Skip to main content
x
በንፁኃን ሕይወት የሚቆምሩ ለፍርድ ይቅረቡ!

በንፁኃን ሕይወት የሚቆምሩ ለፍርድ ይቅረቡ!

መሰንበቻውን በምሥራቁ የአገሪቱ ክፍል እየተስተዋለ ያለው አሳዛኝ ድርጊት የአገር ህልውናን እየተፈታተነ ነው፡፡ በሶማሌ ክልል በወገኖቻችን ላይ የተፈጸመው ግድያ፣ ዘረፋና ጭካኔ የተሞላበት ድርጊት ከባድ ጊዜ ውስጥ እንዳለን ያሳያል፡፡ ለዓመታት ሲዘመርለት የነበረው ፌዴራሊዝም፣ አገሪቱ በቀላሉ ተሰባሪ መሆኗን በተለያዩ ገጽታዎች እያጋለጠ ነው፡፡ አንድ ክልል ውስጥ ችግር ሲፈጠር ‹‹መጤ›› በሚባሉ ሌሎች የአገሪቱ ዜጎች ላይ የሚፈጸሙ አስነዋሪ ወንጀሎች ይኼንን አባባል በሚገባ ያጠናክሩታል፡፡ በአገሪቱ መንግሥት የለም ወይ እስኪባል ድረስ ሰዎችን መግደልና ማሰቃየት፣ ከዚያም አልፎ ተርፎ ቤተ እምነቶችን ማቃጠል የተፈጸመበት የሶማሌ ክልል የሰሞኑ ድርጊት ብዙዎችን አሳዝኗል፡፡ በገዛ አገር እንደ ባዕድ እየታደኑ የተገደሉና የተዘረፉ ወገኖች የሚደርስላቸው አጥተው የግፍ ሰለባ ሆነዋል፡፡ አንድ ኢትዮጵያዊ ወገኔ ነው ብሎ በሚያስበው የተደራጀ ኃይል ከሚችለው በላይ ጥቃት እየተፈጸመበት፣ የሚያስጥለው ሕግ አስከባሪ ወይም አለኝታ ሲያጣ በአገሩ ላይ ተስፋ ይቆርጣል፡፡ በሕዝብ ላይ በደል የሚፈጽሙ የሚቆጣጠራቸው ወይም የሚጠይቃቸው ባለመኖሩ ብቻ፣ ሕገወጥነት ከሚታገሱት በላይ እየሆነ ነው፡፡ በንፁኃን ሕይወት የሚቆምሩ ለፍርድ መቅረብ አለባቸው፡፡

ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ ለመግለጽ እንደሞከርነው እንደ ሰሞኑ ዓይነት የጭካኔ ድርጊቶች ሲፈጸሙ ዋነኞቹ ተጎጂዎች ሕፃናት፣ ነፍሰ ጡሮች፣ አራሶችና አቅመ ደካሞች ናቸው፡፡ በተጨማሪም ጥረው ግረው በላባቸው የሚኖሩ ባተሌዎች ናቸው፡፡ መንግሥት ደኅንነታቸውን እንደሚያስከብር የሚተማመኑ ሥራ ፈጣሪዎችና የንግድ ሰዎችም እንዲሁ ሰለባ ይሆናሉ፡፡ በአገራቸው በፈለጉት ሥፍራ የመዘዋወር፣ የመኖር፣ የመሥራትና ሀብት የማፍራት ሕጋዊ መብት እንዳላቸው የሚገነዘቡ ወገኖች ግን እያጋጠማቸው ያለው ከዚህ በተቃራኒ ነው፡፡ በጅግጅጋም ሆነ በሌሎች የክልሉ አካባቢዎች ጥቃት የተፈጸመባቸውን ዜጎች፣ ክልሉም ሆነ የፌዴራል መንግሥት የመከላከል ኃላፊነት ነበረባቸው፡፡ ይህ ባለመሆኑ ግን ለጊዜው ቁጥራቸው የማይታወቅ በርካታዎች ሲሞቱ፣ የአካል ጉዳትና ዝርፊያ የተፈጸመባቸው ብዙ ናቸው፡፡ በዚህም ምክንያት ለሥነ ልቦናዊ ጉዳት የተጋለጡም በጣም ብዙ ናቸው፡፡ በድሬዳዋም አሥር ሰዎች የተገደሉ ሲሆን፣ ከሟቾቹ መካከል ሦስቱ ሕፃናት መሆናቸው እጅግ በጣም ያንገበግባል፡፡ የፍትሕ ያለህ ያስብላል፡፡

የአገር መከላከያ ሠራዊትና የፌዴራል ፖሊስ ወደ ሶማሌ ክልል ገብተው ሕግ እያስከበሩ መሆናቸው ተሰምቷል፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ በንፁኃን ላይ ወንጀል የፈጸሙም ሆነ ያስፈጸሙ ኃይሎች በሕግ መጠየቅ አለባቸው፡፡ ከዚህ ቀደም በሺዎች ለሚቆጠሩ ወገኖች ሞትና ለሚሊዮኖች መፈናቀል ምክንያት የሆኑ ኃይሎችን የጠየቃቸው ባለመኖሩ፣ ግጭቶችን በየቦታው መስማት የተለመደ ትዕይንት ሆኗል፡፡ ከግድያና ከተለያዩ አስፀያፊ የወንጀል ድርጊቶች ሸሽተው በአብያተ ክርስቲያናትና በተለያዩ ሥፍራዎች የተጠለሉና የተደበቁ ወገኖች፣ ከአስቸኳይ ዕርዳታ በተጨማሪ ፍትሕ ያስፈልጋቸዋል፡፡ ሕገወጦች እንዳሻቸው እየፈነጩ በዜጎች ሕይወት ላይ ቁማር ሲጫወቱ፣ ዜጎችን በማረጋጋትና መልሶ በማቋቋም ስም ፍትሕን ገሸሽ ማድረግ ተገቢ አይደለም፡፡ በተለይ በክልሎች የተደራጁ ልዩ ኃይል የሚባሉና የእነሱ ድጋፍ ሰጪ መደበኛ ያልሆኑ መዋቅሮች በፍጥነት መፈራረስ አለባቸው፡፡ የዜጎችን ደኅንነት ለመጠበቅ በመንግሥት በጀት የሚተዳደሩ የፀጥታ ተቋማት እያሉ፣ በጎንዮሽ የሚደራጁ ኃይሎች ለአገርና ለሕዝብ ጠንቅ እየሆኑ ነው፡፡ በግልጽም እየታየ ነው፡፡ የሕግ የበላይነት እየተጣሰ ያለው በእነዚህ ኃይሎች መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል፡፡

በአሁኑ ጊዜ በተለያዩ ጎራዎች የተሠለፉ ኃይሎች አገርን የዘነጉ ይመስላሉ፡፡ የአገር ጉዳይ ከእጅ ካመለጠ መመለሻ ስለሌለው በፍጥነት ከተገባበት አዙሪት ውስጥ መውጣት ያስፈልጋል፡፡ ትናንት ለዴሞክራሲና ለሰብዓዊ መብት ሲጮሁ የነበሩ፣ አገሪቱ በለውጥ ጎዳና ውስጥ ሆና ዕገዛ ካላደረጉ ፋይዳቸው ምንድነው? በፌዴራልም ሆነ በክልል የሚገኙ ወገኖች የሕግ የበላይነት ተከብሮ አገር በሥርዓት እንድትተዳደር የማድረግ ከፍተኛ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ በረባ ባልረባው ምክንያት በየቦታው ሁከት ሲቀሰቀስ በግዴለሽነት የሚመለከቱ አመራሮችም ሆኑ የፀጥታ ኃላፊዎች ራሳቸውን ሊመረምሩ ይገባል፡፡ የአገር አንድነትና ዘላቂ ሰላም የሚረጋገጠው፣ የሚመለከታቸው አካላት እየተናበቡና እርስ በርስ ቁጥጥር የሚያደርጉበት አሠራር ሲሰፍን ነው፡፡ ‹‹ማፍረስ ቀላል ባይሆንም መገንባት ግን የበለጠ ከባድ ነው›› የሚለውን አባባል በማስታወስ፣ ወጣቱን ትውልድ ለአገራዊ አንድነትና ዘላቂ ሰላም የበኩሉን እንዲወጣ ማድረግ ጊዜ የማይሰጠው ተግባር መሆን አለበት፡፡ ብሔርን መነሻ ያደረገ ግጭትና ውድመት አገርን ያጠፋል፡፡ ሕዝብን ይበትናል፡፡ በሕግና በሥርዓት መመራት ካልተቻለ ውጤቱ የከፋ ይሆናል፡፡

እንደሚታወቀው በተለያዩ ክልሎች የሚከሰቱ ግጭቶች በሙሉ ከሕዝብ ጋር የሚገናኙ አይደሉም፡፡ ሕዝብ ለዘመናት አብሮ ኖሯል፡፡ ችግር ሲያጋጥምም አንዱ ሌላውን እየሸፈነ ወይም ከለላ እየሰጠ በመኖርም ይታወቃል፡፡ በተለይ በዚህ ዘመን ለሚፈጠሩ ችግሮች ዋነኞቹ ተጠያቂዎች የፖለቲካ አመራሮች ናቸው፡፡ ሥልጣን ላይ ከወጡ በፍፁም መውረድ የማይፈልጉ አመራሮች በሕዝብ ስም እየነገዱ፣ በንፁኃን ዜጎች ደም እጃቸውን ይለቃለቃሉ፡፡ ሥልጣን የሚያስገኘውን ጥቅም ላለማጣት ሲሉም ሕዝብን እርስ በርስ ያባላሉ፡፡ በተለይ በስሜታዊነት የሚነዱ ኃይሎችን እያደራጁ ሕዝብ ውስጥ በማሰማራት ግድያ ይፈጽማሉ፣ ይዘርፋሉ፣ ያፈናቅላሉ፡፡ በሕግ ስለማይጠየቁም የሕግ የበላይነትን እየደፈጠጡ አገር ያተራምሳሉ፡፡ በአሁኗ ኢትዮጵያ ይህ ድርጊት በአስቸኳይ ቆሞ ዜጎች ፍትሕ ማግኘት አለባቸው፡፡ አስነዋሪ ድርጊቶችን የሚፈጽሙ አመራሮችም ሆኑ ተከታዮቻቸው በሕግ መዳኘት ይኖርባቸዋል፡፡ ሕገወጥነት በሕጋዊነት ላይ እየነገሠ የትም መድረስ አይቻልም፡፡

መንግሥት የዜጎችን ሰላምና ደኅንነት የማስከበር ሕጋዊ ኃላፊነት አለበት፡፡ በየትኛውም ሥፍራ የሚገኙ ዜጎች ጉዳት ሲደርስባቸውና ከለላ ሲያጡ፣ የሚኖሩበት ክልል እስኪፈቅድ ድረስ እየተባለ ብዙ ጉዳት ደርሷል፡፡ ሰሞኑን በሶማሌ ክልል አሰቃቂ ድርጊቶች ሲፈጸሙና የድረሱልን ጥሪዎች በተለያዩ መንገዶች ሲስተጋቡ የተፈጠረው ድንጋጤ፣ ነገ ምን ዋስትና ይኖራል የሚል ጥያቄ በብዙዎች ዘንድ አጭሯል፡፡ የሕዝብን ሕይወት ያመሰቃቀሉና አገርን የሚያተራምስ ድርጊት የፈጸሙ ሰዎች ለሕግ ካልቀረቡ፣ በሌሎች ዜጎች ላይ ሕግን እንዴት ተፈጻሚ ማድረግ ይቻላል? ሁሉም ሰው በሕግ ፊት እኩል መሆኑ በሚነገርበት አገር ውስጥ፣ አንዱ ያሻውን እየፈጸመ እንደፈለገ ሲሆን ሌላውን እንዴት መጠየቅ ይቻላል? አንድ ዜጋ በሕገወጥ ተግባር ላይ ሲገኝ እንደሚጠየቀው ሁሉ፣ በአገርና በሕዝብ ላይ አስነዋሪ ወንጀል የሚፈጽሙ አመራሮችም መጠየቅ አለባቸው፡፡ ግልጽነትና ተጠያቂነት በሌለው ሥርዓት ውስጥ ተኮትኩተው ያደጉና እንደ ልባቸው የሆኑ ሰዎች በቃችሁ መባል አለባቸው፡፡ የሕግ የበላይነት ተረጋግጦ ሕገወጥነት አደብ መግዛት አለበት፡፡ በንፁኃን ሕይወት ላይ የሚቆምሩ ለፍርድ ይቅረቡ!