Skip to main content
x
ለክቡር ሚኒስትሩ በቅርቡ ከእስር የተፈታ ደላላ ይደውልላቸዋል

ለክቡር ሚኒስትሩ በቅርቡ ከእስር የተፈታ ደላላ ይደውልላቸዋል

[ለክቡር ሚኒስትሩ ሌላ ሚኒስትር ስልክ ይደውሉላቸዋል]

 • ሰላም ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እንዴት ነህ ወዳጄ?
 • ምንድነው እየተካሄደ ያለው ክቡር ሚኒስትር?
 • ደግሞ ምን ተካሄደ?
 • እንደ አዲስ ማገርሸት ጀመረ እኮ?
 • ምኑ ነው እንደ አዲስ ያገረሸው?
 • ሚዲያ አይከታተሉም እንዴ ክቡር ሚኒስትር?
 • ሰውዬ እኔ የዓለም ዋንጫ ከጀመረ በኋላ ከእሱ ውጪ ምንም ነገር አልከታተልም፡፡
 • እየቀለዱ ነው ክቡር ሚኒስትር?
 • በዓለም ዋንጫ ቀልድ የለም፡፡
 • እርስዎ እኮ የአገር አመራር ነዎት?
 • ብሆንስ ታዲያ?
 • ጊዜዎን በንባብና በምርምር በማሳለፍ ለሕዝቡ አቅጣጫ መስጠት ሲገባዎት፣ የእግር ኳስ እያዩ ጊዜዎን ያጠፋሉ?
 • ሰውዬ እንዳትሳሳት፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር ሳላውቅ የእግር ኳስ አሠልጣኝ ሆኑ እንዴ?
 • ስማ ከእግር ኳስ ብዙ የምንማረው ነገር አለ፡፡
 • ማለት?
 • አየህ አሥራ አንድ ተጨዋቾች እንዴት ለጋራ ግብ እንደሚሠሩ ብዙ የምንማርበት መድረክ ነው፡፡
 • ኧረ ይተው ክቡር ሚኒስትር?
 • በዚያ ላይ ደግሞ እግር ኳሳችን የወደቀ በመሆኑ እንዴት ማንሳት እንደምንችል የምንማርበት መድረክ ነው፡፡
 • ምን አሉኝ ክቡር ሚኒስትር?
 • ኳሳችንን ለማሳደግ ሙሉ የዓለም ዋንጫውን መመልከት አለብኝ፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር መስመር ግን እየሳቱ ይመስለኛል፡፡
 • ያልገባኝ ነገር ግን ብላችሁ ብላችሁ ኳስ አትይ ልትሉኝ ነው?
 • ክቡር ሚኒስትር ኳስ ከማየት ይልቅ ሊሠሯቸው የሚገቡ በርካታ ሥራዎች አሉ፡፡
 • እኔ ግን እንዲያውም የፈለግኩት እዚያው ሩሲያ ሄዶ ማየት ነበር፡፡
 • እ. . .
 • ይኸው ዶላር የለም ምናምን በሚል ተልካሻ ምክንያት ነው ያስቀራችሁኝ፡፡
 • እኔ የሚገርመኝ በዚህ አቅምዎ እዚህ ኃላፊነት ላይ መቀመጥዎ ነው?
 • ለመሆኑ አንተን ማን ነው ደረጃ መዳቢ ያደረገህ?
 • ለማንኛውም ግን አገሪቱ ውስጥ እየተፈጸሙ ያሉ ነገሮች አሳስበውኛል፡፡
 • ምኑ ነው ያሳሰበህ?
 • ይኸው እንደገና ብጥብጥና ግጭቱ አገርሽቷል አይደል እንዴ?
 • የምን ግጭት ነው?
 • ደቡብ ክልል ግጭት ተከስቷል አይደል እንዴ?
 • ምን?
 • ሰዎች ሞተዋል እኮ?
 • ስማ ድሮ አገሪቱ ላትበጠበጥ ትችላለች ብለህ ታስብ ነበር?
 • ምን እያሉ ነው?
 • መጀመርያውኑ እኔ ይቅር ተው ብልም የሚሰማኝ አጥቼ እኮ ነው?
 • አልገባኝም ክቡር ሚኒስትር?
 • ይኼ ሁሉ አሸባሪ ተፈቶ አገር እንዴት ሰላም ይሆናል?
 • ምን እያሉ ነው ክቡር ሚኒስትር?
 • መጀመርያውኑ እኔ አይፈቱ ብዬ የተከራከርኩት ለዚህ ነው፡፡
 • አሁን ወደ ኋላ የማንመለስበት አዲስ ምዕራፍ ውስጥ ነን ያለነው፡፡
 • የአዲሱን ምዕራፍ ውጤትማ ይኸው እያየነው ነው፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር ሰዎቹ የተለቀቁት እኮ በአገሪቱ ውስጥ ሰላም ለማስፈን ነው፡፡
 • አሸባሪ እየለቀቁ የምን ሰላም ነው?
 • ክቡር ሚኒስትር እነዚህ ሰዎች አሸባሪዎች ለመሆናቸው ምን ማስረጃ አለዎት?
 • ማስረጃ ስንፈልግ እኮ ነው አገሪቱ የተዘረፈችው፡፡
 • ለማንኛውም ክቡር ሚኒስትር ሕዝቡን አሸባሪ ነው ማለት ከባድ ይመስለኛል፡፡
 • ታዲያ ማን ነው አሸባሪ?
 • እኛው!

[ለክቡር ሚኒስትሩ በቅርቡ ከእስር የተፈታ ደላላ ይደውልላቸዋል]

 • ክቡር ሚኒስትር እናንተ ግን ታጥቦ ጭቃ ናችሁ?
 • ምን እያልክ ነው?
 • አድሮ ቃሪያ ናችሁ እያልኩ ነው፡፡
 • ምንም አልገባኝም?
 • አገር ተሻሻለ ስንል ጭራሽ ብሶባችሁ ቁጭ ይላለ እንዴ?
 • ምን ሆነህ ነው?
 • ይኼ መንግሥት የፍቅር መንግሥት ሆኗል ብለን ሳንጨርስ እንዴት ታሳፍሩናላችሁ?
 • የፍቅር መንግሥት ስለመሆናችን ትጠራጠራለህ?
 • በሚገባ እንጂ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • የፍቅር መንግሥት ስለሆንን አይደል እንዴ አንተን የፈታንህ?
 • ግን ምን ያደርጋል ክቡር ሚኒስትር?
 • እንዴት ማለት?
 • ይኸው ይቺ አገር ብዙ ተስፋ አላት ብዬ ገና ከእስር እንደወጣሁ ስንትና ስንት ፕሮጀክቶች ነድፌ ለመንቀሳቀስ እያሰብኩ ነበር፡፡
 • ይኼማ የሚበረታታ እንቅስቃሴ ነው፡፡
 • ታዲያ ምን ያደርጋል ክቡር ሚኒስትር?
 • ምን ሆንክ?
 • ያ ሁሉ መነቃቃቴ ላይ ቀዝቃዛ ውኃ እኮ ነው የቸለሳችሁብኝ፡፡
 • ማን ነው የቸለሰብህ?
 • ሰሞኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያሉትን አልሰሙም እንዴ?
 • ያው እሳቸው ብዙ ነገር ስለሚያወሩ ስለየትኛው ነው የምትለኝ?
 • ለፓርላማ ሪፖርታቸውን ያቀረቡ ቀን ሰው ሁሉ ኳሱን ትቶ እሳቸውን ሲያይ እኔም መከታተል ጀመርኩ፡፡
 • የፓርላማው ውይይት ጥሩ ነበር አይደል?
 • ክቡር ሚኒስትር እኔማ በንዴት ቲቪውን ልሰብረው ነበር፡፡
 • ለምን?
 • ስለእኔ ነበር እኮ ሲያወሩ የነበሩት፡፡
 • ስለአንተ ደግሞ ምን አሉ?
 • ይቅርታ የተደረገላቸው ሙሰኞች ዳግመኛ ሊታሰሩ ይችላሉ አሉ እኮ?
 • ታዲያ አንተ ንፁህ አይደለህ እንዴ?
 • ክቡር ሚኒስትር እሱንማ እኔም እርስዎም ጠንቅቀን እናውቀዋለን፡፡
 • ምኑን?
 • ምን ያህል በሙስና የተጨማለቅኩ መሆኔን ነዋ?
 • እሱማ ይታወቃል፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር እኔ እኮ ብቻዬን ፋብሪካ የዋጥኩ ሰው ነኝ፡፡
 • እሱስ ልክ ብለሃል፡፡
 • ይኸው አሁን የዋጥኩትን ፋብሪካ እዚሁ አገሬ ላይ እተፋዋለሁ ብዬ ተነቃቅቼ ሳበቃ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ውኃ ቸለሱብኝ፡፡
 • ስማ ዋናው ነገር አንድና አንድ ነው፡፡
 • ምንድነው ክቡር ሚኒስትር?
 • ይህች አገር እንድትለማ ትፈልጋለህ?
 • ምን ነካዎት ክቡር ሚኒስትር?
 • ማለት?
 • ይኸው የዋጥሁትን ፋብሪካ ለመትፋት ተዘጋጅቼያለሁ ስልዎት?
 • በቃ ለልማቱ ይኼን ያህል ተነሳሽነት ካለህ ችግር የለውም፡፡
 • እንዴት ማለት ክቡር ሚኒስትር?
 • አንተ በልማቱ የምትሳተፍበትን ቦታ እኔ አመቻችልሃለሁ፡፡
 • የማለማው ቦታ ያገኙልኛል?
 • በሚገባ፡፡
 • የትኛውን ቦታ እንዳለማ ፈልገው ነው?
 • ማረሚያ ቤቱን!

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚስታቸው ጋር እያወሩ ነው]

 • ስሚ ይኼን ሁሉ ሱፍ ታይዋለሽ አይደል?
 • ምን ሆነ?
 • ይኼን ቡትቶ ጠራርገሽ ከቁም ሳጥኑ ውስጥ አውጭልኝ፡፡
 • ምን?
 • እንደውም ለተቸገረ ያለበለዚያ ገጠር ላሉ ዘመዶችሽ ስጪያቸው፡፡
 • ለምን?
 • እንዲያውም የሚገዛሽ አገኘሽ ብትሸጪያቸው መልካም ነው፡፡
 • አልገባኝም ግን?
 • ከሁለት ሱፍ ውጪ ሌላው እኮ የሚረባ አይደለም፡፡
 • እስከዛሬ ስታደርጋቸው የነበሩ ሱፎች አይደሉ እንዴ?
 • ይኸው እነዚህ ሱፎች ብቻ ናቸው ጋዜጣዊ መግለጫ ሲኖረኝ የማደርጋቸው፣ ሌሎቹን አልፈልጋቸውም፡፡
 • ምን ነክቶህ ነው ግን?
 • አንቺ ሚዲያ አትከታተይም እንዴ?
 • ሰሞኑን ብዙም እየተከታተልኩ አይደለም፡፡
 • ስሚ አሁን ነገሮች በብርሃን ፍጥነት እየሄዱ ስለሆነ ከሚዲያ መራቅ የለብሽም፡፡
 • ለምን?
 • አገሪቱ ላይ በአንዴ ብዙ ነገሮች እየተፈጸሙ ስለሆነ፣ በንቃት መከታተል አለብሽ፡፡
 • ምንድነው የምታወራው?
 • ከዘመኑ ጋር መፍጠን አለብሽ፡፡
 • ምን ይደረግ ነው የምትለው?
 • ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰሞኑን ያሉትን አልሰማሽም እንዴ?
 • ምን አሉ ደግሞ?
 • የሥራ አስፈጻሚ ስብሰባ በቀጥታ ይተላለፋል ብለዋል፡፡
 • እና ታዲያ?
 •  ስብሰባዎቻችን በቲቪ ከተላለፉ ሕዝቡ ሊያየኝ ነዋ፡፡
 • ቢያይህስ?
 • ፕሮቶኮሌን መጠበቅ የለብኝም?
 • እሱማ አለብህ፡፡
 • አሁን እንደምንም ብዬ አንቺን ጣሊያን ሚላን እልክሻለሁ፡፡
 • እሺ?
 • ከዚያ ብራንድ ሱፎችን ይዘሽ ትመጫለሽ፡፡
 • ጤነኛ ነህ ግን ሰውዬ?
 • ምነው?
 • አሁን እንኳን ከስህተትህ ለመማር ዝግጁ አይደለህም ማለት ነው?
 • ምን አደረግኩ?
 • ጭልጥ ያለ እንቅልፍ ወስዶሃል ልበል?
 • የምን እንቅልፍ ነው?
 • አሁን እኮ ሙስናን መጠየፍ ካልጀመርክ መጨረሻህ የት እንደሆነ አታውቅም?
 • እኔ እኮ ለሥራዬ የሚያግዘኝን ነገር ነው እንድታደርጊልኝ የጠየቅኩሽ?
 • ምኑ ነው ለሥራህ የሚያግዝህ?
 • አለባበሴ ነዋ፡፡
 • ምን?
 • ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዴት እንደሚዘንጡ አታያቸውም?
 • ወይ ግሩም?
 • አለባበሴ የሚማርክ ከሆነ ለጥሩ ቦታ ልታጭ እችላለሁ፡፡
 • ስማ ቁም ነገሩ አለባበስ ሳይሆን ሌላ ነው፡፡
 • ነገርኩሽ ፖለቲካ ከዝነጣ ነው የሚጀመረው፡፡
 • ለማንኛውም ዘንጠህ የምታወራው ከሌለህ ስም እንዳያወጡልህ፡፡
 • ምን ብለው?
 • ትጥቅ ብቻ!

[ክቡር ሚኒስትሩ ከአማካሪያቸው ጋር እያወሩ ነው]

 • ሥራችን ከዚህ በኋላ በጣም ሊጠናከር እንደሚችል ታውቃለህ?
 • እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
 • ያው አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዙሩን አክረውታል፡፡
 • እሱማ ግልጽ ነው፡፡
 • ስለዚህ እኛም አፈጻጸማችንን በ11 በመቶ ማሳደግ አለብን፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር ለአፈጻማችን ማነቆ የሆኑት እኮ እርስዎ ነዎት፡፡
 • እንዴት?
 • ይኸው ስንትና ስንት ሪፖርቶች ባስገባም የእርስዎን ጠረጴዛ ማሞቅ ሆኗል ሥራቸው፡፡
 • እ. . .
 • በተለይ የዓለም ዋንጫ ከተጀመረ በኋላ ሙሉ ጊዜዎን ኳስ ሲመለከቱ ነው የሚያሳልፉት፡፡
 • ለመሆኑ አንተን አማክረኝ እንጂ ተቆጣጠረኝ ብዬሃለሁ?
 • ኧረ እኔ ማማከር ነው ሥራዬ፡፡
 • ስለዚህ ይኼን መመርያ ለሁሉም ነው የምሰጠው፡፡
 • እሺ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ምን ሆነህ ነው ግን አሥር ጊዜ እየተንጠራራህ በመስኮት የምትመለከተው?
 • አይ ያው ሰሞኑን ከፍተኛ ሥጋት ውስጥ ነኝ፡፡
 • ምን ሆነህ?
 • ሰሞኑን አልሰሙም እንዴ?
 • ምኑን?
 • ከተማ ውስጥ ተለቀዋል እየተባለ ነው፡፡
 • ምኖች ናቸው የተለቀቁት?
 • የቀን ጅቦች!