረጉ ዝግጁነቶችን አስመልክቶ መለሳለሶች መታየታቸውና ከመሪዎች አስቀድሞ ሊደረግ ታቅዶ የነበረው የቅድመ ዝግጅት ስብሰባ ላይ የሰሜን ኮሪያ ተወካዮች በመቅረት፣ የአሜሪካ ልዑካን ለረዥም ሰዓታት እንዲጠብቋቸው ማድረጋቸው ነው፡፡ ሰሜን ኮሪያ ስልክ ለማንሳት እንኳን ፈቃደኛ ሳትሆን ቀርታለች ብለውም ወቅሰዋታል፡፡

በድጋሚ ያንሰራራው የኪምና የትራምፕ ውይይት ተስፋ
ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሐሳባቸውን በመለወጥ የሰሜን ኮሪያ አቻቸውን በሲንጋፖር ለማግኘት ፍላጎት አሳይተዋል

 

ከዚህ ባለፈም የሰሜን ኮሪያ የውጭ ግንኙነት ምክትል ሚኒስትሯ ኪም ኪዬ ግዋን ሰሜን ኮሪያ የመሪዎቹ ግንኙነቶች እንዲደረጉ ማንንም እንደማትለማመጥና አሜሪካ የመሪዎቹ ስብሰባ እንዳይካሄድ የምታደርግ ከሆነ፣ ሁለቱ አገሮች የኑክሌር ጦር መሣሪያ ጡንቻዎቻቸውን ለማሳየት የሚገደዱ እንደሆነ መናገራቸው ይበልጥ አሜሪካውያንን ያስቆጣ ነበር፡፡

ምክትል ሚኒስትሯ ይኼንን እንዲሉ ያስቻላቸው የአሜሪካ ምክትል ፕሬዚዳንት ማይክ ፔንስ ውይይት ፍሬ ማፍራት የማይችል ከሆነ፣ የመጨረሻው አማራጭ ሊሆን የሚችለው የጋዳፊ ሞዴል እንደሆነ መናገራቸው ነው፡፡

ይህ አንድም እ.ኤ.አ. በ2003 የቀድሞ የሊቢያ ፕሬዚዳንት ሙአመር ጋዳፊ የጦር መሣሪያቸውንና ተያያዥ ንብረቶችን ለአሜሪካ ለማስረከብ መስማማታቸውን የሚያመላክት ሲሆን፣ አንድም እ.ኤ.አ. በ2011 በኔቶ የታገዘውንና ጋዳፊን በመግደል ከሥልጣን ያስወገደው ዕርምጃ ሊሆን ይችላል ብለው የመስኩ ባለሙያዎች ትንታኔ ሲሰጡበት ነበር፡፡

ዶናልድ ትራምፕ የውይይቱን መቅረት ለማሳወቅ ራሳቸው በቃል እየተናገሩ ባስጻፉት ደብዳቤያቸው የሦስት አሜሪካውያን ከሰሜን ኮሪያ እስር መፈታት አድንቀውና ጥሩ ዕርምጃ እንደሆነ ገልጸው፣ ‹‹ለእናንተ እጅግ ጠቃሚ የሆነው ነገር ግን ለእኛ እምብዛም የማይበጀን ግንኙነት መቋረጡ በዓለም ታሪክ በአሳዛኝነቱ ይመዘገባል፡፡ እናንተ ስላላችሁ የኑክሌር አቅም ታወራላችሁ፣ የእኛ ግን እጅግ የላቀ ነው፡፡ በጥቅም ላይ እንዳይውልም የዘወትር ጸሎቴ ነው፤›› ብለው ነበር፡፡

የዚህ ስብሰባ በድንገት መሰረዝ ያስደነገጣቸው የደቡብ ኮሪያ መሪ ሙን ጃኤ ኢን፣ ከዶናልድ ትራምፕ ጋር ተስፋ ሰጪ ውይይት አድርገውና ከኑክሌር ጦር መሣሪያ ነፃ የሆነ የኮሪያ ልሳነ ምድር ለማምጣት አልመው ተመልሰው ሳለ፣ በተፈጠረው ነገር ግራ በመጋባት ከሌሊቱ ስድስት ሰዓት ሊሆን ደቂቃዎች ሲቀሩት ካቢኔያቸውን ለስብሰባ ጠርተውም ነበር፡፡ ከቢሮዋቸው የወጣውም ምስል፣ ግራ መበጋባትና በድንጋጤ የተኮማተረ ፊታቸውን ያሳይ ነበር፡፡

በድጋሚ ያንሰራራው የኪምና የትራምፕ ውይይት ተስፋ
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፒኦ በቅርቡ ኪም ጆንግ ኡንን አግኝተዋቸው ነበር

 

ዶናልድ ትራምፕ የስብሰባውን መሰረዝ የሚገልጸውን ደብዳቤ ይፋ ባደረጉበት ወቅት፣ ሰሜን ኮሪያ የኑክሌር መሞከሪያ ዋሻዎቿን ስታፈራርስ ነበር፡፡ በሥፍራው ይኼንን ለመዘገብ ከታደሙት ጋዜጠኞች አንዱ ዊል ሪፕሌይ ደብዳቤውን በሥፍራው ለነበሩት የሰሜን ኮሪያ ባለሥልጣናት ሲያነብላቸውም ድንጋጤ ፊታቸው ላይ ይነበብ እንደነበርም ተናግሯል፡፡

ኪም ጆንግ ኡንና ሌሎች የሰሜን ኮሪያ ባለሥልጣናት፣ ዶናልድ ትራምፕ የስብሰባውን መሰረዝ ቢናገሩም አገራቸው ግን ግንኙነቱ ዕውን እንዲሆን በሙሉ አቅማቸው እንደሚሠሩ ተናግረዋል፡፡ ይህም ኪም ጆንግ ኡን ከዶናልድ ትራምፕ በበለጠ ብልጥነትን ያሳዩበት ክስተት ነው፡፡

ይባስ ብለውም ዶናልድ ትራምፕ የስብሰባው መሰረዝ የጦርነት ዕድሎችን አስፍቷል ወይ ተብለው ሲጠየቁ፣ ‹‹ምን ሊፈጠር እንደሚችል የምናይ ይሆናል፤›› ሲሉ መልሰው ነበር፡፡

ይህ የሰሜን ኮሪያ ጥረት ፍሬ አፍርቶ ኖሮ በሁለቱ አገሮች መካከል በድጋሚ ውይይቶችና ንግግሮች ተጀምረው የሁለቱ መሪዎች ግንኙነት ሊካሄድ እንደሚችል ተስፋ የሚፈነጥቁ ዜናዎች ከወደ ኋይት ሀውስ እየተሰሙ ነው፡፡

ዶናልድ ትራምፕም የግንኙነቱን መሰረዝ ይፋ ባደረጉበት አንደበታቸው መልሰው፣ ስብሰባው ሊካሄድ የሚችልበት ሁኔታ ሊኖር እንደሚችልም ተናግረዋል፡፡ ሰኞ ግንቦት 20 ቀን 2010 ዓ.ም. የአሜሪካ የሥራ ኃፊዎችም ስለቀጣዩ ስብሰባ ለመወያየት ፒዮንግያንግ መግባታቸው ታውቋል፡፡ በሰሜን ኮሪያ የቀድሞ የስለላ ድርጅት ኃላፊ የሚመራ ልዑክም ወደ አሜሪካ ማቅናቱ ተሰምቷል፡፡

‹‹ሰሜን ኮሪያ እጅግ ትልቅ አቅም ያላትና አንድ ቀን ታላቅ የኢኮኖሚና የፋይናንስ አቅም ያላት አገር እንደምትሆን ከልቤ አምናለሁ፡፡ በዚህ ረገድ ከኪም ጆንግ ኡን ጋርም እንስማማለን፡፡ ይሆናልም፤›› ሲሉ ዶናልድ ትራምፕ በትዊተር ገጻቸው ላይ አስፍረው ነበር፡፡

ይህ ስብሰባ እንዲካሄድ በእጅጉ ጥረት እያደረገች የምትገኘው ሰሜን ኮሪያ፣ ሐሙስ ግንቦት 16 ቀን 2010 ዓ.ም. እና ሰኞ ግንቦት 20 ቀን 2010 ዓ.ም. ሁለት ከፍተኛ የኪም ጆንግ ኡን አማካሪዎች ስብሰባውን ያቀላጥፉ ዘንድ ወደ ሲንጋፖርና ወደ አሜሪካ ኒውዮርክ መላኳ ታውቋል፡፡

ወደ አሜሪካ ከበረሩት የኪም አማካሪ ጋር የተደረገውን ውይይት አስመልክተው በትዊተር ገጻቸው ላይ የጻፉት ዶናልድ ትራምፕ፣ ‹‹ከሰሜን ኮሪያ ጋር ለሚደረገው ውይይት ጠንካራ የሆነ የጋራ ቡድን መሥርተናል፡፡ ስለስብሰባውና ሌሎች ተጨማሪ ነገሮች ውይይቶች እየተደረጉ ነው፤›› ሲሉ አስፍረዋል፡፡

ሁለቱ አገሮች ውይይታቸውን ለማድረግ በድጋሚ መነሳሳታቸው ጨልሞ የነበረውን የኮሪያ ልሳነ ምድር ሰላምና ከኑክሌር ጦር መሣሪያ ነፃ የመሆን ተስፋ በድጋሚ እንዲያንሰራራ ዕድሉ ተመቻችቷል፡፡

በድጋሚ ያንሰራራው የኪምና የትራምፕ ውይይት ተስፋ
ሰሜን ኮሪያ በቅርቡ ካወደመቻቸው የኑክሌር መሞከሪያ ጣቢያዎች አንዱ