Skip to main content
x
ቋንቋን እንደ አንድነት ድልድይ

ቋንቋን እንደ አንድነት ድልድይ

በሥልጣኔ ተምሳሌትነቷ በዓለም የታሪክ መዝገብ ላይ ስሟ የተጻፈው ጥንታዊቷ ባቢሎን በአስተዳደር ሥርዓቷ በሀሙራቢ ሕግ በይበልጥ ትታወቃለች፡፡ ሌሎችም ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም ማኅበራዊና ባህላዊ እሴቶቿ ከታሪክ መዛግብት እንዳትጠፋ ያደረጓት የጥንታዊ ሥልጣኔ አሻራ መገኛም ነች፡፡ ከዚህ ባለፈ ግን በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ውስጥም የምትጠቀስበትና ጥንታዊነቷን በይበልጥ ከሚያጎሉ ነገሮች መካከል የባቢሎን ግንብ አንዱ ነው፡፡

     በዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ውስጥ በሰው ልጆች መካከል ለተፈጠረው የቋንቋ ተለያይነት ምክንያት ሆና ትቀርባለች፡፡ እንደ ማስተማሪያና መቀጣጫ ሆኖ የሚቀርበው የባቢሎን ግንብ ታሪክ ውስጥ ባቢሎናውያን ከቀሪው ዓለም የተለየ መሠረቱ መሬት ሠገነቱ ደግሞ መንግሥተ ሰማያት ድረስ የተዘረጋ ግንብ (ከተማ) ለመገንባት ሲሉ የደረሰባቸውን ያሳያል፡፡

     ምድራዊውን ሕይወት ከሰማያዊው የሚያገናኝ ድልድይ ይሆን ዘንድ የተጀመረው ግንባታ በከፊል ሳይጠናቀቅ የፈጣሪ ቁጣ ግንበኞቹ ተነጋግረው እንዳይግባቡ፣ የተለያዩ ቋንቋዎችን እንዲናገሩ ሆነ፡፡ በዚህም የጀመሩትን ማገባደድ ተስኗቸው በምድር ዙሪያ ተበታትነው ለመኖር መዳረጋቸውን በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ውስጥ ይነበባል፡፡

     ይህ ሃይማኖታዊ ታሪክ በዓለም ላይ አንድ ዓይነት ቋንቋ እንዳይነገር ባቢሎንን ምክንያት ሲያደርግ በሌላ በኩል ከርሱ በተቃራኒው ቋንቋ ከመግባቢያ መሣሪያነት ባለፈ አንድነት፣ ተለያይነት መሆኑንም ያሳያል፡፡ ቋንቋ አብሮነት የሚጠናከርበት፣ የማኅበረሰብ መሠረት፣ የሰውነት ባህሪ መገለጫ ሌላም ብዙ ነገር ማለት ነው፡፡ ቋንቋ ሥልታዊ ምት ያለው ድምፅ፣ የተጠና ምልክት፣ እንቅስቃሴና ድርጊትም ነው፡፡ በደመነፍስ የሚያውቁት ተፈጥሯዊ ፀጋ ሳይሆን ምናልበት ትምህርት ቤት መግባት ሳያስፈልግ ማንኛውም ሰው መማሩን ሳያውቀው ከውልደቱ ጀምሮ የሚማረው ክህሎት ነው፡፡

     ሰምተው የማያውቁትን ቃል፣ ልሳንና የአነጋገር ዘዬ ለመጀመርያ ጊዜ ሲሰሙ ከድምፅ እርግብግቢት መውጣትና መውረድ ባሻገር ትርጉም ያለው መልዕክት መቀበል የማይችሉትን ያህል ቋንቋ ውስብስብ ባህሪ አለው፡፡ አንድ ሕፃን ሲወለድ ጀምሮ በደመነፍስ የሚያውቃቸው ጡት መጥባት፣ መተኛትና መንቃት የመሳሰሉት በተፈጥሮው እንደሚያውቃቸው ድርጊቶች ሳይሆን ቋንቋ መልዕክት የመቀበልና የመመለስ ክህሎት የሚጠይቅ በጊዜ ሒደት የሚዳብር ሰውኛ ነገር ነው፡፡

     አንዳንድ ምሁራን በቋንቋ መግባባት የሰውነት መገለጫና ለሰው ልጆች ብቻ የተሰጠ ልዩ ችሎታ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ በቋንቋ ለመግባባት ግን ሰው ብቻ መሆን በቂ አይደለም፡፡ የአንድ ባህል አካል መሆንና አብሮ መኖር ግድ ይላል፡፡ እንደ ታርዛን በዱር የሚያድጉ ሰው ስለሆኑ ብቻ በቋንቋ መግባባት እንደማይችሉ ከገፀ ባህሪው መረዳት ይቻላል፡፡ በሰዎች ቋንቋ ለመግባባት ሰው መሆን አንዱ መሥፈርት እንጂ መጀመርያም መጨረሻም አይሆንም፡፡

     በዓለም ላይ ከሚነገሩት 7,000 የሚሆኑ ቋንቋዎች መካከል አንዱን ለመናገር የአንድ ማኅበረሰብ አካል ሆኖ መፈጠር ግድ ነው፡፡ እነዚህ በምድር የሚነገሩ ቋንቋዎች በድምፅ አወጣጥና አወራረድ፣ ዘዬና ቅኝታቸው የተለያየ መገለጫ፣ መደብና መለኪያ አላቸው፡፡ ኩሽቲክ፣ ኦሞቲክ፣ ሴሚቲክና ናይሎቲክ በሚል በአራት የቋንቋ ቤተሰቦች የተከፈሉ ናቸው፡፡

ጥናቶች እንደሚያሳዩት፣ ጨቅላ ሕፃናት በየቀኑ የሚሰሟቸውን ንግግሮች ቀድቶ የሚያስቀመጥ የአዕምሮ ክፍል አላቸው፡፡ ይህ የአዕምሮ ክፍል ከጊዜ በኋላ የሚጠፋ ሲሆን፣ ቀድቶ የሚያስቀምጣቸውን ንግግሮች ድምጾች በሕፃኑ ጆሮ ደጋግሞ በማጫወት የቋንቋውን ተፈጥሮና ባህሪ እንዲላመዱት ያግዛቸዋል፡፡ በዚህና በዙሪያቸው ባሉ ሰዎች ዕርዳታ በአካባቢያቸው ከሚነገር ቋንቋ ጋር ሕፃናት ይተዋወቃሉ፡፡

በተወለዱ ከዘጠኝ እስከ አሥራ ሁለት ወራት ጊዜ ውስጥም የመጀመርያ ቃላቸውን ይናገራሉ፡፡ የአንድ ዓመት ሕፃን እስከ አምስት የሚደርሱ የቃላት ስብስቦች ሊያውቅ ይችላል፡፡ አንዳንዶቹም እስከ 30 የሚደርሱ ቃላቶችን የሚያውቁባቸው አጋጣሚዎች አሉ፡፡ ሁለት ዓመት ሲሞላቸው በአማካይ እስከ 150 ቃላቶችን ይጠራሉ፡፡ አምስት ዓመት እስኪሞላቸው የቋንቋቸውን ቅኝትና የሰዋሰው ሥርዓት ጥንቅቅ አድርገው ያውቃሉ፡፡ ስድስት ዓመት በሞላቸው ሰዓት የሚያውቋቸው የቃላት ስብስቦች ቁጥር ወደ 14,000 ከፍ ይላል፡፡

በዚህ መልኩ ከምንም ተነስተው ብዙ ነገር ማለት የሚያስችላቸውን የአፍ መፍቻ ቋንቋ ሲማሩ ቋንቋው ከመግባቢያ መሣሪያነት ባለፈ የማንነታቸው መገለጫ ጭምር ይሆናል፡፡ ራሳቸውንም ሆነ ሐሳባቸውን በነፃነት ለመግለጽ የሚያመቻቸው ይኸው አፍ መፍቻ ቋንቋቸው ይሆናል፡፡ ሊደብቁት የማይችሉት የማንነታቸው አካል ሆኖ እንደ ጥላ ይከተላቸዋል፡፡ ሁለተኛ ቋንቋቸውን ሲናገሩ ከአፍ መፍቻ ተፅዕኖ ሳይላቀቁ ነው፡፡

በአራት የቋንቋ ቤተሰቦች ሥር የሚመደቡት 7,000 የሚሆኑ የዓለም ቋንቋዎች መካከል ማንደሪን፣ እንግሊዝኛ፣ ስፓኒሽ፣ ህንደኛ፣ ራሽያኛ፣ ዓረብኛ፣ ፖርቱጊዝ፣ ፈረንሣይኛና የጀርመንኛ ቋንቋዎች በስፋት እንደሚነገሩ ቢቢሲ በቅርቡ ያወጣው ሪፖርት ያሳያል፡፡ ካሉት 7,000 ቋንቋዎች መካከል 90 በመቶ የሚሆነውን የሚናገሩት ከዓለም ሕዝቦች መካከል ጥቂት የሚባሉት ናቸው፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ የበርካታ ብሔረሰቦች መኖሪያ በሆኑ አገሮች የሚነገሩ ቋንቋዎች ከዚሁ ምድብ ሊጠቃለሉ ይችላሉ፡፡

ከ80 በላይ ብሔረሰቦች እንደሚኖሩባት በሚነገርላት ኢትዮጵያ የቋንቋ ልዩነት ከክልል ክልል ብቻም ሳይሆን አንዳንዴ ከቦታ ቦታ የሚለያይባቸው አጋጣሚዎች አሉ፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች ከቦታ ቦታ የሚደረጉ ፍልሰቶችም የአንዱ ማኅበረሰብ አካል ከአፍ መፍቻ ቋንቋው በተጨማሪ ከሌላ ቋንቋ ጋር እንዲተዋወቅ ሁለተኛ ቋንቋ እንዲናገር መንገዱን ይጠርጋል፡፡ መሰል አጋጣሚዎች ታዲያ አንድ ቋንቋ እንዲወለድ፣ እንዲያድግና እንዲያረጅ ምክንያት ናቸው፡፡ በሌላ በኩልም ጎን ለጎን እንዲያድጉ በተወሰነ መልኩም ቢሆን እንዲወራረሱ የራሱ አስተዋጽኦ አለው፡፡ የቋንቋ መወራረስ ወይም አንዱ ከሌላው የሚጋራው ቃላት፣ ስሞች ቃለ ምሳሌዎች በስፋት ከሚታይባቸው ቋንቋዎች መካከል አማርኛና ኦሮምኛን ማንሳት ይቻላል፡፡

ይህንንም በአማርኛና በኦሮምኛ ቋንቋ መካከል ያለውን የውርርስ መነሻና ውጤት በወለጋና ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ በጋራ የተዘጋጀው ጥናታዊ ጽሑፍ በሁለቱ ሕዝቦች መካከል ያለውን የባህል ትስስርና የቋንቋ መወራረስ አጉልቶ ያሳያል፡፡ ጥናቱ የሁለቱን ሕዝቦች ግንኙነት በዓባይ አጎራባች አካባቢዎች ማለትም በጎጃምና በወለጋ ነዋሪዎች ላይ የተመሠረተና የግንኙነቱን መነሻና ውጤት የሚያሳይ ነው፡፡

በጥናቱ መሠረት፣ ከ16ኛው ክፍለ ዘመን እስከ 19ኛው አጋማሽ ድረስ ከኦሮሞ መስፋፋት ጋር ተያይዞ የኦሮሞ ተወላጆች ዓባይን ተሻግረው ይስፍሩ ነበር፡፡ ይህም የኦሮሞ ሕዝብ ባህልና ቋንቋ ከአማራው እንዲተዋወቅ መነሻ ምክንያት ሆነ፡፡ ከ19ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ወዲህ ደግሞ የአማራ ሕዝብ በተራው ወደ ኦሮሞ ግዛት በመሻገር በኦሮሞ ቋንቋና ሃይማኖት ላይ ተፅዕኖ መፍጠር ችሏል፡፡ በእነዚህ ሁለት ዘመናት ውስጥ ሁለቱ ሕዝቦች ቋንቋን ጨምሮ የአስተዳደር ሥርዓት፣ ባህል የመወራረስ፣ በትዳር የመጣመር ነገር ነበራቸው፡፡

በወለጋ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ አስተማሪው አቶ ደሳለኝ ቶሌራ እንደሚሉት፣ ከሆሮ ጉድሩ ተነስቶ ወደ ጎጃም የተሻገረው አምሩ የተባለ ጎሳ ከጎጃም ተዋልዷል፡፡ የሁለቱ የደም ቅጂ የሆነው ራስ ኃይሉ የጎጃምን አስተዳደር መመሥረትም ቻለ፡፡ ከአማራ ወገን የነበሩ ወታደሮችም ዓባይን ተሻግረው በኦሮሞ ግዛት ውስጥ እንዲቆዩ (ካምፕ እንዲያደርጉ) ይደረግ በነበረበት ወቅት አብዛኞቹ ወታደሮች ከኦሮሞ ሴቶች ተጋብተው ወልደዋል፡፡

በዚህ መልኩ በደም ሲተሳሰሩ በጉዲፈቻና በአበልጅ ሥርዓት ደግሞ እንደ ሠርገኛ ጤፍ ሆነው እንዲቀላቀሉ ሆኗል፡፡ ይህ ቋንቋውም በዚሁ መጠን እንዲወራረስ ሕዝቦችም ከአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ውጪ ሁለተኛ ቋንቋ እንዲማሩ ዕድል ከፍቷል፡፡ ‹‹የኦርቶዶክስ እምነት ወደ ወለጋ መስፋፋት ጋር ተያይዞ የሚካኤልና የገብርኤል ማኅበር ይወጣል፡፡ ኦሮሞም ማኅበር የሚለውን የአማርኛ ቃል በመጋራት ማበራ እያሉ ይደግሳሉ፤›› ብለዋል አቶ ደሳለኝ፡፡

ከአቶ ደሳለኝ ምሳሌ ሃይማኖታዊ ይዘት ያለውን ድግስ ኦሮሞ  ባህሉ አድርጎ ሲወስድ ቃሉንም በሚያመቸው ቅላፄ አድርጎ ማበራ ሲል ቋንቋ መጋራቱን ያሳያል፡፡ መሠረቱ ከኦሮምኛ የሆነው ጉዲፈቻም ሙሉ ቃሉን እንዲሁም ባህሉ የአማርኛ ቋንቋና የሕዝቡ ባህል አካል ሆኖ ዛሬም ድረስ ጥቅም ላይ ይውላል፡፡ መንደር የሚለውን የአማርኛ ቃል በኦሮምኛ ብዙም ለውጥ ሳይደረግበት መንደራ ይሉታል፡፡ ገዳምንም እንደዚሁ ገዳሚ፣ ሠፈርን ሠፈሪ፣ ወራ ኢሉን ወረኢሉ በሚል ሁለቱም ቋንቋዎች የቦታ ስሞችን ሳይቀር ተጋርተዋል፡፡

የማዕረግ መጠሪያዎችንም እንደዚሁ ተወራርሰው ይጠቀማሉ፡፡ ባላባትን ባላባት፣ ቀኝ አዝማችን ቀኝ አዝማቻ፣ ንጉሥን ንጉሣ፣ ግራዝማችን ግራዝማቻ፣ ሚዜን ሚንጄ፣ አበልጅን አበልጂ ይላሉ፡፡ ማኅበራዊ ኑሮና ትስስርን የሚያሳዩ ስብሰባዎችን ለምሳሌ ሰንበትን ሰንበቴ፣ ማኅበርን ማበራ፣ ደቦንም እንዲሁ ብዙም የድምፅ ለውጥ ሳይደረግበት ኦሮምኛው ከአማርኛና አማርኛው ከኦሮምኛ ቋንቋ ጋር የተዳቀሉ፣ የተጋሩ ቃላት በመዝገበ ቃላታቸው ደምረው ዛሬ ድረስ ይጠቀማሉ፡፡

እንደ ጥናቱ የአንድነትና የአብሮነት ሲያልፍም የብዝኃነት ቅመም ሆኖ የሚያገለግለው ቋንቋ አንዳንዴ የተቃርኖ፣ አንዳንዴ ደግሞ የሰላም መሠረት ሆኖ ይመጣል፡፡ እንደ ሰው በማኅበረሰብ ውስጥ ተወልዶ ያድጋል፣ ይሞታል፡፡ አንዳንዴ ከማኅበረሰብ ማኅበረሰብ መለያ ግድግዳ ሲሆን፣ ግጭትን ሲያጭር እንደ ኦሮሞና አማራ ሕዝብ መካከል ደግሞ የአንድነት ድልድይ የሚዘረጉ የታሪክ አጋጣሚ ሆኖ በጥናቱ ብቅ ብሏል፡፡ ቋንቋ ፖለቲካ፣ ባህል፣ ኢኮኖሚም ነው፡፡ ባሰቡለት ዓላማ ሁሉ ጠምዝዘው መሣሪያ ሊያደርጉት የሚችሉት የሰላምና የግጭት መነሻ ሊሆን የሚችል ነገር ነው፡፡