Skip to main content
x
ክቡር ሚኒስትሩ በጣም ተናደው ከሚስታቸው ጋር እያወሩ ነው

ክቡር ሚኒስትሩ በጣም ተናደው ከሚስታቸው ጋር እያወሩ ነው

[ለክቡር ሚኒስትሩ በጣም ተናደው መኪናቸው ውስጥ ሲገቡ ሾፌራቸው እያነጋገራቸው ነው]

 • ምነው ክቡር ሚኒስትር?
 • ምነው?
 • ፊትዎ በጣም ጠቋቁሯል፡፡
 • ዛሬ እኮ ስንትና ስንት ስልክ ነው የተቀበልኩት፡፡
 • የምን ስልክ?
 • ሁሉም የሚደውልልኝ የቀን ጅብ ተባልኩ ምናምን ሲለኝ ግራ ገብቶኝ ነው፡፡
 • ለምን ግራ ገባዎት?
 • ይኼ ነገር እኔንም ይመለከተኛል ወይ ብዬ ነዋ?
 • እሱን እንኳን እኔ አላውቅም ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ምን የሚሉት ፈሊጥ ነው ግን ይኼ የቀን ጅብ?
 • እሱ እውነት ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እንዴት?
 • ክቡር ሚኒስትር ብዙ ጊዜ ቢሮ ስለሚውሉ አያውቁም ማለት ነው፡፡
 • ምኑን ነው የማላውቀው?
 • ከተማዋ እኮ በቀን ጅቦች ተወራለች፡፡
 • ምን ማለት ነው?
 • በየሄዱበት የቀን ጅብ ብቻ አይደለም እንዴ ያለው?
 • አልገባኝም?
 • ዝም ብለው ቀበሌ ሲሄዱ ቀጠን ቀጠን ያሉ የቀን ጅቦች ያገኛሉ፡፡
 • ምን ማለት ነው?
 • መታወቂያ ለማሳደስም ሆነ ለማውጣት ወይም የሆነ ማስረጃ ለማግኘት ኪስዎን ካልዳበሱ አገልግሎት ማግኘት አይችሉም፡፡
 • እሱን እንኳን አውቃለሁ፡፡
 • ስለዚህ እነዚህ የሕዝብ ስልኮች የቀን ጅብ ነው የሚባሉት፡፡
 • እነዚህን ነው እንዴ ሰው የቀን ጅቦች የሚለው?
 • እዚህ ብቻ አይቆምም፡፡
 • ሌላ ደግሞ ምን አለ?
 • ለምሳሌ ሚስትዎ ልትወልድ ብላ ሆስፒታል ሲሄዱ በቀዶ ጥገና እንጂ በምጥ መውለድ አትችልም የሚሉ አሉ፡፡
 • ይኼ እኮ የእነሱ ሙያ ነው፡፡
 • እንዳይሳሳቱ ክቡር ሚኒስትር በቀዶ ጥገና የምትወልደው ሴት በምጥ ከምትወልደው የምትከፍለው ገንዘብ ከእጥፍ በላይ ስለሆነ አውቀው ነው እንዲህ የሚሉት፡፡
 • ኧረ በሰው ሙያ አትግባ?
 • ክቡር ሚኒስትር ነገርኩዎ እነዚህ ሐኪሞችም የቀን ጅቦች ናቸው፡፡
 • ስማ ታዲያ ሐኪምና የቀበሌ ጉዳይ ፈጻሚን ነው ሰው የቀን ጅብ እያለ የሚያወራው?
 • ከአስኮ እስከ መርካቶ ያለው ነጋዴ ሕዝብ ላይ 500 ፐርሰንት አትርፎ አይደል እንዴ የሚሸጠው?
 • ይኼ እኮ የነፃ ገበያ መርህ ነው፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር ይኼ የቀን ጅብነት ነው፡፡
 • ወይ ጣጣ?
 • ሌላ ልጨምርልዎ ክቡር ሚኒስትር?
 • እሺ ቀጥል፡፡
 • የፍትሕ ሥርዓቱን መለከቱ ገንዘብዎ ነው ፍትሕ የሚያመጣልዎት፡፡
 • እ. . .
 • እንዲያውም የፍትሕ ሥርዓት ከሚባል የገንዘብ ሥርዓት ቢባል ይቀላል፡፡
 • እና በየዘርፉ ነው የቀን ጅቦች ያሉት?
 • ክቡር ሚኒስትር የቀን ጅብ ሃይማኖት፣ ብሔርና ዜግነት የለውም፡፡
 • ምን ማለት ነው?
 • የቀን ጅብ ማለት የማይገባውን ጥቅም ባልተገባ መንገድ ለማግኘት የሚጥር ሰው ማለት ነው፡፡
 • እ . . .
 • ክቡር ሚኒስትር የቀን ጅብ ነጭ ወይም ጥቁር፣ ወንድ ወይም ሴት፣ ትንሽ ወይም ትልቅ ሳይመርጥ ብቻ በየትኛውም ማንነት ሊኖር የሚችል ነው፡፡
 • አሁን ገባኝ፡፡
 • ለማንኛውም እርስዎም ከቀን ጅቦች ቢጠነቀቁ ጥሩ ነው፡፡
 • እነዚህ ጅቦች ግን ማታ ማታ ይወጣሉ?
 • ክቡር ሚኒስትር አይቀልዱ እንጂ?
 • ኧረ እኔ እየቀለድኩ አይደለም፡፡
 • ለነገሩ ሁኔታዎን ሳየው እርስዎም እየመሰሉኝ ነው፡፡
 • ምን?
 • የቀን ጅብ!

[ክቡር ሚኒስትሩ በጣም ተናደው ከሚስታቸው ጋር እያወሩ ነው]

 • ወይ ጉድ፡፡
 • ምን ሆንክ?
 • በተከበርኩበት አገር እንደዚህ ልዋረድ?
 • ምን ሆንክ?
 • ይኼው የራሴ ሾፌር የቀን ጅብ ብሎኝ አረፈ፡፡
 • መቼ?
 • አሁን በመኪና እየመጣን፡፡
 • ምን አለህ?
 • ሳይህ ሳይህ የቀን ጅብ ትመስላለህ አይለኝ መሰለሽ?
 • ከእሱ ጋር መቀላለድህ እኮ ነው እንዲህ ያስደፈረህ?
 • የተደፈርኩትማ በሌላ በመደፈሬ ነው፡፡
 • ማን ደፈረህ?
 • ስሚ እኔ ለዚህች አገር ሰለቸን ደከመኝ ሳልል ሠርቼ የተረፈኝ አንድ ነገር ነው፡፡
 • ምን?
 • በሽታና ስድብ፡፡
 • ምን እያልክ ነው?
 • ስኳርና ደሜን ተሸክሜ ባገለገልኩ ይኼው ስድብ ተጨመረልኝ፡፡
 • ሾፌር ሰደበኝ ብለህ ነው?
 • አለቃችንስ ቢሆኑ በአደባባይ አይደለም እንዴ የቀን ጅብ ያሉን?
 • አለቃችሁ እኮ ሥራችሁን አይቶ ነው የቀን ጅብ ያላችሁ፡፡
 • አሁን ግን በዛ፡፡
 • እንዴት ማለት?
 • የቀን ጅቡን ተቀብዬ ብቀመጥ ሌላ ተጨመረልኝ፡፡
 • ሌላ ምን?
 • ይኼው ነገ ደግሞ እሾህ ሊለኝ ነው፡፡
 • እሱስ ልክ ነህ፡፡
 • ከነገ ወዲያ ደግሞ ጠማማ ዛፍ ልባል ነው፡፡
 • ምን ይደረግ ታዲያ?
 • ሳምንት ደግሞ አይጥ ልባል ነው፡፡
 • ምነው እንደዚህ ከነከነህ ግን?
 • ስሚ ይችን አገር ባቀና ጠማማ ዛፍ ልባል?
 • እሱን እንኳን ተወው፡፡
 • ምነው?
 • አገሪቱን ስላጣመምካት እኮ ነው ጠማማ ዛፍ የተባልከው፡፡
 • እሺ ሌላው ቢቀር አገሪቱ ላይ እሾህ የሆኑባትን እነ ድህነት እየነቀልኩ እሾህ ልባል?
 • አሁን አንተ ድህነትን ነቀልክ ወይስ ተከልክ?
 • አንቺም ከእነሱ ጋር ተደመርሽ?
 • ሥራህን ታውቀዋለህ ብዬ ነው፡፡
 • እሺ ሁሉም ይቅርና እኔን ክብር ያለኝን ሰው አይጥ ብሎ ማዋረድ አይከብድም?
 • እሱንም እኮ ያገኘኸው በይቅርታ ነው፡፡
 • የምን ይቅርታ?
 • ከጅብነት ወደ አይጥነት የተደረገልህ በይቅርታ መርህ ነው፡፡
 • አንቺ ራሱ የምታወሪውን አታውቂም፡፡
 • ለማንኛውም እኔንም አንድ የአይጥና የድመት ፊልምን አስታወስከኝ፡፡
 • የምን ፊልም?
 • ፊልሙ ላይ አይጧ ልክ እንደ አንተ ሌባ፣ አጥፊ፣ ተንኮለኛና ሴረኛ ነች፡፡
 • ምንድነው የምታወራው?
 • ስለዚህ እኔም ከዚህ በኋላ አዲስ የቤት ስም አውጥቼልሃለሁ፡፡
 • ማን ልትይኝ?
 • ጄሪ!

[ክቡር ሚኒስትሩ ከደላላ ወዳጃቸው ጋር ቢሮ ተገናኝተው እያወሩ ነው]

 • ክቡር ሚኒስትር ሰሞኑን በጣም ብፈልግዎም ላገኝዎ ግን አልቻልኩም፡፡
 • ሰውዬ በዚህ ጊዜ ከአንተ ጋር መገናኘት የለብኝም፡፡
 • ለምን ክቡር ሚኒስትር?
 • ስማ እኔ ሌላ ጣጣ ውስጥ መግባት አልፈልግም፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር እኔ ምን ያህል በጥንቃቄ እንደምንቀሳቀስ መቼም ያውቃሉ?
 • ምን ፈልገህ ነው ቢሮ የመጣኸው?
 • አዲስ ለምንከፍተው ድርጅት የብቃት ማረጋገጫ ያስፈልጋል፡፡
 • የምን የብቃት ማረጋገጫ?
 • ድርጅቱን ለመክፈት ኃላፊው ሦስት ማስተርስ ሊኖረው ይገባል፡፡
 • ምን አሰብክ ታዲያ?
 • ያው በዚህ በአሥራ አምስት ቀናት ውስጥ ለእርስዎ ሦስተኛ ማስተርስ አመጣለሁ፡፡
 • ከየት ነው የምታመጣው?
 • ከሚመጣበት ነዋ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እ . . . 
 • ባለፈው ያስመጣሁልዎት የምን ነበር?
 • ትራንስፎርሜሽናል ሊደርሽፕ፡፡
 • የበፊቱ ኤምቢኤ ነበር አይደል?
 • በትክክል፡፡
 • ስለዚህ አሁን በሲስተማቲክ ማኔጅመንት አመጣልዎታለሁ፡፡
 • እንደዚያ የሚባል የትምህርት ዘርፍ አለ እንዴ?
 • ባይኖርም እንፈጥራለና፡፡
 • ካልክማ ይሁን፡፡
 • ባይሆን ቤት ትንሽ ዝግጅት አድርገው ጋዋን ለብሰው መነሳት አለብዎ፡፡
 • ድግስ ያስፈልጋል ብለህ ነው?
 • እሱማ ወሳኝ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ለምን?
 • አዩ አገሪቱ እንደዚህ እየጦዘች እርስዎ ሦስተኛ ማስተርስ መያዝዎ የዓላማ ፅናት እንዳለዎት ነው የሚያሳው፡፡
 • የአንተ አስተሳሰብ እኮ ይገርመኛል፡፡
 • ለሌላ ኃላፊነትም ሊያበቃዎ ይችላል፡፡
 • እሱስ ልክ ብለሃል፡፡
 • አሁን ወደ ዋናው ቁም ነገሮች እንሂድ፡፡
 • ምንድነው እሱ?
 • ሲመረቁ እኮ የሚያገኙት ሁለት ነገሮች ነው፡፡
 • ምንድን ናቸው፡፡
 • አንደኛው ዲግሪዎን ነው፡፡
 • እሺ፡፡
 • ሁለተኛው ደግሞ ፕሮጀክቱ ሲፈጸም ዕድገትዎን ያገኛሉ፡፡
 • የምን ዕድገት?
 • የታክስ ከፋይነትዎ ዕድገት ያመጣል፡፡
 • እኮ ምን ዓይነት ዕድገት?
 • ያው ከፍ ማለትዎ አይቀርማ፡፡
 • ወደ ምን?
 • ወደ ደረጃ ሀ!

[ክቡር ሚኒስትሩ አማካሪያቸውን ቢሯቸው ያስጠሩታል]

 • ያስጠራሁህ አንድ ጉዳይ ላይ እንድንወያይ ነው፡፡
 • የምን ጉዳይ ክቡር ሚኒስትር?
 • የሚኒስቴር መሥሪያ ቤታችን የሚሠራቸውን ሥራዎች ለምን ለሚዲያ ይፋ አናደርግም?
 • ባለፈው ከነገርናቸው ውጪ የሠራነው ሥራ የለም እኮ?
 • ቢሆንም ከሚዲያ ጋር ግንኙንት መፍጠሩ መልካም ነው፡፡
 • ያው በኋላ ላይ ሚዲያዎቹ ራሳቸው እንዳያፋጥጡን ብዬ ነው፡፡
 • ልማታዊ ሚዲያዎቹን ጥራልኝ፡፡
 • የትኞቹን ሚዲያዎች?
 • ለነገሩ አሁን ልማታዊ ሚዲያ የት አለ?
 • እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
 • አንዴ ሠልፍ ነው፣ ሌላ ጊዜ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ነው፣ ወይም ደግሞ ግጭት ነው የሚዘግቡት፡፡
 • ታዲያ ይኼን መዘገብ ምን ችግር አለው?
 • አገሪቱ ውስጥ እኮ ከዳር እስከ ዳር ልማት ነው እየተካሄደ ያለው፡፡
 • ኧረ ይተው ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ለምንድነው የምተወው?
 • ስለእንደዚያ ዓይነት ልማት ሰው መስማት አይፈልግም፡፡
 • ታዲያ መስማት የሚፈልገው ስለደም ልገሳና ሠልፍ ነው?
 • ምን ሆኑ ክቡር ሚኒስትር?
 • ምን ሆንኩ?
 • ሰው መስማት የሚፈልገው ስለአንድነት፣ ስለፍቅር፣ ስለይቅርታና ስለመደመር ነው፡፡
 • የምን ፍቅር ነው በየቦታው ግጭት አይደል እንዴ ያለው?
 • ክቡር ሚኒስትር አገሪቱ ለመፍረስ አፋፍ ላይ ደርሳ ነው የተረፈችው፡፡
 • እስኪ ተወኝ፡፡
 • ለማንኛውም ጊዜው የፍቅር፣ የአንድነት፣ የይቅርታና የመደመር ነው፡፡
 • ኦ ኦ . . . ሰውዬ?
 • እኔ የምመክርዎ እንዲደመሩ ነው፡፡
 • የምን መደመር ነው?
 • የማይደመሩ ከሆነ የሚጠብቅዎ ምን እንደሆነ ያውቁታል፡፡
 • ምንድነው የሚጠብቀኝ?
 • መቀነስ!