Skip to main content
x
የፎረንሲክ ምርመራና የሥነ ምረዛ ሕክምና

የፎረንሲክ ምርመራና የሥነ ምረዛ ሕክምና

የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሕክምና ኮሌጅ በፎረንሲክና በሥነ ምረዛ ላይ ያተኮረ የምርመራ፣ የድኅረ ምረቃ መርኃ ግብርና የሕክምና አገልግሎቶች በመስጠት ላይ ነው፡፡ ከእነዚህም መካከል የፎረንሲክ አገልግሎት በድኅረ ምረቃና በምርመራ፣ የሥነ ምረዛው አገልግሎት ደግሞ ሕክምናን ያለሙ ናቸው፡፡

የኮሌጁ የአካዳሚክና ምርምር ምክትል ፕሮቮስት ዶ/ር ባልካቸው ንጋቱ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ መርኃ ግብሩ የሚካሄዴው ለሦስት ዓመት ሆኖ 13 ሐኪሞች እየተከታተሉት ናቸው፡፡ የፎረንሲክ መርኃ ግብሩ ከተጀመረ ሁለት ዓመት የሞላው ሲሆን፣ ሐኪሞቹ ከአንድ ዓመት በኋላ ተመርቀው ወደ አገልግሎት ይሰማራሉ፡፡

ይህ የፎረንሲክ መርኃ ግብር እየተሰጠ ያለው ህንድ ካልካታ ከሚገኘው ማኒፖል ዩኒቨርሲቲ ጋር የሕክምና ኮሌጁ ባደረገው ስምምነት መሠረት ነው፡፡ በስምምነቱ መሠረት ምሩቃኑ ዓለም በዘርፉ የደረሰበትን ደረጃ ለማወቅ እንዲያስችላቸው በየዓመቱ ለሦስት ወራት ያህል ወደ ካልካታ እያቀኑ በተጠቀሰው ዩኒቨርሲቲ ሥልጠና እንደሚያገኙ ዶ/ር ባልካቸው ተናግረዋል፡፡

ተማሪዎቹ ሙያው የሚጠይቀውን ክህሎት ኖሯቸው እንዲወጡ ለማድረግ በኮሌጁ በኩል የማያቋርጥ ድጋፍ እንደሚደረግላቸው፣ ፕሮግራሙንም ወደ ሌሎች ተቋማት በማስፋፋት ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ላይ የሚኖረውን ጫና መቀነስ እንደሚቻል ገልጸዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በሆስፒታሉ ያለው የፎረንሲክ ምርመራ የሚካሄደው በአንድ ኢትዮጵያዊና በአራት የህንድ ባለሙያዎች መሆኑን ምክትል ፕሮቮስቱ አመልክተው፣ ከአንድ ዓመት በኋላ የምርመራው አገልግሎት ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያውያን እንደሚካሄድ አስረድተዋል፡፡

የፎረንሲክና የሥነ ምረዛ ምርመራና ሕክምና ለሁለት ዓመታት ያህል ይካሄድ የነበረው በአዲስ የእሳት ቃጠሎና ድንገተኛ አደጋ ሕክምና ማዕከል ውስጥ እንደነበር ዶ/ር ባልካቸው ገልጸው፣ ከዚህ ወር መጀመርያ አንስቶ ምርመራውና ሕክምናው በሆስፒታሉ ቅጥር ግቢ ለዚሁ ሲባል በተሠራው አዲስ ሕንፃ እንደሚዛወር ተናግረዋል፡፡

አዲሱ ሕንፃ ለምርመራው፣ ለሥልጠናውና ለሕክምና አገልግሎቶች እጅግ ምቹ ከመሆኑ ባሻገር፣ ለዚህም አስፈላጊና መሠረታዊ ናቸው በተባሉት ልዩ ልዩ መሣሪያዎች በሚገባ የተደራጀ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡

እንደ ምክትል ፕሮቮስቱ ገለጻ የፎረንሲክና የዲኤንኤ ምርመራዎች በተለይ ለፍትሕ ሥራ ስኬታማነት እጅግ ጠቃሚ ናቸው፡፡ ሆኖም የዴኤንኤ ምርመራ የሚሠራው ውጭ አገር በመላክ ሲሆን፣ በአገር ውስጥ አገልግሎቱን ለመስጠት ቢያንስ የአንድ መቶ ሃምሳ ሚሊዮን ዶላር መሣሪያዎች ግዥ ያስፈልጉታል፡፡

‹‹አንድ መቶ ሚሊዮን ሕዝብ ባለበት አገር የዲኤንኤ ምርመራ አለመኖሩ የሚያስቆጭ ነው፤›› ያሉት ዶ/ር ባልካቸው፣ ይህም መቀየር አለበት በሚል መንፈስ ምርመራው በኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች እንዲሰጥ የማድረግ ሐሳብና ዕቅድ እንዳለ አስረድተዋል፡፡

ዕቅዱም ተግባራዊ እንዲሆን ከፌዴራል ፖሊስ፣ ከፍትሕ አካላት፣ ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና ጉዳዩ በይበልጥ ከሚመለከታቸው መንግሥታዊ አካላት ተገቢው ዕገዛና ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡  

የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሕክምና ኮሌጅ በአሁኑ ወቅት ልዩ ልዩ የሕክምና ማዕከላትን እያስገነባ የሕክምናውን ዘርፍ በማስፋፋት ላይ ነው፡፡ ከማዕከላቱም መካከል የልብ፣ የካንሰርና የሆድ ዕቃ (አንጀት፣ ጣፊያ፣ ጉበት) ማዕከላት ይገኙበታል፡፡

ከተቋቋመ ከግማሽ ምዕተ ዓመታት በላይ እንዳስቆጠረና ሲመሠረትም የነበረው ዓላማ የአቅም ችግር ላለባቸው ወገኖች ነፃ የሕክምና አገልግሎት ለመስጠት እንደነበር ከሆስፒታሉ የተገኙ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ የዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታል የአስክሬን ምርመራ ክፍል ላይ የሕክምናው ኮሌጅ የማሻሻያ ሥራ እያካሄደ ነው፡፡ ሥራው ከሦስት ሳምንታት በኋላ እንደሚጠናቀቅና የኮሌጁ ባለሙያዎች እዚያ እየሄዱ አገልግሎት እንዲሰጡ እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡