Skip to main content
x
‹‹የማረም ብቃት ያላቸው ኦፊሰሮች የሉንም›› ፓስተር ዳንኤል ገብረ ሥላሴ፣ የጀስትስ ፎር ኦል ፒኤፍ ኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት

‹‹የማረም ብቃት ያላቸው ኦፊሰሮች የሉንም›› ፓስተር ዳንኤል ገብረ ሥላሴ፣ የጀስትስ ፎር ኦል ፒኤፍ ኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት

ጀስትስ ፎር ኦል የተቋቋመው ከ26 ዓመታት በፊት በ1984 ዓ.ም. ነው፡፡ በኢትዮጵያ ይከሰቱ የነበሩና እየተከሰቱ ያሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ማሻሻል፣ የሕግ የበላይነት የተረጋገጠበትን አገር የመፍጠር ዓላማ ያለው ድርጅት ነው፡፡ ጀስትስ ፎር ኦልን የመሠረቱት ፓስተር ዳንኤልን ጨምሮ አምስት የሕግ ባለሙያዎች የነበሩ ሰዎች ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት የአባላቱ ቁጥር ወደ 150 ደርሷል፡፡ አባላቶቹ የሕግ፣ የኢኮኖሚክስ፣ የሶሾሎጂ ባለሙያዎችን ያካተተ እንዲሁም በሴቶችና ሕፃናት ላይ የሚሠሩ፣ በግጭት አፈታት፣ የፍትሕ ሥርዓቱን ተዋናዮች የሚያሠለጥኑ ባለሙያዎችን ያቀፈ ነው፡፡ ማረሚያ ቤቶች ደረጃቸውን ጠብቀው እንዲሠሩም የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን የሚያደርግ ሲሆን፣ አጠቃላይ ተግባሩንና በማረሚያ ቤቶች አካባቢ የሚከሰቱ የመብት ጥሰት ጉዳዮችን በተመለከተ ሻሂዳ ሁሴን ፓስተር ዳንኤል ገብረሥላሴን አነጋግራቸዋለች፡፡

ሪፖርተር፡- ጀስትስ ፎር ኦል መንግሥታዊ ያልሆነ ተቋም መሆኑ ይታወቃል፡፡  ተግባራቶቹን ለማከናወን የሚያስፈልጉትን በጀቶች ወይም ገቢ እንዴት ነው የሚያገኘው?

ፓስተር ዳንኤል፡- ብዙ ዓመት ስለቆየን ብዙ ሥራዎች አሉብን፡፡ ጥሩ ውጤት ማስመዝገብ ስንችል መንግሥትም ሌሎች ለጋሽ ድርጅቶችም ትኩረት ይሰጡናል፡፡ እኛ በእዚህ ረገድ ጥሩ ድግግሞሽ ነው ያለን፡፡ ጀስትስ ፎር ኦል መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ነው፡፡ ነገር ግን በኤንጂኦ ሕግ አንቀጽ 3 ንዑስ አንቀጽ ለ ሥር ከመንግሥት ጋር የሁለትዮሽ ግንኙነት ተፈራርመው የሚሠሩ ድርጅቶችን ሕግ ተፅዕኖ አያደርግባቸውም ይላል፡፡ ስለዚህ ከየትኛውም ዓለም አቀፍ ድርጅት ገቢ ማሰባሰብ እንችላለን፡፡ ለምንቀርፃቸው ፕሮጀክቶች የሚያስፈልገውን ገንዘብ አናጣም፡፡ እኛ ብቻ አይደለንም የተወሰኑ ድርጅቶችም እንዲህ ከመንግሥት ጋር በስምምነት ይሠራሉ፡፡

ሪፖርተር፡- ጀስትስ ፎር ኦል በዋናነት ትኩረቱን አድርጎ የሚሠራው በምን ጉዳዮች ላይ ነው?

ፓስተር ዳንኤል፡- የሰብዓዊ መብቶችን ማስጠበቅና የሕግ የበላይነት የተከበረባቸውን አገር መፍጠር ዋና ዓላማው ነው፡፡ የሰው ልጅ ክቡር ነው፡፡ በክቡርነቱ በሰብዓዊ መብቱ ላይ ጥሰት ሊደረግ አይገባም፡፡ ሰብዓዊ መብት ሲከበር የአገር ሉአላዊነት የሕዝብ ሰብዓዊ መብት ይከበራል፣ የሕግ የበላይነት የተረጋገጠበት በሕግ የሚመራ አገር ለመፍጠር ያስችላል፡፡

ሪፖርተር፡- ይንን የተቋቋማችሁለትን ዓላማ ለማሳካት ምን ምን ዓይነት ሥራዎችን ትሠራላችሁ?

ፓስተር ዳንኤል፡- አራት ዓይነት ሥራዎችን እንሠራለን፡፡ የመጀመርያው የአቅም ግንባታ ሥራ ነው፡፡ የመጨረሻው የሥልጣን ባለቤት ለሆነው ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ለሕግ ተርጓሚው አካል፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሚመራውን ካቢኔ ወይም ለሕግ አስፈጻሚውን አካል እንደየአስፈላጊነቱ የተለያዩ ሥልጠናዎችን እንሰጣለን፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ የፖሊሲ ዳያሎግና የአድቮኬሲ ሥራ ነው፡፡ በእዚህ ረገድ ምርጥ የሚባሉ ተሞክሮዎችን ከውጭ አገር በመውሰድ ኢትዮጵያ የምታወጣቸው ሕጎች፣ የፈረመቻቸውን ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎችን ጨምሮ ስታንዳርድ የሆነ የፖሊሲ አቅጣጫ እንዲኖራት ሥልጠና እንሰጣለን፡፡ አንዱ ክልል ጥሩ ሲሠራ እሱን ቤንች ማርክ በማድረግ ክልሎች እርስ በርስ የሚማማሩበት አሠራርን መፍጠርም ሌላው ነው፡፡ አራተኛው በአገሪቱ ግጭት የሚከሰትባቸውን ቦታዎች በጥናት እየለየን የተረጋጋች አገር ለመፍጠር የምንሠራው ሥራ ነው፡፡ ሰላምና መረጋጋት ሲኖር ነው ሕግ የሚፈጸመው፡፡ ሰላም ከሌለ ሕግ ሊፈጸም አይችልም፡፡ ስለዚህ በግጭት አፈታት የሠለጠኑ ባለሙያዎች ስላሉን መረጋጋት እንዲመጣ የሙያ እገዛ እናደርጋለን፡፡

ሪፖርተር፡- በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ከባባድ ግጭቶች ተከስቷል እየተከሰተም ይገኛል፡፡ በእዚህ ላይ የግጭት አፈታት ባለሙያዎቻችሁን ተጠቅማችሁ ምን ማድረግ ችላችኋል?

ፓስተር ዳንኤል፡- አሁን ያለው ሁኔታ የ27 ዓመቱ ነፀብራቅ ነው፡፡ የክልሎች አመሠራረት በብሔር ላይ ነው፡፡ ሁሉም ሕገ መንግሥቱን ሲተገብር የቆየው በብሔሩ ነው፡፡ የብሔር እኩልነት መምጣቱ ጥሩ ነው፡፡ ነገር ግን ይህ መስመሩን ስቶ ወጥቶ የብሔር የበላይነት በኢትዮጵያዊነት ላይ ጎልቶ እንዲወጣ አደረገ፡፡ ኢትዮጵያዊነት በብሔር ተውጦ ነበር የቆየው፡፡ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የኢትዮጵያዊነትን ካርድ ነው የመዘዙት፡፡ ኢትዮጵያዊ ሲባል የሁሉንም ልብ ነካ፡፡ በአገር ውስጥ ከአገር ውጭ ያሉም ሁሉ እኩል እንዲሰማቸው አደረገ፡፡ ነገር ግን ከ27 ዓመታት ውስጥ የተከሰተው ችግር በአንድ ጀንበር የሚፈታ አይደለም፡፡ 27 ዓመት የጠፋውን ለማስተካከል 27 ዓመታት መሥራት ግድ ይላል፡፡ የኛ ድርጅት ባለው አቅም እንደ ኤንጂኦ የግጭቶችን ዋና መነሻ ጥናት እናደርጋለን፡፡ ከዚያም ቦታው ላይ ሄደን አግባብ ያለው ሥልጠና እንሰጣለን፡፡ ይህ ግን በኛ አቅም ብቻ የሚሠራ ሳይሆን 100 ሚሊዮን የኢትዮጵያ ሕዝብ ሊረባረብበት የሚገባ ነው፡፡ ባለን አቅም ግን የቻልነውን እየሠራን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ከሚፈጠርባቸው አገሮች መካከል ኢትዮጵያ አንዷ ስለመሆኗ ይነገራል፡፡ በዚህ ይስማማሉ?

ፓስተር ዳንኤል፡- ኢትዮጵያ በሰብዓዊ መብት ጥሰት የታወቀች አገር ነች የሚለውን ሙሉ ለሙሉ አልወስድም፡፡ ሰብዓዊ መብት ይጣሳልን? ከሆነ ግን አዎ ይጣሳል፡፡ ለእዚህም የመጣንበት ታሪካችን ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡ ከዘውዳዊ አገዛዝ ቀጥታ ወደ አምባገነኑ የደርግ ሥርዓት ነው የመጣነው፡፡ እዚያ ደግሞ የብሔረሰቦችን እኩልነት እናመጣለን ብለን የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመያዝ ጥሩ ሕገ መንግሥት ቀረፅን፡፡ በዚያ ሒደት ውስጥ የሰብዓዊ መብት ረግጣ የለም ማለት አይቻልም፡፡ ይኼንን ለመቅረፍ ግን ብዙ ሥራዎች እየተሠሩ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የሰብዓዊ መብት ረገጣ ያለባቸው ቦታዎች በቁጥር ጥቂት ናቸው፡፡ የጎላ ችግር የሚታይባቸው ቦታዎች ቢበዛ አምስት ቢሆኑ ነው፡፡ የአስተሳሰብ ችግር እንዲሁም አመራሩ ለሰብዓዊ መብት ጥበቃ የሚሰጠው ትኩረት አነስተኛ በመሆኑ ታች ላይ ያሉ የአመራሩ አካላት የመብት ጥሰት ሲያደርሱ ታይቷል፡፡ ነገር ግን ሁሉም የአመራር አካላት የሰብዓዊ መብት ጥሰት ያደርሳሉ ማለት አይደለም፡፡ የተሻሻሉ ነገሮችም አሉ፡፡ ለምሳሌ ማረሚያ ቤቶችን ብንመለከት ማረሚያ ቤት እስታንዳርድ አልነበረውም ነበር፡፡ የቅርብ ጊዜ ታሪካችን እንደ ሚያሳየው ሰዎች በዋስ ቤት ነበር የሚታሰሩት፡፡ የ40 እና 50 ዓመት ታሪካችንን ብናይ ሰዎች በሀብታም ቤትም ይታሰሩ ነበር፡፡ ከእዚያ በኋላ ደግሞ ደርግ ቢመጣም ምንም ዓይነት የመሠረት ልማት ለውጥ ሳይኖር በትንንሽ ቤቶች ውስጥ የመታሰር ነገር በእዚያው ቀጠለ፡፡ ለመጀመርያ ጊዜ ደረጃውን የጠበቀ ማረሚያ ቤት የተገነባው በጀስትስ ፎር ኦል ነው፡፡ ይህ ደረጃውን የጠበቀ ማረሚያ ቤት በአዳማ የተገነባው ከ13 ዓመታት በፊት ነበር፡፡ ይኼንን ለክልሎች በማሳየት ተመሳሳይ ማረሚያ ቤት መቐለ፣ ሐዋሳ፣ ባህር ዳር፣ ጎንደር እንዲሁም በኦሮሚያ ሰባት በሚሆኑ አካባቢዎች ላይ እንዲገነባ ሆኗል፡፡ በማረሚያ ቤቶች የመጣው ለውጥ በአገሪቱ የሰብዓዊ መብት አጠባበቅም የመጣ ለውጥ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ደረጃውን የጠበቀ ማረሚያ ቤት በትንሹ ምን ምን ነገሮችን ያካተተ እንዲሆን ይጠበቃል?

ፓስተር ዳንኤል፡- ጣሪያው ከወለሉ ያለው ርዝመት፣ መስኮት፣ ሻወር ቤት መኖሩ ይታያል፡፡ የአልጋው ርዝመትና ስፋትም ይታያል፡፡ ቦርዲንግ እስኩል ሊመስል ይችላል፡፡ ነገር ግን የሰው ልጅ ስጋውን ሳይሆን አስተሳሰቡን ነው የምትቀጪው፡፡ በእዚህ መሠረት የተዘጋጁ ብዙ ሕጎች ወጥተው ጥሩ ተሞክሮዎችም አሉ፡፡ ነገር ግን ማስፈጸም ነው ያቃተን፡፡

ሪፖርተር፡- የሰብዓዊ መብት ጥሰት ገኖ የወጣባቸው ቦታዎች የትኞቹ ናቸው?

ፓስተር ዳንኤል፡- የምርመራ ቦታዎች ናቸው፡፡ በሚዲያ ወጥቶ የምናየውም ይህንኑ ነው፡፡ በከፊል ደግሞ በፌዴራል ደረጃ በሚገኙ ማረሚያ ቤቶች ነው፡፡ ክልል ላይ ብንሄድ ግን ከእዚህ የተለየ ነገር እንደምናገኝ አምናለው፡፡ ያለው ጥሰት በተለያዩ ክፍሎች እንጂ በአገር አቀፍ ደረጃ አይደለም፡፡ እንደ አጠቃላይ ግን የሰብዓዊ መብት አጠባበቅ በኢትዮጵያ ተሻሽሏልም የመብት ረገጣ አሁንም ድረስ አለ፡፡ በማደግ ላይ ያለን በመሆኑ ወደፊት ሁኔታዎች እየተቀየሩ እንደሚሄዱ አምናለሁ፡፡ ከ27 ዓመታት በፊት ያለውን ነገር ብናይ እየተለወጥን መምጣታችንን በግልጽ ማወቅ ይቻላል፡፡ ያኔ በሰብዓዊ መብት አጠባበቅ ረገድ ታች ነበርን፡፡ አሁን ትንሽም ቢሆን ተሻሽለናል፡፡ ነገር ግን የዓለም የዴሞክራሲ ባህል፣ የሕግ የበላይነት የሚረጋገጥበትን ጥግ፣ ለሰብዓዊ መብት ጥበቃ ረገድ ጫፍ ላይ የደረሱ አገሮች ጋር የምናወዳድረው ከሆነ ልክ ነው የእኛ ትልቅ ችግር አለበት፡፡

ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ማረሚያ ቤቶች ምን ያህል ደረጃቸውን የጠበቁ ናቸው?

ፓስተር ዳንኤል፡- የአዲስ አበባውን ፌዴራል ማረሚያ ቤት ብንወስድ አዲስ ማረሚያ ቤት እያሠራ ነው ያለው፡፡ እዚያው ውስጥ ደግሞ የሴት ታራሚዎች መኖሪያን እኛ አሠርተናል፡፡ መንግሥትም ትልቅ በጀት መድቦ ሌላ ማረሚያ ቤት እየሠራ እንደሆነ አውቃለሁ፡፡ ነገር ግን ግንባታው ተጠናቆ አዲሱ ቦታ እስኪሄዱ ድረስ በቆርቆሮ ቤቶች ውስጥ የሚኖሩ ታራሚዎች በእዚህ ክረምት በጣም ይሰቃያሉ፡፡ በተለይም ደግሞ በቃሊቲ ማረሚያ የመተፋፈግ፣ በቂ ብርሃን የማግኘት፣ የፍራሽና የመታጠቢያ ቤት እጥረት ሊኖር ይችላል፡፡ በክረምት ዝናብ አለ ቅዝቃዜው ከባድ ይሆናል፡፡ በእዚህ ቦታ ላይ ማረም እጅግ በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ በገጠር የሚገኙ ማረሚያ ቤቶችም እንደዚህ ዓይነት ችግር አለባቸው፡፡ የአካባቢውን ማኅበረሰብ እያስተባበሩ፣ እንጨት፣ ቆርቆሮና ሚስማር እያስገዙ እየሠሩ ብዙዎቹ ተቀይረዋል፡፡ ነገር ግን መንግሥት በቂ ትኩረት ሰጥቶ ሊሠራበት የሚገባ አሳሳቢ ጉዳይ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ካለው የመሠረተ ልማት ችግር በተጨማሪ ታራሚዎች ከፍተኛ የመብት ጥሰት እንደ ሚደርስባቸው፣ ኢሰብዓዊ የሆኑ የድብደባ የአካል ጉዳት እንደ ሚደርስባቸው በተለያዩ ሚዲያዎችም ከሰሞኑ በብዛት እየተዘገበ ይገኛል፡፡ በዚህ ላይ ምን ይላሉ?

ፓስተር ዳንኤል፡- ታራሚዎች ወንጀለኛ ከሚያደርጋቸው ባህሪ እንዴት ታርመው መውጣት ይችላሉ የሚለውን ጉዳይ በተመለከተ የተዘጋጀ ፖሊሲና ጋይድ ላይን አለ፡፡ በማረሚያ ቤት ውስጥ ቁጭ ብለው እንዳይውሉ የተለያዩ ሙያዎችን ተምረው እንዲሠሩ ይደረጋል፡፡ ታራሚውን የሚከታተል የዲሲፕሊን ኮሚቴም አለ፡፡ ይኼንን ሥራ አልሠራም በሚል ታራሚዎች ከዲሲፕሊን ኮሚቴዎች ጋር የሚጋጩበት ሁኔታ ሊኖር ይችላል፡፡ ከእዚህ ሌላ ግን ፍርድ ቤት ጥፋተኛ ነው ብሎ የቀጣውን ታራሚ የማረሚያ ቤት ኦፊሰሮች ጥፋተኛ የተባለበትን አንቀጽና የወንጀል ስም እስከ መጨረሻው በመስጠት ማረም ሲገባቸው ደግመው የሚቀጡ አሉ፡፡ የማረሚያ ቤት ተልዕኮ ግን ይኼ አይደለም፡፡ ፍርድ ቤት ጥፋተኛ ያለውን በወንጀልም ይሁን በአሸባሪነት ይቅጣው፡፡ ከቀጣው በኋላ ማረሚያ ቤት ወንጀለኛውን ለመለወጥ ነው መሥራት ያለበትን፡፡ በአንዳንድ ማረሚያ ቤቶች ግን አሠራራቸው ፈጽሞ የተሳሳተ ነው፡፡ የዕርምት ጊዜውን ጨርሶ እስኪወጣ ድረስ ሌባ፣ አሸባሪና ነፍሰ ገዳይ እያሉ እንዲቆዩ የሚያደርጉ አሉ፡፡ ከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የደረሰባቸውን እስረኞች  ምስክርነት ሲሰጡ በመገናኛ ብዙኃን ተመልክቻለሁ፡፡ በጣም ከባድና አሳዛኝ ድርጊት ነው፡፡ ይህንን ድርጊት ፈጽመዋል የተባሉ ሰዎች በሕግ መጠየቅ አለባቸው፡፡ በአጠቃላይ ግን የማረም ብቃት ያላቸው ኦፊሰሮች የሉንም፡፡ ለእዚህም ዋናው ምክንያት የማረሚያ ቤት ሥራ በውድድር የሚገባበት፣ ለሥራ የሚያነሳሱ (ኦንሴንቲቭ) ማበረታቻዎች የሚያውቅ፣ ደመወዙ አነስተኛ የሆነ በእዚህ የሥራ መስክ ተቀጥሮ የመሥራት ፍላጎት ያላቸው ሰዎች ቁጥርም አነስተኛ የሆነ ነው፡፡ ስለዚህም ወደዚህ የሥራ መደብ የተማረ የሰው ኃይል መግባት አይፈልግም፡፡ ቦታው ላይ መሥራት የሚችል በሞላርም በትምህርት ዝግጅት ደረጃ ብቁ የሆነ ሰው ተቀጥሮ የመሥራት ፍላጎት የለውም፡፡ ይህ ቦታ የሙያ ቦታ መሆን ሲገባው የመጨረሻ የሥራ ቦታ ተደርጎ ነው የሚወሰደው፡፡  ስለዚህ መንግሥት በቦታው ላይ የሙያ ሰዎችን ለመመደብ አሠራሩን እንደገና መከለስ ይኖርበታል፡፡ ይህ ብቻም ሳይሆን ሥልጠናውም እንዲሁም የማረም ሥራውን የሚሠሩ ብቁ የሆኑ ባለሙያዎች እንዲሆኑ ያስፈልጋል፡፡ ይኼንን  ለማድረግም ያለው ውስን አቅም ስለማይፈቅድ የበጀቱም ጉዳይ ሊታሰብበት ይገባል፡፡

ሪፖርተር፡- ታዳጊ ታራሚዎች በተመለከተ የተለያዩ ችግሮች አሉ? መታሰር የማይገባቸው ታዳጊዎች ሳይቀሩ አማራጭ አመራር ባለመኖሩ ማረሚያ ቤቶች ለመግባት ይገደዳሉ፡፡ ይህንን እንዴት ያዩታል?

ፓስተር ዳንኤል፡- የክልል መንግሥታትም ሆኑ የፌዴራል መንግሥት አንድ የዘነጉት ነገር አለ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የወጣት ጥፋተኛ ማዕከል አንድ ብቻ ነው ያለው፡፡ እዚህ አዲስ አበባ ውስጥ ሜክሲኮ አካባቢ ነው ያለው፡፡ እሱም በጣም አነስተኛነና በአንዴ ከ80 በላይ ታራሚዎች በላይ መያዝ አይችልም፡፡ ይኼንን ለማስተካከል በፌዴራል ጉዳዮች ይመራ የሚል ሐሳብ በአንድ ስብሰባ ላይ ተነስቶ ነበር፡፡ ነገር ግን መንግሥት አላስፈጸመውም፡፡ የወጣት ጥፋተኛ ማዕከሎች በእያንዳንዱ ማረሚያ ቤት መኖር አለበት፡፡ ታዳጊዎችን ከአዋቂዎች ጋር ማሰር ሕጉ አይፈቅድም፡፡ አሁን እየሠራን ያለነው በዘልማድ ነው፡፡ ይኼንን ልማዳዊ አሠራር በሙያ መቀየር አለብን፡፡ አሠራሩን ግልጽ የሚያደርግ ፖሊሲና ማኑዋል እንዲሁም ሥራው ባለቤት ሊኖረው ይገባል፡፡ ይኼንን የሚመራ በማረሚያ ቤት ሥር አንድ ዲፓርትመንት ሊቋቋም ይችላል ወይም ከማረሚያ ቤት ውጪ ሊቋቋም ይችላል፡፡ ሌላው ኢትዮጵያ የሌላት ነገር የሪኢንተግሪቪን ፖሊሲ ሲሆን፣ በእዚህ ላይ የአድቮኬሲ ሥራ እየሠራን እንገኛለን፡፡ አንድ ሰው ከማረሚያ ቤት ከወጣ በኋላ ዞር ብሎ የሚያየው የለም፡፡ ከማረሚያ ቤት የሚወጡ በትክክል ተቀይረዋል ወይ? የሚለውን መከታተል ያስፈልጋል፡፡ ነገር ግን ባለው አሠራር ከማረሚያ ቤት ከወጡ በኋላ ማንም ዞር ብሎ አያያቸውም፡፡ ብዙ ጊዜ ተደጋጋሚ ጥፋት የሚያጠፉ ደጋጋሚ ወንጀለኞች ይኖራሉ፡፡ ይህ የሚሆነው ማረሚያ ቤት ሳሉ በትክክል አልታረሙም፣ ሲወጡም ደግሞ ከማኅበረሰቡ ጋር የሚቀላቀሉበት ፖሊሲ የለንም ማለት ነው፡፡ በሌላው ዓለም ይኼንን የሪኢንተግሪሽን ጉዳይን የሚከታተሉ ኦፊሰሮች አሉ፡፡ በኛም አገር የሪኢንቴግሪሽን ጉዳይን የተመለከተ ራሱን የቻለ የፖለቲካ ተቋም ሊገነባ ይገባል፡፡

ሪፖርተር፡- የአዕምሮ ሕመምተኞችን በመደበኛ ማረሚያ ቤቶች ተቀላቅለው ሲታሰሩ ይታያል፡፡ ለሠራው ሥራ ኃላፊነት መውሰድ የማይችልን ሰው መቅጣት ከሕግ አንፃር እንዴት ይታያል?

ፓስተር ዳንኤል፡- የአዕምሮ ሕመምተኞች ፖሊሲና አዋጅ በኢትዮጵያ ውስጥ የለም፡፡ ስለዚህ የታመመ ሰው ቀጥታ ወደ ማረሚያ ቤት ይገባል፡፡ መሆን ያለበት ግን አንድ የአዕምሮ ሕመምተኛ መኪና ሲሰብር አልያም ሌላ ጥፋት ሲያጠፋ አይደለም መያዝ ያለበት፡፡ ጥፋት ከመፈጸሙ በፊት የሕመም ምልክቶች በሚያሳይበት ጊዜ ወደ ማገገሚያ ማዕከል ነው መግባት ያለበት፡፡ ይህ የሚመራበት ፖሊሲና አዋጅ ኢትዮጵያ ውስጥ የለም፡፡ ከአማኑኤል ሆስፒታል ጋር ጥናት አድርገን ለጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የሚገባ ረቂቅ አዘጋጅን ነበር፡፡ ነገር ግን እስካሁ በሥራ ላይ አልዋለም፡፡ ይኼንን ችግር የሚፈታው በፖሊሲ፣ በማኑዋል ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በቂ መረጃ ሳይገኝባቸው ወደ ፍትሕ ሥርዓት እንዲገቡና ለዓመታት በማረሚያ ቤቶች እንዲቆዩ የሚደረጉ አሉ፡፡ አንዳንድ ጊዜ የቀረበባቸውን ክስ መከላከል ሳያስፈልጋቸው፣ አንዳንዴም ክስ ለመመሥረት የሚያስችል መረጃ ሳይገኝባቸው በነፃ እንዲለቀቁ ይደረጋል፡፡ ተከራክረው ነፃ የሚወጡም አሉ፡፡ ነገር ግን እኚህ ሰዎች በማረሚያ ቤት በቆዩባቸው ጊዜያት ከሥራ ገበታ ከመነሳት ጀምሮ የተለያዩ ችግሮች ያጋጥማቸዋል፡፡ የፍትሕ ሥርዓቱ የበደላቸውን እነዲህ ያሉ ዜጎች እንዴት ነው ፍትሕ ማግኘት የሚችሉት?

ፓስተር ዳንኤል፡- በሌላው አገር ሰዎች ከጥፋት ነፃ ሆነው በነፃ ሲለቀቁ መንግሥት ካሳ እንዲከፍል ይዳረጋል፡፡ የሚዘገይ ፍትሕ አይደለም፡፡ ይህ ማለት አንድ ሰው ጥፋተኛ ከሆነ ፍትሕ ማግኘት አለበት፣ ጥፋተኛ ካልሆነ ደግሞ መለቀቅ አለበት፡፡ የፍትሕ ሥርዓቱ በጊዜ ምላሽ ማይሰጥ ከሆነ፣ ሥርዓቱ እየተዳከመ ከሄደ የሕግ የበላይነት ሚባል ነገር ላይሠራ ይችላል፡፡ ለእዚህ እኮ ነው የሕዝቡ እሮሮ ላይ የደረሰው፡፡ የአገሪቱ የፍትሕ ሥርዓት ተደራሽ፣ ቀልጣፋ በሕዝብ አመኔታ እንዲያገኝ እንዲህ ያሉ ክፍተቶች መታረም ይኖርባቸዋል፡፡ ከእዚህ ውጪ ባሉ የአሠራር ችግሮች የሚበደሉ እንዳሉ ባደረግነው ጥናት አይተናል፡፡ እስከ አራት ዓመታት ድረስ ፍርድ ቤት ተመላልሶ ፍትሕ ሳያገኝ 12 ዓመታት ማረሚያ ቤት ቆይቶ የሞተ ሰው አውቃለሁ፡፡ ለወጡት ተመስገን ነው፡፡ ፍትሕ ሳያገኙ እስር ቤት የሚሞቱም አሉ፡፡

ሪፖርተር፡- ፍርድ ቤት እንዲለቀቁ ካዘዘ በኋላ ግልጽ ባልሆነ ምክንያት በማረሚያ ቤቶች ቆይተናል የሚሉ አቤቱታዎች ያጋጥማሉ፡፡ መሰል ጉዳዮ አጋጥምዎት ያውቃል?

ፓስተር ዳንኤል፡- ፍርድ ቤት ከለቀቁ በኋላ የሚያስር ሰው ራሱ ወንጀለኛ ነው፡፡ በሕጉ መሠረት ሊቀጣ ይገባዋል፡፡ የፍትሕ ማረጋገጫ ፍርድ ቤት ነው፡፡ ማንም ሰው ከሕጉ በታች እንጂ በላይ አይደለም፡፡ ካጋጠሙን ጉዳዮች መካከል መፈቻ ዘግይቶባቸው ማረሚያ ቤት የሚቆዩ አሉ፡፡ በቢሮክራሲ ምክንያት ዶክሜንቶች ሳይደርሳቸው የሚቆዩም አሉ፡፡ ግን ማረሚያ ቤቱ አልታረሙም ብሎ ሲያምን መፈቻ የተከለከሉ አጋጥሞኛል፡፡ ከእዚህ ውጪ ግን ፍርድ ቤት እንዲለቀቁ ትዕዛዝ ሰጥቶ ታስረው የቀሩ አላጋጠሙኝም፡፡