Skip to main content
x
በእንቆቅልሽ የተሞላው የዶናልድ ትራምፕና የኪም ጆንግ ኡን የሲንጋፖር ውይይትና ስምምነት
የሰሜን ኮሪያ ፕሬዚዳንት ኪም ጆንግ ኡን ከአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር በሲንጋፖር ካፔላ ሪዞርት ለመጀመርያ ጊዜ ተገናኝተው እጅ ለእጅ ሲጨባበጡ

በእንቆቅልሽ የተሞላው የዶናልድ ትራምፕና የኪም ጆንግ ኡን የሲንጋፖር ውይይትና ስምምነት

ሀዋርድ ኤክስ የሚኖረው ሆንግ ኮንግ ሲሆን ቁርጥ የሰሜን ኮሪያን ፕሬዚዳንት ኪም ጆንግ ኡንን ይመስላል፡፡ ከዚህ ቀደም በድርጊት ማስመሰል ጥበቡ ዶናልድ ትራምፕን ከሚያስመስለው የሙያ አጋሩ ዴኒስ አለን ጋር በመሆን፣ በደቡብ ኮሪያ ፕዮንግቻንግ በተካሄደው የክረምት ኦሊምፒክ በጭራሽ ካልገመቱ ተሳታፊዎች ጋር ፎቶ በመነሳትና አብሮ በመቀመጥ ከፍተኛ ትኩረትን ሊስብ የቻለ ኮሜዲያን ነው፡፡

ዶናልድ ትራምፕና ኪም ጆንግ ኡን ሊገናኙ ቀነ ቀጠሮ ሰኔ 5 ቀን 2010 ዓ.ም. በያዙባት በሲንጋፖር ከተማም ይህ አስመሳይ ድርጊት  ተከስቷል፡፡ በዚህ ጊዜ ግን ዶናልድ ትራምፕን ከሚያስመስለው የሙያ አጋሩ ጋር በመሆን፣ የመሪዎቹን አልባሳትና የፀጉር አሠራር በማስመሰል ሬስቶራንት ውስጥ ቁጭ ብለው ምግብ በመመገብ ከሰዎች ጋር ድንገት ፎቶግራፎችን በመነሳት አላበቃም፡፡ በሲንጋፖር የፀጥታ ኃላፊዎች በቁጥጥር ሥር እንዲውልም አደረገው እንጂ፡፡

ኪም ጆንግ ኡን በድብቅ ሲንጋፖር ገብቶ ከሆነስ ማን ያውቃል የሚል ጥርጣሬ ያደረባቸው የሲንጋፖር የፀጥታ ኃላፊዎች፣ ሀዋርድ ኤክስን ምርመራ ክፍል አስገብተው ስለፖለቲካ አመለካከቱና በሌላ አገሮች ብጥብጥና አመፅ ውስጥ ተሳትፎ ኖሮት ያውቅ እንደሆነ ጠይቀውታል፡፡ ከዚያም የመሪዎቹ ውይይት የሚደረግበት ሥፍራ በፍፁም እንዳይደርስ ማስጠንቀቂያ ሰጥተው ይሸኙታል፡፡

በእንቆቅልሽ የተሞላው የዶናልድ ትራምፕና የኪም ጆንግ ኡን የሲንጋፖር ውይይትና ስምምነት
በደቡብ ኮሪያ ሴኡል ከተማ ሀዋርድ ኤክስና ዴኒስ አለን ሁለቱን መሪዎች ተመስለው አድናቂዎቻቸውን ሲያስደስቱ

 

ሀዋርድም በሰዎች ዓይን ውስጥ በድጋሚ ገባ፡፡ ስለሁለቱ መሪዎች ውይይት ሲጠየቅም፣ ‹‹ሁለቱ መሪዎች እጅግ ጥሩ ጊዜን አብረው የሚያሳልፉ ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም ሁለቱም አንድ ዓይነት ናቸውና፤›› ሲልም ከመርማሪዎቹ ከተሰናበተ በኋላ ተናግሮ ነበር፡፡

ይኼ ምን ያህል የሰሜን ኮሪያና የአሜሪካ ጉዳይ ዓለም አቀፍ ትኩረት እንዳገኘ ማመላከቻ ነው፡፡ ይሁንና ዶናልድ ትራምፕ ከውይይቱ ሦስት ቀናት ቀደም ብለው ከቡድን ሰባት አባል አገሮች ጋር ባደረጉት ስብሰባ የቀረበላቸውን ጥያቄ ባለመቀበላቸው ለዚህኛው ስብሰባ በቂ ዝግጅት እንዳይደረግ ተፅዕኖ ሊኖረው ይችላል የሚሉ ነበሩ፡፡

የዶናልድ ትራምፕ አሜሪካ፣ ጀርመን፣ ፈረንሣይ፣ ጣሊያን፣ ካናዳ፣ እንግሊዝና ጃፓን በአባልነት፣ የአውሮፓ ኅብረት ደግሞ በተሳታፊነት የተካፈሉበትና በኩቤክ ካናዳ የተካሄደው የቡድን ሰባት አገሮች ከእስራኤልና ፍልስጤም ጉዳይ፣ እስከ አፍሪካ ዕድገት ራዕይ 2063 ድረስ ባካተተው ውይይት ላይ መስማማት ያልቻሉበት አንድ መሠረተ ጉዳይ ነበር፡፡ የዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር በንግድ አጋሮች ላይ የጣለው የአልሙኒየምና የብረታ ብረት ቀረጥ ነው፡፡

በዚህ ቀረጥ ላይ መስማማት ያቃታቸው ሰባቱ አገሮች የተለያዩ የመልስ ምቶችን ለመስጠት ዝግጅት ላይ የነበሩ ሲሆን፣ ዶናልድ ትራምፕ ግን በዚህ ደስተኛ አልነበሩም፡፡ የአስተናጋጅ አገር ካናዳ ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶን ለመዝለፍና የተላለፈውን መግለጫ ላለመቀበልም ዶናልድ ትራምፕ አውሮፕላን ላይ እስከሚወጡ ድረስ ብቻ ነበር ጊዜ የፈጀባቸው፡፡

በእንቆቅልሽ የተሞላው የዶናልድ ትራምፕና የኪም ጆንግ ኡን የሲንጋፖር ውይይትና ስምምነት
የሰሜን ኮሪያ ፕሬዚዳንት ኪም ጆንግ ኡን በሲንጋፖር አቀባበል ሲደረግላቸው

 

ጠቅላይ ሚኒስትር ትሩዶን ‹‹እምነተ ቢስና ደካማ›› በማለት በትዊተር ገጻቸው ላይ ያሰፈሩት ዶናልድ ትራምፕ፣ ካናዳ በድርድሩ ወቅት ደካማ አቋም ማንፀባረቋንና የአሜሪካን ታሪፍ እንደ ስድብ በመቁጠር እንደተናገረች አክለዋል፡፡

ነገር ግን ‹እውን ይህ እንደሚሆን አልተጠበቀምን?› ብለው የሚጠይቁ ነበሩ፡፡ ምክንያቱም ውይይቶቹ ጠንካራ እንደሆኑ ተወስቷልና፡፡

የዶናልድ ትራምፕ የኢኮኖሚ ጉዳዮች አማካሪ ላሪ ኩድሎው ትሩዶ የትራምፕን ግፊት እንደማይቀበለው ለሕዝቡ በመናገራቸው እሳቸው ናቸው ያጠፉት ብለው፣ ‹‹በሴኡኦልም ልዩ ሥፍራ ይጠብቃቸዋል፤›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ከዚህ ውጥረት ያየለበት ስብሰባ በኋላ ነው እንግዲህ ዶናልድ ትራምፕ ወደ ሲንጋፖር ያቀኑት፡፡ ሲንጋፖር ሲደርሱም ልክ ለሰሜን ኮሪያው ኪም እንዳደረጉት ሁሉ ከአውሮፕላን ማረፊያ የሲንጋፖር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቪቪያን ባላክሪሽናን ነበሩ የተቀበሏቸው፡፡

የዶናልድ ትራምፕና የኪም ጆንግ ኡን ስምምነት እዚህ ላይ ለመድረስ ብዙ ርቀት ተጉዟል፡፡ የሁለቱ መሪዎች ግንኙነት የተጠነሰሰው እ.ኤ.አ. ማርች 8 ቀን 2018 ሲሆን፣ የሰሜን ኮሪያ እንነጋገር ጥሪ በደቡብ ኮሪያ በኩል ለፕሬዚዳንት ትራምፕ ሲቀርብም ነበር፡፡

ቀጥሎም ኤፕሪል 18 ቀን 2018 ዶናልድ ትራምፕ በቅርቡ ከሲአይኤ ዳይሬክተርነት አንስተው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ያደረጓቸው ማይክ ፖምፒዮ ከሰሜን ኮሪያ መሪዎች ጋር በሚስጥር መገናኘታቸውን ተናገሩ፡፡ ኤፕሪል 21 ቀን ሰሜን ኮሪያ የኑክሌርና የሚሳይል ሙከራዎቿን እንደምታቆም እንዳታስታወቀች፣ ኤፕሪል 27 ቀን የሰሜን ኮሪያ ፕሬዚዳንት ኪም ጆንግ ኡንና የደቡብ ኮሪያ ፕሬዚዳንት ሙን ጃኤ ኢን በሁለቱ አገሮች ድንበር ላይ ተገናኙ፡፡ ሰሜን ኮሪያም ሜይ 9 ቀን ሦስት አሜሪካውያን እስረኞችን ለቀቀች፡፡ ዶናልድ ትራምፕም ኪም ጆንግ ኡንን ጁን 12 ቀን እንደሚያገኙ ሜይ 10 ቀን ይፋ አደረጉ፡፡

በእንቆቅልሽ የተሞላው የዶናልድ ትራምፕና የኪም ጆንግ ኡን የሲንጋፖር ውይይትና ስምምነት
ፕሬዚዳንት ትራምፕ በካናዳ ኩቤክ ግዛት በተካሄደው የቡድን ሰባት አገሮች ስብሰባ ላይ ከጀርመን መራሒተ መንግሥት አንገላ መርከልና ከሌሎች አገሮች መሪዎች ጋር ሲከራከሩ

 

ይሁንና ከሁለት ሳምንታት በኋላ ሜይ 24 ቀን ዶናልድ ትራምፕ ግልጽ ጥላቻን የሚያንፀባርቁ መልዕክቶች ከሰሜን ኮሪያ ተሰምተዋል በማለት ግንኙነቱን እንደሰረዙት ተናገሩ፡፡ በዚህም ብዙዎች ግራ መጋባትና ድንጋጤ ላይ ወደቁ፡፡ ኪም ጆንግ ኡንም ለግንኙነቱ ዝግጁነታቸውና ቁርጠኝነታቸውን ገለጹ፡፡

ቀጥሎም የኪም ጆንግ ኡንን ጥሪና ደብዳቤ ተከትሎ ጁን 1 ቀን ዶናልድ ትራምፕ ውይይቱ እንደሚካሄድ በድጋሚ ይፋ አደረጉ፡፡ የዶናልድ ትራምፕ ጠበቃ ሩዲ ጉሊያኒ ኪም ከትራምፕ ጋር የሚደረገው ውይይት እንዳይቀር፣ በጉልበታቸው ተንበርክከውና በእጃቸው ተንሰፍስፈው ለመኑ ሲሉ ተናገሩ፡፡

ለዶናልድ ትራምፕ የእዚህ ውይይት የመጨረሻ ግብ ሰሜን ኮሪያ የኑክሌር ጦር መሣሪያን ሙሉ በሙሉ እንድታስወግድ በጅምርነት የሚያገለግል ሲሆን፣ ኪም ጆንግ ኡን በኢኮኖሚ ልማት ላይ ያተኮረ ግብ ላይ ያልማሉ፡፡ ግራም ነፈሰ ቀኝ ሁለቱ መሪዎች ተገናኝተው መፍትሔ የሚያስቀምጡ ከሆነ፣ በዓለም ታሪክ ትልቁ ድርድርና ውጤት ያስገኘ ዲፕሎማሲ ሆኖ ይመዘገባል ተብሏል፡፡

ዶናልድ ትራምፕና ኪም ጆንግ ኡን በሲንጋፖር ካፔላ ሪዞርት ማክሰኞ ሰኔ 5 ቀን 2010 ዓ.ም.  ተገናኝተው ከተለያዩ በኋላ፣ የሰሜን ኮሪያን የኑክሌር ጦር መሣሪያዎች ሙሉ በሙሉ ለማውደም ስምምነት ላይ መድረሳቸውን አስታውቀዋል፡፡ ፕሬዚዳንት ትራምፕ ከስምምነቱ በኋላ በሰጡት መግለጫ፣ የሰሜን ኮሪያ የኑክሌር መሣሪያዎች ሙሉ በሙሉ ከጥቅም ውጪ እስኪሆኑ ድረስ ማዕቀቡ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

 ‹‹ሰሜን ኮሪያ ዋነኛውን የኑክሌር ሙከራ ጣቢያዋን አውድማለች፡፡ ነገር ግን ከዚህ የበለጠ በማድረግ ከተቀረው ዓለም በንግድና በመሳሰሉት ግንኙነቷን ለማስቀጠል ገደብ አይደረግባትም፤›› ሲሉም አስታውቀዋል፡፡ በዚህም መሠረት ሰሜን ኮሪያ የኑክሌር ትጥቋን መፍታቷ ከተረጋገጠና ሥጋት መሆኗ ካቆመ ማዕቀቡ አይቀጥልም ሲሉም አክለዋል፡፡ የሰሜን ኮሪያ ፕሬዚዳንትንም፣ ‹‹በጣም አስፈላጊ፣ በጣም ተደራዳሪ፣ ባለተሰጥኦ አዕምሮና አገሩን የሚያፈቅር ሰው ነው፤›› ብለዋቸዋል፡፡ ወደፊት ኋይት ሐውስ እንደሚጋብዟቸውም ለጋዜጠኞች አስረድተዋል፡፡

ወጣቱ ኪም ጆንግ በበኩላቸው ሁለቱም ያለፈውን ለመርሳት መስማማታቸውን ገልጸው፣ ‹‹ዓለም ትልቅ ለውጥ ያያል፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹ፕሬዚዳንት ትራምፕ ይህ ውይይት እንዲካሄድ በማድረጋቸው ምሥጋናዬን አቀርብላቸዋለሁ፤›› በማለት ከትራምፕ ጋር ያደረጉትን ስምምነት አሞካሽተዋል፡፡ ሁለቱም መሪዎች መጀመርያ ለመገናኘት ከሊሞዚኖቻቸው ሲወርዱ ኮስታራ ፊት ይታይባቸው የነበረ ቢሆንም፣ ከተገናኙና ከተወያዩ በኋላ ግን በፈገግታ ምሥጋና ሲለዋወጡ መታየታቸውን በሥፍራው የነበሩ ታዋቂ ሚዲያዎች ዘግበዋል፡፡ ይህንን ያህል ምዕራፍ ተጉዘው ስምምነት ላይ መድረስ መቻላቸው ግን ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አዲስ ክስተት ሆኗል፡፡

‹‹ይህ የአንድ ጊዜ ዕድል ነው፤›› ሲሉ ዶናልድ ትራምፕም የገለጹት ለዚህ ይመስላል፡፡