Skip to main content
x
‹‹ብቸኛውን ክሊኒክ ከሥራ ማገድ በአካባቢው ኅብረተሰብ ላይ የጤና ችግር ያስከትላል››

‹‹ብቸኛውን ክሊኒክ ከሥራ ማገድ በአካባቢው ኅብረተሰብ ላይ የጤና ችግር ያስከትላል››

ዶ/ር ጥላሁን ደምስ፣ የአዲስ ቪዥን ስፔሻሊቲ የውስጥ ደዌ ሕክምና

ክሊኒክ ዋና ሥራ አስኪያጅ

ዶ/ር ጥላሁን ደምስ ተወልደው ያደጉት፣ እንዲሁም የአንደኛና የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን የተከታተሉት በአማራ ክልል ብቸና ከተማ ነው፡፡ በጎንደር ኮሌጅ ኦፍ ሜዲካል ሳይንስም (ጎንደር ዩኒቨርሲቲ) በሕክምና ሳይንስ የመጀመርያ ዲግሪ ሠርተዋል፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ ጥቁር አንበሳ ሪፈራል ሆስፒታል ለሦስት ዓመታት ያህል የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስት ትምህርት ተከታትለዋል፡፡ በሥራ ዓለምም በደብረ ማርቆስ ሆስፒታል ተመድበው በሙያቸው አገልግለዋል፡፡ ሆስፒታሉን በሜዲካል ዳይሬክተርነትም መርተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በደብረ ማርቆስ ከተማ አዲስ ቪዥን ስፔሻሊቲ የውስጥ ደዌ ሕክምና ክሊኒክ በግላቸው አቋቁመው ለከተማውና ለአካባቢው ማኅበረሰብ የጤና አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ፡፡ በክሊኒኩ አገልግሎት አሰጣጥና ተያያዥ በሆኑ ጉዳዮች ዙሪያ ዶ/ር ጥላሁንን አቶ ታደሰ ገብረማርያም አነጋግሯቸዋል፡፡ 

ሪፖርተር፡- አዲስ ቪዥን ክሊኒክ መቼና እንዴት እንደተቋቋመ ቢገልጹልን?

ዶ/ር ጥላሁን፡- ክሊኒኩ የተቋቋመው በ2004 ዓ.ም. ሲሆን፣ የተቋቋመው የኢትዮጵያ የምግብ፣ መድኃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን ያወጣውን ዝቅተኛ ደረጃ አሟልቶ መገኘቱ ከተረጋገጠ በኋላ ነው፡፡ ባለሥልጣኑ ያወጣውንም ባለ አረንጓዴ የብቃት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት ተሰጥቶታል፡፡ ክሊኒኩ በደብረ ማርቆስ ሥር ለሚገኙ ወረዳዎች ከፍተኛ አገልግሎት እያበረከተ ለመሆኑ የአካባቢው ኅብረተሰብ የሚመሰክርለትና የሚመለከታቸው መንግሥታዊ ተቋማትም ምስክርነት የሚሰጡት ለመሆኑ በተለያየ ጊዜያት ከግልና ከመንግሥት የተበረከተለትን የምስክር ወረቀቶች ለማስረጃነት ማቅረብ ይቻላል፡፡  

ሪፖርተር፡- የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ጤና ጥበቃ ቢሮ በክሊኒኩ ላይ አንዳንድ አስተዳደራዊ ዕርምጃ መውሰዱ ይነገራል፡፡ ይህ ለምን ሆነ?

ዶ/ር ጥላሁን፡- የአገሪቱን የጤና ፖሊሲ መሠረት በማድረግ በርካታ የግል ጤና ተቋማት አገራዊ ስታንዳርድን (ደረጃ) መሠረት በማድረግ እንዲቋቋሙ፣ እንዲሁም ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ የፈቃድና ቁጥጥር ሥራ በቢሮው አማካይነት ለመሠራቱ ለማንም የተሰወረ አይደለም፡፡ በዚህም መሠረት የክልሉ ጤና ቢሮ ቁጥጥር ቡድን ለቁጥጥር ሥራ በወጣበት ወቅት ክሊኒኩ መታየቱ ተገምግሟል፡፡ በኢንስፔክሽንም ወቅት በክሊኒኩ ውስጥ በሥራ ብዛት ምክንያት የታለፉ ግድፈቶች ተከስተዋል፡፡ 

ሪፖርተር፡- ግድፈቶቹን ቢዘረዝሩልን?

ዶ/ር ጥላሁን፡- በተቆጣጣሪ አካሉ (ጤና ጥበቃ) ያልተመዘገቡ ወይም መረጃቸው ያልተያያዘ ባለሙያዎችን ማሠራት፣ ደረጃውን የጠበቀ የቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓት አለመተግበርና በድንገተኛ ክፍል ውስጥ የመጠቀሚያ ጊዜቸው ያለፈባቸው መድኃኒቶች መገኘት ናቸው፡፡ ከመድኃኒቶቹም መካከል የመጠቀሚያው ጊዜያቸው እ.ኤ.አ. ዲሴምበር 2017 እና ዲሴምበር 2018 ያለፈባቸው ቲታኖስ አንቲቶክሲን፣ ሃዮሲንና ፖታሲየም ክሎራይድ ኢንጄክሽንና ካልሲየም ግሉኮናት መድኃኒቶች ይገኙባቸዋል፡፡ ከዚህም ሌላ ኤችሲ ካሊበራቶር ፎርሲ ቢሲ ማሽን (የላብራቶር ሪኢጄንት) ግማሽ ሊትር የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ካለፈባቸው መካከል ተጠቃሾች ናቸው፡፡ የተገኙት የማያገለግሉ መድኃኒቶች በሚከማቹበት መደርደርያ (ሼልፍ) ላይ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ በካሽ ረጂስተር አይተም ሊስት ውስጥ አንድም የመጠቀሚያው ጊዜ ያለፈበት መድኃኒት አልተከተተም ወይም አልተያዘም፡፡   

ሪፖርተር፡- በክሊኒኩ ላይ ምን ዓይነት ዕርምጃ ነው የተወሰደው?

ዶ/ር ጥላሁን፡- ከሚያዝያ 30 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ ለሦስት ወራት ያህል ከሥራ እንዲታገድ ተደርጓል፡፡

ሪፖርተር፡- ዕገዳውን እንዴት ተቀበሉት? የተከሰቱ ግድፈቶችን ለማስተካከል ያደረጉት ጥረት ምን ይመስላል?

ዶ/ር ጥላሁን፡- የተጠቀሱት ችግሮች በሥራ ብዛት ምክንያት መከሰታቸውን ለመግለጽ እወዳለሁ፡፡ ይህ በመሆኑ ከአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ጤና ቢሮ ቁጥጥርና ኮሚቴዎች ጋር ተግባብተን ግድፈቶቹ ወዲያውኑ ታርመውና ተስተካክለው ለቢሮው ሪፖርት ተደርጓል፡፡ ይህ መሆኑ እየታወቀ ብቸኛ የሆነውን ስፔሻላይዝድ ክሊኒክ ከሥራ ማገድ በአካባቢው ኅብረተሰብ ላይ የባሰ የጤና ችግር እንዲከሰት ማድረግ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡

ሪፖርተር፡- የተወሰደውን የዕርምትና የማስተካከል ሥራ ቢያብራሩልን?

ዶ/ር ጥላሁን፡- በጤና ጥበቃ ቢሮ ያልተመዘገቡ (መረጃቸው ያልተያያዘ) ባለሙያዎችን ማሠራት በሚለው የባለሙያዎችን የትምህርት ማስረጃ በአካባቢው በሚገኘው ጤና ጽሕፈት ቤት መረጃቸው ነበር፡፡ ቢሮው የስፔሻሊቲ ክሊኒኮች የትምህርት ማስረጃ መቀመጥ (መያያዝ) ያለበት በክልሉ ጤና ቢሮ መሆኑን ከዚህ በፊት በቃልም ሆነ በጽሑፍ አልገለጽንም፡፡ ይህም ሆኖ ግን አሁን በተሰጠን መመርያ መሠረት ሁሉንም የባለሙያዎች ማስረጃ ከጤና ጽሕፈት ቤቱ በሸኚ ደብዳቤ ተቀብለን ለክልሉ ጤና ቢሮ የላክንና የተያያዘ መሆኑ መታወቅ ይኖርበታል፡፡ ከዚህም ሌላ የክሊኒኩ ሁለት ባለሙያዎች ዶክሜንታቸው እስከሚስተካከል ድረስ ከሚያዝያ 20 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ በደብዳቤ ከሥራ ታግደዋል፡፡

ሪፖርተር፡- የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈባቸውን መድኃኒቶች በተመለከተ ምን ዕርምጃ ተወስዷል?

ዶ/ር ጥላሁን፡- የተወሰደውን ዕርምጃ ከመግለጼ በፊት አንድ ማስረዳት የምፈልገው ነገር አለ፡፡ እሱም ለድንገተኛ ከተቀመጡ መድኃኒቶች ጋር ክሊኒኩ የማይጠቀምባቸውና የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፉ መድኃኒቶች ከተለዩበት በስህተት ተቀላቅለው መገኘታቸውን ነው፡፡ ይህም ሆኖ ግን የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈባቸውን መድኃኒቶች በመለየት እንዲወገዱልን ለደብረ ማርቆስ ከተማ አስተዳደር ጤና አጠባበቅ ጽሕፈት ቤት በደብዳቤ ጠይቀናል፡፡ በነርስ ክፍል ያሉትን የድንገተኛ መድኃኒቶች እንዲከታተሉ ኃላፊነት የተሰጣቸው የክፍሉ ባለሙያዎች በፈጸሙት ጥፋት በዲሲፕሊን እንዲጠየቁ ተደርጓል፡፡ ተቆጣጣሪ ቡድኑ ደረጃውን የጠበቀ የቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓት አለመኖር ባቀረበው ክስ መሠረት በአሁኑ ሰዓት ይህንን ያስተካከለልንና ሦስት የቆሻሻ ማጠራቀሚያ (ደስት ቢን) ሲስተም መቀመጡንም በዚህ አጋጣሚ ለመግለጽ እወዳለሁ፡፡ ከዚህም ሌላ የኢንፌክሽን ፐሪቬንሽን ባለሙዎች ከምሥራቅ ጎጃም ጤና መምርያ በመጡ ባለሙያዎች ለሦስት ቀናት ሥልጠና ተሰጥቶአቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ክሊኒኩ ለበሽተኞች መድኃኒት መስጠት ቢፈልግ ከየት ነው የሚወስደው?

ዶ/ር ጥላሁን፡- ክሊኒኩ በቅርብ ርቀት የሚገኝና ደረጃውን የጠበቀ የራሱ የሆነ መድኃኒት ቤት አለው፡፡ ለታካሚዎች የሚያስፈልገውንም መድኃኒት የሚጠቀመው ከዚሁ መድኃኒት ቤት ብቻ ነው፡፡  

ሪፖርተር፡- ክሊኒኩ ከዚህ በፊት እንዳሁኑ ዓይነት ዕገዳ ወይም ቅጣት ተጥሎበት ያውቃል?

ዶ/ር ጥላሁን፡- በክሊኒኩ ላይ ከዚህ በፊት በተካሄደበት የኢንስፔክሽን ሥራ ምንም ዓይነት የቃልም ሆነ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶት አያውቅም፡፡ እንዲያውም በክልሉ ከሚገኙ የግል ጤና ተቋማት ከፍተኛ ደረጃ (አረንጓዴ ላይሰንስ) ያለው ነው፡፡ ከ25 በላይ ቋሚና ከአምስት በላይ ተመላላሽ ባለሙያዎችንና ሠራተኞችን የሚያስተዳድር ነው፡፡ ይህም ከግንዛቤ ተያይዞ የተለመደውን አገልግሎት እንዲቀጥል በመወትወት ላይ ነን፡፡  

ሪፖርተር፡- ክሊኒኩ አገልግሎቱን እንዲቀጥል በማድረግ ከጎናችሁ የቆሙ የመንግሥት ተቋማት አሉ?

ዶ/ር ጥላሁን፡- አዎ አሉ፡፡ ለዚህም የደብረ ማርቆስ ከተማ አስተዳደር ጤና ጥበቃ ጽሕፈት ቤት፣ የምሥራቅ ጎጃም ዞን ጤና ጥበቃ መምርያና የምሥራቅ ጎጃም ዞን አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ተጠቃሾች ናቸው፡፡ እነዚህ መንግሥታዊ ተቋማት ዕገዳው በማስጠንቀቂያ እንዲተላለፍ የሚገልጽ የውሳኔ ሐሳብ ለአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የጤና ቢሮ ሰጥተዋል፡፡ ድርጅቶቹ ይህንን የውሳኔ ሐሳብ ሊያቀርቡ የቻሉት ክሊኒኩ ፈጠራቸው የተባሉት ግድፈቶች በፍጥነት የሚታረሙና ተቆጣጣሪው አካል በግኝቶቹ ላይ አስተያየት በሰጡ በማግሥቱ የተስተካከሉ መሆኑን በመገንዘባቸው ነው፡፡ ከዚህም ሌላ ክሊኒኩ እስካሁን ካለው የመልካም ሥራ አፈጻጸም በተለይ ለማኅበረሰቡ በዕውቀትና በገንዘብ ድጋፍ በማድረግ እየሰጠ ያለው አገልገሎት፣ እንዲሁም የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ሰጪ ባለሙያዎች አሟልቶ በመሥራት በከተማችን ፋና ወጊ መሆኑንም ስለሚያውቁ ነው፡፡  

ሪፖርተር፡- በተለይ የምሥራቅ ጎጃም ዞን አስተዳደር ጽሕፈት ቤት የክሊኒኩን ከሥራ መታገድ የሚያስከትለውን አሉታዊ ተፅዕኖ አስመልክቶ ለክልሉ ጤና ጥበቃ ቢሮ የጻፈው ደብዳቤ እንዳለ ነግረውናል፡፡ የደብዳቤውን ፍሬ ሐሳብ በአጭሩ ቢገልጹልን?

ዶ/ር ጥላሁን፡- የደብረ ማርቆስ ሪፈራል ሆስፒታል አሁን ባለበት ነባራዊ ሁኔታ ለከፍተኛ የሥራ መጨናነቅ የተዳረገ ከመሆኑም በላይ በሽተኞች ማረፊያ አጥተው ለከፍተኛ እንግልት እየተዳረጉ መሆኑን፣ በሆስፒታሉ ያሉ የሕክምና ባለሙዎች ከበሽተኛ ፍሰት የተነሳ ከአቅም በላይ አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙ መሆናቸው፣ ዞናችንን ጨምሮ ከአጎራባች ዞኖችና ከክልሎች የሚመጡ ተገልጋዮች የተለያዩ ምርመራዎችን ለማግኘት በተሟላ መንገድ የተደራጀ የጤና ተቋም በዞናችን የሌለ መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡ በዚህ ላይ ደግሞ በአዲስ ቪዥን የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስት ክሊኒክ ላይ የተወሰደው ዕርምጃ ካለው አጠቃላይ ጫና ጋር ተዳምሮ ሲወሰድ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ ስለሆነም ለሦስት ወራት እንዲዘጋ የተወሰነውን ውሳኔ እንደገና በማየት ሌሎች የቅጣት አማራጮችን በመከተል ኅብረተሰቡ ከጤና ተቋሙ ማግኘት ያለበትን አገልግሎት እንዲያገኝ ውሳኔውን እንደገና እንዲጠና የሚጠይቅ ነው፡፡  

ሪፖርተር፡- ቢሮው የቀረቡለትን አማራጭ የውሳኔ ሐሳቦችን እንዴት ተመለከተው?

ዶ/ር ጥላሁን፡- የጤና ጥበቃ ቢሮ ለዚህ የሰጠው መልስ ጉዳዩን እንደገና እናየዋለን የሚል ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ክሊኒኩ የሕክምና አገልግሎት የሚሰጠው በክፍያ መሆኑ አያጠያይቅም፡፡ የመክፈል አቅም የሌላቸው ታካሚዎች ሲመጡ ይመልሳቸዋል? ወይስ አገልግሎት እንዲያገኙ በማድረግ ይተባበራል?

ዶ/ር ጥላሁን፡- የአቅም ማነስ ችግር ላጋጠማቸው ታካሚዎች ካልከፈላችሁ አላክማችሁም የሚል አቋም የለውም፡፡ በተቻለ መጠን ሕክምናውን በነፃ እንዲያገኙ ይደረጋል፡፡ ግፋ ቢል ደሃ ለመሆናቸው የሚያረጋግጥ ማስረጃ ጉዳዩ ከሚመለከተው አካል እንዲያመጡ ይደረጋል፡፡ ለምሳሌ ያህልም አንድ የደብረ ማርቆስ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የዘጠነኛ ክፍል ተማሪ የሆነችውን በ2010 ዓ.ም. የትምህርት ዘመን በ1ኛው ሴሚስተር 96.9 በመቶ በማምጣት ከክፍሉ 1ኛ ከአጠቃላይ ተማሪዎች 2ኛ የወጣችውን ተማሪ በደረሰባት ሕመም ክሊኒኩ ነፃ ሕክምና በመስጠት ሕመሟ እንዲሻላት አድርጓል፡፡